117 results found with an empty search
- የአስም ህመም በኢትዮጵያ
ድንገት ቢታፈኑ ... ምን ይሰማዎታል? ለ እያንዳንዷ ቅንጣት አየር መታገል አይጨንቅም?! በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ፤ በተለይም ለህጻናት ፤ ይህ ምናባዊ ጉዳይ አይደለም። ድንገት ሊያጋጥማቸው የሚችል እውነታ ነው። የትንፋሽ ቱቦአቸው ተዘግቶ አየር ለመሳብ ሲታገሉ ፤ የትንፋሽ ቱቦአቸውን የሚያረጋጋ መድሐኒት ከሌለ ፤ ጉዳቱ አይሎ እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል። አስም የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቃ ህመም ሲሆን ፤ ከህጻን እስከ አዋቂ ሁሉንም የእድሜ ክልል ያጠቃል። ህመሙ ያለባቸው ሰዎች የመተንፈሻ አካላቸው የውስጥ ስጋ (respiratory mucosa) እጅጉን ሰበበኛና ቁጡ ነው። ይህም ማለት በመደበኛ ነገር(የአስም ቀስቃሽ አካላት) ሊቆጣ እና ሊያብጥ ይችላል። ችግሩ ታድያ መቆጣቱ ብቻ ሳይሆን ፤ በማበጡ የመተንፈሻ ቱቦ ይጠባል። እዚህ ላይ የመተንፈሻ አካል የሚያመርታቸው ወፍራም ፈሳሾች (አክታ) ሲጨመር ፤ አየር መውጣት እና መግባት ያስቸግራል። ይታፈናል። የሚያረጋጋው መድሀኒት ካላገኘ እብጠቱ እያደገ ሂዶ ፤ አየር ቱቦን ሊደፍን ይችላል። ህመሙ እንዲህ ሆኖ ሳለ በሀገር ደረጃ ለአስም በቂ አጽንኦት አልሰጠነውም። ባሉብን አንገብጋቢ ጉዳዮች ወደ ኋላ ከገፋናቸው የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች አንዱ ነው። የአስም ብሔራው ቀን የለንም ፣ ብሔራዊ እቅድ አላወጣንም። በሕዝብ ተቋማት ውስጥ በቂ መሰረታዊ መድኃኒቶች የሉም። የህመሙ ስርጭት ግን እየተሰፋፋ ነው። ታማሚም ግንዛቤ ኖሮት ህክምና እስኪመጣና ፤ መድሐኒቱ እስኪገኝ በጸጥታ ብዙ ኢትዮጵያውያን ይሞታሉ። በማይታይ አፋኝ ትንፋሻቸውን ይሰረቃሉ። 🌍 የአስም ስርጭት እ.ኤ.አ. በ2019 በአለም ዙሪያ አስም ከነበረባቸው ከ262 ሚሊዮን በላይ ከሚሆኑ ሰዎች መሀል ፤ ከ455,000 በላይ በአስም የተነሳ መሞታቸውን የአለም ጤና ድርጅት በ2021 ያወጣው መረጃ ይጠቁማል። የአለምአቀፍ የአስም ሪፖርት ደግሞ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት የአስም በሽታ ስርጭት እየጨመረ መሆኑን የኢትዮጵያ ከተሞችን ጠቅሶ ገልጿል። በኢትዮጵያ ከ ዘጠኝ አመት በፊት የተደረገ የዳሰሳ ጥናት በበኩሉ ፤ የአስም መጠን በከተማ ነዋሪዎች ላይ እየጨመረ መሆኑን አሳይቷል። አገር አቀፍ መረጃ ባይኖረንም ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የአስም ህመም ተጠቂ ቁጥር ከ 8.7 እስከ 9.2 በመቶ እንደሚደርስ ይገመታል። ይህም በትንሹ 10 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን የአስም ህመም እንዳለባቸው ያመላክታል። በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የተደረገ ጥናት በበኩሉ እድሜያቸው ለትምህርት ከደረሱ ህጻናት መሀከል 13.3 በመቶ የሚሆኑት የአስም ምልክቶች እንደሚያሳዩ ይገልጻል። በኢትዮጵያ ድንገትኛ ክፍል ከሚያመጡ 5ቱ ዋና ዋና ህመሞች መካከል አስም አንዱ ነው። በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ያሉ የአስም ህመምተኞችስ? በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ብዙ የአስም ታማሚዎች በጭራሽ አይመረመሩም። ምልክታቸውን ችላ ብለው ያልፋሉ። ለዚህም ህይወታቸው አደጋ ላይ ነው። 🔥የአስም ህመም ጠንሳሽ ምክንያቶች በኢትዮጵያ 🏙️ የከተማ አየር ብክለት የአዲስ አበባ የአየር ጥራት መጠን ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው። ባሉ መረጃዎች የከተማው አየር የአለም ጤና ድርጅት የደህንነት ወሰኖችን ይጥሳል ። የአየር ጥራቱም እየተባባሰ ይገኛል። ለዚህም የመኪና ጭስ፣ የመንገዶች አቧራ ፣ በግንባታ እና በኢንዱስትሪ የሚወጡ አየር በካይ ጋዞች እና ንጥረ ነገሮች ፣ እንዲሁም ከሚቃጠሉ ማገዶዎች እና ቆሻሻዎች የሚወጡ ውህዶች ተጠቃሽ ምክንያቶች ይሆናሉ። እ.ኤ.አ. በ 2022 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ የአየር ብክለት ጥናት ፒኤም 2.5 ክምችት የዓለም ጤና ድርጅት ከሚያስቀምጠው ገደብ ከ 5-7 እጥፍ እንደሚደርስ እና ይህም አስም ላለባቸው ሰዎችች ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩን አመላክቷል። 🔥 የቤት ውስጥ የአየር ብክለት አዎ የቤት ውስጥ አየርም ይበከላል። ከ90% በላይ የሚሆኑት የገጠር አባወራዎች እና 60% የሚጠጉ የከተማ ቤቶች አሁንም ምግብ ለማብሰል ከሰል፣ማገዶና ኩበት ይጠቀማሉ። ይህንን ተከትሎ ለሚመጣ አየር መበከል ዋነኛ ተጋላጮች ፤ ቤት ውስጥ የሚውሉ ህጻናት እና ሴቶች ናቸው። 🧬 በቤተሰብ የሚመጣ ተጋላጭነት እና የድህነት ጥምር ዝቅተኛ ግንዛቤና የዘገየ ምርመራ በዘር ከሚመጣ ተጋላጭነት ጋር ተጣምረው ፤ የአስም ታማሚዎችን ቁጥርን እየጨመሩ ይገኛሉ። እዚህ ላይ ያልተሟላ የመድሀኒት አቅርቦት ሲታከልበት ችግሩን ይባባሳል። ለምሳሌ፡ ሳልቡታሞል እና ኮርቲኮስቴሮይድ መተንፈሻ መድሀኒቶች ህይወት አድን እና አስፈላጊ ቢሆኑም በተሟላ ሁኔታ የሉም። መድህኒቶቹ በግል ፋርማሲዎችም ከተገኙ ዋጋቸው ከፍተኛ ነው። ይህም በደሀው የማህበረሰብ ክፍል ዘንድ ያለውን የአስም መድሀኒት ተደራሽነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባል። መድሐኒቱን ካልገዙ ህመሙ ይባባስባቸዋል። ከገዙ ደግሞ መሰረታዊ ፍላጎታቸው ላይ ተጽእኖ አለው። ይህ አሳዛኝ አዙሪት ነው። ይብሱኑ መድሀኒቶቹ ሙሉ በሙሉ የሚጠፉበትም ጊዜዎች ጥቂት አይደሉም። 📚 አስም ህመም የሚያስከፍለው ክፍያ ያልታከመ አስም ያለባቸው ልጆች ፤ በአመት በአማካይ 18 የትምህርት ቀናት ያመልጣቸዋል። አስም ያለባቸው አዋቂዎች በህመሙ የተነሳ ፤ በአመት ከ10-15 የስራ ገበታቸው ላይ አይገኙም። ለመድሃኒት፣ ለክሊኒክ ጉብኝት እና ለትራንስፖርት ብቻ ብዙዎች በሺዎች ያውጣሉ። ይህም ወደ የገንዘብ ችግር ይገፋቸዋል። ሆኖም ከ80% በላይ የሚሆነው የአስም በሽታ ሞትን ፤ በጊዜው በሚደረግ ምርመራና በትክክለኛ መድሃኒት መከላከል ይቻላል። ⚠️ የአስም ህመም ቀስቃሾች⚠️ የአስም ምልክቶች በተለያዩ የአካባቢ እና አካላዊ ምክንያቶች ሊነሳሱ ወይም ሊባባሱ ይችላሉ። አብዛኞቹ ቀስቃሾች እለትተእለት ኑሮ ላይ የተለመዱ ሊሆኑ ይችላሉ። ከእነኝህ መሀል ፡ የቤት ውስጥ ጭስ፡ ምግብ ስናበስል የምንጠቀማቸው ነዳጆች ጭስ (ከሰል፣ ማገዶ፣ ኩበት፣ ወ.ዘ.ተ...) አቧራዎች ፡ ከመንገዶች፣ ከግንባታዎች እንዱሁም ከተለያዩ ምንጮች የሚመጡ አቧራዎች ጠንካራ ጠረኖች/ሽታዎች ፡ከዕጣን፣ ከሰንደል ፣ ከሽቶዎች ፣ ጠረን ካላቸው ሳሙናዎች/ማጽጃዎች፣ ወ.ዘ.ተ... የሚመጡ ጠንካራ ሽታዎች ቀዝቃዛ አየር - የሚተነፍሱት አየር ቀዝቃዛ ከሆነ እንደ ጉንፋን ያሉ የላይኛው የመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽኖች ። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ (በተለይ ስለ ህመማቸው የማያውቁ ልጆች አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ስለማያደርጉ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ያፍናቸዋል) 🌧️ በወቅት ተለዋዋጭ የሆኑ ቀስቃሽ ምክንያቶቹ በበጋ፡ - ከፍተኛ የአቧራ፣ ንፋስ እና የመተንፈሻ ኢንፌክሽኖች በክረምት: ቀዝቃዛ እርጥብ አየር በጸደይ : የአበባ ብናኝ ፣ በተለያዩ አካላት ላይ ያደጉ ሻጋታዎች ። በዚህም የተነሳ በወቅቶች ላይ ተመስርቶ የሚዋዥቁ የአስም ህመም ምልክቶች ይታያሉ። 🚨 ምን ምልክቶች ያሳያል? አስም ሁልጊዜ በደንብ የሚታዩ ምልክቶች ላያሳይ ይችላል። ህመሙ በዝምታ ሊያሰቃይ ይችላል። 👀 የተለመዱ ምልክቶች: ሲተነፍሱ (አየር ሲያስወጡ) እንደ ፉጨት የሚመስል(ወይም ሲር የሚል) ተደራቢ ድምጽ። ሲነጋ ወይም ሲመሽ ማሳል / አየር ማነስ። የደረት መጭነቅ ወይም የደረት ህመም ትንፋሽ ማጠር ወይም በፍጥነት መተንፈስ ለትንሽ ስራ አብዝቶ መድከም 🛑 አሳሳቢ ምልክቶቹ (የህክምና ድንገተኛ አደጋ) ቃላት ለማውጣት መቸገር። ሙሉ ዓረፍተ ነገር መናገር አለመቻል። በሚተነፍሱበት ጊዜ የአፍንጫ ቀዳዳ መስፋት ወይም የጎድን አጥንት መሰርጎድ ከንፈር ወይም ጣቶች ወደ ሰማያዊነት መለወጥ ለአስም በሚሳቡ የመተንፈሻ መድሐኒቶችም ወስደው የአስም ምልክቶቹ አለመጥፋት። እነኝህን ምልክቶች ካዩ ፤ አፋጣኝ ድንገተኛ ህክምና ያስፈልጋልና ፈጽሞ አይዘናጉ። አቅራቢያ ወደሚገኝ የጤና ተቋም በፍጥነት ይሂዱ። 💡በአስም ዙሪያ ምን ሊደረግ ይችላል? ✅ 1. ብሔራዊ እውቅና በኢትዮጵያ አሁን አስም ቀዳሚ ስፍራ አልተሰጠውም። ለዚህም እውቅና ተሰጥቶት በአገር አቀፍ ደረጃ የአስም ህመም እንክብካቤ እና ስልጠና ያስፈልጋል። በህመሙ ዙሪያ በተሟላ ደረጃ መረጃ መሰብሰብ ይኖርበታል። ✅ 2. የህዝብ ግንዛቤ ዘመቻዎች ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከ50% በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ፤ በአስም ዙሪያ የተሳሳተ ግንዛቤ አላቸው። ለዚህም ለማህበረሰቡ ስለ አስም ህመም ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረው ፤ መሰራት ይኖርበታል። ለዚህም በሬዲዮ፣ በቲቪ፣ በትምህርት ቤቶች እና በሃይማኖታዊ መድረኮች ላይ ፤ ግንዛቤን የሚያሳድጉ ትምህርታዊ ዘመቻዎች ያስፈልጋሉ። የአስም ህመም ተላላፊ አለመሆኑም መታወቅ ይኖርበታል። ✅ 3. የአስም መድሐኒቶች ተደራሽነት መጨመር አለበት። አስፈላጊ የአስም መድሃኒቶች በነጻ የሚቀርቡ የህዝብ አስፈላጊ መድሃኒት ጥቅል ውስጥ ተካተው ፤ ተመጣጣኝና ያልተቋረጠ አቅርቦትን መረጋገጥ የሚችልበት መንገድ መዘጋጀት ይኖርበታል። የሳልቡታሞልን እና የኮርቲሲቶሮይድ መተንፈሻ መድሀኒቶች ህይወት አዳኝ ናቸውና ፤ ሀገር ውስጥ ያላቸው አቅርቦት ፈጽም መቋረጥ የለበትም። ✅ 4. ንጹህ አየር እና የአካባቢ ጥበቃ ቆሻሻ ማቃጠል በማህበረሰብ ደረጃ መቆም አለበት። ቤቶች በደንብ መናፈስ አለባቸው። ቤት ውስጥ ካበሰሉ በካይ ጭስ የሌላቸውን የማብሰያ ነዳጆች ይጠቀሙ። ኤሌክትሪክ ይጠቀሙ። 🧒 ለወላጆች እና አስተማሪዎች ምልክቶቹን ይወቁ። የአስም ህይወት አድን መድሀኒቶችን (inhalers) በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያስቀምጡ። አስም ያለባቸው ልጆች አካል ብቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ፤ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ መከናወኑን ያ ረጋግጡ። (ለምሳሌ፣ አስፈላጊ ከሆነ ከቅድመ-ልምምድ በፊት inhaler አጠቃቀምን ይወቁ) ልጆች ከመለስተኛ እንቅስቃሴ በኋላ ድካም ከተሰማቸው እንዲናገሩ አበረታቷቸው። 🗣️ ስለ አስም መነጋገር ይኖርብናል። መቆጣጠር በሚቻል ህመም ወገናችን መሰቃየት የለበትም። ንግግራቸው ሳይገድብ ቃላቸውን ሳይሰናክል፣ እስትንፋሳቸውን ሳይሰርቅ በፊት እንከላከለው። በግንዛቤ ላይ የተመሰረተ ተግባራዊ ለውጥ ማምጫ ጊዜው አሁን ነው።
- 🌿ጤና አዳም ጀርባ ያለው ሳይንስ
ብዙ ኢትዮጵያዋያን ሲታመሙ ፤ አልያም ጤናቸውን ለመጠበቅ ጤና አዳም ይጠቀማሉ። ለትኩሳት ፣ ለሆድ ህመም ወ.ዘ.ተ የሚጠጣው ውስጥ ጤና አዳም ቅጠል ተደርጎ ይመጣል። ህመም ሳይኖር እራሱ ፤ ቡና፣ ሻይ እና ወተት ላይ እንደ ልማድ ጤና አዳም የሚከቱ ብዙዎች ናቸው። ለምን? ለቃናው ወይስ ጤናን ለማጎልበት። ስንታመም እናቶቻችን/አያቶቻችን ምግብ ውስጥ አድርገው የሚሰጡን ጤና አዳም የሚያሽለው በእናት/አያት ፍቅር ታጅሎ መቅረቡ ነው ? ወይስ መድሐኒትነት ኖሮት ? ጤና አዳም ታሪክ በአለም ዙሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ ጤና አዳም እንበለው እንጅ ፤ የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም ። በአለም ዙሪያ ይታወቃል። የሰው ልጅ ጤና አዳምን እንደመድሐኒትነት መጠቀም ከጀመረ ፤ ሺ አመታት ተቆጥረዋል። ግሪካዊው ሐኪም በአንደኛው መቶ ክፍለዘመን በጻፈው የሕክምና መጽሐፍ ላይ ፤ ጤና አዳአም ለነርቭ ሕመሞች ፣ ለምግብ መፈጨት ችግር እንዲሁም ለመርዛማ ንክሻ መድሐኒትነት እንዳለው አስፍሯል። የጥንት የሮም ወታደሮችም ራሳቸውን ከበሽታ እና ከክፉ መናፍስት ለመከላከል ፤ ጤናዳም ይይዙ ነበር። በሌሎች ማህበረሰቦች ጤና አዳም ለወር አበባ ህመም ማስታገሻ ፤ እንዲሁም ለ ምግብ መፈጨት ችግሮች ይውል ነበር። በሜዲትራንያ ባሉ ሀገራት ደግሞ ፤ ጤና አዳምን ከቤት አጠገብ መትከል ፤ መጥፎ እድልን ያርቃል ብለው ይታመን ነበር። በቀኝ ግዛት ዘመን የተዋወቀ ቢሆንም ፤ በደቡብ አሜሪካ (ላቲን አሜሪካ) ደግሞ ፤ ለሆድ ሕመም እንዲሁም ክፉ መንፈስ ለማባረር ፤ጤና አዳም ይውል ነበር። እንደ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሞሮኮ፣ ግብፅ ባሉ አረብ አገራት በሻይ እና በምግቦች ውስጥ ተደርጎ ፤ ኢንፌክሽን ህመሞችን ለማከም እና ህመም ለማስታገስ ይጠቀሙት ነበር። ኢትዮጵያም ጤና አዳም ከዘመን ዘመን ሲሸጋገር የመጣ ፤ ለብዙ ህመሞች ፍቱን የሆነ ባህላዊ ህክምና ነው። በባህላዊ ህክምና ባለውም የጤና ጠቀሜታ ፤ የአዳም ጤና (የሰው ልጅ ጤና) በመባል ይጠራል። በባህላዊ ህክምና ለ ኢንፌክሽን ህመሞች ፣ ለትኩሳት ፣ ለራስ ምታት ፣ ለሆድ ህመም ፣ ለምግብ መፈጨት ችግር ፣ ለደም ግፊት፣ ለ ድኅረ ወሊድ እንክብካቤ ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል። የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አብዝቶ ከሚጠቀማቸው ባህላዊ መድሐኒትነት ካላቸው ቅጠሎች ይካተታል። ከመድሐኒትነቱ ባሻገር ፤ ከማንነታችን ጋርም ቁርኝነት አለው። ከ ጤና አዳም ጋር ብዙዎቻችን ትውስታ አለን። አንድ ጥያቄ እንጠይቅ እስቲ... እነኝህ በዘመናት ፣ በኪሎ ሜትሮች ፣ በባህል እና በእምነት የተራራቁ ማህበረሰቦች ውስጥ ፤ ጤና አዳም እንዴት ተቀራራቢ የጤና ጠቀሜታ ሊኖረው ቻለ? የ አጋጣሚ ጉዳይ ፣ የባህል ትስስር ወይስ እውነተኛ የጤና ጠቀሜታ ኖሮት? ይህን ጥያቄ ለመመለስና የጤና ጠቀሜታውን ለመለየት፤ ሳይንቲስቶች በጤና አዳም መድሐኒታዊ ባህሪ ዙሪያ ላይ ብዙ ጥናቶችን አካሂደዋል። ሙሉ ጠቀሜታውን ለመረዳት እና ወደ ዘመናዊ ህክምና ለማምጣት አሁንም ጥናቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ። የጤና አዳም ተክል ሳይንሳዊ ግንዛቤ ጤና አዳም ተክል በሳይንሳዊ ስሙ ሩታ ቻልፕንሲስ (Ruta chalepensis) ይባላል። ሳይንስ አሁን በተረዳው ደረጃ ፤ ይህ ቅጠል በውስጡ ብዙ የፈውስ አቅም ያላቸው ውህዶች አሉት። ከእነኝህ ውህዶች የጤና ጠቀሜታቸውን ሳይንስ ለይቶ የተረዳው የሚከተሉትን ነው። ጤና አዳም በውስጡ ጸረ ኦክሲዳንት ባህሪ ያላቸው ውህዶች አሉት። እነኝህ ፍላቭኖይድስ የሚባሉት ውህዶች ፤ ሰውነታችንን ይደግፋሉ። የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል አቅም ይደግፋሉ። የፀረ-ባክቴሪያ፣ ፀረ-ፈንገስ እና ፀረ-ተባይ ባህሪያትን ያላቸው ዘይቶች በውስጡ አሉት። እነኝህ ዘይቶች (2-undecanone & methyl-nonyl-ketone) በተለያዩ ባክቴሪያዎች ላይ ( E. Coli, Staphylococcus Aureus) ላይ አሉታዊ ተጸእኖ እንዳላቸው ጥናቶች ያሳያሉ። የህመም ማስታገሻ ባህሪ ያላቸው ውህዶችም (Alkaloids, furocoumarins chalepensin) ተገኝተዋል። እነኝህ ውህዶች ህመምን ከመቀነስ ባሻገር ፤ በፀረ-ተሕዋስያን ( antibiotics) ባህሪ አላቸው። ከዚህም ባሻገር ውስጡ ያሉ ውህዶች የደም ስር ግድግዳዎችን ያላላሉ (ያሰፋሉ)። ይህም የደም ግፊት መጠንን ይቀንሳሉ። ይህ ባህሪያቸው በእንሰሳት ላይ በተደረጉ ጥናቶች ተረጋግጧል። ሙሉ በሙሉ ያልተረጋገጡ ፤ ገና በጥናት ላይ ያሉ ባህሪያቶቹ ደግሞ የሚከተሉት ናቸው። የደም ቅጥነትን/ውፍረትን የሚለውጡ ውህዶች በውስጡ ተገኝትዋል። ሆኖም ግን የእነኝህ ውህዶች ልዩ ባህሪ ፤ ደምን ማቅጠን ይሆን ማወፈር ገና አልተረጋገጠም። ነርቭ ላይም ተጽእኖ ያላቸውም ውህዶች ተገኝተዋል። እነኝህም ውህዶች ነርቭን ያደንዝዙ ያነቃቁ ገና እየተጠና ነው። ከዚህም ባሻገር ውስጡ ያሉ አንዳንድ ውህዶች የካንሰር ህዋሳት ላይ ያለው ተጽእኖም በጥናት ላይ ነው። ይህ አፈ ታሪክ፣ትውፊት ወይም መላምት አይደለም። በዘመናዊ መንገድ ሲጠና የተገኙ የጤና አዳም አስደናቂ መድሐኒታዊ ባህሪያቱ ናቸው። የቅድሙን ጥያቄ ስንመልስ ... "አዎ ጤና አዳም እውነተኛ ብዙ የጤና ጠቀሜታ አለው።" እንደውም ይህ እጽዋት የባክቴሪያዎችን እድገት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚገታ እንደውም አቅሙ ከአንዳንድ መድሐኒቶች ጋር ሊወዳደር እንደሚችል ሁሉ ያሳየ የላብራቶሪ ጥናት አለ። ⚠️ ጥንቃቄ የመድሐኒትነት ጥቅሙን ከተረዳን ፤ ውስጡ ያሉት ውህዶች ያላቸው የመድሐኒትነት ባህሪ ኃይለኛ መሆኑን መገንዘብ አለብን። ባህላዊ ህክምና ብዙ ጊዜ ተግዳሮቱ ፤ የመድሐኒቶችን ውህድ መጠን መለየቱ ላይ ነው። ውስጡ ያሉ ውህዶች ሲበዙ ጉዳት ሊያመጡ ፤ አልያም ህመም ሊያባብሱ ወይም መድሐኒት ጋር ሊቃረኑ ይችላሉ። ስለዚህ መጠኑን ሁሌ መጠንቀቅ አግባብ ነው። በዋነኝነት መጠንቀቅ ያለብን፡ እርግዝና ጊዜ መጠንቀቅ አለብን። የማህጽን ጡንቻ እንዲኮማተር የሚያደርጉ ውህዶች ስላሉት፤ በእርግዝና ጊዜ አይመከርም። በእንሰሳቶች ላይ የተደረጉ ጥናቶች ይህንን አረጋግጠዋል። ጥናቶቹ እንደሚያሳዩት ከሆነ መጠኑ በበዛ ቁጥር ማህጸን የመኮማተር ኃይሉ ይጠነክራል። ይህ ደግሞ እርግዝና እንዲቋረጥ ሊያደርግ ይችላል። ለዚህም ይሆናል አንዳንድ ማህበረሰቦች በባህላዊ ህክምና ጽንስ ለማቋረጥ የሚጠቀሙት። ቅድም በመድሐኒትነት የጠቀስናቸው ውህዶች (furancoumairns, alkaloids and flavonois) ሲበዙ ፤ ጉበትን ሊጎዱ ይችላሉ። ለዚህ አብዝቶ ጤና አዳም መውሰድ አይመከርም። ይህ በጥናቶች ተረጋግጧል። ካሉት ውህዶች አንዱ (furanocoumarin) የጉበት የመድሐኒት ማርከሻ ኤንዛይም (CYP3A4) ያከሽፋል። በዚህም የተነሳ የተለያዩ መድሐኒቶችን ስራ ለውጦ ፤ መርዛማ ያደርጋቸዋል ። ስለዚህ መድሐኒት ለሚወስድ ሰው ጥንቃቄ ማደረጉ መልካም ነው። በተለይ ጤና አዳም በብዛት ከተወሰደ። "እስከዛሬ ስወስድ ምንም አልሆንኩም!"ብለው ካሰቡ ይህንን ያስታውሉ፤ ቁልፉ ያለው ከመጠኑ ጋር ነው። ጤና አዳም ብዙ በሳይንስ የተረጋገጠ ጥቅም ያለው ተክል ቢሆንም ፤ ሲወስዱ ጥንቃቄ ያድርጉ። አብዝቶ መውሰድ ከደህንነቱ ፤ ጉዳቱ እንዲያይል ሊያደርግ ይችላል። ከዘመናዊ ህክምና ይጠቃለል ይሆን? ይህ ቅጠል ከባህላዊ ህክምና የመጣ ስለሆነ ፤ ወደ ዘመናዊ ህክምና እስኪጠቃለል ብዙ ጥናቶች ያስፈልጋሉ። ውስጡ መድሐኒትነት ያላቸው ንጥረ ነገሮች ፤ ለሚያዱኑት ህመም ብቻ እንዲሆኑ ተደርገው ተለይተው መመረት አለባቸው። ይህ ደግሞ ረዥም ጊዜ ይፈጃል። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ጥናት እያካሂዱ ያሉ ተቋማት እና ግለሰቦች ራሱ ትኩረት ሰጥተው ማጥናት የጀመሩት በቅርብ ጊዜ ነው። በአለም ዙሪያ ያሉ ተመራማሪዎች የመድኃኒትነቱን መጠንን፣ የመርዛማነት ገደቦችን እና የውህዶችን መለየት ዙሪያ እየሰሩ ነው። ከሱ አንጥረን ያወጣነው ውህድ ሆነ ጤናዳም ቅጠሉ ፤ በዘመናዊ መንገድ ተዘጋጅቶ ፤ የብዙ ሰዎች ጤና በዘመናዊ መልክ ማከሙ የማይቀር ነው። ስምን መልአክ ያወጣዋል እንዲሉ... ጤናዎን እንዲያግዝ ጤና አዳምን ይጠቀሙ።
- ትኩረት የሚነፍገው አቅለብላቢው የአእምሮ ህመም (ADHD)
አሁን ያለንበት የፈረንጆች የጁን ወር ፤ በአለም አቀፍ የወንዶች የአእምሮ ጤና ወር ነው። ለዚህም ይህ ጽሁፋችን ከሴቶች ይልቅ ወንዶችን ሶስት እጥፍ ስለሚያጠቃው የአእምሮ ህመም እናወራለን። ህመሙ በባህሪው ትኩረት የሚነፍግ እና አቁነጥናጭ ስለሆነ ፤ ይህንን ባህሪውን በሚገልጸው ስሙ አቴንሽን ደፊሲት ህይፐርአክቲቭ ዲሶርደር (attention deficit hyperactive disorder ) ወይም ኤዲኤች ዲ(ADHD) በመባል ይጠራል። ይህ የአእምሮ ህመም ከ 2.5 እስከ 3.4 ፐርሰንት የሚሆኑ ጎልማሶችን እና ከ 5 እስከ 7 ፐርሰንት የሚሆኑ ህጻናትን በአለም ዙሪያ ያጠቃል። አንዳንድ መረጃዎች ደግሞ በአለማችን 366 ሚሊየን ጎልማሶች እና 6.5 ሚሊየን ህጻናት በህመሙ ተጠቂ እንደሆኑ ያሳያሉ። አብዛኞቹ ታማሚዎች ህመሙ እንዳለባቸው እንኳን አያውቁም። ለዚህም አስፈላጊ የህክምና እርዳታ አያገኙም። ይህ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ይብሳል። ህመሙ በዋነኝነት ከአእምሮ አሰራር/ አመሰራረት ጋር የተያያዘ ነው። ከህመሙ ጋር የተያያዘውን እክል ቀለል ባለ ቋንቋ ስንገልጽው፡ የአእምሮአችን ትኩረት ፣ ተነሳሽነት ፣ ጊዜ አጠቃቀም እና ራስን መቆጣጠር ጋር የተያያዙ የአእምሮአችን ክፍሎች ተባብረው ለመስራት ሲቸገሩ ይፈጠራል። እነኝህ የአእምሮአችን ክፍሎችም እርስ በእርስ ሳይናበቡ በየግላቸው ይሰራሉ። ይህም ደግሞ በተለያየ ውስብስብ ምክንያት የሚከሰት ቢሆንም ፤ ትኩረት፣ ተነሳሽነት፣ ጊዜ አጠቃቀም እንዲሁም እራስን መቆጣጠር ችሎታ እንዲሰናከል ያደርጋል። ህመሙ ለብዙዎች እድሜ ልክ ሲሆን ፤ ታማሚዎች በልጅነት እድሜያቸው ጊዜ በትምህርታቸው ይቸገራሉ። አድገውም በስራቸው እንዲሁ። ሰነፍ ባይሆኑም ህመሙ ሰነፍ ያስመስላቸዋል። ውጤታማነትን ይዘርፋቸዋል። ተነሳሽነት የላቸውም። ጊዜ ያባክናሉ። ሀሳባቸውን የተሰበሰበ አይደለም። አደብ አይገዙም። ብዙ ታማሚዎች ህመሙ እንዳለባቸው ስለማያውቁ ፤ እራሳቸውን ሰነፍ ፣ አልያም ደደብ አድርገው ይወስዳሉ። ህመሙ በበኩሉ መፍትሔ ካልተሰጠው ፤ የትምህርት አቅምን አኮላሽቶ ከማስቀረት አልፎ ፤ አድገው እራሱ በስራ ውጤታማ እንዳይሆኑ ያደርጋል። በራስ ያለ መተማመንንም ያመነምናል። 🔬መንስኤው ታድያ ምንድን ነው? እላይ እንደገለጽነው የዚህ ህመም መስረት ከነርቭ (አንጎል) ጋር የተያያዘ ሲሆን ፤ ለህመሙ መያዝ ተጋላጭነት የሚጨምሩ ምክንያቶች መካከል ፡ 🧬 ከዘረመል ጋር የተያያዙ ምክንያቶች ፡ ህመሙ በዋነኝነት በዘር የሚተላለፍ ነው። ለዚህም በቤተሰብ ውስጥ ህመሙ ያለበት ሰው ካለ ፤ ሌላ የቤተሰብ አባል የመያዝ እድሉ ከፍተኛ ነው። ህመሙ ያለባቸውም ወላጆች ልጆቻቸው ላይ ምልክቶቹን ቢከታተሉ ይመረጣል። 🧠 የአንጎል ችግሮች ፡ ህመሙ ከአንጎል ችግሮች ጋር ይያዛል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ፤ ህመሙ ያለባቸው ሰዎች ትኩረትን እና መነሳሳትን በሚቆጣጠሩ የጭንቅላት አከባቢዎች ላይ ያለ የአእምሮ ስራ የተገደበ ነው። 🤰 ቅደመ ወሊድ ምክንያቶችም ለዚህ ህመም አጋላጭ ተደርገው ይጠቀሳሉ። ያለጊዜ መወለድ፣ በእርግዝና ጊዜ የእናቶች ማጨስና አልኮል መጠጣት ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው። 🥦🍊 ከአመጋገብ ጋር የተያያዙ ምክንያቶች ሊያጋልጡ ይችላሉ። በተለይ ቪታሚን ቢ (vitamin B9 & B12) እጥረት ፤ ህጻናት ምልክቱን እንዲያሳዩ ይደረጋል። 🌍 እንደ ሊድ(lead) ያሉ ንጥረነገሮችም በአከባቢያችን ካሉ ፤ ለህመሙ ሊያጋልጡ እንደሚችሉ ጥናቶቹ ያመላክታሉ። ከዚህም ባሻገር ሞባይል አብዝቶ መጠቀም፣ ቲቪ አብዝቶ ማየት፣ እንቅልፍ ማነስ፣ አከባቢ ላይ አስጨናቂ ነገር መኖር ፤ የህመሙ ምልክቶች እንዲባባሱ ያደርጋል። 🚸 ችላ የማይባሉት ምልክቶች ይህ ህመም ምልክቶች ብዙውን ጊዜ ከ6 አመት ጀሞር የሚታዩ ሲሆኑ እስከ አዋቂነት ድረስ ይዘልቃሉ። ምልክቶቹ በዋነኝነት በሶስት የሚፈረጁ ሲሆን እነኝህም ትኩረት ማጣት ይህ ህመም ያለባቸው ሰዎች ትኩረታቸውን መሰብሰብ ያስቸግራቸዋል። በቀላሉ ሀሳባቸው ይበተናል። ለነገሮች ዝግጁ ለመሆን ይቸገራሉ። ቤታቸው፣ ክፍላቸው የተደራጀ (ስርአት ያለው) አይሆንም። አብዝተው ይዘነጋሉ። ቁልፎች እና ትናንሽ እቃዎችን ጠፍተውባቸው መፈለግ ልማዳቸው ነው። ያሰቡት ይጠፋባቸዋል። ይብሱኑ ስራም ይዘነጋሉ። አብዝተው ይቅለበለባሉ እነኝህ ታማሚዎች ነገሮች ላይ መፍጠን ያበዛሉ። አርፈው መቀመጥ ይቸገራሉ። ይቁነጠነጣሉ። ሲያወሩ እራሱ በብዛት ነው። ግልፍተኛ ናቸው ይህ ህመም ያለባቸው ስዎች በጉዳዮች ግልፍተኝነት ያጠቃቸዋል። ራሳቸውን የመቆጣጠር አቅማቸው ጠንካራ አይደለም። ለዚህም ሳያስቡ ያወራሉ። ሳያስተውሉ ድርጊቶችን ይፈጽማሉ። ለዚህም ራሳቸውን አደጋ የሚጥል ሁኔታ ውስጥ ሊያገኙ ይችላሉ። አውርተን እስክንጨርስ ከመጠበቅ ፤ ወሬ መሀል ሊያቋርጡን ይችላሉ። ህጻናቶች በትምህርታቸው ደካማ ሲሆኑ፤ አዋቂዎች ደግሞ ብዙ ስራ ሊለዋውጡ ይችላሉ ። ውጤታማነት ያስቸገራቸዋል። አልያም በዝምታ በጭንቀት ይሰቃያሉ። የታማሚዎች ህይወት ይህ ህመም ያለባቸው መደበኛ ህይወት ሲመሩ እክሎች ያጋጥማቸዋል። ጭንቅላታቸው ነገሮችን የሚፈጽምበት መንገድ የተለየ ስለሆነ ፤ በማህበረሰባዊ ህይወት፣ በትምህርት እንዲሁም በስራ ላይ ተግዳሮቶች አያጡም። 🎒 በት/ቤት፡- ብሩህነትን ማጣት ይህ ህመም ያለበት አንድ ልጅ " ሰነፍ ነህ"፣ "አስቸጋሪ ልጅ ነው" ፣ "መማር አይፈልግም" የሚሉትን ቃላት ደጋግሞ ሰምቷቸዋል። ሆኖም ግን እወነታው በተቃራኒ ነው። እነኝህ ልጆች እንደውም የፈጠራ ችሎታቸው የላቀ ብሩህ ናቸው። የማወቅ ጉጉታቸውም አስገራሚ ነው። ጠያቂ ናቸው። ምን ያድርጉ ታድያ?! የአእምሮአቸው እምቅ ኃይል በህመሙ የፊጥኝ ታስሯል። አፉ የታፈነ ሰው ሲያወራ እንደማይሰማን፤ ህመሙን አልፎ የእነሱን ብሩህ አእምሮ ማየት አዳጋች ነው። 📉 በዚህም የተነሳ ከጤነኛ ልጅ አንጻር ህመሙ ያለባቸው ልጆች ፤ ትምህርት የማቋረጥ እድላቸው በሶስት እጥፍ ይጨምራል። ብዙዎች ተምረው አይጨርሱም። ከእነኝህ መህል ደግሞ አስፈላጊውን የትምህርት እና የ ስነልቦና እገዛ የሚያገኙት እጅጉን አናሳ ናቸው። 👷 በስራ ላይ፡ ብልኹ ቸልተኛ ሰራተኛ። እንደ ህጻናቱ ህመሙ ያለባቸው አዋቂዎች ፤ አእምሮአቸው ብሩህ ሆኖ በፈጠራ የተሞላ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን ያለ ህክምና ድጋፍ ብዙውን ጊዜ። ስራን በተገቢው ሰአት ለማድረስ ይቸገራሉ። ሀሳባቸውን መሰብሰብ ለእነርሱ ትግል ነው። ስራ እንደለዋወጡ ነው። ነገር ስለሚዘነጉ ፤ ሰው ስለማያስተውሉ ስራ ቦታ ያለ ማህበረሰባዊ ህይወት ላይ ሊቸገሩ ይችላሉ። ቸልተኛ ስለሚመስሉ ሊገለሉ ይችላሉ። ሁሉም ህመሙ ያለባቸው ስነፍ ወይም ቸልተኛ አይደሉም። አንዳንዶቹ ህመሙ ያመጣባችውን ተግዳሮቶች አልፈው ፤ እጅጉን ስኬታማ ሊሆኑ ይችላሉ ። ስራ ፈጣሪዎች፣ ዶክተሮች፣ ኢንጅነሮች፣ አርቲስቶች... ሆነው ሊገኙ ይችላሉ። እንደማሰናከሉ ሁሉ ፤ ለውጤታማነታቸውም ህመሙ አስተዋእጾ ይኖረዋል። የኢትዮጵያ እውነታ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው መረጃ ከሆነ ፤ ይህ ህመም እምብዛም አይታይም። ይሄ ግን የምሰራች አይደለም! ከማብሰራችን በፊት ለምን ብለን ብንጠይቅ መልካም ነው። ለምን? በኢትዮጵያ ውስጥ ❌በህመሙ ዙሪያ ላይ ምንም አይነት አገር አቀፍ መረጃ የለም። ❌ ህመሙን በህጻናት ላይ የሚያክሙ የህጻናት ስነልቦና ሐኪሞች ቁጥር በጣሙን ትንሽ ነው። ❌አስተማሪዎች ስለ ህመሙ ግንዛቤ የላቸውም። ❌ የ ህመሙ ምርመራ በትምህርት ቤቶች የለም። ❌ ህመሙ የልጁ ንዝዕላልነት/ ስንፍና፣ አልያም የወላጅ አስተዳደግ ፣ እንዲሁም ዋልጌ ባህሪ ተደርጎ ይወሰዳል። ❌ልጆቹም ትምህርት አቋርጠው ስለሚወጡ ፤ የሚያስተውል አካል ላይኖር ይችላል። ❌ቸልተኛ ልጅ ሆነ ቸልተኛ ሰው በባህላችን ንቀት ስለሚመስለን አንወድም። ከመረዳት ይልቅ እናገላቸዋለን። 💡 ታድያ ምን እናሻሽል? 🔎 ግንዛቤያችን ፈጽሞ መሻሻል አለበት። የአእምሮ ጤና ማለት ዘርፈ ብዙ ነው። እብደት ብቻ አይደለም። 👨👩👧👦 ወላጆች ስለህመሙ ማወቅ አለባቸው። ልጁ ህመሙ እንዳለበት ሊረዳ አይችልም። ከተጠራጠሩ የሰነ ልቦና ሐኪም ጋር ይዘው መሄድ ይኖርባቸዋል። 💊በስነ ልቦና ህክምና እና በሚሰጡ መድሐኒቶች የልጁ ውጤታማነት ሊሻሻል ይችላልና ፤ ወላጆች ህክምና ይዘው ለመሄድ ማመንታት የለባቸውም። 🧑🏫 የትምህርት ቤት ድጋፍ ያስፈልጋል። መምህራኖቻችን ስለ ህመሙ ማወቅ ይኖርባቸዋል። ህመሙ ያለባቸውን ልጆች እንዴት ማስተማር እንዳለባቸው መገንዘብ ይኖርባቸዋል። 👩💼 አሰሪዎች ስለ ህመሙ ቢያውቁ ውጤታማ ሰራተኞቻቸውን አያጡም። አሰራርን በመለወጥና የስራ ቦታዎችን በማሻሻል ፤ የእነኝን ህመምተኞች ብሩህ አእምሮ ለድርጅታቸው ትርፋማነት ሊጠቀሙት ይችላሉ። ማሳረጊያ ነጥብ ይህ ህመም የስንፍና ሆነ ተገቢ ያልሆኑ ባህሪያት ሰበብ አይደለም። ህመሙ ያለባቸው ሰዎች ራሳቸውን የመቆጣጠር አቅማቸው ስላልጠነከረ ፤ ተነሳሽነታቸው ዝቅተኛ ስለሆነ የሚመጣ ነው። የህመሙ መሰናክል ታማሚዎች ለራሳቸው የሚሰጡትን ቦታ አውርዶ ፤ ጭንቀት ውስጥ ይከታቸዋል። ስለዚህም ተረድተናቸው ፤ ማገዝ አለብን። የኛ በመረዳት ላይ የተመሰረት ትንሽ ተግባር ፤ ለእነሱ ህይወት ቀያሪ ሊሆን ይቻላል።
