top of page

ለብርድ ህመም ፍቱን መድሐኒቱን ያውቃሉ?

መቼም ከሙቀት ወደ ቅዝቃዜ ሲወጡ ብርድ እንዳይመታኝ ብለው ፈርተው ያውቃሉ። አንዴም ሆነ ሌላ ጊዜ ታሞ የሚያውቅ ሰው ፣ ወደ ቀዝቃዛ አየር ሲወጣ ብርድ እንደሚመታ እርግጠኛ ነው። ለዚህም ከእራሳችን አልፈን ሌላ ሰው ስንመክር ፤ ብርድ እንዳይመታህ/ሽ እንላለን። ይህ አነጋገር ባብዛኞቻችን ወይ ብለነዋል ወይ ሰምተነዋል። ለቀዝቃዛ አየር፣ ለንፋስ ወይም ለዝናብ ሰውነታችን ሲጋለጥ ፤ ይህ የበረደ አየር ወደ ውስጥ ገብቶ በሽታ እንደሚያመጣ ብዙዎች ያስባሉ። ህመሙም ቀላል ባለመሆኑ ፤ በመላምታቸው እርግጠኛ ናችው። በተለምዶ ብርድ ሲያም :-

  • ደረት ይወጋል

  • ያስላል (የጠነከረ ሳል)

  • ሰውነት ይዳከማል ወይም ይዝላል

  • ትኩሳትም አንዳንዴ ሊኖረው ይችላል


የበሽታ አምጪ ሰበቡም ቀዝቃዛ አየር ተደርጎ ስለሚወሰድ ፤ የተለምዶ ህክምናው ልብስ መደረብ፣ መስኮት መዝጋት ፣ ትኩስ ነገር መጠጣት ናቸው። እንደውም አንዳንዴ ሳሉ ጠንከር ካለ ፤ በጠዋት ማር በእንቁላል ውሰድበት የሚልም አይጠፋም።


እውነት ብርድ የሚባል በሽታ አለን?


በተለምዶ ብርድን የምንረዳው እንዲህ ቢሆንም ፤ በ ዘመናዊ ህክምናው ብርድ የሚባል በሽታ የለም። አብዛኛው ሰው እንደሚያስበው ፤ አየር የበሽታ አምጭ ተህዋስ መሆን አይችልም። የበሽታ አምጪ ተህዋስን ግን መሸከም ይችላል።


የብርድ ህመም ብለን የምንጠራው ፤ የተለያዩ በሽታዎች ስብጥር ነው። እነኝህ ህመሞች በተለይም የላይኛው የትንፋሽ ቧንቧ ክፍል ያሳምማሉ ወይም ያጠቃሉ። ከአየር ቧንቧም ባሻገር የጡንቻ ህመም ሆነ የጀርባ አጥንት ህመም ሲሰማም እራሱ ፤ ብርድ መቶኝ ነው ብሎ ማሰብና ከቀዝቃዛ አየር ጋር ማዛመድ እጁጉን ተለምዷል።


ይብሱኑ በሆስፒታል የጋራ መኝታ ክፍሎች ውስጥ ያሉ ታማሚዎች ፤ በዚህ የተሳሳተ አስተሳሰብ ተመስርተው ፤ ብርድ እንዳይመታቸው ፤ መስኮቶች እና በሮችን ጥርቅም አድርገው ይዘጋሉ። በተመሳሳይ ሁኔታ በሳል ህመም የታመመ ሰው ታክሲ ውስጥ ሳሉ እንዳይብስበት ፤ ብርድ እንዳናስመታው አሳስቦ መስኮት እንድንዘጋ አጥብቆ መጠየቁ አይቀርም።


ይህ ደግሞ ታላቅ እርማት የሚያስፈልገው ተግባር ነው።


ግን ይህ መላምት እንዴት መጣ? 


