ጸጥተኛው መንገድ፡ ከከፍተኛ የደም ግፊት ወደ ኩላሊት ውድቀት
- Zebeaman Tibebu
- Dec 16, 2025
- 2 min read
ይህን ያውቃሉ?
በአለም ዙሪያ ከ 5 ሰዎች ውስጥ አንዱ( 1.4 ቢሊየን ሰዎች) የደም ግፊት በሽታ አለባቸው። ደም ግፊት ካለባቸው አምስት ሰዎች ውስጥ በአማካይ አንዱ (21 %) ስር የስደደ የኩላሊት በሽታ አለበት። ይህ ማለት በአለም ዙሪያ 294 ሚሊየን ሰዎች በደም ግፊት ምክንያት የመጣ የኩላሊት በሽታ አለባቸው።

በኢትዮጵያም መረጃዎች ተመሳሳይ ስርጭት ያሳያሉ። ከ 3 አመት በፊት በተደረገ ጥናት ከ 5 ኢትዮጵያውያን ውስጥ በአማካይ አንዱ (19.6 በመቶ) የ ደም ግፊት አለበት። በኩላሊት በሽታዎች ዙሪያ ሀገር አቀፍ ጥናት ባይኖርም ፤ አንድ አምስተኛ የሚጠጉ የደም ግፊት በሽተኞች (21.7%) ስር የሰደደ የኩላሊት በሽታ (CKD) አለባቸው።
ይህ ቀላል ቁጥር አይደለም!
በኢትዮጵያ ባሉ የጤና ተቋማት ፤ ሰዎች በየጊዜው ከባድ የኩላሊት ጉዳት/በሽታ እንዳለባቸው ፤ በድንገት ይሰማሉ። ይህም ብዙዎችን ያስደነግጣል። እንዴትም ብለው ብዙዎች ይጠይቃሉ?
ምላሹ ቀላል ነው።!
ለዓመታት ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የደም ግፊት ኩላሊትን ይጎዳል።
አሳዛኙ ሁኔታ ደም ግፊትም ኩላሊት በሽታም እንዳለባቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያውቁም አሉ።
ለምን ካሉ ፡
የደም ግፊት ድምጽ የለውም! ምልክቶችም ላይሳይ ይችላል። ቁጥጥር ስር ካልዋለ ልብን ይጎዳል ፤ ኩላሊትን በለሆሳስ ያጠፋል።
የተሟሉ የዲያሊሲስ ተቋማት ውስን በሆኑባት ኢትዮጵያ ደግሞ ፤ ይህ እጅጉን ሊያሳስብ ይገባል። ያሉን የዲያሊሲስ ህክምና አገልግቶቾች በከተሞች ከመገኘታቸው ባሻገር ፤ ሂሳባቸው ከፍ ያለ ነው። ይህም ረዥም ጊዜ የኩላሊት እጥበት ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የህክምና ወጪ ኢኮኖሚን ያቃውሳል።

የደከመ ኩላሊትን ከማከም የኩላሊት በሽታን መከላከሉ ቀላል ነው። ቁልፉ ደግሞ የደም ግፊትን መቆጣጠር ነው።
ደም ግፊት እንዴት ኩላሊት በሽታ ያመጣል?
ይህን ለመረዳት ኩላሊትዎን እንደ ማጥለያ አድርገው ይውሰዷቸው። እነኝህ ጥቃቅን ማጥለያዎች አያርፉም። ደም በየደቂቃው በውስጣቸው ያልፋል። ቆሻሻን ፣ ትርፍ ፈሳሽን እና መርዛማ ኬሚካሎች አስወግደው ፤ አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን (ፕሮቲንን ጨምሮ) ሰውነት ውስጥ ያስቀራሉ።
ታድያ እነኝህ ማጥለያዎች በስርአት እንዲሰሩ የሚያርፍባቸው ግፊት ትክክለኛ መጠን መሆን አለበት።
ግፊቱ ሲበዛስ?

