top of page

የዝሆኔ በሽታ ምንድነው? እንዴት ይከሰታል? መከላከያ መንገዶቹስ

ብዙዎች ከእርግማን ጋር ያያይዙታል! አንዳንዶች ደግሞ.... ከመጥፎ መናፍስት


ይህ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ፤ የሰውነት ገጽታቸው ከመለወጡም ባሻገር ፤ ብዙ ጊዜ ከማህበረሰብ የተገለሉ ናቸው። በጀርባቸው ሰዎች ይንሾካሾካሉ።



ከተፈጥሮ እና ከዘር ጋር የሚያይዙትም ጥቂቶች አይደሉም። ሆኖም በሽታው ከውልደት በኋላ የሚመጣ፤ ገሀድ ያለ ለውጥ እስኪያሳይ ድረስ አመታት የሚፈጅ ነው። ከትንኝ ንክሻ እስከ ካንሰር ፤ ይህንን በሽታ ሊያመጡት ይችላሉ።


ዛሬ የምናነሳው በሐሩራማ የአለም ክፍል በስፋት የተሰራጨው ፤ በአገራችን ኢትዮጵያም ደግሞ ከአንድ ሚሊየን በላይ ሰዎችን ስለሚያጠቃው የዝሆኔ በሽታ ነው።


ይህ በሽታ በአብዛኛው ጊዜ አስቀድሞ መከላከል ቢቻልም ፤ በብዙኃኑ ዘንድ ባለ የተሳሳተ አረዳድ ፤ በሽታው አሰቃቂ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል።


ስለ በሽታው በጥልቅ እንመልከት።


🌍 የዝሆኔ በሽታ በትክክል ምንድን ነው?


የዝሆኔ በሽታን የሚያሳይ ምስል፡ በቀኝ በኩል የዝሆኔ በሽታን የሚያመጣው የፊላርያ ትል ይታያል
የዝሆኔ በሽታን የሚያሳይ ምስል፡ በቀኝ በኩል የዝሆኔ በሽታን የሚያመጣው የፊላርያ ትል ይታያል

የዝሆኔ በሽታ (elephantiasis) በራሱ ገዳይ አይደለም። ይልቁንም የሰውነታችን የንፍፊት ሥርዓት (lymphatic system) ላይ ለረጅም ጊዜ በሚደርስ ከፍተኛ ጉዳት ምክንያት የሚመጣ፤ የመጨረሻውና የከፋው የሕመም ደረጃ ነው።


ይህ አደገኛ ጉዳት ሲከሰት አንድ የአካል ክፍል—በተለይም እግር፣ እጅ፣ ጡት፣ ወይም የወንድ የዘር ፍሬ ከረጢት—በቋሚነት እንዲያብጥ፤ እንዲወፍር፤ እንዲሁም እንዲጠነክር ያደርጋል። ብዙዎች ባያውቁትም፦

አዎ! የወንድ የዘር ፍሬ እና የሴት ልጅ ጡትን ሊያጠቃ ይችላል።

እነኝህ የሊምፋቲክ ፊላሪያሲስ ሥር የሰደዱና በጣም የተለመዱ ምልክቶች ውስጥ ነው።


በበሽታው ምክንያት የተጠቃው አካባቢ ያለው ቆዳ ቀስ በቀስ እየሻከረ፣ እየደረቀና፣ እየደደረ በመሄድ ሙሉ በሙሉ የዝሆንን ቆዳ ይመስላል። በሽታው ይህንን ታዋቂ ስያሜውን ያገኘውም፤ ከዚህ ባህሪው በመነሳት ነው።


እንዲህ ከማጋጠሙ በፊት ያለው የንፍፊት ሥርዓት መቋረጥ እና የፈሳሽ መከማቸት ሕመም 'ሊምፌዴማ' (lymphedema) ተብሎ ይጠራል። በኋላ ላይ ቆዳው ከመጠን በላይ ወፍሮ፣ ጠንክሮና ተለውጦ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ሲደርስ በተለምዶ 'የዝሆኔ በሽታ' (elephantiasis) ይሰኛል።


🦟 መንስኤው ምንድን ነው?



በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዚህ በሽታ መከሰት ግንባር ቀደሙ እና ዋነኛው ተላላፊ መንስኤ 'ሊምፋቲክ ፊላሪያሲስ' (lymphatic filariasis) የተሰኘው ሕመም ነው። ይህ ሕመም በደም ውስጥ በሚዘዋወሩ፣ በአይን በማይታዩ ደቃቅ ክር መሰል ጥገኛ ትላትሎች አማካኝነት የሚመጣ ሲሆን፤ ትላትሎቹ ወደ ሰውነታችን የሚገቡት ደግሞ በትንኝ ንክሻ ነው። በሽታውን ሊያመጡ የሚችሉ የተለያዩ የተህዋስያን ዝርያዎች ቢኖሩም፤ ከፍተኛውን እና ቀዳሚውን ድርሻ የሚወስደው ግን 'ዉቸሬሪያ ባንክሮፍቲ' (Wuchereria bancrofti) የተሰኘው የትል ዝርያ ነው።


እነዚህ ጥገኛ ትላትሎች በሽታው ካለበት ሰው ወደ ጤነኛ ሰው የሚተላለፉት፤ ትንኞች በሚያደርጉት ተደጋጋሚ ንክሻ አማካኝነት ነው።

አብዛኛውን ጊዜ አንድ ነጠላ የትንኝ ንክሻ ብቻ፤ ለዝሆኔ በሽታ አይዳርግም።

ለረጅም ጊዜ በተደጋጋሚ ለትንኝ ንክሻ መጋለጥ ግን፤ ትላትሎቹ የንፍፊት ዝውውርን ቀስ በቀስ እንዲያበላሹት ሰፊ ዕድል ይሰጣቸዋል።


🔬ይህንን ጉዳት የሚያደርሱት እንዴት ነው?


በበሽታው የተበከለች ትንኝ ሰውን በሚነክስበት ቅጽበት፤ በአይን የማይታዩ ጥቃቅን የትላትል እጮችን ወደ ቆዳ ውስጥ ታስገባለች። እነዚህ እጮች ከቆዳ ስር በመነሳት በቀጥታ ወደ ንፍፊት ሥርዓት (lymphatic system) ይጓዛሉ።


ንፍፊት ውስጥ የተጠራቀመ የፊላርያ ትል
ንፍፊት ውስጥ የተጠራቀመ የፊላርያ ትል

ንፍፊት ሥርዓት ውስጥ እንደደረሱም እዚያው አድገው ይጎለምሳሉ። እነዚህ ትላትሎች በሰውነታችን ውስጥ ከ5 እስከ 8 ዓመታት፤ አንዳንዴም ከዚያ በላይ በሕይወት የመኖር አቅም አላቸው። በዚህ ረጅም የሕይወት ዘመናቸው ውስጥ መደበኛውን የሊምፍ ፈሳሽ ዝውውር ሙሉ በሙሉ ያውኩታል። በሚያደርሱትም ተከታታይ ጥቃት ምክንያት ተደጋጋሚ የሰውነት መቆጣትንና መቅላትን በመፍጠር የንፍፊት ቧንቧዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ያበላሻሉ።


ሆኖም ግን በዝሆኔ በሽታ ከፍተኛ የአካል ጉዳት የሚደርሰው ፤ በትላትሎቹ ቀጥተኛ ጥቃት ብቻ አይደለም። ይልቁንም የራሳችን የሰውነት በሽታ መከላከያ ሥርዓት ጥገኞቹን ለማጥፋት በሚሰጠው ከባድ አጸፋዊ ምላሽ ጭምር ነው። ከዚህም በተጨማሪ የንፍፊት ሥርዓቱ በመጎዳቱና ፈሳሽ በመቆሙ ምክንያት የሚከሰቱ ተደጋጋሚ የባክቴሪያ ኢንፌክሽኖች ለቆዳው መሻከርና ለበሽታው መባባስ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።


⚠️ ትላትሉ ያለበት ሰው ሁሉ የዝሆኔ በሽታ ይይዘዋል?

አስገራሚው እውነታ ይሄ ነው፣ አይይዘውም!

እንደውም በኢንፌክሽኑ ከተያዙት ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ግልጽ የሆነ እብጠት በጭራሽ አይታይባቸውም። ሌሎች ደግሞ ለዓመታት ምንም ዓይነት ምልክት ሳይታይባቸው ይቆያሉ። በመጨረሻም ወደ ከፋ የንፍፊት እብጠት አልያም የዘር ፍሬ ከረጢት ማበጥ (hydrocele) ደረጃ ላይ የሚደርሱት የተወሰኑት ብቻ ናቸው።



❗ የዝሆኔ በሽታ ሁልጊዜ በጥገኛ ትላትል ብቻ አይመጣም


ይህ በጣም ወሳኝ የሆነ እውነታ ነው!

