በአልን ተከትሎ የሚመጣ የጨጓራ ህመም
- Zebeaman Tibebu
- Apr 19
- 4 min read
ባለታሪኩ ታሪኩ
ባለፉት አንድ አመት በቢሮ ህይወት የተጠመደው ታሪኩ ፤ የስፖርት ፍቅሩ መልሶ አገረሸበት። በፊት እኮ ቀልጣፋ ጠንካራ እስፖርተኛ ነበር። የዛኔ ስፖርት አዘውትሮ ይሰራ ነበር። አሁን የኑሮ ጉዳይ ሆነና ፤ ቀኑን የሚያሳልፈው በቢሮው ተቆልፎ ነው። ስብሰባዎችን እየተካፈለ ካልሆነ ፤ ከኮምፒዩተሩ ላይ ተጥዶ ሲሰራ ይውላል። ከቢሮ ወንበሩ የሚነሳው ወይ ለስብሰባ ወይ ለምግብ ነው። ይህንንም ተከትሎ ሰውነቱ መግዘፍ መጀመሩ፤ ከማሳሰብ አልፎ ቁጭት ስላስገባው ፤ በዚህኛው እሁድ እንደድሮው እስፖርት ሊሰራ ቆረጠ።
እሁድም ሲደርስ በጠዋት ከወፎች ቀድሞ ተነሳ። ተነስቶም ፤ አቧራ ያነተበውን የተረሳ የ ጂም ቦርሳውን ከፍቶ ፤ የመሮጫ ጫማውን እና የስፖርት ልብሱን አጠለቀ። እንዳቀደውም ፤ እልኸኛው ታሪኩ በፊት በነበረው የስፖርት ቁመና ተማምኖ ፤ ተነስቶ ተፈተለክ። አላሟሟቀም ፤ አላሳሰበም... እልህ ብቻ... ህመም ሲሰማዋም አላቆመም.. ሊያቆምም አልፈለገም... ጭድ እንዳየ ኮርማ ገሰገሰ። ገስግሶም ሩቅ አልደረሰም ። ሰውነቱ በዚህ ፍጥነት መስራት ስላልመደ ፤ አዙሮት ወደቀ። በሰመመን ውስጥ ሆኖ ሰዎችን ሲንጫጩ ፤ ከዚያም መኪና ውስጥ ሲገባ ይሰማው ነበር።
ለሱ አፍታ ከመሰለው ከሰመመን ሲነቃ ፤ ራሱን ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ተኝቶ አገኘው።

ይህ ትርክት የታሪኩ ብቻ ሳይሆን የአብዛኞቻችን ነው። በአል በደረሰ ጊዜ ስፖርት የምናሰራው ጨጓራችን እጣፈንታ ይህ ነው። እረፍትና ቀለል ያለ ምግብ ለወራት የለመደ ጨጓራችን ፤ በበአል ፌሽታ ተነሳስቶ ስራ ሲበዛበት ፤ ህመም መውደቁ የሚጠበቅ ነገር ነው።
ከጾም በኋላ ስለሚገባ አመጋገብ ከዚህ በፊት የተወያየን ቢሆንም ፤ ዛሬ ስለጨጓራ ሀመም ለይተን እናወጋለን። ከአመጋገብ ጉድለት ጋር ተያይዞ የሚመጣ የጨጓራ ህመም በቀላሉ መከላከል የምንችለው ፤ ሆኖም ግን ብዙዎች በበአል ወቅት የሚያስቸግር ህመም ነው።
በየቤታችን እሰየው በአል ደረሰ ብለን ፤ ተሰባስበን ፤ አቅማችን የፈቀደውን በቅቤ፣ በዘይት፣ በቅመማት አጣፍጠን በፌሽታ መመገብ የተለመደ ነው።
በ ሆስፒታል ደግሞ ፤ ከቀትር በኋላ እስከቀጣይ ቀናት የጨጓራ ህመም ታካሚዎችን ማስተናገድ ፤ በጤና ባለሙያዎች እጅጉን የተለመደ ክስተት ነው። አንድ ታካሚ እያቃጠለው ሆዱን ይዞ ሲመጣ ፤ ሌላኛው ትውከት (አንዳንዴ ደም የቀላቀለ) አስቸግሮት ይመጣል። በበዓላት ስሞንም እንዲህ አይነት ምልክት ያላቸው ታካሚዎችን የድንገትኛ ክፍል በብዛት ያስተናግዳል። አንዱ ከሌላው እየተከታተለ ይጎርፋል። መሀል ለሊትም የሚመጣ ታካሚ ጥቂት አይደለም።
