የቀሲል 5 ጥቅሞች እና አስፈላጊ ጥንቃቄዎች
በየመንገዱ፣ በፈገግታ የታጀቡ የሃረር ቆንጆዎችን ወይም የድሬዳዋ ውቦችን ሲያዩ ፊታቸው ላይ ቀለል ያለ አረንጓዴ ቀለም አስተውለው ያውቃሉ?

አንዳንዶችማ የነገሩ ፍቅር እጅግ ገብቷቸው፣ ቀሲሉ ፊታቸው ላይ አሻራውን ጥሎ እስኪቀር ድረስ አዘውትረው ሲቀቡት እንመለከታለን።
ለመሆኑ ይህ በምስራቅ አፍሪካ በተለይም በሶማሌ ማህበረሰብ ዘንድ ለዘመናት የውበት መጠበቂያ ሆኖ የኖረው፤ ዛሬ ደግሞ ከጅጅጋ እስከ አዲስ አበባ ባሉ ወጣቶች ዘንድ በስፋት እየተለመደ የመጣው “አረንጓዴው ዱቄት” — ቀሲል ምንድነው?
ብዙዎቻችን ቀሲልን ዝም ብሎ ተራ ባህላዊ የፊት ማስዋቢያ አድርገን ልናስበው እንችላለን። “ሳይንስ ምን ያውቀውና!” ብለው ካሰቡ ግን ተሳስተዋል። ምክንያቱም ዛሬ ይሄ ድንቅ የተፈጥሮ ዱቄት የዓለም አቀፍ የውበት ኢንደስትሪን ቀልብ መሳብ ጀምሯል። ታዲያ ለትውልድ የዘለቀው ይሄ የዘልማድ እውነት፤ በሳይንሱ መነጽር ሲታይ ምን ይመስላል? ተረት ነው ወይስ እውነተኛ የቆዳ ፈውስ?
🌿 ለመሆኑ ቀሲል ምንድነው?

መጀመሪያ ስለ ቀሲል ምንነት እንወቅ። እውነተኛው ቀሲል የሚዘጋጀው “ጎብ” (Gob Tree) ተብሎ ከሚጠራውና በሳይንሳዊ ስሙ Ziziphus mauritiana ከሚባለው የእፅዋት ዝርያ ላይ የሚገኝ ቅጠል ደርቆና ተፈጭቶ ነው። ሆኖም እዚህ ላይ ሳይንሳዊ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
ብዙ የበይነመረብ ምንጮች ቀሲልን “የክርስቶስ እሾህ” (Ziziphus spina-christi) ከተባለው ዝርያ ጋር ያቀላቅሉታል። ነገር ግን በባህላዊ የውበት ልማድ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውለው እውነተኛው ቀሲል የሚመረተውየጎብ ዛፍ ከሚሰኘው(Ziziphus mauritiana) ከተባለው ተክል ነው። ሁሉቱም ዝርያቸው አንድ ቢሆንም (Ziziphus)፤ የተለያየ ባዮሎጂካዊ ባህሪ ያላቸው አላቸው። ስለዚህ ይህ ጽሑፍ የሚያተኩረው በቀጥታ በ ጎብ ዛፍ (Ziziphus mauritiana) ቅጠል ላይ በተደረጉ ሳይንሳዊ ምርምሮች ላይ ብቻ ነው።🫧 5 በሳይንስ የተረጋገጡ ጥቅሞች
ታዲያ ይህ በረሃማ በሆኑት የአገራችን ክፍሎች የሚበቅለው የጎብ ዛፍ ቅጠል፣ ለቆዳችን እንዲህ ፍፁም ፈውስ ሊሆን የቻለው ለምንድነው? መልሱ በቅጠሉ ውስጥ በተደበቁት ተፈጥሯዊ የባዮኬሚስትሪ ውህዶች ውስጥ ይገኛል!

ሳይንስ ስለ ቀሲል (Ziziphus mauritiana) የሚነግረንን 5 አስገራሚ እውነታዎች አንድ በአንድ እንያቸው፡-
1. ሙሉ በሙሉ ተፈጥሯዊ የሆነ የፊት ማጽጃ (Soap-Free Cleanser)
ቀሲልን ከውሃ ጋር ቀላቅለው ፊትዎን ሲታጠቡ ትንሽ እንደ ሳሙና ለስላሳ አረፋ የመፍጠር ባህሪ ያስተውላሉ።
ይህ ለምን ሆነ?
የኬሚስትሪ ሳይንስ ግልጽ ምላሽ አለው። የጎብ ቅጠል በውስጡ ሳፖኒን (Saponins) የተባሉ ተፈጥሯዊ ማጽጃዎችን በከፍተኛ መጠን ይዟል። በፋብሪካ የሚመረቱት ኬሚካል የበዛባቸው ሳሙናዎች የቆዳችንን የተፈጥሮ ዘይት (Lipid barrier) አጥበው በማድረቅ ለብጉርና ለድርቀት ሲያጋልጡ ፤ ቀሲል ግን ቆዳን ሳያደርቅ ቆሻሻንና ከመጠን በላይ የሆነ ቅባቶችን በጥልቀት ፈልፍሎ ያወጣል።
አዎ እንደሳሙና ብቻ በመጠቀም ጥቅሙን ማግኘት ይችላሉ!
2. ጠንካራ የፀረ-ኦክሲዳንት (Antioxidant) አቅም

