ፈለግ አለብዎ? ምን ያድርጉ?
በጥፍርዎ ዙሪያ ያለው ቆዳ ተልጦና ቆስሎ፣ “ፈለግ” አውጥቶብዎት ያውቃል?

መጀመሪያ ላይ ጉዳት የሌለው ትንሽ ነገር ይመስላል። ነገር ግን በልብስ ሲያዝ፤ ወይ ደግሞ ሳያውቁት እጅዎን ኪስዎ ውስጥ ሲከቱ የሚሰማው ህመም ቀላል አይደለም። ውሃ ሲነካውማ ይለበልባል። ይህ ትኩረትዎን ይሰርቃል። ከሚለበልበው ቁስል ለመገላገልም ብለው በእጅዎ ለመንጨት ወይም በጥርስዎ ነክሰው ለመቁረጥ ይዳዳዎታል።
ግን እዚህ ጋ ይቁሙ!
ያን የተላጠ ቆዳ በኃይል መጎተት ቢዳዳዎትም፤ አያድርጉት። መፍትሔ ሳይሆን፤ ትልቅ ስህተት ነው። ይህ ድርጊት ከፈለጉ ሥር ያለውን ስጋ ቆዳ አብሮ ስለሚቀደው ለከፍተኛ ህመም፣ ለደም መፍሰስ፣ አልፎ ተርፎም ለኢንፌክሽን በር ይከፍታል።
ታዲያ ይህ “ፈለግ” ለምን ይወጣል? ጣታችንን ለከፋ ኢንፌክሽን ሳናጋልጥስ እንዴት በደህና ማስወገድ እንችላለን?
ፈለግ ምንድን ነው?

ፈለግ የሚባለው በጥፍር ዙሪያ ያለው የቆዳ ክፍል ሲደርቅና ሲሰነጠቅ፤ የቆዳው የላይኛው ክፍል ተልጦ/ተነስቶ የሚታይበት ሁኔታ ነው። እዚህ ላይ ሊያስተውሉት የሚገባው ነገር
ፈለግ ጥፍሩን ሳይሆን፤ ጥፍሩ ዙሪያ ያለውን ስስ ቆዳ ብቻ የሚያጠቃ መሆኑን ነው።
ይህ የተላጠ ቆዳ መጠኑ እጅግ በጣም ትንሽ ቢሆንም፤ በጣታችን ጫፎች ላይ በርካታ የሕመም ስሜት ተቀባይ የነርቭ ጫፎች (nerve endings) ስላሉ፤ መላጡ ሕመም አለው። በልብስ ሲጎተት ወይም ሳያውቁት ሲነኩትም የሚለበልብ ሕመም ያስከትላል።
በተጨማሪም ቆዳው በመላጡ የሰውነታችን የመጀመሪያ የጥበቃ ግንብ ይፈርሳል። በዚህም በቆዳው ውስጥ ባክቴሪያ ከገባ በጥፍር ዙሪያ ኢንፌክሽን ሊፈጠር ይችላል። ይህ ሁኔታ ፓሮኒኪያ (Paronychia) ይባላል። ምልክቶቹም መቅላት፣ ማበጥ፣ ሙቀት፣ ሕመምና አንዳንዴ መግል መኖር ናቸው።
ፈለግ ለምን ይወጣል?

