top of page

እናቶችን በተግባር እናመስግን

የዛሬ አስር አመት በፊት  ገደማ  አንዲት በገጠሪቷ ክፍል የምትገኝ እርጉዝ እናት ፤ የመውለጃ ጊዜዋ ይደርስና አዋላጆች ይጠራሉ። እንዳሰበችውም ከቤቷ ትወልዳለች። የወለደችው ልጅ ጤነኛ ቢሆንም ፤ የእንግዴ ልጇ አልወጣም ነበር። በዚህም የተነሳ ከማህጸኗ የማያቁርጥ ደም ይፈሳት ጀመር።  
ይች ምስኪን እናት ህይወት ሰጥታ ፤ ህይወቷ አደጋ ላይ ወደቀ። የምጥ ጊዜዋ አልቆ ፤ የልጇን ለቅሶ ሰምታ ህመሟ የሚታገሰው ፤ ቁስሏ የሚሽር እናት ፤ ህመሟ ተራዘመ።  በሁኔታው የተደናገጡ ቤተሰቦችም ፤ በአፋጣኝ ወደ ህክምና ተቋም ይዘው መሄድ እንዳለባቸው ወሰኑ። 
ይህንን ህመም የአከባቢው ሰዎች ያውቁታል። ብዙ እናቶችን ሰርቋቸዋል። ታድያ ሀሳብ የገባቸው የአከባቢው ሰዎች ፤ ይቺን ምስኪን እናት ከ ቃሬዛ ጭነው ፤ መንገድ ጀመሩ።  ግን ይህ የእናት ሌባ እንዳይቀማቸው ፤ ይችን እመጫት እንዳያስቀር ፤ በጥይት ጓጓታ እና በቆርቆሮ ኳኳታ ሌባውን እያስፈራሩ ይዘዋት ሄዱ።  
በቅርብ ያለ ጤና ጣቢያም እንደደረሱ አፋጣኝ የህክምና እርዳታ በማግኘቷ ይችህ ሞት አፋፍ ላይ የነበረች እናት ህይወቷ ሊተርፍ ቻለ። እሷም ይኽው  ታሪኳን ለመተረክ በቃች።

ይህንን ታሪክ ለማስቀረት ባለፉት አመታት ውስጥ ብዙ ተሰርቷል። ሆኖም ግን በቤታቸው ሲወልዱ ፤ ከዚህም የከፋ እድል ያጋጠማቸው እናቶች ዛሬም አይጠፉም።


ይህ የኢትዮጵያ እናቶች ታሪክ ነው።


በዛሬዋ የ እናቶች ቀን ፤ አለም በድሎት ላይ ሆኖ በአበቦች እና ባማሩ ስጦታዎች ታጅቦ ሲያከብር ፤ እኛ ደግሞ ጤናማ ፣ ከወሊድ ጋር በተያያዘ እናት የማትሞትባትን ኢትዮጵያ ለእናቶቻችን ማበርከት ተስኖን ይኸው እንገኛለን።

አንድ እናት ኢትዮጵያ ውስጥ


በእርግዝና ባበጡ እግሮቹዋ ረዝም እርቀቶችን ትጓዛለች ፤ የጉልበት ስራን ትሰራለች።


ሞትን ተገዳድራ ለልጇ ህይወት ትሰጣለች።


አለም ላይ ያለ ችግር ቢጫንባትም እንኳ ፤ ያለመታከት ከልጇ ጎን ትቆማለች። በጭንቅ ውስጥ ሆና ለልጇ ፈገግ ትላለች።


ይህ የኢትዮጵያውያን እናቶቻችን ያልተወሳ ጀግንነት ነው።



የእናትነት ስጋት


በኢትዮጵያ ውስጥ መንግስት ሆነ ባለድርሻ አካላት የእናቶችን ህይወት ለማሻሻል ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል ፤ እያደረጉ ይገኛል። የዛሬ 34 አመት እ.ኤ.አ. በ 1990 በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚወለዱ 100 000 ህጻናት 1400 እናቶች ይሞቱ ነበር።



