top of page

ትኩረት የሚነፍገው አቅለብላቢው የአእምሮ ህመም (ADHD)


አሁን ያለንበት የፈረንጆች የጁን ወር ፤ በአለም አቀፍ የወንዶች የአእምሮ ጤና ወር ነው። ለዚህም ይህ ጽሁፋችን ከሴቶች ይልቅ ወንዶችን ሶስት እጥፍ ስለሚያጠቃው የአእምሮ ህመም እናወራለን። ህመሙ በባህሪው ትኩረት የሚነፍግ እና አቁነጥናጭ ስለሆነ ፤ ይህንን ባህሪውን በሚገልጸው ስሙ አቴንሽን ደፊሲት ህይፐርአክቲቭ ዲሶርደር (attention deficit hyperactive disorder ) ወይም ኤዲኤች ዲ(ADHD) በመባል ይጠራል።


ይህ የአእምሮ ህመም ከ 2.5 እስከ 3.4 ፐርሰንት የሚሆኑ ጎልማሶችን እና ከ 5 እስከ 7 ፐርሰንት የሚሆኑ ህጻናትን በአለም ዙሪያ ያጠቃል። አንዳንድ መረጃዎች ደግሞ በአለማችን 366 ሚሊየን ጎልማሶች እና 6.5 ሚሊየን ህጻናት በህመሙ ተጠቂ እንደሆኑ ያሳያሉ። አብዛኞቹ ታማሚዎች ህመሙ እንዳለባቸው እንኳን አያውቁም። ለዚህም አስፈላጊ የህክምና እርዳታ አያገኙም። ይህ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ይብሳል።


ህመሙ በዋነኝነት ከአእምሮ አሰራር/ አመሰራረት ጋር የተያያዘ ነው። ከህመሙ ጋር የተያያዘውን እክል ቀለል ባለ ቋንቋ ስንገልጽው፡

የአእምሮአችን ትኩረት ፣ ተነሳሽነት ፣ ጊዜ አጠቃቀም እና ራስን መቆጣጠር ጋር የተያያዙ የአእምሮአችን ክፍሎች ተባብረው ለመስራት ሲቸገሩ ይፈጠራል። እነኝህ የአእምሮአችን ክፍሎችም እርስ በእርስ ሳይናበቡ በየግላቸው ይሰራሉ።  ይህም ደግሞ በተለያየ ውስብስብ ምክንያት የሚከሰት ቢሆንም ፤ ትኩረት፣ ተነሳሽነት፣ ጊዜ አጠቃቀም እንዲሁም እራስን መቆጣጠር ችሎታ እንዲሰናከል ያደርጋል። 

ህመሙ ለብዙዎች እድሜ ልክ ሲሆን ፤ ታማሚዎች በልጅነት እድሜያቸው ጊዜ በትምህርታቸው ይቸገራሉ። አድገውም በስራቸው እንዲሁ። ሰነፍ ባይሆኑም ህመሙ ሰነፍ ያስመስላቸዋል። ውጤታማነትን ይዘርፋቸዋል። ተነሳሽነት የላቸውም። ጊዜ ያባክናሉ። ሀሳባቸውን የተሰበሰበ አይደለም። አደብ አይገዙም።


ብዙ ታማሚዎች ህመሙ እንዳለባቸው ስለማያውቁ ፤ እራሳቸውን ሰነፍ ፣ አልያም ደደብ አድርገው ይወስዳሉ።

ህመሙ በበኩሉ መፍትሔ ካልተሰጠው ፤ የትምህርት አቅምን አኮላሽቶ ከማስቀረት አልፎ ፤ አድገው እራሱ በስራ ውጤታማ እንዳይሆኑ ያደርጋል። በራስ ያለ መተማመንንም ያመነምናል።


🔬መንስኤው ታድያ ምንድን ነው?