- እናቶቻችን ለምንድነው በሳንባ ካንሰር እየተጠቁ ያሉት?
ገና ወፎች ሳይጮሁ ነበር ከ እንቅልፏ የተነሳችው። ልጆቿ ትምህርት ቤት ይሄዳሉ። ባለቤቷም ቀኑን ሙሉ ስራ ይውላል። ምግብ ማዘጋጀት ነበረባት። ገና የጸሀይ ጮራዋ ሳይታይ ተነስታ ከሰል አያያዘች። ምግብ አበሰለች። ልጆቿ ሲነሱ። ቤቱ ሞቅ ብሏል። ምግብ ቀርቧል ፣ ሻይ ፈልቷል ፣ ምሳቃቸው ታስሯል። ደስ አላቸው። ባሏን ሽኝታ ወደ ማእድ ቤት ገባች። ባሏ ሰርቶ የሚያመጣው በቂ ስላልነበር ፤ ይህች እናት ሙልሙል መጋገር ጀመረች። ይህች እናት ኑሮዋን ለማገዝ እንጀራ ጋግራ ሙልሙል ሸጣ ኑሮዋን ታግዝ ነበር። የሞላላት ቀን 50 እንጀራ ፣ 100 ሙልሙል ትሸጣለች። ባሏና ልጆቿ ከስራ ሲመለሱ እራት አዘገጃጅታ ሁሉን አሟልታ ነበር የምትጠብቃቸው። ከ 20 አመት በኋላ... ልጆቿ ዩንቨርስቲ ጨርሰው ፤ ስራ ጀምረዋል። ታድያ ይህች እናት የሳል ህመም ሰነበተባት። መድሐኒት ወስዳለች፤ ግን አልተሻላታም። የሳንባ ምችም ተብላ ታክማ ነበር። ሌላው ህመም ሲለቃት ሳሉ ግን አልተዋትም ነበር። ከቀን ወደ ቀን ሰውነቷ እየመነመነ መጣ። ጤናዋ ጉዳይ ያሳሰባቸው ልጆች ወደ ሀኪም ቤት ይዘዋት ሄዱ። ዜናው ግን ፈጽሞ ያልጠበቁት ነበር። ሁሉቱም ሳንባዋ በሳንባ ካንሰር ተጠቅቷል። ደነገጡ! ቤቷን ለማቅናት ስትለፋ የተነፈሰችው የማገዶ ጭስ ፤ ይህን ይዞ እንደሚመጣ ቀድመው ቢያውቁ ምን ያደርጉ ነበር ? ሳንባ ካንሰር ምንድነው የሳንባ ካንሰር በዓለም ላይ ካሉት ገዳይ ነቀርሳዎች አንዱ ነው። በገዳይነቱ ከጡት፣ ከፕሮስቴት፣ እና ከአንጀት ካንሰር ይበልጣል። በህይወት ያሉ የካንሰሩ ታማሚዎችም ያለባቸው ስቃይ/ ህመም ቀላል አይደለም። ለዚህ ካንሰር አጋላጭ ምክንያቶች ተብለው የሚጠቀሱት ማጨስ፣ የአየር ብክለት፣ እንደ ራደን እና አስቤስቶስ ያሉ ኬሚካሎች ፤ እንዲሁም በቤተሰብ የሳንባ ካንሰር መኖር ናቸው። በአብዛኛው የአለም ክፍል ይህ ካንሰር ከሲጋራ ማጨስ እንዲሁም ፤ ከኢንዱስትሪ ኬሚካሎች ተጋላጭነት ጋር የተያያዘ ነው። እንደውም በምእራቡ አለም 80 ፐርሰንት የሚሆነው ከሲጋራ ማጨስ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። ሲጋራ በውስጡ ወደ 60 የሚጠጉ ካንሰር አምጪ ኬሚካሎች ስላሉት ይህንን ካንሰር ያመጣል። ሆኖም ግን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገራት ላይ የዚህ ካንሰር ዋነኛ ገፈት ቀማሾች ፤ ሲጋራ የማያጨሱ የቤት እመቤቶች ሆነው ይገኛሉ። ለምን? በእነኝህ አገራት ለዚህ ካንሰር ዋነኛ አጋላጭ ምክንያት ተደርጎ የሚገለጸው የቤት ውስጥ አየር መበከል ነው። ይህም በባህላዊ መንገድ ቤት ውስጥ ምግብ ከማብሰል ጋር ይያዛል። አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ቤቶች (ከ 85 እስከ 92 ፐርሰንት) ፤ ለአንድም ይሁን ለሌላ ግልጋሎት ለቀን የምግብ ፍጆታቸው ከሰል፣ እንጨት፣ የአዝእርት አገዳ ፣ ኩበት ፣ ወ.ዘ.ተ... ይጠቀማሉ። እነኝህ አይነት የኃይል ምንጮች ባዮ ማስ ፊዩል ሲባሉ ፤ እነሱ ሲቃጠሉ የሚወጣው ጭስ ከባድ የጤና ጠንቅ አለው። በውስጡ ብዙ ካንሰር አምጭ ኬሚካሎችን የያዘ ነው። እነኝህ ኬሚካሎች እና ጋዞች ውስጥ በጥቂቱ፡ ደማችን ውስጥ በቀላል ገብተው የሚቆዩ ብዙ ጤና ጠንቅ ያላቸው ደቃቅ ኬሚካሎች (PM10 & PM 2.5)። ካርቦን ሞኖክሳይድ ፎርማልዲሃይድ የናይትሮጅን ውህዶች ሌሎች ካንሰር አምጪ ኬሚካሎች፣ ወ.ዘ.ተ... ይህንን ለመሸሽ የቡታ ጋዝ የሚጠቀሙ ቢኖሩም ፤ ቡታ ጋዝ ውስጥ ያለው ነጭ ጋዝ ጤና ጠንቁ የተሻለ አይደለም። ለዚህ ተመራጭ የኤሌክትሪክ ስቶቭ አልያም ፤ ሜቴን ወይም ኢታኖል የሚጠቀሙ የሲሊንደር ስቶቮች ናቸው ። እነኝህም ነዳጆች በደንብ አየር የማይናፈስበት ቤት ውስጥ ሲቃጠሉ ፤ አብዛኛው የቤተሰብ አባላት ለጭሱ ተጋላጭ ይሆናሉ። ለዚህም ግንባር ቀደም ተጋላጭ የሚሆኑት ፤ ምግባችንን ሲያበስሉ የሚውሉ እናቶቻችን ናቸው። እነሱም ቀን በቀን ሳያቋርጡ ፤ ይህን መርዛማ ጭስ ይተነፍሱታል። ጭሱ ውስጥ ያለውም ኬሚካል ሳንባቸውን ይጎዳል ፤ ያሳምማል። ይህ ህመም በአመታት ውስጥ ሲደጋጋመ የሳንባ ካንሰር/ነቀርሳ ይሆናል። የአለም ጤና ድርጅት እንደሚገልጸው ይህንን ጭስ የምትተነፍስ ሴት/እናት 400 ሲጋራዎች እንደሚያጨስ ሰው ተጋላጭነት አላት። ታድያ ኢትዮጵያ ላይ ሳንባ ካንሰር ታማሚዎች እድሜ በሲጋራ ሳንባ ካንሰር ከመጣባቸው ሰዎች ቢያንስ እንዴት ይደንቅ። 📊 አሳሳቢው እውነታ የቤት ውስጥ የአየር ብክለት በዓለም ዙሪያ በየአመቱ ከ4 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ይገድላል። ኢትዮጵያ ውስጥ በሴቶች ላይ ከሚደርሱት ስርሰደድ የሳንባ ህመሞች መካከል ፤ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በቤት ውስጥ በሚያጋጥም የአየር ብክለት የተከሰቱ ናቸው። በኢትዮጵያ ካሉ አሰር የገጠራማ ቤቶች ዘጠኙ ፤ ለኃይል ፍጆታ በዋነኝነት እንደ ከሰል ፣ ኩበትና የማገዶ እንጨት ይጠቀማሉ። ለዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሴቶች እና ህጻናት በቀን በአማካይ 3 ሰአታት ያህል ለጭስ ይጋለጣሉ። በየአመቱ ከ 50,000 እስከ 67,830 ኢትዮጵያውያን በዚህ የተነሳ ይሞታሉ። ከሌላው አለም አንጻር ኢትዮጵያ ውስጥ የሳንባ ካንሰር በጎልማሳነት እድሜ ያጋጥማል። ብዙ የኢትዮጵያውያን እናቶች ምግብ ሲያበስሉ ፤ መርዛማ ጭስ ይስባሉ። ቤተሰባቸውን ለመመገብ ፤ እራሳቸውን ለአደጋ ያጋልጣሉ። 🚨 ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምልክቶች፡ ምን ማየት ይኖርቦታል? ታድያ የሳንባ ካንሰር በአንድ ቀን የሚፈጠር ድንገተኛ ክስተት አይደሉም። ቀስበቀስ በአመታት ውስጥ የሚመጣ እንጅ። ለዚህም በመጦሪያ በማረፊያ እድሜያቸው፣ ውድ እናቶቻችን ሀኪም ቤት ይንከራተታሉ። ከዛ በፊት በነበሩት አመታት ላይ ጠቋሚ ምልክቶች ቢኖሩም ፤ ችላ ተብለው ይታለፋሉ። ጉንፋን ወይን ከእድሜ ጋር የሚመጡ ተድርገው ይታሰባሉ። እነኝህ ምልክቶች ምንድን ናቸው? የማያቋርጥ ደረቅ ሳል በቀላል ተግባራት ላይ የትንፋሽ ማጠር በተደጋጋሚ የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን የአስም አይነት ትንፋሽ ጋር ተደራቢ ድምጽ ድካም ደረትን መጭመቅ/ማፈን ሰውነት መክሳት (ክብደት መቀነስ) እነዚህ ምልክቶች ከጥቂት ሳምንታት በላይ ከቆዩ ወይም ተደጋግመው ከመጡ አይጠብቁ። ምርመራ በአፋጣኝ ያድርጉ። 💡 ታድያ ምን እናድርግ? መከላከያ መንገዶቹ ምንድን ናቸው? በተቻለ ሁኔታ የዘመናዊ የኤሌክትሪክ ምድጃን አልያም የሲሊንደር ስቶቭ (ኢታኖል እና ሜታኖል) መጠቀም። እሱ ተያይዞ የሚመጣው የኤሌክትሪክ ክፍያ እና የስቶቭ ወጪ አብዛኛው የማህበረስብ ክፍል ሊከበደው ይችላል። ይህ ካልሆነ ግን ፡ ከተቻለ ከቤት ውጭ ማብሰል። ቤት ውስጥ ካበሰሉ፣ መስኮቶች ይክፈቱ። አየር እንዲናፈስ ያድርጉ። የእናቶችን ግንዛቤ ከፍ ማድረግ። ይህንን መረጃ እርስዎም ለጎረቤቶት እና ለቤተስብዎ ያካፍሉ። ቤት ውስጥ ማብሰል ግድ ከሆነ ፤ የጭስ ማውጫ ወይም የዘመኑ (ጭስ የሚቀንሱ) ማብሰያዎችን ይጠቀሙ። እድሜ ከ 50 አመት ካለፈ በኋላ በየአመቱ የሳንባ ካንሰር ምርመራ ቢደረግ መልካም ነው። ይህ ደግሞ ለረዥም አመት በባህላዊ መንገድ ሲያበስሉ ለነበሩ እናቶች እጅጉን አስፈላጊ ነው። 💬 እናታችን እኛን ልታበላ መሞት የለባትም። ኢትዮጵያ ውስጥ እናቶቻችንን ብናከብርም ፤ ለእነሱ የምናደርገው ጥበቃ ከዚህ መጀመር አለበት። ለማገዶ የምንጠቀመው እንጨት ፤ በዝምታ እናቶቻችንን በሳንባ ካንሰር እየነጠቀን መሆኑን ማየት ይኖርብናል። 👉 እናትቶቻችን፣ እህቶቻችን ወይም ጎረቤቶቻችን በከሰል ወይም በማገዶ ሲያበስሉ ስናይ እንምከራቸው። መስኮት ይክፈቱ ፤ ሳንባ ምርመራ ያድርጉ። የነገ ጤናችን ዛሬ በምናደርገው ተግባራዊ ለውጥ የተመሰረተ ነውና ፤ ችላ አንበል።
- The Fight To End Cervical Cancer & Ethiopian Reality
The Story She Was Only 35. Selam had always been a go-getter — the first in her family to wake before sunrise, the last to go to bed, working to care for children, home, and a small coffee shop in Addis Ababa. But then came the bleeding — slight at first, and then persistent. She attributed it to stress or maybe menopause too early. What she did not know was that an unseen intruder had been growing inside of her: cervical cancer, the second most common cancer among women in Ethiopia, and one that takes more than 5,000 Ethiopian women's lives every year. But Selam's story does not have to be the fate of millions like her. For this killer, as opposed to so many others, can be prevented, treated, even eradicated. The Enemy Within: What is Cervical Cancer? Cervical cancer starts in the cervix — the tube that connects the womb and the vagina. It develops when cells there begin to grow and divide uncontrollably due to chronic infection with a common virus: the human papillomavirus (HPV). You’ve probably heard of HPV. In fact, almost everyone gets it at some point. But while most HPV infections clear on their own, some high-risk strains can linger and quietly damage cells — for years — eventually causing cancer. Globally, over 660,000 women developed cervical cancer in 2022 and 350,000 died from it — nearly 1,000 women every day. In Ethiopia alone, over 7445 women develop it yearly, and 5,318 die — many in the prime of their lives, mothers, daughters, caregivers (based on 2020 estimate). Symptoms: The Whisper Before the Storm Cervical cancer does not scream — it whispers. Most women in the early stages feel nothing. But as cancer advances, it speaks through symptoms: Unusual vaginal bleeding (during sex, between periods, or following menopause) Smelly or watery discharge Pain during sexual intercourse Pelvic or back pain Swollen legs Loss of weight and weakness These are symptoms that most people overlook. But they matter. Because when they're noticed, cancer may already be in its advanced stages. The Good News? It's Beatable. Cervical cancer is one of the only fully preventable cancers. The secrets? Vaccination. Screening. Treatment. Let's dissect it. HPV Vaccination: A Shield for the Next Generation The HPV vaccine, administered prior to girls becoming sexually active, stops cervical cancer in its tracks up to 90% of the time. And the good news? A single dose protects for life. WHO's 2030 Target: 90% of girls vaccinated by age 15 70% of women tested by 35 and 45 years 90% of treated women if tested positive In Ethiopia, the Ministry of Health immunized girls with two doses from 2018. But in 2024, it dramatically changed — adopting WHO's revised single-dose recommendation and expanding coverage among girls 9–14 years. The dividend? Over 6.8 million girls immunized in a single campaign, bringing the national total to over 13 million protected girls — an enormous public health achievement. 