የፌስቱላ ስውር ስቃይ እና ተስፋው
- Zebeaman Tibebu
- 1 day ago
- 4 min read
የአንድ ሴት የዝምታ ሸክም... እና የብዙዎች ስውር ስቃይ

አንዲት ወጣት እናት ከሰዓታት ከባድ ምጥ በኋላ ልጇን በሰላም አቀፈች። ነገር ግን የስቃይዋ ምዕራፍ በዚያ አላበቃም ነበር። ከጥቂት ቀናት በኋላ ሽንቷን መቆጣጠር አቃታት። በቀንም በሌሊትም ያለማቋረጥ የሚፈሰው ሽንት፤ ልብሷን ማበላሸት ጀመረ። ከቤተሰብ ጋር መቀመጥ፣ ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ መሳተፍ አልፎ ተርፎም ፤ ልጇን በደስታ ማቀፍ የማይታሰብ ሆነባት። ከሰው ተገልላ በቤት ውስጥ በጭንቀት ቀረች።
ለምን?

ይህች እናት ያጋጠማት ከወሊድ ጋር የተያያዘ ፌስቱላ ችግር (Obstetric Fistula) ይባላል።
ይህ የአንድ ሴት እውነታ ብቻ አይደለም!
በዓለም ዙሪያ በግምት 457,000 የሚሆኑ ሴቶች በወሊድ ወቅት በሚከሰት የፌስቱላ በሽታ ይያዛሉ። ይህ በሽታ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የአፍሪካ አገራት በብዛት የተለመደ ነው። አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በእነዚህ ክልሎች ከ100,000 ሴቶች ውስጥ ከ36 እስከ 71 የሚሆኑትን በዚህ በሽታ ይጠቃሉ።
ታድያ ፌስቱላ ምንድን ነው?
ፌስቱላ (Fistula) ማለት በመደበኛነት መገናኘት የሌለባቸው ሁለት የሰውነት ክፍሎች መካከል የሚፈጠር ያልተፈለገ፤ ተፈጥሮአዊ ያልሆነ ክፍተት / ቀዳዳ ነው።
ይህ ቀዳዳ አብዛኛውን ጊዜ የሚፈጠረው በሁለት በኩል ነው፦
በሽንት ፊኛ (Bladder) እና በማህጸን (Vagina) መካከል
ወይም በአንጀት (Rectum) እና በማህጸን (Vagina) መካከል ነው።

በዚህ ቀዳዳ ምክንያት፤ ሽንት ወይም ሰገራ በምንም መልኩ መቆጣጠር ሳይቻል በቀጣይነት እና ያለማቋረጥ ወደ ውጭ ይፈሳል። ይህ አካላዊ ስቃይ ብቻ ሳይሆን፤ የእናቶችን ማኅበራዊ ሕይወት ሙሉ በሙሉ የሚያናጋ እና ክብርን የሚነካ ከባድ ሸክም ነው።
ችግሩ እንዴት ይፈጠራል?

የወሊድ ፌስቱላ በአብዛኛው የሚከሰተው በተራዘመ እና በተስተጓጎለ ምጥ (Obstructed Labor) ምክንያት ነው። አንዲት እናት ያለ ሕክምና ዕርዳታ ለሰዓታት አልፎ ተርፎም ለቀናት በምጥ ስትሰቃይ፤ ሕፃኑ በወሊድ መንገድ ውስጥ ተጣብቆ ይቆያል። በዚህ ጊዜ የሕፃኑ ራስ በእናቱ የዳሌ አጥንት እና በውስጠኛው ለስላሳ ስጋ (ቲሹዎች) ላይ እጅግ ከባድ ጫና ይፈጥራል።
ይህ ቀጣይነት ያለው ግፊት ወደዚያ አካባቢ የሚሄደውን የደም ዝውውር ሙሉ በሙሉ ያሳጣዋል። የደም ዝውውር ሲቋረጥ ደግሞ የማህጸን ግድግዳ ስጋ ይሞታል። በሳምንት ጊዜ ውስጥም ይህ ስጋ በስብሶ በመውደቁ በእነኝህ አካላት መካከል ቀዳዳ /ፌስቱላ ይፈጥራል። ከዚህ ሁሉ ስቃይ በኋላ ግን የሚያሳዝነው፤ በብዙ አጋጣሚዎች የሕጻኑም ሕይወት ላይተርፍ ይችላል። ለእናቲቱ የአካልና የሥነ-ልቦና ስብራት ብቻ ሳይሆን የልጅ ማጣት ሐዘንም ይደራረብባታል።
ከሕክምናው በስተጀርባ ያለው እውነተኛው ምስጢር
ፌስቱላ የሕክምና ችግር ብቻ አይደለም። ሥር የሰደደ የድህነት፣ የፆታ እኩልነት እጦት፣ የሕፃናት ጋብቻ እና የሴቶች መብት ጥሰት ውጤት የሚወልደው ማኅበራዊ ቀውስ ነው።