እውነት ለመናገር ይህን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ፤ በብዙ ባህሎች ያለ አስተሳሰብ ነው።  የኛን ሀገር እነኚህን ከቅዝቃዜ ጋር የተገናኙ ህመሞች ብርድ የሚል ስያሜ ሰጠናቸው እንጂ ፤ በአውሮፓ፣ በእስያ እና በላቲን አሜሪካም ተመሳሳይ እምነቶች አሉ።



ለምን?


ምክንያቱም እነኝህ ማህበረሰቦች እንዳስተዋሉት ከሆነ ቀዝቃዛ አየር እና ህመም ብዙውን ጊዜ በተመሳሳይ ወቅት ይመጣሉ። ለምሳሌ የጉንፋን ህመም ከሚንሰራፋባቸው ጊዜያት መሀል የዝናብ ወራት ናቸው። የአለርጂ ህመም በበኩሉ እንደ ጥቅምት እና ህዳር ያሉ ነፋሻ ጊዜያት ላይ ሊጨምር ይችላል።


 

እንዴት ቀዝቃዛ አየር ለህመም ያጋልጣል?


የእነኝህ ማህበረሰቦችም መላምት እውነት አለው።


  • በቅርብ የወጡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ቀዝቃዛ አየር የሰውነት በተለይም የትንፋሽ ቧንቧን የበሽታ የመከላከል አቅም ይቀንሳል። በፊት በእንሰሶች ላይ የተረጋገጠ ቢሆንም ፤ በቅርብ በሰዎች ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያመላክተው ደግሞ ፤ አፍንጫችን ሆነ የላይኛው የትንፋሽ ቱቦ ከሰውነት ሙቀት በ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ የሙቀት መጠኑ ከቀነሰ ፤ የትንፋሽ አካላት የበሽታ የመከላከል አቅም በግማሽ ይወርዳል። ይህም ደግሞ ለበሽታ የመጋለጥ እድሉን ያሰፋል።


ይህ ብቻ ለህመሙ አጋላጭ ቢሆን ኖሮ ፤ በህመሙ አንደኛ የሚጠቁት በረዶአማ አከባቢ የሚኖሩ ፈረንጆች ነበሩ። ሆኖም ግን አብዛኞቹ በሽታ አምጪው ተህዋስ ቅዝቃዚው ስለሚገላቸው ፤ ተጠቂነቱ ይቀንሳል።


  • እዚህ ላይ ይብሱኑ ብለን ደግሞ ፤ በእነኝህ ቀዝቃዛ ወራት ፤ ቅዝቃዜን ሸሽተን ሙቀትን ፈልገን ፤ አብዛኛውን ጊዜ የምናሳልፈው በቤታችን ወይም በመዝናኛ ቦታዎች ተሰብስበን ነው። ይህ ባህሪ መልካምነት ቢኖረውም ፤ አየር ስለማይዘዋወር ፤ በትንፋሽ የሚተላለፉ በሽታ አምጪ ተህዋሳት በቀላሉ እንዲሰራጩ እድል ይከፍታል። ለምሳሌ አንድ ታክሲ 13 ሰው ይይዛል። ከ እነኝህ ተሳፋሪዎች ውስጥ አንዱ ጉንፋን ይዞት ቢሆን ፤ መስኮቶች ከተዘጉ ሁሉም ተሳፋሪ ለ ጉንፋን አምጪው ቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ ይጋለጣል። ታድያ ግን በጉንፋን መያዛችን ወይም ሳንባ ምች መሆኑ የሚወሰነው ፤ ባለን የበሽታ የመከላከል አቅም ልክ ነው።



ይህ የሳል ህመም ያለበት ሰው የታመመው ሳንባ ነቀርሳ ቢሆንስ ?