2. Screening: Discovering Trouble Before It Spreads Vaccination is not sufficient. For women adults who may be already exposed, screening is crucial. Ethiopia uses Visual Inspection with Acetic Acid (VIA) — an inexpensive method where vinegar is painted on the cervix and abnormal changes are looked for by nurses. It's fast, inexpensive, and available in most health centers. Objective: Screen 1 million women per year. Already, more than 1.6 million Ethiopian women have been screened at least once in a lifetime — a start, but far short of the goal. More needs to be done to reach rural women, where access is more difficult and stigma is greater. 3. Treating the Precancer, Saving the Future If lesions are caught early enough, they can be destroyed in the field using cryotherapy or heat ablation — no surgery, no hospital stay. For more advanced cases, Ethiopia is increasing the availability of chemotherapy and surgery at regional referral hospitals, though supplies remain tight. Challenges on the Battlefront Despite advances, there are challenges: Stigma and misinformation about pelvic exams and HPV Limited awareness in rural communities Lack of trained health professionals, especially in rural areas Infrastructure gaps for treatment services But maybe the greatest barrier? Silence. Too many women still don't know. And too many men aren't talking about it either — even though cervical cancer is a men's issue as well, considering HPV is a sexually transmitted infection. What Can You Do? 💉Get your daughters (and sons) vaccinated 👩⚕️Encourage sisters, mothers, wives to screen 📣 Speak out — break the silence that fuels stigma 🫂Unite with survivors and families 🧠 Learn and teach your community The Dream: Elimination is Possible WHO launched the world's first-ever global plan to eliminate a cancer. And Ethiopia is breaking the mold — with vaccines, screening, policy, and people like you. Cervical cancer will one day be something we talk about, not a sentence we live. Selam's story needn't be repeated. Let's make cervical cancer history — not her story For Further Reading Age Standardize Cervical Cancer Mortality Rate in 100,000 Cervical Cancer- WHO Human Papilloma Virus and Related Cancers, Fact sheet 2023 The human papillomavirus (HPV) single-dose schedule elevated the total number of vaccinated girls in Ethiopia to over 13 million
- አደገኛው የጉበት ቫይረስ ፡ ሔፓታይተስ ቢ
ይህ አዲስ አበባ ውስጥ ያለ አንድ ቤተሰብ ታሪክ ነው። አባት ደጋግመው 'ቀኝ ሆዴ አሞኛል' ማለት ሲያበዙ፤ ልጆች ሀሳብ ገብቷቸው የጤና ተቋም ይዘዋቸው ይሄዳሉ። ምርመራም ሲደረግ ፤ የህመማቸው ምንጭ የጉበት ጠባሳ እንዲሁም የጉብት ካንሰር እንደሆነ ይነገራቸዋል። ይህን ጊዜ ልጆች እጅጉን ይደናገጣሉ። አባታቸው ጤነኛ እንደሆኑ ነበር የሚያውቁት። ታድያ የተደናገጡት ልጆችም እርግጠኛ ለመሆን የጉበት ስፔሻሊስት ጋር ይዘዋቸው ይሄዳሉ። ስፔሻሊስቷም ካንሰሩ የደረጀ መሆኑን እንዲሁም (Hepatocellular carcinoma BCLC stage C) ፤ ደማቸው ውስጥ የሄፕታይተስ ቢ የጉበት ቫይረስ እንደሚገኝ አስረድታቸው ፤ ህክምና ክትትል ይጀምራሉ። ጉዳዩ ዱብዳ የሆነባቸው ልጆች ፤ አባታቸው መዳን የሚችልበትን መንገድ ለማወቅ ውጭ እስካሉ የህክምና ባለሙያዎች ድረስ ይሄዳሉ። ሆኖም ግን ካንሰሩ መጋቢ የደም ስርን ስለነካ ፤ ያለው የህክምና አማራጭ የተገደበ መሆኑንና ፤ ዋናው ህክምና የእገዛ ህክምና (palliative care) መሆኑን ያስረግጡላቸዋል። ታድይ ይህ ዜና ቀላል አልነበረም። ያላቸውን ቅሪት ሸጠው ሆነ ፤ የስው ፊት አይተው ፤ አንድ አባታቸውን ለማሳከም የወሰኑት ልጆች ፤ ተስፋቸው ሟጨጨ። የሚያደርጉት ግራ ገባቸው። የእገዛ ህክምና ብቻ እንደ መፍትሔነት አልዋጥ ቢላቸውም ፤ ህክምና ክትትላቸውን አጥብቀው ቀጠሉ። ባላቸው አቅም አባታቸውን ለማስታመም ቢሞክሩም ፤ እኝህ አባት ከቀን ወደ ቀን እየተዳከሙ መጡ። ምግብ አልበላ አላቸው። ከበሉም ምግብ ሆዳቸው አይረጋም። ሰውነታቸው እየመነመነ መጣ። ታድያ ድንገት አንድ ቀን በአፋቸው በኩል ደም ገንፍሎ መጣ ። ድንገተኛ ክፍል ይዘዋቸው ቢሄዱም ፤ ህይወታቸውን ግን ማዳን አልተቻለም ። ይህ የአንድ ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ቁንጽል ታሪክ ቢሆን ፤ እንዴት መልካም ነበር። የአንጀት እና ጉበት ክትትል ክፍል ለሳምንት ቢያሳልፉ ፤ ብዙ ተመሳሳይ ታሪኮችን ይሰማሉ። ዛሬ የምናነሳው ስለ ካንሰር አይደለም። ካንሰር በማምጣታቸው ከሚታወቁ ቫይረሶች መሀከል ዋነኛ ተጠቃሽ ስለሆነው ፤ ሁሉንም የሰውነታችንን ክፍል ስለሚያጠቃው ፤ ሄፓታይተስ ቢ ስለሚባለው የጉበት ቫይረስ ነው። ይህ ቫይረስ ከ ኤች አይቪ ኤድስ ጋር ተመሳሳይነት ቢኖረውም ፤ በአንዳንድ ባህሪው ከ ኤች አይ ቪ ኤድስ ይብሳል። መልካሙ ነገር ግን ክትባት አለው። ሄፓታይተስ ቢ ቫይረስ በኢትዮጵያ የጉበት ቫይረስ በኤሌክትሮን ማይክሮስኮፕ ሲታይ ሀገራችን ኢትዮጵያ ይህ የጉበት ቫይረስ ስርጭታቸው ከፍተኛ ከሆኑ ሀገራት ውስጥ ትመደባለች። ቫይረሱ ከ 8 እስከ 12 ፐርሰንት የማህበረሰቡን ክፍል እንደሚያጠቃ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ ማለት በትንሹ አስር ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ይህ የጉበት ቫይረስ አለባቸው። ባብዛኞቹ የተያዙት በህጻንነት እድሜያቸው ቫይረሱ ካለበት የቤተሰብ አባል መሆኑ ፤ አሳዛኝ ያደርገዋል። ለዚህም የጎልማሳ እድሜ ላይ ሲደርሱ ፤ ቫይረሱ ከባድ የጉበት ጥቃት ያደርሳል። ቫይረሱ የጉበት ጠባሳ (cirrhosis) ለማምጣት እስከ 20 አመት ፤ እንዲሁም የጉበት ካንሰር (hepatocellular carcinoma (HCC) ) ለማምጣት እሰክ 30 አመት የሚፈጅበት ቢሆንም ፤ ብዙ ታካሚዎች ሲመረመሩ ጉበታቸው የከፋ ጉዳት ደረጃ ደርሶበት ይገኛል። ቀድሞ የህክምና ምርመራ ተደርጎ ቢሆን ፤ ጉበት ጠንካራ ጉዳት ሳይደርስበት መቆጣጠር ይቻል ነበር። እኝህ ባለታሪክ አባት ከአመታት በፊት ጉበታቸውን ተመርምረው ቢሆን ፤ የህይወታቸውን አቅጣጫ እንዴት መለወጥ ይቻል ነበር? ⚠️ የ ህመሙ ምልክቶች ይህ ህመም ጉበት ላይ ጠንካራ ጉዳት እስኪያደርስ ድረስ ፤ ፈጽሞ ምልክት ላያሳይ ይችላል ። በሽታው ሲጀምር የሚያሳያቸው ምልክቶች ፤ እንደ ተራ ኢንፌክሽን ችላ ተብለው ሊታለፉ ይችላሉ። ህመሙ የጀመረ ሰሞን የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያሳይ ይችላል። ድካም የምግብ ፍላጎት መቀነስ ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ ህመሙ ሲጀመር ጠንካራ ከሆነ የሚከተሉት ሊስተዋሉ ይችላሉ። የሆድ ህመም ሽንት መጥቆር ቆዳ እና አይን ቢጫ መሆን ለረዥም ጊዜ ቫይረሱ ሰውነታችን ውስጥ ቆይቶ ጉበታችንን ሲያቆስል ደግሞ ፤ እንደደረሰው የጉዳት መጠን የተለያዩ ተጨማሪ ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ። የሆድ እና የእግሮች እብጠት (እነኝህ ምልክቶች መታየት ሲጀምሩ ፤ በተለምዶ የወፍ በሽታ ተብሎ ይጠራል) ምግብ ፍላጎት ፈጽሞ መጥፋት ደም ማስታወክ የሰገራ መንጣት የባህሪ መለወጥ ወደ ካንሰር ከተለወጠ ካንሰሩ እንደተሰራጨበት አካል ምልክቶቹ ይለያያል ጉዳቱ ጠንካራ ከሆነ ጉበት እጅጉን ይደክማል ፣ ጭንቅላትን አጥቅቶ ባህሪ ይለውጣል፣ ኩላሊት ድካምም ሊያመጣ ይችላል። ⚠️ መተላለፊያ መንገዶቹ የጉበት ቫይረስ በዋነኝነት የሚተላለፈው ፤ ከታመመ ሰው የወጣ የሰውነት ፈሳሽ ንክኪ ሲኖር ነው። ለዚህ የሚያጋልጡ ማንኛዎም አይነት ድርጊቶች ሆኑ ባህሪያት ፤ ለበሽታው የመጋለጥ እድልን ይጨምራሉ። እነኝህም፡ ከ አንድ በላይ ሰው ጋር የ ፍቅር ግንኙነት መኖር ክታመመ ሰው ጋር ግብረ ስጋ ግንኝነት መኖር ከታመመ ሰው ጋር ስለት ያላቸው እቃዎችን በመጋራት በስርአቱ ያልተመረመረ ደምን መቀበል በቀዶ ጥገና ወቅትም (ይህ ደግሞ በዋነኝነት ጤና ባለሙያዎችን ይመለከታል) እናት ቫይረሱ ካለባት ፤ በወሊድ ጊዜ በሚኖር የደም እና የሰውነት ፈሳሽ ንክኪ ሊተላለፍ ይችላል። ስቴራላይዝ ባልተደረጉ መገልገያዎች ድድን መነቀስ፣ ጆሮን መበሳትና ንቅሳት መነቀስ አሳዛኙ እውነታ ! ብዙ የቫይረሱ ተጠቂዎች መሉ በሙሉ ጤናማ እንደሆኑ ስለሚሰማቸው ፤ ሳያውቁ ያሰራጫሉ ። 🛡️ መከላከያ መንገዶች ክትባት ቫይረሱን መከላከል የሚያስችል ክትባት አለው። ክትባት መውሰድ ይኖርብዎታል። እንደ ፈረንጆች ከ 2007 ዓ.ም ጀምሮ የጨቅላ ህጻናት ክትባት ጋር ተደባልቆ ስለሚሰጥ ተጋላጭነቱ ከፍተኛ የሆነው ከዛ በፊት ለተወለዱ ግለሰቦች ነው። ስለዚህም ልጅዎን ክትባት ያስከትቡ። እርስዎም ክትባት ከጀመሩ ፤ አንድ ክትባት ብቻ በቂ አይደለም። ሙሉ ክትባት ይውሰዱ። ክትባቱን አሟልተው ከወሰዱ ፤ ከአስር አመት በኋላ የደም ምርመራ ያድርጉ። የቫይረሱ መከላከያ መጠን ከተመናመነ ፤ ማጠናከሪያ ክትባት መከተብ ይኖርቦታል። ከክትባት ባሻገርስ እላይ ከተጠቀሱት አደገኛ ባህሪያት እራስዎን ይጠብቁ። በግብረ ስጋ ግንኙነት ጊዜ ኮንዶም ይጠቀሙ። ስለት ያለው መገልገያ እቃ አይጋሩ። ድድዎን ሲነቀሱ፣ ጆሮ ሲበሱ እንዲሁም ንቅሳት ሲነቀሱ ይጠንቀቁ። የሚነቀሱበት ስፍራ ህክምናዊ ጥንቃቄ (እቃዎቹን ስቴራላይዝ) እንደሚደርግ ያረጋግጡ ። ካልሆነ ለጤናዎ ቅድሚያ ይስጡ። ቫይረሱ ያለባቸው ነፍሰ ጡር እናቶች ከወሊድ በኋላ ባሉ 3 ቀናት ውስጥ ፤ ለልጆቻቸው የ ቫይረሱን መቃወምያ መሰጠት ይኖርባቸዋል። ታመው እስኪሄድ አይጠብቁ። በመደብኛ ሁኔታ ጉበትዎን ይመርመሩ። ስለቫይረሱ የተሟላ ግንዛቤ ይኑርዎ። 💊 ቫይረሱ ካለብዎስ ምን ያድርጉ? በሕክምና ለቫይረሱ ፈውስ ባይኖረውም ፤ ቫይረሱን ተከትሎ የሚመጣ ጉዳትን መቆጣጠር ይቻላል። ስለዚህም ከጉበት ስፔሻሊስት ጋር ተነጋግረው ፤ የፀረ-ቫይረስ መድሐኒቶችን ይውሰዱ። ምንም ቢሆን ቀድም ህክምና ለመጀመር አያመንቱ። ማመንታቶት ዋጋ ያስከፍልቶታል። ወደሌላ ሰው እንዳያስተላልፉ ይጠንቀቁ። በተለይ የዚህ አንደኛ ተጠቂ ቤተሰብዎ ናቸውና ያስከትቧቸው። የቅድሙ ባለታሪክ ልጆችስ እጣ ፈንታ ምን ይሆን? ተከትበው ይሆን!? ያስተውሉ በተግባራዊ ለውጥ የእርሶንም የቤተሰቦንም ጤና መጠበቅ ይችላሉ። አያመንቱ! ይከተቡ! ጤናዎን ይምረጡ!
