ከልጣጩ እስከ ፍሬው የሕክምና ጥቅም ያለው ፓፓያ
- Zebeaman Tibebu
- Jul 21
- 3 min read

በባህላዊ ህክምና ፓፓያ ለተለያዩ ጥቅሞች ሲውል ቆይቷል። የፓፓይ ፍሬ ለጉበት ህክምና ፤ እንዲሁም እንደ ጸረተባይነት ጥቅም ላይ ውሏል። ቅጠሉ ወባን ጨምሮ ለትኩሳት ህመሞች ያገለግል ነበር። ለወር አበባ ህመምም የሚጠቀሙበት ነበሩ። ልጣጩ ደግሞ የሰውነትን መቆጣትን ለማከም ይውል ነበር።
ታድያ ይህ ባዶ መላምት አልነበረም።
🌍 ዘመናዊ ሳይንስ ገና ጥቅሞቹን ማረጋገጥ የጀመረ ቢሆንም ፤ የፓፓያ ቅጠል የመድሐኒትነት አቅም ግን የሚካድ ሆኖ አልተገኘም።
ሳይንስ እንዳገኘው የፓፓያ የጤና ጥቅሙ ከምግብ መፈጨት እስከ ውበት ፤ እንዲሁም በሽታ መከላከል ድረስ ይደርሳል።
እነኝህን የጤና ጠቀሜታዎች አንድ በአንድ ዘርዝረን እንመልከት ።
🧡 የፓፓያ የሚበላው ክፍል/ ፍሬ/ ስጋ
ይህ እምቅ የኃይል ምንጭ ነው። የበሰለ ፓፓያ ጭማቂ በሚከተሉት የበለፀገ ነው፡
ቫይታሚን ሲ (ከፍተኛ የሆነ የቪታሚን ሲ ክምችት አለው ። ይህም በህክምና ከሚመከረው (RDA) በ ሁለት እጥፍ የላቀ ነው።) ፣
ቫይታሚን ኤ፣
ቪታሚን ቢ 9 (ፎሌት)፣
ቫይታሚን ኢ፣
ማግኒዥየም እና
ኃይለኛ ጸረ ኦክሲዳንት የሆነው ሊኮፔን በውስጡ ይገኛሉ።
እነዚህ ንጥረ ነገሮች በሽታ የመከላከል አቅምን ያጎለብታሉ። ለአይን እና ለልብ ጤንነት አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። ውስጡ ያለው ሊኮፔን ሰውነት እንዳይቆጣ ያደርጋል። ሰውነት ውስጥ ያለ የኦክሲዳንት (መርዛማነት ያለው ኬሚካል) መጠንንም ይቀንሳል። ለዚህም ስር ለሰደዱ የ ልብ እና የነርቭ ህመሞች ላይ ተጸእኖ ይፈጥራል።

📚 በኒውሮኢንዶክሪኖሎጂ ሌተርስ (2013) ላይ የተደረገ ጥናት ፤ የተብላላ (fermented) ፓፓያ አልዛይመር ሀመም ባለባቸው ታካሚዎች ላይ ፤ ህመሙን የሚያባብሰውን የኦክሲዳንት መጠን ቀንሷል። ሆኖም ግን በዚህ ዙሪያ ጥናቶች በብዛት መደረግ ይኖርባቸዋል።
🧪 ፓፔን (ፓፓያ ውስጥ ያለ ዋነኛ ምግብ መፍጫ ኤንዛይም)
ባልበሰለ ፓፓያ እና በ ፓፓያ ልጣጭ ውስጥ ፓፔን የሚባል ኤንዛይም አለ። ይህ ኢንዛይም ፕሮቲንን የሚያልም በመሆኑ ፤ ፕሮቲን ያላቸው ምግቦችን ለመፍጨት ያግዛል። ለዚህም በባህላዊ መንገድ የምግብ መፈጨትን እንዲያግዝ ፣ የሆድ መወጠርን ለመቀነስ ፓፓያ መብላት ይመከራል።
🧬 በዚህ ኤንዛይም ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች ቢኖሩም ፤ ያለውን ጠቀሜታ ለማስረገጥ እና ከዘመናዊ ህክምና እንዲካተት በደንብ መጠናት ይኖርበታል። እስከአሁን የተደረጉ ጥናቶች የምግብ አለመፈጨት ላለባቸው ሰዎች ጠቀሜታ ሊኖረው እንደሚችል ጠቁመዋል።
⚠️ ታድያ ግን ይህ ፕሮቲንን የሚሰብር ኤንዛይም (እንደማንኛውም ኤንዛይም) ፤ የምግብ ቱቦን ሊያስቆጣ የሚችልባቸው ሁኔታዎች አሉ። ለዚህም የአንጀት /ጨጓራ መቆጣት ያለባቸው ሰዎች ፤ ፓፓያን ከበሉ በኋላ የምግብ መቆጣት ሊያጋጥማቸው ይችላል።
🌿 የፓፓያ ቅጠል

