117 results found with an empty search
- ❗ሾተላይ
ልጅን ለመጠበቅ የተፈጠረው የ እናት ማህጸን ለጽንስ መሞቻ ሊሆን ይችላልን? አዎ, ለአብዛኞቻችን ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው። የእናትን ጤና ለመጠበቅ የተዘጋጀው የበሽታ መከላከያ ስርአት ፤ ለልጅ ሞት መንስኤ ሲሆን ማሰብ ከባድ ነው። ይህ ተረት አይደለም ? ሳይንሳዊ መላምትም? እርስዎም ስለዚህ ሰምተው ያውቃሉ። በተለምዶ ስሙ ሾተላይ ይባላል ። በህክምና ስሙ የአር ኤች አለመስማማት/አለመጣጣምን ተከትሎ የሚመጣው የሄሞላይቲክ ዲዚዝ ኦፍ ዘ ኒው ቦርን። ይህ በሽታ የ እናት የበሽታ መከላከያ ስርአት በማህጸን ውስጥ ያለውን ጽንስ ሲያጠቃ የሚፈጠር ነው። ጽንሱ ላይ ከባድ ጉዳት ከማድረስ ባሻገር ሞት ሊያደርስ ይችላል። ' የእናት በሽታ የመከላከል ስርአት በማህጸን ውስጥ ያለውን ጽንስ ፤ ድምጽ ሳያሰማ ሲያጠፋ የሚፈጠር ነው። ይህ የጤና እክል በዓይን ባይታይም ፤ ውጤቱ ግን እጅግ አሳዛኝ ነው። እናቶች ልጆቻቸውን ይሰረቃሉ። ስማቸውም ይጠለሻል። አንድ ታሪክ እናውራ። ታሪኩ የሆነው ከ አመታት በፊት ነው። በገጠሪቷ የኢትዮጵያ ክፍል የምትኖር አንዲች ሴት ፤ ገና የመጀመሪያ ልጇን እንዳረገዘች ድንገት ያስወርዳታል። በዚህ የተከፋች እናት ደግማ ለማርገዝ አልዘገየችም። ሆኖም ግን ሁለተኛ ልጇ ሳይወለድ ይሞታል። ይህች ጉጉ እናት ልቧ ቢሰበርም ፤ ደግማ ደጋግማ ብትሞክርም ፤ የልጆቿ እጣ ተመሳሳይ ይሆናል። ይህች ምስኪን እናት የመጨረሻ እርግዝናዋ ክትትል አዲስ አበባ ነበርና ፤ ለቀጣይ እርግዝና ቀድማ እንድትመጣ ትመከራለች። ታድያ በተመከረችው መንገድ ይህች እናት በክረምት ቀድማ የከሰል መኪና ላይ ተጭና ትመጣለች። ሆስፒታልም ተኝታ ክትትል ታደርጋለች። ክትትል እያደረገችም አንድ ቀን ድንገት የልጁ እንቅስቃሴ አልሰማ ሲላት ዶክተሮቹን ትጠራለች። ሀኪሞቹም በአልትራሳውንድ ሲያዩትም ጽንሱ ሞቷል። የሰባተኛ ጽንስዋ እጣ ተመሳሳይ ሆነ። ይህንን ሁሉ ስቃይዋን እና ህመሟን የሚያውቁ ባለሙያዎች ምን ያድርጉ? ለዚህች ተስፈኛ እናት ማን ይንገራት? ምን ይበሏት? ይህ የሾተላይ እናቶች እውነታ ነው። 🧬 ታድያ ሾተላይ ምንድን ነው? በተለምዶ ሾተላይ ያለባት እናት የተረገመች ፤ ልጆቿን የሚበላ/የሚጨርስ መንፈስ የተጠጋት ፤ ተደርጎ ነው የሚወሰደው። ለዚህም እነዚህ እናቶች ይገለላሉ። ባሎቻቸው ይፈቷቸዋል። ለትዳርም አይፈለጉም። ስማቸው የጠቆረ ነው። እውነት ሾተላይ የእናት ችግር ነውን ? ይህንን ለመመለስ መጀመሪያ ስለ ሾተላይ እንረዳ። ሰው ልጅ ካለው የደም አይነት መለያ ፕሮቲኖች መሀከል አር ኤች( Rh (Rhesus)) ፋክተር የሚባል የደም መለያ ፕሮቲን አለ። ይህ ፕሮቲን ያላቸው Rh-positive ሲባሉ ፤ የሌላቸው Rh-ነጌቲቭ ይባላሉ። ደሞ አይነትዎን ሲገልጹ ፖዘቲቭ እና ኔጌቲቭ የሚሉት ይህንን ነው። ለምሳሌ ኦ ፖዘቲቭ እና ኦ ኔጌቲቭ። ታድያ ሾተላይ የሚኖራቸው የአር ኤች ፋክተር የሌላቸው (አር ኤች ኔጌቲቭ) እናቶች ናቸው። እንዴት ይፈጠራል? አር ኤች ኔጌቲቭ የሆነች ሴት ባለቤቷ ኔጌቲቭ ከሆነ ፤ ሁለቱም ፕሮቲኑ ደማቸው ውስጥ ስለሌለ ችግር የለውም። ችግሩ የሚከሰተው አር ኤች ኔጌቲቭ የሆነች ሴት አር ኤች ፖዘቲቭ ከሆነ ሰው ስታረግዝ ነው። ይህም ሆዷ ውስጥ ያለው ጽንስ አር ኤች ፖዘቲቭ ሊሆን ይችላል። የእናትየው የበሽታ የመከላከል ስርአት አር ኤች ፕሮቲን በውስጡ ስለሌለው ፤ ይህን የደም ፕሮቲን አያውቀውም። ለዚህም ለእናቷ ሰውነት እንግዳ ይሆንበታል። ለዚህም የጽንሱ ደም ውስጥ ያለውን ይህንን ፕሮቲን ሲያገኝ ፤ የእናት ሰውነት በበሽታ አምጪ ተህዋስ እንደተወረረ ያህል ይቆጣል። ለዚህም ወራሪውን ፕሮቲን ለማጥፋት ፤ ጽኑስን ያጠቃል። ይጎዳል። ይገድላል። ይህ እንዲፈጠር የጽንስ ደም የእናት የበሽታ መከላከያ ስርአት ጋር መገናኘት አለበት። በተፈጥሮ ጽንስ ለእናት ሰውነት እንግዳ በመሆኑ ፤ ሰውነታችን ከእናት ህዋስት ለይቶ ነው የሚያስቀምጠው። የጽንስ እና የእናት ሰውነት ህዋሳት አይገናኙም ። ሆኖም ግን እናት በምትወልድበት ጊዜ/ ወይም ሲያስወርዳት የጽንስ ደም ህዋሳት ከእናት ደም ጋር ይደባለቃሉ። የዚህን ጊዜ የእናት ሰውነት የተወረረ ስለሚመስለው ፤ ወራሪ ሀይልን የሚያጠፋ መርዝ(antibody) ያዘጋጃል። ይህም መርዝ ይህንን ፕሮቲን ፈልጎ የሚደመሥሥ ነው። ታድያ ደሙ የተደባለቀው በወሊድ ጊዜ ስለሆነ ፤ የመጀመሪያው እርግዝና ያለችግር ይወለዳል። ሆኖም ግን በቀጣይ እርግዝናዎች ላይ ችግር ያጋጥማል። የጽንሱ የደም ህዋሳት በእናት በሽታ መከላከያ ይጠቃሉ። ለዚህም ጽንሱ የደም በሽታ ያጋጥመዋል። ሆዱ እና ደረቱ ያብጣል። በሽታው ሲብስም ጽንስ ማህጸን ውስጥ ይሞታል። ለዚህም ሾተላይ ያለባቸው እናቶች የመጀመሪያ እርግዝናቸው ላይ ችግር የለም። ቀጣይ እርግዝና ግን ፤ ያለ ህክምና እርዳታ የከፋ ይሆናል። ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት ከእነዚህ ሕፃናት መካከል ግማሽ የሚሆኑት በሕይወት አይተርፉም ። 📊 የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በደቡብ ኢትዮጵያ አርባምንጭ ዙሪያ ውራጃ የተደረገ የማህበረሰብ ጥናት እንደሚያመላክተው ፤ ከእርጉዝ ሴቶች ውስጥ 6.2% የሚሆኑት አር ኤች ኔጌቲቭ የደም አይነት አላቸው ። በቡሌ ሆራ ዩንቨርስቲ ሆስፒታል የተደረገ ጥናት በበኩሉ ከታዳጊ ሴቶች መሀክል 6.4% የሚሆኑት የደም አይነታቸው አር ኤች ኔጌቲቭ ነው ። ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ 10 ነፍሰ ጡሮች አንዷ የ አርኤች ነጌቲቭ የደም አይነት አላት። በወላይታ ሶዶ የተደረገ ጥናት ደግሞ 9.8 % ነፍሰጡር እናቶች የቀይ የደምሴል የሚያጠቃው አንቲቦዲ ደማቸው ውስጥ ተገኝቷል። ቡሎ ሆራ የተወለዱት ልጆች መሀከልም 14.3 ፕርሰንት የሚሆኑት ሲወለዱ ቢጫ ቆዳ እና አይን አሳይተዋል ። (ይህ የዚህ በሽታ መጠነኛ ምልክት ሊሆን ይችላል።) 💡 መከላከል ይቻላል። አዎ ሾተላይን መከላከል ይቻላል። አንድ መርፌ አንድ ሕይወት ያድናል። የእናትን የነገ የመውለድ ተስፋን ያለመልማል። ይህ መከላከያ መርፌ ፤ የእናት ሰውነት መርዛማ አንቲባዮቲክስ እንዳያመርት ያደርገዋል። ስሙም አንታይ ዲ ኢሚኖግሎቡሊን ነው። የእናቲቱ በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት የህጻኑን ቀይ ህዋሳት እንዳያጠቁ ይከላከላል። የደም አይነቷ ኔጌቲቭ የሆነ ሁሉም እናት ስለዚህ መርፌ ማወቅ አለባቸው። መርፌው መቼ መቼ ይሰጣል ? ✅ በእርግዝና ጊዜ 28 ሳምንት ላይ ✅ ከወሊድ በኋላ በ 48 ሰአት ውስጥ እንደገና ይሰጣል። (ይህ ግን ህጻኑ የደም አይነቱ ፖዘቲቭ ከሆነ ነው)። እናት የልጇ የደም ምርመራ ተደርጎ ይህ ማርከሻ መድሐኒት ካልተሰጣት ፤ ሰውነቷ ጽንሱን መቃወሚያ ስለሚያመርት፤ ቀጣይ እርግዝናዎች ይሰናከላሉ። 💉ታድያ መፍትሔው እያለ ለምን አሁንም በገጠር እና በከተማ ሾተላይ ያጋጥማል? የእርጉዝ እናቶች እና የባለቤቶቻቸው የግንዛቤ ጉድለትሳላለ ፤ አንዳንድ የጤና ሰራተኞች ጋር ያለ የግንዛቤ ክፍተት በመኖሩ፤ የዚህ መቃወሚያ መድሐኒት አለመገኘቱም ከተገኘም ዋጋው ለዝቅተኛ የማህበረሰብ ክፍል በመወደዱ ፤ አሁንም ሾተላይ እያጋጠመ ይገኛል። ⚠️ አንድ ነገር ቀረ ስለ ሾተላይ እና መከላከያ መንገዱ አሁን ግንዛቤ ጨብጠዋል። ታድያ ይህንን ለሌላ ማሳወቅ አለብዎ። ማንኛውም እናት የሾተላይ እጣ ሊያጋጥማት አይገባም።
- የማጅራት ገትር ህመም ምልክቶች እና መከላከያዎቹ
ለመሆኑ ስለ ማጅራት ገትር ምን ያህል ያውቃሉ? ለምንስ ማጅራት ገትር ተባለ? ብዙውን ጊዜ በህጻናት የሚታወቅ ህመም ቢሆንም ፤ ሁሉንም የእድሜ ክልል እንደሚያጠቃ ያውቃሉ? 📍 ማጅራት ገትር ምንድን ነው? ማጅራት ገትር በእንግሊዘኛ ስሙ ሜኒንጃይተስ(meningitis) ሲባል ፤ በአንጎልና በአከርካሪ ዙሪያ ያሉ ጠባቂ ሽፋኖች ወይንም ልባሶች(meninges) ፤ በተለያዩ በሽታ አምጪ ተህዋሶች ሲጠቁ የሚያጋጥም ኢንፌክሽን ነው። ይህም ኢንፌክሽን በባክቴሪያ፣ በቫይረስ፣ በፈንገስ፣ አልፎ ተርፎም ጥገኛ ተውሳኮች ምክንያት ሊመጣ ይችላል። ከሁሉም ግን በአደገኝነቱ በባክቴሪያ የሚመጣው ይብሳል። ይህ በሽታ ከደረጀ በሰዓታት ውስጥ እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል። ከበሽታው የተረፉት ሰዎችም ዘላቂ የአካል ጉዳት ሊኖርባቸው ይችላል። በሽታውን የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ህክምና ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህም የሕመም ምልክቶቹን መለየት ይኖርብዎታል።- ዋነኛ ምልክቶቹ ትኩሳት ከባድ ራስ ምታት የአንገት ግትርነት/ ማጅራት መገተር ግራ መጋባት ወይም እንቅልፍ ማጣት ወይም እንቅልፍ ማብዛት በዕድሜ በገፉ ሰዎች ላይ የህመም ምልክቶች ስውር ሊሆኑ ይችላሉ። 📍 የማጅራት ገትር በኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የማጅራት ገትር ሕመም ከተንሰራፋባቸው ሀገራት መሀል ትጠቀሳላች። ለዚህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ የማጅራት ገትር ሰንሰለት አገራት ውስጥ ትገኛለች። ይህም ሰንሰለት ከሴኔጋል ጀምሮ የተዘረጋ ሲሆን ፤ የማጅራት ገትር ወረርሽኝ በብዛት ያጋጥምበታል። ወረርሽኙ በብዛት የሚስፋፋው በደረቅ ወራት (ከ ታህሳስ እስከ ሰኔ) ባሉት ነው። አቧራ ፣ ነፋስና የተጣበበ መኖሪያ ለኢንፌክሽኑ ስርጭት ተስማሚ እድልን ይፈጥራሉ። የማጅራት ገትር ሰንሰለት (በቀይ ያሉት ወረርሽኙ የተስፋፋባቸው ሀገራት ሲሆኑ ፤ ኢትዮጵያም ተካታለች) ከዛሬ 3 አመት በፊት (እ.ኤ.አ በ2022 መጀመሪያ ላይ) የዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ ወረርሽኝ መከሰቱን ዘግቦ ነበር። በዚህም ጊዜ በኢትዮጵያ 11 ክልሎች የተጠረጠሩ 1,398 ታማሚዎች ሲገኙ 13 ሰዎች መሞታቸው ተረጋገጧል ወረርሽኙ በኦሮሚያ፣ ሶማሊና ደቡብ ክልል በይበልጥ ተስፋፍቶ ነበር። ይህ ብቸኛው ወረርሽኝ አልነበረም። በየጥቂት ዓመታት ደጋግሞ ፈጽሞ አለመጥፋቱን የሚያሳይ ወረርሽኝ ይከሰታል። ምንም እንኳን በብዛት ወረርሽኝ የሚያመጣው ሴሮ ግሩፕ ኤ የተባለው የሚኒንጆኮከስ (serogroup A meningococcus ) ባክቴሪያ ዝርያ ነው። ሆኖም ግን በቅርብ አመታት ሴሮ ግሩፕ ሲ( C), ደብሊው( W), እና ኤክስ (X) የሚባሉት ዝርያዎች በብዛት ወረርሽኝ እያመጡ ይገኛሉ። ከሚያጋጥሙ ተላላፊ በሽታዎች አንጻር ፤ የማጅራት ገትር ህመም መጠን አነስተኛ ቢሆንም እንኳ ፤ በየአመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ በበሽታው ይያዛሉ። የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ፤ በኢትዮጵያ ስርጭቱ ከወቅት እና ከመልክአምድራዊ ሁኔታ ጋር ይያዛል። ለምሳሌ ስርጭቱ በአዲስ አበባ እና በአማራ ክልል በ ታህሳስ ወር ሲያይል ፤ በኦሮሚያና በ ሲደማ በህዳር ወር ያይላል። በአፋር ፣ በደቡብ ክልል እና ትግራይ ደግሞ ፤ ወደ ሰኔ አከባቢ ስርጭቱ ይጨምራል። የልጆች ብቻ ህመም አይደለም ም። ሁሉንም እድሜ ክልል ያጠቃል። 👶 በሽታው የሚበረታባቸው ልጆች የማጅራት ገትር ህመም በብዛት በህጻናት ነው የሚታወቀው። ለማጅራት ገትር ህመም ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት በከፍተኛ የተጋለጡ ናቸው ። በሽታ የመከላከል አቅማቸው በደንብ ጎልብቶ አልጨረሰም። በትምህርት ቤቶች በተለይም በተጨናነቁ ክፍሎች ውስጥ የማጅራት ገትር የሚያመጡ ባክቴሪያዎች በቀላሉ ይሰራጫሉ። ከሁለት አመት በፊት(እ.ኤ.አ 2023) በጥበበ ጊዮን፣ በደብረ ታቦር ፣ እና በደብረ ማርቆስ ኮምፕሪኸንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች የተደረገ ጥናት እንደሚያመላክተው ፡ 85.8% ማጅራት ገትር የነበራቸው ህጻናት ትኩሳት ነበራቸው 71.2% የአንገት ወይም ማጅራት ግትርነት ነበረባቸው ከ4 ልጆች መሀል በአማካይ አንዱ ሞቷል አልያም ሆስፒታል ለረዥም ጊዜ ቆይቷል። ብዙ ጊዜ ወላጆች የልጆች ህመም በቀናት ውስጥ ሊባባስ እንደሚችል አይገነዘቡም። ህመሙ ፈጽሞ ጊዜ አይሰጥም። በቀናት ውስጥ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። 👨 🦱 ችላ የሚባሉት ጎልማሶች የማጅራት ገትር ህመም በአዋቂዎች ዘንድ እምብዛም አይነሳም። ጎልማሶች የበሽታ የመከላከል አቅማቸው የተሻለ በመሆኑ ፤ ተጋላጭነታቸው ይቀንሳል። ተጋላጭነታቸው ቢያንስም በማጅራት ገትር ይጠቃሉ። በእነርሱም ዘንድ የማጅራት ገትር ህመም መጠን እየጨመረ ይገኛል። በጎንደር ዩንቨርስቲ ሆስፒታልም የተደረገ የ 10 ዓመት ዳሰሳ ጥናት(2011- 2020) ይህንን ጠቁሟል። ጥናቱ እንደሚያሳየው ፡ ከታከሙ 3,683 አዋቂዎች መካከል 1.3 ፐርሰንቱ በባክቴሪያ ምክንያት የመጣ የማጅራት ገትር አሳይተዋል። ብዙ ታማሚዎች ከተለመዱት ትኩሳት እና ማጅራት ገትር ምልክት ይልቅ ፤ ለየት ያሉ እንደ ግራ መጋባት አይነት ምልክቶችን አሳይተዋል ። ከህጻናት አንጻር አዋቂዎች ወደ ሆስፒታል ለመሄድ ያመነታሉ። ህመሙንም እንደ ጉንፋን አድርገው ፤ እስኪብስ ቸል ሊሉት ይችላሉ። ታድያ ይህ ዋጋ ያስከፍላል ። እያንዳንዷ ሰአት ትርጉም አላት ። 👴 የሚረሱ ሰለባዎች አዛውንቶች በዕድሜ የገፉ ሰዎች የበሽታ የመከላከል አቅማቸው እየተዳከመ ስለሚመጣ ፤ የማጅራት ገትር የመያዝ እድላቸው የሰፋ ነው። የህመሙም ዳፋ በእነርሱ ያይላል። እድሜያቸው ከ 65 ዓመት በላይ ከሆኑ የማጅራት ገትር ካለባቸው አዛውንቶች ውስጥ እሰከ 30 በመቶ የሚሆኑት ፤ በህመሙ የተነሳ ሊሞቱ ይችላሉ። እዚህ ጋር አሳሳቢው ጉዳይ፤ በአዛውንቶች ላይ ህመሙን መለየት ሊከብድ ይችላል። አዛውንቶች የተለመዱትን የትኩሳት እና የአንገት መገተር ምልክት ላያሳዩ ይችላሉ። በእነኝህ ምልክቶች ፈንታ አንደበታቸው ሊንተባተብ ፣ ግራ ሊጋቡ ፣ የማስታወስ ችግር ሊያሳዩ ፣ ንቃት ሊቀንሱ ይችላሉ። አዛውንቶች የሌላ ሰው ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ስለሚሆኑ ፤ ለተንከባካቢያቸው እነኝህን ምልክቶች ከእርጅና ይልቅ በ ኢንፌክሽን ህመም የመጡ መሆናቸውን ላይረዳ ይችላል። ይህም የሚንከባከባቸው ሰው በቀላሉ ህመሞቹን ለይቶ ፤ ወደ ሆስፒታል ለመውሰድ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል። በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ድግሞ የህክምናው ተደራሽነት ውስን በመሆኑ ፤ ጤና ተቋም በሚደርሱበት ጊዜ ዘግይተው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን በጊዜ ከተገኘ እና አስፈላጊ ህክምና ከተደረገ ፤ ህመሙ ጉዳት ሳያደርስ ሊድን ይችላል። 