❗ሾተላይ
- Zebeaman Tibebu
- Jul 31
- 3 min read
ልጅን ለመጠበቅ የተፈጠረው የ እናት ማህጸን ለጽንስ መሞቻ ሊሆን ይችላልን?
አዎ, ለአብዛኞቻችን ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው።
የእናትን ጤና ለመጠበቅ የተዘጋጀው የበሽታ መከላከያ ስርአት ፤ ለልጅ ሞት መንስኤ ሲሆን ማሰብ ከባድ ነው።
ይህ ተረት አይደለም ? ሳይንሳዊ መላምትም?

እርስዎም ስለዚህ ሰምተው ያውቃሉ። በተለምዶ ስሙ ሾተላይ ይባላል። በህክምና ስሙ የአር ኤች አለመስማማት/አለመጣጣምን ተከትሎ የሚመጣው የሄሞላይቲክ ዲዚዝ ኦፍ ዘ ኒው ቦርን።
ይህ በሽታ የ እናት የበሽታ መከላከያ ስርአት በማህጸን ውስጥ ያለውን ጽንስ ሲያጠቃ የሚፈጠር ነው። ጽንሱ ላይ ከባድ ጉዳት ከማድረስ ባሻገር ሞት ሊያደርስ ይችላል። '
የእናት በሽታ የመከላከል ስርአት በማህጸን ውስጥ ያለውን ጽንስ ፤ ድምጽ ሳያሰማ ሲያጠፋ የሚፈጠር ነው።
ይህ የጤና እክል በዓይን ባይታይም ፤ ውጤቱ ግን እጅግ አሳዛኝ ነው።
እናቶች ልጆቻቸውን ይሰረቃሉ። ስማቸውም ይጠለሻል።
አንድ ታሪክ እናውራ። ታሪኩ የሆነው ከ አመታት በፊት ነው።
በገጠሪቷ የኢትዮጵያ ክፍል የምትኖር አንዲች ሴት ፤ ገና የመጀመሪያ ልጇን እንዳረገዘች ድንገት ያስወርዳታል። በዚህ የተከፋች እናት ደግማ ለማርገዝ አልዘገየችም። ሆኖም ግን ሁለተኛ ልጇ ሳይወለድ ይሞታል። ይህች ጉጉ እናት ልቧ ቢሰበርም ፤ ደግማ ደጋግማ ብትሞክርም ፤ የልጆቿ እጣ ተመሳሳይ ይሆናል።
ይህች ምስኪን እናት የመጨረሻ እርግዝናዋ ክትትል አዲስ አበባ ነበርና ፤ ለቀጣይ እርግዝና ቀድማ እንድትመጣ ትመከራለች።
ታድያ በተመከረችው መንገድ ይህች እናት በክረምት ቀድማ የከሰል መኪና ላይ ተጭና ትመጣለች። ሆስፒታልም ተኝታ ክትትል ታደርጋለች። ክትትል እያደረገችም አንድ ቀን ድንገት የልጁ እንቅስቃሴ አልሰማ ሲላት ዶክተሮቹን ትጠራለች። ሀኪሞቹም በአልትራሳውንድ ሲያዩትም ጽንሱ ሞቷል። የሰባተኛ ጽንስዋ እጣ ተመሳሳይ ሆነ።
ይህንን ሁሉ ስቃይዋን እና ህመሟን የሚያውቁ ባለሙያዎች ምን ያድርጉ? ለዚህች ተስፈኛ እናት ማን ይንገራት? ምን ይበሏት?
ይህ የሾተላይ እናቶች እውነታ ነው።
🧬 ታድያ ሾተላይ ምንድን ነው?
በተለምዶ ሾተላይ ያለባት እናት የተረገመች ፤ ልጆቿን የሚበላ/የሚጨርስ መንፈስ የተጠጋት ፤ ተደርጎ ነው የሚወሰደው። ለዚህም እነዚህ እናቶች ይገለላሉ። ባሎቻቸው ይፈቷቸዋል። ለትዳርም አይፈለጉም። ስማቸው የጠቆረ ነው።
እውነት ሾተላይ የእናት ችግር ነውን ?