ምንም እንኳን 'ሊምፋቲክ ፊላሪያሲስ' በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት የሚታወቅ መንስኤ ቢሆንም፤ የሊምፍ ፈሳሽ ዝውውርን የሚያስተጓጉሉ ሌሎች በርካታ ሕመሞችም ለዝሆኔ በሽታ ሊዳርጉ ይችላሉ።


ለምሳሌ የንፍፊት ቧንቧዎችን ወይም እጢዎችን የሚያጠቃ ካንሰር፤ የንፍፊት እጢዎችን የማስወገጃ የቀዶ ሕክምና፤ የጨረር ሕክምና (Radiation therapy)፤ ከባድና ተደጋጋሚ የባክቴሪያ ኢንፌክሽኖች፤ ከውልደት ጀምሮ የሚከተሉ የሊምፍ ሥርዓት ችግሮች፤ እንዲሁም ዘላቂና ከፍተኛ አካላዊ አደጋ ወይም ስብራት ለዚህ ሕመም መከሰት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ከእነዚህም በተጨማሪ ያለ ጫማ ለረጅም ጊዜ በመራመድ የሚመጣው ‘ፖዶኮኒዮሲስም’ (podoconiosis) ሌላው ዋነኛ መንስኤ ነው።


የሕክምናው ዓይነት የሚወሰነው ፤ በሽታውን ባመጣው መሠረታዊ መንሥኤ ላይ ተመስርቶ ነው።

👣 ቀዳሚ ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?


የዝሆኔ በሽታ በአካል ላይ በግልጽ ተለይቶ ከመታየቱ በፊት፤ ሕመምተኞች በርካታ ቀደምት ምልክቶችን ሊያስተውሉ ይችላሉ። ከእነዚህም መካከል፦

የዝሆኔ በሽታ እየጀመራት ያለች ወጣት እግሮች
የዝሆኔ በሽታ እየጀመራት ያለች ወጣት እግሮች

✅ ተደጋጋሚ ትኩሳት፣

✅ ማንቀጥቀጥ፣

✅ የሚያም የንፍፊት እጢዎች እብጠት፤

✅ የሚያም የንፍፊት ቧንቧዎች መቅላት፤

✅ እየመጣ መልሶ የሚጠፋ እብጠት ።


በአንጻሩ ደግሞ፤ አንዳንድ ሰዎች ምንም ዓይነት የሕመም ስሜት ላይታይባቸው ይችላል። ይሄም ለዓመታት ሊቆይ ይችላል።


🚨 በኋላስ ምን ይከሰታል?

የንፍፊት ሥርዓት ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ ሲሄድ፤ ቀደም ሲል እየጠፋ ይመጣ የነበረው እብጠት ሙሉ በሙሉ ቋሚ እየሆነ ይመጣል። የተጠቃው አካልም ቀስ በቀስ መጠኑ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይሄዳል። በዚህ ሂደት ውስጥም ቆዳው ይወፍራል፤ ይደርቃል፤ ይጠነክራል፤ ይሻክራል፤ ይታጠፋል፤ እንዲሁም ለመታጠብና ለመንከባከብ እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል።


በሽታው የላቀ ደረጃ ላይ ሲደርስ፦

  • መራመድ እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል።

  • ልብሶች ከእንግዲህ ልክ ሊሆኑ አይችሉም፤ ይጠባሉ።

  • ጫማ ማድረግ ፈጽሞ የማይታሰብ ይሆናል።

  • ዕለታዊ ተግባራትን ማከናወን ይዳግታል።


የዝሆኔ በሽታ መንስኤዎች በኢትዮጵያ


በኢትዮጵያ የዝሆኔ በሽታ ዋነኛ መንስኤዎች ውስጥ ተጠቃሽ የሚሆኑት ሁለት ናቸው።


አንደኛው ቀደም ሲል ያነሳነው በትንኝ ንክሻ የሚመጣው የሊምፋቲክ ፊላርያሲስ በሽታ ሲሆን፤ ይህም በቆላማ አከባቢዎች ላይ በብዛት ይታያል። የሚመለከታቸውም ባለድርሻ አካላት ይህንን በሽታ ለማጥፋትና የትንኟን ቁጥጥር ለማድረግ በአሁኑ ወቅት እየተረባረቡ ይገኛሉ።


ሌላኛው እና በሀገራችን በስፋት የሚታወቀው መንስኤ ደግሞ ፖዶኮኒዮሲስ (podoconiosis) ነው። ፖዶኮኒዮሲስ በጥገኛ ትላትል ወይም በትንኝ ንክሻ የሚመጣ አይደለም። ለዚህ በሽታ በተፈጥሮአቸው ተጋላጭ ያላቸው ሰዎች አሉ። እነኝህ ሰዎች ማእድናት በብዛት ያሉት ቀይ አፈር (እሳተ ገሞራማ አፈር) ላይ ለበርካታ ዓመታት ያለ ጫማ ሲራመዱ ይከሰታል።



ይህ በሽታ ከሊምፋቲክ ፊላርያሲስ በተለየ መልኩ በዋነኝነት ሁለቱንም የታችኛውን የእግር ክፍሎች እኩል ያጠቃል። በኢትዮጵያም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን እንደሚያጠቃ ይገመታል። አብዛኞቹም ታካሚዎች የሚገኙትበደጋማ የኢትዮጵያ ክፍል ነው። በተለይም በሽታው በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በምዕራብ ኢትዮጵያ፣ እንዲሁም በአማራ ክልሎች ውስጥ ከፍተኛ ስርጭት አለው። በዚህም ምክንያት በእነኝህ አከባቢዎች በግብርና የሚተዳደሩ ሰዎች ለበሽታው ያላቸው ተጋላጭነት እጅግ ከፍ ያለ ነው።


💊 የዝሆኔ በሽታ ይታከማል?

