የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽንና መዘዙ
- Zebeaman Tibebu
- 3 days ago
- 3 min read
💧ስለ ሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ሰምተው እንደሚያውቁ ጥርጥር የለውም።
እጅጉን የተንሰራፋ እና የተለመደ ህመም ከመሆኑ የተነሳ ፤ ከ20 ሰዎች አንዱ በየአመቱ በሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ይታመማል።
እርስዎ በዚህ አመት ሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ታመው ነበር? የታመመ ሰውስ ያውቃሉ?
ምልክቶቹስ ምን ምን ናቸው ?
🌍ለምን ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ትኩረት መስጠት ይገባል?🚨

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን (UTIs) በጣም ከተለመዱ የባክቴሪያ ኢንፌክሽኖች መሀል ይጠቀሳል። በየአመቱ 150 ሚሊየን ሰዎች በሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ይታመማሉ። ከእነኝህም ውስጥ ወደ 300 ሺ የሚጠጉት ፤ ከሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ጋር በተያያዘ መዘዝ ይሞታሉ።
የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ሁሉንም እድሜ ክልል ያጠቃል። በሽታው በተለይ ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው፣ ሆስፒታል የተኙ ፣ የሽንት መሽኛ ካታተር የገባላቸው ፣ የበሽታ የመከላከል አቅማቸው የተዳከሙ ሰዎችን በይበልጥ እና በደረጀ መልኩ ያጠቃል። ከወንዶች ይልቅ ሴቶች በይበልጥ ይጠቃሉ። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ
ከ ሁለት ሴቶች አንዷ በህይወት ዘመኗ ቢያንስ አንድ ጊዜ በሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ትታመማለች።
ከ10 ሴቶች አንዷ በአመት አንዴ በ ሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ትጠቃለች።
ከ 4 ሴቶች ውስጥ አንዷ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ደጋግማ ትታመማለች።
አስደንጋጩ እውነታ ፡ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን በአለም ዙሪያ እየጨመረ ይገኛል።
ባለፉት አመታት ውስጥ የህክምና አቅማችን እየጎለበተ ቢመጣም ፤ የተለያዩ እጅጉን የላቀ አቅም ያላቸው የ ባክቴሪያ መከላከያዎች (አንቲ ባዮቲክስ) ቢሰሩም ፤ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን መጠን ባለፉት 30 አመታት ውስጥ በ ሁለት ሶስተኛ (68 %) ጨምሯል።
ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?
ኢትዮጵያ ውስጥ የተደረጉ የተለያዩ ጥናቶች ፤ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ስርጭት መጠን ምናልባት ሊበልጥ እንደሚችል ያሳያሉ።
በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ፤ 21.1 በመቶ የሚሆኑት የሽንትቧንቧ ኢንፌክሽን አለባቸው። ከእነኝህም ውስጥ አብዛኛው ሴቶች ናቸው።
በአዲስ አበባ 446 ታማሚዎችን ያሳተፈ ጥናት በበኩሉ ፤ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ስርጭት 31.6% መሆኑን ጠቁሟል።
በባሌ የተደረገ ጥናት እንዳሚያመላክተው ከሆነ ፤ የ ሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ስርጭት (ምልክት የምያሳየውን ጨምሮ) በነፍሰጡር ሴቶች መሀል 26% ይደርሳል።
🦠 በህመሙ እንዴት ይያዛሉ?

የሽንት ቧንቧችን የውስጥ ክፍል ከበሽታ አምጪ ባክቴሪያ በተፈጥሮ የጸዳ ነው። ሆኖም ግን አጋላጭ ምክንያቶች ሲከሰቱ በሽታ አምጪ ባክቴሪያዎች የሽንት ቧንቧን ይወራሉ። ከሽንት መውጫ ጫፍ ተነስተው ወደ ፊኛ ያመራሉ። ሃይ ባይ ከሌላቸው (መድሀኒት ካልወሰዱ) ወደ ኩላሊትም ይደርሳሉ። አቅሙ ከደረጀም ወደ ደም ውስጥ ገብቶ ለሕይወት እጅጉን አስጊ ኢንፌክሽን ሊያመጡ ይችላሉ።
ታድይ ይህ ያልተጠበቀ ክፉ እንግዳ (በሽታ አምጪ ባክቴሪያ) የሽንት ቧንቧን ያጠቃል። ይህም የሽንት ቧንቧችንን ያስቆጣል። ለዚህ አጸፋዊ ምላሽ የሚሰጠው ሰውነታችን ባክቴሪያውን ፈጽሞ ማጥፋት ከተሳነው ፤ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ይከሰታል።
ይህ ተጋላጭነት እና አጸፋዊ ምላሽ ከሰውነታችን የበሽታ መከላከል አቅም ጋር የተቆራኘ ነው። ለዚህም በሽታ የመከላከል አቅማቸው የተዳከመና ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው ሰዎች የመያዝ እድላቸው ይሰፋል። የሽንት መሽኛ ቱቦም የተደረገላቸው ሰዎች ቱቦው ባክቴሪያውን እሰከ ፊኛ መርቶ ስለሚገባ ፤ በሽንት ቧንቧ ደጋግመው ይጠቃሉ። ሴቶች በተፈጥሮ የሽንት ቱቧቸው አጠር እና ቀጥ ያለ በመሆኑ ፤ ባክቴሪያው መንገዱ ይቀልለታል። ለዚህም በሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን በብዛት ይጠቃሉ።
🔥 ምልክቶቹን ማወቅ አለብን?
የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ምልክት ላያሳይ ይችላል። የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ካለብዎ ፤ ሊያሳዩ የሚችሉዋቸው ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው።

