የተረሳ ህይወት፡ የመርሳት ህመም በኢትዮጵያ
- Zebeaman Tibebu
- Apr 21
- 4 min read
Updated: Apr 22
ያሳደጉን እናቶቻችን፣ አባቶቻችንና ፣ አያቶቻችን በህይወት እያሉ ሰብአዊ ቁመናቸውን አጥተው ፤ ነገሮችን ሙሉ ዘንግተው ፤ ሁሉን እርግፍ አርገው ትተው ማየት ልብ የሚሰብር ነው።
እስቲ አስቡት ... አንድ የሰው ፊት አይቶ ፣ እላይ ታች ብሎ፣ ገስጾና መክሮ ያሳደገ አባት መስዕዋት የከፈለላቸውን ልጆቹን ሲረሳ ፤ ያቀናው ጎጆ ሲጠፋበት ፤ የሰፈሩ ደራሽ ዋርካ እንዳልነበር ብቻውን እቤት ሲቀር..
ይህ በማህበረሰብ ፍቅር ተቀርጾ ላደገ ኢትዮጵያዊ ለማሰብ የሚከብድ ፤ ግን የሚጋተው እውነታ ነው። በእኛም ባያጋጥምም ፤ በምናቀስ ሰው አይተን ይሆናል። "እሳቸው ሰው መለየት ተስኗቸዋል" ብለን ለልጆቻቸውስ ያዘንንበት ጊዜ የለምን?

እኔ ከጋጠመኝ ላጫውታችሁ... ወደ አስር የሚጠጉ ልጆች ያሳደጉ አባት (አሁን እድሜያቸው 80 ያልፋል) ፤ የደም ግፊት እና የፓርኪንሰን ህመም ነበረባቸው። የህክምና ክትትላቸውን ግን ደካማ የሚባል ነበር። የዛሬ 10 አመት ገደማ ሰውነታችው በከፊል ስለተዳከመ ፤ ሀኪም ቤት ሲሄዱ የስትሮክ ህመም እንዳጋጠማቸው ተነግሯቸው ፤ ለተወሰኑ ቀናት ታክመው ይወጣሉ። በቀጣይ አመታትም ስሞችን መዘንጋት ፣ ጉዳዮችን ማምታታት ፣ እቃ ያስቀመጡበትን ስፍራ ፈጽሞ መዘንጋት ባህሪያትን ያሳዩ ጀመር። ቤተሰብም ሆነ እሳቸው ከእርጅና ጋር አያይዘውት ፤ ደንታ አልሰጡትም ነበር። በጊዜው ጡረታ ላይ ስለነበሩ ፤ በየቀን ተግባራቸው ላይ ያለውን ለውጥ ብዙም አላስተዋሉትም ነበር። ሆኖም ግን ፤ በቀጣይ አመታት ቤተክርስትያን እንደወትሮው ሳይሆን በአላትን እየመረጡ አልፎ አልፎ መሄድ ጀመሩ። በማህበረሰባዊ ኑሮ ላይ የሚታወቀው ተጫዋችነታቸው መደብዘዝ ጀምሮ ፤ ወደ ኋላ ላይ ከልጆቻቸው ጋር የሚኖራቸው ጨዋታ መቀነስ ጀመረ። ልጆቻቸው 'አባዬ ባህሪው ተለውጧል' ብለው ለጎረቤት ያወሩ ነበር። በቀጣይ አመታት ጨዋታውም ቀረ ፣ ቤተክርስትያኑም ቀረ። ሩቅ ሄደው ሲመለሱ ቤታቸው እየጠፋባቸው ስለተቸገሩ ፤ ልጆቻቸው ከቤት እንዳይወጡ ከለከሉዋቸው። የልጆቻቸው መልክ እና ስም ፈጽሞ ይዛባባቸው ነበር። እቤት ያቆዩዋቸው ልጆቻቸው የህመሙን መባስ ሲመለከቱ ፤ ብቻችውን አምኖ ቤት ውስጥ መተው ስለከበዳቸው ፤ ሁልጊዜ አብሮአቸው የሚንከባከባቸው አንድ ሰው እንዲኖር አደረጉ።

ይህ ህመም በህክምናው ዲመንሺያ ይባላል። ዲመንሽያ የመዘንጋት ህመም ብቻ አይደለም። በተለያየ ምክንያት የአንድ ግለሰብ የማስታወስ፣ የማስተዋል ፣ የመገንዘብ፣ የመስራት፣ የመግባባት አቅም እየተመናመነ እንዲመጣ የሚያደርግ ህመም ነው። ብዙ ሰው የሚያውቀው የመርሳት ህመም በሚለው መጠሪያ ነው። ለዚህም በሙሉ ደረጃ ባይገልጸውም ከዚህ በኋላ ላለው ይህንን ስያሜ መጠቀም እንችላለን።