🧪 አስፈላጊው ህክምና ይህ በሽታ ከተጠረጠረ ለማረጋገጥ ፤ ከደም ምርመራ ባሻገር ከአከርካሪ አጥንት የሚወሰድ የፈሳሽ ምርመራ ያስፈልጋል። ይህም በሽታ አምጪ ተህዋሱ መኖሩን ሊያመላክት ይችላል። ነገር ግን ህክምናው ይህ ምርመራ እስኪደርስ አይጠበቅም። ለታካሚ የሚሰጠውም የፀረ ተህዋስ መድሐኒት ፤ እንደተጠረጠረው ህመም አምጪ ተህዋስ በመጠኑ ሊለያይ ይችላል። ታድያ ይህ ህክምና በጊዜ ካልተደረገ ፤ በሽታው እስከ ሞት ሊያደርስ ይቻላል። እንደ አንዳንድ ጥናቶች ከሆነ ከታመሙት መሀከል ከ 20 እስከ 30 ፐርሰንት የሚሆኑት ሊሞቱ ይችላሉ። በሕይወት የተረፉት ሰዎች እራሱ ፤ ቋሚ ጉዳት ሊኖርባቸው ይችላል። ሞቱም ሆነ ዘላቂ ጉዳቱ እድሜያቸው በገፋ ታማሚዎች ላይ ያይላል። በእነኝህ ታካሚዎች ላይ ቋሚ የመስማት ችግር ፣ የማሰብ ችሎታ መዛባት ፣ የእንቅስቃሴ እና የመናገር እክልም ሊያጋጥማቸው ይችላል። 🛡️ እንዴት እንከላከለው? በክትባት መከላከል ይቻላል። ኢትዮጵያ ላይ በታየው ዋነኛ ባክቴሪያ የሆነ የሴሮ ግሩፕ ኤን የሚከላከለው ክትባት በመሰጠቱ፤ አመርቂ ውጤት ታይቷል። ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት ፤ በሌሎች ዝርያዎች የሚመጣው ወረርሽኝ እያየለ መጥቷል። ለዚህም እነኝን ተደራሽ የሚያደርጉ ክትባቶች መሰጠት ይኖባቸዋል። በዚህም ዙሪያ እየተሰራ ይገኛል። እንደ ግለሰብ እና እንደ ማህበረሰብ ስለ በሽታው እና ምልክቶቹ የተሟላ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል። ለዚህም ማንኛውም ታማሚ ከላይ የተጠቀሱትን ምልክቶች ካሳየ ፤ በ48 ሰዓታት ውስጥ የሕክምና እርዳታ እንዲያገኝ ማገዝ አለብን ። ጸረ ተህዋሳት (አንቲባዮቲክ) የለመዱ ተህዋሳት የማጅራት ገትር እያመጡ እንደሆነ ፤ታማሚዎችም ላይ የከፉ ጉዳት እያመጡ መሆኑን የሚያሳዩ ጥናቶች አሉ። የምንወስደውንም አንቲባዮቲክ ፤ በህክምና ባለሙያ የታዘዘ ብቻ መሆን አለበት። ⚠️ ለማጠቃልያ እነኝህን ምልክቶች ያስተውሉ ምልክት ልጆች አዋቂዎች በዕድሜ የገፉ ሰዎች ከፍተኛ ትኩሳት ✅ ✅ 🔄 አንዳንዴ የአንገት ግትርነት ✅ ✅ 🔄 እምብዛም አይታይም ማስመለስ ✅ ✅ 🔄 እምብዛም አይታይም ግራ መጋባት ✅ ✅ ✅ መንዘፍዘፍ ✅ 🔄 አንዳንዴ 🔄 አንዳንዴ ብርሀን አለመቻል/ መመጥላት ✅ ✅ 🔄 እምብዛም አይታይም 🛑 እርሶም ሆነ በዙሪያዎ ያሉ ሰዎች እነኝህን ምልክቶች ካሳዩ ፤ በአፋጣኝ ወደ ሆስፒታል መሄድ ይኖርባቸዋል። ✅ ያስተውሉ ማጅራት ገትር በፍጥነት የሚገድል ከመሆኑም በላይ ፤ ዘላቂ ጉዳት ያስከትላል። ሁሉንም የ እድሜ ክልል ቢያጠቃም ፤ የበሽታ የመከላከል አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ አዛውንቶች እና ህጻናቶች ላይ ያይላል። መከተብ ፣ የተሟላ ግንዛቤ መኖር ፣ እንዲሁም ቀደም ብሎ የሆስፒታል ምርመራ ማድረግ እጅጉን ጠቃሚ ነው። በሽታው እስኪደረጅ አንጠብቅ። መከላከል ይቻላል። እርሱም አሁኑኑ እርምጃ የምንወስድ ከሆነ ብቻ ነው ።
- 🔥 When the Body Rebels?
Are you a young woman stuck in years of constant weariness? Have you suffered puffy joints with achy pain that worsens in the early morning? In Ethiopia, it is not uncommon to find patients suffering from long-standing symptoms that persist for many years. Men battling mysterious rashes. Children growing up to develop chronic diseases too complex for their age. The culprit? A group of diseases so terribly misunderstood that often they remain undiagnosed for decades—autoimmune diseases. These are diseases in which the body's immune system mistakenly attacks its own healthy tissue. What Happens When the Defender Becomes the Attacker? Your immune system is your own army. It is trained to identify and destroy viruses, bacteria, and anything alien. But with autoimmune diseases, this army loses its way. It starts mistaking your own organs, joints, skin, and tissues for enemies. And what happens next? Inflammation, pain, organ damage, and a roller coaster of chronic symptoms that baffle even seasoned physicians. More than 80 autoimmune diseases have been identified, each attacking a different part of the body. A few are household names—type 1 diabetes, for example, or rheumatoid arthritis—while others, like myasthenia gravis or autoimmune hepatitis, operate in relative anonymity. Yet they all share one thing: they're increasing, both globally and in our own community. Both the World Health Organization (WHO) and National Institutes of Health (NIH) report a steady rise in autoimmune disorders, especially in low- and middle-income countries. And Ethiopia is no different. Autoimmune Diseases You Need to Know About While there are more than 80 diseases, some are more prevalent—and disabling—than others: Lupus (SLE): Called "the great imitator," lupus attacks the skin, joints, kidneys, brain, and more. In Ethiopia, women between the ages of 15–45 are increasingly being diagnosed, after years of being misdiagnosed as "stress" or "hormonal problems." Rheumatoid Arthritis (RA): Not a disease of just the elderly—RA causes joint deformity and disability in people as young as their 20s. Ethiopian studies illustrate that RA is underdiagnosed due to limited access to specialists. Type 1 Diabetes: This autoimmune form hits children and teenagers, destroying insulin-producing cells in the pancreas. Its emergence in sub-Saharan Africa has been staggering, with the International Diabetes Federation (IDF) projecting a 10% annual rise in numbers of type 1. Hashimoto's Thyroiditis and Graves' Disease: Both thyroid gland-related, they cause fatigue, weight loss or gain, depression, and infertility. But thyroid screening is not covered under routine care in Ethiopia. Psoriasis and Vitiligo: These skin autoimmune conditions not only present physically but also with huge social stigmatization. Many patients avoid being treated for shame or local culture. Other conditions like Multiple Sclerosis (MS), Celiac Disease, Myasthenia Gravis, Sjogren's Syndrome, and Autoimmune Hepatitis are increasingly encountered in tertiary centers and specialist clinics—at least at late stages. Why Are Autoimmune Diseases On the Rise in Ethiopia? Causes are complex, but specialists list some key triggers: Urbanization and the "Hygiene Hypothesis": As sanitation improves and infection abates, our immune system has less chance to fight—potentially increasing the likelihood of turning against the body itself. Environmental Toxins: Pollution from factories, plastics, pesticides, and processed foods can all interfere with immune control. Hormonal and Genetic Factors: Autoimmune diseases primarily affect women. Some are genetically determined, so a family history is crucial. Delayed Diagnosis: The World Autoimmune and Autoinflammatory Diseases Foundation (WAAD) points out that poor resource patients are diagnosed years after symptom onset, typically after damage is irreversible. There are few rheumatologists in the entire country of Ethiopia, and most of them reside in Addis Ababa. Most patients see general practitioners for consultation who are not trained on autoimmune red flags. What Can We Do? Awareness is the First Defense It's time we stop treating autoimmune symptoms as spurious or psychological. Here's what needs to happen: Invest in diagnostic equipment: Testing like ANA, rheumatoid factor, anti-dsDNA, and thyroid antibodies is not luxury—they're essential. Empower patients to speak up: Fatigue, joint pain, unintentional weight change, and rashes deserve more attention. Incorporate autoimmune diseases into national health plans and NCD (Non-Communicable Disease) strategies. 📢 Final Word: It's Not in Your Head—It Might Be Your Immune System Autoimmune diseases do exist, are on the rise, and quietly ravaging the lives of Ethiopian communities. The sooner we see them, talk about them, and advocate for better care, the more lives we can improve—and save. Let’s stop dismissing symptoms. Let’s start connecting the dots. Sources Mayo Clinic – Autoimmune Diseases Overview NIAID – Autoimmune Diseases WHO – Noncommunicable Diseases Fact Sheet The Autoimmune Association – Understanding Autoimmune Diseases NIH – Understanding Sex Differences in Autoimmune Disease Autoimmune Diseases
- ከልጣጩ እስከ ፍሬው የሕክምና ጥቅም ያለው ፓፓያ