- የኩላሊት ጠጠር መንስኤዎች እና መከላከያ መንገዶች
አንድ ቀን ከጓደኞችዎ ጋር ወጥተው እየተዝናኑ ነው እንበል ፤ ድንገት ከባድ የሆነ የሚሰነጥቅ ቁርጠት/ ውጋት ከእንብርትዎ በታች ያለውን ሆድዎን ቢያናውጠውስ? ይህ ዱብዳ የሆነ ህመም የማያስቆም የማያስቀምጥ እጅጉን ጠንካራ ቢሆንስ? እርስዎንም በዙሪያዎ ያሉትንም እንዴት ይረብሽ? ምንም ያጋጠምዎ አደጋ የለም። የበሉትም ምግብም አይደለም። የሚያሰቃይ ህመም ብቻ! ይህ ህመም የኩላሊት ጠጠር ህመም ሊሆን ይችላል። ህመሙ ያጋጠመበት ስፍራ ይለያይ እንጂ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ቀናቸውን አቅውሷል፣ እንቅልፍ አሳጥቷል ፣ሰላማቸውን ነፍጓል። እንደ አሴረ ጠላት ህመሙ በሽምቅ ነው የሚያጠቃው። ያልታሰበ ጊዜ ፣ ያልታሰበ ስአት ድንገት ለመግለጽ የሚያዳግት ህመም። ሲሸኑ ያለውን ህመም ፍራቻም ሽንትቤት መሄድ የጠሉም አይጠፉም። 🧊 ታዲያ የኩላሊት ጠጠር ምንድነው? የኩላሊት ጠጠር ስሙ እንደሚያመላክተው ኩላሊት ውስጥ የተገኘ ጠጠር የሚያመጣው ህመም ነው። ታድያ ይህ ጠጠር ከየት መጣ? ኩላሊት ጠጠር ኩላሊት ውስጥ የተከማቹ ማዕድናት፣ጨዎች እና አንዳንድ ንጥረ ነገሮች ፤ በጊዜ ብዛት የሚሰሯቸው ጥቃቅን ጠጠሮች ናቸው። አሸዋ ማህል እንደምናገኛችው ደቃቅ አንጸባራቂ ጠጠሮች አርገው መውሰድ ይችላሉ። ብዙ ጊዜ እነኚህ ጥቃቅን ጠጠሮች የሚሰሩት በ ካልሺየም ኦክሳሌት ፣ ዩሪክ አሲድ እና ስትሩቫይት በሚባሉ ውህዶች ነው። ጥቃቅንነታቸው አያታልዎ። ህመማቸው ግን ፈጽሞ እንደጥቃቅንነታቸው አይደለም። እንደ አሸዋ የላሙ ወይም እንደ ድንጋይ አንኳር ቢያክሉም እንኳን ፤ በጠባቡ የ ሽንት ቱቦ (ureter) ከሽንት ጋር ተደባልቀው ሲያልፉ ፤ እጅጉን ከባድ ህመም ያመጣሉ። ህመሙም እነኝህ ጠጠሮች ጠባቡን የሽንት ቱቦ ሲዘጉት ፤ ሰውነታችን እነሱን ገፍቶ ለማሳለፍ በሚያደርገው ጥረት የሚፈጠር ነው። የዚህ ጥረት ውጤት ግን እጅጉን ከባድ ህመም ነው። ህመሙ የሰው ልጅ ከሚያጋጥማቸው ከባድ ህመሞች ተርታ የሚመደብ ነው። ታድያ ምልክቶቹ ምንድን ናቸው? ከኩላሊት ጠጠር ምልክቶች በጥቂቶቹ ከባድ ቅጽበታዊ የመቁረጥ/የመውጋት ህመም ይሰማናል። ህመሙ በዋነኝነት የሚሰማው ከ እንብርታችን በታች ባለው ሆዳችን ክፍል በተለይም በጎን አከባቢ ነው። ይህ ህመም የታችኛው ጀርባችን ላይም ሊሰማ ይችላል። ህመሙ በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ ፤ ሊያቅለሸልሽ እንዲሁም ትውከት ሊያመጣ ይችላል። ሽንት ቶሎ ቶሎ የመምጣት ፍላጎት ሊኖር ይችላል። ሽንት ሲሸኑ ከባድ ህመም ሊኖር ይችላል። ሽንት ደም ሊቀላቅል ይችላል። አንዳንዴም አሸዋ መሳይ ጠጠሮች ተደባልቀው ሊወጡ አልያም ሽንት አፈር ሊመስል ይችላል። ተጨማሪ ኢንፌክሽን ካለ ሽንት አመዳማ መልክ ሊኖረው ወይም ሽታው ሊተነፍግ ይችላል። ታድያ እነኝህ ምልክቶች ከተሰማዎ አስኪሻልዎ አይጠብቁ። በቅርብዎ ያለ የጤና ተቋም ሄደው ህክምናን ያድርጉ። ትናንሾቹ ጠጠሮች በራሳቸው ሊወጡ ሲችሉ ትላልቆቹ ግን ህክምና ያስፈልጋቸዋል። እንዳሉበት ቦታ እና ሁኔታ በሰርጀሪ ወይም በሚያደቅ ሞገድ (ECSWT) ሊታከሙ ይችላሉ። 🩺 የኩላሊት ጠጠር ለምን ይከሰታል? እነኝህ ጠጠሮች የሚከስቱት ፤ ኩላሊት ውስጥ የሚከማች የማእድናት፣ የጨዎች እና የ ሌሎች ንጥረነገሮች/ውህዶች ዝቃጭ ሲበዛ ነው። ይህ በተፈጥሮ ኩላሊት ሊያስወግደው የሚችል ቢሆንም ፤ ሰውነታችን የሚያስወግድበት አቅም በተለያየ ምክንያት ሲሰናከል ኩላሊት ጠጠር ያመጣል። በኢትዮጵያ ውስጥም የኩላሊት ጠጠርን እያመጡ ያሉ ዋነኛ መንስኤዎች የሚከተሉት ናቸው። ✅ የውሀ እጥረት ዋነኛ መንስኤ ነው። ሞቃታማ ክልሎች ላይ የሚኖሩ ሰዎች ብዙ የጉልበት ስራ የሚሰሩ ሰዎች ፣ እንዲሁም የሚጠጡት የውሀ መጠን ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎች ሰውነታቸው ውስጥ ያለው የውሀ መጠን ስለሚመናመን ፤ ኩላሊታቸው ውስጥ የሚከማቸውን ዝቃጭ ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ይቸገራሉ። ይህም ደግሞ ጠጠሮቹ እንዲፈጠሩ መሰረት ይጥላል። እርስዎስ በቀን ምን ያህል ሊትር ውሀ ይጠጣሉ? ✅ ከፍተኛ የፕሮቲን መጠን ያላቸውን ምግቦች መመገብም ይህን ጠጠር ያመጣል። በጣሙን ስጋ ተመጋቢ ማህበረሰብ እንደመሆናችን ፤ አመጋገባችን የኩላሊት ጠጠር ዋነኛ መንስኤዎች ውስጥ ይጠቀሳል። ብዙ ስጋ ስንመገብ ሰውነታችን ውስጥ የ ዩሪክ አሲድ መጠን ይጨምራል። ይህም ኩላሊት ላይ ክምችቱ ሲበዛ የኩላሊት ጠጠር ያመጣል። ✅ጨው የበዛበት ምግብ ስንመገብ ፤ በሽንት በኩል የምናወጣውን የካልሺየም ማዕድን እንዲጨምር ይሆናል። ይህ ደግሞ ከሌሎች ንጥረ ነገሮች ጋር እየተደባለቀ ጠጠር ይሰራል። ✅ ከዚህም ባሻገር ቸኮሌት አብዝተን ስንመገብ፣ ልውዝ፣ ስፒናች፣ ቀይስር አይነት በኦክሳሌት (oxalate) ንጥረነገር የበለጸጉ ምግቦችን ስናዘወትር ለኩላሊት ጠጠር የመጋለጥ እድላችን ይጨምራል። ✅ ከእነኝህም በተጨማሪ የቤተሰብ ታሪክ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት እና ኢንፌክሽኖች እንደ መንስኤ ይጠቀሳሉ። 💡 የኩላሊት ጠጠርን መከላከል ይቻላል? አዎ! በደንብ። ከላይ እንደተመለከቷቸው የኩላሊት ጠጠር አምጪ መንስኤዎች አብዛኞቹን መከላከል ይቻላል። ምን ያድርጉ መሰልዎ 1. ዉሀ በበቂ መጠን በየቀኑ ይጠጡ። ሽንትዎ መጥቆር ወይም በጣም ቢጫ ከሆነ ፤ የውሀ መጠንዎ ቀንሷል ማለት ነው ስለዚህ ውሀ ይጠጡ። በትንሹ ከ2.5 እስከ 3 ሊትር ውሀ እንዲጠጡ ይመከራል። አመጋገብዎ ላይ የጨው እና የ ስጋ መጠንን ይገድቡ። በኦክሳሌት ንጥረ ነገር የበለጸጉ ምግቦችን (ቸኮሌት፣ ለውዝ፣ ቀይስር፣ ወ.ዘ.ተ) አያዘውትሩ ጤናማ ክብደትን ለመጠበቅ አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ። ህመም ምልክት እስኪያጋጥምዎ አይጠብቁ። በየተወሰነ ጊዜ መደበኛ ምርመራን ያድርጉ። መቼም ቢሆን ለመከላከል አይስነፉ! ያልታከመ ኩላሊት ጠጠር ለኩላሊት ድክመት እንደሚያጋልጥ ይወቁ። 🔚 የተግባር ጥሪ አሁን ምክንያቱን አውቀዋል። ምልክቶቹን ተረድተዋል። መከላከያ መንገዶቹንም ተገንዝበዋል። የሚቀረው ብቸኛ ነገር የእርሶ ተግባር ነው። 👉እስኪያምዎ አይጠብቁ በተግባራዊ ለውጥ ጤናዎን ይጠብቁ።
- 🌿 ሺ ህመም የሚፈራው ቅጠል - ሽፈራው
ሽፈራው ቅጠል ወስደው ያውቃሉ ? ስለ ጤና ጠቀሜታውስ በጥልቅ ያውቃሉ? ከደም ግፊት ባሻገር ለስኳር ህመምስ ያለውን ጠቀሜታ? ከኢትዮጵያ ቆላ መሬት ጀምሮ እስከ ሂማልያ ተራሮች ግርጌ ባሉ ሀገራት ድረስ ይህ ተክል በደንብ ይታወቃል። በእንግሊዘኛ ስሙ ሞሪንጋ በአማርኛ ሽፈራው ተብሎ ይጠራል። ለዘመናት በአፍሪካ፣ በእስያ እና በመካከለኛው ምስራቅ ባሉ ሀገራት ባህል ህክምና ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል። አይዩሪቪዲክ ሜድሰን በመባል የሚታወቀው የህንድ የባህላዊ ህክምና ውስጥም ከ300 በላይ በሽታዎችን እንደሚያክም ይነገራል። በአፍሪካ ስነ እጽዋት እውቀት ደግሞ ፤ ይህ ቅጠል ኢንፌክሽኖችን ፣ የተለያዩ እብጠቶችን ለማከም ግልጋሎት ሲውል ቆይቷል። ነገር ግን የሽፈራው ቅጠል ጠቀሜታ በታሪክ እና በባህላዊ ህክምና ውስጥ ብቻ ተቀብሮ የቆየ አይደለም። በቅርብ አመታት የዘመናዊ ህክምና ትኩረትን ስለሳበ በቅጠሉ ዙሪያ ብዙ ጥናቶች/ ምርምሮች ተደርገዋል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሞሪንጋ በቫይታሚን ሲ፣ ካልሲየም፣ ፖታሲየም እና ፕሮቲን የበለፀገ ከመሆኑ ባሻገር የአንቲ አክሲዳንት ባህሪ ያላቸው ንጥረ ነገሮች (እንደ quercetin እና chlorogenic አሲድ) አሉት። በዚህም የተነሳ ጤና ላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ሊኖረው ችሏል። የጤና ጠቀሜታው ይህ ተክል ጤና ላይ ባለው ጠቀሜታ "ተአምረኛው ዛፍ” ወይም “የሕይወት ዛፍ” የሚል ተቀጽላ ስያሜ ተሰጥቶታል። ዋና ዋና የጤና ጠቀሜታዎቹ የሚከተሉት ናቸው። 🌱 የላቀ የንጥረ ነገር ስብስብ አለው። የሽፈራው ቅጠሎች በውስጣቸው የሚከተሉት ንጥረ ነገሮች አሏቸው፡- • ቫይታሚን፡ የሰውነታችንን የበሽታ መከላከል አቅም የሚያጎለብቱና የቆዳ ጤንነትን የሚደግፉ በሆኑት በቫይታሚን ኤ፣ ቫይታሚን ሲ እና ቫይታሚን ኢ የበለፀገ ነው። • ማዕድን፡ ከፍተኛ የካልሲየም፣ የፖታስየም እና የብረት መጠን ስላለው ፤ የአጥንት ጤናን ከመደገፍ ባሻገር ፤ የደም ግፊትን ለመቆጣጠር ያግዛል። • ፕሮቲኖች፡- ዋነኛ የሚባሉት አስፈላጊ ዘጠኙን አሚኖ አሲዶች አሟልቶ በውስጡ የያዘ በመሆኑ ፤ ከእጽዋት የተቀመመ ተመራጭ የፕሮቲን ምንጭ ያደርገዋል። እነኝህ ንጥረ ነገሮች ስላሉት ፤ ጤናን ይደግፋል፣ የኃይል መጠን ይጨምራል፣ እና የበሽታ መከላከያ አቅምን ያጎለብታል። 💖 የልብ እና ደምስር ጤናን ይጠብቃል ። የሽፈራው ውስጡ አንቲኦክሲዳንት ባህሪያት ያላቸው ንጥረ ነገሮች ስላሉት ፤ የኮሌስትሮል መጠንን ይቀንሳል። ይህም ኮሌስትሮል በደም ወሳጅ ቧንቧዎች ላይ እንዳይከማች ለመከላከል ይረዳል። ከዚህም ባሻገር ሰውነታችን እንዳይቆጣ ስለሚያደርግ (anti-inflammatory) ፤ የደም ግፊትን ቁጥጥርን ያሻሽላል እንዲሁም የልብን ጤናን ይደግፋል። 🩸 የደም ስኳር ቁጥጥር ያሻሽላል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሽፈራው በደም ውስጥ ያለውን የደም ላይ ያለ የስኳር መጠን ስለሚቀንስ ስኳር በሽታ ላለባቸው እንዲሁም ለስኳር ተጋላጭነት ላለባቸው ሰዎች ጠቀሜታ አለው። ውስጡ ያሉት ንጥረነገሮች ለኢንሱሊን ሰውነታችን ያለውን ምላሽ (insulin sensitivity) ያሻሽላሉ። እንዲሁም ከአንጀት ውስጥ ወደ ደም የሚገባውን የግሉኮስ መጠን ይቀንሳሉ። ይህም የስኳር ቁጥጥርን እጅጉን ያግዛል። 🧠 የአዕምሮ ደህንነትን ይጠብቃል። ሽፈራው ከ ፀረ-ኦክሲዳንት ባሻገር ፤ ነርቮቻችንን የሚጠብቁ ንጥረ ነገሮች በውስጡ ስላሉ የአዕምሮ ጤናን ያግዛል። ለዚህም ስሜታችንን ፣ የማስታወስ ችሎታችንን እና አስተሳሰባችንን ያሻሽላል ። ከዚህም አልፎ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ድብርት እና ጭንቀትንም ይቆጣጠራል። 🛡️ የበሽታ መከላከያ ስርዓትን ይደግፋል። እላይ በተዘረዘሩት ንጥረነገሮች የተነሳ ፤ ሽፈራው የሰውነታችን የበሽታ የመከላከል አቅምን የበለጠ ያጠናክራል። ባክቴሪያን ስለሚቃወም ፤ እንዲሁም ሰውነታችን እንዳይቆጣ ስለሚከላከል ፤ ስውነታችን በሽታ አምጪ ተህዋሳትን የሚቃወምበትን አቅም ያበረታል። 🌿 ሽፈራውን ወደ አመጋገብዎ እንዴት ማካተት ይችላሉ። አድርቀው ከፈጩት በኋላ ፤ ዱቄቱን በ ሻይ ሾርባ እና ጁሶች ውስጥ መደባለቅ ይችላሉ። አንዳንድ እንደ መድሀኒት የተዘጋጁ ፤ የሽፈራው እንክብሎችን መውሰድ ይችላሉ። እንዲሁም ቅጠሉን በማብሰል፣ በማፍላት፣ እንደሰላጣም በማድረግ መጠቀም ይችላሉ። ታድያ ግን ሽፈራውን ሲወስዱ ፤ ሰውነትዎት ከቅጠሉ ጋር መስማማቱን ለማስተዋል እንዲቻልዎ ፤ በአንድ ጊዜ ብዙ በመውሰድ አይጀምሩ። በመጠኑ እያደረጉ ደጋግመው ይውሰዱ። ያስተውሉ ይህ የህክምና መተኪያ አይደለም። የሚወስዱትን መድሀኒት ቅያሪም አይደለም። ይህ የእርሶን ጤና መደገፊያ ፣ ህክምናዎን ማገዣ ነው። የሚወስዱትን መድሀኒት ለማቆምም ዶክተርዎን ያማክሩ። ማጠቃለያ ሽፈራው በአያቶቻችን ጥበብ ላይ የተመሠረተ ፤ በዘመናዊ ሳይንስ የተረጋገጠ ፤ ጠቀሜታ ያለው ተአምረኛ ቅጠል ነው። እንዳሻዎት አድርገው ሊመገቡት የሚችሉት ፤ ትልቅ የጤና ጥቅም ያለው ተክል ነው። ስለዚህ በሚቀጥለው ጊዜ በሽፈራው ዛፍ አጠገብ ሲያልፉ ፤ ያለውን የላቀ የጤና ጠቀሜታ ያስታውሱ።
- Can a Text Message Save a Mother's Life? An Exploration of Mobile Health in Ethiopia
