🌞 የቫይታሚን ዲ እጥረት 13 ወር ፀሀይ ባላት አገር
- Zebeaman Tibebu
- 8 hours ago
- 3 min read
ኢትዮጵያ ራሷን “የአስራ ሶስት ወር የፀሀይ ብርሃን” አገር መሆኗን በኩራት ፈርጃለች። ሆኖም ግን የቫይታሚን ዲ እጥረት ስርጭት በኢትዮጵያ ከፍተኛ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ። ዶክተሮችም ይመሰክራሉ።
ታድያ እንዲህ ፀሀያማ ሀገር እየኖርን ፤ የቫይታሚን ዲ እጥረት እንዴት ሊከሰት ቻለ?
በጂኦግራፊ እንኳን ካየነው ፤ ኢትዮጵያ የምድር ወገብ አከባቢ ስለምትገኝ ፤ በአለማችን ከፍተኛ የፀሀይ ብርሀን ከሚያገኙ ሀገራት ተርታ ትገኛለች። አዲስ አበባ በበኩሏ ፤ መልክአምድራዊ አቀማመጧ ለዚህ የተመቸ ነው። ከባህር ወለል 2300 ሜትር በላይ የምትገኝ ፤ ወይን አደጋ ከተማ ናት። ከምድር ወገብም በስተሰሜን 9 ዲግሪ ርቀት ስለምትገኝ ፤ የለጓሷ ፀሀይ ጨረር ሳይታጠፍ በቀጥታ ያገኛታል። በተፈጥሮ አቀማመጧ የቫይታሚን ዲ እጥረትን መከላከል አለባት።

ነገር ግን የቫይታሚን ዲ እጥረት በከተማዎቻችን በሰፊ እየታየ ይገኛል። ከፍተኛው የቫይታሚን ዲ እጥረት መጠንም በአዲስ አበባ ተመዝግቧል።
በገጠር የሚኖሩ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ችግር ያለባቸው ህጻናት ላይ ዝቅተኛ የ ቫይታሚን ዲ እጥረት ቢያጋጥም ላይደንቀን ይችል ይሆናል። ነገር ግን ይህ በከፍተኛ ደረጃ እየታየባቸው ያሉት የከተማ ህጻናት ናቸው።
ይህ የህጻናት ብቻ ችግር አይደለም።ሁሉንም እድሜ የሚያጠቃ ችግር ነው። ህጻናት፣ ነፍሰጡር ሴቶች እና የመውለድ እድሜያቸው ያለፉ ሴቶች በይበልጥ ተጋላጭነት አለባቸው።
ታድይ እንዴት?
ፀሀይዋ እንደው እዛው አለች። የአኗኗር ዘይቤአችን ግን ተለውጧል።
የአኗኗር ዘይቤያችን እንዴት ተለወጠ?

ከተሞቻችን ወደ ጎን ብቻ ሳይሆን ወደ ላይም እያደጉ ነው። በኮንዶሚኒየም፣ በአፓርታማ ወይም በፎቅ ያሉ ልጆች ፤ የሚጫወቱት እቤት ውስጥ ከፀሀይ ብርሀን እርቀው ነው።
የቢሮ ሰራተኞችም ከፀሀይ እኩል ተነስተው ከቤት የወጡ ፤ ፀሀይ ስትገባ ነው ወደ ቤት የሚገቡት። የቀን ውሎአቸውም በግርግዳ መሀል በቢሮ ውስጥ ነው። አብዛኛው የቀን እንቅስቃሴያቸው ከፀሀይ የራቀ ስለሆነ ፤ በቂ የፀሀይ ብርሀን አያገኙም።
ሴቶች ሲንቀሳቀሱ ዣንጥላ ይይዛሉ። አልያም ሰን ስክሪን(ፀሀይ መከላከያ) ይቀባሉ።
እናቶች ልጆቻቸውን ፀሀይ ሲያሞቁ ፤ ቫዝሊን ቀብተው ስለሆነ ፤ ቫዝሊኑ ጠቃሚውን የፀሀይ ጨረር ይመልሰዋል።
በኮንዶሚኒየም እና አፓርታማ የሚኖሩ እናቶች ደግሞ ከቤታቸው ሆነው በመስታወት ውስጥ የምትገባውን ፀሀይ ስለሚያሞቁ ፤ ጠቃሚ የሆነው የፀሀይ ጨረር በመስታወቱ ተንጸባርቆ ይመለሳል።
ታድያ ይህ ከፀሀይ የራቀ አኗኗራችን ለቫይታሚን ዲ እጥረት ቢያጋልጥ እንዴት ይደንቅ?