ዋና ዋና ምክንያቶቹ የሚከተሉት ናቸው።
1️⃣ የሕፃናት ጋብቻ (ያለዕድሜ ጋብቻ)
በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ውስጥ ልጃገረዶች ገና ሰውነታቸው ሳይጎለብት ፤ እና የዳሌ አጥንታቸው ሙሉ በሙሉ ሳይዳብር ፤ ለትዳር ይዳረጋሉ። ከዚያም ወዲያውኑ ወደ እርግዝና ይገባሉ። ገና ያልጠነከረውና ጠባብ የሆነው የዳሌ አጥንታቸው የተፈጥሮ ወሊድን ማስተናገድ ስለማይችል፤ ምጥ በእጅጉ ይራዘማል፤ ይህም በቀጥታ ለፌስቱላ አደጋ ያጋልጣቸዋል።
2️⃣ ፆታዊ ጥቃት እና አስገድዶ መድፈር
ፆታዊ ጥቃት በተለይ በሕፃናትና በወጣት ልጃገረዶች ላይ ሲደርስ፤ ከባድ የብልት፣ የሽንት ፊኛ እና የፊንጢጣ የውስጥ አካላት መቀደድና መጎዳትን ያስከትላል። በአንዳንድ አሰቃቂ ሁኔታዎች ጥቃቱ ራሱ በቀጥታ ፌስቱላን ሊፈጥር ይችላል። ከዚህም ባለፈ፤ ጥቃቱ የሚያስከትለው ያልተፈለገ እርግዝና፤ ልጃገረዶቹን በልጅነታቸው ለወሊድ ይዳርጋቸዋል። ያልዳበረ ሰውነታቸውም ለተያያዙ የወሊድ አደጋዎች ተጋላጭ ይሆናል።

3️⃣ ሥር የሰደደ ድህነት
ብዙ እናቶች የወሊድ ምጥ ሲጀምርባቸው፤ ወደ ጤና ተቋም በጊዜው መድረስ አይችሉም። የሚኖሩበት አካባቢ ርቀት፣ የትራንስፖርት እጥረት፣ ለሕክምና የሚሆን የገንዘብ አቅም ማጣት እና በአቅራቢያቸው የጤና ተቋማት አለመኖር ምጡ ተስተጓጉሎ አካላቸው እስኪጎዳ ድረስ በቤት ውስጥ እንዲቆዩ ያስገድዳቸዋል። ይህም ድህነት እናቶችን ለሕይወት ዘመን ስቃይ አሳልፎ ይሰጣል።
ፌስቱላ ከሰውነት በላይ ሕይወትን ይጎዳል!
የፌስቱላ አሰቃቂ ጉዳት በሰውነት ላይ በሚፈጠረው ቀዳዳ ብቻ አያበቃም። በሽታው የአካልን ጤና ብቻ ሳይሆን፤ የአንዲትን እናት ሰብዕና፣ ተስፋ እና መላ ሕይወቷን ቀስ በቀስ ሰልቅጦ የሚያጠፋ ስውር ጠላት ነው።

