top of page

ሳይንስ ያልፈታው እንቆቅልሽ፦ የአእምሮ ጤና እውነታዎች

ለመሆኑ በሰውነትዎ ውስጥ የሚገኘው እጅግ ሚስጥራዊው አካል የትኛው እንደሆነ ያውቃሉ?

ሳይንስ አቅሙ የፈቀደውን ያህል ቢመራመረውም፤ ምስጢሩን ሙሉ በሙሉ ሊፈታው ያልቻለው ያ እንቆቅልሽ አካል ማን ይመስልዎታል?



ልብ አይደለም፤ ጉበትና ኩላሊትም አይደሉም፤ የማንነታችን መገለጫ የሆነው ዘረመላችን (DNA) እንኳን አይደለም!

ይህን ጽሑፍ አሁን ሲያነቡ፤ መልእክቱን ተረድቶ የሚተነትነው፤ በራስ ቅልዎ ውስጥ በፈሳሽ ተከቦ ፤ በመንሳፈፍ ሕይወትዎን የሚመራውና ፤ በአማካይ 1.3 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ያ ድንቅ አካል—አእምሮዎ ነው።


የሰው ልጅ አእምሮን ማጥናት ከጀመረ ዘመናት ቢቆጠሩም፤ እስካሁን ያወቅነው ግን ቅንጣቱን ያህል ብቻ ነው። አንዳንዶችማ ፈጽሞ ሙሉ በሙሉ ልንረዳው አንችልም ብለው ያምናሉ። ሌሎችን አካላት መርምሮ ከመረዳት አልፎ፤ ራሱን በራሱ ማጥናት የቻለ ብቸኛው ልዩ አካልም እርሱ ነው።


የሰውን ልጅ ወደ ጨረቃ በላክንበት፤ በረቀቁ ሮቦቶች ቀዶ ጥገና በምናከናውንበት እና የሰውን ልጅ የዘር ውርስ ኮድ (Genome) በፈታንበት በዚህ የረቀቀ ዘመን፤ ሳይንቲስቶች አሁንም ይህ ተአምረኛ አካል እንዴት ሐሳብን፣ ስሜትን፣ ትውስታን፣ ሕልምን፣ የፈጠራ ጥበብን፣ ፍቅርን፣ ፍርሃትን እና ራሱን ንቃተ-ህሊናን (Consciousness) እንደሚፈጥር ለማወቅ እየተጉ ነው።



እርስዎ...

  • እያንዳንዱ የሚያስተላልፉት ውሳኔ፣

  • እያንዳንዱ የሚለዩት/የሚያውቁት ፊት፣

  • በልብዎ ያቀፉት እያንዳንዱ ውድ ትውስታ፣

  • እና በውስጥዎ የሚመላለሰው እያንዳንዱ ስሜት...


...ይህ ሁሉ የሚፈልቀው ወደ 86 ቢሊዮን ከሚጠጉ የነርቭ ሕዋሳት (Neurons) በተሸመነው ፤ በዚህ አስደናቂ የአካል ክፍል ውስጥ ነው።


ነገር ግን አብዛኞቻችን ስለ "ጤና" ስናስብ ወደ አእምሯችን የሚመጣው የደም ግፊት፣ ስኳር፣ ኮሌስትሮል፣ የሰውነት ክብደት ወይም ኢንፌክሽን ነው፤ ሁሉንም የሰውነት ክፍሎች ከጀርባ ሆኖ በዝምታ የሚዘውረውን ይህንን ዋና መሪ ግን ብዙ ጊዜ እንዘነጋዋለን።

ይህ ደግሞ በዘመናዊ ሕክምና ውስጥ እጅግ ወሳኝ ወደሆነ፤ ነገር ግን ሰፊ የተሳሳተ ግንዛቤ ወደተወሰደበት አንገብጋቢ ርዕስ ያመጣናል፦ የአእምሮ ጤና (Mental Health)


የአእምሮ ጤና ሲባል ምን ይታይዎታል? ይህን አብዛኛው ሰው ይሳሳታል!