ፈለግ መውጣት በአብዛኛው በጥፍር ዙሪያ በሚደርሱ ጥቃቅን ጉዳቶች ሳቢያ የሚከሰት ነው። ለዚህ ደግሞ ዋነኞቹ ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፦
የቆዳ መድረቅ ፦ በጥፍር ዙሪያ ያለው ቆዳ የተፈጥሮ እርጥበቱን ሲያጣ የመለጠጥ አቅሙ ይደክማል። በዚህም ምክንያት ቆዳው በቀላሉ የመሰነጠቅና የመላጥ ዕድሉ ከፍተኛ ይሆናል። ይህም ፈለግን ያስከትላል።
እጅን አብዝቶ መታጠብና ለኬሚካሎች መጋለጥ፦ እጅን በተደጋጋሚ በሳሙናና በውሃ መታጠብ፤ እንዲሁም የልብስ ማጠቢያና የቤት ውስጥ ማጽጃ ኬሚካሎችን ያለ ጓንት መጠቀም፤ የቆዳን የተፈጥሮ ዘይት ያመነምናል። የቆዳ ወዝም ታጥቦ በመሄዱ፤ ቆዳው እንዲሻክርና እንዲቆጣ ይሆናል። ይህም ለፈለግ ያጋልጣል።
የጥፍር ዙሪያ ቆዳን በስህተት መቁረጥ ፦ ጥፍርዎን በሚቆርጡበት ጊዜ፤ በጥፍር ዙሪያ ያለውን ስስ ቆዳ (cuticle) ከልክ በላይ ከቆረጡት፤ ይህ ቆዳውን ያቆስላል፤ ለፈለግም ሊያጋልጥ ይችላል።
ጥፍርን የመንከስ ልማድ ፦ ጥፍርን የመንከስ ወይም በጥፍር ዙሪያ ያለውን ቆዳ የመጎተት ልማድ፤ ለቆዳ መላጥ ዋነኛው መንስኤ ነው። ይህ ፈለግን ከማስከተል አልፎ፤ ቀደም ሲል የተነሳን ትንሽ ፈለግ ለመቁረጥ ወይም በእጅ ለመንጨት መሞከር ደግሞ ቁስሉን ይበልጥ ያሰፋዋል። ፈለጉን ያባብሰዋል።
የአመጋገብ ችግር፦ ሰውነታችን ለቆዳ ጤናና ለቁስል ፈውስ የሚያስፈልጉትን ንጥረ ምግቦች ማግኘት አለበት። እንደ ፕሮቲን፣ ብረትና ዚንክ ያሉ ንጥረ ምግቦች እጥረት በቆዳና በጥፍር ጤና ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። ሆኖም ፈለግ መውጣት ብቻውን የንጥረ ምግብ እጥረት ምልክት አይደለም።
ፈለግን መጎተት ለምን አደገኛ ነው?

የተነሳውን ፈለግ በኃይል ጎትቶ ማስወገድ ትልቅ ስህተት ነው።
ምክንያቱም ሲጎትቱት የተላጠው የደረቀ ቆዳ ብቻ ሳይሆን፤ ከሥሩ ያለው ጤናማና ሕያው የቆዳ ክፍል አብሮ ሊነሳ ይችላል። ይህ ደግሞ ከባድ የሚለበልብ ሕመም ያስከትላል። ደምም ሊፈስ ይችላል። ቆዳው ተለይቶ በሚነሳበት ጊዜ ጣትዎ ላይ በቀላሉ የማይድንና ለንክኪ በጣም የሚያም ክፍት ቁስል ይተዋል። ከዚህም ባሻገር ለኢንፌክሽን በር ይከፍታል።
ባክቴሪያ አንዴ ወደ ውስጥ ከገባ ደግሞ በጥፍሩ ዙሪያ ያለው ቆዳ ይቆጣል። በከፍተኛ ሁኔታ ይቀላል፣ ያብጣል፣ እንዲሁም የውጋት ሕመም ያመጣል። ሁኔታው እየገፋ ሲሄድም መግል ይይዛል። ይህ የጤና እክል በሕክምናው ዓለም ፓሮኒኪያ (Paronychia) የሚባል የጥፍር አካባቢ ኢንፌክሽን ነው።
ስለዚህ ፈለግ ሲወጣ ዋናው ጉዳይ ቆዳውን ማንሳት ሳይሆን፤ ቁስሉ እንዳይመረዝ እንዴት በጥንቃቄ መያዝ እንዳለብን ማወቁ ላይ ነው።
✅ ፈለግ ሲወጣ ምን ማድረግ አለብን?
ፈለግ በሚወጣበት ጊዜ ቁስሉ እንዳይመረዝ እና ጣትዎ ለከፋ ኢንፌክሽን እንዳይጋለጥ የሚከተሉትን ቀላልና ፍፁም ጥንቃቄ የተሞላባቸውን እርምጃዎች መከተል ያስፈልጋል፦

ደረጃ 1፦ እጅዎንና ቦታውን በደንብ ያጽዱ
እጅዎን በሳሙናና በንጹህ ውሃ በስርአት ይታጠቡ። ፈለጉ የወጣበትን የጥፍር ዙሪያ አካባቢየሚገኝ ቆሻሻን ለማጽዳትና ባክቴሪያዎችን ለማስወገድ በቀስታና በደንብ ይታጠቡት።
ደረጃ 2፦ ቆዳውን በፍጹም አይጎትቱ!
የተንጠለጠለውን ቆዳ በጥርስ ለመንከስ፣ በጣት ለመንጨት ወይም በማንኛውም ነገር ለመጎተት በፍጹም አይሞክሩ።