እላይ እንደገለጽነው የዚህ ህመም መስረት ከነርቭ (አንጎል) ጋር የተያያዘ ሲሆን ፤ ለህመሙ መያዝ ተጋላጭነት የሚጨምሩ ምክንያቶች መካከል ፡

🧬ከዘረመል ጋር የተያያዙ ምክንያቶች፡ ህመሙ በዋነኝነት በዘር የሚተላለፍ ነው። ለዚህም በቤተሰብ ውስጥ ህመሙ ያለበት ሰው ካለ ፤ ሌላ የቤተሰብ አባል የመያዝ እድሉ ከፍተኛ ነው። ህመሙ ያለባቸውም ወላጆች ልጆቻቸው ላይ ምልክቶቹን ቢከታተሉ ይመረጣል።


🧠የአንጎል ችግሮች፡ ህመሙ ከአንጎል ችግሮች ጋር ይያዛል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ፤ ህመሙ ያለባቸው ሰዎች ትኩረትን እና መነሳሳትን በሚቆጣጠሩ የጭንቅላት አከባቢዎች ላይ ያለ የአእምሮ ስራ የተገደበ ነው።

🤰 ቅደመ ወሊድ ምክንያቶችም ለዚህ ህመም አጋላጭ ተደርገው ይጠቀሳሉ። ያለጊዜ መወለድ፣ በእርግዝና ጊዜ የእናቶች ማጨስና አልኮል መጠጣት ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው።


🥦🍊ከአመጋገብ ጋር የተያያዙ ምክንያቶች ሊያጋልጡ ይችላሉ። በተለይ ቪታሚን ቢ (vitamin B9 & B12) እጥረት ፤ ህጻናት ምልክቱን እንዲያሳዩ ይደረጋል።


🌍 እንደ ሊድ(lead) ያሉ ንጥረነገሮችም በአከባቢያችን ካሉ ፤ ለህመሙ ሊያጋልጡ እንደሚችሉ ጥናቶቹ ያመላክታሉ።


ከዚህም ባሻገር ሞባይል አብዝቶ መጠቀም፣ ቲቪ አብዝቶ ማየት፣ እንቅልፍ ማነስ፣ አከባቢ ላይ አስጨናቂ ነገር መኖር ፤ የህመሙ ምልክቶች እንዲባባሱ ያደርጋል።

🚸 ችላ የማይባሉት ምልክቶች


ይህ ህመም ምልክቶች ብዙውን ጊዜ ከ6 አመት ጀሞር የሚታዩ ሲሆኑ እስከ አዋቂነት ድረስ ይዘልቃሉ። ምልክቶቹ በዋነኝነት በሶስት የሚፈረጁ ሲሆን እነኝህም


  1. ትኩረት ማጣት

ይህ ህመም ያለባቸው ሰዎች ትኩረታቸውን መሰብሰብ ያስቸግራቸዋል። በቀላሉ ሀሳባቸው ይበተናል። ለነገሮች ዝግጁ ለመሆን ይቸገራሉ። ቤታቸው፣ ክፍላቸው የተደራጀ (ስርአት ያለው) አይሆንም። አብዝተው ይዘነጋሉ። ቁልፎች እና ትናንሽ እቃዎችን ጠፍተውባቸው መፈለግ ልማዳቸው ነው። ያሰቡት ይጠፋባቸዋል። ይብሱኑ ስራም ይዘነጋሉ።


  1. አብዝተው ይቅለበለባሉ


እነኝህ ታማሚዎች ነገሮች ላይ መፍጠን ያበዛሉ። አርፈው መቀመጥ ይቸገራሉ። ይቁነጠነጣሉ። ሲያወሩ እራሱ በብዛት ነው።


  1. ግልፍተኛ ናቸው


ይህ ህመም ያለባቸው ስዎች በጉዳዮች ግልፍተኝነት ያጠቃቸዋል። ራሳቸውን የመቆጣጠር አቅማቸው ጠንካራ አይደለም። ለዚህም ሳያስቡ ያወራሉ። ሳያስተውሉ ድርጊቶችን ይፈጽማሉ። ለዚህም ራሳቸውን አደጋ የሚጥል ሁኔታ ውስጥ ሊያገኙ ይችላሉ። አውርተን እስክንጨርስ ከመጠበቅ ፤ ወሬ መሀል ሊያቋርጡን ይችላሉ።


ህጻናቶች በትምህርታቸው ደካማ ሲሆኑ፤ አዋቂዎች ደግሞ ብዙ ስራ ሊለዋውጡ ይችላሉ ። ውጤታማነት ያስቸገራቸዋል። አልያም በዝምታ በጭንቀት ይሰቃያሉ።