ባለፉት አስርት ዓመታት  የእናቶችን ጤና አገልግሎት ለማሻሻል ብዙ የተሰራ ቢሆንም ፤ አሁንም እናትነት ትልቅ የህዝብ ጤና ስጋት ሆኖ ቀጥሏል።


  • እ.ኤ.አ. በ 2022 በ EDHS መሠረት በህይወት ለሚወለዱ 100 000 ህጻናት 267 እናቶች ይሞታሉ ። ይህ ቁጥር ከበፊቱ እጅጉን የቀነሰ ቁጥር ቢሆንም ፤ ትንሽ ግን አይደለም። በኢትዮጵያ የህዝብ ብዛት ካሰላነው ፤ በ አመት ውስጥ ወደ 12 ሚሊየን ልጆች ይወለዳሉ። ይህ ማለት በዚህ አመት ብቻ ፤ 32 000 የሚጠጉ እናቶች ህይወት ሊሰጡ ህይወት ያጣሉ። 32 000 ልጆች እናቶቻቸውን ሳያውቁ ያድጋሉ ።


እስቲ ያስቡት ፤ ከእነኝህ ጨቅላ ህጻናት ውስጥ አንዱ እርሶ ሆነው ቢሆኑስ ?

  • በኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም ከ40% በላይ የሚሆኑት እናቶች በቤት ውስጥ ይወልዳሉ። የሰለጠነ የህክምና እርዳታ ስለማያገኙም ፤ ህይወታቸው አደጋ ላይ ነው። ንጹህ ውሀና ኤሌክትሪክ በሌለበት የሚወልዱትስ?


  • በእርግዘና ወቅት የሚፈጠሩ ህመሞች እንደ ደም ግፊት(preeclamcia) ፣ የስኳር ህመም ፣ እንዲሁም የደም ማነስ(anemia) ቀድሞ ለማወቅ ፤ የተሟላ የቅድመ ወሊድ ክትትል ያስፈልጋል። ሆኖም ግን አስፈላጊ የሆነውን አራት የቅድመ ወሊድ ክትትል የሚያደርጉ እናቶች 43% ብቻ ናቸው።


እነኝህ ቁጥሮች እናቶች የሚያጋጥማቸው ተግዳሮቶች የሚያሳዩ ፤ ቅንጫቢ እውነታዎች ናቸው። ሆኖም ግን ይሁ ሁሉ ቢደራረብባት የኢትዮጵያ እናት ፤ ለልጆቿ እና ለቤተሰብዋ ስትል ትጀግናለች። ፈገግ ትላለች።