  • ከዚህም ባሻገር አበቦች በሚያብበት ጊዜ ያለ ደረቅ ነፋሻማ አየር ፤ አብሮት የተለያዩ ብናኞችን (በተለይ የአበባ ብናኝ) ይዞ ስለሚመጣ ፤ እንደ አስም እና ሳይነስ አይነት ህመም ያለባቸው ሰዎች ህመማቸው ይባባሳል።


እዚህ ጋር ማስተዋል ያለብን ፣ ቀዝቃዛ አየር አይደለም ብርድን የሚያመጣው። እንደውም ብርድን ለመሸሽ የምናደርጋቸው ባህሪያት ፣ በጋራ የምንጠቀምባቸው መመገቢይ ቁሶች ላይ ያለው ባክቴሪያ ወይም ቫይረስ ነው።

የመተንፈሻ አካልን የሚያጠቁ ቫይረሶች: - እንደ ራይኖቫይረስ ፣ ኮሮና ቫይረስ፣ የኢንፍልዌንዛ ቫይረስ፣ ወ.ዘ.ተ ፤ ወደ ትንፋሽ አካሎቻችን ከገቡ ፤ ለማራባት አመቺ ሁኔታን ይፈልጋሉ። ሰውነታችን ከተቋቋማቸው ምንም ምልክት ሳይኖረው ይጠፋሉ።


ሆኖም ግን ኢንፌክሽን ከፈጠሩ ፤ ጉሮሮአችን ይቆስላል ፣ ትኩሳት ይኖረናል ፣ ድካም ይሰማናል። የታችኛው የትንፋሽ ቧንቧን ካስቆጡ ደግሞ ፤ የበረታ ሳል ፣ አክታ፣ የደረት ህመም (መውጋት) አይነት ምልክት ልናሳይ እንችላለን። እነኝህ ምልክቶች ሰውነታችን ከኢንፌክሽን አምጪ ተህዋስ ጋር እያደረገ ያለውን ግብግብ የሚያሳዩ እንጂ ፤ አየር ቆዳዎትን አልፎ ደረትዎ ውስጥ ወይም ሆድ እቃዎ ውስጥ ገብቶ ፤ የሚመጡ አይደሉም።


ስለዚህ አየር እንዲንቀሳቀስ በማድረግ፣ መስኮት በመክፈት፣ በሽታ አምጪ ተህዋሱ እንዲወጣ በማድረግ እራስዎን ሊጠብቁ ይችላሉ።


ቀዝቃዛ አየር ሳያጋጥምዎ እንዴት ብርድ መታኝ ብለው የሚያውቁ ከሆነ ፤ ምክንያቱ ከላይ የጠቀስነው ነው እንጂ ፤ እንቅልፍ ላይ ሆነው ተገላልጠው የመጣቦት ህመም አይደለም ።

እንዴት እናስታርቀው ታድያ?


የብርድ የምንለው በሽታ ባይኖርም ፤ የህመም ምልክቶቹ ግን እውነት ናቸው። ህመሞቹን ደግሞ መከላከል ይቻላል።


✔️ ለኮቪድ ጊዜ ያደርጉት እንደነበረው አይነት ጥንቃቄን ቢያደርጉ ፤ እጅ መታጠብ ፣ የሳል ህመም ካለብዎ ጭምብል መልበስ ፣ ከታመሙ ሰዎች ጋር ያሎትን ቅርበት መቀነስ እንድንከላከለው ያግዛል።


✔️በተለይ በተለይ ሰው የተሰበሰበት ክፍል ውስጥ መስኮት እና በር ዘግተው ፤ የአየር እንቅስቃሴን ፈጽሞ አይገድቡ።  አየር ከታፈነ ፤ የሳንባ ነቀርሳን ጨምሮ ለብዙ የአየር ቧንቧ ህመሞች ሊጋለጡ ይችላሉ።


ትክክለኛው አደጋ ነፋሱ/ ቅዝቃዜው ሳይሆን እራስን አለመጠበቅ ፤ ህመም ምልክት ሲያሳዩ ፤ ህክምና አለመፈለግ ነው።

ስለዚህ ከዛሬ በኋላ ...

 

የብርድን ትርክትን እናርም።


የተግባር ለውጥ ያስፈልጋል።


ሙቀትንም መሻታችን መልካም ቢሆንም አየር እንቅስቃሴ አለመኖሩ ለትንፋሽ ህመም ያጋልጣል።


አየሩን ሳይሆን ቫይረሱን እንሽሽ።

 

Comments


bottom of page