የወንድ መሀንነት መንስኤዎች፣ ምልክቶች እና ዘመናዊ የሕክምና መፍትሔዎች
- Zebeaman Tibebu
- 1 day ago
- 6 min read
"ሳይመጣ የቀረው ልጅ..."
እነኝህ ወጣት ጥንዶች ከተጋቡ ሰባት ዓመታት ተቆጠሩ። ነገር ግን አሁንም ሁለት ናቸው፤ ገና ሦስት አልሆኑም።
በየበዓላቱ፣ በየሰርጉ እና ዘመድ ሊጠይቁ በሄዱ ቁጥር ያው አንድ ጥያቄ ይደጋገማል፦ "መቼ ነው እንግዲህ የምስራች የምንሰማው? መቼ ነው ልጅ ወልዳችሁ የምትስሙት?"
መጀመሪያ አካባቢ በፈገግታ አሳለፉት። ቀጥሎም በሳቅ ለማስተባበል ሞከሩ። ጥያቄው እየበረታ ሰላማቸውን ሲነሳቸው ግን፤ የቤተሰብ እና የዘመድ ስብሰባዎችን ሙሉ በሙሉ አቆሙ።
ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ግን የሐሜት ወሬዎች ናኙ። ከእነርሱ በላይ ምስጢራቸውን አውቀው የተገኙ ዘመዶች ሚስቲቱን ብቻ ተጠያቂ አደረጓት። የቅርብ ጓደኞች የተለያዩ ባህላዊ መድኃኒቶችን ጠቆሙ። አንዳንዶች ደግሞ "ሌላ ሴት አግባ" እያሉ ባልየውን በግልጽ መከሩት።

በመጨረሻም ጥንዶቹ ወደ ልዩ የወሊድ ሕክምና ክሊኒክ (Fertility Clinic) ሄደው ተመረመሩ። እዚያ ግን ማንም ያልጠበቀው እውነት ተገለጠ።
ችግሩ ከሚስቲቱ ጋር አልነበረም፤ የባልየው የዘር ፈሳሽ (Sperm) ጥራት እና ብዛት አናሳ ነበር።
ይህ የእነሱ ታሪክ ብቻ አይደለም። በኢትዮጵያም ሆነ በመላው ዓለም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጥንዶች ልጅ የመውለድ ፈተና ይገጥማቸዋል። ሆኖም ግን ሁልጊዜ አንድ ወሳኝ እውነት በባህልና በዕውቀት ማነስ ተሸፋፍኖ ያልፋል፤ ይኸውም ወንዱም የዚህ ችግር ዋነኛ ምክንያት ሊሆን የመቻል ዕድሉ እኩል መሆኑ ነው።
ዛሬ ስለ ወንድ ልጅ መሀንነት (Male Infertility) መንስኤዎች፣ ማኅበራዊ ጫናዎች እና ሳይንሳዊ መፍትሔዎች በጥልቀት እናነሳለን።
የወንድ መሀንነት እጅግ የተለመደ ነው!
በሕክምና ሳይንስ ጥናት መሠረት፤ መሀንነት የሚባለው ጥንዶች ምንም ዓይነት የእርግዝና መከላከያ ሳይጠቀሙ፤ ለ12 ወራት ወይም ከዚያ በላይ በዘወትር የግብረ-ሥጋ ግንኙነት እርግዝና መፈጠር ሲሳናቸው ነው።

በባለሙያዎች በተደረጉ መጠነ ሰፊ የመራቢያ ጤና ጥናቶች መሠረት፤ በዓለም ዙሪያ ለሚከሰቱት የመውለድ ችግሮች ከ40% እስከ 50% የሚሆነው ድርሻ ከወንዶች ጋር በተያያዙ ምክንያቶች የሚከሰት ነው። ይህ ማለት የችግሩ ግማሽ አካል ወንዱ ነው ማለት ነው።
በሌላ አነጋገር፦
የወንድ መሀንነት እጅግ ብርቅዬ ክስተት / ያልተለመደ እንግዳ ነገር አይደለም።
ነገር ግን በኢትዮጵያ ባለው ማኅበራዊ እና ባህላዊ አመለካከት ምክንያት፤ የወሊድ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ በሴቷ ላይ ብቻ ስለሚጣል ጨርሶ ለመመርመር የማይፈልጉ ወንዶች ጥቂት አይደሉም። ይህ መዘግየት ውድ የሆነውን ጊዜ ያባክናል፤ ከፍተኛ ገንዘብ ያስወጣል፤ እንዲሁም በትዳር አጋሮች መካከል የስነ-ልቦና እና የስሜት ውጥረት እንዲፈጠር ያደርጋል። አልፎ ተርፎም ለትዳሮች መፍረስ ዋነኛ ምክንያት ይሆናል።
የወንድ መሀንነት በትክክል ምንድን ነው?