"Sometimes, the most powerful intervention isn't a surgery, a medicine, or even a doctor. Sometimes, it's a single message—delivered at the right moment, to the right woman, in the right place." Imagine a mother in the Ethiopian highlands holding her gravid abdomen. She has not attended her last two antenatal appointments. Amidst all her chores and responsibilities, she shouldered, she forgot again. She cares truly, yet her clinic is far away, transport is unsafe, and the days blur into each other in chores, childcare, and survival. Then, picture this same mother receives a text message: "Reminder: You have a health check-up this Friday. The doctor shall be waiting for you." She nods, making a plan to go to the hospital the next day. And that small nudge—only ten words—may be the difference between death and life. This isn’t a far-fetched story. It’s a glimpse into the quiet revolution transforming maternal healthcare in Ethiopia and beyond. It’s called mobile health, or mHealth, and it is slowly proving that technology doesn’t have to be loud to be life-saving. The Struggle Behind the Statistics Ethiopia has made major strides in maternal health over the past two decades. But the numbers still whisper tragedy. Just 43% of women receive the recommended four or more antenatal care visits According to the 2019 Ethiopian Mini Demographic and Health Survey. Fifty percent give birth with a skilled birth attendant. Only one-third of mothers (34%) receive postnatal care (PNC). These aren't statistics. These are testimonies of mothers giving birth without anyone to turn to, of lost babies, of undiagnosed complications. Behind each statistic is a woman who may not have known when to leave, how to arrive, or why it was so important. Distance, deprivation, and health system gaps remain in the way of too many mothers. Women residing nearer to a health facility—30 minutes or less—are more than twice as likely to have maternal health services as those two hours or more away. Urban-rural inequalities, poor infrastructure, and ineffective health information flow widen the gap. And that's where digital health comes in quietly. The Power of a Ping Across the country, cell phones are becoming more common, even in rural areas. In urban centers like Addis Ababa, all individuals have a phone, and digital tools are being used for banking, texting, and daily chores. Why not save lives too? mHealth uses simple technology—SMS reminders, mobile apps, and electronic records—to connect women with care. And it's working. Take, for instance, Northwest Ethiopia, where digitizing health records in communities tripled the number of women receiving the full continuum of maternal care. It increased from 10.6% to 32.5%. That means more mothers accessing ANC, delivering to professionals, and returning for PNC. A review of middle- and low-income countries discovered that mHealth interventions improve children's immunization and antenatal attendance rates. And in Ethiopia, technology like the Electronic Community Health Information System (eCHIS) is being rolled out to allow health workers to track pregnancy, warn of danger signs, and trace away missing mothers. In centres like St. Paul's in Addis Ababa, reminders by SMS & call have recently been introduced to remind pregnant women to return for their ANC visits, deliver in facilities, and return for follow-up. These messages are short, simple, and culturally tailored. They don't replace doctors. They help them. And perhaps most importantly, they reach women where they are—at their convenience, in their control, in their own hands. A Cost-Effective Lifeline We typically conceptualize innovation as being expensive. But a carefully constructed SMS reminder program is less than one dollar per user in the majority of settings. Compared to the expense of emergency obstetric care—or the psychological cost of a lost mother or infant—this is one of the cheapest tools in our arsenal. In the Amhara region, health workers using a mobile-based maternal and child health program not only considered it acceptable and feasible, but life-changing in terms of delivery of services. These technologies remind, record, and respond—so no mother gets lost in the cracks of the system. Beyond the Text: A Change in Thinking The best thing about mHealth is not so much the messages, but the shift in thinking. It says: "You are not forgotten. Your life matters. And we will reach out to you before it's too late." It gives health workers better data. It gives women a voice, a schedule, and a plan. And it puts public health outside of the clinic and into the community—into her hands. Can a Text Message Save a Life? Maybe not single-handedly, but it can send a mother off, prepare a midwife, make a father stand by, and connect the dots in a system that too often leaves women behind. In a country where o ne in four women still receives no ANC , and where maternal death remains at 267 per 100,000 live births , all help is needed. And sometimes, the smallest gesture is a message. Sent. Received. Applied. That is the soft power of mobile health. That is the message that Ethiopia is beginning to send—not just with phones, but with hope. Resources Determinants of optimal antenatal care visit among pregnant women in Ethiopia: a multilevel analysis of Ethiopian mini demographic health survey 2019 data | Reproductive Health Digitalizing the community health information system improved women’s retention on the maternal continuum of care pathway in northwest Ethiopia: A quasi-experimental study | PLOS One Impact of mHealth interventions on maternal, newborn, and child health from conception to 24 months postpartum in low- and middle-income countries: a systematic review | BMC Medicine Electronic maternal and child health application usability, feasibility and acceptability among healthcare providers in Amhara region, Ethiopia | PLOS Digital Health
- የተስፈኛ እናት ፍርሀት ፡ የኦቲዝም ጉዞ በኢትዮጵያ
