top of page

❤️ የልብ ቧንቧ በሽታ ለምን ያጋጥማል?

Updated: Nov 3

እንደ ልብዎ ያለ ታታሪ ማሽን ያውቃሉ?


በየእለቱ እኮ ልብዎ ወደ 7,000 ሊትር የሚጠጋ ደም ያዘዋውራል። በቀን ከ1000 ጊዜ በላይ ሙሉ ደሞዎን ያዘዋውራል።


ልብዎ ይህንን ሲሰራ ታድያ ፤ የራሱ የሆነ ስርአት አለው። የልብ ክፍሎች እርስ በእርስ ተናበው እና ተጣጥመው ነው የሚሰሩት።

ree

በቀኝ በኩል ያሉት ያልተጣራ ደም ተቀብለው ወደ ሳንባ ሲልኩ ፤ በግራ ያሉት ደግሞ የተጣራውን ደም ተቀብለው ለሰውነት ያዳርሳሉ።


ይህንን ስራ በሚሰራበት ጊዜ ልብዎን ስራውን የሚያስተባብሩ የልብ ቧንቧዎች አሉ። እነኝህ ቧንቧዎች ዘብ ናቸው ። ቀጣይ የልብ ክፍል ስራውን ሰርቶ እስኪጨርስ ፤ ደምን ወረፋ አስይዘው ፤ መንገድ ዘግተው ይጠብቃሉ። ቀጣይ ክፍል ስራውን ሲጨርስም ፤ ከፍተው ደሙን ያሳልፋሉ። ይህንን በማድረጋቸው ደም ያለቦታው እንዳይገባ/እንዳይደባለቅ ፣ በቅደም ተከተሉ እንዲሄድ ያስችላል።ይህ ኡደት ቀኑን ሙሉ ይቀጥላል።

 

መቼም አያርፉም!

ከመጀመሪያ እስትፋንሳችን እስከ መጨረሻዋ ቅጽበት ይሰራሉ። በቀን 100,000 ጊዜ በላይ ይዘጋሉ ከ100,000 ጊዜ በላይ ይከፈታሉ።


የልብ ቧንቧዎች ከሌሉስ?

እነኝህ ቧንቧዎች ከሌሉማ ... ደም ስርአት አይኖረውም። ይደበላለቃል። ልብም ስራውን መስራት አይችልም።

 

እነኝህ ቧንቧዎች ችግር ካጋጠማቸውስ?

እንደችግሩ ደረጃ ደም ስርአት መጣስ ይጀምራል። ወደተሳሳተ አቅጣጫ ይሄዳል። ወደ ኋላ ይመለሳል። በአጠቃላይ የልብ ስራ ይስተጓጎላል

 

የልብ ስራ ተስተጓጎለ ማለት ፤ በቂ ደም ለሰውነት አይዳረስም ማለት ነው። ይህ ደግሞ ብዙ እክል ያስከትላል።


⚙️ የቧንቧ ችግሮች እንዴት ይከሰታሉ?


ልባችን አራት ቧንቧ ሲኖረው ፤ እነኝህ ቧንቧዎች ስራቸው በትክክለኛ ሰአት መከፈት እና መዘጋት ነው። ሲከፈቱ በደንብ ግርብብ ብለው መከፈት ሲኖርባቸው ፤ ሲዘጉ ደግሞ ደም  በማያሳልፍ  ደረጃ  ግጥም  ብለው  መሆን  አለበት ።  ታድያ  የቧንቧ  በሽታዎች  አጋጠሙ  የምንለው የልብ ቧንቧ  ይህ ስራው ሲስተጓጎል ነው። ለዚህም ችግሩ እንደሚከተለው ሊሆን ይችላል። 


ree

  • በትክክል መክፈት አለመቻል (ስቴኖሲስ) - ይህ በሌላ ስሙ የልብ ቧንቧ መጥበብ ሊባል ይችላል። የዚህ ችግር መሰረቱ የልብ ቧንቧ ሙሉ በሙሉ መከፈት አለመቻሉ ነው። ለዚህም ደም የሚያልፍበት ቀዳዳ ይጠባል። ይህ ደግሞ ከአንድ የልብ ክፍል ወደ ሌላ የሚሸጋገረውን የደም ፍሰት ይገድባል። በቂ ደምም ወደ ቀጣይ የልብ ክፍል መተላለፍ ይሳነዋል።

     