ብዙዎቻችን "የአእምሮ ጤና" የሚለውን ሐረግ ስንሰማ፤ ወዲያውኑ ወደ አእምሯችን የሚመጣው "የአእምሮ ሕመም" ወይም "እብደት" ነው።

ነገር ግን የአእምሮ ጤና ከዚህ እጅግ የሰፋ እና ጥልቅ ትርጉም አለው፤ የአእምሮ ጤና ማለት የስሜታችን፣ የስነ-ልቦናችን እና ከሰዎች ጋር ያለን ማኅበራዊ ሕይወት ሚዛኑን ጠብቆ የመቀጠል ሁኔታ ነው። እንዴት እንደምናስብ፣ እንደምንማር፣ ውሳኔ እንደምናስተላልፍ፣ ውጥረትን እንደምንቋቋም እና ከሌሎች ጋር እንዴት እንደምንግባባ የሚወስን መሠረት ነው።


እያንዳንዱ ሰው አካላዊ ጤና እንዳለው ሁሉ፤ እያንዳንዱ ሰው የአእምሮ ጤናም አለው። የአእምሮ ጤና ግብ በየቀኑ እና በእያንዳንዱ ሰከንድ ፍጹም ደስተኛ መሆን አይደለም። ይህ ከተፈጥሮ ሕግ ውጭ ነው።


ይልቁንም፤ መልካም የአእምሮ ጤና ማለት ሕይወት የሚጥልብንን ፈተና የመላመድ፣ ከውድቀቶች በብርታት የመነሳት፣ ማኅበራዊ ግንኙነቶችን የመጠበቅ እና በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ውጤታማ ሆኖ የመቀጠል ብቃት ነው።


የአስደናቂው አእምሮ ሚዛን ሲናጋስ?

አእምሮ በሚታወቀው ዓለም ውስጥ የሚገኝ፤ እጅግ ውስብስብ መዋቅር ተደርጎ ይወሰዳል።

በውስጡም በቢሊዮን የሚቆጠሩ የነርቭ ህዋሳት ፤ እንደ ሴሮቶኒን (Serotonin)፣ ዶፓሚን (Dopamine)፣ ኖሬፒኔፍሪን (Norepinephrine) እና ጋባ (GABA) ባሉ ረቂቅ ኬሚካላዊ መልእክተኞች አማካኝነት ይግባባሉ። እነዚህ ኬሚካሎች ስሜታችንን፣ ተነሳሽነታችንን፣ ትኩረታችንን፣ እንቅልፋችንን እና ስሜታዊ ምላሾቻችንን የሚቆጣጠሩ ዋና ዘዋሪዎች ናቸው።

ታዲያ ይህ ሥርዓት በዘር ውርስ፣ በማያቋርጥ የኑሮ ውጥረት፣ በአሰቃቂ ሁኔታዎች ወይም በአካላዊ ሕመም ምክንያት ሲታወክ፤ የአእምሮ ጤናችን አደጋ ላይ ይወድቃል፤ ይዛባል፤ ይናጋል። የዚህን ጊዜ የሰውነታችን መሪ ስለታመመ፤ አጠቃላይ ሕይወታችን መመሰቃቀሉ አይቀሬ ነው።


የአእምሮ ጤና እክሎችም በቀላሉ "በፍላጎት ወይም በቁርጠኝነት" ብቻ የማይፈቱት፤ ከአእምሮ ጤና በስተጀርባ ባሉት እውነተኛ ባዮሎጂያዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ሂደቶች የተነሳ ነው።


በዝምታ የሚያሰቃዩት ህመሞች

በዓለም ዙሪያ ሰዎችን በብዛት ከሚያጠቁ የአእምሮ ጤና እክሎች መካከል፤ ድብርት (Depression) እና የጭንቀት በሽታዎች (Anxiety Disorders) ግንባር ቀደሞቹ ናቸው።



ብዙዎች ድብርት የተለመደና ተራ ነገር እንደሆነ ያስባሉ። ነገር ግን ድብርት ተራ የሐዘን ስሜት ብቻ አይደለም። ድብርት ያለበት ሰው የማያቋርጥና ስር የሰደደ የድካም ስሜት ሊሰማው፣ ቀደም ሲል ደስታን ይሰጡት የነበሩ ነገሮች ትርጉም ሊያጡበት፣ ትኩረት ለማድረግ ሊቸገር፣ እንቅልፍ እና የምግብ ፍላጎቱ ሊዛባ እንዲሁም የዕለት ተዕለት ቀላል ሥራዎች እንኳ እንደ ተራራ ሊከብዱት ይችላሉ።


