ትኩስ ምግብ በመብላት ስለሚመጣው ካንሰር ያውቃሉ?
- Zebeaman Tibebu
- Jun 29
- 3 min read
የሚወዱት ምግብ ምንድነው?

በጠዋት በቅቤ የታሸ እጅግ ጣፋጭ ትኩስ ገንፎ እየበሉ ፤ በቅመሞች በጣፈጠ ሻይ ማወራረድ? ከቤተስብዎ ጋር እየተጋሩ ቢበሉትስ ?
ይህ ቁርስ ብቻ አይደለም ፤ የአብሮነታችን መገለጫ የባህላችን አካል ነው። ጾም ስንፈሰክ ከምንመርጣቸው ምግቦች መሀል ይካተታል። ክተሰበርን ወይም በሽታ ከጣለን ደግሞ ትኩስ መረቅ እንፋሎቱ ሳይወጣ መጠጣት እንመርጣለን።
ታድያ ይህ የአመጋገብ ባህላችን መሰረቱ ፍቅርና አብሮነት ቢሆንም ይዞት የሚመጣው ነቀርሳ እንዳለስ ያውቃሉ?
እውነታው ይሄ ነው።

ይህ ነቀርሳ የጉሮሮ ካንሰር (esophageal cancer) ሲባል ፤ እጅጉን ገዳይ ከሚባሉ የካንሰር አይነቶች ውስጥ ነው። በሽታው ብዙ ጊዜ አርፍዶ የሚታወቅ ሲሆን ፤ ትኩስ ምግብ የሚመገቡ የኢትዮጵያ ክፍሎች ላይ በዝምታ እየተንሰራፋ ይገኛል።
በፈረንጆች በ 2020 በወጣው አለም አቀፍ ጥናት (GLOBOCAN 2020) መሰረት
ኢትዮጵያ ውስጥ በ 2020 ብቻ 1,674 አዳዲስ የጉሮሮ ካንሰር ታማሚዎች የተገኙ ሲሆን ፤ 87 ፐርሰንቱ (1455 ሰዎች) በዚሁ አመት ሞተዋል።
ለዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ዋነኛ ገዳይ ከሚባሉ 10 ካንሰሮች ውስጥ የጉሮሮ ካንሰር ይጠቀሳል።
አሳዛኙ እውነታ ፡ አብዛኞቹ የጉሮሮ ካንሰር ተጠቂዎች አጭሰው የማያውቁ ፣ የማይጠጡ እና በቤተሰባቸው የጉሮሮ ካንሰር ታሪክ የሌላቸው ናቸው።
የኢትዮጵያ አመጋገብ ለምን አስጊ ሁኔታ ሊሆን ይችላል?