ስለ መሀንነት በደንብ ለመረዳት፤ የዘር ሕዋስ እንዴት እንደሚመረት ማወቁ ይጠቅማል። በወንዶች የዘር ፍሬ (Testes) ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዘር ሕዋሳት በየቀኑ ይመረታሉ፤ ይህ አጠቃላይ የምርት ሂደት ደግሞ ከ64 እስከ 72 ቀናት አካባቢ ይወስዳል።
እርግዝና በተፈጥሯዊ መንገድ እንዲፈጠር እነዚህ የዘር ሕዋሳት የሚከተሉትን ከባድ የባዮሎጂ መስፈርቶች ማሟላት አለባቸው፦
በብዛት መመረት አለባቸው ➔ በየቀኑ በቂ በሆነ ቁጥር (በሚሊዮኖች) መመረት አለባቸው።
↓
ጤናማ ቅርጽ መያዝ ➔ ዕድገታቸው የተሟላ መሆንና መደበኛ ቅርጽ (ራስ እና ጭራ) መያዝ አለባቸው።
↓
ፈጣን እንቅስቃሴ ማድረግ ➔በፈሳሹ ውስጥ ወደ ፊት በብቃት መዋኘት መቻል አለባቸው።
↓
በወንድ ልጅ ብልት ጫፍ መውጣት➔ እነኝህ ህዋሳት ባልተደፈኑ/ክፍት በሆኑ ቱቦዎች ተጉዘው በወንድ ብልት ጫፍ መውጣት አለባቸው።
↓
ከሴት እንቁላል ጋር መጣመር ➔ ጉዞውን ተቋቁመው የሴቷን እንቁላል ሲያገኙ፤ ግድግዳውን ሰንጥቀው ገብተው መዋሃድ አለባቸው።ይህ ሂደት በብዙ ረቂቅ እና ጥንቃቄ በተሞላበት የሰውነት ዑደት ላይ የተመሰረተ ነው። በሆርሞን ደረጃ በጭንቅላት ውስጥ የሚገኙት ሃይፖታላመስ (Hypothalamus) እና ፒቱታሪ (Pituitary) እጢዎች፤ የወንድ የዘር ፍሬ (Testes) ቴስቶስትሮን የተሰኘውን ሆርሞን እና ጤናማ የዘር ሕዋስ (Sperm) እንዲያመርት ማዘዝ አለባቸው።
በዚህ ሂደት ውስጥ በማናቸውም ደረጃ ላይ የሚፈጠር ጥቃቅን መስተጓጎል እንኳን፤ የመውለድ ዕድልን በእጅጉ ይቀንሰዋል።
በመሆኑም መሀንነት ሊከሰት የሚችለው፦
የምርት መጠኑ እጅጉን አናሳ ሲሆን፤
የሕዋሳቱ መመረት ፈጽሞ ሲያቆም፤
የዘር ሕዋሱ ቅርጽ የተሟላ ሳይሆን ሲቀር፤
የዘር ሕዋሱ የመዋኘት እንቅስቃሴ ሲደክም፤
የዘር ሕዋስ መውጫው ቱቦ ሲዘጋ፤
አልያም የሆርሞን መዛባት ሲያጋጥም ነው።
እነኝህን ሊያመጡ የሚችሉ ብዙ የጤና እክሎች አሉ።
ለወንድ መሀንነት ምክንያት የሆኑ 7 ዋና ዋና መንስኤዎች