መርሳት ህመም እንደ ስኳር ወይም ኤች አይቪ አንድ በሽታ ብቻ አይደለም። ከላይ የተጠቀሱት የህመም ምልክቶች የወል ስም ነው። በብዙ የበሽታ አይነቶች ሊመጣ ይችላል። ህመሙም የአእምሮአችን ስራ መዳከም ጋር ሲያያዝ ፤ ጭንቅላታችን ውስጥ ያሉት የነርቭ ህዋሳት ሲዳከሙ/ሲሞቱ ሊመጣ ይችላል። የመርሳት ህመም የማስታወስ ችሎታን ብቻ ሳይሆን ነጻነት ፣ ማንነትን ፣ ክብርን እንዲሁም ማህበራዊ መስተጋብሮችን ያሳጣል። ለዚህም የሕይወት ሌባ ነው። ታማሚዎች፣ እራሳቸውን፣ ታሪካቸውን፣ ቤተሰባቸውን ሊረሱ ይችላሉ። በሰው እጅ መጣሉ ራሳችውን ያስተዳድሩ ለነበር አረጋውያን ከባድ ያደርገዋል።
ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት የህመሙ ስርጭቱን እየጨመረ እየመጣ ይገኛል። የዓለም ጤና ድርጅት እንደገለጸው ፤ በፈረንጆቹ 2021ዓ.ም ብቻ በአለም ዙሪያ 57 ሚሊየን የሚቆጠሩ ግለሰቦች መርሳት ህመም ነበረባቸው። ከ እነዚህ ውስጥ 60 በመቶው የመርሳት ችግር ያለባቸው ሰዎች የሚኖሩት በእነኝህ አገራት ውስጥ ነበር። ይህም አሃዝ በ2050 ወደ 71 በመቶ ከፍ ሊል ይችላል ተብሎ ይጠበቃል። አረጋውያንን ለሞት ከሚዳርጉ ህመሞች መካከልም 7ተኛ ደረጃን ይይዛል። ህመሙ እነኝህን እድሜያቸው የገፋ ሰዎችን ከአካል ጉዳተኛ ጎራ ይከታል። የህመሙ ዋነኛ መንስኤ ከሚባሉት ውስጥ ፤ አልዛይመር 70 ፐርሰንቱን ቢይዝም እንደ ፓርኪንሰንስ ፣ የጭንቅላት ጥቃት፣ እንዲሁም የተለያዩ ተጓዳኝ በሽታዎች (ስኳር፣ ደም ግፊት፣ ስትሮክ፣ ወ.ዘ.ተ...) ለህመሙ ያጋልጣሉ።
የመርሳት ህመም መንስኤው ምንድን ነው?

ይህ ህመም በተለያዩ በሽታዎች አማካይነት የሚከሰት ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሚመጣ ነው። ለህመሙ አጋላጭ ተበለው የሚታሰቡ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ።
እድሜ ፡ በዋነኝነት አዛውንቶችን ቢያጠቃም ፤አንዳንዴ ወጣቶችንም ሊይዝ ይችላል።
የደም ግፊት ህመም
የስኳር ህመም
የውፍረት መጨመር (ቢኤምአይ ከ 25 በላይ መሆን)
ማጨስ
አልኮል አብዝቶ መጠጣት
ስንፍና (ስራ ሳይሰሩ አርፎ መቀመጥ)
የብቸኝነት ኑሮ
ጭንቀት
ከ እነኝህም ባሻገር ስኳርን፣ ደምግፊትን እንዲሁም የተለያዩ ህመሞችን ተከትሎ ስትሮክ ካጋጠመ የመርሳት ህመም የማጋጠም እድሉ ይጨምራል።
ታድያ ስርጭቱ በኢትዮጵያ ምን ይመስላል?