ይህንን ለመመለስ መጀመሪያ ስለ ሾተላይ እንረዳ። ሰው ልጅ ካለው የደም አይነት መለያ ፕሮቲኖች መሀከል አር ኤች( Rh (Rhesus)) ፋክተር የሚባል የደም መለያ ፕሮቲን አለ። ይህ ፕሮቲን ያላቸው Rh-positive ሲባሉ ፤ የሌላቸው Rh-ነጌቲቭ ይባላሉ።
ደሞ አይነትዎን ሲገልጹ ፖዘቲቭ እና ኔጌቲቭ የሚሉት ይህንን ነው። ለምሳሌ ኦ ፖዘቲቭ እና ኦ ኔጌቲቭ።
ታድያ ሾተላይ የሚኖራቸው የአር ኤች ፋክተር የሌላቸው (አር ኤች ኔጌቲቭ) እናቶች ናቸው።
እንዴት ይፈጠራል?
አር ኤች ኔጌቲቭ የሆነች ሴት ባለቤቷ ኔጌቲቭ ከሆነ ፤ ሁለቱም ፕሮቲኑ ደማቸው ውስጥ ስለሌለ ችግር የለውም።
ችግሩ የሚከሰተው አር ኤች ኔጌቲቭ የሆነች ሴት አር ኤች ፖዘቲቭ ከሆነ ሰው ስታረግዝ ነው። ይህም ሆዷ ውስጥ ያለው ጽንስ አር ኤች ፖዘቲቭ ሊሆን ይችላል።
የእናትየው የበሽታ የመከላከል ስርአት አር ኤች ፕሮቲን በውስጡ ስለሌለው ፤ ይህን የደም ፕሮቲን አያውቀውም። ለዚህም ለእናቷ ሰውነት እንግዳ ይሆንበታል። ለዚህም የጽንሱ ደም ውስጥ ያለውን ይህንን ፕሮቲን ሲያገኝ ፤ የእናት ሰውነት በበሽታ አምጪ ተህዋስ እንደተወረረ ያህል ይቆጣል።
ለዚህም ወራሪውን ፕሮቲን ለማጥፋት ፤ ጽኑስን ያጠቃል። ይጎዳል። ይገድላል።

ይህ እንዲፈጠር የጽንስ ደም የእናት የበሽታ መከላከያ ስርአት ጋር መገናኘት አለበት። በተፈጥሮ ጽንስ ለእናት ሰውነት እንግዳ በመሆኑ ፤ ሰውነታችን ከእናት ህዋስት ለይቶ ነው የሚያስቀምጠው። የጽንስ እና የእናት ሰውነት ህዋሳት አይገናኙም ። ሆኖም ግን እናት በምትወልድበት ጊዜ/ ወይም ሲያስወርዳት የጽንስ ደም ህዋሳት ከእናት ደም ጋር ይደባለቃሉ።
የዚህን ጊዜ የእናት ሰውነት የተወረረ ስለሚመስለው ፤ ወራሪ ሀይልን የሚያጠፋ መርዝ(antibody) ያዘጋጃል። ይህም መርዝ ይህንን ፕሮቲን ፈልጎ የሚደመሥሥ ነው። ታድያ ደሙ የተደባለቀው በወሊድ ጊዜ ስለሆነ ፤ የመጀመሪያው እርግዝና ያለችግር ይወለዳል።
ሆኖም ግን በቀጣይ እርግዝናዎች ላይ ችግር ያጋጥማል። የጽንሱ የደም ህዋሳት በእናት በሽታ መከላከያ ይጠቃሉ። ለዚህም ጽንሱ የደም በሽታ ያጋጥመዋል። ሆዱ እና ደረቱ ያብጣል። በሽታው ሲብስም ጽንስ ማህጸን ውስጥ ይሞታል።

