ከነጭ ቆዳዎች በስተጀርባ ፡ የለምጽ እጣ በኢትዮጵያ
- Zebeaman Tibebu
- Apr 14
- 4 min read
ውበት ለየፈርጁ ቢሆንም ፤ ቆዳችን ውበታችን ነው። የቆዳችን ጤና የ ውበት መለኪያ መስፈርት የሆነውም ለዚህም ነው። የቆዳችን ሁኔታ መልካችንን ይወስናል ፣ በራስ መተማመናችንን ይጨምራል ወይም ያመነምናል።

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ የለምጽ ህሙማን አሉ። ነገር ግን በተሳሳተ መረጃ ላይ በተመሰረተ ዝምታ እና መገለል ህመማቸው ተረስቶ ፤ ችግራቸው ተዘንግቷል።
ዛሬ የምናወጋው ስለ ቆዳ ህመም ብቻ አይደለም። ስለ ውበት፣ ስለ ማንነት እና ስለ ክብርም ጭምር እንጂ። በአስቸኳይ መለወጥ ስላለብን ትውፊት ነው የምንነጋገረው።
ለምጽ ምንድን ነው?
ለምጽ ህመም በ ህክምናው ቪትሊጎ (Vitiligo) የሚባል ሲሆን ፤ የቆዳ ቀለም የሚያመነጩ ህዋሳት በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ሲጠቁ የሚፈጠር ነው። እነኝህ ህዋሳት በመሞታቸው የተነሳ ፤ ቆዳችን ቀለም ማምረት ስለማይችል ፤ በስፍራው ቆዳችን ቀለም አልባ/ ነጭ ይሆናል።

ከፊታችን እስከ እግራችን ድረስ ያለ የትኛውም ቆዳ በዚህ ህመም ሊጠቃ ይችላል። ከቆዳ ባሻገር እነኝህ ህዋሳት ስላሉባቸው አይናችንን እና ጸጉራችንንም ሊያጠቃ ይችላል።
በህክምናው ከሆነ ህመሙ አሳሳቢ የደዌ ስጋት/ችግር የለውም። ሆኖም ግን ፤ ከፍተኛ የሆነ የ ስነ ልቦና እና የማህበራዊ ተጽእኖ አለው። የዚህ ቀውስ አስከፊነት ገኖ የሚታየው ፤ በለምጽ ዙሪያ ላይ የተገደበ አመለካከት ያለው ማህበረሰብ መካከል ነው።
በአለማችን ከ1-2 % የሚሆን ወይም 70 ሚሊየን አከባቢ የሚገመት ህዝብ በዚህ ህመም ይጠቃል። ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ላይ የህመሙ መጠን ከፍ ይላል ተብሎ ይታሰባል። በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ፤ በሀገሪቷ የለምጽ ህመም 3% የሚሆነውን የማህበረሰብ ክፍል ያጠቃል። በኢትዮጵያ የለምጽ ህመም ስርጭት ደረጃ የሚያሳይ የሀገር አቀፍ መረጃ ባይኖርም ፤ የቆዳ ህክምና ማእከሎች ከሚታዩ ዋነኛ የቆዳ ህመሞች ውስጥ ይጠቀሳል።
መንስኤው ምንድነው?