ባለፉት አመታት አገራችን ኢትዮጵያም ባሳየችው የጤና እመርታ ፤ እድሜያቸው የገፋ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። እ.ኤ.አ. በ2023 የተባበሩት መንግስታት ባወጣው መረጃ ፤ ከ65 አመት እድሜ በላይ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ወደ 3 ፐርሰንት እንደሚሆኑ ይገመታል።
በመርሳት ህመም ዙሪያ ላይ ያለው መረጃ ውስን ቢሆንም ፤ ያሉት ጥናቶች እስከ 23% የሚሆኑ አዛውንቶችን ሊያጠቃ እንደሚችል ያሳያሉ። በቀጣይ አመታትም ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞች መበራከትን ፤ እንዲሁም የመኪና/ የተፈጥሮ አደጋ መጨመርን ተከትሎ ህመሙ በቀጣይ አመታት እንደሚጨምር ይገመታል። የትክክለኛ አሀዝ አለመኖሩ በራሱ ፣ ለ ህመሙ የሰጠነውን ቦታ አመላካች ነው።
ክስርጭቱ መስፋፋት ባሻገር፣ ይህ ህመም እንክብካቤ የተሟላ አይደለም። ይህም የሆነበት ምክንያት፡
በህመሙ ዙሪያ ላይ ዝቅተኛ ግንዛቤ መኖር፡- የመርሳት በሽታን ብዙ ሰው እንደ እብደት፣ እርጅና አልፎ ተርፎም ከመንፈስ ጋር አያይዞ ይረዳዋል። ይህንንም ተከትሎ እነኝህ ታካሚዎች መገለል ያጋጥማቸዋል።
የምርመራ እጥረት፡- ይህንን ህመም በአፋጣኝ አውቆ ህክምና ለማስጀምር የሚያስፈልጉ የምርመራ ተቋማትም በብዛት የሉም። እንክብካቤ መስጫ ተቋማትን ጉድለትም ይስተዋላል።
ህመሙን ያማከለ ብሄራዊ ፖሊሲ/ስትራቴጂ አለመኖር ፦ የዓለም ጤና ድርጅት ለሁሉም አባል ሀገራት የዲመንሺያ ህመም ዙሪያ ላይ ስትራቴጂ እንዲቀርጹ መምሪያ ቢያስቀምጥም ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ገና አልተተገበረም።
ህመሙ ደግሞ ከታማሚው እኩል በቤተሰብ ላይ ያለው ጫና ከባድ ነው። የሀገር ሽማግሌዎች በሚከበሩበት እና የቤተሰብ ትስስር ትልቅ ቦታ በሚሰጥበት ማህበረሰብ ውስጥ ፣ የሚወዱትን ሰው በህይወት እያለ ማጣት በጣም አሳዛኝ ነው። ብዙዎችም ቤተሰባቸን ላለማጣት በየሀኪምቤቱ ተንከራተዋል፣ በስሜት ዝለዋል፣ ያላቸውን ቅሪት አፍስሰዋል።
ምልክቶቹ
ህመሙ ከመጀመሩ በፊት ታማሚዎች ቀድመው ስሜታቸውን መቆጣጠር ሊያቅታቸው ፣ ባህሪያቸው ሊለውጥ እና በነገሮች ላይ ያላቸው ተነሳሽነት ሊዳከም ይችላል። አዘውትረው ሊጨነቁ ፣ ሊናደዱ ፣ ሊበሳጩ ይችላሉ። ምልክቶቹ ከ ጊዜ ወደጊዜ እየተባባሱ ይመጣሉ። ህመሙ ሲጀምራቸው አከባቢ ነገሮችን/ እቃዎችን ይረሳሉ። ቅድም ያወሩትን ደግምው ሊያነሱ ይችላሉ። እያወሩ ቃላት ሊጠፉባቸውይችላል። የለመዱትን መደበኛ ንግግር መከታተል ያዳግታቸዋል። ቦታን መለየት ግራ ሊያጋባቸው ይችላል። የተለመዱ ተግባራትን ማከናወን ይችገራሉ።
ሲባባስ የሚወዱትን ሰው እንኳን ፈጽሞ መለየት ሊያቅታቸው ይችላል። ከዚህም ባሻገር የመናገር ችሎታቸውን ሊያጡ፣ እራሳቸውን መንከባከብ ሊያቅታቸው ይችላል። የዚህን ጊዜ ቀን ከሌት እንክብካቤ የሚያደርግላቸው አካል ያስፈልጋል።
የመርሳት ችግርን መቆጣጠር፡ ምን ማድረግ ይቻላል?
