top of page

የታችኛው ጀርባ ህመም ምንድነው? ለምን ይመጣል?

የጀርባ ህመም ሁልጊዜ በአደጋ አይጀምርም!


ድንገት በአዘቦት ቀን ረዥም ሰአት ቆመው ወይም ተቀምጠው ፤ አልያም ከባድ ስራ ሲሰሩ ውለው፤ ምሽት ላይ ከድካምዎ ሊያርፉ ጋደም ሲሉ ፤ ህመሙን ያስተውሉታል።


ማረፊያዎ ሰአት ላይ የታችኛው ጀርባዎ ላይ ህመም ይሰማዎታል።



መጀመሪያ ላይ ችላ ይሉታል። ምንም አይደለም ብለው ይዘነጉታል። ምናልባትም ድካም ፤ አልያም እድሜ እያሉ ምክንያት ይዘረዝሩለታል።

እንደእርስዎ በአለም ዙሪያ በጀርባ ህመም የሚሰቃዩ ከግማሽ ቢሊየን በላይ ሰዎች አሉ። በአለም ዙሪያ ከሚኖሩ 10 ሰዎች ውስጥ ስምንቱ በህይወት ዘመናቸው የጀርባ ህመም እንደሚያጋጥማቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ። አብዛዎቹም የበሽታውን መንስኤ እንኳን በቅጡ አያውቁም።


ሆኖም ግን እንደሚታሰበው የጀርባ ህመም አንድ በሽታ አይደለም። ሁልጊዜም የዲስክ መንሸራተት አይደለም።


የጀርባ ህመም ምንድን ነው?


የጀርባ ህመም የሚባለው የአከርካሪ አጥንት ዙሪያ የሚሰማ ህመም ነው። በብዛት ህመሙ የሚስተዋለው ሰውነትን የሚሸከመው የታችኛው ጀርባ (ወገብ )አካባቢ ነው። በዚህም ጽሁፍ የምናነሳው ስለዚህ የታችኛችው የጀርባ ህመም ነው።

ይህ ክፍል ከላይ ያለውን ሰውነት ክብደት ችሎ ወደ እግር የሚያስተላልፍ ነው። ለረዥም ሰአት ሲቆሙ ፣ ሲቀመጡ ፣ አንድ አቋም ይዘው ሲቆዩ ፣ ሲታጠፉ ፣ እቃ ሲያነሱ የታችኛው ጀርባዎ አብዝቶ ይሰራል። ከእርሶ እኩል ከፍ ዝቅ ይላል። ለዚህም በእለታዊ እንቅስቃሴዎ ውስጥ ታችኛው ጀርባዎ ላይ ከባድ ጫና ሊያድርበት ይችላል። በጊዜ ውስጥም ሊጎዳ፣ ህመም ሊያመጣ ይችላል። ለዚህም የዚህኛው የጀርባ ክፍል ህመም በርክቶ ይስተዋላል።

የጀርባ ህመም ምልክቱም ለየቅሉ ነው። አንዳንዶች ምቾት ማጣት ሲሰማቸው ሌሎች እንቅስቃሴ የሚገድብ ከባድ ህመም ይኖራቸዋል። ህመሙ መውጋት ፣ መቆጥቆጥ፣ ማቃጠል ፣ መደንዘዝ ፣ ወደ እግር የሚሰራጭ የኤሌክትሪክ ንዝረት የሚመስል ሊሆን ይችላል። ህመሙ በአንዳንዶች ለጥቂት ቀናት ብቻ ሲቆይ ፤ ሌሎች ለአመታት ይሰቃያሉ። እንቅልፍ ያጣሉ። ስራቸውና ማህበራዊ ኑሮዋቸው ይሰናከላል።


የጀርባ ህመም አንድ በሽታ አይደለም


የጀርባ ህመም ፈጽሞ አንድ በሽታ አይደለም። የብዙ በሽታዎች ምልክት ነው። ሆኖም ግን ከ 10 የጀርባ ህመም ካለባቸው ሰዎች ውስጥ ዘጠኙ ምንም በሽታ አይገኝባቸውም። የሚደረጉ የላብራቶሪ ምርመራዎችም ጠቋሚ አይሆኑም። ይህ ማለት ግን ህመሙ ምናባዊ ነው ማለት አይደለም።


የአከርካሪ አጥንት መጋጠሚያዎች፣ ጅማቶች፣ እና ዲስኮች የሚኖራቸው መስተጻምር ለውጥ ይህን ህመም ሊያመጣ ይችላል። ሆኖም ግን በላብራቶሪ አይስተዋልም።

በተረፉት 10 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች ላይ ይህ የሚከሰተው በሚከተሉት ምክንያቶች ነው።


  • የዲስክ መንሸራተትን ተከትሎ በሚመጣ የነርቭ መታፈን

  • የአከርካሪ አጥንት መጥበብ (spinal stenosis)

  • የአከርካሪ አጥንት መሳሳት (በቪታሚን ዲ ማነስ አልያም በሆርሞን ችግሮችም ሊመጣ ይችላል)

  • የአከርካሪ አጥንት መሰበር

  • የአከራክሪ አጥንት መጋጠሚያዎች መቆጣት (spondyloarthritis / ankylosing spondylitis)

  • ኢንፌክሽኖች

  • የህብለሰረሰር አልያም አከርካሪ አጥንት እጢ

  • ወደ አከራካሪ አጥንት የተሰራጨ ካንሰር


የጀርባ ህመም አጋላጭ መንስኤዎች?