  • በትክክል መዝጋት አለመቻል (ሪገርጂቴሽን/ ኢንሰፊሸንሲ)- ይህ ደግሞ የልብ ቧንቧ ገጥሞ መዝጋት ባለመቻሉ ይከሰታል። ለዚህም ያለፈ ደምን ዘግቶ መያዝ ይሳነዋል። ልብም ደምን ወደፊት ለመግፋት በምትኮማተርበት ወቅት ፤ ይህ ቧንቧ ደፍኖ ስለማይዘጋ ፤ ደም ወደ ኋላ ያገረሻል / እየተመለሰ ያስቸገራል። ለዚህም ወደፊት የሚጓዘው ደም መጠን ይቀንሳል።


ብዙ ጊዜ እነኝህ ችግሮች በአንድ ጀምበር የሚከሰቱ አይደሉም። ቀስ በቀስ በጊዜ ውስጥ እየተባባሱ የሚመጡ እክሎች ናቸው። የህክምና እገዛም ካልተደረገላቸው ልብ ላይ ጫናን ያሳድራሉ።


ወደፊት የሚልከው ደም ያነሰበት አልያም ወደ ኋላ የሚቀረው ደም የበዛበት ልብም ፤ ይህንን ለማስተካከል የበለጠ እንዲሠራ ይሆናል። ይህም ትርፍ ስራ ልብን ይብሱኑ ያጨናንቃል። ይህም የልብ ቧንቧ በሽታውን ያባብሳል። ይህም ለከፋ ችግር ያጋልጣል።

 


🧬 ለምን እነኝህ ችግሮች ይከሰታሉ? (መንስኤዎቹ)


የልብ ቧንቧ ችግሮች ከመሬት ተነስተው የሚመጡ አይደሉም።  በብዙ አጋላጭ ምክንያቶች ሊከሰቱ ይችላሉ። ከእነኝህ ውስጥ ጥቂቶቹ

ree

ከዚህ በፊት ስለዚህ የልብ ቧንቧ ችግር ያወሳን ሲሆን ፤ የበሽታ መክላከያ ስርአታችን የልብ ቧንቧዎችን ማጥቃት ሲጀምር የሚፈጠር ነው። በይበልጥ ለመረዳት ያንብቡት። ጽሁፉ እንደሚያብራራውም ካልታከመ የጉሮሮ ህመም ጋር ግንኙነት አለው።


ይህም ከኢንፌክሽን ጋር ተያያዥነት ስላለው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገራት ላይ እጅጉን የተለመደ ነው። በሀገራችን ኢትዮጵያ ካሉ የልብ ታማሚዎች መሀል ከፊሉ ይህ የልብ ቧንቧ ችግር አለባቸው።


🔹 2. ከእርጅና/ ከእድሜ ጋር የተያያዙ የልብ ቧንቧ ለውጦች

ree
እስቲ አስቡት... እያንዳንዱ የልብዎ ቧንቧ በአመት 75 ሚሊየን ጊዜ ተከፍቶ ይዘጋል።

ሳያሰልስ የሚሰራ ይህ ቧንቧ ህይወት ዘመናችንን ሙሉ ስለሚሰራ ፤ ዘመን በጨመረ ቁጥር በእንቅስቃሴ ብዛት እንዲሁም ከእድሜ ጋር በተያያዙ ለውጦች እየደደረ ይመጣል። ይህም መደደር ቧንቧው በአግባቡ እንዳይከፈት እንዳይዘጋ ያደርጋል።


ለዚህም ይህ ችግር ይህ በአዛውንቶች ወይም እድሚያቸው በገፋ ሰዎች ላይ የተለመደ ነው። በተለይም እድሜያቸው ከ60 ያለፉ ሰዎች ላይ በይበልጥ ይታያል።  የካልሲየም ማዕድን መጨመርም ይህንን መደደር ሊያስከትል ይችላል። በዚህ ችግር በብዛት ሲጠቃ የሚስተዋለው ከልብ ቧንቧዎች መሀከል የኦርቲክ ቫልብ የሚባለው ነው።


🔹 3. ከውልደት ጋር የሚያያዙ የልብ ቧንቧ በሽታዎች

አንዳንድ የቧንቧች ችግሮች ከውልደት ጀምሮ ሊከሰቱ ይችላሉ። ይህም ችግር ከቧንቧው አቀማመጥ/አመሰራረት ጋር የተያያዘ ነው።

ree

🔹 4. የልብ ቧንቧ ኢንፌክሽን

አንዳንድ ደማችን ውስጥ የገቡ በሽታ አምጪ ተህዋሳት የልብ ቧንቧን ወረው ጉዳት ሊያደርሱበት ይችላሉ። ብዙዎን ጊዜ እነኝህ ባክቴሪያዎች የሚመጡት ከጥርስ ኢንፌክሽን ፣ በደም ስር ከሚወሰድ አደገኛ እጽ እንዲሁም አንዳንድ ቆዳን ሰውነትን የሚቀዱ ህክምናዎችን ተከተለው ነው።