እነኝህ ማጥለያዎች ከፍ ባለ ግፊት ውስጥ በሚሰሩበት ጊዜ ይጎዳሉ። መደበኛ ማጥለያ ግፊት ብናበዛበት እንደሚቀደድ/ እንደሚበጣጠስ ሁሉ ፤ እነኝህ ማጥለያዎች ጠባሳ ያመጣሉ። ስራቸው ይስተጓጎላል። ያስቀሩት የነበረው ፕሮቲን በሽንት በኩል አምልጦ መውጣት ይጀምራል። የፕሮቲኑ አፈንግጦ መውጣት ከኩላሊት ጉዳት የመጀመሪያ ምልክቶች መሀከል ይካተታል።
ኩላሊትን የሚመግቡ የደም ስሮችም ያለውን ከፍተኛ ግፊት ለመቋቋም ግድግዳቸው ይወፍራል።
ይህ የደም ግፊት ለወራት ወይም ለዓመታት ከፍ ያለ ሆኖ ሲቆይ፤ የኩላሊት ስራ እየተዳከመ ይመጣል። የኩላሊት ውድቀት ይመጣል።
ሂደቱ ግን ዝግ ያለ ፤ እንዲሁም ህመም የሌለው ነው። ለዚህም ብዙ ጊዜ ሰዎች የኩላሊት በሽታቸውን የሚያውቁት ጉዳቱ ካየለ በኋላ ፤ የኩላሊት ውድቀት ሲጀምር ነው።
ይህም ያዘናጋል። ብዙዎችም ደም ግፊታቸውን ለመቆጣጠር ይሰንፋሉ። መድሀኒቶቻቸውን በስርአት አይወስዱም። በመደበኛ ሁኔታ ደም ግፊታቸውን አይከታተሉም።
ይህንን ለመከላከል የደም ግፊትዎ ስንት ቢሆን ይመከራል?
ይህ እንደታካሚው ስለሚለያይ ፤ ዶክተርዎን ቢያማክሩት ይመረጣል። ታካሚ እንዳለበት የደም ግፊት ደረጃ ፤ ግቡ ሊለያይ ይቻላል።

አለም አቀፍ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት የደም ግፊት መጠንዎ ከ 140/90 እንዲያንስ ይመከራል። ከተቻለ ከ130/80 ቢሆን እጅጉን ተመራጭ ነው። ሆኖም ግን ዶክተርዎን ያማክሩ።
የደም ግፊት ካለብዎ እነኝህን ምልክቶች ችላ አይበሉ!
እላይ እንደጠቀስነው ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ ቀድሞ ምልክት አያሳይም። እነኝህን ምልክቶች ግን ካዩ ፤ የኩላሊት ጉዳትን አመላካች ማስጠንቀቂያ ምልክቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ ችላ አይበሉ።
የእግር(ቁርጭምጭሚት ጋር) እና አይን አከባቢ ያለ እብጠት
ሽንት ላይ አረፍ መኖር (ሽንት ውስጥ ፕሮቲን መደባለቁን ያመላክታል)
ምንጩ ያልታወቀ ድካም
የሽንት መጠን መቀነስ
የምግብ ፍላጎ መቀነስ
ማቅለሽለሽና ማስታወክ
ምልክቶቹን አይተው በሄዱ ጊዜ እንኳን ፤ ኩላሊት ከባድ ጉዳት አጋጥሞት ሊሆን ይችላል።
ቢሆንም ምልክቶቹን እንዳዩ በአፋጣኝ መሄድዎ ፤ ጉዳቱን ባለበት ለመቆጣጠር ያስችላል።
ምልክቶቹን ከማወቅ በላይ ፤ መደበኛ የኩላሊት ምርመራ ማድረግ ይመከራል። ይህም የኩላሊት ጉዳት ገና ሳይጀምር ለመያዝ ያስቻላል።
ለመከላከል ምን ያድርጉ?
ከፍተኛ የደም ግፊት ካለብዎ / የደም ግፊት ያለበት ሰው የሚንከባከቡ ከሆነ የሚከተሉትን ያድርጉ።

የደም ግፊትዎን በየጊዜው ይለኩ። ምልክቶች አይጠብቁ። አቅራቢያዎ ያለ ፋርማሲ ወይም የጤና ተቋም ሄደው ይመርመሩ።
ዶክተርዎ ያዘዘልዎ መድሃኒቶችን ያለማቋረጥ ይውሰዱ። መድሀኒት መዝለል ኩላሊት ላይ ጉዳት እንዲያጋጥም እድል ይከፍታል።
የሚመገቡትን የጨው መጠንን ይቀንሱ። ጨው የደም ግፊት መጨመር ጋር ከፍተኛ ቁርኝት አለው።
መደበኛ አካላዊ እንቅስቃሴ ያድርጉ።
ጤናማ ክብደትን ይጠብቁ።
መደበኛ የኩላሊት ምርመራ ያድርጉ። ኩላሊትዎ ተዳክሞ እስኪሄዱ አይጠብቁ። እንደ ደም ክሪያቲኒን እና ሽንት ምርመራ ያሉ ቀላል ምርመራዎች ራሲ ጉዳት መኖሩን ሊጠቁሙ ይችላሉ።
ያስተውሉ ፡ መጠነኛ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች እንኳን የደም ግፊትን ቁጥጥርን ያሻሽላሉ።





Comments