1. ቫሪኮሲል (Varicocele)
ቫሪኮሲል ማለት በዘር ፍሬ ከረጢት ውስጥ የሚገኙት የደም ሥሮች ማበጥ ወይም መስፋፋት ችግር ነው። ይህ እክል በቀዶ ሕክምና በቀላሉ ሊስተካከል የሚችል የወንድ መሀንነት መንስኤ ነው። እነዚህ ያበጡ ሥሮች ደም እዚያው እንዲተኛ በማድረግ፤ የዘር ፍሬውን ሙቀት እንዲጨምር ያደርጋሉ። ይህም የዘር ሕዋስ ምርትን እና ጥራትን በቀጥታ በመጉዳት ለመሀንነት ያጋልጣል።
2. የሆርሞን መዛባት
የዘር ሕዋስ ምርት መስመርን የሚቆጣጠሩ ሆርሞኖች ላይ መስተጓጎል ሲፈጠር፤ የመውለድ አቅም በእጅጉ ይዳከማል። ለምሳሌ እንደ ቴስቶስትሮን (Testosterone)፣ FSH፣ LH ወይም ፕሮላክቲን (Prolactin) ያሉት ሆርሞኖች ሲዛቡ መሀንነት ይመጣል።
3. ኢንፌክሽኖች
አንዳንድ ኢንፌክሽኖች በመራቢያ አካላት ላይ ዘላቂ ጠባሳ ሊጥሉ ወይም የዘር ሕዋስ ምርትን ለጊዜው ሊያቆሙ ይችላሉ። ከእነዚህም መካከል በአግባቡ ያልታከሙ የአባላዘር በሽታዎች፣ የዘር ፍሬ መቆጣት (Orchitis)፣ የፕሮስቴት መቆጣት (Prostatitis) እና የዘር ፍሬ ቱቦ ኢንፌክሽኖች (Epididymitis) ተጠቃሽ ናቸው።

4. የመራቢያ ቱቦ መደፈን
አንድ ሰው ፍጹም ጤናማ የዘር ሕዋስ ሊያመርት ይችላል። ነገር ግን በተፈጥሮ የመራቢያ ቱቦ መደፈን ምክንያት፤ ሕዋሳቱ ከሰውነት መውጣት ሊሳናቸው ይችላል። ይህ መዘጋት ከዚህ ቀደም በደረሱ ጉዳቶች፣ በቀዶ ጥገናዎች ወይም በኢንፌክሽኖች ሳቢያ ሊፈጠር ይችላል።
5. የዘረመል (Genetic) ችግሮች
አንዳንድ ወንዶች ከመራቢያ አካላት ዕድገት ጋር የተያያዙ የዘረመል (Chromosomal) እክሎችን(ለምሳሌ ክላይንፌልተር ሲንድሮም (Klinefelter Syndrome) )ይዘው ይወለዳሉ። በመሆኑም እነዚህ ወንዶች ከልጅነት ጀምሮ የመውለድ አቅማቸው የተገደበ ሊሆን ይችላል።

6. የኑሮ ዘይቤ እና ጎጂ ልማዶች
የምንመርጠው የኑሮ ዘይቤ በመራቢያ ጤናችን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አለው። በሕክምና ምርምሮች የተረጋገጠው እውነታ እንደሚያሳየው ሲጋራ ማጨስ፣ ከልክ በላይ የአልኮል መጠጥ መውሰድ፣ ውፍረት፣ ሥር የሰደደ ጭንቀት እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የዘር ሕዋስ ቁጥርንና የመዋኘት ብቃትን በእጅጉ ዝቅ ያደርጋሉ።
በኢትዮጵያ የተደረጉ ጥናቶች ፤ በኑሮ ዘይቤ እና በወንድ መሀንነት መካከል ከፍተኛ ግንኙነት እንዳለ አረጋግጠዋል። አዘውትሮ ጫት መቃም እና ከፍተኛ የአልኮል ፍጆታ የዘር ህዋስ እንቅስቃሴን ከመጉዳትና ቅርጹን ከማዛባት ባለፈ፤ በአንዳንድ ታካሚዎች ላይ የዘር ህዋስ ሙሉ በሙሉ የመጥፋት (azoospermia) ዕድልን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምሩ በተጨባጭ ታይቷል።
7. የአካባቢ እና የሥራ ላይ ተጋላጭነቶች
ለረጅም ጊዜ ለከፍተኛ የኢንዱስትሪ ሙቀት ፣ እንደ ሊድ (Lead) ላሉ ከባድ ማዕድናት ፣ ለአንዳንድ ፀረ-ተባይ መድኃኒቶችና ለኬሚካል መርዞች መጋለጥ መሀንነት ሊያመጣ ይችላል። እንዲሁም ላፕቶፕን ሁልጊዜ ታፋ ላይ አድርጎ መጠቀም፤ የዘር ሕዋስ የሚያመርቱትን ህዋሳትን ክፉኛ ሊጎዳ ይችላል።
ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