🔹 5. ሌሎች ምክንያቶች

የከፍተኛ የደም ግፊት ፣ ቁጥጥር ስር ያልዋለ ስኳር በሽታ ፣ ከፍተኛ የሆነ የኮሌስትሮል መጠን፣ የደረት የጨረር ህክምና የልብ ቧንቧ ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ። እንደ ሉፐስ ያሉ የበሽታ መከላከያ ስርአትን የሚያጠቁ በሽታዎችም ይህንን ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ።  


🌍 ስርጭቱስ ምን ይመስላል?

ree

በአለም አቀፍ ደረጃ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የልብ ቧንቧ ችግር (VHD) እንዳለባቸው ይገመታል። በማደግ ላይ ባሉ አገራት ይህ ችግር ከ ሪዩማቲክ የልብ ሕመም ምክንያት ይመጣል። ይህ በሽታ በተለይም በአፍሪካ እና በደቡብ እስያ ዋነኛው የልብ ቧንቧ በሽታ መንስኤ ሆኖ ይጠቀሳል። ባደጉ አገራት ደግሞ በተቃራኒው ከእድሜ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የልብ ቧንቧ ችግሮች ይስተዋላሉ።



⚠️ ምልክቶቹን እንዴት መለየት ይቻላል?


የልብ ቧንቧ ችግር ኖርዎቦት ላያውቁ ይችላሉ።

ያለብዎ የልብ ቧንቧ ችግር የልብ ስርአትን በደንብ እስካላስተጓጎለ ድረስ በሽታው ከጀርባ ሳይታወቅ ሊጎለብት ይችላል። ለዚህም ታማሚዎች በሽታው እንዳለባቸው ሳይጠረጥሩ አመታት ሊቆዩ ይችላል። በሽታው ደርጅቶ የልብ ስራ ላይ እክል ካመጣ ግን የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያዩ ይችላሉ፡


ree

  • የትንፋሽ ማጠር (በተለይ በእንቅስቃሴ ወቅት አልያም በጀርባዎ ለጥ ብለው ሲተኙ)

  • የደረት ሕመም

  • ደረት ላይ የመጫን ስሜት

  • ድካም/ አቅም ማጣት

  • የልብ ምት መፍጠን ስሜት አልያም ልብ ምት የዘለለ መምሰል

  • የሰውነት እብጠት (በቁርጭምጭሚት ወይም በሆድ አከባቢ ያለ እብጠት)

  • ራስን መሳት ወይም ማዞር ሊስተዋሉ ይችላሉ።


ደርጅቶ እዚህ የደረሰ የቧንቧ ችግር ታድያ ፤ አሁንም ህክምና ካልተደረገለት .... የልብ ድካም፣ ስትሮክ ወይም ድንገተኛ  ሞት ሊያመጣ ይችላል።


🩺 እንዴት ብለው ተመርምረው ጤናዎን ይወቁ?


ree

በህክምናው የልብ ቧንቧ ችግሮችን ለመለየት የተለያዩ ምርመራዎች ማድረግ ይቻላል። እነኝህም ውስጥ የተወሰኑት አነሆ፡

  • የልብ አልትራሳውንድ /ኤኮካርዲዮግራፊ (Echocardiography (ECHO))  ይህ ተመራጩ የምርመራ አማራጭ ሲሆን ፤ የልብን ግድግዳ / ቧንቧዎቹን እንዲሁም  እንዲሁም አወቃቀሩን በምስል ሊያሳይ ይችላል። በልብ ስፔሻሊስት ባለሙያም የሚደረግ ምርመራ ነው።


  • ኢሲጂ (ኤሌክትሮካርዲዮግራም /electrocardiogram) ይህም ልብ የምትለቀውን ሞገድ በመመዝገብ የልብ ቧንቧ ችግር ካለ በእጅ አዙር ሊያሳይ ይችላል። የልብ አመታት ለውጥ እንዲሁም የልብ መጠን መግዘፍንም ሊያሳይ ይችላል።


ከዚህ ባሻገር ባለሙያው እንደአስፈላጊነቱ  የተለያዩ ኢሜጂንጎችን (የደረት ኤክስ ሬይ እንዲሁም ሌሎችን) ፣ የላብራቶሪ ምርመራዎችን እንዲሁም ለየት የልብ ምርመራዎችን ሊያዝ ይችላል። በእነርሱም ተመርኩዞ የልብ ቧንቧ እና ልብ ያሉበትን ለመለየት ያስችላል።


💊 እንዴትስ ይታከማል?