የጀርባ ህመም አጋላጭ በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩት ይችላሉ። ከእነኝህ ውስጥ ጥቂቶቹ

  • ረዥም ሰአት መቀመጥ ፣ መቆም፣ አንድ አቁም ይዞ መቆየት

  • ደጋግሞ መታጠፍ ፣ መነሳት

  • በእድሜ ውስጥ የሚመጡ የአከርካሪ አጥንት ለውጦች

  • በቂ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ

  • ውፍረት (ከመጠን በላይ የሰው ክብደት)

  • ሲጋራ ማጨስ(አዎ፣ አከርካሪውንም ይነካል) ናቸው።


    ከዚህም ባሻገር በእርግዝና ወቅት እናቶች የሚያመጧቸው ለውጦች ጀርባ ህመም ሊያስከትሉ ይችላሉ። የመውለጃ እድሜያቸው ያለፉ ሴቶች ደግሞ ፤ አጥንት መሳሳት ስለሚያጋጥማቸው ለጀርባ ህመም ተጋላጭነት አላቸው።


ውጥረት፣ ጭንቀት እና ደካማ እንቅልፍ ደግሞ የጀርባ ህመም ን ይበልጥኑ ያባብሳሉ። ረዘም ላለ ጊዜ እንዲቆይ ያደርጉታል።


ምን ማድረግ ይመከራል?


👉 የጀርባ ህመም ሕክምናዎች ህመሙን በአንድ ጀምበር "አያስተካክሉም"።

እጅጉን አመርቂ ውጤት የሚታየው በጊዜ ውስጥ ነው። በክትትል የሚፈለገው ለውጥ ሊመጣ ይችላል። ለዚህም የሚከተሉት ይመከራሉ።

  • ይንቀሳቀሱ! መለስተኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የተሻለ ለውጥ ያመጣል። በተለይም ጀርባዎን እንዲያግዝ የጥንካሬ እና የማሳሳብ ስፖርቶችን ይስሩ።

  • እንደ አስፈላጊነቱ ህመም ማስታገሻ ይውሰዱ።

  • የአልጋ ላይ እረፍት ያድርጉ። ጀርባ ላይ ያለውን ጫና ይቀንሳል። ረዥም ሰአት ማረፍ ግን አይመከርም።

  • የጀርባ ደጋፊ ማቀፊያዎችን እንደ ሀኪምዎ ምክር ያድርጉ።


የጀርባ ህመምን መከላከል ይቻላል?

የጀርባ ህመምን ለመከላከል የሚከተሉትን ያድርጉ።

  • ጀርባን የሚያግዙ ጡንቻዎችን ያጠናክሩ።

  • ትንሽ ይቀመጡ ፣ የበለጠ ይንቀሳቀሱ።

  • ቁመናዎን ያስተካክሉ። ቀጥ ብለው ይቀመጡ። ቀጥ ብለው ይቁሙ።

  • ክብደት ሲያነሱ ይጠንቀቁ።

  • ጤናማ ክብደት ይኑርዎት።

  • ማጨስን ያ ቁሙ።

  • ጭንቀትን ይቆጣጠሩ እና በደንብ ይተኙ።


መቼ የህክምና እርዳታ ይፈልጉ?

መለስተኛ የጀርባ ህመም በእንቅስቃሴ እና በመሠረታዊ እንክብካቤ ሊሻሻል ይችላል። ይሁን እንጂ የሚከተሉትን ካስተዋሉ ፈጽሞ ችላ እንዳይሉ። በአፋጣኝ የህክምና እርዳታ ይፈልጉ።


.

  • ከ2 ሳምንት በላይ እንክብካቤ አድርገውለት ካልተሻልዎት ፤ አልያም እየባሰ ከመጣ ፤

  • ከጀርባ ተነስቶ ወደ አንድ ወይም ሁለቱም እግሮች ላይ የሚሰራጭ ህመም ከሆነ። በተለይ ህመሙ መደንዘዝ፣ እንደኤሌትሪክ መንዘር እንዲሁም የእግር መስነፍ ካለው፤

  • ለመራመድ ካስቸገርዎ። የእግሮችውን እንቅስቃሴ ለማዘዝ/ለመቆጣጠር ከከበድዎ ፤

  • ሽንት እና ሰገራ መቆጣጠር ካቃትዎ (ይህ አፋጣኝ ቀዶ ህክምና የሚያስፈልገው በሽታ ምልክት ሊሆን ስለሚችል አይዘግዩ) ፤

  • ከህመሙ ጋር ትኩሳት፣ ላብ ማጥመቅ እንዲሁም ከፍተኛ ክብደት መቀነስ ካለ ፤

  • ከህመሙ በፊት አካላዊ ጉዳት ደርሶብዎ ከነበረ ፤

  • የሚታወቅ ህመም ካለብዎ (ለምሳሌ፡ ሳንባ ነቀርሳ፣ ኤች አይቪ የመሳሰሉት ካለብዎ)፤

  • የካንሰር በሽታ ካለብዎ ፤ አልያም ከነበረብዎ ፤

  • ስቴሮይድ ያለባቸው መድሀኒቶችን ለረዥም ጊዜ ከወሰዱ፤

  • ህመሙ የማያቋርጥ ከሆነ ፤ አቅራቢያዎ ወዳለ ጤና ተቋም ይሂዱ።


እነኝህ ምልክቶች ካስተዋሉ ፤ ፈጽሞ ችላ አይበሉ። ከጀርባ ያለ ጠንከር ያለ በሽታ አመላካች ሊሆኑ ይችላሉና የህክምና እርዳታ ይፈልጉ።


ያስተውሉ!

የተለመደ ነው ብለው ችላ አይበሉ። ዶክተርዎን ያማክሩ። ዛሬውኑ ጤናዎን ይምረጡ!


 

Comments


bottom of page