የወንድ መሀንነት ትልቁ አስገራሚ ባሕሪው፤ ብዙ ጊዜ ምንም ግልጽ ምልክት አለማሳየቱ ነው። አንድ ሰው በአካል ጠንካራ፣ ሙሉ ጉልበት ያለው እና ሙሉ በሙሉ ጤናማ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ሕይወት የሚመራ ቢሆንም፤ በላብራቶሪ ምርመራ ብቻ ሊታወቅ የሚችል ከባድ የዘር ሕዋስ ችግር ሊኖርበት ይችላል።
በብዙ አጋጣሚዎች እርግዝና አለመፈጠሩ ብቻ ብቸኛው ምልክት ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን፤ አንዳንድ መሀንነት የሚያመጡ የሕክምና ችግሮች ሲያጋጥሙ ወንዶች የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያስተውሉ ይችላሉ፦
የግብረ-ሥጋ ግንኙነት መስተጓጎል፦ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ፍላጎት መቀነስ፣ በግንኙነት ጊዜ ለመጨረስ እጅግ ረጅም ጊዜ መውሰድ፣ የወንድ ዘር ፈሳሽ ፈጽሞ አለመፍሰስ ወይም ስሜትን ጠብቆ ለማቆየት መቸገር (Erectile Dysfunction)፤
የአካል ምቾት ማጣት፦ በዘር ፍሬ አካባቢ የሚሰማ የሚደጋገም ሕመም፣ እብጠት ወይም የሚዳሰስ እብጠታ መሰል ነገር መኖር፤
የሆርሞን ለውጦች፦ የፊት ወይም የሰውነት ፀጉር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ፤ ወይም የወንድ ጡት አካባቢ መግዘፍና ማበጥ (Gynecomastia)።
ያስተውሉ፦ አንድ ወንድ አልጋ ላይ ጎበዝ ሆነ ማለት፤ የመውለድ አቅሙ ፍጹም ጤናማ ነው ማለት አይደለም።
እንዴት ይመረመራል?

ወንድ ላይ ያለ የመሀንነት ችግርን ለመለየት፤ የጤና ባለሙያው አጠቃላይ የአካል ብቃት እና የጤና ታሪክ ምርመራ ከማድረጉም ባሻገር የሚከተሉትን ምርመራዎች ሊያዝ ይችላል፦
የዘር ፈሳሽ ምርመራ ፦ ይህ የሁሉም ምርመራዎች ዋና መሠረት ነው፤ ላቦራቶሪው የፈሳሹን መጠን፣ አጠቃላይ የዘር ሕዋስ ቁጥርን፣ የመዋኘት ፍጥነታቸውን እና አካላዊ ቅርጻቸውን ይገመግማል።
የሆርሞን ምርመራ፦ የደም ምርመራ በማድረግ የዘር ሕዋስ ምርትን የሚቆጣጠሩትን እንደ ቴስቶስትሮን (Testosterone)፤ FSH እና LH ያሉ ሆርሞኖችን መጠን ማወቅ ይቻላል።
የአልትራሳውንድ ምርመራ፦ የዘር ፍሬ አልትራሳውንድ በማድረግ የዘር ፍሬ አቀማመጥን፣ የደም ሥሮችን ሁኔታ (ለምሳሌ ቫሪኮሲል መኖሩን) እና የዘር ፍሬ መውጫ ቱቦዎችን መዋቅር በቅርበት ማጤን ይቻላል።
የዘረመል ምርመራ፦ ይህ ምርመራ የዘር ሕዋስ ቁጥር እጅግ አነስተኛ ለሆነባቸው ወይም የዘረመል ችግር ለሚጠረጠርባቸው ወንዶች የሚደረግ ልዩ ምርመራ ነው።
የወንድ መሀንነት ይታከማል?
አዎ፤ የወንድ መሀንነት ይታከማል!