ደረጃ 3፦ የተነሳውን ቆዳ ብቻ በጥንቃቄ ይቁረጡ
ቆዳው ተለይቶ የወጣና በቀላሉ ሊቆረጥ የሚችል ከሆነ፤ ንጹህ በሆነ የጥፍር መቁረጫ በመጠቀም የተንጠለጠለውን የደረቀ ቆዳ ብቻ በቀስታ ከሥሩ ይቁረጡት። እዚህ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ጤናማውን የቆዳ ክፍል እንዳይቆርጡ ይለዩ።
(ማሳሰቢያ፦ ጥፍር መቁረጫውን ከሌሎች ሰዎች ጋር በፍጹም አይጋሩ። ከመጠቀምዎ በፊትና በኋላም በአልኮል በደንብ ያጽዱት። ቆዳው አስቀድሞ እየደማ ከሆነ ወይም በጣም ካመመዎት በራስዎ ለመቁረጥ አይሞክሩ።)ደረጃ 4፦ የቆዳውን እርጥበት ይጠብቁ
ቆዳው ከደረቀ መልሶ ስለሚሰነጠቅ፤ የጥፍር ዙሪያውን የቆዳ እርጥበት መጠበቂያ ክሬም (Moisturizer) ወይም ቫዝሊን በመቀባት ማለስለስ ያስፈልጋል። ክፍት ቁስል ወይም ደም መፍሰስ ካለ ደግሞ ከተጨማሪ ቆሻሻና ግጭት ለመጠበቅ ንጹህ የቁስል ፕላስተር ይለጥፉበት።
መቼ መጨነቅ አለብን?

ፈለግ በአብዛኛው ጊዜ ቀለል ባሉ የቤት ውስጥ እንክብካቤዎች ሊድን የሚችል ቢሆንም፤ ሁኔታው ተባብሶ ወደ ከፋ ኢንፌክሽን ከተቀየረ ግን የሕክምና እርዳታ ያስፈልገዋል። ስለዚህ ከሚከተሉት ምልክቶች መካከል አንዱ እንኳ ካጋጠመዎት ሳይዘገዩ የጤና ባለሙያን ያማክሩ፦
የቆዳ መቅላትና ማበጥ ፦ በጥፍሩ ዙሪያ ያለው የቆዳ ክፍል በከፍተኛ ሁኔታ ቀልቶና አብጦ ሲወጠር፤
የሕመም ስሜት መጨመር፦ የሕመም ስሜቱ ከቀን ወደ ቀን እየባሰበት ሲሄድ ወይም አካባቢው ሲነኩት በጣም ሲሞቅ፤
መግል መቋጠር ፦ በጥፍሩ ጠርዝ ስር መግል የያዘ አነስተኛ እብጠት (ቁስል) ካለ፤
የትኩሳት ስሜት ፦ ከፍተኛ የሰውነት ትኩሳት ካለብዎት ወይም መቅላቱና ማበጡ ወደ መላው ጣትዎና እጅዎ ከተስፋፋ፤
የጤና ባለሙያ ያማክሩ።
ፈለግ እንዳይደጋገም ምን ማድረግ አለብን?

ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ከማከም ይልቅ አስቀድሞ እንዳይፈጠር መከላከል እጅግ ይቀላል። ለዚህም በጥፍርዎ ዙሪያ ያለው ቆዳ ጤናማና ለስላሳ ሆኖ እንዲቀጥል ፣ እንዳይላጥ/እንዳይሰነጣጠቅ የሚከተሉትን 5 የዕለት ተዕለት ልማዶች ያዘውትሩ፦
1. እጅዎን በሳሙናና በንጹህ ውሃ ይታጠቡ። በጥፍሩ ዙሪያ ያለውን ቦታ በቀስታ ያጽዱ።
2. ቆዳውን አይጎትቱ፤ በጥርስም አይንከሱት። ይህ ቁስሉን ሊያሰፋና ለኢንፌክሽን ሊያጋልጥ ይችላል።
3. ተለይቶ የወጣውን ቆዳ ብቻ በጥንቃቄ ይቁረጡ። ቆዳው በቀላሉ የሚለይ ከሆነ፤ ንጹህ የጥፍር መቁረጫ በመጠቀም የተንጠለጠለውን ክፍል ብቻ ይቁረጡ። ቆዳው ከሥሩ ከተያያዘ፣ እየደማ ከሆነ፣ ወይም እጅግ ከሚያም ከሆነ አይቁረጡት።
4. ቆዳውን ከመድረቅ ይጠብቁ። ቫዝሊን ወይም ሽታ የሌለው የቆዳ ክሬም ይጠቀሙ። ክፍት ቁስል ካለ፤ በንጹህ ፕላስተር ይሸፍኑት።
5. የኢንፌክሽን ምልክቶችን ይከታተሉ። መቅላትና ማበጥ ከታየ፣ ሕመም እየጨመረ ከሄደ፣ ወይም መግል ከታየ የጤና ባለሙያን ያማክሩ።




Comments