የለምጽ ህመምን ዋነኛ መንስኤን ሳይንስ ሙሉ በሙሉ የተረዳው ባይሆንም ፤ የሰውነታችን የበሽታ የመከላከል ህዋሳት የቆዳ ቀለም አመንጪ ህዋሳትን (በልዩ ስማቸው ሜላኖሳይትን) ሲገድሏቸው ህመሙ ይከሰታል። ከዚህም ሌላ የለምጽ ህመም ፦
ዘረመል ጋር ተያያዥነት አለ።። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ከ20-30% የሚሆኑት የለምጽ ህመምተኞች የለምጽ ህመም ያለበት የቤተሰብ አባል አላቸው።
ለሰውነታችን ጠንቅ የሆኑት ከብዙ ህመሞች ጋር ተያያዥነት ያላቸው የ ፍሪ ራዲካልስ (Free Radicals) መብዛት ጋርም ተያያዥነት አለው።
ከዚህም ባሻገር በነርቭ ህዋሳት የሚመረቱ አንዳንድ ኬሚካሎች ከለምጽ ህመም ጋር ቁርኝት እንዳላቸው ተገኝቷል።
እንዲሁም ከዚህ በፊት ጥቃት የደረሰበት ቆዳ (በቆዳ ህመም ሆነ በጉዳት) ላይ ከጊዜ በኋላ በስፍራው ያሉ የቆዳ ቀለም አምራች ህዋሳት ሲሞቱ ለምጽ ያመጣል።
ማህበረሰባዊ፣ የግል፣ የስራ ጫና ህመሙ እንዲባባስ ያደርጋል። በለምጽ የተጎዳው የቆዳ ክፍል እንዲሰፋ ያደርጋል።
ተጋላጭነት ያለው የማህበረስብ ክፍል ማነው?

ለምጽ ህመም ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ሳይለይ ፤ ከህጻን እሰከ አዋቂ የሚያጠቃ ህመም ቢሆንም ፤ ባብዛኛውን ጊዜ ከ 30 አመት እድሜ በፊት ይከሰታል። የህመሙ ተጋላጭነት በሚከተሉት ላይ ይጨምራል ፦
በቤተሰብ የ ለምጽ ህመም ያለባቸው እና
የሰውነታችን የበሽታ የመከላከል ስርአት ችግር ጋር የተያያዘ ህመም (auto immune diseases) ያለባቸው (ለምሳሌ ታይሮይድ ሆርሞን ችግሮች፣ ስኳር ህመም እንዲሁም ሌሎች)
የበሽታው ተጋላጭነት በወንዶች እና በሲቶች መካከል እኩል ቢሆንም ፤ ከወንዶች ይልቅ ሲቶች በሽታውን ሪፖርት ያደጋሉ።
የህክምና አማራጮቹ ምንድናቸው?
የለምጽ ህመም በዘመናዊ ህክምና ዘላቂ መፍትሔ ያለው ባይሆንም ፤ በለምጽ የተጠቃው የቆዳ ክፍል እንዳይስፋፋ የሚያደርጉ ፣ ቀለሙን ወደነበረበት የሚመልሱ የህክምና አማራጮች አሉ። ሆኖም ግን እነኝህ የህክምና አማራጮች ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ተደራሽ አይደሉም።
በዚህም የተነሳ ብዙዎች ወደ ባህላዊ ህክምና አማራጮች ያመራሉ። በለምጽ ዙሪያ ያለው አስተሳሰብ በበኩሉ ከዘመናዊ ይልቅ ባህላዊ አማራጮችን ያበረታታል። አሁን በህክምና ካሉ አማራጮች ውስጥ ጥቂቶቹ፡
የሚቀቡ መድሀኒቶች
በውስጣቸው ኮርቲኮስቴሮይድ የያዙ የቆዳ መድሀኒቶች ፤ የሰውነታችን የበሽታ የመከላከል አቅም ስለሚያለዝቡ ቀድመው ከተጀመሩ የቆዳን ቀለም ሊመለስ ይችላል። ህመሙንም መቆጣጠር ይቻትላል። እንደ ፊት ያሉ አሳሳቢ ቦታዎች ጋር ከሆነ ደግሞ ሌሎች አምራጭ መድሀኒቶችን መጠቀም እንችላለን።