በባህላዊ ህክምና ፓፓያ ለተለያዩ ጥቅሞች ሲውል ቆይቷል። የፓፓይ ፍሬ ለጉበት ህክምና ፤ እንዲሁም እንደ ጸረተባይነት ጥቅም ላይ ውሏል። ቅጠሉ ወባን ጨምሮ ለትኩሳት ህመሞች ያገለግል ነበር። ለወር አበባ ህመምም የሚጠቀሙበት ነበሩ። ልጣጩ ደግሞ የሰውነትን መቆጣትን ለማከም ይውል ነበር። ታድያ ይህ ባዶ መላምት አልነበረም። 🌍 ዘመናዊ ሳይንስ ገና ጥቅሞቹን ማረጋገጥ የጀመረ ቢሆንም ፤ የፓፓያ ቅጠል የመድሐኒትነት አቅም ግን የሚካድ ሆኖ አልተገኘም። ሳይንስ እንዳገኘው የፓፓያ የጤና ጥቅሙ ከምግብ መፈጨት እስከ ውበት ፤ እንዲሁም በሽታ መከላከል ድረስ ይደርሳል። እነኝህን የጤና ጠቀሜታዎች አንድ በአንድ ዘርዝረን እንመልከት ። 🧡 የፓፓያ የሚበላው ክፍል/ ፍሬ/ ስጋ ይህ እምቅ የኃይል ምንጭ ነው። የበሰለ ፓፓያ ጭማቂ በሚከተሉት የበለፀገ ነው፡ ቫይታሚን ሲ (ከፍተኛ የሆነ የቪታሚን ሲ ክምችት አለው ። ይህም በህክምና ከሚመከረው (RDA) በ ሁለት እጥፍ የላቀ ነው።) ፣ ቫይታሚን ኤ ፣ ቪታሚን ቢ 9 (ፎሌት)፣ ቫይታሚን ኢ ፣ ማግኒዥየም እና ኃይለኛ ጸረ ኦክሲዳንት የሆነው ሊኮፔን በውስጡ ይገኛሉ። እነዚህ ንጥረ ነገሮች በሽታ የመከላከል አቅምን ያጎለብታሉ። ለአይን እና ለልብ ጤንነት አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። ውስጡ ያለው ሊኮፔን ሰውነት እንዳይቆጣ ያደርጋል። ሰውነት ውስጥ ያለ የኦክሲዳንት (መርዛማነት ያለው ኬሚካል) መጠንንም ይቀንሳል። ለዚህም ስር ለሰደዱ የ ልብ እና የነርቭ ህመሞች ላይ ተጸእኖ ይፈጥራል። 📚 በኒውሮኢንዶክሪኖሎጂ ሌተርስ (2013) ላይ የተደረገ ጥናት ፤ የተብላላ (fermented) ፓፓያ አልዛይመር ሀመም ባለባቸው ታካሚዎች ላይ ፤ ህመሙን የሚያባብሰውን የኦክሲዳንት መጠን ቀንሷል። ሆኖም ግን በዚህ ዙሪያ ጥናቶች በብዛት መደረግ ይኖርባቸዋል። 🧪 ፓፔን (ፓፓያ ውስጥ ያለ ዋነኛ ምግብ መፍጫ ኤንዛይም) ባልበሰለ ፓፓያ እና በ ፓፓያ ልጣጭ ውስጥ ፓፔን የሚባል ኤንዛይም አለ። ይህ ኢንዛይም ፕሮቲንን የሚያልም በመሆኑ ፤ ፕሮቲን ያላቸው ምግቦችን ለመፍጨት ያግዛል። ለዚህም በባህላዊ መንገድ የምግብ መፈጨትን እንዲያግዝ ፣ የሆድ መወጠርን ለመቀነስ ፓፓያ መብላት ይመከራል። 🧬 በዚህ ኤንዛይም ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች ቢኖሩም ፤ ያለውን ጠቀሜታ ለማስረገጥ እና ከዘመናዊ ህክምና እንዲካተት በደንብ መጠናት ይኖርበታል። እስከአሁን የተደረጉ ጥናቶች የምግብ አለመፈጨት ላለባቸው ሰዎች ጠቀሜታ ሊኖረው እንደሚችል ጠቁመዋል። ⚠️ ታድያ ግን ይህ ፕሮቲንን የሚሰብር ኤንዛይም (እንደማንኛውም ኤንዛይም) ፤ የምግብ ቱቦን ሊያስቆጣ የሚችልባቸው ሁኔታዎች አሉ። ለዚህም የአንጀት /ጨጓራ መቆጣት ያለባቸው ሰዎች ፤ ፓፓያን ከበሉ በኋላ የምግብ መቆጣት ሊያጋጥማቸው ይችላል። 🌿 የፓፓያ ቅጠል የፓፓያ ቅጠል መራራ ከመሆኑ ባሻገር ፤ ብዙ ጊዜ ቸል ይባላል። ሆኖም ግን በቅርብ የተደረጉ ጥናቶች የደንግ (Dengue Fever) ቫይረስ ህመምን የማከም አቅም እንዳለው ጠቁመዋል። እዚህ ጋር ስለ ደንግ ቫይረስ ህመም ጥቂት እንበል። የደንግ ቫይረስ የደንግ ትኩሳት(ፌቨር)የሚባል ከባድ የትኩሳት ህመም ያመጣል። ይህ የደንግ ፌቨር ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ከ 12 አመት በፊት (እንደፈረንጆች በ2013) በድሬዳዋ ሲሆን ፤ በጊዜው 9441 ሰዎች እንደተጠቁ ሲደሲ ይጠቁማል። ከዚህም በኋላ በነበሩት አመታት በደቡብ እና ምስራቅ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የተለያዩ ክልሎችን አጥቅቷል። 📊 ሳይንሱ ምን ይላል? ከህመሙ ዋነኛ ምልክቶች ውስጥ አንዱ የ ፕሌትሌት መመናመን ነው። ታድያ መራራው የፓፓያ ቅጠል ጭማቂ ፤ የዚህ ህመም ታማሚዎች ላይ የፕሌትሌት መጠን እንዲጨምር ያግዛል። ለዚህም የሆስፒታል ቆይታቸው እንዲቀንስ ማድረጉን የሚያሳዩ ጥናቶች አሉ። 🩸 ታድያ ግን ከፈዋሽ ህክምና ተርታ ለመግባት ገና ብዙ ጥናቶች መደረግ ይኖርባቸዋል። እንደ ፈዋሽ ህክምና ባንጠቀመውም ፤ ህመሙ ላለባቸው ሰዎች ከሚመገቡት ምግብ ጋር በመደባለቅ ፤ እንደ ደጋፊ ህክምና መጠቀም እንችላለን። 🌱 የፓፓያ ዘር/ፍሬ ብዙ ጊዜ የፓፓያ ፍሬ ከተበላ በኋላ ውስጡ ያለው ዘር ተጥሎ ማየት የተለመደ ነው። ያለውን የጤና ጠቀሜታ የሚያቅ ፤ ይህ ብክነት መሆኑን ይረዳል። 🧪 የተደረጉ ጥናቶችም ይህንኑ መስክረዋል። የፓፓያ ዘር የጸረ ትላትል/ ተባይ ባህሪ ያላቸው ውህዶች አሉት። ለዚህም የአንጀት ትላትልን ሊያክም ወይም ሊያስወግድ የሚችል አቅም አለው። የፓፓያ ዘር ውስጥ ጉበትን የሚጠግኑ / የሚደግፉ ውህዶችም አሉት። ለዚህም ጉበታቸው ለተቆጣባቸው ፤ መቆጣቱ እንዲቀንስ እና የጉበት ምርመራቸው ጤናማ ደረጃ እንዲመለስ ያግዛል። በተለይም የመድሐኒት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ፤ የጉበት ጉዳት ላይ ተጽእኖ አለው። ፀረ-ባክቴሪያ እና ፀረ-ፈንገስ ባህሪም አለው። ውስጡ እንደ ቤንዚል አይሶታዮሳይኔት አይነት ውህዶች ስላሉት ፤ ባክቴሪያን እና ፈንገስን ሊቃወም ይችላል። እዚ ጋር ማስተዋል ያለብን ነገር፡ 🔬 አብዛኞቹ ጥናቶች በእንስሳት የተደረጉ ናቸው። ይህ ማለት ሙከራዎቹ በእንሰሳት ላይ አመርቂ ለውጥ አሳይተዋል ( በእንሰሳት ሳይሞከር ፤ በሰዎች ላይ መድሐኒትነት ያለውን ማንኛውንም ውህድ መሞከር ስለማይቻል )። መጠናቸው ትንሽ ቢሆንም በሰዎች ላይ ይህንን የሚደግፉ ጥናቶችም አሉ። ሆኖም ግን ወደ ዘመናዊ ህክምና ሙሉ በሙሉ ከመግባቱ በፊት ፤ በደንብ መጠናት ይኖርበታል። ⚠️ ጠቃሚ ማስጠንቀቂያ፡- የፓፓይ ዘር ዱቄት/ጭማቂዎች ሲወሰድ ፤ ጊዜያዊ መካንነት እንደሚያመጣ በእንሰሳት ላይ የተደረጉ ሙከራዎች አሳይተዋል። በሰው ልጅ ያለው ተጽእኖ ገና ባይጠናም ፤ አብዝቶ መጠቀም ተመሳሳይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል። ለዚህም ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ✨ የፓፓያ ልጣጭስ? የፓፓያ ልጣጭን በቆዳ ላይ ማሸት ፤ ለቆዳ ጠቀሜታ ይኖረው ይሆን? የላብራቶሪ ጥናቶች ፓፓያ ቡግርን የመቀነስ ፤ እንዲሁም ቆዳን የማጥራት ጠቀሜታ ሊኖረው እንደሚችል ጠቁመዋል። የፓፓያ ልጣጭን በዚህ መንገድ የተጠቀሙ ግለሰቦችም ፤ ቆዳቸው እንደጠራ በማህበራዊ ድህረ ገጾች ላይ ሲገልጹ ይታያሉ። ታድያ ይህንን የቆዳ ጠቀሜታ ያመጣሉ ተብለው የሚታሰቡት ውህዶች የሚከተሉት ናቸው፡ የፓፓያ ልጣጭ በውስጡ ፓፔን እና አልፋ ሃይድሮክሲ አሲድስ አለው። እነኝህ ውህዶች የሞተ ቆዳን ከላይ የመግፈፍ አቅም አላቸው። ለዚህም የቆዳን ጤና ያግዛሉ። ልጣጩ ውስጥ ያሉ ፀረ ኦክሲዳንቶች (ፖሊፌኖል እና ፍላቭኖይድስ) የባክቴሪያን እድገት ይቃወማሉ። የቆዳን ጤና የሚረብሸውን መርዛማ የኦክሲዳንት መጠንም ይቀንሳሉ። ይህ ደግሞ የቆዳን ጤና ያሻሽላል። ውበትንም ያጎላል። 👩🔬 ታድይ እርስዎስ ለቆዳዎ ጤና እንዴት ያድርጉ፡- የፓፓያ ልጣጭ ውስጡን በፊትዎ ላይ ተቀብተው ፤ ከ 5-10 ደቂቃ ያቆዩት። ከዛም በውሀ ይታጠቡ/ያስለቅቁት። ታድያ ግን የፓፓያ አለርጅ እና በቀላሉ የሚቆጣ ቆዳ ካለዎት መጠንቀቁ መልካም ነው። 💇♀️ የፀጉር እና የራስ ቅል ጤና ዙሪያ አንዳንድ የሻሞፖ እና ቅባት አምራቾች ምን ያላሉ? የፓፓያ ጭማቂ በአንዳንድ ሻምፖዎች እና ቅባቶች ውስጥ ይገኛል። አምራቾቹም ይህንንም ማድረጋቸው ፡ፎሮፎርን እንደሚቀንስ ፤ የሚያሳክክ የራስ ቅል ቆዳን እንደሚያረጋጋ እንዲሁም ፤ የሚሰባበር ጸጉርን እንደሚያጠነክር ይገልጻሉ። ታድያ ይሄ ግን በሳይንስ የተደገፈ አይደለም። ሳይንስ አሁን ያረጋገጠው ፤ የፊት ውበት ጠቀሜታ እንዳለው ነው። ጸጉር እና የራስ ቅል ላይ ባለው ጠቀሜታ ዙሪያ ገና ጥናቶች ያስፈልጋሉ። 📌 ታድያ እርስዎ እንዴት ይጠቀሙት? ክፍሉ ጥቅሙ አጠቃቀሙ የሚበላው ክፍል/የፓፓያውን ስጋ//ውስጡን በሽታ የመከላከል አቅምን ያግዛል። ለልብም ጤና ጠቃሚ ነው። የምግብ መፈጨትን ያያግዛል። ጥሬ እንዳለ ይመገቡት። በሰላጣና በጭማቂ መልክም መጠቀም ይችላሉ ዘሩ//ፍሬው ጉበትን ያግዛል/ይጠብቃል። ጸረ ተባይ ባህሪ አለው።። ዘሩን በዱቄት መልክ አዘጋጅተው መጠቀም ይችላሉ። ሆኖም ግን አልፎ አልፎ ይጠቀሙ። ቅጠሉ ፕሌትሌት መጠንን በደንግ ህመም ጊዜ ይጨምራል። በጁስ መልክ ወይም እንደሻይ አድርገው መጠቀም ይችላሉ። ቆዳው/ልጣጩ የሞተ ቆዳን ያስወግዳል፣ የጸረ ጀርም ባህሪ አለው ቆዳዎት ላይ ይቀቡት ። የመጨረሻ ሀሳብ ፓፓያ ብዙ የጤና ጠቀሜታ ያለው ፍራፍሬ ነው። ሆኖም ግን ተአምራዊ ፈውስ አይደለም። መድሐኒትን አይተካም። ህክምናን ለማገዝ ልንጠቀምበት እንችላለን። ከቅጠሉ እስከ ዘሩ ሁሉነገሩ የጤና ጠቀሜታ ያለው ተክል ነው። ለዚህም ይብሉት፣ እንደጁስ ይጠቀሙት፣ እንደሻይ አፍልተው ይጠጡት ፤ ቆዳዎን ይቀቡት። እንደ ብቸኛ የህክምና መፍትሔ ፈጽሞ እንዳይወስዱት። ላለብዎ የጤና እክል ሐኪምዎን ያማክሩ።
- 🌞 የቫይታሚን ዲ እጥረት 13 ወር ፀሀይ ባላት አገር
ኢትዮጵያ ራሷን “የአስራ ሶስት ወር የፀሀይ ብርሃን” አገር መሆኗን በኩራት ፈርጃለች። ሆኖም ግን የቫይታሚን ዲ እጥረት ስርጭት በኢትዮጵያ ከፍተኛ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ። ዶክተሮችም ይመሰክራሉ። ታድያ እንዲህ ፀሀያማ ሀገር እየኖርን ፤ የቫይታሚን ዲ እጥረት እንዴት ሊከሰት ቻለ? በጂኦግራፊ እንኳን ካየነው ፤ ኢትዮጵያ የምድር ወገብ አከባቢ ስለምትገኝ ፤ በአለማችን ከፍተኛ የፀሀይ ብርሀን ከሚያገኙ ሀገራት ተርታ ትገኛለች። አዲስ አበባ በበኩሏ ፤ መልክአምድራዊ አቀማመጧ ለዚህ የተመቸ ነው። ከባህር ወለል 2300 ሜትር በላይ የምትገኝ ፤ ወይን አደጋ ከተማ ናት። ከምድር ወገብም በስተሰሜን 9 ዲግሪ ርቀት ስለምትገኝ ፤ የለጓሷ ፀሀይ ጨረር ሳይታጠፍ በቀጥታ ያገኛታል። በተፈጥሮ አቀማመጧ የቫይታሚን ዲ እጥረትን መከላከል አለባት። ነገር ግን የቫይታሚን ዲ እጥረት በከተማዎቻችን በሰፊ እየታየ ይገኛል። ከፍተኛው የቫይታሚን ዲ እጥረት መጠንም በአዲስ አበባ ተመዝግቧል። በገጠር የሚኖሩ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ችግር ያለባቸው ህጻናት ላይ ዝቅተኛ የ ቫይታሚን ዲ እጥረት ቢያጋጥም ላይደንቀን ይችል ይሆናል። ነገር ግን ይህ በከፍተኛ ደረጃ እየታየባቸው ያሉት የከተማ ህጻናት ናቸው። ይህ የህጻናት ብቻ ችግር አይደለም።ሁሉንም እድሜ የሚያጠቃ ችግር ነው። ህጻናት፣ ነፍሰጡር ሴቶች እና የመውለድ እድሜያቸው ያለፉ ሴቶች በይበልጥ ተጋላጭነት አለባቸው። ታድይ እንዴት? ፀሀይዋ እንደው እዛው አለች። የአኗኗር ዘይቤአችን ግን ተለውጧል። የአኗኗር ዘይቤያችን እንዴት ተለወጠ? ከተሞቻችን ወደ ጎን ብቻ ሳይሆን ወደ ላይም እያደጉ ነው። በኮንዶሚኒየም፣ በአፓርታማ ወይም በፎቅ ያሉ ልጆች ፤ የሚጫወቱት እቤት ውስጥ ከፀሀይ ብርሀን እርቀው ነው። የቢሮ ሰራተኞችም ከፀሀይ እኩል ተነስተው ከቤት የወጡ ፤ ፀሀይ ስትገባ ነው ወደ ቤት የሚገቡት። የቀን ውሎአቸውም በግርግዳ መሀል በቢሮ ውስጥ ነው። አብዛኛው የቀን እንቅስቃሴያቸው ከፀሀይ የራቀ ስለሆነ ፤ በቂ የፀሀይ ብርሀን አያገኙም። ሴቶች ሲንቀሳቀሱ ዣንጥላ ይይዛሉ። አልያም ሰን ስክሪን(ፀሀይ መከላከያ) ይቀባሉ። እናቶች ልጆቻቸውን ፀሀይ ሲያሞቁ ፤ ቫዝሊን ቀብተው ስለሆነ ፤ ቫዝሊኑ ጠቃሚውን የፀሀይ ጨረር ይመልሰዋል። በኮንዶሚኒየም እና አፓርታማ የሚኖሩ እናቶች ደግሞ ከቤታቸው ሆነው በመስታወት ውስጥ የምትገባውን ፀሀይ ስለሚያሞቁ ፤ ጠቃሚ የሆነው የፀሀይ ጨረር በመስታወቱ ተንጸባርቆ ይመለሳል። ታድያ ይህ ከፀሀይ የራቀ አኗኗራችን ለቫይታሚን ዲ እጥረት ቢያጋልጥ እንዴት ይደንቅ? ምን ያህል የፀሀይ ብርሀን ያስፈልገኛል? በስራ መሀል የምናገኛት ቅንጭብ የፀሀይ ብርሀን የሰውነታችንን የቫይታሚን ዲ መጠን ለመጠበቅ በቂ ላትሆን ትችላለች። ለዚህም የቫይታሚን ዲ ከ 30 እስከ 50 ደቂቃ ፀሀይ ላይ መቆየት ይኖርብናል ። ከጠዋት ፀሀይ ይልቅ ከ 4 ሰአት በኋላ ያለው የፀሀይ ጨረር ይመረጣል። ከዚህም ደግሞ የቀትር ፀሀይ ይበልጥ ኃይል አለው። 🧬 ቫይታሚን ዲ ሲቀንስ ምን ይሆናል? የቫይታሚን ዲ ቁርኝት ከ አጥንት ጋር ብቻ አይደለም። ሰውነታችን ውስጥ ካሉ የተለያዩ ስርአቶች እና አካላት ጋር ይገናኛል። ከበሽታ መከላከያ ስርአት ፣ ከጡንቻ ጥንካሬ ጋር ፣ ከስሜታችን ጋር ፣ ከኢንሱሊን ስራ ጋር ፣ እንዲሁም ከነርቭ ጋር ይገናኛል። ሲቀንስ ምልክቶቹ ለዘብተኛ ሊመሰሉ ይችላሉ። ጉዳታቸው ግን ከፍተኛ ነው። በልጆች ላይ፡ መቀንጨር ፣ የአጥንት መዛባት፣ የዘገየ እድገት እና የእግር አጥንት መጣመም/መቆልመም (ሪኬትስ) ሊያመጣ ይችላል። በአዋቂዎች ውስጥ: ድካም ፣ ሥር የሰደደ ሕመም ፣ የጡንቻ ድክመት፣ ድብርትና ለተደጋጋሚ ኢንፌክሽን ሊያጋልጥ ይችላል። በነፍሰ ጡር ሴቶች ላይ፡ ደካማ የፅንስ አጥንት እድገት፣ በእርግዝና ጊዜ ለሚያጋጥም የስኳር በሽታ፣ የደም ግፊት (ፕሪክላምሺያ) ሊያጋልጥ ይችላል። እንዲሁም የጽንስ ክብደት መቀነስ ሊያመጣ ይችላል። 📊 ስርጭቱ ምን ይመስላል 📍ከ አንድ አመት በፊት የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው የቫይታሚን ዲ እጥረት ስርጭት በኢትዮጵያ 56 ፐርሰንት (40-72%) ይደርሳል። ከዚህም ውስጥ በአዲስ አበባ ስርጭቱ በጣም ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል ( 74 ፐርሰንት)። ቀጣይ ከፍተኛ ስርጭት የተመዘገበው በአማራ ክልል 42 ፐርሰንት እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል 41 ፐርሰንት ነው። 📍 በደቡብ ኢትዮጵያ በእርጉዝ እናቶች መሀከል የተደረገ ጥናት እንዳመላከተው ደግሞ ከ 3 እርጉዝ እናቶች መሀክል አንዷ የቫይታሚን ዲ እጥረት አለባት ። የቫይታሚን ዲ እጥረት ከተገኘባቸው እናቶች መሀክል አብዛኞቹ (88.8%) የደማቸው የቫይታሚን ዲ መጠን እጅጉን የተመናመነ ነበር። 📍 እድሜያቸው ለትምህርት በደረሱ ህጻናት ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው 42% የሚሆኑት የቫይታሚን ዲ እጥረት እንዳለባቸው አረጋግጧል። በከተማ ከሚኖሩ 10 ህጻናት ከ6 በላይ የሚሆኑት ይህ እጥረት ሲታይባቸው ፤ በ ገጠር ከሚኖሩ 10 ህጻናት ውስጥ ግን አራቱ ብቻ የቫይታሚን ዲ እጥረት ይታባቸዋል። እነኝህ ጥናቶች የሚያሳይቱ ቅንጫቢ እውነታ የቫይታሚን ዲ እጥረትን ነባራዊ ሁኔታ በተወሰነ መልኩ ያሳያል። ታድያ በፀሀያማ ሀገር እየኖርን ፤ የፀሀይ እጦት ጋር የተያያዘ ህመም መንሰራፋቱ ፤ እጅጉን አስገራሚ ነው። ለነገሩ " የአባይን ልጅ ውሀ ጠማው" አይደል ተረቱ። 🛠 ታድያ ምን ሊደረግ ይችላል? በበቂ ደረጃ በየቀኑ ፀሀይ ይሙቁ። ቢያንስ ለ 30 ደቂቃ ክንዶችዎን እና እግሮችዎን ሳይሸፍኑ ፤ የፀሀይ ብርሀን ቢያገኝዎ ይመረጣል። ከጠዋቱም ፀሀይ የእኩለ ቀን ላይ ተመራጭ ነው። በቫይታሚን ዲ የበለጸጉ ምግቦችን ይመገ። ። እንቁላል፣ ወተት፣ ዓሳ ቫይታሚን ዲ በውስጣቸው አለ። ከዚህም ባሻገር የበለፀጉ ዘይቶች ወይም ዱቄትም የቫይታሚን ዲ በውስጣቸው ይገኛል። የተጋላጭነት ደረጃቸው ከፍተኛ የሆኑ ሰዎች መደበኛ ምርመራ ማድረግ ይኖርባቸዋል። እነኝህም እርጉዝ ሴቶች፣ ህጻናት፣ የመውለጃ እድሜያቸው ያለፈ ሴቶች ፣ ሥር የሰደደ ሕመም ያለባቸው ሰዎች፣ የቢሮ ሰራተኞች ናቸው። ጤናማ የደም ደረጃ ከ 30 እስከ 50 ነው። በቂ የፀሀይ ብርሀን የማያገኙ ከሆነ ፣ ታሚን ዲ እና ካልሲየም እንክብሎችን መውሰድ ይችላሉ ። ሁሌ ቅድሚያ ተመራጩ የተፈጥሮ መፍትሔ መሆኑን ይወቁ። የደምዎትን የቫይታሚን ዲ መጠን ለማገዝ በቀን ከ600-800 IU መውሰድዎት በቂ ነው። ይህንን ግንዛቤ ለሌሎች ማዳረስ አለብን። ትምህርትቤቶች ፣ ክሊኒኮች፣ ሚዲያዎች የቫይታሚን ዲ መጠንን የሚጠብቁ ባህርያዊ ለውጦችን ማስተዋወቅ አለባቸው። ✨ዋና ነጥብ በጸሀያማ ሀገር ውስጥ እየኖርን የቫይታሚን ዲ እጥረት ለመፍታት ፤ ከውጭ የሚገባ መፍትሔ አያስፈልገንም። የተሟላ ግንዛቤ ይኑርዎ። አበላልዎን አኗኗርዎን ያስተካክሉ። የቫይታሚን ዲ እጥረ ለዘብተኝነቱ አያታልዎ። ከተባባሰ ህመሙ ሰላም ይነሳል፣ የአእምሮ ጤናን ይረብሻል፣ ከስር ያለ በሽታን ያባብሳል። ካልደረስንበት ደግሞ የከፋ ጉዳት ያመጣል። በግንዛቤ ላይ በተመሰረተ ተግባራዊ እርምጃ ጤናችንን እንጠብቅ።
- የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽንና መዘዙ