አንዳንድ የሀረር እና የድሬዳዋ ሴቶች ዕድሜያቸው ቢገፋም ቆዳቸው ተፈጥሯዊ ጤንነቱንና ልስላሴውን ጠብቆ የመቆየቱ ምስጢር ከቀሲል የተፈጥሮ ይዘት ጋር የተያያዘ ነው።
ሳይንሳዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የቀሲል ቅጠል በፖሊፌኖልስ (Polyphenols) እና ፍላቮኖይድስ (Flavonoids) የበለፀገ ነው። እነዚህ ኃይለኛ አንቲኦክሲዳንቶች ቆዳችን በሞገዳማ የፀሐይ ጨረር (UV) እና በአየር ብክለት ምክንያት በፍጥነት እንዳያረጅ፣ እንዳይጨማደድና ሕዋሳቶች እንዳይጎዱ ያግዛሉ። ለዚህም ቆዳ ልስላሴውን ጠብቆ እንዲቆይ፤ እንዳይሸበሸብ ይረዳሉ።
3. የበሽታ አምጪ ሕዋሳት ጠላት (Antimicrobial)

ፊት ላይ ለሚወጡ አላስፈላጊ እብጠቶችና ለብጉር መባባስ ዋናው ምክንያት በተዘጉ የቆዳ ቀዳዳዎች ላይ በብዛት የሚያድግና የሚባዛ ባክቴሪያ ነው። በቤተ-ሙከራ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት፤ የጎብ ቅጠል ጭማቂ (extract) እነዚህን ባክቴሪያዎች የማጥፋት ከፍተኛ አቅም አለው። ይህ ግኝት ቀሲልን አዘውትረው የሚቀቡ ሴቶች ላይ የሚስተዋለውን የቆዳ ጥራትና የብጉር መቀነስ ተፈጥሯዊ ምክንያት በግልጽ ያሳየናል።
ነገር ግን እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን አንድ ትልቅ ሳይንሳዊ እውነት አለ፤ ይህ አስደናቂ የተባይ ማጥፋት አቅም የተረጋገጠው በቤተ-ሙከራ ደረጃ ብቻ ነው። በሳይንሱ ዓለም በቀሲል ላይ በሰዎች ቆዳ ላይ የተደረጉ ቀጥተኛ ክሊኒካዊ ጥናቶች አሁንም ውስን ናቸው።4. የቆዳ መቆጣትንና እብጠትን የማስታገስ ባህሪ (Anti-inflammatory)

በተለያዩ የቅድመ-ክሊኒካዊ (Pre-clinical) ጥናቶች መረዳት እንደተቻለው፤ በቅጠሉ ውስጥ የሚገኙት ንቁ ንጥረ ነገሮች የቆዳን መቆጣት (inflammation) የመቀነስ ከፍተኛ አቅም አላቸው። ቆዳ በተለያዩ ውጫዊ ምክንያቶች፤ በንፋስ ወይም በፀሐይ ሲቆጣ፣ ሲቀላ ወይም ሲሻክር ቀሲልን እንደ ማስክ መጠቀም ቆዳው በፍጥነት እንዲያገግም እና በተፈጥሮ እራስን የማደስ ሂደቱን (Healing process) እንዲያፋጥን ያደርገዋል።
5. ለራስ ቅልና ለፀጉር ጤንነት ሁለገብ ጠቀሜታ

በምስራቅ ኢትዮጵያ ባህል ውስጥ እናቶቻችን ቀሲልን ለፊት ብቻ አይጠቀሙትም። እንደ ተፈጥሯዊ ሻምፑ እና የፀጉር ማስክም ያገለግላል። በውስጡ ያሉት ሳፖኒኖች (Saponins) የራስ ቅልን ሳያሻክሩ በጥልቀት ያጸዳሉ፤ የፎረፎር መፈጠርን ይከላከላሉ። እንዲሁም በውስጡ ያሉት ንጥረ ነገሮች ፀጉር ተፈጥሯዊ አንጸባራቂነቱን፣ ርዝመቱንና ልስላሴውን ይዞ እንዲቆይ ያደርጋሉ።
በአጭሩ፤ እናቶቻችንና እህቶቻችን “ቀሲል ለፊት ጥሩ ነው” ብለው ለዘመናት ሲጠቀሙበት የኖሩት ልማድ፣ ዛሬ በቤተ-ሙከራ በሳይንቲስቶች ተረጋግጧል። ቀሲል ተራ የዘልማድ ወሬ ሳይሆን፣ ተፈጥሮ ያበረከተችልን እውነተኛ የውበት ስጦታ ነው!
⚠️ 4 ልንገነዘባቸው የሚገቡ ወሳኝ ጥንቃቄዎች