በተመሳሳይ ሁኔታ ጭንቀትም ከተራ "ሥጋት" ያለፈ ነው፤ ይህ እክል ከአቅም በላይ የሆነ ፍርሃትን፣ ሐሳብ መበታተንን፣ እረፍት ማጣትን፣ የመተኛት እምቢተኝነትን፣ የልብ ምት መፍጠንን እና የማያቋርጥ የውጥረት ስሜትን ይዞ ይመጣል።

እነዚህ እክሎች ለፈተና የሚዘጋጁ ተማሪዎችን፣ ቤተሰብ የሚንከባከቡ ወላጆችን፣ የጤና ባለሙያዎችን፣ ነጋዴዎችንና የሀገር መሪዎችን ሳይቀር እኩል ሊያጠቁ ይችላሉ።


የአእምሮ ጤና ተግዳሮቶች ማዕረግም ሆነ ሀብት አይመርጡም።

አእምሮ ለአካል፣ አካል ለአእምሮ

ለብዙ አሥርት ዓመታት ሕክምና አእምሮንና አካልን እንደ ሁለት የተለያዩ አካላት ይመለከታቸው ነበር። ዘመናዊ ሳይንስ ግን ሁለቱ በማይበጠስ ገመድ የተሳሰሩ መሆናቸውን አረጋግጧል።


የማያቋርጥ ሥነ-ልቦናዊ ውጥረት በእንቅልፍ ጥራት፣ በሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም፣ በደም ግፊት፣ በደም ውስጥ ስኳር ቁጥጥር እና በልብ ጤና ላይ ጭምር ቀጥተኛ አደጋ ያሳድራል።


በተመሳሳይ ጊዜ፤ እንደ ስኳር፣ ደም ግፊት፣ የኩላሊት በሽታ ወይም ካንሰር ካሉ ሥር የሰደዱ ሕመሞች ጋር የሚኖሩ ግለሰቦችም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው ከባድ የአእምሮ ጫና ያድርባቸዋል። ረዥም ጊዜ የሚቆዩ ሕመሞች ስሜትን፣ አስተሳሰብንና እይታን ሊረብሹ ይችላሉ።


አእምሮ በአካል ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ፤ አካል በአእምሮ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።

አንዱ ያለ ሌላው ህይወት ሊኖረው አይችልም።


ጤናማ አእምሮን ለመገንባት የሚያስፈልጉ ወርቃማ ልማዶች



ፍጹም የአእምሮ ጤናን በአንድ ጀምበር የሚያረጋግጥ አስማታዊ ቀመር ባይኖርም፤ ምርምሮች እንደሚጠቁሙት እነዚህን ልማዶች ማዘውተር የአእምሮን ደህንነት በጥልቀት ይደግፋል፦


  1. በቀን ከ 7 እስከ 9 ሰዓት ይተኙ፦ እንቅልፍ የቅንጦት አይደለም። አእምሮ ራሱን የሚያድስበት እና የሚጠግንበት ዋናው የሥራ ሰዓቱ ነው።

  2. የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያዘውትሩ፦ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተር የአእምሮን የኬሚካል ሚዛን ያስተካክላል። ስሜትንና ተነሳሽነትንም ያድሳል።

  3. ማኅበራዊ ግንኙነትዎን ያጠንክሩ፦ ከቤተሰብ፣ ከወዳጆች እና ከማኅበረሰብ ጋር ጠንካራ ማኅበራዊ ሕይወት መመሥረት፤ የአእምሮ ጤናን የሚጠብቅ ታላቅ የሥነ-ልቦና ጋሻ ነው።

  4. ውጥረትን ቀድመው ያክሙ፦ በጸሎት፣ በአርምሞ (Meditation)፣ በእንቅስቃሴ ወይም ትርፍ ጊዜን በሚወዱት ነገር በማሳለፍ፤ ውጥረትዎን ቀድመው ይቀንሱ።