ለዚህም ሾተላይ ያለባቸው እናቶች የመጀመሪያ እርግዝናቸው ላይ ችግር የለም። ቀጣይ እርግዝና ግን ፤ ያለ ህክምና እርዳታ የከፋ ይሆናል።
ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት ከእነዚህ ሕፃናት መካከል ግማሽ የሚሆኑት በሕይወት አይተርፉም።
📊 የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ
በደቡብ ኢትዮጵያ አርባምንጭ ዙሪያ ውራጃ የተደረገ የማህበረሰብ ጥናት እንደሚያመላክተው ፤ ከእርጉዝ ሴቶች ውስጥ 6.2% የሚሆኑት አር ኤች ኔጌቲቭ የደም አይነት አላቸው።
በቡሌ ሆራ ዩንቨርስቲ ሆስፒታል የተደረገ ጥናት በበኩሉ ከታዳጊ ሴቶች መሀክል 6.4% የሚሆኑት የደም አይነታቸው አር ኤች ኔጌቲቭ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ 10 ነፍሰ ጡሮች አንዷ የ አርኤች ነጌቲቭ የደም አይነት አላት።
በወላይታ ሶዶ የተደረገ ጥናት ደግሞ 9.8 % ነፍሰጡር እናቶች የቀይ የደምሴል የሚያጠቃው አንቲቦዲ ደማቸው ውስጥ ተገኝቷል።
ቡሎ ሆራ የተወለዱት ልጆች መሀከልም 14.3 ፕርሰንት የሚሆኑት ሲወለዱ ቢጫ ቆዳ እና አይን አሳይተዋል። (ይህ የዚህ በሽታ መጠነኛ ምልክት ሊሆን ይችላል።)
💡 መከላከል ይቻላል።
አዎ ሾተላይን መከላከል ይቻላል። አንድ መርፌ አንድ ሕይወት ያድናል። የእናትን የነገ የመውለድ ተስፋን ያለመልማል።

ይህ መከላከያ መርፌ ፤ የእናት ሰውነት መርዛማ አንቲባዮቲክስ እንዳያመርት ያደርገዋል። ስሙም አንታይ ዲ ኢሚኖግሎቡሊን ነው። የእናቲቱ በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት የህጻኑን ቀይ ህዋሳት እንዳያጠቁ ይከላከላል።
የደም አይነቷ ኔጌቲቭ የሆነ ሁሉም እናት ስለዚህ መርፌ ማወቅ አለባቸው።
መርፌው መቼ መቼ ይሰጣል ?
✅ በእርግዝና ጊዜ 28 ሳምንት ላይ
✅ ከወሊድ በኋላ በ 48 ሰአት ውስጥ እንደገና ይሰጣል። (ይህ ግን ህጻኑ የደም አይነቱ ፖዘቲቭ ከሆነ ነው)።
እናት የልጇ የደም ምርመራ ተደርጎ ይህ ማርከሻ መድሐኒት ካልተሰጣት ፤ ሰውነቷ ጽንሱን መቃወሚያ ስለሚያመርት፤ ቀጣይ እርግዝናዎች ይሰናከላሉ።
💉ታድያ መፍትሔው እያለ ለምን አሁንም በገጠር እና በከተማ ሾተላይ ያጋጥማል?
የእርጉዝ እናቶች እና የባለቤቶቻቸው የግንዛቤ ጉድለትሳላለ ፤
አንዳንድ የጤና ሰራተኞች ጋር ያለ የግንዛቤ ክፍተት በመኖሩ፤
የዚህ መቃወሚያ መድሐኒት አለመገኘቱም ከተገኘም ዋጋው ለዝቅተኛ የማህበረሰብ ክፍል በመወደዱ ፤ አሁንም ሾተላይ እያጋጠመ ይገኛል።
⚠️ አንድ ነገር ቀረ
ስለ ሾተላይ እና መከላከያ መንገዱ አሁን ግንዛቤ ጨብጠዋል።
ታድያ ይህንን ለሌላ ማሳወቅ አለብዎ።
ማንኛውም እናት የሾተላይ እጣ ሊያጋጥማት አይገባም።
コメント