ማንም የማያየው ጥንካሬ

ይህን ጥንካሬዋን ማንም አያይላትም ። ጀብዱ የለውምና ገሀድ አይወጣም። ሆኖም ግን በዝምታዋ ውስጥም ይች እናት ጀግንነት አላት።



  • የወለደ ሰውነቷ ሳይጠግን ፤ በደንብ ሳትታረስ ወደ ስራ የምትመለስ እናት አለች።


  • እንቅልፍ የጣላቸውን ቤተሰቧን ላለመበጥበጥ ፤ ምጥዋን ለመታገስ የምትሞክርም እናት አለች።


  • አድራሽ ሰው ሆነ ትራንስፖርት አጥታ ፤ በምጥ ላይ ሆና ፤ ወደ ህክምና ተቋም በእግሯ የምትሄድ እናትም አለች።


  • በሾተላይ ልጆቿን አጥታ ፤ ሌላ ልጅ ለመውለድ ፤ ህይወቷን አደጋ ላይ ጥላ ፤ ግብ ግብ ላይ ያለች እናት አለች።


  • እላይ ከጠቀስናቸው እያንዳንዱ ቁጥሮች ጀርባ ፤ የቤቷ ማጀት የሆነች አንድ እናት አለች።


ባለፉት አመታት ብዙ አሻሽለናል። " እናት ለምን ትሙት" የሚል እንቅስቃሴ ጀምረን ፤ አለምን ያስደመመ ለውጥ አምጥተናል። የእናቶች ሞት ቀንሷል። የጤና ሰራዊቶች፣ ኤክስተንሽን ባለሙያዎች በየመንደሩ እርጉዝ እናቶችን እየቃረሙ ፤ ክትትል እንድታገኝ ለማድረግ ይሞክራሉ። በአንዳንድ ሆስፒታሎች የሚደረጉ የዘመኑ የስልክ እና የጽሁፍ መልእክቶች ፤ እናቶች የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤ እንዲያደርጉ በማስታወስ ፤ ክትትል እያሻሽሉ ይገኛሉ።


ግን አሁንም እናቶች ስጋት አለባቸው።


አስፈላጊው ለውጥ


  • የኢትይጵያ የጤና ሚኒስተር በ2030 የእናቶችን ሞት ወደ 140 ለመቀነስ ፤ እቅድ አውጥቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተረባረበ ይገኛል።


  • መሀል አዲስ አበባም ሆነ መንገድ የሌለበት ገጠሪቷ ኢትዮጵያ ላይ ያለች እያንዳንዷ እናት ፤ በወሊድ ዙሪያ በሰለጠነ ባለሙያ መታከም ይኖርባታል።


  • እንደዚህ ርቀው በሚገኙ አከባቢዎች ላሉ እናቶች ፤ በወሊድ ጊዜ መጠበቂያ ቤቶች እና የድንገተኛ ጊዜ እንክብካቤ ማዕከሎችን ማስፋፋት መቻል አለብን።


  • የእናቶችን እንክብካቤ ተድረሽነት ለመጨመርም ፤ የ ዘመኑ የዲጂታል መሳሪያዎችን መጠቀም ይኖርብናል።


እርስዎስ?


በቅርብዎ የምትገኝ እርጉዝ እናት አለች?


  • እንግዲያውስ የወሊድ ክትትል ሳታቋርጥ እንድታደርግ ፤ የዶክተሮችዋን ምክር በስርአት እንድትተገብር ይምከሯት።


  • ቤተሰብዎ ወይም በጎረቤትዎ እርጉዝ እናት ካለች ያግዟት። የመውለጃዋ ሰሞን ሲቃረብ ወደ ጤና ተቋም የሚወስድ ትራንስፖርት እንድታዘጋጅ ይምከሯት። ካልቻለች እርስዎ ያዘጋጁላት።


  • ወሊድዋ በ ጤና ተቋም እንዲሆን ይገፋፏት።


  • ከዚህ በኋላ እነኝህ ጀግና እናቶቻችንን በ አስፈላጊው የጤና እርዳታ ማገዝ አለብን። እናቶቻችን በ እናቶች ቀን ብቻ አበባ የምናበረክትላቸው ፣ በሚያምሩ ቃላት የምናጅባቸው አይሁን ።


  • በተግባር በእርግዝናቸው ፣ በወሊዳቸው እንዲሁም በ ድህረወሊድ ጊዜያቸው ጤናቸውን መጠበቁን እናረጋግጥ።




እንዲህ እንበላቸው ....


ውድ እናት ፣
ያለብሽን ድካም፣ እንግልት እና ፈተና ስረዳ ፤ ጥንካሬሽን አየሁ ። አንቺ የኢትዮጵያ ህዝብ የልብ ትርታ ነሽ።
ዛሬ በባዶ ቃል ሳይሆን በአዲስ ቃል ኪዳን ፣ እናከብርሻለን።
በተግባር ከጎንሽ ነን። እንደኖርሽልን እንኑርልሽ።
ከዚህ በኋላ ወሊድ ላንቺ ደስታ ብቻ እንጂ ስጋትን አያመጣም።


Comments


bottom of page