  5. እርዳታ ለመጠየቅ አያመንቱ፦ የማያቋርጥ የደረት ሕመም አስቸኳይ የሕክምና ክትትል እንደሚያስፈልገው ሁሉ፤ ስር የሰደደ የስሜት መታወክም የባለሙያ ድጋፍ ያስፈልገዋል። በአቅራቢያዎ ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ ያማክሩ።


ሁላችንም ልንማረው የሚገባ ታላቅ እውነት



ከምናደርጋቸው ስህተቶች ሁሉ ትልቁ ስህተት "በስሜት መጎዳትን ወይም ማልቀስን" እንደ ድክመት መቁጠር ነው፤ የሕክምና ሳይንስ ግን የሚነግረን ፍጹም ተቃራኒውን ነው።


የአእምሮ ጤና እክሎች ማንኛውም የሰው ልጅ ሊጋፈጣቸው የሚችሉ የተለመዱ የጤና ፈተናዎች ናቸው። እነሱም በባዮሎጂ፣ በሕይወት ተሞክሮ፣ በአካባቢ እና በማኅበራዊ ጫናዎች መካከል ባሉ ውስብስብ ሽክርክሪቶች የሚፈጠሩ እንጂ፤ የባህሪ ደካማነት አይደሉም።


ድጋፍ መፈለግ የሽንፈት ምልክት አይደለም! ይልቁንም ጤና አካልን እና አእምሮን በእኩል እንደሚያካትት የተረዳንበት ትልቅ የብልህነት ምልክት ነው።


ማሳረጊያ ጥያቄ?

የሰው ልጅ አእምሮ አሁንም በሳይንስ ዓለም ውስጥ ትልቁ ምስጢር ነው። እርሱ ትውስታዎቻችንን ያክማል፣ ማንነታችንን ይቀርጻል፣ ሕልሞቻችንን ይፈጥራል፣ እንዲሁም ውሳኔዎቻችንን ይመራል።


ታዲያ ለአእምሮ ጤናችን የምንሰጠው እንክብካቤ፤ ለልባችን፣ ለሳንባችን እና ለኩላሊታችን ከምንሰጠው ትኩረት ያነሰ መሆን አለበት?

ውይይቱን እንቀጥል!

የግንቦት ወር (May) በዓለም አቀፍ ደረጃ "የአእምሮ ጤና ግንዛቤ ወር" ተብሎ ይከበራል፤ ዛሬም የዚህ ወር የመጨረሻው ቀን ነው።


ይህ ርዕስ በአንድ ጽሑፍ ብቻ ተዳስሶ የሚያልቅ አይደለም፤ ከምናስብበት መንገድ ጀምሮ እስከምንኖርበት፣ እስከምንሠራበት እና ግንኙነቶችን እስከምንገነባበት ድረስ ሕይወታችንን በሙሉ የሚነካ ሰፊ ዓለም ነው።


ይህንንም ተደራሽ ለማድረግ፤ ያዘጋጀናቸውን የሚከተሉትን ትምህርታዊ ጽሑፎች መመልከት ይችላሉ፦


📱 የማኅበራዊ ሚዲያ አብዝቶ መጠቀም በአእምሮ ላይ ያለው ተጽዕኖ፦ በዚህ ጽሑፍ ከመጠን በላይ የስማርትፎን አጠቃቀም በትኩረት፣ በእንቅልፍ እና በአእምሮ ደኅንነት ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በምርምር አስደግፈን አቅርበናል።


💙 ራስን የማጥፋት አደጋን ለመረዳት፦ ስለ አደጋው ምልክቶች፣ ስለተለመዱ የተሳሳቱ አመለካከቶች እና ቀድሞ ድጋፍ የማግኘት አስፈላጊነትን የሚዳስሱ ሁለት አስተማሪ ቪዲዮዎችን በዩቲዩብ (YouTube) ገጻችን አጋርተናል።



ባለፈው ዓመትም በአእምሮ ጤና ዙሪያ ያዘጋጀናቸውን ጽሑፎች ለማንበብ፤ ድኅረ ገጻችንን ይጎብኙ።

ለአእምሮዎ ጤና ቦታ ይስጡ!

bottom of page