የታማሚዎች ህይወት


ይህ ህመም ያለባቸው መደበኛ ህይወት ሲመሩ እክሎች ያጋጥማቸዋል። ጭንቅላታቸው ነገሮችን የሚፈጽምበት መንገድ የተለየ ስለሆነ ፤ በማህበረሰባዊ ህይወት፣ በትምህርት እንዲሁም በስራ ላይ ተግዳሮቶች አያጡም።


🎒 በት/ቤት፡- ብሩህነትን ማጣት


ይህ ህመም ያለበት አንድ ልጅ " ሰነፍ ነህ"፣ "አስቸጋሪ ልጅ ነው" ፣ "መማር አይፈልግም" የሚሉትን ቃላት ደጋግሞ ሰምቷቸዋል።


ሆኖም ግን እወነታው በተቃራኒ ነው።

እነኝህ ልጆች እንደውም የፈጠራ ችሎታቸው የላቀ ብሩህ ናቸው። የማወቅ ጉጉታቸውም አስገራሚ ነው። ጠያቂ ናቸው።

ምን ያድርጉ ታድያ?!


የአእምሮአቸው እምቅ ኃይል በህመሙ የፊጥኝ ታስሯል።


አፉ የታፈነ ሰው ሲያወራ እንደማይሰማን፤ ህመሙን አልፎ የእነሱን ብሩህ አእምሮ ማየት አዳጋች ነው።

📉 በዚህም የተነሳ


  • ከጤነኛ ልጅ አንጻር ህመሙ ያለባቸው ልጆች ፤ ትምህርት የማቋረጥ እድላቸው በሶስት እጥፍ ይጨምራል። ብዙዎች ተምረው አይጨርሱም።


  • ከእነኝህ መህል ደግሞ አስፈላጊውን የትምህርት እና የ ስነልቦና እገዛ የሚያገኙት እጅጉን አናሳ ናቸው።



👷 በስራ ላይ፡ ብልኹ ቸልተኛ ሰራተኛ።

እንደ ህጻናቱ ህመሙ ያለባቸው አዋቂዎች ፤ አእምሮአቸው ብሩህ ሆኖ በፈጠራ የተሞላ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን ያለ ህክምና ድጋፍ ብዙውን ጊዜ።


  • ስራን በተገቢው ሰአት ለማድረስ ይቸገራሉ።


  • ሀሳባቸውን መሰብሰብ ለእነርሱ ትግል ነው።


  • ስራ እንደለዋወጡ ነው።


  • ነገር ስለሚዘነጉ ፤ ሰው ስለማያስተውሉ ስራ ቦታ ያለ ማህበረሰባዊ ህይወት ላይ ሊቸገሩ ይችላሉ።


  • ቸልተኛ ስለሚመስሉ ሊገለሉ ይችላሉ።


ሁሉም ህመሙ ያለባቸው ስነፍ ወይም ቸልተኛ አይደሉም። አንዳንዶቹ ህመሙ ያመጣባችውን ተግዳሮቶች አልፈው ፤ እጅጉን ስኬታማ ሊሆኑ ይችላሉ ። ስራ ፈጣሪዎች፣ ዶክተሮች፣ ኢንጅነሮች፣ አርቲስቶች... ሆነው ሊገኙ ይችላሉ።


እንደማሰናከሉ ሁሉ ፤ ለውጤታማነታቸውም ህመሙ አስተዋእጾ ይኖረዋል።

የኢትዮጵያ እውነታ


ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው መረጃ ከሆነ ፤ ይህ ህመም እምብዛም አይታይም። ይሄ ግን የምሰራች አይደለም! ከማብሰራችን በፊት ለምን ብለን ብንጠይቅ መልካም ነው።


ለምን?