ሽንት ደጋግሞ መሽናት
ሽንት ሲሸኑ ማቃጠል
ሽንት ቀለም መለወጥ
ሽንት ሽታ መኖር
ከእንብርት በታች የሚሰማ የሆድ ህመም
ትኩሳት/ ብርድ ብርድ ማለት
ድካም
የምግብ ፍላጎት መቀነስ
ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ ናቸው ።
እነኝህን ምልክቶች ካዩ ፤ በአቅራቢያዎ ወደሚገኝ ጤና ተቋም ሄደው ይታከሙ።
💔 ከሚታሰበው በላይ ከባድ የሆነበት ምክንያት ምንድነው?
በቀላል ህክምና እርዳታ ከሚሻሉ ህመሞች መሀከል ነው ብለው፤ ስለ ሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ፈጽሞ መዘናጋት የለብዎትም።
የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን በህክምና እርዳታ ቁጥጥር ላይ ካልዋለ ፤ መዘዙ ከበድ ሊል ይችላል። ወደሚከተሉትም ሊያመራ ይችላል።
ኪላሊትን አጥቅቶ ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ ሊያስከትል ይችላል። ይህም ከባድ ህመም ከመሆኑ በላይ ፤ ኩላሊት ላይ ጉዳት ያደርሳል።
ለህይወት አስጊ የሆነ የደም ውስጥ ኢንፌክሽን ያመጣል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለም አቀፍ ደረጃ እስከ 5% የሚደርሱ ከባድ የደም ውስጥ ኢንፌክሽኖች በሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ይከስታሉ። በዚህም ከታመሙ 10 ሰዎች ውስጥ አራቱ ይሞታሉ።
የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ያጋጠመው በእርግዝና ወቅት ከሆነ ፤ ጉዳቱ ከእናት አልፎ ጽንሱንም ያጠቃል። ምጥ ያለጊዜው እንዲመጣ ያደርጋል። የጽንስ ክብደት ይቀንሳል። የእናትየውንም ህይወት አደጋ ላይ ይጥላል።
ተደጋጋሚ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽኖች ያለባቸው ሰዎች ለህይወታቸው ከባድ እክል ይፈጥራል። በተደጋጋሚ በህመሙ የተነሳ ከስራ ቦታቸው ይቀራሉ። ከስራም ይባረራሉ። የህመሙ ምልክቶች ከማህበረሰብ እንዲርቁ ያደርጋቸዋል። ይህም ጭንቀት ውስጥ ሊከታቸው ይችላል።
💊 ሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ይታከማል።
አዎ በ አንቲባዮቲክስ መድሀኒቶችና በህክምና ክትትል ሊታከም ይችላል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የመድኃኒት አቅርቦት ውስንነት ፤ የህክምናውን ውጤታማነት በመጠኑ ቢገታም ፤ ባሉን መድኃኒቶች በደንብ መታከም ይችላል። ታክሞም ይድናል።
🚫 ታድያ ለመከላከል ምን ያድርጉ?

ህመሙ እስኪይዝዎ መጠበቅ የለብዎትም። ተጋላጭነትዎን መቀነስ ይችላሉ። ዛሬውኑ የሚከተሉትን ያድርጉ።
💧በቂ ውሀ ይጠጡ። ይህም ከሽንት ቱቦ ውስጥ የገቡ ባክቴሪያዎችን አጥቦ ያወጣል።
🧼 ንጽህናዎን ይጥብቁ። ይህም ባክቴሪያው እንዳይዛመት ያደርጋል።
🚽 ሽንትዎን አይቋጥሩ።
🚽 ሴቶች ከግብረ ስጋ ግንኙነት በኋላ ቢሸኑ ፤ በሽታ ተጋላጭነትን ይቀንሳሉ። ይህም ምክንያቱ ወደ ሽንት ቧንቧ የገባው ባክቴሪያ ፤ በሽንቱ ታጥቦ ስለሚያወጣ ነው።
🚫🧴 ሴቶች ንጽህናቸውን ሲጠብቁ፣ የሽንት ቧንቧን ከሚያስቆጡ አካላት መቆጠብ ይኖርባቸዋል። ለዚህም የሚከተሉትን አይጠቀሙ።
❌ ሻካራ ሳሙናዎች
❌ ስፐርሚሳይዶች (spermicides)
❌ የተለያየ ኬሚካል ያላቸው ንጽህና መጠበቂያዎች
❌ቅባቶች
💉የስኳር ህመም እና ሌሎች ተጓዳኝ ህመሞች ካለብዎ ፤ ደግሞ እነሱን ይቆጣጠሩ። የህክምና ክትትል ያድርጉ።
የተፈጥሮአዊ አማራጭም አለ።

ፕሪሞን (ክራንቤሪን) አዘውትሮ መመገብ ወይም ጭማቂውን መጠጣት ፤ የሽንት ቧንቧን ጤና ያሻሽላል። የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽንን ይቀንሳል።
💊 ከታመሙ ደግሞ በራስዎ መድሃኒት አይውሰዱ። ከላብራቶሪ ምርመራ በኋላ ፤ በዶክተርዎ ምክር ፤ ትክክለኛውን መድሐኒት መውሰድ ይኖርብዎታል
📢 ትኩረት እና እንክብካቤ ሊደረግለት የሚገባ አሳሳቢ የጤና ችግር ነው።
🎯 ጤናዎ ከግንዛቤ ይጀምራል። ግንዛቤን ከተግባር ጋር አጣምረው ፤ ጤናዎን ይጠብቁ። ህይወትዎን ያሻሽሉ።
አያመንቱ። ዛሬውኑ እርምጃ ይውሰዱ።
Comments