በባህላችን ትኩስ ነገር እንወዳለን። እንፋሎት ሳይወጣ ሳይቀዘቅዝ ተጋፍተን መብላት ይመከራል። ቡናም ፣ ሻይም ፣ መረቅም፣ ገንፎም፣ ወ.ዘ.ተ... ሳይቀዘቅዝ ነው መበላት ያለበት ብለን እናስባለን። አፋችንን እያቃጠለን "ሥ ....ሥ ...ሥ " እያልን ፤ በትንፋሽ እያበረድን መጠጣት ልምድ ነው። ካበረድነው መልካም አይደለም። አንዳንዴ ጋባዣችን ከማክበር ፤ ምግቡን ከመውደድ ጋር እናያይዘዋለን።
በአንድ በኩልም ለጤና መልካም አድርገን እናስባለን። አንድ ሰው ከተሰበረ የአጃ ሾርባ ወይም የበግ መረቅ በትኩሱ እንዲጠጣ እንመክራለን። ጉንፋን ከያዘን ትኩስ ወተት፣ ትኩስ ሻይ በቶሎ መጠጣቱ ፍቱን ያደርገዋል። ብርድ ብርድ ካለማ... ምክራችን እንዳለ ትኩስ ነገር ነው።
ይህ አስተሳሰባችን በአንድ በኩል ትክክል ነው። የበሽታ አምጪ ተህዋሳትን ሙቀቱ ስለሚገል ፣ ከምግብ ጋር የተያያዘ ኢንፌክሽን የመያዝ እድላችን ይቀንሳል። ታድያ ግን በእጃችን ለመያዝ የከበደ ፣ ለአፋችን ያቃጠለ ምግብ ለጉሮሮአችንስ ምን ያደርግ ይሆን?
ለዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ የጉሮሮ ካንሰር በከፍተኛ ደረጃ እየተመዘገበ ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ በ ጉሮሮ ካንሰር ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች ምን ይላሉ?
✅ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ክፍል ውስጥ በተደረገ የ 5 አመት ዳሰሳ ጥናት ፤ በጉሮሮ ካንሰር ታማሚዎች ላይ የሚታየው የካንሰር አይነት ፤ ለረዥም ጊዜ ካለ የትኩስ ነገር ጉዳት ጋር ተያይዥነት እንዳለው አመላክቷል።
✅ በጳውሎስ ሆስፒታል የተደረገ ጥናትም ተመሳሳይ ውጤት ከማሳየቱ ባሻገር ፤ 85 ፐርሰንት የሚሆኑት ታማሚዎች በሽታው ከገፋ(ከደረጀ) በኋላ ለህክምና እንደሚሄዱ አሳይቷል።
✅ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተደረገ ጥናት ደግሞ ፤ ህመሙ ካለባቸው ሰዎች መሀከል 99 ፐርሰንቱ በየቀኑ ትኩስ ነገር አዘውተረው እንደሚጠቀሙ አግኝቷል።
✅ የካንሰሩን መንስኤዎችን ለመለየት በአዲስ አበባ ከተማ የተደረገ ጥናት በበኩሉ ፤ ቀን በቀን በጣም ትኩስ ነገሮችን መጠቀም ፣ አትክልት እና ፍራፍሬን አዘውትሮ አለመመገብ ለህመሙ እንደሚያጋልጥ ገልጻል።
ግን ትኩስ ነገር እውነት ካንሰር ያመጣልን ወይስ መላምት ነው?

ከ65 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ሙቀት ያላቸው ምግቦች ካንሰር አምጪ (Category 2A) ተብለው ፤ በአለም ጤና ድርጅት አካል የሆነው በአለም አቀፍ የካንሰር ምርምር ኤጀንሲ( IARC) ተፈርጀዋል።
እንዴት ካንሰር ያመጣሉ?
የጉሮሮ ስጋችን ለከፍተኛ ሙቀት ሲጋለጥ ፤ የጉሮሮ ስጋችንን በሙቀቱ ይቃጠላል። ይህ ደግሞ ምግቡ የነካው የጉሮሮ ስጋ እንዲቆጣ ወይም እንዲቆስል ያደርጋል።
ይህ መቁሰል እና መቆጣት አንዴ ወይም የተወሰኑ ጊዜያት ብቻ ከሆነ ፤ እራሱን ሙሉ በሙሉ ስለሚጠግን ችግር የለውም። ታድያ ግን ሲደጋገም ፤ የጉሮሮአችን ህዋሳት ወደ ካንሰር ህዋሳት መለወጥ ይጀምራሉ። የዚህን ጊዜ የጉሮሮ ካንሰር ይሆናል።
በላንሴት ኦንኮሎጂ የሪሰርች መጽሄት ላይ እ.ኤ.አ በ2019 ላይ የታተመ ትንታኔም ፤ አዘውትረው ትኩስ መጠጦችን የሚጠጡ ሰዎች ፤ የጉሮሮ ካንሰር የመያዝ እድላቸው በ 90% እንደሚጨምር ይዘግባል።
ምልክቶቹ
ካልተጠነቀቅን ፤ ካልተከላከልን ፤ ካንሰሩ ደርጅቶ ጉሮሮን እስኪያጠብ ድረስ ምልክት አያሳይም።
⚠️ መጀመሪያ ላይ የሚታዩ ምልክቶች፡-
ደረቅ ምግብ የመዋጥ ችግር። ሲውጡ መቸገር። ታማሚዎች በምግብ መታነቅ ብለው ሊገልጹት ይችላሉ።
የደረት ህመም ወይም ደረት ላይ ደስ የማይል ስሜት መሰማት ወይም ደረት መጫን።
የጨጓራ የሜመስል አይነት የማቃጠል ስሜት
ድካም
ትንሽ በልቶ መጥገብ
ክብደት መቀነስ
⚠️ በሽታው እየገፋ ሲመጣ የሚታዩ ምልክቶች፡-
ፈሳሽ በሚውጡበት ጊዜ ህመም መሰማት ወይም መጠጥ መዋጥ አለምቻል።
ድምጽ መለወጥ
ረዥም ጊዜ የሚቆይ ሳል
ትውከት (ደም የቀላቀለ)
ክብደት ይብሱኑ መቀነስ።
ይብሱኑ አብዛኞቹ ታማሜዎች ወደ ህክምና የሚመጡት ህመሞቹን እንደተመለከቱ ሳይሆን ፤ ከ 4 እስከ 7 ወር ቆይተው ፤ ወይም ምልክቶቹ አስቸጋሪ ሲሆኑባቸው ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ 80% የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን አርፍደው ነው ካንሰሩ የሚገኝባቸው። ይህ ደግሞ የህክምና ውጤታማነትን ይቀንሳል።
ገንፎ ተዉ እያልን አይደለም። ቡናም ፣ሻይም እንዲሁ።