📊 ከህመሙ ጀርባ ያሉት ቁጥሮች

ከአንጀት እና ጨጓራ የህክምና ክፍል ከሚስተናገዱ ህመሞች ውስጥ ፤ የጨጓራ ሀመም ምልክቶች እጅግ የተለመዱና ዋነኛ ናቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የችግሩን መጠን እና ስፋት ያሉት ሙሉ በሙሉ ባይገልጹም ፤ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ከሆነ፦
በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የ ጨጓራ አንጀት ክፍል ውስጥ ከሚታዩ 5 ታካሚዎች መሀል በአማካይ አንዱ (21.6%) የምግብ አለመፈጨት ችግር (ዲስፔፕዢያ) አለበት። ለዚህም በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱት አጋላጭ ህመሞች የጨጓራ መቆጣት (ጋስትራይተስ) እና የጨጓራ/አንጀት ቁስለት (ፒዩዲ)ናቸው።
በደሴ ሪፈራል ሆስፒታል የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ደግሞ ፤ የምግብ አለመፈጨት ችግር ካለባቸው ታካሚዎች ወደ ግማሽ የሚጠጉት የተሟላ ምርመራ አያደርጉም።
ከኢትዮጵያ ህዝብ መሀከል ከፊሉ የሚሆነው (52.2%) የጨጓራ ባክቴሪያ ኢንፌክሽን ይኖርበታል ተብሎ ይታሰባል። የምግብ አለመፈጨት ችግር ከሚያሳዩ ታካሚዎች መካከል ደግሞ ፤ ወደ 80% የሚጠጉት ላይ ይህ ባክቴሪያ ይገኛል።
በምእራቡ አለም ሀገራት በበዓላት ጊዜ የሚያጋጥመው የ ጨጓራ ህመም አብዛኛው ከጭንቀት (holiday stress) ጋር ተያይዞ ቢሆንም ፤ በኢትዮጵያ ግን ከአመጋገብ ጋር የተያያዙ ምክንያቶች እንደሆኑ ይጠቀሳል። ጾምን ተከትለው ባሉ ትላልቅ በዓላትን ላይ አብዝቶ ከመብላት ፤ እንዲሁም የጨጓራ ህመም ቀስቃሽ ምግቦችን ከመመገብ ጋር ይያዛሉ። በዚህም የተነሳ ከወትሮው በበለጠ መልኩ ፤ የጨጓራ ህመም ታካሚዎች ወደ ጤና ተቋም ይመጣሉ።
🍖 በሽታ ቀስቃሹ አመጋገብ፡ የበአል እና የጨጓራ ቁርኝት
🥘 1. ከጾም በኋላ ያለ ድንገተኛ የአመጋገብ ለውጥ (ጭዱ)

ከዚህ በፊት ከጾም በኋላ ስለሚገባ አመጋገብ እንደገለጽነው ፤ ጾም ሲፈታ የሚኖር ድንገተኛ የአመጋገብ ለውጥ ፤ የምግብ ቱቦ ጋር የሚያያዙ ህመሞችን ያባብሳል። ከአመት እረፍት በኋላ ለመፈትለክ እንዳቃተው ታሪኩ ፤ ከረዥም ጾም በኋላ አብዝተን ከባድ ምግብ ስንመገብ ፤ ጨጓራችን የምግብ አለመፈጨት ችግር ያጋጥመዋል።