የፓፓያ ቅጠል መራራ ከመሆኑ ባሻገር ፤ ብዙ ጊዜ ቸል ይባላል። ሆኖም ግን በቅርብ የተደረጉ ጥናቶች የደንግ (Dengue Fever) ቫይረስ ህመምን የማከም አቅም እንዳለው ጠቁመዋል።
እዚህ ጋር ስለ ደንግ ቫይረስ ህመም ጥቂት እንበል። የደንግ ቫይረስ የደንግ ትኩሳት(ፌቨር)የሚባል ከባድ የትኩሳት ህመም ያመጣል። ይህ የደንግ ፌቨር ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ከ 12 አመት በፊት (እንደፈረንጆች በ2013) በድሬዳዋ ሲሆን ፤ በጊዜው 9441 ሰዎች እንደተጠቁ ሲደሲ ይጠቁማል። ከዚህም በኋላ በነበሩት አመታት በደቡብ እና ምስራቅ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የተለያዩ ክልሎችን አጥቅቷል።
📊 ሳይንሱ ምን ይላል?
ከህመሙ ዋነኛ ምልክቶች ውስጥ አንዱ የ ፕሌትሌት መመናመን ነው። ታድያ መራራው የፓፓያ ቅጠል ጭማቂ ፤ የዚህ ህመም ታማሚዎች ላይ የፕሌትሌት መጠን እንዲጨምር ያግዛል። ለዚህም የሆስፒታል ቆይታቸው እንዲቀንስ ማድረጉን የሚያሳዩ ጥናቶች አሉ።
🩸 ታድያ ግን ከፈዋሽ ህክምና ተርታ ለመግባት ገና ብዙ ጥናቶች መደረግ ይኖርባቸዋል።
እንደ ፈዋሽ ህክምና ባንጠቀመውም ፤ ህመሙ ላለባቸው ሰዎች ከሚመገቡት ምግብ ጋር በመደባለቅ ፤ እንደ ደጋፊ ህክምና መጠቀም እንችላለን።
🌱 የፓፓያ ዘር/ፍሬ
ብዙ ጊዜ የፓፓያ ፍሬ ከተበላ በኋላ ውስጡ ያለው ዘር ተጥሎ ማየት የተለመደ ነው። ያለውን የጤና ጠቀሜታ የሚያቅ ፤ ይህ ብክነት መሆኑን ይረዳል።

🧪 የተደረጉ ጥናቶችም ይህንኑ መስክረዋል።
የፓፓያ ዘር የጸረ ትላትል/ ተባይ ባህሪ ያላቸው ውህዶች አሉት። ለዚህም የአንጀት ትላትልን ሊያክም ወይም ሊያስወግድ የሚችል አቅም አለው።
የፓፓያ ዘር ውስጥ ጉበትን የሚጠግኑ / የሚደግፉ ውህዶችም አሉት። ለዚህም ጉበታቸው ለተቆጣባቸው ፤ መቆጣቱ እንዲቀንስ እና የጉበት ምርመራቸው ጤናማ ደረጃ እንዲመለስ ያግዛል። በተለይም የመድሐኒት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ፤ የጉበት ጉዳት ላይ ተጽእኖ አለው።
ፀረ-ባክቴሪያ እና ፀረ-ፈንገስ ባህሪም አለው። ውስጡ እንደ ቤንዚል አይሶታዮሳይኔት አይነት ውህዶች ስላሉት ፤ ባክቴሪያን እና ፈንገስን ሊቃወም ይችላል።
እዚ ጋር ማስተዋል ያለብን ነገር፡
🔬 አብዛኞቹ ጥናቶች በእንስሳት የተደረጉ ናቸው። ይህ ማለት ሙከራዎቹ በእንሰሳት ላይ አመርቂ ለውጥ አሳይተዋል ( በእንሰሳት ሳይሞከር ፤ በሰዎች ላይ መድሐኒትነት ያለውን ማንኛውንም ውህድ መሞከር ስለማይቻል)። መጠናቸው ትንሽ ቢሆንም በሰዎች ላይ ይህንን የሚደግፉ ጥናቶችም አሉ። ሆኖም ግን ወደ ዘመናዊ ህክምና ሙሉ በሙሉ ከመግባቱ በፊት ፤ በደንብ መጠናት ይኖርበታል።
⚠️ ጠቃሚ ማስጠንቀቂያ፡-
የፓፓይ ዘር ዱቄት/ጭማቂዎች ሲወሰድ ፤ ጊዜያዊ መካንነት እንደሚያመጣ በእንሰሳት ላይ የተደረጉ ሙከራዎች አሳይተዋል። በሰው ልጅ ያለው ተጽእኖ ገና ባይጠናም ፤ አብዝቶ መጠቀም ተመሳሳይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል። ለዚህም ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
✨ የፓፓያ ልጣጭስ?
የፓፓያ ልጣጭን በቆዳ ላይ ማሸት ፤ ለቆዳ ጠቀሜታ ይኖረው ይሆን?

