top of page

የኩላሊት ጠጠር መንስኤዎች እና መከላከያ መንገዶች

 አንድ ቀን ከጓደኞችዎ ጋር ወጥተው እየተዝናኑ ነው እንበል ፤ ድንገት ከባድ የሆነ የሚሰነጥቅ ቁርጠት/ ውጋት ከእንብርትዎ በታች ያለውን ሆድዎን ቢያናውጠውስ? ይህ ዱብዳ የሆነ ህመም የማያስቆም የማያስቀምጥ እጅጉን ጠንካራ ቢሆንስ? እርስዎንም በዙሪያዎ ያሉትንም እንዴት ይረብሽ?  ምንም ያጋጠምዎ አደጋ የለም። የበሉትም ምግብም አይደለም። የሚያሰቃይ ህመም ብቻ!


ይህ ህመም የኩላሊት ጠጠር ህመም ሊሆን ይችላል። ህመሙ ያጋጠመበት ስፍራ ይለያይ እንጂ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ቀናቸውን አቅውሷል፣ እንቅልፍ አሳጥቷል ፣ሰላማቸውን ነፍጓል። እንደ አሴረ ጠላት ህመሙ በሽምቅ ነው የሚያጠቃው። ያልታሰበ ጊዜ ፣ ያልታሰበ ስአት ድንገት ለመግለጽ የሚያዳግት ህመም። ሲሸኑ ያለውን ህመም ፍራቻም ሽንትቤት መሄድ የጠሉም አይጠፉም።



🧊 ታዲያ የኩላሊት ጠጠር ምንድነው?


የኩላሊት ጠጠር ስሙ እንደሚያመላክተው ኩላሊት ውስጥ የተገኘ ጠጠር የሚያመጣው ህመም ነው። ታድያ ይህ ጠጠር ከየት መጣ?


ኩላሊት ጠጠር ኩላሊት ውስጥ የተከማቹ ማዕድናት፣ጨዎች እና አንዳንድ ንጥረ ነገሮች ፤ በጊዜ ብዛት የሚሰሯቸው ጥቃቅን ጠጠሮች ናቸው። አሸዋ ማህል እንደምናገኛችው ደቃቅ አንጸባራቂ ጠጠሮች አርገው መውሰድ ይችላሉ። ብዙ ጊዜ እነኚህ ጥቃቅን ጠጠሮች የሚሰሩት በ ካልሺየም ኦክሳሌት ፣ ዩሪክ አሲድ እና ስትሩቫይት በሚባሉ ውህዶች ነው።



ጥቃቅንነታቸው አያታልዎ። ህመማቸው ግን ፈጽሞ እንደጥቃቅንነታቸው አይደለም። እንደ አሸዋ የላሙ ወይም እንደ ድንጋይ አንኳር ቢያክሉም እንኳን ፤ በጠባቡ የ ሽንት ቱቦ (ureter) ከሽንት ጋር ተደባልቀው ሲያልፉ ፤ እጅጉን ከባድ ህመም ያመጣሉ። ህመሙም እነኝህ ጠጠሮች ጠባቡን የሽንት ቱቦ ሲዘጉት ፤ ሰውነታችን እነሱን ገፍቶ ለማሳለፍ በሚያደርገው ጥረት የሚፈጠር ነው።


የዚህ ጥረት ውጤት ግን እጅጉን ከባድ ህመም ነው። ህመሙ የሰው ልጅ ከሚያጋጥማቸው ከባድ ህመሞች ተርታ የሚመደብ ነው።


ታድያ ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?


ከኩላሊት ጠጠር ምልክቶች በጥቂቶቹ


  1. ከባድ ቅጽበታዊ የመቁረጥ/የመውጋት ህመም ይሰማናል። ህመሙ በዋነኝነት የሚሰማው ከ እንብርታችን በታች ባለው ሆዳችን ክፍል በተለይም በጎን አከባቢ ነው። ይህ ህመም የታችኛው ጀርባችን ላይም ሊሰማ ይችላል።


  2. ህመሙ በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ ፤ ሊያቅለሸልሽ እንዲሁም ትውከት ሊያመጣ ይችላል።


  3. ሽንት ቶሎ ቶሎ የመምጣት ፍላጎት ሊኖር ይችላል።


  4. ሽንት ሲሸኑ ከባድ ህመም ሊኖር ይችላል።


  5. ሽንት ደም ሊቀላቅል ይችላል። አንዳንዴም አሸዋ መሳይ ጠጠሮች ተደባልቀው ሊወጡ አልያም ሽንት አፈር ሊመስል ይችላል።


  6. ተጨማሪ ኢንፌክሽን ካለ ሽንት አመዳማ መልክ ሊኖረው ወይም ሽታው ሊተነፍግ ይችላል።



ታድያ እነኝህ ምልክቶች ከተሰማዎ አስኪሻልዎ አይጠብቁ። በቅርብዎ ያለ የጤና ተቋም ሄደው ህክምናን ያድርጉ።


ትናንሾቹ ጠጠሮች በራሳቸው ሊወጡ ሲችሉ ትላልቆቹ ግን ህክምና ያስፈልጋቸዋል። እንዳሉበት ቦታ እና ሁኔታ በሰርጀሪ ወይም በሚያደቅ ሞገድ (ECSWT) ሊታከሙ ይችላሉ።

🩺 የኩላሊት ጠጠር ለምን ይከሰታል?