መሀንነትን እንዳመጣው የጤና እክል ዓይነት የሚወሰኑ፤ በርካታ የሕክምና አማራጮች አሉ። ለምሳሌ፦
የመድኃኒት ሕክምና፦ የሆርሞን መዛባትን በተገቢው መድኃኒት በማከም ፤ በ3 እስከ 6 ወራት ውስጥ ጤናማ የዘር ሕዋስ ምርት እንዲመለስ ማድረግ ይቻላል። እንዲሁም በመራቢያ አካላት ላይ ያሉ ኢንፌክሽኖች ፤ በተመረጡ አንቲባዮቲኮች ሙሉ በሙሉ ይጠፋሉ።
የቀዶ ሕክምና፦ እንደ ቫሪኮሲል እና የዘር ፈሳሽ መውጫ ቱቦ መደፈን ያሉ እክሎች ፤ በቀዶ ሕክምና በቀላሉ ሊስተካከሉ ይችላሉ።
የረቀቁ የቴክኖሎጂ አማራጮች፦ በተፈጥሯዊ መንገድ መፀነስ አሁንም አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜ፤ የወንድ የዘር ፈሳሽ ተወስዶ በቀጥታ የሴቷ ማሕፀን ውስጥ በማድረግ (IUI)፤ አልያም በቤተ-ሙከራ ፅንስን በመፍጠር (IVF) ማርገዝ ይቻላል። አንድ ጤናማ የዘር ሕዋስ ብቻ ተለይቶ በቀጥታ ወደ ሴቷ እንቁላል ውስጥ እንዲገባ የሚደረግበት የረቀቀ ዘዴም (ICSI) ሌላው ትልቅ አማራጭ ነው።
ነገር ግን፤ በዘረመል (Genetic) ችግሮች እና በአንዳንድ ውስብስብ ምክንያቶች የሚመጣ፤ የወንድ የዘር ፍሬ ሕዋስ በሰውነት ውስጥ ፈጽሞ የማይመረትበት (Severe Azoospermia) የመሀንነት ዓይነት፤ አሁን ባለው ዘመናዊ ሕክምና ሙሉ በሙሉ ሊስተካከል እንደማይችል መታወቅ አለበት።
በኢትዮጵያም በወቅቱ 22 አከባቢ የሚገኘው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል አካል የሆነው ምቹ ክሊኒክ፤ በስነ ተዋልዶ ዙሪያ በአገራችን ከፍተኛ የሚባሉ የሕክምና አማራጮችን እየሰጠ ይገኛል። በዚህ ዙሪያ ላይ ምርመራ የሚፈልጉ ጥንዶች ፤ በጋራ ሄደው መታየት ይችላሉ።
ስለ መሀንነት ሲነሳ የሚረሳው እውነታ

የወንድ መሀንነት ተፅዕኖ ከአካላዊ ጉዳት በላይ ይሄዳል!
የአንድን ወንድ በራስ የመተማመን ስሜት ይነካል ትዳርን ያናውጣል። እንዲሁም ወደ ከባድ የሀፍረት፣ የብቸኝነት፣ የጭንቀት እና የውጥረት ስሜቶች ያመራል። ብዙ ወንዶችም እንደ ጉድለት ስለሚያዩት፤ ችግራቸውን አያማክሩም። በዝምታ ይሰቃያሉ። ራሳቸውን ከማኅበራዊ ሁነቶች የሚያገሉም አሉ።
ይህንን ዝምታ መስበር ግን ለመዳን የመጀመሪያው ትልቅ እርምጃ ነው። የሕክምና እርዳታ መፈለግ ፈጽሞ የደካማነት ምልክት አይደለም።
መሀንነትን ለመከላከል እያንዳንዱ ወንድ ዛሬ ሊያደርጋቸው የሚገቡ 5 ነገሮች

ሲጋራ ማጨስን፣ ጫት መቃምን እና አልኮል አብዝቶ መጠጣትን ያቁሙ።
ጤናማ የሰውነት ክብደትን ይጠብቁ።
መሀንነትን ከጠረጠሩ ቀድመው ይመርመሩ።
ደህንነቱ የተጠበቀ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት በማድረግ፤ ራስዎን ከአባላዘር በሽታዎች ይጠብቁ።
የመራቢያ አካል ኢንፌክሽን ምልክቶች ካዩ ቀደም ብለው ይታከሙ፤ ይህ መጣደፍ ዘላቂ ጠባሳ እንዳይፈጠር ይከላከላል።
ለጤናዎ ቦታ ይስጡ! የህይወት ዘይቤዎን ያስተካክሉ! መሀንነት ከማጋጠሙ በፊት ዛሬውኑ እርምጃ ይውሰዱ!




Comments