በዚህ በሽታ የተጠቁ ብዙ እናቶችና እህቶቻችን፦
ከቤተሰብ ይገለላሉ፦ ያለፈቃዳቸው በሚፈሰው ሽንትና ሰገራ ምክንያት የሚመጣውን ጠረን መቋቋም ባለመቻላቸው፤ በጣም የሚወዷቸው ሰዎችና የትዳር አጋሮቻቸው ሳይቀሩ ጥለዋቸው ይሸሻሉ።
ከማኅበረሰብ ይርቃሉ፦ ሰዉ ያማኛል፣ ያገለኛል በሚል ፍርሃትና ኃፍረት ራሳቸውን ከማንኛውም ማኅበራዊ ግንኙነት(እድር፣ ዕቁብና ሰርግ )ያገላሉ። ገና በወጣትነታቸው በጨለማ ክፍል ውስጥ ብቻቸውን እንዲቀመጡ ይፈረድባቸዋል።
ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ፦ ወጣት ልጃገረዶች በዚህ ችግር ምክንያት ወደ ትምህርት ገበታ መመለስ አይችሉም፤ የወደፊት ብሩህ ተስፋቸውና ሕልማቸው ገና በጠዋቱ ይቀጫል።
ሥራቸውን ያጣሉ፦ የመንቀሳቀስ አቅማቸው ስለሚገደብና የሰዎች መስተጋብር ስለሚከብዳቸው፤ የዕለት ጉርሳቸውን የሚገነቡበትን የሥራ ዕድልና የኢኮኖሚ ነፃነታቸውን ሙሉ በሙሉ ያጣሉ።
ለድብርትና ለጭንቀት ይጋለጣሉ፦ ይህ ሁሉ መገለልና የብቸኝነት ኑሮ ለከፍተኛ የሥነ-ልቦና ቀውስ፣ ለከባድ ድብርት (Depression) ያመራል። በሕይወት ተስፋ መቁረጥ የሚያጋጥማቸው ጥቂቶች አይደሉም።
ይህም ፌስቱላን ከአካላዊ በሽታ በላይ፤ የአንዲትን ሴት ሰብአዊ ክብር መሬት ላይ የሚጥል ጥልቅ ማኅበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ቀውስ ያደርገዋል።
ፌስቱላ ሊታከም ይችላል?
መልሱ አዎን ነው!
ማንም እናት ወይም እህት በዚህ በሽታ ምክንያት እድሜ ልኳን በጨለማ ክፍል ውስጥ ልትቀጣ አይገባም። የወሊድ ፌስቱላ ታክሞ፤ ድኖ፤ የጠፋውን ሰብአዊ ክብር ሙሉ በሙሉ መልሶ ማግኘት የሚቻልበት ተስፋ አለ።

ህክምናውስ ምንድነው?
እያንዳንዱ የሰውነት አካል ጉዳት የተለያየ እንደመሆኑ መጠን፤ የሚሰጠው የሕክምና ዓይነትም እንደ ፌስቱላው ዓይነት፣ እንደ ተፈጠረበት ቦታ፣ እና እንደ ቀዳዳው ስፋት ወይም መጠን ይለያያል። የህክምና አማራጮቹ የሚከተሉት ናቸው።
የቀዶ ጥገና ሕክምና ፦ በአብዛኛው በወሊድ የመጣ ፌስቱላ ቀዳዳን ለመስፋት፤ እንዲሁም የተፈጥሮ የሽንት ወይም የሰገራ መተላለፊያ መስመርን እንደገና ለመጠገን ጥንቃቄ የተሞላበት ቀዶ ጥገና ያስፈልጋል። ይህ ቀዶ ጥገና እናቶችን ወደ ቀድሞ ጤናማ ህይወታቸው የመመለስ አቅም አለው።
ተጨማሪ የእንክብካቤ ሕክምናዎች፦ በአንዳንድ ሁኔታዎች ላይ ቀዶ ጥገና ከመደረጉ በፊት ወይም በኋላ ኢንፌክሽንን በፀረ-ተህዋሲያን (Antibiotics) መድሀኒት መቆጣጠር፣ የተጎዳውን ስጋ( tissue) ማከም፣ የአካል ብቃትን እና የተመጣጠነ ምግብ ሁኔታን ማሻሻል፣ እንዲሁም የዳሌ ጡንቻዎችን ለማጠናከር የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች (Physiotherapy) ሊያስፈልጉ ይችላሉ።
እዚህ ላይ ልናስተውለው የሚገባው ትልቁ ወሳኝ ነጥብ፤ ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ቀደም ብሎ ሕክምና መፈለግ እጅጉን ይመረጣል። ይህም የሕክምናውን ውጤታማነት የተሻለ ያደርገዋል። እናቶች በሽታውን ደብቀው ባቆዩት ቁጥር ተጨማሪ የጤና እና የሥነ-ልቦና ጉዳቶች ስለሚደራረቡባቸው፤ መፍትሔውን ቀድሞ መፈለግ የሕክምናውን ስኬት በእጅጉ ይጨምራል።
መልካሙ ዜና ምንድን ነው?
ምንም እንኳን የወሊድ ፌስቱላ አስፈሪ እና አሰቃቂ የህይወት ጠባሳ ቢሆንም፤ ትልቁ የምሥራች ግን ይህ ነው፦
ፌስቱላ ብዙ ጊዜ መከላከል የምንችለው ሕመም ነው!