💧ስለ ሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ሰምተው እንደሚያውቁ ጥርጥር የለውም። እጅጉን የተንሰራፋ እና የተለመደ ህመም ከመሆኑ የተነሳ ፤ ከ20 ሰዎች አንዱ በየአመቱ በሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ይታመማል። እርስዎ በዚህ አመት ሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ታመው ነበር? የታመመ ሰውስ ያውቃሉ? ምልክቶቹስ ምን ምን ናቸው ? 🌍ለምን ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ትኩረት መስጠት ይገባል?🚨 የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን (UTIs) በጣም ከተለመዱ የባክቴሪያ ኢንፌክሽኖች መሀል ይጠቀሳል። በየአመቱ 150 ሚሊየን ሰዎች በሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ይታመማሉ። ከእነኝህም ውስጥ ወደ 300 ሺ የሚጠጉት ፤ ከሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ጋር በተያያዘ መዘዝ ይሞታሉ። የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ሁሉንም እድሜ ክልል ያጠቃል። በሽታው በተለይ ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው፣ ሆስፒታል የተኙ ፣ የሽንት መሽኛ ካታተር የገባላቸው ፣ የበሽታ የመከላከል አቅማቸው የተዳከሙ ሰዎችን በይበልጥ እና በደረጀ መልኩ ያጠቃል። ከወንዶች ይልቅ ሴቶች በይበልጥ ይጠቃሉ። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ከ ሁለት ሴቶች አንዷ በህይወት ዘመኗ ቢያንስ አንድ ጊዜ በሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ትታመማለች። ከ10 ሴቶች አንዷ በአመት አንዴ በ ሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ትጠቃለች። ከ 4 ሴቶች ውስጥ አንዷ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ደጋግማ ትታመማለች። አስደንጋጩ እውነታ ፡ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን በአለም ዙሪያ እየጨመረ ይገኛል። ባለፉት አመታት ውስጥ የህክምና አቅማችን እየጎለበተ ቢመጣም ፤ የተለያዩ እጅጉን የላቀ አቅም ያላቸው የ ባክቴሪያ መከላከያዎች (አንቲ ባዮቲክስ) ቢሰሩም ፤ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን መጠን ባለፉት 30 አመታት ውስጥ በ ሁለት ሶስተኛ (68 %) ጨምሯል። ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ምን ይመስላል? ኢትዮጵያ ውስጥ የተደረጉ የተለያዩ ጥናቶች ፤ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ስርጭት መጠን ምናልባት ሊበልጥ እንደሚችል ያሳያሉ። በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ፤ 21.1 በመቶ የሚሆኑት የሽንትቧንቧ ኢንፌክሽን አለባቸው። ከእነኝህም ውስጥ አብዛኛው ሴቶች ናቸው። በአዲስ አበባ 446 ታማሚዎችን ያሳተፈ ጥናት በበኩሉ ፤ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ስርጭት 31.6% መሆኑን ጠቁሟል። በባሌ የተደረገ ጥናት እንዳሚያመላክተው ከሆነ ፤ የ ሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ስርጭት (ምልክት የምያሳየውን ጨምሮ) በነፍሰጡር ሴቶች መሀል 26% ይደርሳል። 🦠 በህመሙ እንዴት ይያዛሉ? የሽንት ቧንቧችን የውስጥ ክፍል ከበሽታ አምጪ ባክቴሪያ በተፈጥሮ የጸዳ ነው። ሆኖም ግን አጋላጭ ምክንያቶች ሲከሰቱ በሽታ አምጪ ባክቴሪያዎች የሽንት ቧንቧን ይወራሉ። ከሽንት መውጫ ጫፍ ተነስተው ወደ ፊኛ ያመራሉ። ሃይ ባይ ከሌላቸው (መድሀኒት ካልወሰዱ) ወደ ኩላሊትም ይደርሳሉ። አቅሙ ከደረጀም ወደ ደም ውስጥ ገብቶ ለሕይወት እጅጉን አስጊ ኢንፌክሽን ሊያመጡ ይችላሉ። ታድይ ይህ ያልተጠበቀ ክፉ እንግዳ (በሽታ አምጪ ባክቴሪያ) የሽንት ቧንቧን ያጠቃል። ይህም የሽንት ቧንቧችንን ያስቆጣል። ለዚህ አጸፋዊ ምላሽ የሚሰጠው ሰውነታችን ባክቴሪያውን ፈጽሞ ማጥፋት ከተሳነው ፤ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ይከሰታል። ይህ ተጋላጭነት እና አጸፋዊ ምላሽ ከሰውነታችን የበሽታ መከላከል አቅም ጋር የተቆራኘ ነው። ለዚህም በሽታ የመከላከል አቅማቸው የተዳከመና ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው ሰዎች የመያዝ እድላቸው ይሰፋል። የሽንት መሽኛ ቱቦም የተደረገላቸው ሰዎች ቱቦው ባክቴሪያውን እሰከ ፊኛ መርቶ ስለሚገባ ፤ በሽንት ቧንቧ ደጋግመው ይጠቃሉ። ሴቶች በተፈጥሮ የሽንት ቱቧቸው አጠር እና ቀጥ ያለ በመሆኑ ፤ ባክቴሪያው መንገዱ ይቀልለታል። ለዚህም በሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን በብዛት ይጠቃሉ። 🔥 ምልክቶቹን ማወቅ አለብን? የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ምልክት ላያሳይ ይችላል። የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ካለብዎ ፤ ሊያሳዩ የሚችሉዋቸው ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው። ሽንት ደጋግሞ መሽናት ሽንት ሲሸኑ ማቃጠል ሽንት ቀለም መለወጥ ሽንት ሽታ መኖር ከእንብርት በታች የሚሰማ የሆድ ህመም ትኩሳት/ ብርድ ብርድ ማለት ድካም የምግብ ፍላጎት መቀነስ ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ ናቸው ። እነኝህን ምልክቶች ካዩ ፤ በአቅራቢያዎ ወደሚገኝ ጤና ተቋም ሄደው ይታከሙ። 💔 ከሚታሰበው በላይ ከባድ የሆነበት ምክንያት ምንድነው? በቀላል ህክምና እርዳታ ከሚሻሉ ህመሞች መሀከል ነው ብለው፤ ስለ ሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ፈጽሞ መዘናጋት የለብዎትም። የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን በህክምና እርዳታ ቁጥጥር ላይ ካልዋለ ፤ መዘዙ ከበድ ሊል ይችላል። ወደሚከተሉትም ሊያመራ ይችላል። ኪላሊትን አጥቅቶ ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ ሊያስከትል ይችላል። ይህም ከባድ ህመም ከመሆኑ በላይ ፤ ኩላሊት ላይ ጉዳት ያደርሳል። ለህይወት አስጊ የሆነ የደም ውስጥ ኢንፌክሽን ያመጣል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለም አቀፍ ደረጃ እስከ 5% የሚደርሱ ከባድ የደም ውስጥ ኢንፌክሽኖች በሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ይከስታሉ። በዚህም ከታመሙ 10 ሰዎች ውስጥ አራቱ ይሞታሉ። የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ያጋጠመው በእርግዝና ወቅት ከሆነ ፤ ጉዳቱ ከእናት አልፎ ጽንሱንም ያጠቃል። ምጥ ያለጊዜው እንዲመጣ ያደርጋል። የጽንስ ክብደት ይቀንሳል። የእናትየውንም ህይወት አደጋ ላይ ይጥላል። ተደጋጋሚ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽኖች ያለባቸው ሰዎች ለህይወታቸው ከባድ እክል ይፈጥራል። በተደጋጋሚ በህመሙ የተነሳ ከስራ ቦታቸው ይቀራሉ። ከስራም ይባረራሉ። የህመሙ ምልክቶች ከማህበረሰብ እንዲርቁ ያደርጋቸዋል። ይህም ጭንቀት ውስጥ ሊከታቸው ይችላል። 💊 ሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ይታከማል። አዎ በ አንቲባዮቲክስ መድሀኒቶችና በህክምና ክትትል ሊታከም ይችላል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የመድኃኒት አቅርቦት ውስንነት ፤ የህክምናውን ውጤታማነት በመጠኑ ቢገታም ፤ ባሉን መድኃኒቶች በደንብ መታከም ይችላል። ታክሞም ይድናል። 🚫 ታድያ ለመከላከል ምን ያድርጉ? ህመሙ እስኪይዝዎ መጠበቅ የለብዎትም። ተጋላጭነትዎን መቀነስ ይችላሉ። ዛሬውኑ የሚከተሉትን ያድርጉ። 💧 በቂ ውሀ ይጠጡ። ይህም ከሽንት ቱቦ ውስጥ የገቡ ባክቴሪያዎችን አጥቦ ያወጣል። 🧼 ንጽህናዎን ይጥብቁ። ይህም ባክቴሪያው እንዳይዛመት ያደርጋል። 🚽 ሽንትዎን አይቋጥሩ። 🚽 ሴቶች ከግብረ ስጋ ግንኙነት በኋላ ቢሸኑ ፤ በሽታ ተጋላጭነትን ይቀንሳሉ። ይህም ምክንያቱ ወደ ሽንት ቧንቧ የገባው ባክቴሪያ ፤ በሽንቱ ታጥቦ ስለሚያወጣ ነው። 🚫🧴 ሴቶች ንጽህናቸውን ሲጠብቁ፣ የሽንት ቧንቧን ከሚያስቆጡ አካላት መቆጠብ ይኖርባቸዋል። ለዚህም የሚከተሉትን አይጠቀሙ። ❌ ሻካራ ሳሙናዎች ❌ ስፐርሚሳይዶች (spermicides) ❌ የተለያየ ኬሚካል ያላቸው ንጽህና መጠበቂያዎች ❌ቅባቶች 💉የስኳር ህመም እና ሌሎች ተጓዳኝ ህመሞች ካለብዎ ፤ ደግሞ እነሱን ይቆጣጠሩ። የህክምና ክትትል ያድርጉ። የተፈጥሮአዊ አማራጭም አለ። ፕሪሞን (ክራንቤሪን) አዘውትሮ መመገብ ወይም ጭማቂውን መጠጣት ፤ የሽንት ቧንቧን ጤና ያሻሽላል። የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽንን ይቀንሳል። 💊 ከታመሙ ደግሞ በራስዎ መድሃኒት አይውሰዱ። ከላብራቶሪ ምርመራ በኋላ ፤ በዶክተርዎ ምክር ፤ ትክክለኛውን መድሐኒት መውሰድ ይኖርብዎታል 📢 ትኩረት እና እንክብካቤ ሊደረግለት የሚገባ አሳሳቢ የጤና ችግር ነው። 🎯 ጤናዎ ከግንዛቤ ይጀምራል። ግንዛቤን ከተግባር ጋር አጣምረው ፤ ጤናዎን ይጠብቁ። ህይወትዎን ያሻሽሉ። አያመንቱ። ዛሬውኑ እርምጃ ይውሰዱ።
- ሶስት አመት የፈጀው አለም አቀፍ ወረርሽኝ፡🐒 የዝንጀሮ ፈንጣጣ
ስለ ዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ ምን ያህል ያውቃሉ? 📜 ታሪኩ በ1958 ጀመረ… እንደፈረንጆቹ 1958 ዓ.ም በዴንማርክ የሚገኙ ሳይንቲስቶች ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በጦጣ ዝርያዎች መሀከል ፈንጣጣ (ፖክስ) የሚመስል ቫይረስ አገኙ። ቫይረሱ ያልተለመደ የፈንጣጣ አይነት ስለነበር ፤ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ብለው ሰየሙት (monkeypox)። በዝንጀሮ ይሰየም እንጅ ፤ የዱር አይጥ ዝርያዎችንም እንደሚያጠቃ በቀጣይ አመታት ታውቋል። ከዚህ ባሻገር ቫይረሱ ከእንሰሳት ወደ ሰው ልጅ የመተላለፍ አቅም አለው። እንደፈረንጆቹ በ1970 ዓ.ም የመጀመሪያው የቫይረሱ ታማሚ ሰው ፤ በአፍሪካዊቷ አገር በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተገኘ። በቀጣይ አመታት ውስጥ ታድያ በዩጋንዳ ፣ በቡሩንዲ ፣ በሴራሊዮን እና በሌሎች በርካታ የአፍሪካ ሀገራትም ተሰራጨ። ከአፍሪካ ባሻገር ቫይረሱ በ ህንድ፣ በካናዳ ፣ አሜሪካ እንዲሁም አንዳንድ የአውሮፓ ሀገር እንደተሰራጨ ሪፖርቶች ያሳያሉ። የቫይረሱ የመጀመሪያ ስርጭቶች በሀገራት ደረጃ የተወሰኑ ነበሩ። 🌍የአለም አቀፍ ወረርሽኝ የዛሬ ሶስት አመት ገደማ በፈረንጆች ሜይ ወር 2022 ዓ.ም ፤ የቫይረሱ ስርጭት ወደ አለም አቀፍ ደረጃ አደገ። ቫይረሱ መጀመሪያ በተገኘባት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በቡሪንዲ ቫይረሱ እጅጉን ተስፋፋ። በአፍሪካ ፣ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ እና አንዳንድ እስያ ክፍሎች በብዛት ተሰራጨ። እንደ ፈረንጆች ኦገስት 2022 የ ዝንጀሮ ፈንጣጣ አለም አቀፍ ስርጭት ጎረቤታችን ኬንያም የመጀመሪያው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ ከ አንድ አመት በፊት ተገኘ። እስከአሁን ድረስ ቫይረሱ ስርጭት በኬንያ አልቆመም። ይህንን ስርጭት ለመግታት የኬንያ መንግስት ከሁለት ወር በፊት (በፈረንጆቹ አፕሪል 2025) ወደ 10 ሺ የሚጠጋ የቫይረሱ ክትባት አስገብታለች። ሲዲሲ ከ ሁለት ሳምንት በፊት እንዳወጣው መረጃ፤ እስከ አሁን በአለም ዙሪያ ቫይረሱ ወደ102 000 ሰዎች ያጠቃ ሲሆን ፤ 220 ደግሞ በቫይረሱ የተነሳ ሞተዋል። ታድያ ምን ተለወጠ? ለምን ላለፉት 50 አመታት ያወቅነው ቫይረስ ፤ አሁን ላይ አለም አቀፍ ወረርሽኝ አመጣ? ይህ ቫይረስ ሁለት ዋነኛ ዝርያዎች ሲኖሩት እነሱም ክላድ አንድ (ኮንጎን ያጠቃው ዝርያ) እና ክላድ ሁለት (ምእራብ አፍሪካ አገራትን ያጠቃ ዝርያ) ተብለው ይለያሉ። በፈረንጆች 2022 ዓ.ም ጀምሮ የእነኝህ ዝርያዎች ባህሪ ለውጥ አሳይቷል። ይህም ለውጥ ዘረመል ደርጃ የመጣ ለውጥ ሲሆን ፤ በሳይንቲስቶች በጥልቀት እየተጠና ይገኛል። ከዚህም ባሻገር በቅርብ አመታት ውስጥ የሰው ልጆች ራሱ በሽታ በመከላከል ዙሪያ ላይ ያመጧቸው ለውጦች ፤ ለቫይረሱ አጋላጭነትን እንደጨመሩ ጥናቶች ይጠቁማሉ (emergence of APOBEC3 mutation)። የቫይረሱ ስርጭት በኢትዮጵያ ሀገራች ኢትዮጵያም የዚህ በሽታ ገፈት ከደረሳት ይኸው ሀያ አራት ቀናት ተቆጠሩ። የመጀመሪያው የቫይረሱ ታማሚ የ 21 ቀን እድሜ ያለው ጨቅላ ህጻን ልጅ ሲሆን አባቱ ጎረቤት አገር ሄዶ እንደነበር ጤና ጥበቃ ግንቦት 17 2017 ዓ.ም በለቀቀው መግለጫ ጠቁማል። ጤና ጥበቃ ሚኒስተር ሰኔ 10 2017 ዓ.ም እንደለቀቀው መረጃ፤ ከተደረጉት 220 ላብራቶሪ ምርመራዎች መሀከል የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ 22 ሰዎች ላይ መገኘቱን ገልጿል ። ከተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ 14 ሲያገግሙ፤ ሰባቱ ለይቶ ህክምና ላይ እንደሚገኙ አመላክቷል። ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ምክንያት እስከአሁን አንድ ሰው መሞቱን ጠቅሷል። 🦠 የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ ምንድነው? ይህ ቫይረስ ስሙ እንደሚያመላክተው የፈንጣጣ ቫይረስ አይነት ነው። በፊት ከምናውቃቸው የሰው ፈንጣጣ (small pox) ፣ የከብት ፈንጣጣ (cow pox) ቫይረሶች ጋር እጅጉን ይመሳሰላል። ዘራቸውም ባህሪያቸውም ተቀራራቢ ነው። የህመሙ ዋነኛ ምልክቶቹ የቫይረሱ ሽፍታ በቀናቶች ውስጥ የሚያሳየውለውጥ እንደ ጉንፋን የሚመስሉ ምልክቶች ሽፍታ ትኩሳት የንፍፊት እብጠትና ድካም ናቸው። ሕመሙ ካየለ ግን ፤ እስከሞት የሚያደርሱ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል። 🚨 ህመሙ እንዴት ይሰራጫል? ቫይረሱ የሚተላለፈው ህመሙ ካለበት ሰው ጋር 👥 ቆዳ ለቆዳ ንክኪ ሲኖር 💋ግብረ-ሥጋ ግንኙነት ካለ 🤒 አልጋ ልብስ (ብርድ ልብስ) ፣ ልብስ ወይም ፎጣ ከተጋራን 💨 ህመሙ ያለበት ሰው ካሳለብን/ ካስነጠሰብን 🐀 በበሽታው ከተያዙ እንስሳት (በተለይ ከአይጦችና ጦጣ ዝርያዎች) ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ሲኖረን ነው። ❗ቫይረሱ እንደ ኮቪድ አየር ወለድ አይደለም። በትንፋሽ የመተላለፍ እድል ይኑረው እንጂ ፤ ዋነኛ መተላለፊያው የአካል ንክኪ ነው።