አዎ ይታከማል! ነገር ግን ሕክምናው የሚወሰነው በሽታው ባለበት ደረጃ ላይ ነው።

የፊላሪያ ኢንፌክሽን መኖሩ በምርመራ ከተረጋገጠ፤ ጥገኛ ትላትሎቹን ለማጥፋት በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ መመሪያዎች የተመከሩ የፀረ-ጥገኛ መድኃኒቶች ሊሰጡ ይችላሉ። እነኝህ መድኃኒቶች ትላትሉን በመግደል፤ ከዚህ በኋላ የሚደርሰውን ተጨማሪ ጉዳት ይከላከላሉ። ሆኖም ግን ቀደም ሲል በንፍፊት ሥርዓት ላይ የደረሰውን ዘላቂ የአካል ጉዳት መቀልበስ አይችሉም።


ሥር የሰደደ የሊምፍ እብጠት ላለባቸው ሰዎች፤ ሕክምናው ትኩረት የሚያደርገው የሰውነትን ተግባር ማሻሻልና በሽታው እንዳይባባስ መግታት ላይ ነው። ለዚህም የሚከተሉትን እንዲያደርጉ ይመከራል!


✔ የተጎዳውን አካል በየቀኑ በጥንቃቄ መታጠብ፣

✔ ቆዳን በቅባት ማለስለስ፣

✔ ትናንሽ ቁስሎችን በፍጥነት ማከም፣

✔ የንፍፊት ፈሳሽ ዝውውርን የሚያነቃቁ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ፣

✔ ምቹ በሆነ ሁኔታ እግርን ከፍ አድርጎ መስቀል፣

✔ የባክቴሪያ ኢንፌክሽኖችን በአፋጣኝ ማከም ይመከራል።


 ከእነዚህም በተጨማሪ ለተመረጡ ታካሚዎች እብጠቱን ለመቀነስ ጫና የሚያሳድሩ ልዩ ሕክምናዎችና፣ ጠባብ ታይቶች (compression therapy) ሊታዘዙ ይችላሉ።


የዘር ፍሬ ማበጥ (hydrocele) ላለባቸው ወንዶች፤ ቀዶ ጥገና በአብዛኛው ብቸኛው አስተማማኝና ዘላቂው የሕክምና መፍትሔ ነው።


🚶 ሕመምተኞች መደበኛ ሕይወት መምራት ይችላሉ?

በትክክል ይችላሉ!

በርካታ ሕመምተኞች ቀጣይነት ያለው የራስ-እንክባካቤ በማድረግ የሕይወት ጥራታቸውን በከፍተኛ ደረጃ ማሻሻል ይችላሉ። ይህም በጥናቶች የተደገፈ ነው።


🛡 የዝሆኔ በሽታን መከላከል ይቻላል?

አዎ!

በትንኝ ንክሻ ለሚመጣው የሊምፋቲክ ፊላሪያሲስ ሕመም መከላከያ ዘዴዎች፦

  • በፀረ-ተባይ የተነከሩ የአልጋ አጎበሮችን ተጠቅሞ መተኛት፣

  • የትንኝ መራቢያ ቦታዎችን ማጥፋት፣

  • በማኅበረሰብ ደረጃ የሚሰጡ የጅምላ መድኃኒት እደላ ፕሮግራሞች ላይ በንቃት መሳተፍ፣

  • ዘላቂ እብጠት ካስተዋሉ በአፋጣኝ የሕክምና እርዳታ መፈለግ ይመከራል።

ከአፈር ንክኪ ለሚመጣው የፖዶኮኒዮሲስ ሕመም ደግሞ፦

ፖዶኮኒዮሲስን በሚከተሉት መንገዶች ሙሉ በሙሉ መከላከል ይቻላል፦

  • መከላከያ ጫማዎችን በቋሚነት ማድረግ፣

  • እግርን በየቀኑ በሳሙናና በንጹህ ውሃ መታጠብ፣

  • ጥቃቅን የቆዳ መቆሳሰሎችን ወዲያውኑ መንከባከብ፣

  • የደረቀ ቆዳን እንዲለሰልስ ቅባት በመቀባት፣

  • እንዲሁም እብጠት በሚጀምርበት ጊዜ ቀድሞ ወደ ሕክምና በመሄድ መከላከል ይቻላል።


ከማጋጠሙ በፊት ይከላከሉ! ለጤናዎ ቦታ ይስጡ!



Comments


bottom of page