የጨጓራ ህመምን የሚያባብሱ ምግቦች የምንላቸው
ከፍተኛ ቅባት ያላቸው ምግቦች
ኮምጣጣነት ያላቸው ምግቦች
ቅመም የበዛበት ምግቦች (ጨጓራ ህመም ተንኳሽ) ናቸው።
እነኝህ ምግቦች ጨጓራችን ላይ ስራ ያበዛሉ፣ አሲድ እንዲመረት ያደርጋሉ፣ ወይንም ጨጓራን ያስቆጣሉ። በዚህም የተነሳ ለጨጓራ ህመም ያጋልጣሉ ወይንም ያባብሳሉ።
🥂 2. በአልን ተከትሎ ያለ የአልኮል መጠጥ እና የመድሀኒት ማስታገሻዎች (ክርቢቱ)

ምግብ እንዲያባላ ፤ ጨዋታ እንዲያስኬድ እንደ ጠጅ፣ ጠላ፣ አረቄ ፣ አልያም ቢራ ያሉ ባህላዊ ወይም ዘመናዊ መጠጦች በበአል ወቅት መጠቀም የተለመደ ነው።
ጨጓራችን በተፈጥሮው የሚያመርተው አሲድ እንዳይጎዳው ፤ መከለያ እንደ ነጠላ ያለ ልባስ አለው። አልኮል ደግሞ በባህሪው ይህንን ነጠላ በማቃጠል ፤ እንዲሳሳ በማድረግ ፤ የጨጓራችን ስጋ ለአሲዱ እንዲጋለጥ ያደርገዋል። በተጨማሪም አሲዱ በብዛት እንዲመረት ስለሚያደርግ ፤ የጨጓራ ህመምን በማባባስ እጥፍ ድርብ ሚና አለው።
ለሚሰሙን ህመሞች ሆነ (እራስ ምታትን ጨምሮ) ከአልኮል ጋር ተያይዘው ለሚመጡ የሀንጎቨር ምልክቶች ፤ የምንወስዳቸው ህመም ማስታገሻዎች (እንደ ዳይክሎፌናክ አይቡፕሮፌን አይነት) የጨጓራ መከላከያ የሆነውን ልባስ ይብሱኑ ያሳሳሉ። ይህ ግን በአንድ ጀምበር የሚፈጠር አይደለም።
ጨጓራ ላለበት ሰው ቀርቶ ለጤነኛ ሰው ፤ ጨጓራ ለመፍጨት የሚከብደውን ምግብ (ጭዱን) ከተመገበ ፤ እሱን ለመፍጨት የሚመነጨው አሲድ መከላከያ ልባስ በ አልኮል ሆነ በመድሀኒት ከሳሳ ፤ የጨጓራ ስጋ በቀላሉ በአሲዱ ይቃጠላል። የዛን ጊዜ ጨጓራ ህመም (ጋስትራይተስ) ያጋጥማል።
🕐 3. የተመሰቃቀለ አመጋገብ (ለኳሹ አካል)

የበዓል ጊዜ አመጋገብ እጅጉን ቅጥ ያጣ ነው። አንዳንዱ ቁርስ ብዙም ሳይበላ ይውልና ፤ ምሳ ላይ ለመፍጨት የሚያዳግቱ (ቅባት እና ቅመም የበዛባቸውን) ምግቦች አብዝቶ ይመገባል። ሌላው ምሳን ከተመገበ በኋላ ፤ ጨዋታውን በአልኮል እያጣጣመ ያመሻሽና ፤ ማታ እጅጉን አረፋፍዶ ተመግቦ ፤ ወደ መኝታው ያመራል።
ይህ ግለሰብ እስከአሁን በጨጓራ ካልታመም እንኳን ፤ ለጨጉራ ህምም የሚያጋልጠው የመጨረሻው የቀመሩ አካል ነው። ስንተኛ በተፈጥሮ የምግብ አፈጫጨት ስርአታችን ስለሚቀዘቅዝ ፤ ምግብ ሳይፈጭ ብዙ ሰአት ይቆያል። ብዙ የተሸከመው ጨጓራችን ፤ በአሲድ የላመውን ፣ በአልኮል የታሸውን ምግብ ፤ ሽቅብ ወደላይ ይተፋል። የዚህን ጊዜ ደረታችንን ያቃጠለናል የጨጓራ አሲድ ማገርሸት ህመም ምልክቶችን እናሳያለን። ሊያስታውክም ይችላል።
ታድያ የኢትዮጵያን ሁኔታ ምን ለየው?
