top of page

ሶስት አመት የፈጀው አለም አቀፍ ወረርሽኝ፡🐒 የዝንጀሮ ፈንጣጣ

Updated: Jul 11

ስለ ዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ ምን ያህል ያውቃሉ?

ree

📜 ታሪኩ በ1958 ጀመረ…


እንደፈረንጆቹ 1958 ዓ.ም በዴንማርክ የሚገኙ ሳይንቲስቶች ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በጦጣ ዝርያዎች መሀከል ፈንጣጣ (ፖክስ) የሚመስል ቫይረስ አገኙ። ቫይረሱ ያልተለመደ የፈንጣጣ አይነት ስለነበር ፤ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ብለው ሰየሙት (monkeypox)። በዝንጀሮ ይሰየም እንጅ ፤ የዱር አይጥ ዝርያዎችንም እንደሚያጠቃ በቀጣይ አመታት ታውቋል። ከዚህ ባሻገር ቫይረሱ ከእንሰሳት ወደ ሰው ልጅ የመተላለፍ አቅም አለው።

እንደፈረንጆቹ በ1970 ዓ.ም የመጀመሪያው የቫይረሱ ታማሚ ሰው ፤ በአፍሪካዊቷ አገር በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተገኘ።

በቀጣይ አመታት ውስጥ ታድያ በዩጋንዳ ፣ በቡሩንዲ ፣ በሴራሊዮን እና በሌሎች በርካታ የአፍሪካ ሀገራትም ተሰራጨ። ከአፍሪካ ባሻገር ቫይረሱ በ ህንድ፣ በካናዳ ፣ አሜሪካ እንዲሁም አንዳንድ የአውሮፓ ሀገር እንደተሰራጨ ሪፖርቶች ያሳያሉ። የቫይረሱ የመጀመሪያ ስርጭቶች በሀገራት ደረጃ የተወሰኑ ነበሩ።


🌍የአለም አቀፍ ወረርሽኝ


የዛሬ ሶስት አመት ገደማ በፈረንጆች ሜይ ወር 2022 ዓ.ም ፤ የቫይረሱ ስርጭት ወደ አለም አቀፍ ደረጃ አደገ። ቫይረሱ መጀመሪያ በተገኘባት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በቡሪንዲ ቫይረሱ እጅጉን ተስፋፋ። በአፍሪካ ፣ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ እና አንዳንድ እስያ ክፍሎች በብዛት ተሰራጨ።

እንደ ፈረንጆች ኦገስት 2022 የ ዝንጀሮ ፈንጣጣ አለም አቀፍ ስርጭት
እንደ ፈረንጆች ኦገስት 2022 የ ዝንጀሮ ፈንጣጣ አለም አቀፍ ስርጭት

ጎረቤታችን ኬንያም የመጀመሪያው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ ከ አንድ አመት በፊት ተገኘ። እስከአሁን ድረስ ቫይረሱ ስርጭት በኬንያ አልቆመም። ይህንን ስርጭት ለመግታት የኬንያ መንግስት ከሁለት ወር በፊት (በፈረንጆቹ አፕሪል 2025) ወደ 10 ሺ የሚጠጋ የቫይረሱ ክትባት አስገብታለች።


ሲዲሲ ከ ሁለት ሳምንት በፊት እንዳወጣው መረጃ፤ እስከ አሁን በአለም ዙሪያ ቫይረሱ ወደ102 000 ሰዎች ያጠቃ ሲሆን ፤  220 ደግሞ በቫይረሱ የተነሳ ሞተዋል። 
ታድያ ምን ተለወጠ? ለምን ላለፉት 50 አመታት ያወቅነው ቫይረስ ፤ አሁን ላይ አለም አቀፍ ወረርሽኝ አመጣ?

ይህ ቫይረስ ሁለት ዋነኛ ዝርያዎች ሲኖሩት እነሱም ክላድ አንድ (ኮንጎን ያጠቃው ዝርያ) እና ክላድ ሁለት (ምእራብ አፍሪካ አገራትን ያጠቃ ዝርያ) ተብለው ይለያሉ። በፈረንጆች 2022 ዓ.ም ጀምሮ የእነኝህ ዝርያዎች ባህሪ ለውጥ አሳይቷል። ይህም ለውጥ ዘረመል ደርጃ የመጣ ለውጥ ሲሆን ፤ በሳይንቲስቶች በጥልቀት እየተጠና ይገኛል።


ከዚህም ባሻገር በቅርብ አመታት ውስጥ የሰው ልጆች ራሱ በሽታ በመከላከል ዙሪያ ላይ ያመጧቸው ለውጦች ፤ ለቫይረሱ አጋላጭነትን እንደጨመሩ ጥናቶች ይጠቁማሉ (emergence of APOBEC3 mutation)።  


የቫይረሱ ስርጭት በኢትዮጵያ


ሀገራች ኢትዮጵያም የዚህ በሽታ ገፈት ከደረሳት ይኸው ሀያ አራት ቀናት ተቆጠሩ። የመጀመሪያው የቫይረሱ ታማሚ የ 21 ቀን እድሜ ያለው ጨቅላ ህጻን ልጅ ሲሆን አባቱ ጎረቤት አገር ሄዶ እንደነበር ጤና ጥበቃ ግንቦት 17 2017 ዓ.ም በለቀቀው መግለጫ ጠቁማል።


ጤና ጥበቃ ሚኒስተር ሰኔ 10 2017 ዓ.ም እንደለቀቀው መረጃ፤ ከተደረጉት 220 ላብራቶሪ ምርመራዎች መሀከል የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ 22 ሰዎች ላይ መገኘቱን ገልጿል። ከተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ 14 ሲያገግሙ፤ ሰባቱ ለይቶ ህክምና ላይ እንደሚገኙ አመላክቷል። ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ምክንያት እስከአሁን አንድ ሰው መሞቱን ጠቅሷል።


🦠 የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ ምንድነው?