የብርሀን ህክምና
ቀለል ያለ የብርሀን ህክምናዎችን በመጠቀም የቆዳ መልክን መመለስ ይቻላል። የጸሀይ ብርሀን በተፈጥሮ የቀለም አምራች ህዋሳቶች ቀለም አብዝተው እንዲያመርቱ በማድረግ ፤ ቅየቆዳ ቀለማችን ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አለው። ለዚህም ጸሀይ ብዙ ሲመታን መልካችን ይጠቁራል። በተቃራኒው ደግሞ ጸሀይ ለረዥም ጊዜ ካለገኘን እንገረጣለን።
ይህም ህክምና አርተፍሻል የጸሀይ ብርሀንን (UVB) የተጎዳው የቆዳ ክፍል ላይ በማድረግ ፤ የተዳከሙት ቀለም አምራች ህዋሳት እንዲነቃቁ ፤ ቀለም ማምረት እንዲጀምሩ ያደርጋል። ህክምናው የቆዳ ቀለም የመመለስ አቅም ያለው ቢሆንም ፤ በቀላሉ አይገኝም።
የቀዶ ጥገና ህክምና
የለምጽ ህመሙ መስፋፋት ያቆመ ከሆነ እና አነስ ያለቦታን ከሆነ ያጠቃው ፤ በቀዶ ህክምና የተጠቃው ቆዳ በጤነኛ ቆዳ እንዲተካ ማድረግ ይቻላል። እንዲሁም የ ቆዳ ህዋሳቶቹን ንቅለ ተከላም ማድረግ ይቻላል። ነገር ግን ህክምናው በኢትዮጵያ በስፋት የለም።
የመዋቢያ አማራጮች
በሜካፕ በለምጽ የተጠቃውን የሰውነት ክፍል መከለል/ማረም/ ማስተካከል ይቻላል።
የስነልቦና ድጋፍ
በዚህ ህመም ለተጠቁ ሰዎችን ማማከር ፤ እንዲሁም ማህበረሰባዊ ድጋፍ መስጠት አስፈላጊ ነው። እነኝህ ግለሰቦች በማህበረሰብ የተሳሳተ አስተሳስብ የተነሳ ፤ የአእምሮ ጤና እክል ያጋጥማቸዋል። ነገር ግን ባሉ የአእሞሮ ጤና ሐኪም ውስንነት ፤ የ ስነልቦና ድጋፍ ለእነርሱ ተደራሽ ላይሆን ይችላል።
የመገለል ምእራፍ እና የአእምሮ ጠንቁ

የለምጽ ህመምን ባብዛኛውን ጊዜ በተሳሳተ መንገድ እንረዳዋለን። በተለይም በገጠር የሚኖሩ ማህበረሰቦች የለምጽ ህመምን ከእርግማን፣ ከክፉ መናፍስት ወይም ከመለኮታዊ ቅጣት ጋር ያዛምዱታል።
ይህንን አስመልክቶ በመቀሌ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው፡-
48% የሚሆኑት ለምጽን ከሊፕረሲ ህመም ምልክት ጋር ያሳስቱትታል።
28% የሚሆኑት በመንፈሳዊ ችግር የተከሰተ ነው ብለው ያስባሉ።
24% የሚሆኑት በቡዳ የሚመጣ ነው ብለው ያስባሉ።
36% የሚሆኑት በኃጢያት ምክንያት እንደሚመጣ ያምናሉ።
አንድሶስተኛ የሚሆኑት ከኢንፌክሽን ጋር ያያይዙታል።
እራሶትን ለትዳር እያዘጋጀ ያለ አፍላ ወጣት አድርገው ያስቡ እስቲ...
ድንገት ለ ትዳር ያጩት ሰው የለምጽ ህመም ሲያጋጥምዎ ጋብቻውን ቢያፈርስ ምን ይሰማዎታል? እርስዎ ለምጽ ስላለብዎ ቤተሰብዎ በእርስዎ የተነሳ ቢሸማቀቅስ ? የእርሶን ህመም አፍሮበት ለመደበቅ ቢጥርስ?