እስካሁን ስለ ቀሲል አስደናቂ የተፈጥሮ ጥቅሞች አየን። ነገር ግን እዚህ ጋ ቆም ብለን ማሰብ ያለብን አንድ ትልቅ እውነት አለ። ብዙዎቻችን “ተፈጥሯዊ የሆነ ነገር ሁሉ ሙሉ በሙሉ ምንም ጉዳት የለውም” ብለን እናምናለን። ይሁን እንጂ ሳይንስ የሚነግረን ሌላ ነው። ቀሲል ምንም እንኳን የእጽዋት ዱቄት ቢሆንም፤ ልክ እንደማንኛውም ሕክምናዊ ጠቀሜታ እንዳለው ነገር ሳይንሳዊ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል።
በተለይ በሀገራችን በየድህረ ገጹ የሚወጡ ማስታወቂያዎችን አይተን ዘለን ከመግባታችን በፊት፤ ልንገነዘባቸው የሚገቡ 4 ወሳኝ ጥንቃቄዎች እነዚህ ናቸው፡-
1. ተፈጥሯዊ ንጥረ ነገሮችም አለርጂ ሊያመጡ ይችላሉ
ዕፅዋት በውስጣቸው እጅግ ውስብስብ የሆኑ የኬሚካል ውህዶችን አጣምረው ይዘዋል። የህክምና ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፤ ቀሲል በአንዳንድ ስስ ቆዳ ባላቸው ሰዎች ላይ ድንገተኛ የቆዳ መቆጣት፣ ማሳከክ እና አለርጂ (Contact Dermatitis) ሊቀሰቅስ ይችላል። የሰዎች የቆዳ አይነትና ስሜታዊነት ስለሚለያይ፣ ቀሲልን በሙሉ ፊትዎ ላይ ከመቀባትዎ በፊት ሁልጊዜም እጅዎ ወይም መንጋጋዎ ስር በትንሹ በመቀባት ለቀሲል አለርጂ እንዳለብዎ ማወቅ ግድ ይላል።

2. የባህላዊ ምርቶች ንጽህና እና የጥራት ቁጥጥር ማነስ
መርካቶም ይሁን በየአጥቢያችን ያሉ ባህላዊ ገበያዎች ውስጥ የሚሸጡ የዕፅዋት ዱቄቶች ትልቁ ፈተና ደረጃውን የጠበቀ የጥራት ቁጥጥር አለመኖሩ ነው። የሚገዙት አረንጓዴ ዱቄት 100% ንጹህ የቀሲል ቅጠል ላይሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ትርፍ ለማግኘት ሲባል በሌሎች ርካሽ ቅጠሎች የመቀላቀል ወይም በዝግጅት ወቅት ፤ በሌላ ቅጥል/ንጥረ ነገር የመበከል ዕድሉ ሰፊ ነው። ስለዚህ ሁልጊዜም ከታመነ እና ንጽህናውን ከሚጠብቅ ምንጭ መግዛት ይመረጣል።
3. ክፍት ቁስል ላይ በጭራሽ አትቀቡት
በባህል ደረጃ “ቁስል ያድናል” ተብሎ ቢነገርለትም፣ በቤት ውስጥ ወይም በባህል የሚፈጨው የቀሲል ዱቄት፤ ስቴራላይዝ አልተደረገም። በመሆኑም ቀሲል መቀባት፤ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል። ለተጨማሪ የባክቴሪያ ኢንፌክሽን፤ ለ ቁስል መባባስ ሊያጋልጥ ይችላል። ለዚህም ጠባሳ እንዳይፈጥር ክፍት ቁስል ላይ ከመቀባት ይቆጠቡ።
4. ቀሲል የቆዳ ሐኪም ምርመራን ሊተካ አይችልም

ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የቆዳ ችግር ስር የሰደደ ኃይለኛ ብጉር ወይም ከባድ የፀጉር መርገፍ ካጋጠመዎት መንስኤው የሆርሞን መዛባት፣ የአመጋገብ ችግር ወይም ሌላ የውስጥ ደዌ ሊሆን ይችላል። ይህንን ችግር በባህላዊ መንገድ በቀሲል ብቻ ለማከም መሞከር ትክክለኛውን የህክምና ምርመራ ሊያዘገይ እና ጉዳቱን ሊያባብሰው ይችላል። ከተፈጥሮ እንክብካቤ ጎን ለጎን የቆዳ ሀኪም ማማከር ብልህነት ነው።
ያስተውሉ!
ቀሲል በውስጡ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን የያዘ የተፈጥሮ ስጦታ ነው። ነገር ግን ሁሉንም የቆዳ ችግሮች በአንድ ጊዜ የሚፈውስ ተአምር አይደለም።
ቀሲልን እንደ ጥሩ የተፈጥሮ የቆዳ እንክብካቤ (Skincare routine) እንጂ እንደ ህክምና መድኃኒት መወሰድ የለበትም።




Cool