እንድ ማህበረሰብ አጹጿማችን የተለየ ባህሪ አለው። እርም ብለን ቅባት ካለው ምግብ ስለምንርቅ ፤ ጨጓሯችን ቢሮ እንደተቀመጠው ታሪኩ ፤ እንኳን ተፈትልኮ መሮጥ ቀርቶ ፤ሶምሶማ ሩጫም እንኳን አይችልም።
የ ጨጓራ ባክቴሪያ ኢንፌክሽን መጠን በኢትዮጵያ ከፍተኛ ስለሆነ ፤ ለጨጓራ ህመም ተጋላጭነት አለን።
ባብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል የህክምና ክትትል እምብዛም ስለሌለው ፤ ብሶበት ሆስፒታል ከመምጣቱ በፊት የጨጓራ ህመም ይኑርበት/አይኑርበት አያውቅም።
👩🏽⚕️ምን ማድረግ እንችላለን?
✅በበአል ጊዜ ሊኖሮት ስለሚገባ አመጋገብ ያንብቡ/ ይወቁ። አመጋገቦትን ያስተካክሉ። በዚህ ዙሪያ የበፊት ፖስታችንን እዚህ ያንብቡ። ከጾምን በኋላ ምን እንመገብ?
✅የህመም ምልክት ካለብዎ ፤ ፋርማሲ ሄደው መድሀኒት ከመውስድ ይልቅ፤ ሀኪም ቤት ሄደው የተሟላ ህክምና ያድርጉ።
✅የህምም ማስታገሻ ሲወስዱ ፤ ለጨጓራ ህመም የማያጋልጡትን መውሰድ ይኖርብዎታል። ለዚህም የጤና ባለሙያ ያማክሩ።
✅የጨጓራ ህመም ካለብዎት
መድሀኒትዎን ሳያቋርጡ በስርአት ይውሰዱ።
ቅባት ያለው ምግብ አዝውትረው/አብዝተው አይውሰዱ።።
ቅመም የበዛበት ምግብ ያስወግዱ።
ቡናን አይጠጡ።
አልኮል ያስወግዱ።
ጭንቀት ይቀንሱ።
መደምደምያ ሐሳብ
በዓላት ሆኑ አከባበራቸው የማንነታችን መገለጫ የአብሮነታችን መታውቂያ መልካም ባህሎቻችን ቢሆኑም ፤ በበዓላት ጊዜ ያለንን አመጋገብ እንጠንቀቅ።
በበአል ወቅት በመጠኑ እንመገብ፣ ቅባት አናብዛ፣ አልክል እንጠንቀቅ።
ያስትውሉ ጦሱ ሀኪም ቤት ታክሞ ከመመለስ አልፎ የከፋ ደረጃ ሊያደርስ ይችላል።
ስለዚህም በበአል ጊዜ የሚኖርዎት አመጋገብ በጤናዎት ላይ የተመሰረት እንዲሆን ያድርጉ።
እርሶም ተገንዝበው ለሌሎች ያስተምሩ።
መልካም በአል!
Comments