ይህ መገለል ከባድ የሆነ ተጸእኖ አእምሮ ላይ ይፈጥራል። በራስ መተማመንን ይገድላል። መልካችን ጉድለት/ጉድፈት እንዳለበት እንዲሰማን ያደርጋል። ከዚህም ጫና ለመሸሽ ከማህበረሰባዊ ትስስሮች ራስን ማግለል ይመጣል። ቤተክርስትያንም ለመሄድ የሚፈሩ ጥቂት አይደሉም። ይህንን መገለል ተከትሎ ታድያ የአእምሮ ጤና እክል ይፈጠራል።
አለምአቀፍ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ፤ ከግማሽ በላይ (54.5%) የሚሆኑት የለምጽ ህመምተኞች የጭንቀት ህመም አለባቸው።
ከዚህ ውስጥ ወደ አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ፤ እጅጉን የጠነከረ ጭንቀት ይኖርባቸዋል።
በኢትዮጵያ በለምጽ ዙሪያ የተሰራ ጥናት ባይኖርም ፤ ረዥም ጊዜ የሚቆይ የ ቆዳ ህመም ካለባቸው ሰዎች መሀከል 23.6% የጭንቀት ህመም አለባቸው።
ይህው ጥናት እንደሚያሳየው ፤ የጭንቀት ህመሙ በማህበረሰብ ደረጃ መገለል የሚያደርሱ የቆዳ ህመሞች መሀከል ይበረታል።
የጤና አቅማችንስ ለምጽን ለማከም የቱ ጋር ይገኛል?
በኢትዮጵያ የቆዳ ህክምና ተደራሽነት በጣም የተገደበ ነው። ያሉን የቆዳ ስፔሻሊስት ሀኪሞች በመቶዎች ቢቆጠሩ ነው። ይህ ደግሞ ለሙሉ ኢትዮጵያ ህዝብ በቂ አይደለም። አንድ የቆዳ ሀኪም በሚሊየኖች ለሆኑ ኢትዮጵያውያን ህክምና መስጠት ይኖርበታል ። ከእነኝህ ቆዳ ሀኪምች ውስጥ አብዛኞቹ በከተማዎች ውስጥ ሲገኙ ፤ ከእነርሱም መሀከል ትልቁ ቁጥር ያለው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው። ይህ ደግሞ የገጠሩ ማህበረሰብ ወደ ባህል ህክምና ባለሙያዎች እንዲያዘነብል ይገፋፋዋል።
ለቆዳ ህክምና አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችም በብዛት አይገኙም። ለዚህም የህክምና አማራጮችቱ የተገደቡ ይሆናሉ። ሲገኙም ዋጋቸው ከፍ ያለ ይሆናል።
ግንዛቤ የመፍጠር ግዴታ አለብን

በዚህ ዙሪያ እስከአሁን ያለው ለውጥ መልካም ነው። ጥቂት የማይባለው የማህበረሰብ ክፍል አስተሳሰቡ ተሻሽሏል። በዚህም ዙሪያ ላይ እየሰሩ ያሉ አንዳንድ አካልት አሉ። ለምጽን እንደ ጉድለት ሳይሆን እንደ ልዩነት፣ ውበት እና ጥንካሬ የሚያሳዩ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴዎች ፤ ወደ ኢትዮጵያ መድረኮች መድረስ ጀምረዋል።
ሆኖም ግን ገና ይቀረናል። ከትንሽ እስከ ትልቁ የማህበረሰብ ክፍል ስለ ለምጽ እና መንስኤው አጥርቶ መረዳት ይኖርበታል። የዛኔ ነው መገለል ፈጽሞ ሊቆም የሚችለው። በምእራቡ አለም የውብት መገለጫ አድርገው ለምጽ ያለባቸው ሞዴሎች ሲስፋፉ ፤ እኛ ግን ለምጽ ያለባቸውን የማህበረሰብ ክፍል በ ጎሪጥ እያየን መኖር ማቆም አለብን። ለዚህም ማህበራዊ ሚድያዎች ላይ ሰፋ ያለዘመቻ ያስፈልጋል።
ማሳረጊያ ሀሳብ
የለምጽ ህመም መፍትሔው ከሆስፒታል ደጅ አያልቅም። በማህበረሰብ ውስጥም እገዛ ያስፈልገዋል። የጉድለት/ የጉድፍ ምልክት ሳይሆን የጉራማይሌ ተፈጥሮ አንዱ የሚስብ መልክ ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል።
በእንግዳ ተቀባይነት፣ በባህሉ እና በትውፊቱ ለሚኮራ ማህበረሰብ ይህን ማስተዋል ምኑ ነው?
Comments