በኢትዮጵያ ውስጥ


❌በህመሙ ዙሪያ ላይ ምንም አይነት አገር አቀፍ መረጃ የለም።


❌ ህመሙን በህጻናት ላይ የሚያክሙ የህጻናት ስነልቦና ሐኪሞች ቁጥር በጣሙን ትንሽ ነው።


❌አስተማሪዎች ስለ ህመሙ ግንዛቤ የላቸውም።


❌ የ ህመሙ ምርመራ በትምህርት ቤቶች የለም።


❌ ህመሙ የልጁ ንዝዕላልነት/ ስንፍና፣ አልያም የወላጅ አስተዳደግ ፣ እንዲሁም ዋልጌ ባህሪ ተደርጎ ይወሰዳል።


❌ልጆቹም ትምህርት አቋርጠው ስለሚወጡ ፤ የሚያስተውል አካል ላይኖር ይችላል።


❌ቸልተኛ ልጅ ሆነ ቸልተኛ ሰው በባህላችን ንቀት ስለሚመስለን አንወድም። ከመረዳት ይልቅ እናገላቸዋለን።



💡 ታድያ ምን እናሻሽል?

🔎ግንዛቤያችን ፈጽሞ መሻሻል አለበት። የአእምሮ ጤና ማለት ዘርፈ ብዙ ነው። እብደት ብቻ አይደለም።


👨‍👩‍👧‍👦ወላጆች ስለህመሙ ማወቅ አለባቸው። ልጁ ህመሙ እንዳለበት ሊረዳ አይችልም። ከተጠራጠሩ የሰነ ልቦና ሐኪም ጋር ይዘው መሄድ ይኖርባቸዋል።


💊በስነ ልቦና ህክምና እና በሚሰጡ መድሐኒቶች የልጁ ውጤታማነት ሊሻሻል ይችላልና ፤ ወላጆች ህክምና ይዘው ለመሄድ ማመንታት የለባቸውም።


🧑‍🏫 የትምህርት ቤት ድጋፍ ያስፈልጋል። መምህራኖቻችን ስለ ህመሙ ማወቅ ይኖርባቸዋል። ህመሙ ያለባቸውን ልጆች እንዴት ማስተማር እንዳለባቸው መገንዘብ ይኖርባቸዋል።


👩‍💼 አሰሪዎች ስለ ህመሙ ቢያውቁ ውጤታማ ሰራተኞቻቸውን አያጡም። አሰራርን በመለወጥና የስራ ቦታዎችን በማሻሻል ፤ የእነኝን ህመምተኞች ብሩህ አእምሮ ለድርጅታቸው ትርፋማነት ሊጠቀሙት ይችላሉ።



ማሳረጊያ ነጥብ


ይህ ህመም የስንፍና ሆነ ተገቢ ያልሆኑ ባህሪያት ሰበብ አይደለም። ህመሙ ያለባቸው ሰዎች ራሳቸውን የመቆጣጠር አቅማቸው ስላልጠነከረ ፤ ተነሳሽነታቸው ዝቅተኛ ስለሆነ የሚመጣ ነው። የህመሙ መሰናክል ታማሚዎች ለራሳቸው የሚሰጡትን ቦታ አውርዶ ፤ ጭንቀት ውስጥ ይከታቸዋል።


ስለዚህም ተረድተናቸው ፤ ማገዝ አለብን።


የኛ በመረዳት ላይ የተመሰረት ትንሽ ተግባር ፤ ለእነሱ ህይወት ቀያሪ ሊሆን ይቻላል።



2 Comments


Guest
Jun 18

At Couponzatps, we're dedicated to helping you find the best First Line Pods discount code so you can enjoy premium vaping pods without overspending. In a competitive market alongside brands like JUUL, Vuse, and SMOK, First Line Pods stands out for its smooth flavor and reliable quality. Couponzatps verifies each cataloged First Line Pods discount code, removing expired or faulty offers to ensure a seamless checkout experience. Trust Couponzatps to deliver genuine savings—discover your ideal vape pods today with confidence.

Like

Guest
Jun 18

UAND Solutions specializes in SuiteScript development, offering tailored NetSuite automation and customization services to streamline business operations. With deep expertise in SuiteScript development, UAND Solutions helps clients create custom workflows, scripts, and business logic that enhance NetSuite’s native functionality. Whether it’s client-side, server-side, or scheduled scripting, their team delivers efficient, scalable solutions aligned with your unique business processes. UAND Solutions ensures seamless integration, increased productivity, and long-term support for businesses looking to fully leverage their NetSuite ERP platform.

Like
bottom of page