❗ ❓ ማን የበለጠ አደጋ ላይ ነው? ለቫይረሱ ለመያዝ ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸው አካላት የሚከተሉት ናቸው። 🔹 የጤና ባለሙያዎች 🔹 የወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ 🔹ከአንድ በላይ ሰው ጋር ግብረስጋ ግንኙነት የሚፈጽሙ ሰዎች 🔹 ህጻናት እና የበሽታ መከላከል አቅም የሌላቸው ሰዎች 🔍 እርስዎ ሊጠነቁዋቸው የሚገቡ ምልክቶች፡- ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት እና የሰውነት ህመም ንፍፊት እብጠት ካለ በአፍ ፣ በብልት ፣ በእጆች ፣ በእግሮች ወይም በአይን አካባቢ ያሉ ሽፍታዎች እነኝህ ሽፍታዎች ከቀናት በኋላ ወደ ቁስል ይለወጣሉ 🕑 ምልክቶች የሚታዩት በተጋለጡ ከ5-21 ቀናት በኋላ ነው። 💉 ሕክምናውና እና ውጤቱ ቫይረሱ አብዛኛው ሰው ከ2-4 ሳምንታት ውስጥ ይድናል። ለቫይረሱ ታካሚ የሚደረጉት ህክምናዎች የሚከተሉት ናቸው። 🔹 የድጋፍ እንክብካቤ (ፈሳሽ፣ ህመም ማስታገሻ፣ ቁስሉን መንከባከብ) ቁልፍ ነው። 🔹 የፀረ-ቫይረስ መድሃኒቶች ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ. 🔹 ለፈንጣጣ የተሰሩ ክትባቶች ይከላከሉታል (ከፈንጣጣ ጋር ስለሚመሳሰል)። ሆኖም ግን በኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ የአፍሪካ አገሮች መድሀኒቶቹ አቅራቦት ውስን ነው። 🛡️ መከላከያ መንገዶች እራስዎን እና ማህበረሰብዎን ለመጠበቅ እነኝህን ያድርጉ። ✅ ምልክቱን ከታየ ሰው ጋር የቅርብ ግንኙነትን ያስወግዱ። ✅ ልብስ፣ አንሶላ ወይም ፎጣ አይጋሩ። ✅ የግብረ ሥጋ ግንኙነትን ሲያድርጉ እራስዎን ይጠብቁ ። ✅ በተደጋጋሚ እጅዎን ይታጠቡ። ✅ሌሎችን ያስተምሩ። ✅ አጠራጣሪ ምልክቶችን/ ሽፍታዎችን በአፋጣኝ ለጤና ባለስልጣናት ያሳውቁ 🗣️ ያስተውሉ ወረርሽኝ ችላ በማለት አይጠፋም። እንደውም ይስፋፋል። 📣 የተጠቀሱትን ተግባራት ይፈጽሙ። እርስዎንም ማህበረሰብዎን ይጠብቁ። ይህንን መረጃ ለሌሎች ያጋሩ። ሞንኪ ፖክስን ለመከላከል፤ ተግባራዊ ለውጥ ማድረጊያው ሰአት አሁን ነው።
- ከእድሜ ጋር የሚያያዘው የአጥንት መሳሳት ህመም
ለመሆኑ ሰው ወለም ብሎት የቁርጭምጭሚት ቀዶ ህክምና ሊያስፈልገው ይችላልን? ምን ይመስልዎታል? ያጋጠመው ሰውስ ያውቃሉ? ይህ የምታውቁት ሰው ወንድ ነው ሴት? እድሜውስ? የወለምታ ስብራት (እውነተኛ ታሪክ) እናት እጅጉን ታታሪ በመሆናቸው ፤ በ80 አመታቸው እንኳን ይሰሩ ነበር። ታድያ አንድ ጠማማ ቀን ላይ ከስራ ሲመለሱ ፤ ታክሲ ሊይዙ ሲሉ ፤ ድንገት ወለም ብሏቸው ወደቁ። ላለፉት ስንት አስርት አመታት እላይ እታች ብለው ፤ ልጆቿቸውን ለቁም ነገር ላበቁ እናት ወለምታ ተራ ነበር። ከዚህ በላይ አሸን ጊዜ ወድቀው ተነስተዋል። እንዳሳለፉት ህይወት ፤ እንደተጋፈጡት ችግር ፤ ለእኝህ እናት ወለምታ ምናቸው? ሆኖም ግን ያሁኑ ወለምታ ለየት ያለ ሆነባቸው። ምንም ልባቸው ቢጀግንም የዚህ ወለምታ ቁስል የሚሽር አልሆን አላቸው። የዚህን ጊዜ ልጆቻቸው ተሯሩጠው ሀኪም ቤት ይዘዋቸው ሄዱ። እና እዛም የተደረገው የኤክስ ሬይ ምርመራው ፈጽሞ ያልጠበቁት ሆነ። አንድ አጥንት አይደለም። የግራ እግራቸው ሁለቱም አጥንቶች ቁርጭምጭሚታቸው አከባቢ ተሰብረዋል። ልጆች ማመን ከበዳቸው። "ወለም ነው እኮ ያላት!" ይላሉ ህመሙን ሲያስረዱ ። ይህ ስብራት በህክምናው የፖትስ ስብራት (Potts fracture) ሲባል፤ በእዚህ የእድሜ ክልል የተለመደ ነው። እኝህ እናትም በቀጣይ ቀን በቀዶ ህክምና ስብራታቸው ተስተካከለላቸው ። ሆስፒታል ውስጥ ለ ሁለት ሳምንት ከቆዩ በኋላ ወደ ቤት ተመለሱ። ከሆስፒታል ከወጡም በኋላ ፈጽሞ ለማገገም ረዥም ጊዜ ወሰደባቸው። ሆኖም ግን ሙሉ ፈውስ አላገኙም። እንደድሮው ተሳፍረው ሩቅ ሄደው ስራ ሰርቶ መምጣት ተሳናቸው። እንቅስቃሴያቸው ተገደበ። ከ ቀዶ ህክምናው በኋላ መጣ ሄድ የሚል፤ በቅዝቃዜ የሚብስ ህመም ነበረባቸው። ታድያ ግን ይህ ታሪክ የእኝህ እናት ብቻ አይደለም። ብዙ እድሜያቸው የገፋ እናቶቻችን ፤ አንዳንድ ህመም ያለባቸው ፤ ደካማ አመጋገብ ያለባቸው ቤተሰቦቻችን ተመሳሳይ እክል አጋጥሟቸዋል። እንኳን ወለም ብሏቸው አልያም አደናቅፏቸው ይቅርና ፤ ዘለው ሲያርፉ አጥንታቸው የተሰበረም አይጠፉም። ይህ የሚፈጠረው በአጥንት መሳሳት የተነሳ ነው። በዚህም ትምህርታዊ ጽሁፍ ፤ በይበልጥ ሴቶችን ስለሚያጠቃው የአጥንት መሳሳት አይነት በትኩረት እናነሳለን። 🌪 የአጥንት መሳሳት ምንድን ነው? የአጥንት መሳሳት ህመም ፡ በግራ በኩል የሚታየው ጤናማ አጥንትነው። በመሀል እና በቀኝ ያሉት የሳሱ አጥንቶች ናቸው። የአጥንት መሳሳት በህክምና ስሙ ኦስቲዮፖሮሲስ ሲባል ፤ የ አጥንታችን ጥንካሬ ከቀን ወደቀን እየተመናመነ ሲመጣ የሚከሰት ነው። ይህ ሲያጋጥም አጥንታችን በመገንባት ፋንታ እየፈረሰ ይመጣል። አጥንታችንን ጥንካሬ የሚሰጡት የካልሺየም እና የ ፎስፌት ማእድናት ፤ አጥንት ውስጥ ያላቸው መጠን ይቀንሳል። ለዚህም አጥንታችን ይሳሳል። ስለሳሳም በቀላል ኃይል ይሰበራል። ለዚህም ሲዘሉ ፤ ድንገት ፈጣን እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ፤ ወለም ሲላቸው ፤ ሲያደናቅፋቸው ፤ አጥንታቸው ይሰበራል። አጥንታቻው ስለሳሳ ፤ አሁን ትንሿ ኃይል ያይለ ጉዳቷ ታደርሳለች። አዳልጧቸው ወድቀው ፤ በመኪና እንደተገጩ ደረጃ የዳሌ ስብራት ጋጥማቸዋል። ይህም ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች አሉት። ከእድሜ ጋር የሚያያዝ ቢሆንም ፤ በሁሉም የእድሜ ክልል ይከሰታል። እድሜ ሲገፋ ሰውነት እራሱን የመገንባት አቅሙ ስለሚዳከም ፤ የአጥንት መሳሳትም በይበልጥ ይከሰታል። ከወንዶች ይልቅ ሴቶችን አብዝቶ ያጠቃል። 👩🏽🦳 ሴቶችን ለምን በይበልጥ ያጠቃሉ? አጥንት መሳሳት ሴቶች ላይ ማየሉ ፤ በዋነኝነት ከሆርሞን ጋር ይያዛል። ሴቶች በመውለጃ እድሚያቸው ላይ ሆነው ፤ ያላቸው የ ኢስትሮጅን ሆሮሞን (Estrogen) መጠን ከፍተኛ ነው። ይህ ሆርሞን ደግሞ አጥንት ውስጡ ገንቢ የሆኑ ማእድናትን እንዲያስቀምጥ ስለሚያደርግ ፤ አጥንት ጥንካሬው እንዲጠበቅ ያደርጋል። ለዚህም በሴቶች አጥንት ጥንካሬ ላይ ከፍተኛ የሆነ ሚና ይጫወታል። የሴቶች የ ኢስትሮጅን ሆርሞን መጠን ከእድሜ ጋር ሴቶች የመውለጃ እድሜያቸው ካለፈ በኋላ የዚህ ሆርሞን መጠን እየቀነሰ ይመጣል። ይህም ሆርሞን መጠን መቀነሱ ፤ ሙሉ የሰውነት አካላት ላይ ተጽእኖ ያሳድራል። በመቀነሱ አጥንት ላይ ያለው ተጽእኖ እንዲሁ ይዳከማል። አሁን አጥንት ውስጥ ገንቢ የሆኑ ማእድናት አይቆዩም። ይህም በመሆኑ የአጥንትን ጥንካሬን መጠበቅ ይሳነዋል። መረጃዎች እንደሚያሳይቱ ከሆነ ፤ ሴቶች ማረጥ ከጀመሩ በኋላ ባሉ ከ5-7 ዓመታት ውስጥ ፤ እስከ 20% የሚሆነውን የአጥንት ክብደት ሊያጡ ይችላሉ። እድሜ በገፋ ቁጥር ፤ የዚህ ሆርሞን መጠንም እጅጉን እየቀነሰ ይመጣል። የአጥንትም መሳሳትም እንዲሁ። ለዚህም እድሜ ሲጨምር ፤ አጥንት በቀላል እንቅስቃሴ የመሰበር እድሉ እያየለ ይመጣል። በአለም አቀፍ ደረጃ እድሜያቸው ከ50 በላይ ከሆናቸው ሶስት ሴቶች አንዷ አንዷ የአጥንት ስብራት ያጋጥማታል። ምልክቶቹ ምንድን ናቸው? የአጥንት መሳሳት ማስጠንቀቂያ ምልክቶች የሉትም። አጥንት ሲሳሳ ምንም አይሰማም። በመስታወት ውስጥ አያዩትም። ጉዳቱ ቀስበቀስ የሚደረጅ ነው። ቁመት ይቀንሳል (ብዙውን ጊዜ ከ3-5 ሴ.ሜ ወይም ከዚያ በላይ) አቋም ይለወጣል። ሰውነት ይጎብጣል። የአከርካሪ አጥንትን ከተጠቃ ፤ ጥቃቅን የአከርካሪ አጥንት ስብራቶች ያጋጥማሉ። ለዚህም በጀርባ ህመም ይሰቃያሉ። በቀላል እንቅስቃሴዎች ከባድ የሆነ ጉዳት ያጋጥማል። የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የአጥንት መሳሳት ተከትሎ የሚመጡ ስብራቶችን የሚያሳይ ሀገር አቀፍ መረጃ የለንም። ስለ አጥንት መሳሳት ሰምተው የማያውቁ ሴቶችም ጥቂት አይደሉም። አንዳንዶች ስብራት ሲያጋጥማቸው ነው ስለ አጥንት መሳሳት የሚያውቁት። በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ ደረጃ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ከሆነ፡ እስራኤል አገር ከሄዱ ኢትዮጵያዊ ቤተ እስራኤላውያን መሀከል 38.7% የአጥንት መሳሳት አለባቸው። ይህ እስራኤል ሀገር ከተወለዱ ኢትዮጵያዊ ቤተ እስራኤላውያን አንጻር በ 33.6 % (5.2% ነው) ይበልጣል። ይህም የሚያመላክተው ከአኗኗራችን እና ከአመጋገባችን ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ነው። በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከታከሙ አስር የአጥንት ስብራት ህሙማን መሀከል ፤ አንዱ ስብራት በአጥንት መሳሳት የተነሳ የመጣ ነው። እድሜያቸው ከ 40 አመት በላይ ከሆኑ አስር የአጥንት ስብራት ታማሚዎች መሀከል ደግሞ ፤ ሶስቱ ስብራት ያጋጠማቸው በአጥንት መሳሳት የተነሳ ነው ። በትግራይ ውስጥ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ደግሞ ፤ ከ አጥንት ስብራት ታካሚዎች መሀከል 9.3% የሚሆኑት የአጥንት መሳሳት አለባቸው። አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት እድሜያቸው ከ40-49 የሚሆኑ ሴቶች ናቸው። ከከተማ አንጻር በገጠሯ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ግለሰቦች ለአጥንት መሳሳት ያላቸው ተጋላጭነት በእጥፍ ይጨምራል። ለምን እንዲህ ተንሰራፋ? በሀገራችን ኢትዮጵያ የአጥንት መሳሳት ህመም ደረጃ ከፍ ለማለቱ የተለያዩ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ። ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ግን አኗኗራችን እና አመጋገባችን ነው። ለዚህም በቤተ እስራኤላውያን ዘንድ የተሰራውን ጥናት ዋቢ አድርጎ መጥቀስ ይቻላል። ለዚህ መንስኤ ሊሆኑ ከሚችሉ ልማዶቻችን በጥቂቱ፡ በካልስየም የበለጸጉ የወተት ተዋጽኦዎች ተዘውትረው አይወሰዱም። ይህን አዘውትረው ከወሰዱ የሚወስዱት ህጻናት ናቸው። የመውለጃ እድሜያቸው ያለፈ ሴቶችም ፤ በደንብ አዘውትረው መውሰድ አለባቸው። ብዙ ሴቶች (በተለይ በገጠሪቷ ኢትዮጵያ) አብዛኛውን ጊዜ ሲንቀሳቀሱ ፤ ከላይ እስከታች ቆዳቸውን የሚሸፍኑ ልብሶችን ይለብሳሉ። የ ጸሀይ ብርሀን የሚያገኘው ሰውነታቸው እጅጉን ውስን ነው ። ይህ ደግሞ የቫይታሚን ዲ ደማቸው ውስጥ እንዳይጎለብት ይገድበዋል። ይህም ለአጥንት መሳሳት ያጋልጣል። አካል እንቅስቃሴ አዘውትሮ መስራት የተለመደ አይደለም። አካል እንቅስቃሴን ከወጣትነት ጋር የማያያዝ ብሂል አለ። እድሜ ሲገፋ አጥንትን ማጠንከር የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች ቢያስፈልጉም ፤ ይህ ፈጽሞ አልተለመደም። በእርጅና ዘመን ማን አስቦበት?! እድሜ ሲገፋ ከሚመጡ የጀርባ ህመም መንስኤዎች ውስጥ አንዱ የጀርባ አጥንት መሳሳት ይኖርበታል። ታድያ ግን ሴቶች ቁመታቸው ሲያጥር ፤ የጀርባ ህመም ሲያይል ፤ ሲጎብጡ የአጥንት መሳሳት ተብሎ አይታሰብም። መደበኛ ምርመራ አልተለመደም። በተለይ የማረጫ እድሜ ያለፉ ሴቶች የአጥንታቸውን ጤና መከታተል ቢኖርባቸውም ፤ ማን አስተውሎት ? የ ችግሩ መጠን የአጥንት መሳሳትን ፈጽሞ እንደቀላል ማየት የለብንም። የአጥንት መሳሳት ዳፋው ከአጥንት አልፎ ፤ ህይወትን ያሰናክላል። የአልጋ ቁራኛ ያደርጋል። ከከፋም እስከሞት ሊያደርስ ይችላል። በአለም አቀፍ ደረጃ የዳሌ ስብራት ካጋጠማቸው 5 ሴቶች አንዷ ፤ ዳሌ ስብራት በአጋጠማት በአመቱ ውስጥ ትሞታለች። የዳሌ ስብራት ካጋጠማቸው እስከ 40% የሚሆኑት ሴቶች ለተረፈው ህይወታቸው ጥገኛ ይሆናሉ። ንጽህናቸውን ለመጠበቅ ፤ መጸዳጃ ቤት ለመጠቀም ፤ ለመንቀሳቀስ የሌላ ሰው እገዛን ይፈልጋሉ። ቤተሰብን ቀጥ አድርገው ያስተዳድሩ የነበሩ እናቶች ፤ ሸክም ሲሆኑ ይጨነቃሉ ። ስብራቱን ተከትሎ ከማህበራዊ ቁርኝት መራቃቸው ፤ ይህንን ጭንቀት ያብሰዋል። በገንዘብም ጥገኛ ይሆናሉ። በህክምናው በኩል ካየነው ደግሞ ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለው ደረጃ ለህክምና በብዙ ሺዎች ያስፈልጋል። ታድያ አንድ ከእጀ ወደ አፍ ኑሮ የምትኖር እናት እጣዋ ምን ይሆን ? ለ እነኝህ ስብራቶች በሀገር ደረጃ ብዙ ትኩረት የተሰጠ ባለመሆኑ ፤ ታካሚዎች ህክምና ለማግኘት ይዘገያሉ። የማገገሚያ ህክምናም የተሟላ ባለመሆኑ ብዙዎች ከጉዳት ጋር ህይወትን ይመራሉ። መልካሙ ዜና ግን ፈጽሞ መከላከል ይቻላል። 💪🏽ከዛሬ ጀምሮ ምን ማድረግ ይችላሉ? ከዚህ በኋላ የአጥንት መሳሳት ህመምን ችላ ማለት የለብዎትም። ልማዶትን በመለወጥ ፤ አኗኗሮትን በማስተካከል መከላከል ይችላሉ። ለዚህም የሚከተሉትን ተግባራዊ ለውጥ ያድርጉ። እድሜዎ ከ 40 አመት በላይ ያለ ሴት ነዎት? እድሜው የገፋ የቤተሰብ አባል አለዎት?መልስዎ አዎ ከሆነ እነኝህ ምክሮች በይበልጥ እርስዎን ይመለከታሉ። አበላልን ያስተካክሉ፡ በካልሽየም የበለጸጉ ምግቦችን ፤ በተለይ የወተት ተዋጽኦዎችን ፤ ቢያንስ በሳምንት 4 ጊዜ መጠቀም የ አጥንት መሳሳት ተጋላጭነት በደንብ ይቀንሳል (ኢትዮጵያ ውስጥ የተደረገ ጥናት ይህን አረጋግጧል)። እንቅስቃሴ ያዘውትሩ ፡ ለጉልበት ስራ አይቦዝኑ። አጥንት የሚያጠነክሩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን (መ ራመድ፣ ቀላል ሸክሞችን መሸከም፣ ደረጃዎችን መውጣት፣ መደነስ ) ያዘውትሩ። ሲጋራ አያጭሱ ። አጥንት ያሳሳል። የተመጣጠነ ምግብ ይመገቡ። ኮካኮላ መጠጣት አያዘውትሩ። ውስጥ ያለው ፎስፎሪክ አሲድ ከአጥንት መሳሳት ጋር ይያዛልና ፤ ተጋላጭነት ካለብዎ ፤ ኮካኮላ መጠጣት አያዘውትሩ። ክብደትዎ ጤናማ ደረጃ ያድርጉ። መክሳት ወይም ዝቅተኛ ቢኤም አይ ከ አጥንት መሳሳት ጋር ቁርኝት አለው። አለባበስዎን ያሻሽሉ። ጸሀይን አብዝቶ የሚከልል አለባበስ አይኑርዎ። በቂ የጸሀይ ብርሀን ለአጥንትዎ ጤና አስፈላጊ ነው። ቢያንስ በቀን ከ 15 እስከ 30 ደቂቃ በቂ የጸሀይ ብርሀን ማግኘት አለብዎ። በተለይ ሴቶች እድሜያቸው ከ 40 አመት በላይ ከሆነ ፤ መደበኛ የአጥንት ምርመራ ማድረግ አለባቸው። በምግብ በቂ ካልሽየም መጠን መውሰድ ካልተቻለ በእንክብል ይወሰዱ (Calcium and vitamin D supplement)። በተለይ ሴቶች የመውለጃ እደሜያቸው ካለፈ ዶክተር አማክረው ይውሰዱ። 🎯 ስለ አጥንትዎ ጤና እንነጋገር። አጥንትዎ እስኪሳሳ አይጠብቁ። አስቀድመው ይከላከሉ። አጥንትዎን ይገንቡ። ዛሬ የሚያደርጉት ተግባራዊ ለውጥ የአጥንትዎን ጤና ይወስናል። . .