ይህ ቫይረስ ስሙ እንደሚያመላክተው የፈንጣጣ ቫይረስ አይነት ነው። በፊት ከምናውቃቸው የሰው ፈንጣጣ (small pox) ፣ የከብት ፈንጣጣ (cow pox) ቫይረሶች ጋር እጅጉን ይመሳሰላል። ዘራቸውም ባህሪያቸውም ተቀራራቢ ነው። የህመሙ ዋነኛ ምልክቶቹ

የቫይረሱ ሽፍታ በቀናቶች ውስጥ የሚያሳየውለውጥ
የቫይረሱ ሽፍታ በቀናቶች ውስጥ የሚያሳየውለውጥ

  • እንደ ጉንፋን የሚመስሉ ምልክቶች

  • ሽፍታ

  • ትኩሳት

  • የንፍፊት እብጠትና

  • ድካም ናቸው።

ሕመሙ ካየለ ግን ፤ እስከሞት የሚያደርሱ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል።


🚨 ህመሙ እንዴት ይሰራጫል?

ree

ቫይረሱ የሚተላለፈው ህመሙ ካለበት ሰው ጋር


👥 ቆዳ ለቆዳ ንክኪ ሲኖር

💋ግብረ-ሥጋ ግንኙነት ካለ

🤒 አልጋ ልብስ (ብርድ ልብስ) ፣ ልብስ ወይም ፎጣ ከተጋራን

💨 ህመሙ ያለበት ሰው ካሳለብን/ ካስነጠሰብን

🐀 በበሽታው ከተያዙ እንስሳት (በተለይ ከአይጦችና ጦጣ ዝርያዎች) ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ሲኖረን ነው።


❗ቫይረሱ እንደ ኮቪድ አየር ወለድ አይደለም። በትንፋሽ የመተላለፍ እድል ይኑረው እንጂ ፤ ዋነኛ መተላለፊያው የአካል ንክኪ ነው።❗

❓ ማን የበለጠ አደጋ ላይ ነው?


ለቫይረሱ ለመያዝ ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸው አካላት የሚከተሉት ናቸው።


🔹 የጤና ባለሙያዎች

🔹 የወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ

🔹ከአንድ በላይ ሰው ጋር ግብረስጋ ግንኙነት የሚፈጽሙ ሰዎች

🔹 ህጻናት እና የበሽታ መከላከል አቅም የሌላቸው ሰዎች



🔍 እርስዎ ሊጠነቁዋቸው የሚገቡ ምልክቶች፡-


  • ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት እና የሰውነት ህመም


  • ንፍፊት እብጠት ካለ


  • በአፍ ፣ በብልት ፣ በእጆች ፣ በእግሮች ወይም በአይን አካባቢ ያሉ ሽፍታዎች


  • እነኝህ ሽፍታዎች ከቀናት በኋላ ወደ ቁስል ይለወጣሉ


🕑 ምልክቶች የሚታዩት በተጋለጡ ከ5-21 ቀናት በኋላ ነው።

💉 ሕክምናውና እና ውጤቱ

ree

ቫይረሱ አብዛኛው ሰው ከ2-4 ሳምንታት ውስጥ ይድናል። ለቫይረሱ ታካሚ የሚደረጉት ህክምናዎች የሚከተሉት ናቸው።


🔹 የድጋፍ እንክብካቤ (ፈሳሽ፣ ህመም ማስታገሻ፣ ቁስሉን መንከባከብ) ቁልፍ ነው።

🔹 የፀረ-ቫይረስ መድሃኒቶች ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ.

🔹 ለፈንጣጣ የተሰሩ ክትባቶች ይከላከሉታል (ከፈንጣጣ ጋር ስለሚመሳሰል)።


ሆኖም ግን በኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ የአፍሪካ አገሮች መድሀኒቶቹ አቅራቦት ውስን ነው።


🛡️ መከላከያ መንገዶች


እራስዎን እና ማህበረሰብዎን ለመጠበቅ እነኝህን ያድርጉ።


✅ ምልክቱን ከታየ ሰው ጋር የቅርብ ግንኙነትን ያስወግዱ።

✅ ልብስ፣ አንሶላ ወይም ፎጣ አይጋሩ።

✅ የግብረ ሥጋ ግንኙነትን ሲያድርጉ እራስዎን ይጠብቁ ።

✅ በተደጋጋሚ እጅዎን ይታጠቡ።

✅ሌሎችን ያስተምሩ። 

✅ አጠራጣሪ ምልክቶችን/ ሽፍታዎችን በአፋጣኝ ለጤና ባለስልጣናት ያሳውቁ

  

🗣️ ያስተውሉ ወረርሽኝ ችላ በማለት አይጠፋም። እንደውም ይስፋፋል።

 

📣 የተጠቀሱትን ተግባራት ይፈጽሙ። እርስዎንም ማህበረሰብዎን ይጠብቁ። ይህንን መረጃ ለሌሎች ያጋሩ። 

 

ሞንኪ ፖክስን ለመከላከል፤ ተግባራዊ ለውጥ ማድረጊያው ሰአት አሁን ነው። 



Comments


bottom of page