ይህ በባህላችን ላይ የሚደረግ ጦርነት አይደለም። ይህ ግንዛቤ ማስጨበጫ ነው። ገንፎም፣ ቡና፣ ሻይ፣ ወ.ዘ.ተ... ተዉ እያልን አይደለም ።
ችግሩ ከምግቡ ሳይሆን ከሙቀቱ ነውና አስፈላጊውን ጥንቃቄ ያድርጉ። ካንሰር ታመው ከመምጣትዎ በፊት ማቆም የሚችሉት እርስዎ መሆንዎን አይርሱ!
✅ መከላከያ መንገዶቹ
ትኩስ ምግብ ከመብላትዎ ወይም ትኩስ መጠጦችን ከመጠጣትዎ በፊት ከ5-10 ደቂቃዎች ይጠብቁ። ትንሽ ይቀዝቅዝ።
የሚመገቡት ምግብ ቶሎ እንዲቀዘቅዝ የሴራሚክ እና የ እንጨት መመገቢያዎችን መጠቀም ይችላሉ።
ከትኩስ ይልቅ የበረደ ምግብ ጥሩ መሆኑን ለልጆችዎ ይምከሩ።
ብሄራዊ ምላሹ፡ ገና ብዙ ይቀረናል።
ሀገራችን በአሁኑ ወቅት የጉሮሮ ካንሰርን በተመለከተ አገር አቀፍ የ ስክሪኒንግ ወይም የቅድመ ምርመራ ፕሮግራም የላትም። የብሔራዊ የካንሰር መቆጣጠሪያ እቅድ (2020-2029) የጉሮሮ ካንሰርን እያደገ እንዳለ ስጋት ቢወስደውም ፤ ገና ብዙ ይቀራል።
ለቅድመ ምርመራ ወይም ምልክቶቹ ለይተው ቀድመው ካልመጡ ፤ የህክምና አማራጮቹ የተገደቡ ናቸው። ውጤታማነታቸውም እንዲሁ። የእነኝህም ህክምናዎች ተደራሽነት ውስን ነው።
ማሳረጊያ ነጥብ
ባህላችንን ሳንተው ጤናችንን እንጠብቅ። ጉሮሮአችንን እንንከባከብ።
ትኩስ ነገር ከመመገብዎ በፊት ትንሽ ይጠብቁ። ይብረድ። እስከዛ ከቤተሰብዎ ጋር ይጫወቱ።
ይህንን መረጃ ለሌሎች ያጋሩ። እነሱም ግንዛቤ ይኑራቸው። ጤናቸውን ይጠብቁ።
Comments