የላብራቶሪ ጥናቶች ፓፓያ ቡግርን የመቀነስ ፤ እንዲሁም ቆዳን የማጥራት ጠቀሜታ ሊኖረው እንደሚችል ጠቁመዋል። የፓፓያ ልጣጭን በዚህ መንገድ የተጠቀሙ ግለሰቦችም ፤ ቆዳቸው እንደጠራ በማህበራዊ ድህረ ገጾች ላይ ሲገልጹ ይታያሉ።
ታድያ ይህንን የቆዳ ጠቀሜታ ያመጣሉ ተብለው የሚታሰቡት ውህዶች የሚከተሉት ናቸው፡
የፓፓያ ልጣጭ በውስጡ ፓፔን እና አልፋ ሃይድሮክሲ አሲድስ አለው። እነኝህ ውህዶች የሞተ ቆዳን ከላይ የመግፈፍ አቅም አላቸው። ለዚህም የቆዳን ጤና ያግዛሉ።
ልጣጩ ውስጥ ያሉ ፀረ ኦክሲዳንቶች (ፖሊፌኖል እና ፍላቭኖይድስ) የባክቴሪያን እድገት ይቃወማሉ። የቆዳን ጤና የሚረብሸውን መርዛማ የኦክሲዳንት መጠንም ይቀንሳሉ። ይህ ደግሞ የቆዳን ጤና ያሻሽላል። ውበትንም ያጎላል።
👩🔬 ታድይ እርስዎስ ለቆዳዎ ጤና እንዴት ያድርጉ፡-
የፓፓያ ልጣጭ ውስጡን በፊትዎ ላይ ተቀብተው ፤ ከ 5-10 ደቂቃ ያቆዩት። ከዛም በውሀ ይታጠቡ/ያስለቅቁት።
ታድያ ግን የፓፓያ አለርጅ እና በቀላሉ የሚቆጣ ቆዳ ካለዎት መጠንቀቁ መልካም ነው።
💇♀️ የፀጉር እና የራስ ቅል ጤና ዙሪያ አንዳንድ የሻሞፖ እና ቅባት አምራቾች ምን ያላሉ?
የፓፓያ ጭማቂ በአንዳንድ ሻምፖዎች እና ቅባቶች ውስጥ ይገኛል። አምራቾቹም ይህንንም ማድረጋቸው ፡ፎሮፎርን እንደሚቀንስ ፤ የሚያሳክክ የራስ ቅል ቆዳን እንደሚያረጋጋ እንዲሁም ፤ የሚሰባበር ጸጉርን እንደሚያጠነክር ይገልጻሉ።
ታድያ ይሄ ግን በሳይንስ የተደገፈ አይደለም። ሳይንስ አሁን ያረጋገጠው ፤ የፊት ውበት ጠቀሜታ እንዳለው ነው። ጸጉር እና የራስ ቅል ላይ ባለው ጠቀሜታ ዙሪያ ገና ጥናቶች ያስፈልጋሉ።
📌 ታድያ እርስዎ እንዴት ይጠቀሙት?
ክፍሉ | ጥቅሙ | አጠቃቀሙ |
የሚበላው ክፍል/የፓፓያውን ስጋ//ውስጡን | በሽታ የመከላከል አቅምን ያግዛል። ለልብም ጤና ጠቃሚ ነው። የምግብ መፈጨትን ያያግዛል። | ጥሬ እንዳለ ይመገቡት። በሰላጣና በጭማቂ መልክም መጠቀም ይችላሉ |
ዘሩ//ፍሬው | ጉበትን ያግዛል/ይጠብቃል። ጸረ ተባይ ባህሪ አለው።። | ዘሩን በዱቄት መልክ አዘጋጅተው መጠቀም ይችላሉ። ሆኖም ግን አልፎ አልፎ ይጠቀሙ። |
ቅጠሉ | ፕሌትሌት መጠንን በደንግ ህመም ጊዜ ይጨምራል። | በጁስ መልክ ወይም እንደሻይ አድርገው መጠቀም ይችላሉ። |
ቆዳው/ልጣጩ | የሞተ ቆዳን ያስወግዳል፣ የጸረ ጀርም ባህሪ አለው | ቆዳዎት ላይ ይቀቡት ። |
የመጨረሻ ሀሳብ
ፓፓያ ብዙ የጤና ጠቀሜታ ያለው ፍራፍሬ ነው። ሆኖም ግን ተአምራዊ ፈውስ አይደለም። መድሐኒትን አይተካም። ህክምናን ለማገዝ ልንጠቀምበት እንችላለን።
ከቅጠሉ እስከ ዘሩ ሁሉነገሩ የጤና ጠቀሜታ ያለው ተክል ነው። ለዚህም ይብሉት፣ እንደጁስ ይጠቀሙት፣ እንደሻይ አፍልተው ይጠጡት ፤ ቆዳዎን ይቀቡት።
እንደ ብቸኛ የህክምና መፍትሔ ፈጽሞ እንዳይወስዱት። ላለብዎ የጤና እክል ሐኪምዎን ያማክሩ።
Comments