ምን ያህል የፀሀይ ብርሀን ያስፈልገኛል?
በስራ መሀል የምናገኛት ቅንጭብ የፀሀይ ብርሀን የሰውነታችንን የቫይታሚን ዲ መጠን ለመጠበቅ በቂ ላትሆን ትችላለች።
ለዚህም የቫይታሚን ዲ ከ 30 እስከ 50 ደቂቃ ፀሀይ ላይ መቆየት ይኖርብናል። ከጠዋት ፀሀይ ይልቅ ከ 4 ሰአት በኋላ ያለው የፀሀይ ጨረር ይመረጣል። ከዚህም ደግሞ የቀትር ፀሀይ ይበልጥ ኃይል አለው።
🧬 ቫይታሚን ዲ ሲቀንስ ምን ይሆናል?

የቫይታሚን ዲ ቁርኝት ከ አጥንት ጋር ብቻ አይደለም። ሰውነታችን ውስጥ ካሉ የተለያዩ ስርአቶች እና አካላት ጋር ይገናኛል። ከበሽታ መከላከያ ስርአት ፣ ከጡንቻ ጥንካሬ ጋር ፣ ከስሜታችን ጋር ፣ ከኢንሱሊን ስራ ጋር ፣ እንዲሁም ከነርቭ ጋር ይገናኛል።
ሲቀንስ ምልክቶቹ ለዘብተኛ ሊመሰሉ ይችላሉ። ጉዳታቸው ግን ከፍተኛ ነው።
በልጆች ላይ፡ መቀንጨር ፣ የአጥንት መዛባት፣ የዘገየ እድገት እና የእግር አጥንት መጣመም/መቆልመም (ሪኬትስ) ሊያመጣ ይችላል።
በአዋቂዎች ውስጥ: ድካም ፣ ሥር የሰደደ ሕመም ፣ የጡንቻ ድክመት፣ ድብርትና ለተደጋጋሚ ኢንፌክሽን ሊያጋልጥ ይችላል።
በነፍሰ ጡር ሴቶች ላይ፡ ደካማ የፅንስ አጥንት እድገት፣ በእርግዝና ጊዜ ለሚያጋጥም የስኳር በሽታ፣ የደም ግፊት (ፕሪክላምሺያ) ሊያጋልጥ ይችላል። እንዲሁም የጽንስ ክብደት መቀነስ ሊያመጣ ይችላል።
📊 ስርጭቱ ምን ይመስላል
📍ከ አንድ አመት በፊት የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው የቫይታሚን ዲ እጥረት ስርጭት በኢትዮጵያ 56 ፐርሰንት (40-72%) ይደርሳል። ከዚህም ውስጥ በአዲስ አበባ ስርጭቱ በጣም ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል ( 74 ፐርሰንት)። ቀጣይ ከፍተኛ ስርጭት የተመዘገበው በአማራ ክልል 42 ፐርሰንት እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል 41 ፐርሰንት ነው።
📍በደቡብ ኢትዮጵያ በእርጉዝ እናቶች መሀከል የተደረገ ጥናት እንዳመላከተው ደግሞ ከ 3 እርጉዝ እናቶች መሀክል አንዷ የቫይታሚን ዲ እጥረት አለባት። የቫይታሚን ዲ እጥረት ከተገኘባቸው እናቶች መሀክል አብዛኞቹ (88.8%) የደማቸው የቫይታሚን ዲ መጠን እጅጉን የተመናመነ ነበር።
📍 እድሜያቸው ለትምህርት በደረሱ ህጻናት ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው 42% የሚሆኑት የቫይታሚን ዲ እጥረት እንዳለባቸው አረጋግጧል። በከተማ ከሚኖሩ 10 ህጻናት ከ6 በላይ የሚሆኑት ይህ እጥረት ሲታይባቸው ፤ በገጠር ከሚኖሩ 10 ህጻናት ውስጥ ግን አራቱ ብቻ የቫይታሚን ዲ እጥረት ይታባቸዋል።
እነኝህ ጥናቶች የሚያሳይቱ ቅንጫቢ እውነታ የቫይታሚን ዲ እጥረትን ነባራዊ ሁኔታ በተወሰነ መልኩ ያሳያል። ታድያ በፀሀያማ ሀገር እየኖርን ፤ የፀሀይ እጦት ጋር የተያያዘ ህመም መንሰራፋቱ ፤ እጅጉን አስገራሚ ነው። ለነገሩ " የአባይን ልጅ ውሀ ጠማው" አይደል ተረቱ።
🛠 ታድያ ምን ሊደረግ ይችላል?