- የምሽት አይነስውርነት እና ቪታሚን ኤ
ለመሆኑ ዳፍንት ሲባል ሰምተው ያውቃሉ? በማታ ሲሄዱ ከብዙ ነገሮች ጋር ይጋጫሉ? ከብርሀን ጨለም ወዳለ ክፍል ሲገቡ አይኖት ለመላመድ ከሌላው ሰው የበለጠ ጊዜ ይወስዳልን? የምሽት አይነስውርነት ቢኖርቦትስ? 👁️ ለመሆኑ የምሽት ዓይነ ስውርነት ምንድን ነው? የምሽት ዓይነ ስውርነት በተለምዶ ስሙ ዳፍንት ሲባል ፤ በህክምና ስሙ ኒካታሎፒያ (ናይት ብላይንድነስ) ተብሎ ይጠራል። ይህም ራሱን የቻለ በሽታ ሳይሆን ከስር ያለ ህመም ምልክት ነው። ይህ ምልክት መታየቱ ከስር የተደበቀ የምግብ አለመመጣጠን ችግር ማመላካቻ ሊሆን ይችላል። ላስተዋለ አይናችን ላይ ቋሚ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ፤ አመጋገባችንን እንድናስተካክል የማስጠንቀቂያ ጥሪ ነው።። ዳፍንት ከቪታሚኢን ኤ እጥረት ባሻገር ከዘረመል ጋር በሚያይዙ የአይን ህመሞች ፣ በአይን ሞራ፣ በግላኮማ፣ በስኳር ህመም፣ በአንዳንድ መድሀኒቶች ፣ ወ.ዘ.ተ... ሊመጣ ይችላል። እንዲሁም ቪታሚን ኤ ወደ ደም የሚገባበት የጨጓራ ክፍል ቀዶ ህክምና ያደረጉ ሰዎችም ይህንን የህመም ምልክት ሊያሳዩ ይችላሉ። ከእነኝህ መሀል ኢትዮጵያ ውስጥ የተንሰራፋው ፤ ከቪታሚአን ኤ እጥረት ጋር የተያያዘው የምሽት አይነ ስውርነት ህመም ነው። ይህም በብዛት የሚስተዋለው ህጻናት እና እርጉዝ ሴቶች ላይ ነው። ይሄ የምግብ መዛባትን አመላካች የሆነ የማንቂያ ጥሪ ነው። ቪታሚን ኤ ለአይናችን ምን ጠቀሜታ አለው? አይናችን ጀርባ ላይ የሚገኝ ፤ ብርሀንን የማንበብ አቅም ያለው ፤ ሬቲና የሚባል ሥሥ አካል አለ። ይህ አካል ስራውን በስርአት እንዲሰራ ቪታሚን ኤ ያስፈልገዋል። ቪታሚአን ኤ ይህ አካል ካሉት ህዋሳት ውስጥ ሮድስ ለተባሉት ህዋሳት ቪታሚን ኤ አስፈላጊ ነው። እነኝህ ህዋሳት በጨለማ(በደበዘዘ ብርሀን) ውስጥ አጥርተን እንድናይ ያስችሉናል። ቪታሚን ኤ ሰውነታችን ውስጥ ሲያንስ ፤ እነኝ ህዋሳት በደበዘዘ/ደካማ ብርሀን ውስጥ ማየት ያዳግታቸዋል። ለዚህም የማታ/ምሽት ጊዜ እይታ ይሰናከላል። በቂ የቪታሚን ኤ ካለ ፤ ሮድስ ስራቸውን መስራት ስለሚችሉ ፤ እይታዎ የጠራ ይሆናል። 👁️ ከምሽት ዓይነ ስውርነት ባሻገር የቪታሚን ኤ እጥረት ዳፋ በምሽት አይነ ስውርነትና በአይን ብቻ አያበቃም። የበሽታ መከላከል ስርአታችን ይዳከማል። ለኢንፌክሽን ተጋላጨነት ይጨምራል። ቪታሚን ኤ እጥረት አይን ላይ የሚያደርሰው ጉዳት (በግራ ቢቶት ስፖትና በቀኝ የኮርኒያ ጠባሳ/ቁስለት) አይን ላይ እራሱ እስከ ቋሚ አይነ ስውርነት የሚያደርስ ጉዳት ሊያመጣ ይችላል። አይን ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በአራት ደረጃ ሊከፈል ይችላል። የመጀመሪያው ደረጃ የምሽት ዓይነ ስውርነት ነው። ለዚህ ነው ማስጠንቀቂያ ነው የሚባለው) ሁለተኛ ደረጃ ሲደርስ አይን ይደርቃል ። ለዚህም አይን ያቃጥላል ፣ ያሳክካል ፣ በቀላሉም ይቆጣል። ሶስተኛ ደረጃ ሲደርስ አይን ላይ እንግዳ የሆኑ ነጫጭ ስጋዎች ማደግ ይጀምራሉ። በህክምና ስማቸው የ ቢቶት ነጠብጣቦች (bitot spots) ይባላሉ። እስከዚህ ደረጃ አይን ላይ የደረሰው ጉዳት በህክምና እርዳታ/ በቪታሚን ኤ እገዛ ሊመለስ/ሊገለበጥ ይችላል። ከዚህ ከባሰ የአይናችን ነጩ ክፍል (ኮርኒያ) ይቆስላል። ጠባሳ ያመጣል። የዚህን ጊዜ አይናችን ላይ ያለው ጉዳት ቋሚ ይሆናል። ህክምና ካልተደረገ እና ቪታሚን ኤ ካልተሰጠ ሙሉ ዓይነ ስውርነት ደረጃ ሊደርስ ይችላል። አመጋገብን በማስተካከል ይህንን ሁሉ መከላከል ይቻላል። 🌑 የዳፍንት ምልክቶች ምንድን ናቸው? ዝቅተኛ ብርሃን ባለባቸው ስፍራዎች ወይም ጨለም ሲል (ሲመሸ/ሲነጋ) ያለ የእይታ ችግር ። ከደማቅ ብርሀን ወደ ደብዛዛ ስፍራ (ከጸሀይ ወደ ቤት ውስጥ ሊሆን ይችላል) ሲገቡ ፤ አይንዎ ለመላመድ ረዥም ጊዜ መውሰድ። ደካማ ብርሃን ባለባቸው (ጨለም ባሉ) ቦታዎች ላይ ሲንቀሳቀሱ ፤ ከነገሮች ጋር መጋጨት ፣ መደናቀፍ እና መውደቅ። ለዚህም ይህ ህመም ምልክት ያለባቸው ሰዎች መሸት ሲል ወይም ለሊት ላይ ለመንቀሳቀስ ይፈራሉ ። ታድያ ላላስታዋለ ሰው እነኝህ ምልክቶች በቸልታ ይታለፋሉ። ይህም ደግሞ ከስር ያለው በሽታ ያለ ህክምና እርዳታ እንዲደረጅ እድል ይሰጣል። 📉 የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የቪታሚን ኤ እጥረት አለም አቀፍ ስርጭት (ኢትዮጵያ ከፍተኛ ስርጭት ካላቸው ሀገራት ትታያለች) ከዱቦክ 2024 የተወሰደ ኢትዮጵያ ከ 5 አመት በታች ባሉ ህጻናት ላይ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እጅጉን የተንሰራፋ ነው። ላለፉት አስርት አመታት የአለም ጤና ድርጅት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ብዙ ጥረቶችን ያደረጉ ቢሆንም ፤ የቫይታሚን ኤ እጥረት በኢትዮጵያ ውስጥ ዋነኛ 3 ንጥረ ነገር እጥረቶች መሀል ይጠቀሳል። ለዚህም ብዙ ይቀረናል። እ.ኤ.አ. በ 2022 የኢትዮጵያ የስነ-ሕዝብ እና ጤና ዳሰሳ እና የዓለም ጤና ድርጅት ባቀረቡት መረጃ መሠረት፡- 🚸 ከ5 ከ 5አመት በታች ከሆኑ ህጻናት መሀከል ቢያንስ አንዱ የቫይታሚን ኤ እጥረት አለበት። 👩🍼 ከ3 ነፍሰ ጡር እናቶች መካከል አንዷ ቪታሚን ኤ እጥረት ይኖርባታል። ይህም የልጇን ህይወት አደጋ ላይ ይጥላል። ⚰️ የቫይታሚን ኤ እጥረት በየአመቱ በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ህጻናት ሞት ምክንያት ነው። ይህንን ሞት ግን መከላከል ይቻላል። ቫይታሚን ኤ ያጠረው ህጻን የበሽታ የመከላከል አቅሙ ስለሚዳከም ፤ የእንደ ኩፍኝ፣ ተቅማጥ ወይም የሳምባ ምች ባሉ የተለመዱ ኢንፌክሽኖች የመሞት እድሉ በ20-30% የበለጠ ነው። 🚨 ይህ ለምን እየሆነ ነው? ሀገራችን ኢትዮጵያ በአመጋገብ ረገድ እድገት አሳይታለች። ሆኖም ግን የቪታሚን ኤ እጥረት በተለይ በገጠራማ አከባቢዎች እንዲሁም ግጭት ባለባቸው አከባቢዎች ፤ እየተንሰራፋ ይገኛል። ለምን? የ አመጋገብ ባህላችን አንድ ወጥ በመሆኑ፡ ብዙ ጊዜ የምንመገበው ምግብ ተመሳሳይ ነው። የተለያየ የምግብ አይነቶችን ደባልቀን አንመገብም። ለዚህም ዝቅተኛ የ ቫይታሚን ኤ መጠን ያላቸው ምግቦችን (እንጀራ፣ምስር ፣ ሽሮ ፣ ወ.ዘ.ተ) አዘውተረን እንመገባለን። ረሃብና ድርቅ፡ በሀገራችን በተለያዩ ስፍራዎች እየተነሱ ያሉት ድርቅ እና ረሀብ የምግብ ዋስትናችንን እያዳከሙት ይገኛሉ። በዚህም አከባቢ የሚኖሩ ሰዎች የቪታሚን ኤ እጥረት ቢኖርባቸው አይደንቅም። የአስተሳሰብ ክፍተት ፡- ህጻናት ሲመገቡ እንቁላል፣ ጉበት ወይም አትክልት ቅድሚያ አይሰጥም። ዝቅተኛ ግንዛቤ፡ የዳፍንት ህመም ምልክት ብዙ ጊዜ በቸልተኝነት ይታለፋል። እንዲሁም የተለያየ ጊዜ እየተነሳ ያለው የኩፍኝ ወረርሽን በበኩሉ ይህንን የቪታሚን ኤ እጥረት እያባባሰ ይገኛል። 🥕 ቫይታሚን ኤ ከየት ማግኘት እንችላለን? ቪታሚን ኤን በተፈጥሮ ከብዙ አይነት ምግቦች ማግኘት እንችላለን። ከእንሰሳት እንዲሁም ከእጽዋት ምንጮች ልናገኘው እንችላለን። እንደ ጉበት፣ እንቁላል አስኳል፣ ወተት፣ አሳ አይነት የእንሰሳት ተዋጽኦዎች በሬቲኖል በሚባለው የቪታሚን ኤ የበለጸጉ ናቸው። አረንጓዴ ቅጠላማ ተክሎች ( ስፒናች፣ የአበሻ ጎመን፣ ጥቅል ጎመን ) እና ቢጫ/ቡርትካናማ ተክሎች ( ዱባ፣ካሮት፣ ማንጎ፣ ስኳር ድንች ) ካሮቲኖይድ የተባለው ቅድመ ቪታሚን ኤ በውስጣቸው አለ። ታድያ የእርስዎ እና የቤተሰብዎ አመጋገብ ላይ እነኝህን ምግቦች ቢደባልቁስ? የግድ እለት ተእለት መጠቀም የለብዎትም። በየሁለት ቀኑ የተቀቀለ እንቁላል ወይም የተቀቀለ ጎመን እንኳን ከሰጡ ፤ በልጅዎ ላይ ትልቅ ለውጥ ሊመጣ ይችላል። 💉 በሀገራችን ምን እየተደረገ ነው? ምንስ ይጎድላል ? ✅ የቫይታሚን ኤ ዘመቻ፡- የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ዩኒሴፍ ለልጆች ከፍተኛ መጠን ያለው የቫይታሚን ኤ ተጨማሪ ምግቦችን በአመት ሁለት ጊዜ ይሰጣሉ። ይህ ህይወትን ቢያድንም ፤ በቂ አይደለም።. ✅ የስነ-ምግብ ምክር፡- እናቶችን በአመጋገብ ዙሪያ በጤና ባለሙያዎች ትምህርት እየተሰጣቸው ይገኛል። ሆኖም ግን የዚህ ትምህርት የማህበረሰብ ተደራሽነት ውስን ነው። ✅ የ በለፀጉ ምግቦች፡ - በቫይታሚን ኤ የበለፀጉ ምግቦች ለማህበረሰብ እየቀረቡ ይገኛሉ። ነገር ግን እነዚህ ለገጠሩ ማህበረሰብ በቀላሉ የማይገኙ ወይም የማይገዙ ናቸው። ✅ የአደጋ ጊዜ የኩፍኝ ምላሽ፡ የኩፍኝ ወረርሽኝ የሚያክሙ ቡድኖች ፤ አሁን የቫይታሚን እንክብሎችን እንደ ድንገተኛ መድህኒቶች አካተው ይይዛሉ። ሆኖም ግን እንደሀገር የሚያስፈልገን ክኒን ብቻ አይደለም። የባህልና የባህሪ ለውጥ ነው። 🌱 እርስዎስ ምን ያድርጉ? 👩🌾 በቤትዎ ዙሪያ ባለ የአትክልት ስፍራ በቫይታሚን ኤ የበለጸጉ እጽዋትን ይትከሉ። 🐓ለልጅዎ ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ እንቁላል ፣ አሳ አልያም ጉበትን ይመግቡ። 🍼 የጡት ወተት የሕፃን የመጀመሪያ የቫይታሚን ኤ ምንጭ ስለሆነ ፤ ጡት ማጥባትን ይደግፉ። 💉 ልጅዎ የኩፍኝ ክትባት መውሰዱን ያረጋግጡ። ማንኛውም ልጅ ኩፍኝ በሽታን ፈጽሞ ያለ መከላከያ ሊገጥመው አይገባም። 🗣️ የመጨረሻ ቃል፡ ማንኛውም ልጅ በቪታሚን ኤ እጥረት ፤ አይኑን ሆነ ህይወቱን ማጣት የለበትም። የቫይታሚን ኤ እጥረት እጣ ፈንታ አይደለም.። በልጅዎ አመጋገብ ላይ ዛሬውኑ ተግባራዊ ለውጥ ያምጡ። የልጅዎን ጤና ያድሱ።
- 🩸 የደም አይነት እና አመጋገብ፡ ሳይንስ ወይስ ተረት ?