እናቶቻችን እና እህቶቻችን በዚህ ስውር ስቃይ ውስጥ እንዳያልፉ፤ ህብረተሰቡ እጅ ለእጅ ተያይዞ ፤ የሚከተሉትን ወሳኝ እርምጃዎች መተግበር ይችላል፦
የሕፃናት ጋብቻን መከላከል፦ ልጃገረዶች አካላቸው ሳይበስል ለትዳርና ለእርግዝና እንዳይዳረጉ በቁርጠኝነት መከላከል አለብን።
ልጃገረዶችን በትምህርት ማቆየት፦ ሴት ልጆች ተምረው ራሳቸውን እንዲያውቁና የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ በትምህርት ገበታ ላይ መቆየት አለባቸው።
በሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች እገዛ መውለድ፦ እናቶች በቤት ውስጥ በምጥ ከመሰቃየት ይልቅ፣ በሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች ክትትል እንዲወልዱ ማድረግ ያስፈልጋል።
አስቸኳይ የወሊድ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ፦ ምጥ ሲገጥም በአቅራቢያ የሚገኙ የወሊድ ህክምና እንዲሁም የሲኤስ ቀዶ ህክምና አማራጮች ተደራሽ መሆን አለባቸው።
ጾታዊ ጥቃትን መከላከል፦ በልጃገረዶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በማስቆም፤ የውስጥ አካላት መጎዳትን እና ያለዕድሜ እርግዝናን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ይችላላ።
እነዚህ በሙሉ በሚገባ በጋራ ከተተገበሩ፤ ፌስቱላን ከሀገራችን ምድር ጠርጎ ማጥፋት ይቻላል።
ሁላችንም ልናስታውሰው የሚገባ ታላቅ እውነት!
ፌስቱላ ፈጽሞ የሴቶች ዕጣ ፈንታ አይደለም! የሴቶች መብት፣ የእናቶች ጤና እና የማኅበራዊ ፍትሕ ጉዳይ ነው።
ፌስቱላን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ የሆስፒታል ቀዶ ጥገና ብቻ አይፈልግም!
ከዚያ በበለጠ የሕፃናት ጋብቻን በጋራ መቅረፍ፣ ጾታዊ ጥቃትን መከላከል፣ የሴቶችን ትምህርት ማጠናከር እና የእናቶችን ጤና አጠባበቅ ማሻሻልን ይጠይቃል።

የመፍትሔው አባል ለመሆን የሚከተሉትን ያድርጉ!
ይህንን ስውር ስቃይ በጋራ ለማስቆም አሁኑኑ የበኩርዎን ድርሻ ይወጡ፦
መረጃውን አሁኑኑ ያጋሩ ፦ ይህንን ጽሑፍ ለሌሎች በማጋራት ግንዛቤ ይፍጠሩ። ብዙ እናቶች በሽታው ሙሉ በሙሉ እንደሚታከም አያውቁም።
መፍትሔ ይጠቁሙ፦ በአካባቢዎ በዚህ ችግር የተጠቃች እናት ካለች፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በነፃ የሕክምና አገልግሎት ወደሚሰጠው ሐሚሊን ፌስቱላ ሆስፒታል (Hamlin Fistula Ethiopia) ወይም ሌሎች በጎ አድራጎቶች በመጠቆም ሕይወቷን ይታደጉ።
አያግልሉ! ከሕክምና የተመለሱ እናቶችን በፍቅር በመቀበልና በመደገፍ ሰብአዊ ክብራቸውን እንዲያገኙ ያግዙ።




Comments