የልብ ቧንቧ በሽታ ሕክምና በተጎዳው ቧንቧ እና በበሽታው ክብደት ላይ የተመሰረተ ነው።

ree

1. ምልክቶችን ለመቆጣጠር መድሃኒቶች ሊሰጡ ይችላሉ። እንደምልክቱ እብጠትን የሚቀንሱ ፣ የልብ ምትን የሚቆጣጠሩ ፣ የደም መርጋትን የሚከላከሉ፣ ኢንፌክሽንን የሚቃወሙ ፣ የልብን ስራ የሚያቃልሉ መድሀኒቶች ሊታዘዙ ይችላሉ።


2. በቀዶ ጥገና ደግሞ የተጎዳውን ቧንቧ ለመጠገን አልያም በሰው ሰራሽ ቧንቧ የመተካት ሙከራ ሊደረግ ይችላል። የቀዶ ጥገና አማራጩም እንደ ቧንቧው እና እንደ በሽታው አይነት ሊለያይ ይችላል።


ree

3. ጉዳቱ እጅጉን ዝቅተኛ ከሆነ እና የልብን ስራ ካላስተጓጎለ በክትትል ሊታለፍ ይችላል። ይህን ጊዜ የሚመከር የአኗኗር ዘይቤ አለ። ለምሳሌ፡

  • በመደበኛ ሁኔታ ኢሲጂ ምርመራ ማድረግ ይኖርብዎታል።

  • ጨው፣ አልኮል እና ትምባሆ መገደብ ይኖርብዎታል።

  • ኢንፌክሽኖችን ቀደም ብሎ ማከም ይኖርብዎታል።

 

🛡️ ተመራጩ መፍትሔ = መከላከል


እነኝህን ችግሮች መከላከል ይችላል። መከላከሉ የልብን መሰረታዊ መንስኤዎችን ቀደም ብሎ በመፍታት ላይ ያተኩራል። ለዚህም


  • የጉሮሮ መቁሰልን በፍጥነት በማከም የልብ ቧንቧ ጉዳት ሳይመጣ መመለስ ይቻላል። በተለይ በልጆች ላይ የስትሬፕቶኮካል ኢንፌክሽኖች ቀድሞ ማከም ያስፈልጋል።

  • የጥርስ ንፅህናዎን በስርአት መጠበቅ ይኖርብዎታል። ይህም በኢንፌክሽን ምክንያት የሚከሰተውን የልብ ቧንቧ ጉዳት ለመከላከል ያስችላል። 

  • ፈጽሞ አደገኛ እጽ ባለመጠቀምም ይህንን መከላከል ይቻላል። 

  • የደም ግፊትዎን መጠን እና ኮሌስትሮል መጠንም ከተቆጣጠሩ ፤ የልብ ቧንቧ ችግር የማጋጠም እድል ይቀንሳሉ።

  • ተጋላጭነታችው ከፍ ላለ ሰዎች መደበኛ የልብ ምርመራ እና ክትትል በማድረግ ችግሩ ሳያጋጥም ማከም ይቻላል።  

  • ከጥርስ ህክምና  እንዲሁም ቆዳን ወይም አካልን ቀደው የሚገቡ ህክምናዎች በፊት የመከላከያ አንቲባዮቲክ በመውሰድም መከላከል ይችላል።

  • እንደ የደም ግፊት እና የስኳር በሽታ ያሉ ሥር የሰደዱ በሽታዎች ካሉብዎ በህክምና መቆጣጠርዎም ያስፈልጋል።

  • አዘውትረው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግም ይኖርብዎታል።


💬 ታድያ ምን ያላሉ?

ለልብዎ ጤና ቦታ መስጠት ያለብዎ ዛሬ ነው። ከመታመምዎ በፊት ይከላከሉ።


ቀን ከሌት የሚታትረውን ልብዎን ጤና ይጠብቁ ። ግንዛቤዎን ያሻሽሉ ።


በቅድመ ምርመራ፣ በተገቢ ህክምና እና ክትትል ጤናዎን ዛሬ ያረጋግጡ።


የዚህን ማሳያ ይህንን እውነተኛ ታሪክ ይመልከቱ፡ የህዝቅኤልን የልብ ቧንቧ ችግር እና የተደረገለትን ህክምና እና ውጤት ያሳያል።


Comments


bottom of page