ለበርካታ ዓመታት በአለም ዙሪያ የምግብ ገበታዎችን፣ የአመጋገብ ስርአቶችን ፣ የስነ ምግብ ክሊኒኮችን ያዳረሰ ሀሳብ አለ። ይህ ሀሳብ አብዛኛውን የማህበረሰብ ክፍል አስተሳሰብንም ተጠናውቶታል። በማህበራዊ ድህረ ገጾች ያለገደብ ተሰራጭቷል። ይህም የደም አይነት እና የአመጋገብ ቁርኝት ነው። ከዚህ በፊት ሰምተውት ከነበረ ፤ የሚገርም አሳማኝ ይመስላል አይደል? ሳይንሳዊ ሀሳብ ሆኖ ከመቅረቡም ባሻገር ፣ ምስክርነት የሚሰጡለት ሰዎችን በማህበራዊ ድህረገጾች አይተናል። ደምዎት ኦ አይነት ከሆነ ስጋ ያለባቸውን ምግቦች እንዲያዘውትሩ ፤ ኤ ከሆነ ደግሞ የእጽዋት ምግቦችን እንዲመገቡ ይመከራል። ይህ ግን በሳይንስ የሚደገፈው ምን ያህል ነው ብለው ያስባሉ? ያሉን ሳይንሳዊ ጥናቶችስ ምን ይላሉ? 🧬 የደም ዓይነት ምንድን ነው? ይህንን ለመረዳት የደም ዓይነት ምንድን ነው የሚለውን ማወቅ ይኖርብናል። ሰውነታችን በውስጡ ካሉ በትሪሊየን ከሚጠጉ ህዋሳት መሀከል ፤ የደም ህዋሳት ከፍተኛ መጠኑን ይወስዳሉ። የቀይ የደም ህዋሳት ዋነኛ ስራቸው ኦክስጅን ማመመላለስ ሲሆን ፤ በአንድ አንድሚሊየነኛ ሊትር ውስጥ በአማካይ ወድ 5 ሚሊየን የቀይ ደም ህዋሳት ይገኛሉ። እኛ ስራ ቦታ ላይ እንደምናጠልቀው መታወቂያ ወይም ባጅ እነኝህ ቀይ የደም ህዋሳት የ ፕሮቲን መለያ ባጅ (አንቲጅን) አላቸው። ያላቸውንም የአንቲጅን/መታወቂያ አይነት መሰረት በማድረግ ፤ የደም አይነትን እንለያለን። በዚህም ተመስርቶ ብዙ አይነት ስርአቶች ቢኖሩም ፤ በዋነኝነት የምንጠቀማቸው የደም አይነት መለያ ስርአቶች ሁለት ናችው። ኤቢኦ (ABO) ስርአት ፡ ይህም የ ኤ፣ ቢ፣ ኤቢ እና ኦ አንቲጅኖች ተጠቅሞ ይለያል። የ አር ኤች (Rh) ስርአት ፦ ይህም አር ኤች መታወቂያ (አንቲጅን) የያዙትን ፖዘቲቭ ስንል (Rh-positive (+) ) ፤ ያልያዙትን ኔጌቲቭ (Rh-negative (−)) በማለት እንለያለን። ታድያ በመደበኛነት ሁለቱን የደም አይነት ስርአቶች አቆራኝተን የደም አይነትን ኤ + ፣ ኦ−፣ ወ.ዘ.ተ... በማለት ልንለይ እንችላለን። 👉 ያስተውሉ እነዚህ አንቲጂኖች እያንዳንዱ ቀይ የደም ሴል ላይ ያሉ ጥቃቅን ባጅ/መታወቂያ አይነት ምልክት ናቸው። በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት የሰውነታችንን ህዋሳት እና ከእንግዳ ህዋሳትን ለመለየት እነዚህን ባጅዎች ይጠቀማሉ። 💡 ይሁን እንጂ ነገሩ ይህ ነው ፦ እነኝህ ልዩ ባጆች/መታወቂያዎች የቀይ የደም ህዋስ ላይ ብቻ የሚገኙ ምልክቶች ናቸው። ሌላ የሰውነት ህዋሳት ላይ የሉም ። የምግብ መፈጨትን፣ የምግብ መዋሃድን ወይም ስውነታችን ገንቢ ንጥረ ነገሮችን የመቀበል/ የመቃወም ሂደት አይቆጣጠሩም። ታድያስ የቀይ የደም ህዋስ ላይ ያለ መታወቂያ ላይ ተመስርቶ ፤ አመጋገብ ስርአትን መወሰን ይቻላልን? 🌱 የደም ዓይነትና አመጋገብን ያቆራኘው መላምት የመጣው ከየት ነው? ይህ ሀሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበው እንደፈረንጆቹ በ1996 በ ዶክተር ጴጥሮስ ዲ'አዳሞ መፅሃፍ ነው። የመጽሀፉ ርዕስ ለደምዎ አይነት በስርአት ይመገቡ (eat right for your type) የሚል ሲሆን፤ ፅንሰ ሃሳቡ የአመጋገብና የደም አይነትን ቁርኝት ያመላክታል። የመጽሀፉ መላምት እንደሚያመላክተው ከሆነ "እያንዳንዱ የደም አይነት ከሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ (evolution) ጋር የተቆራኘ ነው። በተለያየ ጊዜ የመጡ የዘረመል (ጄኔቲካዊ) ለውጦች የተለያዩ በሰው ልጆች መሀል የተለያዩ የደም አይነቶች እንዲፈጠሩ አስችለዋል። ታድያ ይህ የዘረመል ለውጥ የመጣባቸው ወቅት ላይ ፤ አባቶቻችንን ሲመገቧቸው የነበሩትን ምግቦች ብንመገብ ለሰውነታችን ጠቃሚ ነው። ይህም ከምንመገበው ምግብ ውስጥ ፤ ያሉትን ንጥረ ነገሮች ሰውነታችን በይበልጥ እንዲጠቀም ያስችለዋል። በዚህ የተነሳ አበላላችን ከደም አይነታችን ጋር መመሳሰል አለበት። " ብለው መላምታቸውን ያሰፍራሉ። በመጽሐፉ መሰረት - 🩸 አይነት O "አዳኙ"፡ የመጀመሪያው የደም አይነት ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን። የዛን ጊዜ የሰው ልጅ የእንሰሳት ተዋእጾን አብዝቶ ይመገብ ነበር። ለዚህም ይህ ደም ያለባቸው ሰዎች፤ የከፍተኛ-ፕሮቲን ያላቸው ምግቦችን መመገብ ይኖርባቸዋል። ስጋ ቢያዘውትሩ ይመከራል። 🩸 አይነት A "ገበሬው"፡ ይህ ደግሞ የሰው ልጅ ከ አድን እና ከጫካ ወጥቶ አርሶ መብላት የጀመረ ሰአት የመጣ የደም አይነት ነው ተብሎ ይታሰባል። ለዚህም ይህንን የደም አይነት ያለባቸው ሰዎች ፤አዝእርቶችን ቢያዘውትሩ ይመከራል። 🩸 ዓይነት B ፦ "ዘላኑ" : ይህ ደግሞ የሰው ልጅ ፍልሰት የጀመረበት ሰአት ላይ የመጣ የደም አይነት ነው ተብሎ ይታሰባል። ስለዚህ የዘላኖች አይነት አመጋገብ ማለትም የእንሰሳትም የ እጽዋትም ምግብ ቢመገቡ መልካም ነው። ይህ ደም ያላቸው ሰዎች ከወተት ተዋጽኦ ማዘውተራቸው ጠቃሚ ነው። 🩸 አይነት AB "ዘመናዊ" - ይህ በዝግመት ለውጥ በቅርብ ጊዜ የመጣ የደም አይነት ሲሆን ፤ የ A እና B ድብልቅ ነው። ይህም በፍልሰት ወቅት ኤ እና ቢ የደም አይነት ያላቸው ህዝቦች ሲደባለቁ የመጣ ነው ተብሎ ይታሰባል። የእነኝህ የደም አይነቶች መብላት፣ መጠጣት እንዲሁም ማስወገድ ያለባቸው የምግብ አይነቶች ዝርዝር ሰፊ ነው። ይህ የ ዶክተር ዲ አዳሞ ጥንሥሥ ሀሳብ የያዘ መጽሐፍ ሲሆን ፤ በተጽእኖ ፈጣሪዎች እና አንዳንድ ግለሰቦች ይህ ዝርዝር በተለያየ መልኩ ተለውጦ ሊገኝ ይችላል። በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ይህንን መላምት ተቀብለዋል ። በጤና ላይ ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችም አሞግሰውታል ። እንደውም ይህ አመጋገብ ሕይወታቸውን እንደለወጠ ሲምሉ ሲገዘቱ የሚታዩም አሉ ። ማንኛውም ሀሳብ ከመላምት ወደ ሳይንሳዊ እውነታ ለመሻገር በ ጥናታዊ ጽሁፎች መደገፍ ይኖርበታል። እዚህ ጋር ግን ጥያቂ እንጠይቅ እንደ አለም አቀፍ የደም ልገሳ ማህበረሰብ ከሆነ 47 የደም መለያ ስርአቶች አሉ (ሁለቱን እላይ ጠቅሰናቸዋል)። ታድያ ከእነኝህ ሁሉ የ መለያ ስርአቶች እንዴት አንዱ ብቻ የዚህ መላምት መሰረት ሆነ? ሌሎቹ በዝግመታዊ ለውጥ የመጡ አይደለምን? አንድ የወተት አለርጂ ያለበት የ ቢ የደም አይነት ያለው ሰውስ አመጋገብ ምን ላይ ይመስረት? እንዴትስ ምግብን ከማይቆጣጠር ኦክስጅንን ብቻ ከሚሸከም ህዋስ ላይ ያለ ባጅ ፣ የምግብ መፈጨት ስርአትን ሊወስን ቻለ? ይህ ማለት የጎረቤትዎን መልክ አይቶ ስለ እርስዎ ቤተሰብ ማውራት አይሆንምን? 🔬 ጥናቶች ምን ይላሉ? ይህ አስተሳሰብ ምንም ያህል የተወደደ ቢሆንም ፤ ጥናታዊ ጽሁፎች ይህንን አይደግፉም። ከተደረጉ ጥናቶች ውስጥ ትልቁ ፤ የዛሬ አስር አመት በፊት በፕሎስ ዋን (PLOS ONE (2014) የታተመ ፤ በቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የተገኘ ነው። ይህ ጥናት 1,400 ሰዎች ላይ የተደረገ ሲሆን ፤ ዋነኛ ግኝቶቹ የሚከተሎት ናቸው። ይህ አስተሳሰብ የሚመክረው ፤ የጤናማ የአመጋገብ ልማድን (እንደ አትክልት፣ አዝዕርት፣ አነስተኛ የታሸጉ ምግቦችን) የተከተሉ ሰዎች፤ የደም ዓይነት ምንም ይሁን ምን የተሻለ ጤንነት አሳይተዋል። ሆኖም ግን የተሻለ የጤና ደረጃ መሆናቸው ፤ በደም ዓይነት ላይ ከተመሰረተ የአመጋገብ ሥርዓት ጋር አልተገናኘም። በሃርቫርድ የሕክምና ትምህርት ቤት ፣ በብሪታንያ የስነ ምግብ ማኅበርም የተደረጉ ጥናቶች ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። የደም ዓይነት አመጋገብን ለመወሰን እንደሚችል የሚያሳይ ሳይንሳዊ ማስረጃ የለም። 🧙🏾 ♀️ ትርክቶች እና የህክምና እውነታዎች በዚህ ዙሪያ የተነሱ ጥቂት ሀሳቦችን እንመርምር። ሀሳብ ተረት ወይስ እውነታ? አአይነት O ሰዎች ስጋን በተሻለ መንገድ ይፈጫሉ ❌ ተረት አይነት A ህዝብ አነስተኛ የሆድ አሲድ አለው ❌ ተረት በብዙ ምግቦች ውስጥ የሚገኙት ሌክቲን (የፕሮቲን አይነት) የሚባሉት ንጥረነገሮች አፈጫጨት ፤ እንደየደም አይነቱ ይለያያል። ⚠️ በከፊል እውነታ አለው። የሌክቲን ፕሮቲኖች ከደም አይነቶች ጋር የተለያየ መስተጋብር አላቸው። ሆኖም ግን ይህ አመጋገብ ጋር አይያዝም። አመጋገብን አይወስንም። አይነት AB በባህሪው መንፈሳዊ/ስሜታዊ አይነት ነው ❌ ተረት 🍽️ ታዲያ አንዳንድ ሰዎች በእነዚህ የአመጋገብ ዓይነቶች የተሻለ ስሜት የሚሰማቸው ለምንድን ነው? ምላሹ ቀላል ነው። ይህ መላምት የሚመክራቸው አመጋገቦች ጤናማ አመጋገብ ስርአት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። የታሸገ ምግብ እንዲቀንሱ ፣ የተፈጥሮ ግብአቶችን እንዲጠቀሙ ፣ አለመጠን የበሰሉ ምግቦችንና የዘይት አይነታቸው ጤናማ ያልሆኑ የተጠበሱ ፈጣን ምግቦችን (fast foods) እንዲያስወግዱ ይመክራል። እንዲሁም በቤት ውስጥ የሚዘጋጁ ተጨማሪ ምግቦችን እንዲያዘወትሩ ይመክራል። ይህንን አመጋገብ ስርአት ከተጠቀሙ ጤናማ ይሆናሉ። አመጋገብ ስርአቱ የተወገዱ የምግብ አማራጮች (ለምሳሌ ቀይ ስጋ)ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮችን መተኪያ የምግብ አማራጮችንም (ለምሳሌ የእጽዋት የፕሮቲን ምንጭ) ይመክራል። ለዚህም ጤናማ ምግብ እንዲመገቡ ያደርጋል። መልካሙ ውጤቱ ፤ ከደምዎ ጋር ሳይሆን ከልማድዎ ጋር የተያያዘ ነው። ⚖️ ታድያ የአመጋገብ ስርአትዎን በምን ላይ የተመሰረተ ይሁን? የአመጋገብ ስርአትዎን ቀይ የደም ህዋስ ላይ የሚገኝ መለያ ባጅ (አንቲጅን) ላይ ከመመስረት ይልቅ ፤ በሚከተሉት ላይ ያስመርኩዙ፡ 🧬 ጀነቲክስ/ዘረመል 🦠 የምግብ ቱቦ ላይ ያሉ መልካም ባክቴሪያዎች ስርጭት 🍽️ የሰውነቶት ኡደት ፍጥነት (ሜታቦሊክ) 🧪 ባለብዎ የህክምና ሁኔታዎች (ለምሳሌ የስኳር በሽታ፣ የደም ግፊት፣ የሴሊያክ ህመም ፣ የ ወተት አለርጂ ፣ የሀሞት በሽታ ፣ ወ.ዘ.ተ...) 🎯 በአኗኗር ዘይቤዎት እና የሕይወት ግብዎ 👩 ⚕️ በስነ ምግብ እና የሕክምና ባሉሙያ የተሰጠ የአመጋገብ ምክር የደም ዓይነትስ? የደም አይነት ደም በመስጠት ረገድ በጣም አስፈላጊ ነው ። በምግብ እቅድዎ ውስጥ ግን አይደለም። 🩺ማሳረጊያ ሃሳብ ይህ አስገራሚ መላምት እንጂ የህክምና እውነታ አይደለም። የደም ዓይነትዎ ለሰውነትዎ የሚገባውን ፍጹም የአመጋገብ ልማድ እንደሚወስን ለማመን ቀላል ነው። የደምዎ አይነት በ ድንገተኛ ክፍል ፣ በአይሲዩ ፣ በ ቀዶ ጥገና ክፍል ውስጥ ሊጠቅም ይችላል። በገበታዎ ላይ ግን ትርጉም የላቸውም። ጤና ደግሞ ፈጽሞ ስለ አቋራጭ መፍትሔ አይደለም። በማስረጃ ላይ የተደገፉ ፣ በሳይንስ የሚመከሩ የጤና መፍትሔዎች ያስቡ። እንደ ንፋስ ገነው በሚጠፉ ኢ፟ሳይንሳዊ የጤና መፍትሔዎች(ፋሽኖች) አይታለሉ።
- She Said She Fell! The Hidden Crisis of Gender Based Violence in Ethiopia
🩸 If she suffered while pregnant, what happens to her on ordinary days? 🏥 Five Years Ago at Zewditu Memorial Hospital (true story)... It was around midday when she arrived. A young pregnant woman, clutching her abdomen. She was in severe pain. Her face told a story her words refused to—raccoon eyes, deep bruises, and swelling in places no staircase/floor could reach. Her husband was right beside her, concerned, helpful—too helpful. She said she had fallen down, landed directly on her gravid belly. This is an unlikely story. Her husband confirmed by nodding his head. The obstetric emergency team acted fast. Ultrasound revealed a hemorrhage behind the placenta, the very organ keeping her baby alive. Her clinical signs show trauma (abuse)—the kind not caused by accident. She denied! Without her consent, there was no way of reporting it. As she was in labor, she was admitted immediately. The pain of laboring mothers with APH is significantly higher than normal labor. Her pain was intense. After hours of labor, she gave birth to a beautiful, healthy baby boy 👩⚕️ But even in that moment of joy, one thought lingered in the healthcare team: “If she suffered while pregnant, what happens to her on ordinary days?” ❗What Is Gender-Based Violence? The World Health Organization (WHO) describes Gender-Based Violence (GBV) as: 📝 "Any harmful act that is perpetrated against a person's will, and that is based on socially ascribed gender differences. It includes: 🥊 Physical assault (beatings, choking, slapping) ❌ Sexual violence (rape, coercion, harassment) 😔 Psychological abuse (threats, humiliation, isolation) 💸 Economic control (withholding money, sabotaging employment) ⚔️ Harmful traditional practices (child marriage, FGM, wife inheritance) 📊 The Statistics We Can No Longer Ignore In Ethiopia, the statistics are alarming. 👩❤️👨 One in three married women (34%) has ever experienced intimate partner violence (IPV) at least once in their lives ([EDHS, 2016]; [Chernet & Cherie, 2020]). 🩹 23.5% of women had experienced physical IPV ([Chernet & Cherie, 2020]) 🚫 One in ten women ( 10.1%) indicated having had sexual IPV ([Chernet & Cherie, 2020]). 💔 One in four women (24%) of women indicated having had emotional IPV ([Chernet & Cherie, 2020]). ⏱️ Three in ten married women (30%) had experienced IPV within the last year ([Chernet & Cherie, 2020]). ✂️ Two-thirds of women (65%) in the age group 15–49 have been subjected to Female Genital Mutilation/Cutting (FGM/C) ([EDHS, 2016]) (the number is declining) 👧 Approximately 40% of Ethiopian girls are married under the age of 18, and 14% under the age of 15 ([UN Women Africa, 2022]; [Child Marriage Data Portal, 2023]). 🤐 One in four women received support after being subjected to gender-based violence, with about 66% not reporting the violence to anyone ([EDHS, 2016]; [UN Women Africa, 2022]). 🧠 63% of women and 68% of men consider it acceptable for a husband to beat his wife in certain circumstances ([EDHS, 2016]). 🚨 We have to understand that these are not just numbers. They are a distress call. Every statistic is a woman like Zewditu. Every statistic is a story waiting to be told. 🧨 Why Do Survivors Keep Quiet? 🕯️ Cultural Silence and Shame Our cultural structure and religious teachings shame and suppress women's voices. Holding the pain is a virtue. It is a sacrifice to keep family honor. Speaking out is to betray. Family pride comes before personal safety. 