የተስፈኛዋ እናት ታሪክ (ከእወነተኛ ታሪክ የተቀነጨበ) አንድ ጸጥ ረጭ ያለ ሰፈር መሐል ከሚገኝ ክሊኒክ ውስጥ፤ አንድ እናት የነርቭ ሐኪም መግባቱን ትጠባበቃለች። ሐኪሙ ከተባለው ሰአት በመቆየቱ፤ አይኖቿ መንከራተት ጀመሩ። ልጇን አሞባት ነበር የመጣችው። እሷማ አላመመውም ብላ ብትደመድምም፤ የቅርብ የጤና ባለሙያ የሆነች ጓደኛዋ ስለመከረቻት ነበር የመጣችው። አላስቻላትም... ተነስታ መንጎራደድ ጀመረች። ዶክተሩ መጣ ... ደስ አላት። ካርድ አውጥታ ፤ ልጇን ስታከንፍ ይዛው ገባች። ህመሙን የሚያሳዩ የቪድዮ ምስሎች ቀድታ ስለነበር ለዶክተሩ አሳየችው። እሱም በደንብ ከመረመረው በኋላ ፤ ሞተር ስቴሮታይፕ (motor stereotype) እንደሚባል ከ እድገት ችግሮች በተለይም ከ ኦቲዝም ጋር እንደሚያያዝ ገለጸላት። ይሄኔ ፊቷ ከሰለ። የዶክተሩ ምክር ምኑም ደስ አላላትም ... ለዚህም አጥብቃ ተቃወመችው። ብዙም ሳታወራው ፤ ትእዛዙን ይዛ ፤ ምክሩን እዛው አፍስሳ ፤ ወጣች። ልቧ እየተረበሸ ወደቤት አመራች። ውስጧ ያቃጫላል "ኦቲዝም?! ዳግመኛ?! ሆሆ!" ይህች ሴት የሁለት ወንድ ልጆች እናት ናት። ፍልቅልቁ ትልቁ ልጇ ገና በጨቅላነቱ ነበር ምልክቶችን ያሳየው። ንግግሩ ከእድሜ እኩዮቹ እኩል አልጎለበተም ። ከቋንቋ ችግርም ባሻገር ፤ ከእድሜ እኩዮቹ ጋር ሮጦ አይጫወትም ነበር። መካከለኛ የሆነ የመማር ችግር ስለነበረበት ፤ እሱን ለማስተማር ያልገለበጠችው ድንጋይ አልነበረም። አታወራውም እንጂ ብዙ ለፍታለች። ኢትዮጵያ የ ልዩ እገዛ (special need) ትምህርት ቤቶች በብዛት ስለሌሉ ፤ የተለየ አስትምህሮት ያለው ልጅ መኖር እጅጉን ከባድ ነው። በዚህ ጭንቅ ውስጥ ሳለች አንድ አዲስ አበባ የሚገኝ ት/ቤት ታስገባዋለች። ትምህርትቤቱም መደበኛ ትምህርት ቤት ስለነበር ፤ መማሩ እና መታገዙ ቀርቶ ምልክቶች ባሱበት። እሱን መከታተልና ማስተማር ስለተቸገሩ ፤ ትምህርትቤቱም እንድታስወጣው ነገሯት። አስወጥታው እቤቷ ክትትል ስታደርግለት ፤ ከትምህርትቤቱ የተሻለ ለውጥ አገኘችለት። ታድያ ግን ይህ ዘላቂ መፍትሔ ባለመሆኑ ፤ ይህች እናት ግራ ተጋባች። በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተውጣ ሳለ ፤ አንድ ከመደበኛ ተማሪዎች ጋር ልዩ እገዛ የሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች ያሉበት ት/ቤት አገኘች። ትምህርት ቤቶች ለመውሰድ የሚያመነቱትን ልጇን ፤ በፈቃደኝነት የሚቀበል ማግኘቷ ለሷ እረፍት ነበር። ከህክምና ክትትሉ ጋር ተጨምሮ ትምህርቱን ሲከታተል ፤ ልጇ እጁጉን ደስ የሚል ለውጥ አሳየ። ደስ አላት! ተማረላት! ከእኩዮቹ ጋር ሲጋፋ ማየት ለሷ ተራ አልነበረምና ይቺ እናት ልቧ አረፈ። ታድያ በዚህ ደስታ ላይ እያለች የሚከታተለውም ዶክተር ለውጡ አመርቂ ስለሆነ ከዚህ በኋላ ክትትል እንደማያስፈልጋው ነገራት ። ደስታዋ ወደር አጣ። ተሽሎታል ብላ አሰበች። ቢሆንም የሚማርበት ትምህርት ቤት ግን እንደመደበኛ ተማሪ ሊቀበለው አልቻለም። እሷ በምታውቀው መጠን ብትገልጽላችውም ፤ ስለህመሙ በተረዱት መጠን ሀሳቧን አልተቀበሉትም። በልዩ እገዛ እየተማረ ይቀጥላል ብለዋት ፤ ክርክር ላይ ነች። የልጇን መዳን ልታውጅ እየታገለች ሳለች ፤ እንዴት አንቀበልም ይሏታል? አናደዳት! የ እናት ሆድ አይችልምና ከፋት። በዚህ መሀል ሳለች ችላ እያለች የምታልፈው የሁለተኛ ልጇ ለየት ያሉ ባህሪያት እና እንቅስቃሴዎችን ለጤና ባለሙያ ጓደኛዋ ያሳየቻት። እሷም ህክምና ክትትል እንደሚያስፈልገው ስለመከረቻት ፤ ወደ ቅድሙ ክሊኒክ ይዛው ሄደች። ይህኛው ልጇ እኮ ከታላቁ ጋር የሚመሳሰል ምልክቶችን ማሳየት ከጀመረ ቆይቷል። ልታስተውለው ፈጽሞ አልፈለገችም። ይሄኛውም ተመሳሳይ ህመም አለበት ብላ ማመን አልቻለችም። ድንገት የባህሪ ለውጥ ካሳየ ፤ ሰውነቱን ለየት ያለ እንቅስቃሴ ካደረገ ትቆጣዋለች። ትገስጸዋለች። በውስጧ የምትፈራው አንድ እውነታ ነበር። ይህም እንደታላቁ አሞት ቢሆንስ? ሁለቱም ልጆቿ !? ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነው! ታድያ የዶክተሩ ምክር የልቧን ፍርሀት አረጋገጠላት። ልትቀበለው አልፈቀደችም። "ዶክተሮች ይሳሳታሉ። ይሄም ተሳስቶ ነው።" አለች። ማዘዣ ወረቀቱን ይዛ ወጣች። መልሳ መላልሳ "ሊሆን አይችልም" ትላለች። ሀሳቧን የሚደግፍ ምክር ብቻ ነው የምትፈልገው። በመጀመሪያ ልጇ ብዙ አይታለች። ልትደግመው አትፈልግም። ትዳሯ ላይ ጫና ፈጥሯል። ከትምህርት ቤቶች ጋር ታግላለች። ልጇን መንፈስ አለበት ሰው እንዳይላት ፤ ስትችል ህመሙን ፤ ሳትችል ልጇን ደብቃ ታውቃለች። ያመምው ልጇ መሻሉን ለማሳመን ትግል ላይ ያለች እናት ፤ ሁለተኛውም ተመሳሳይ ህመም አለበት ብሎ ማሰብ ይከብዳታል። ታድያ ይህንን ጽሑፍ ባኖርኩበት ጊዜ ፤ ይቺ ምስኪን እናት ልጇን አንቱታን ያተረፈ የነርቭ ሀኪም ጋር ለማሳየት ፤ ቀጠሮ ይዛ እየጠበቀች ነው። እሷም አንድ ነገር ነው መስማት የምትፈልገው ። ቢሆንላት "ልጅሽ ደህና ነው" አልያም "ኦቲዝም የለበትም “ እውነታው ግን ይቺ እናት እንደፈራችው አይደለም። ኦቲዝም የአንድ ግለሰብ/ልጅ መጨረሻ አይደለም። የኦቲዝም ታማሚዎች ጉዞ ከእኛ ተለየ ማለት ፤ የእነርሱ የከፋ የእኛ ምርጡ ነው ማለት አይደለም። የሁላችም ህይወትና መንገዳችን ለየቅሉ ነው ። ኦቲዝም ህመም በኢትዮጵያ ከበፊት አመታት ለውጥ ቢኖርም ፤ ኦቲዝም ህመም አሁንም በኢትዮጵያ ውስጥ የተሳሳተ ግንዛቤ አለው። ለዚህም የኦቲዝም ታማሚ ቤተሰቦች ብዙ ውጣ ውረድ ያሳልፋሉ። እስቲ አስቡት ይህች እናት ስለኦቲዝም ያላት ግንዛቤ የተሻለ ቢሆን ኖሮ? በአሁኑ ወቅት ስለኦቲዝም ህመም መጠን የሚያሳይ ሀገር አቀፍ መረጃ ባይኖርም ፤ ቁጥሩ እየጨመረ እንደሆነ ይገመታል። ያሉ ጥናቶችም እንደሚገልጹት በየአመቱ በሺ የሚቆጠሩ ህጻናት ያለባቸው ኦቲዝም ህመም ሳይታወቅ ያልፋል (ለምሳሌ ሁለተኛ ልጇ)። ከሁሉም አስከፊው ግን በማህበረሰባችን ዘንድ ያለው የተሳሳተ ግንዛቤ የሚፈጥረው ተግ-ዳሮት ነው። ይህንን ማህበረሰባዊ ግፊት ለመሸሽ ቤተሰቦች እነኝህ ህጻናትን እስከ-መደበቅ ይደርሳሉ። ትምህርትቤቶችም ልዩ እገዛ የሚያስፈልጋቸውን ህጻናት መቀበል አይፈልጉም። ቢፈልጉም እንዴት ማስተማር እንዳለባቸው አያውቁም። ይህንን ትምህርት መስጠት የሚችሉት ትምህርትቤቶችም፤ ጥቂት ከመሆናቸውም ባሻገር፤ አብዛኞቹ በከተማ ነው የሚገኙት። ጥቂት የማይባሉትም ክፍያቸው ቀላል አይደለም። እውነታው ይህ ከሆነ ፤ በገጠሯ ኢትዮጵያ የሚኖሩትስ የኦቲዝም ታማሚዎች እጣቸውስ ምንድነው? የማህበረሰብን ትዝብት ጥሶ ወጥቶ ፤ የልጁን ህመም ተቀብሎ ፤ ማስተማር የሚፈልግ ገበሬስ ምን ያድርግ ? የት ያስተምር? ምልክቶቹን ቀደም ብሎ ማወቅ ይጠቅማል። ኦቲዝም ስፔክትርም ዲስኦርደር (Autism Spectrum Disorder) ህመምን መለየት ይቻላል። እነኝህ ህጻናት ከሌሎች ህጻናት ለየት የሚያረጓቸው ዋነኛ ምልክቶች ፦ • ማህበራዊ ችግሮች – ማህበረሰባዊ ቁርኝት ለመፍጠር ይቸገራሉ። ስንጠራቸው ፣ ስናወራቸው ላይመልሱ ይችላሉ። አይንን ይሸሻሉ። አፍጠው አያዩም። የእኛን አካላዊ ቋንቋም ለመረዳት እጅግ ይቸገራሉ። • የቋንቋ እክሎች– እነኝህ ህጻናት አፋቸውን ሲፈቱ ከእኩዮቻቸው ሊያረፍዱ ይችላሉ። ሲያወሩም ቃላቶቻቸው ይዘገያሉ። ቃላት ይደጋግማሉ። ውይይት ውስጥ መሳተፍ አይፈልጉም። • ድግግሞሽ ያላቸው ባህሪያት– ባህሪያትን አብዝተው ይደጋግማሉ። እጃቸውን፣ እግራቸው፣ እጅና እግራቸውን ፣ ፊቶቻቸውን ባልተለመደ መንገድ ደጋግመው ሊያወራጩ ወይም ሊያንቀሳቅሱ ይችላሉ። • ያልተለመዱ ተስእቦዎች/ዝንባሌዎች- እኛ ፈጽሞ አጽንኦት ለማንሰጣቸው ጉዳዮች/ነገሮች ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጡ ይችላሉ። ለምሳሌ የሚሽከረከሩና የሚንቀሳቀሱ ነገሮች፣ መብራት፣ ድምጽን በደንብ ሲያጤኑ ሊቆዩ ይችላሉ። እነኝህ ምልክቶች ከአንድ አመት እድሜ ጀምሮ ሊታዩ ይችላሉ። ምልክቶቹን ለይቶ ህመሙን ቀደም ብሎ ማወቅ በጣም ወሳኝ ነው ። ማህበረሰባዊ ተግዳሮቶቹ ኦቲዝምን በማህበረሰብ በኩል ያለው እይታ መሻሻል ይኖርበታል። አንዳንዶች ይህ ህመም ቤተሰቦች ለፈጸሙት ኃጢያት ቅጣት አድርገው ያስቡታል። ሌሎች ደግሞ ክፉ መንፈስ ልጆቹ ላይ ሰፍሮ ነው ብለው ያምናሉ። ለዚህም ቤተሰብ ኦቲዝም ያለው ልጅ ካለ ይሳቀቃል። ከትዝብት ለመትረፍ ሲል ገበናውን ይደብቃል። እንግዲህ ገበና እነኝህ ልጆች መሆናቸው ነው። ልጆቹንም ይዘው ወደ ማህበራዊ ግብዣዎች አይሄዱም። አንዳንዳንዴም ኦቲዝሙን ለማዳን ህጻናቱን የከፋ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ሥርዓቶች ያድርጉላቸዋል። በዚህም የተነሳ ዘመናዊ ህክምና የሚመጡት የተወሰኑት ናቸው። ይህ አሳፋሪ ተግባር ልጁን ያገላል ፤ ህመሙን ያባብሳል ፤ ቤተሰብንም ይጎዳል። እዚህ ጋር ታማሚው ልጁም ቢሆንም ህመሙ የቤተሰብ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። ለዚህም ስለኦቲዝም ስናነሳ ፤ ሁሌ በተሰቦቹን ማሰብ አለብን። እነሱም አብረው ነው የሚገለሉት። ለልጁም የሚወስኑለት ፤ ህመሙን የሚቀበሉት ሆነ ፤ የለበትም ብለው ህክምናን የሚከለክሉት ቤተሰቦቹ ነው። እሱማ እድሜውም ሆነ የጭንቅላት አቅሙ ለራሱ ለመወሰን ላይበቃ ይችላል። ስለዚህም ቤተሰብም የ ህክምናው አካል መሆን አለበት ። ይህች ምስኪን እናት ገና ትንሹ ልጇ ምልክት ሲያሳይ ልጇ ፍርሀቷን ችላ ህመሙን እንዲታከም ብትጋፈጥለጽ ኖሮ ? ይህ ልጅ ምን አይነት ለውጥ ያገኝ ነበር ? ህመሙ ደግሞ በባህሪው ቀድሞ ከታከመ ፤ እጅጉን የተሻለ ለውጥ ያመጣል ። የመጀመሪያ ልጇ ለዚህ አንደኛ ምሳሌ ነው። ህመሙን መካድ እና አለመቀበል ደግሞ እንክብካቤን ያዘገያል። ማስተዋል የሚኖርብዎት ጉዳይ ኦቲዝም አንድ ህመም አይደለም። ለዚህም ነው ኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር የሚባለው ። በአማርኛ ስንገልጸ ኦቲዝም ምህዳር አለው። በአንደኛው ጫፍ የእውቀት ፀጋን የተላበሱ እንደ አልበርት አንስታይን እና ኤለን መስክ ያሉ ሊቃውንት አሉ ። በተለይ ኦቲዝም ያለባቸው የሳይንስ ሊቆች የሂሳብ ምጡቃን ጥቂት አይደሉም። በሌላኛው በኩል ሀሳባቸውን የመግለጽ ፣ ቋንቋን የመጠቀም እንዲሁም የማህበራዊ ቁርኝታቸው እጅጉን የተሰናከለ ታማሚዎች ይኖራሉ። ባብዛኛው በእነኝህ መሀል ይገኛል። በጊዜ የህክምና ክትትልና የልዩ እገዛ ማድረግ ፤ የእነኝህ ህጻናት ህመም በምህዳሩ በየትኛው ጫፍ እንዳለ ይወስናል። የልጆቹ የወደፊት ህይወት እንዲሁም ውጤታማነታቸውን ይወስናል። የልጆቹን ውጤታማነት እንዲሁ የመፍጥር መጠነኛ እክል ሊኖራቸው ይችላል። ትምህርት ቤቶቻችን በበኩላቸው በዚህ በኩል እጅጉን መለወጥ ያስፈልጋቸዋል። አሁን ያሉት ጥናቶች እነኝህ ልጆች ከእኩዮቻቸው ለይቶ ከማስተማር ይልቅ ፤ ልዩ እገዛ እየተደረገላቸው አብረዋቸው እንዲማሩ ይመክራሉ። አስተማሪዎቻችንም ይህንን ትምህርት በመስጠት ዙሪያ ስልጠና መውሰድ አለባቸው። ማሳረጊያ እውነታ! ኦቲዝም እርግማን አይደለም። ቅጣትም አይደለም። የአንድ ልጅ የወደፊት ዕጣ ማብቂያም አይደለም ። ዓለምን ማያ ልዩ መንገድ ነው ። እናም እንደማህበረሰብ ምላሻችን በፍቅር፣ በመረዳት ፣ በመቀበል፣ እና በተግባር መጀመር አለበት። ለዛች ለልጆቿ የተስፋን ጥግ እየፈተነች ላለች እናት “የልጆችሽ ተወዳዳሪ የሌለው ህክምና ያንቺ ፍቅር ነው። አይዞሽ ህመሙን አትታገይው። ይልቁኑ ልጅሽ የሚያስፈልገውን እርዳታ ቶሎ እንዲያገኝ በርቺለት እንጂ “ ተግባራዊ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ ነገ አይደለም ! አሁን ነው!
- ለብርድ ህመም ፍቱን መድሐኒቱን ያውቃሉ?
መቼም ከሙቀት ወደ ቅዝቃዜ ሲወጡ ብርድ እንዳይመታኝ ብለው ፈርተው ያውቃሉ። አንዴም ሆነ ሌላ ጊዜ ታሞ የሚያውቅ ሰው ፣ ወደ ቀዝቃዛ አየር ሲወጣ ብርድ እንደሚመታ እርግጠኛ ነው። ለዚህም ከእራሳችን አልፈን ሌላ ሰው ስንመክር ፤ ብርድ እንዳይመታህ/ሽ እንላለን። ይህ አነጋገር ባብዛኞቻችን ወይ ብለነዋል ወይ ሰምተነዋል። ለቀዝቃዛ አየር፣ ለንፋስ ወይም ለዝናብ ሰውነታችን ሲጋለጥ ፤ ይህ የበረደ አየር ወደ ውስጥ ገብቶ በሽታ እንደሚያመጣ ብዙዎች ያስባሉ። ህመሙም ቀላል ባለመሆኑ ፤ በመላምታቸው እርግጠኛ ናችው። በተለምዶ ብርድ ሲያም :- ደረት ይወጋል ያስላል (የጠነከረ ሳል) ሰውነት ይዳከማል ወይም ይዝላል ትኩሳትም አንዳንዴ ሊኖረው ይችላል የበሽታ አምጪ ሰበቡም ቀዝቃዛ አየር ተደርጎ ስለሚወሰድ ፤ የተለምዶ ህክምናው ልብስ መደረብ፣ መስኮት መዝጋት ፣ ትኩስ ነገር መጠጣት ናቸው። እንደውም አንዳንዴ ሳሉ ጠንከር ካለ ፤ በጠዋት ማር በእንቁላል ውሰድበት የሚልም አይጠፋም። እውነት ብርድ የሚባል በሽታ አለን? በተለምዶ ብርድን የምንረዳው እንዲህ ቢሆንም ፤ በ ዘመናዊ ህክምናው ብርድ የሚባል በሽታ የለም። አብዛኛው ሰው እንደሚያስበው ፤ አየር የበሽታ አምጭ ተህዋስ መሆን አይችልም። የበሽታ አምጪ ተህዋስን ግን መሸከም ይችላል። የብርድ ህመም ብለን የምንጠራው ፤ የተለያዩ በሽታዎች ስብጥር ነው። እነኝህ ህመሞች በተለይም የላይኛው የትንፋሽ ቧንቧ ክፍል ያሳምማሉ ወይም ያጠቃሉ። ከአየር ቧንቧም ባሻገር የጡንቻ ህመም ሆነ የጀርባ አጥንት ህመም ሲሰማም እራሱ ፤ ብርድ መቶኝ ነው ብሎ ማሰብና ከቀዝቃዛ አየር ጋር ማዛመድ እጁጉን ተለምዷል። ይብሱኑ በሆስፒታል የጋራ መኝታ ክፍሎች ውስጥ ያሉ ታማሚዎች ፤ በዚህ የተሳሳተ አስተሳሰብ ተመስርተው ፤ ብርድ እንዳይመታቸው ፤ መስኮቶች እና በሮችን ጥርቅም አድርገው ይዘጋሉ። በተመሳሳይ ሁኔታ በሳል ህመም የታመመ ሰው ታክሲ ውስጥ ሳሉ እንዳይብስበት ፤ ብርድ እንዳናስመታው አሳስቦ መስኮት እንድንዘጋ አጥብቆ መጠየቁ አይቀርም። ይህ ደግሞ ታላቅ እርማት የሚያስፈልገው ተግባር ነው። ግን ይህ መላምት እንዴት መጣ? እውነት ለመናገር ይህን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ፤ በብዙ ባህሎች ያለ አስተሳሰብ ነው። የኛን