በበቂ ደረጃ በየቀኑ ፀሀይ ይሙቁ። ቢያንስ ለ 30 ደቂቃ ክንዶችዎን እና እግሮችዎን ሳይሸፍኑ ፤ የፀሀይ ብርሀን ቢያገኝዎ ይመረጣል። ከጠዋቱም ፀሀይ የእኩለ ቀን ላይ ተመራጭ ነው።
በቫይታሚን ዲ የበለጸጉ ምግቦችን ይመገ።። እንቁላል፣ ወተት፣ ዓሳ ቫይታሚን ዲ በውስጣቸው አለ። ከዚህም ባሻገር የበለፀጉ ዘይቶች ወይም ዱቄትም የቫይታሚን ዲ በውስጣቸው ይገኛል።
የተጋላጭነት ደረጃቸው ከፍተኛ የሆኑ ሰዎች መደበኛ ምርመራ ማድረግ ይኖርባቸዋል። እነኝህም እርጉዝ ሴቶች፣ ህጻናት፣ የመውለጃ እድሜያቸው ያለፈ ሴቶች ፣ ሥር የሰደደ ሕመም ያለባቸው ሰዎች፣ የቢሮ ሰራተኞች ናቸው። ጤናማ የደም ደረጃ ከ 30 እስከ 50 ነው።
በቂ የፀሀይ ብርሀን የማያገኙ ከሆነ ፣ ታሚን ዲ እና ካልሲየም እንክብሎችን መውሰድ ይችላሉ። ሁሌ ቅድሚያ ተመራጩ የተፈጥሮ መፍትሔ መሆኑን ይወቁ።
የደምዎትን የቫይታሚን ዲ መጠን ለማገዝ በቀን ከ600-800 IU መውሰድዎት በቂ ነው።
ይህንን ግንዛቤ ለሌሎች ማዳረስ አለብን። ትምህርትቤቶች ፣ ክሊኒኮች፣ ሚዲያዎች የቫይታሚን ዲ መጠንን የሚጠብቁ ባህርያዊ ለውጦችን ማስተዋወቅ አለባቸው።
✨ዋና ነጥብ
በጸሀያማ ሀገር ውስጥ እየኖርን የቫይታሚን ዲ እጥረት ለመፍታት ፤ ከውጭ የሚገባ መፍትሔ አያስፈልገንም። የተሟላ ግንዛቤ ይኑርዎ። አበላልዎን አኗኗርዎን ያስተካክሉ።
የቫይታሚን ዲ እጥረ ለዘብተኝነቱ አያታልዎ። ከተባባሰ ህመሙ ሰላም ይነሳል፣ የአእምሮ ጤናን ይረብሻል፣ ከስር ያለ በሽታን ያባብሳል። ካልደረስንበት ደግሞ የከፋ ጉዳት ያመጣል።
በግንዛቤ ላይ በተመሰረተ ተግባራዊ እርምጃ ጤናችንን እንጠብቅ።
Comments