እነኝህ ጠጠሮች የሚከስቱት ፤ ኩላሊት ውስጥ የሚከማች የማእድናት፣ የጨዎች እና የ ሌሎች ንጥረነገሮች/ውህዶች ዝቃጭ ሲበዛ ነው። ይህ በተፈጥሮ ኩላሊት ሊያስወግደው የሚችል ቢሆንም ፤ ሰውነታችን የሚያስወግድበት አቅም በተለያየ ምክንያት ሲሰናከል ኩላሊት ጠጠር ያመጣል።



በኢትዮጵያ ውስጥም የኩላሊት ጠጠርን እያመጡ ያሉ ዋነኛ መንስኤዎች የሚከተሉት ናቸው።


የውሀ እጥረት ዋነኛ መንስኤ ነው። ሞቃታማ ክልሎች ላይ የሚኖሩ ሰዎች ብዙ የጉልበት ስራ የሚሰሩ ሰዎች ፣ እንዲሁም የሚጠጡት የውሀ መጠን ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎች ሰውነታቸው ውስጥ ያለው የውሀ መጠን ስለሚመናመን ፤ ኩላሊታቸው ውስጥ የሚከማቸውን ዝቃጭ ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ይቸገራሉ። ይህም ደግሞ ጠጠሮቹ እንዲፈጠሩ መሰረት ይጥላል።


እርስዎስ በቀን ምን ያህል ሊትር ውሀ ይጠጣሉ?

✅ ከፍተኛ የፕሮቲን መጠን ያላቸውን ምግቦች መመገብም ይህን ጠጠር ያመጣል። በጣሙን ስጋ ተመጋቢ ማህበረሰብ እንደመሆናችን ፤ አመጋገባችን የኩላሊት ጠጠር ዋነኛ መንስኤዎች ውስጥ ይጠቀሳል። ብዙ ስጋ ስንመገብ ሰውነታችን ውስጥ የ ዩሪክ አሲድ መጠን ይጨምራል። ይህም ኩላሊት ላይ ክምችቱ ሲበዛ የኩላሊት ጠጠር ያመጣል።


✅ጨው የበዛበት ምግብ ስንመገብ ፤ በሽንት በኩል የምናወጣውን የካልሺየም ማዕድን እንዲጨምር ይሆናል። ይህ ደግሞ ከሌሎች ንጥረ ነገሮች ጋር እየተደባለቀ ጠጠር ይሰራል።


✅ ከዚህም ባሻገር ቸኮሌት አብዝተን ስንመገብ፣ ልውዝ፣ ስፒናች፣ ቀይስር አይነት በኦክሳሌት (oxalate) ንጥረነገር የበለጸጉ ምግቦችን ስናዘወትር ለኩላሊት ጠጠር የመጋለጥ እድላችን ይጨምራል።


✅ ከእነኝህም በተጨማሪ የቤተሰብ ታሪክ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት እና ኢንፌክሽኖች እንደ መንስኤ ይጠቀሳሉ።



💡 የኩላሊት ጠጠርን መከላከል ይቻላል?


አዎ! በደንብ። ከላይ እንደተመለከቷቸው የኩላሊት ጠጠር አምጪ መንስኤዎች አብዛኞቹን መከላከል ይቻላል።



ምን ያድርጉ መሰልዎ


1. ዉሀ በበቂ መጠን በየቀኑ ይጠጡ። ሽንትዎ መጥቆር ወይም በጣም ቢጫ ከሆነ ፤ የውሀ መጠንዎ ቀንሷል ማለት ነው ስለዚህ ውሀ ይጠጡ። በትንሹ ከ2.5 እስከ 3 ሊትር ውሀ እንዲጠጡ ይመከራል።


  1. አመጋገብዎ ላይ የጨው እና የ ስጋ መጠንን ይገድቡ።


  2. በኦክሳሌት ንጥረ ነገር የበለጸጉ ምግቦችን (ቸኮሌት፣ ለውዝ፣ ቀይስር፣ ወ.ዘ.ተ) አያዘውትሩ


  3.  ጤናማ ክብደትን ለመጠበቅ አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ።


  4. ህመም ምልክት እስኪያጋጥምዎ አይጠብቁ። በየተወሰነ ጊዜ መደበኛ ምርመራን ያድርጉ።


መቼም ቢሆን ለመከላከል አይስነፉ!

ያልታከመ ኩላሊት ጠጠር ለኩላሊት ድክመት እንደሚያጋልጥ ይወቁ።


🔚 የተግባር ጥሪ


አሁን ምክንያቱን አውቀዋል። ምልክቶቹን ተረድተዋል። መከላከያ መንገዶቹንም ተገንዝበዋል።


የሚቀረው ብቸኛ ነገር የእርሶ ተግባር ነው።

👉እስኪያምዎ አይጠብቁ በተግባራዊ ለውጥ ጤናዎን ይጠብቁ።




Comments


bottom of page