ሀገር እነኚህን ከቅዝቃዜ ጋር የተገናኙ ህመሞች ብርድ የሚል ስያሜ ሰጠናቸው እንጂ ፤ በአውሮፓ፣ በእስያ እና በላቲን አሜሪካም ተመሳሳይ እምነቶች አሉ። ለምን? ምክንያቱም እነኝህ ማህበረሰቦች እንዳስተዋሉት ከሆነ ቀዝቃዛ አየር እና ህመም ብዙውን ጊዜ በተመሳሳይ ወቅት ይመጣሉ። ለምሳሌ የጉንፋን ህመም ከሚንሰራፋባቸው ጊዜያት መሀል የዝናብ ወራት ናቸው። የአለርጂ ህመም በበኩሉ እንደ ጥቅምት እና ህዳር ያሉ ነፋሻ ጊዜያት ላይ ሊጨምር ይችላል። እንዴት ቀዝቃዛ አየር ለህመም ያጋልጣል? የእነኝህ ማህበረሰቦችም መላምት እውነት አለው። በቅርብ የወጡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ቀዝቃዛ አየር የሰውነት በተለይም የትንፋሽ ቧንቧን የበሽታ የመከላከል አቅም ይቀንሳል። በፊት በእንሰሶች ላይ የተረጋገጠ ቢሆንም ፤ በቅርብ በሰዎች ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያመላክተው ደግሞ ፤ አፍንጫችን ሆነ የላይኛው የትንፋሽ ቱቦ ከሰውነት ሙቀት በ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ የሙቀት መጠኑ ከቀነሰ ፤ የትንፋሽ አካላት የበሽታ የመከላከል አቅም በግማሽ ይወርዳል። ይህም ደግሞ ለበሽታ የመጋለጥ እድሉን ያሰፋል። ይህ ብቻ ለህመሙ አጋላጭ ቢሆን ኖሮ ፤ በህመሙ አንደኛ የሚጠቁት በረዶአማ አከባቢ የሚኖሩ ፈረንጆች ነበሩ። ሆኖም ግን አብዛኞቹ በሽታ አምጪው ተህዋስ ቅዝቃዚው ስለሚገላቸው ፤ ተጠቂነቱ ይቀንሳል። እዚህ ላይ ይብሱኑ ብለን ደግሞ ፤ በእነኝህ ቀዝቃዛ ወራት ፤ ቅዝቃዜን ሸሽተን ሙቀትን ፈልገን ፤ አብዛኛውን ጊዜ የምናሳልፈው በቤታችን ወይም በመዝናኛ ቦታዎች ተሰብስበን ነው። ይህ ባህሪ መልካምነት ቢኖረውም ፤ አየር ስለማይዘዋወር ፤ በትንፋሽ የሚተላለፉ በሽታ አምጪ ተህዋሳት በቀላሉ እንዲሰራጩ እድል ይከፍታል። ለምሳሌ አንድ ታክሲ 13 ሰው ይይዛል። ከ እነኝህ ተሳፋሪዎች ውስጥ አንዱ ጉንፋን ይዞት ቢሆን ፤ መስኮቶች ከተዘጉ ሁሉም ተሳፋሪ ለ ጉንፋን አምጪው ቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ ይጋለጣል። ታድያ ግን በጉንፋን መያዛችን ወይም ሳንባ ምች መሆኑ የሚወሰነው ፤ ባለን የበሽታ የመከላከል አቅም ልክ ነው። ይህ የሳል ህመም ያለበት ሰው የታመመው ሳንባ ነቀርሳ ቢሆንስ ? ከዚህም ባሻገር አበቦች በሚያብበት ጊዜ ያለ ደረቅ ነፋሻማ አየር ፤ አብሮት የተለያዩ ብናኞችን (በተለይ የአበባ ብናኝ) ይዞ ስለሚመጣ ፤ እንደ አስም እና ሳይነስ አይነት ህመም ያለባቸው ሰዎች ህመማቸው ይባባሳል። እዚህ ጋር ማስተዋል ያለብን ፣ ቀዝቃዛ አየር አይደለም ብርድን የሚያመጣው። እንደውም ብርድን ለመሸሽ የምናደርጋቸው ባህሪያት ፣ በጋራ የምንጠቀምባቸው መመገቢይ ቁሶች ላይ ያለው ባክቴሪያ ወይም ቫይረስ ነው። የመተንፈሻ አካልን የሚያጠቁ ቫይረሶች: - እንደ ራይኖቫይረስ ፣ ኮሮና ቫይረስ፣ የኢንፍልዌንዛ ቫይረስ፣ ወ.ዘ.ተ ፤ ወደ ትንፋሽ አካሎቻችን ከገቡ ፤ ለማራባት አመቺ ሁኔታን ይፈልጋሉ። ሰውነታችን ከተቋቋማቸው ምንም ምልክት ሳይኖረው ይጠፋሉ። ሆኖም ግን ኢንፌክሽን ከፈጠሩ ፤ ጉሮሮአችን ይቆስላል ፣ ትኩሳት ይኖረናል ፣ ድካም ይሰማናል። የታችኛው የትንፋሽ ቧንቧን ካስቆጡ ደግሞ ፤ የበረታ ሳል ፣ አክታ፣ የደረት ህመም (መውጋት) አይነት ምልክት ልናሳይ እንችላለን። እነኝህ ምልክቶች ሰውነታችን ከኢንፌክሽን አምጪ ተህዋስ ጋር እያደረገ ያለውን ግብግብ የሚያሳዩ እንጂ ፤ አየር ቆዳዎትን አልፎ ደረትዎ ውስጥ ወይም ሆድ እቃዎ ውስጥ ገብቶ ፤ የሚመጡ አይደሉም። ስለዚህ አየር እንዲንቀሳቀስ በማድረግ፣ መስኮት በመክፈት፣ በሽታ አምጪ ተህዋሱ እንዲወጣ በማድረግ እራስዎን ሊጠብቁ ይችላሉ። ቀዝቃዛ አየር ሳያጋጥምዎ እንዴት ብርድ መታኝ ብለው የሚያውቁ ከሆነ ፤ ምክንያቱ ከላይ የጠቀስነው ነው እንጂ ፤ እንቅልፍ ላይ ሆነው ተገላልጠው የመጣቦት ህመም አይደለም ። እንዴት እናስታርቀው ታድያ? የብርድ የምንለው በሽታ ባይኖርም ፤ የህመም ምልክቶቹ ግን እውነት ናቸው። ህመሞቹን ደግሞ መከላከል ይቻላል። ✔️ ለኮቪድ ጊዜ ያደርጉት እንደነበረው አይነት ጥንቃቄን ቢያደርጉ ፤ እጅ መታጠብ ፣ የሳል ህመም ካለብዎ ጭምብል መልበስ ፣ ከታመሙ ሰዎች ጋር ያሎትን ቅርበት መቀነስ እንድንከላከለው ያግዛል። ✔️በተለይ በተለይ ሰው የተሰበሰበት ክፍል ውስጥ መስኮት እና በር ዘግተው ፤ የአየር እንቅስቃሴን ፈጽሞ አይገድቡ። አየር ከታፈነ ፤ የሳንባ ነቀርሳን ጨምሮ ለብዙ የአየር ቧንቧ ህመሞች ሊጋለጡ ይችላሉ። ትክክለኛው አደጋ ነፋሱ/ ቅዝቃዜው ሳይሆን እራስን አለመጠበቅ ፤ ህመም ምልክት ሲያሳዩ ፤ ህክምና አለመፈለግ ነው። ስለዚህ ከዛሬ በኋላ ... የብርድን ትርክትን እናርም። የተግባር ለውጥ ያስፈልጋል። ሙቀትንም መሻታችን መልካም ቢሆንም አየር እንቅስቃሴ አለመኖሩ ለትንፋሽ ህመም ያጋልጣል። አየሩን ሳይሆን ቫይረሱን እንሽሽ።
- እናቶችን በተግባር እናመስግን
የዛሬ አስር አመት በፊት ገደማ አንዲት በገጠሪቷ ክፍል የምትገኝ እርጉዝ እናት ፤ የመውለጃ ጊዜዋ ይደርስና አዋላጆች ይጠራሉ። እንዳሰበችውም ከቤቷ ትወልዳለች። የወለደችው ልጅ ጤነኛ ቢሆንም ፤ የእንግዴ ልጇ አልወጣም ነበር። በዚህም የተነሳ ከማህጸኗ የማያቁርጥ ደም ይፈሳት ጀመር። ይች ምስኪን እናት ህይወት ሰጥታ ፤ ህይወቷ አደጋ ላይ ወደቀ። የምጥ ጊዜዋ አልቆ ፤ የልጇን ለቅሶ ሰምታ ህመሟ የሚታገሰው ፤ ቁስሏ የሚሽር እናት ፤ ህመሟ ተራዘመ። በሁኔታው የተደናገጡ ቤተሰቦችም ፤ በአፋጣኝ ወደ ህክምና ተቋም ይዘው መሄድ እንዳለባቸው ወሰኑ። ይህንን ህመም የአከባቢው ሰዎች ያውቁታል። ብዙ እናቶችን ሰርቋቸዋል። ታድያ ሀሳብ የገባቸው የአከባቢው ሰዎች ፤ ይቺን ምስኪን እናት ከ ቃሬዛ ጭነው ፤ መንገድ ጀመሩ። ግን ይህ የእናት ሌባ እንዳይቀማቸው ፤ ይችን እመጫት እንዳያስቀር ፤ በጥይት ጓጓታ እና በቆርቆሮ ኳኳታ ሌባውን እያስፈራሩ ይዘዋት ሄዱ። በቅርብ ያለ ጤና ጣቢያም እንደደረሱ አፋጣኝ የህክምና እርዳታ በማግኘቷ ይችህ ሞት አፋፍ ላይ የነበረች እናት ህይወቷ ሊተርፍ ቻለ። እሷም ይኽው ታሪኳን ለመተረክ በቃች። ይህንን ታሪክ ለማስቀረት ባለፉት አመታት ውስጥ ብዙ ተሰርቷል። ሆኖም ግን በቤታቸው ሲወልዱ ፤ ከዚህም የከፋ እድል ያጋጠማቸው እናቶች ዛሬም አይጠፉም። ይህ የኢትዮጵያ እናቶች ታሪክ ነው። በዛሬዋ የ እናቶች ቀን ፤ አለም በድሎት ላይ ሆኖ በአበቦች እና ባማሩ ስጦታዎች ታጅቦ ሲያከብር ፤ እኛ ደግሞ ጤናማ ፣ ከወሊድ ጋር በተያያዘ እናት የማትሞትባትን ኢትዮጵያ ለእናቶቻችን ማበርከት ተስኖን ይኸው እንገኛለን። አንድ እናት ኢትዮጵያ ውስጥ በእርግዝና ባበጡ እግሮቹዋ ረዝም እርቀቶችን ትጓዛለች ፤ የጉልበት ስራን ትሰራለች። ሞትን ተገዳድራ ለልጇ ህይወት ትሰጣለች። አለም ላይ ያለ ችግር ቢጫንባትም እንኳ ፤ ያለመታከት ከልጇ ጎን ትቆማለች። በጭንቅ ውስጥ ሆና ለልጇ ፈገግ ትላለች። ይህ የኢትዮጵያውያን እናቶቻችን ያልተወሳ ጀግንነት ነው። የእናትነት ስጋት በኢትዮጵያ ውስጥ መንግስት ሆነ ባለድርሻ አካላት የእናቶችን ህይወት ለማሻሻል ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል ፤ እያደረጉ ይገኛል። የዛሬ 34 አመት እ.ኤ.አ. በ 1990 በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚወለዱ 100 000 ህጻናት 1400 እናቶች ይሞቱ ነበር። ባለፉት አስርት ዓመታት የእናቶችን ጤና አገልግሎት ለማሻሻል ብዙ የተሰራ ቢሆንም ፤ አሁንም እናትነት ትልቅ የህዝብ ጤና ስጋት ሆኖ ቀጥሏል። እ.ኤ.አ. በ 2022 በ EDHS መሠረት በህይወት ለሚወለዱ 100 000 ህጻናት 267 እናቶች ይሞታሉ ። ይህ ቁጥር ከበፊቱ እጅጉን የቀነሰ ቁጥር ቢሆንም ፤ ትንሽ ግን አይደለም። በኢትዮጵያ የህዝብ ብዛት ካሰላነው ፤ በ አመት ውስጥ ወደ 12 ሚሊየን ልጆች ይወለዳሉ። ይህ ማለት በዚህ አመት ብቻ ፤ 32 000 የሚጠጉ እናቶች ህይወት ሊሰጡ ህይወት ያጣሉ። 32 000 ልጆች እናቶቻቸውን ሳያውቁ ያድጋሉ ። እስቲ ያስቡት ፤ ከእነኝህ ጨቅላ ህጻናት ውስጥ አንዱ እርሶ ሆነው ቢሆኑስ ? በኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም ከ40% በላይ የሚሆኑት እናቶች በቤት ውስጥ ይወልዳሉ። የሰለጠነ የህክምና እርዳታ ስለማያገኙም ፤ ህይወታቸው አደጋ ላይ ነው። ንጹህ ውሀና ኤሌክትሪክ በሌለበት የሚወልዱትስ? በእርግዘና ወቅት የሚፈጠሩ ህመሞች እንደ ደም ግፊት(preeclamcia) ፣ የስኳር ህመም ፣ እንዲሁም የደም ማነስ(anemia) ቀድሞ ለማወቅ ፤ የተሟላ የቅድመ ወሊድ ክትትል ያስፈልጋል። ሆኖም ግን አስፈላጊ የሆነውን አራት የቅድመ ወሊድ ክትትል የሚያደርጉ እናቶች 43% ብቻ ናቸው። እነኝህ ቁጥሮች እናቶች የሚያጋጥማቸው ተግዳሮቶች የሚያሳዩ ፤ ቅንጫቢ እውነታዎች ናቸው። ሆኖም ግን ይሁ ሁሉ ቢደራረብባት የኢትዮጵያ እናት ፤ ለልጆቿ እና ለቤተሰብዋ ስትል ትጀግናለች። ፈገግ ትላለች። ማንም የማያየው ጥንካሬ ይህን ጥንካሬዋን ማንም አያይላትም ። ጀብዱ የለውምና ገሀድ አይወጣም። ሆኖም ግን በዝምታዋ ውስጥም ይች እናት ጀግንነት አላት። የወለደ ሰውነቷ ሳይጠግን ፤ በደንብ ሳትታረስ ወደ ስራ የምትመለስ እናት አለች። እንቅልፍ የጣላቸውን ቤተሰቧን ላለመበጥበጥ ፤ ምጥዋን ለመታገስ የምትሞክርም እናት አለች። አድራሽ ሰው ሆነ ትራንስፖርት አጥታ ፤ በምጥ ላይ ሆና ፤ ወደ ህክምና ተቋም በእግሯ የምትሄድ እናትም አለች። በሾተላይ ልጆቿን አጥታ ፤ ሌላ ልጅ ለመውለድ ፤ ህይወቷን አደጋ ላይ ጥላ ፤ ግብ ግብ ላይ ያለች እናት አለች። እላይ ከጠቀስናቸው እያንዳንዱ ቁጥሮች ጀርባ ፤ የቤቷ ማጀት የሆነች አንድ እናት አለች። ባለፉት አመታት ብዙ አሻሽለናል። " እናት ለምን ትሙት" የሚል እንቅስቃሴ ጀምረን ፤ አለምን ያስደመመ ለውጥ አምጥተናል። የእናቶች ሞት ቀንሷል። የጤና ሰራዊቶች፣ ኤክስተንሽን ባለሙያዎች በየመንደሩ እርጉዝ እናቶችን እየቃረሙ ፤ ክትትል እንድታገኝ ለማድረግ ይሞክራሉ። በአንዳንድ ሆስፒታሎች የሚደረጉ የዘመኑ የስልክ እና የጽሁፍ መልእክቶች ፤ እናቶች የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤ እንዲያደርጉ በማስታወስ ፤ ክትትል እያሻሽሉ ይገኛሉ። ግን አሁንም እናቶች ስጋት አለባቸው። አስፈላጊው ለውጥ የኢትይጵያ የጤና ሚኒስተር በ2030 የእናቶችን ሞት ወደ 140 ለመቀነስ ፤ እቅድ አውጥቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተረባረበ ይገኛል። መሀል አዲስ አበባም ሆነ መንገድ የሌለበት ገጠሪቷ ኢትዮጵያ ላይ ያለች እያንዳንዷ እናት ፤ በወሊድ ዙሪያ በሰለጠነ ባለሙያ መታከም ይኖርባታል። እንደዚህ ርቀው በሚገኙ አከባቢዎች ላሉ እናቶች ፤ በወሊድ ጊዜ መጠበቂያ ቤቶች እና የድንገተኛ ጊዜ እንክብካቤ ማዕከሎችን ማስፋፋት መቻል አለብን። የእናቶችን እንክብካቤ ተድረሽነት ለመጨመርም ፤ የ ዘመኑ የዲጂታል መሳሪያዎችን መጠቀም ይኖርብናል። እርስዎስ? በቅርብዎ የምትገኝ እርጉዝ እናት አለች? እንግዲያውስ የወሊድ ክትትል ሳታቋርጥ እንድታደርግ ፤ የዶክተሮችዋን ምክር በስርአት እንድትተገብር ይምከሯት። ቤተሰብዎ ወይም በጎረቤትዎ እርጉዝ እናት ካለች ያግዟት። የመውለጃዋ ሰሞን ሲቃረብ ወደ ጤና ተቋም የሚወስድ ትራንስፖርት እንድታዘጋጅ ይምከሯት። ካልቻለች እርስዎ ያዘጋጁላት። ወሊድዋ በ ጤና ተቋም እንዲሆን ይገፋፏት። ከዚህ በኋላ እነኝህ ጀግና እናቶቻችንን በ አስፈላጊው የጤና እርዳታ ማገዝ አለብን። እናቶቻችን በ እናቶች ቀን ብቻ አበባ የምናበረክትላቸው ፣ በሚያምሩ ቃላት የምናጅባቸው አይሁን ። በተግባር በእርግዝናቸው ፣ በወሊዳቸው እንዲሁም በ ድህረወሊድ ጊዜያቸው ጤናቸውን መጠበቁን እናረጋግጥ። እንዲህ እንበላቸው .... ውድ እናት ፣ ያለብሽን ድካም፣ እንግልት እና ፈተና ስረዳ ፤ ጥንካሬሽን አየሁ ። አንቺ የኢትዮጵያ ህዝብ የልብ ትርታ ነሽ። ዛሬ በባዶ ቃል ሳይሆን በአዲስ ቃል ኪዳን ፣ እናከብርሻለን። በተግባር ከጎንሽ ነን። እንደኖርሽልን እንኑርልሽ። ከዚህ በኋላ ወሊድ ላንቺ ደስታ ብቻ እንጂ ስጋትን አያመጣም።