በአሁኑ ጊዜ ህመሙን ሙሉ በሙሉ መፈወስ የሚያስችል መድሐኒት የለም። ሆኖም ግን የአንጎልን አሰራር የሚያግዙ፣ ተጓዳኝ ለውጦችን የሚያርሙ የተለያዩ መድሀኒቶች በባለሙያዎች ይታዘዛሉ። ህመሙን ግን በውጤታማነት መከላከል እንደሚቻል የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ። የመርሳት ህመም እንዳያጋጥምዎት ከፈለጉ ፡
ጤናማና የተመጣጥነ ምግብ ይመገቡ ።
አካላዊ እንቅስቃሴ ያዘውትሩ ።
አልኮል እና ሲጋራ ፈጽመው ያቁሙ ።
መደበኛ የጤና ምርመራ ያድርጉ ።
ደም ግፊት እና ስኳር ካለብዎት በስርአት መድሐኒቱን ይውሰዱ ህመሙን ይቆጣጠሩ።
የሰውነትዎን ውፍረት እንዲሁም የኮሌስትሮል መጠንዎን ይቆጣጠሩ ።
የሚያዝናናዎት/ የሜወዱትን ነገር አብዝተው ይፈጽሙ (ይዝናኑ/ደስተኛ ሁኑ) ።
የጭንቅላት ስራ ያዘውትሩ ፣ አዲስ ቋንቋን ይማሩ ።

ህመሙ ያለበት የቤተሰብ አባል ካለዎት ፤ ህመሙን አሳፋሪ አድርገን ከመደበቅ ይቆጠቡ ፤ ወቅታዊ እንክብካቤ እና ድጋፍ በማድረግ የህመሙን መባባስ ይቀንሱ። በርህራሄ እና በፍቅር ተሞልተን ፤ ሰብአዊ ክብራቸውን ጠብቀን የምናደርግላቸው እንክብካቤ ፤ የህመሙን ፍጥነት ከመቀነስ አልፎ የተሻለ ህይወት እንዲኖራቸው ያደርጋል።
አሁን እርምጃ መውሰድ አለብን
የመርሳት በሽታ የጤና ችግር ብቻ አይደለም - የሰብአዊ መብት ጉዳይም ነው። በአንድ ወቅት ተንከባክበው ያሳደጉን ቤተሰቦቻችንን ቤት ዘግተን፣ ህመማቸውን በዝምታ መዘንጋት የለብንም።
በዚህም ዙሪያ ላይ ግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻዎች ማድረግ ይኖርብናል። ባለድርሻ አካላትም ለህመሙ አጽንኦት መስጠት አለባቸው። የመርሳት ህመም ስትራተጂ እንደሀገር መንደፍ ይኖርብናል።
ባለድርሻ አካላት በ ዓለም ጤና ድርጅት ምክር መሰረት ስትራቴጂ መቅረጽ ይኖርባቸዋል።
እንክብካቤ ሰጪዎችንም በሚያስፈልገው እንክብካቤ ዙሪያ ግንዛቤ ማስጨበጥ እና ማሰልጠን አለብን።
እናስተውል
ይህንን ህመም ችላ ማለት ትናንትናችንን መርሳት ፤ አዛውንቶችን መተው ነው!
አሁን እየደበዘዘ ያለው ትዝታ፣ ታሪክ፣ ፍቅር በአንድ ወቅት ቤት ያበራ ነው። ለዚህም የሚረሱትን እናስታውስ፤ አለኝታ እንሁናቸው !
Comments