🏚️ No Safe Place to Go Few shelters, fewer trauma units, and limited resources are limited as a nation. Home is not safe for these women. They just have no place to go. 🏥 Health Workers Are Not Prepared Most health workers are not adequately trained at all in how to diagnose or treat GBV. Survivors are stitched up and sent out, and brought back—often to the same people who assaulted them. This could have been the possibility with that pregnant Mother. ⚖️ The Legal System also Fails Them Laws exist, but there is a gap. Cases linger for years. Moreover, victims relive their trauma all over again when they follow legal proceedings. Moreover, they fear retaliation or being accused themselves. 💵 Economic Dependence It is nearly impossible to leave an abuser if you're financially trapped. Some women are faced with a choice between homelessness and abuse. The choice is never simple 🏥 Time to Step Up the Health System The health system can be the first lifeline. It is the point of first contact for most physically abused women. We need to transform clinics and hospitals into spaces where healing and protection occur, rather than just treatment. Debark One stop Clinic When a woman shows up at a center with suspicious trauma, the response should not be: "Treat and send home." It should be: 🗣️ "Are you safe?" 🤝 "Can we help you more than the physical treatment?" 🧍♀️ "You are not alone." We have to understand, mothers will not risk their family. They would choose to suffer in silence rather than incriminate their Family. To be their voice, we have to adjust our response. This simple action can save the lives of the mother and her children. It will break the cycle of abuse. ✅ A Way Forward: Solutions Ethiopia Must Adopt Opening of Debark One Stop Clinic Ending GBV is not a pipe dream. It requires will, policy, compassion, and a sense of urgency. Ethiopia has taken important steps. But there is still a long road ahead. Survivors are falling through the cracks. We must: 👩⚕️ Train all health workers in GBV care → GBV is already integrated into medical and nursing education. However, practical, nationwide training and survivor-friendly spaces in clinics are still lacking. 🏥 Expand and sustain GBV response units in hospitals → One-Stop Centers supported by the government and partners are active in several regions, yet access and rural coverage remain limited. 🏡 Build safer shelters and strengthen helplines → Non-governmental organizations run shelters and hotlines but demand far exceeds supply, especially outside major cities. 📺 Use media as a force for change, not silence → Media outlets are increasingly covering GBV cases. Campaigns exist. Yet consistency is needed. They should be used strategically to challenge harmful norms. 🏫 Integrate consent and gender respect in school curricula → Efforts to revise school content are underway, but practical life skills on relationships, consent, and equality should be scaled across all education levels. ⛪ Mobilize religious and community leaders to lead change → Influential voices have started speaking up—especially around FGM and child marriage—but ongoing training and public support are needed to shift norms at the grassroots. 🚫 Enforce GBV laws with zero tolerance ⚖️ Ensure legal and financial support for survivors → Legal aid and psychosocial support are provided by civil society groups, but broader access—especially for poor and rural women—requires more funding and government coordination. 📣 Last Word: Silence is the Enemy The woman at Zewditu lived. The baby lived. But her tale is a warning—one of how near we're brought to disaster when we turn away. 🗨️ "She said she fell." We must ask, listen, and believe. 🚫 GBV isn't normal 🚫 It isn't cultural. 🚫 It isn't okay. ✅ It's preventable. It takes all of us to stop it. It starts with you! 🔁 Let's stop asking why survivors stayed. ✅ Let's begin to ask what we need to do so they don't have to. Resources for Further Reading Child Marriage Data Portal. (2023). Ethiopia Country Profile. Chernet, A. G., & Cherie, A. (2020). Prevalence and determinants of intimate partner violence among reproductive-age women in Ethiopia: A community-based study using the 2016 EDHS data. BMC Women’s Health, 20, 22. END-GBV Ethiopia Ethiopian Central Statistical Agency (CSA) & ICF. (2016). Ethiopia Demographic and Health Survey 2016. Mapping of Intimate Partner Violence: Evidence From a National Population Survey Trends and Determinants of Female Genital Mutilation in Ethiopia: Multilevel Analysis of 2000, 2005, and 2016 Ethiopian Demographic and Health Surveys UN Women Africa. (2022). Analysis of Violence Against Women in Ethiopia. UNICEF. (2020). Female Genital Mutilation: A New Generation Calls for Ending an Old Practice. Violence Against Women Prevalence Estimates, 2018
- ትኩስ ምግብ በመብላት ስለሚመጣው ካንሰር ያውቃሉ?
የሚወዱት ምግብ ምንድነው? በጠዋት በቅቤ የታሸ እጅግ ጣፋጭ ትኩስ ገንፎ እየበሉ ፤ በቅመሞች በጣፈጠ ሻይ ማወራረድ? ከቤተስብዎ ጋር እየተጋሩ ቢበሉትስ ? ይህ ቁርስ ብቻ አይደለም ፤ የአብሮነታችን መገለጫ የባህላችን አካል ነው። ጾም ስንፈሰክ ከምንመርጣቸው ምግቦች መሀል ይካተታል። ክተሰበርን ወይም በሽታ ከጣለን ደግሞ ትኩስ መረቅ እንፋሎቱ ሳይወጣ መጠጣት እንመርጣለን። ታድያ ይህ የአመጋገብ ባህላችን መሰረቱ ፍቅርና አብሮነት ቢሆንም ይዞት የሚመጣው ነቀርሳ እንዳለስ ያውቃሉ? እውነታው ይሄ ነው። አለም አቀፍ የጉሮሮ ካንሰር ስርጭት። ኢትዮጵያ ፈዛዛ ሰማያዊ ከለር ያላት ሲሆን ፤ ይህ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ ካለ 100,000 ማህበረሰብ መሐል ከ 2 እስከ 3 ሰው (1.8 -2.9)የጉሮሮ ካንስር ይኖርበታል ማለት ነው። ይህ ነቀርሳ የጉሮሮ ካንሰር (esophageal cancer) ሲባል ፤ እጅጉን ገዳይ ከሚባሉ የካንሰር አይነቶች ውስጥ ነው። በሽታው ብዙ ጊዜ አርፍዶ የሚታወቅ ሲሆን ፤ ትኩስ ምግብ የሚመገቡ የኢትዮጵያ ክፍሎች ላይ በዝምታ እየተንሰራፋ ይገኛል። በፈረንጆች በ 2020 በወጣው አለም አቀፍ ጥናት (GLOBOCAN 2020) መሰረት ኢትዮጵያ ውስጥ በ 2020 ብቻ 1,674 አዳዲስ የጉሮሮ ካንሰር ታማሚዎች የተገኙ ሲሆን ፤ 87 ፐርሰንቱ (1455 ሰዎች) በዚሁ አመት ሞተዋል። ለዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ዋነኛ ገዳይ ከሚባሉ 10 ካንሰሮች ውስጥ የጉሮሮ ካንሰር ይጠቀሳል። አሳዛኙ እውነታ ፡ አብዛኞቹ የጉሮሮ ካንሰር ተጠቂዎች አጭሰው የማያውቁ ፣ የማይጠጡ እና በቤተሰባቸው የጉሮሮ ካንሰር ታሪክ የሌላቸው ናቸው። የኢትዮጵያ አመጋገብ ለምን አስጊ ሁኔታ ሊሆን ይችላል? በባህላችን ትኩስ ነገር እንወዳለን። እንፋሎት ሳይወጣ ሳይቀዘቅዝ ተጋፍተን መብላት ይመከራል። ቡናም ፣ ሻይም ፣ መረቅም፣ ገንፎም፣ ወ.ዘ.ተ... ሳይቀዘቅዝ ነው መበላት ያለበት ብለን እናስባለን። አፋችንን እያቃጠለን " ሥ ....ሥ ...ሥ " እያልን ፤ በትንፋሽ እያበረድን መጠጣት ልምድ ነው። ካበረድነው መልካም አይደለም። አንዳንዴ ጋባዣችን ከማክበር ፤ ምግቡን ከመውደድ ጋር እናያይዘዋለን። በአንድ በኩልም ለጤና መልካም አድርገን እናስባለን። አንድ ሰው ከተሰበረ የአጃ ሾርባ ወይም የበግ መረቅ በትኩሱ እንዲጠጣ እንመክራለን። ጉንፋን ከያዘን ትኩስ ወተት፣ ትኩስ ሻይ በቶሎ መጠጣቱ ፍቱን ያደርገዋል። ብርድ ብርድ ካለማ... ምክራችን እንዳለ ትኩስ ነገር ነው። ይህ አስተሳሰባችን በአንድ በኩል ትክክል ነው። የበሽታ አምጪ ተህዋሳትን ሙቀቱ ስለሚገል ፣ ከምግብ ጋር የተያያዘ ኢንፌክሽን የመያዝ እድላችን ይቀንሳል። ታድያ ግን በእጃችን ለመያዝ የከበደ ፣ ለአፋችን ያቃጠለ ምግብ ለጉሮሮአችንስ ምን ያደርግ ይሆን? ለዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ የጉሮሮ ካንሰር በከፍተኛ ደረጃ እየተመዘገበ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ በ ጉሮሮ ካንሰር ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች ምን ይላሉ? ✅ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ክፍል ውስጥ በተደረገ የ 5 አመት ዳሰሳ ጥናት ፤ በጉሮሮ ካንሰር ታማሚዎች ላይ የሚታየው የካንሰር አይነት ፤ ለረዥም ጊዜ ካለ የትኩስ ነገር ጉዳት ጋር ተያይዥነት እንዳለው አመላክቷል። ✅ በጳውሎስ ሆስፒታል የተደረገ ጥናትም ተመሳሳይ ውጤት ከማሳየቱ ባሻገር ፤ 85 ፐርሰንት የሚሆኑት ታማሚዎች በሽታው ከገፋ(ከደረጀ) በኋላ ለህክምና እንደሚሄዱ አሳይቷል። ✅ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተደረገ ጥናት ደግሞ ፤ ህመሙ ካለባቸው ሰዎች መሀከል 99 ፐርሰንቱ በየቀኑ ትኩስ ነገር አዘውተረው እንደሚጠቀሙ አግኝቷል። ✅ የካንሰሩን መንስኤዎችን ለመለየት በአዲስ አበባ ከተማ የተደረገ ጥናት በበኩሉ ፤ ቀን በቀን በጣም ትኩስ ነገሮችን መጠቀም ፣ አትክልት እና ፍራፍሬን አዘውትሮ አለመመገብ ለህመሙ እንደሚያጋልጥ ገልጻል። ግን ትኩስ ነገር እውነት ካንሰር ያመጣልን ወይስ መላምት ነው? ከ65 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ሙቀት ያላቸው ምግቦች ካንሰር አምጪ (Category 2A) ተብለው ፤ በ አለም ጤና ድርጅት አካል የሆነው በአለም አቀፍ የካንሰር ምርምር ኤጀንሲ( IARC) ተፈርጀዋል። እንዴት ካንሰር ያመጣሉ? የጉሮሮ ስጋችን ለከፍተኛ ሙቀት ሲጋለጥ ፤ የጉሮሮ ስጋችንን በሙቀቱ ይቃጠላል። ይህ ደግሞ ምግቡ የነካው የጉሮሮ ስጋ እንዲቆጣ ወይም እንዲቆስል ያደርጋል። ይህ መቁሰል እና መቆጣት አንዴ ወይም የተወሰኑ ጊዜያት ብቻ ከሆነ ፤ እራሱን ሙሉ በሙሉ ስለሚጠግን ችግር የለውም። ታድያ ግን ሲደጋገም ፤ የጉሮሮአችን ህዋሳት ወደ ካንሰር ህዋሳት መለወጥ ይጀምራሉ። የዚህን ጊዜ የጉሮሮ ካንሰር ይሆናል። በላንሴት ኦንኮሎጂ የሪሰርች መጽሄት ላይ እ.ኤ.አ በ2019 ላይ የታተመ ትንታኔም ፤ አዘውትረው ትኩስ መጠጦችን የሚጠጡ ሰዎች ፤ የጉሮሮ ካንሰር የመያዝ እድላቸው በ 90% እንደሚጨምር ይዘግባል። ምልክቶቹ ካልተጠነቀቅን ፤ ካልተከላከልን ፤ ካንሰሩ ደርጅቶ ጉሮሮን እስኪያጠብ ድረስ ምልክት አያሳይም። ⚠️ መጀመሪያ ላይ የሚታዩ ምልክቶች፡- ደረቅ ምግብ የመዋጥ ችግር። ሲውጡ መቸገር። ታማሚዎች በምግብ መታነቅ ብለው ሊገልጹት ይችላሉ። የደረት ህመም ወይም ደረት ላይ ደስ የማይል ስሜት መሰማት ወይም ደረት መጫን። የጨጓራ የሜመስል አይነት የማቃጠል ስሜት ድካም ትንሽ በልቶ መጥገብ ክብደት መቀነስ ⚠️ በሽታው እየገፋ ሲመጣ የሚታዩ ምልክቶች፡- ፈሳሽ በሚውጡበት ጊዜ ህመም መሰማት ወይም መጠጥ መዋጥ አለምቻል። ድምጽ መለወጥ ረዥም ጊዜ የሚቆይ ሳል ትውከት (ደም የቀላቀለ) ክብደት ይብሱኑ መቀነስ። ይብሱኑ አብዛኞቹ ታማሜዎች ወደ ህክምና የሚመጡት ህመሞቹን እንደተመለከቱ ሳይሆን ፤ ከ 4 እስከ 7 ወር ቆይተው ፤ ወይም ምልክቶቹ አስቸጋሪ ሲሆኑባቸው ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ 80% የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን አርፍደው ነው ካንሰሩ የሚገኝባቸው። ይህ ደግሞ የህክምና ውጤታማነትን ይቀንሳል። ገንፎ ተዉ እያልን አይደለም። ቡናም ፣ሻይም እንዲሁ። ይህ በባህላችን ላይ የሚደረግ ጦርነት አይደለም። ይህ ግንዛቤ ማስጨበጫ ነው። ገንፎም፣ ቡና፣ ሻይ፣ ወ.ዘ.ተ... ተዉ እያልን አይደለም ። ችግሩ ከምግቡ ሳይሆን ከሙቀቱ ነውና አስፈላጊውን ጥንቃቄ ያድርጉ። ካንሰር ታመው ከመምጣትዎ በፊት ማቆም የሚችሉት እርስዎ መሆንዎን አይርሱ! ✅ መከላከያ መንገዶቹ ትኩስ ምግብ ከመብላትዎ ወይም ትኩስ መጠጦችን ከመጠጣትዎ በፊት ከ5-10 ደቂቃዎች ይጠብቁ ። ትንሽ ይቀዝቅዝ። የሚመገቡት ምግብ ቶሎ እንዲቀዘቅዝ የሴራሚክ እና የ እንጨት መመገቢያዎችን መጠቀም ይችላሉ። ከትኩስ ይልቅ የበረደ ምግብ ጥሩ መሆኑን ለልጆችዎ ይምከሩ። ብሄራዊ ምላሹ፡ ገና ብዙ ይቀረናል። ሀገራችን በአሁኑ ወቅት የጉሮሮ ካንሰርን በተመለከተ አገር አቀፍ የ ስክሪኒንግ ወይም የቅድመ ምርመራ ፕሮግራም የላትም። የብሔራዊ የካንሰር መቆጣጠሪያ እቅድ (2020-2029) የጉሮሮ ካንሰርን እያደገ እንዳለ ስጋት ቢወስደውም ፤ ገና ብዙ ይቀራል። ለቅድመ ምርመራ ወይም ምልክቶቹ ለይተው ቀድመው ካልመጡ ፤ የህክምና አማራጮቹ የተገደቡ ናቸው። ውጤታማነታቸውም እንዲሁ። የእነኝህም ህክምናዎች ተደራሽነት ውስን ነው። ማሳረጊያ ነጥብ ባህላችንን ሳንተው ጤናችንን እንጠብቅ። ጉሮሮአችንን እንንከባከብ። ትኩስ ነገር ከመመገብዎ በፊት ትንሽ ይጠብቁ። ይብረድ። እስከዛ ከቤተሰብዎ ጋር ይጫወቱ። ይህንን መረጃ ለሌሎች ያጋሩ። እነሱም ግንዛቤ ይኑራቸው። ጤናቸውን ይጠብቁ።












