🦷 ጥርስ በተፈጥሮው ነጭ አይደለም!
- Zebeaman Tibebu
- Feb 2
- 5 min read
Updated: Feb 3
ጥርሶችዎ ምን ይመስላሉ? እንደ ሀጫ በረዶ የነጹ ናቸው ወይስ እንደ ጥጥ ባተሎ መለስተኛ? ወይስ ነትበዋል?
በቴሌቭዝን መስታወት እንደለመድናቸው ማስታወቂያዎች ፤ ጥርስዎ ፈጽሞ ካልነጻ ፈገግታዎ ጎዶሎ ነው።

እርስዎስ ምን ያስባሉ? እውነት ወይስ ሐሰት?
ጥርስ በተፈጥሮው ነጭ አይደለም!
ይህም የተለመደ ነው። ከህክምና አንፃር የየትኛውም ሰው ጥርስ ፈጽሞ ነጭ አይደለም ።
ይህንን ለመረዳት የጥርስን አካላት ማየት ያስፈልጋል። ጥርስ በተፈጥሮው ሶስት አካላት አሉት።

ኢናሜል(Enamel) - የጥርስ መስታወት ሲሆን፤ የጥርስ ውጫዊ ክፍል ነው።
ዴንቲን(Dentin) - ይህ ከጥርስ መስታወት ስር ያለ ሲሆን በተፈጥሮ መለስተኛ ቢጫ ቀለም አለው።
ፐልፕ(pulp)- ይህ የጥርስ ስጋ ሲሆን ውስጡ ደምስሮች እና ነርቮች ይገኛሉ። ይህ በደንቲን የተከለለ ሲሆን ፤ በጥርስ እምብርት ውስጥ ይገኛል። ለዚህም አይታይም።
ኢናሜል በተፈጥሮው የመስታወት ባህሪ ስላለው ፤ የጥርስን የታችኛው ክፍል በከፊል ያሳየናል። ለዚህም ጥርስ ሲመለከቱ በኢናሜል አሻግረው ቢጫውን ደንቲን ነጸብራቅ ነው የሚያዩት።
➡️ ለዚህም ኢናሜል ከሳሳ ጥርስ ይበልጡኑ ቢጫ ቀለም ኖሮት ሊስተዋል ይችላል።
➡️ ኢናሜል ወፍራም ከሆነ ጥርስ ወደ ነጭ የተጠጋ ቢጫ መልክ ይኖረዋል።
ለዚህ ሀጫ በረዶ የመሰለ ጥርስ ፤ ህክምናዊ እውነታ አይደለም።
እንደውም ጥርሶች ነጭ ሆነው ፤ ሊቦረቦሩ ፣ ሊበሰብሱ፣ እንዲሁም በኬሚካል የተጎዱ ሊሆኑ ይችላሉ። በተቃራኒውም ጥርሶች ነጭ ሳይሆኑ ፤ ጤናማ ሊሆኑ ይችላሉ።

የጥርስ ጤና የሚመዘነው ፤
በጥርስ መስታወት ጥንካሬ ፣
ጥርስ ላይ ቆሻሻ ክምችት/አንኳር ባለመኖር፣
ጥርስ መቦርቦር ባለመኖር ፣
ጥርስ በጤናማ ደረጃ ማኘክ በመቻሉ፣
ሙቀትና ቅዝቅዜን በመቻሉ፣
ድድ ጤናማ በመሆኑ፣
እንዲሁም ኢንፌክሽን ባለመኖሩ ነው።
ታድያ ስለጥርስ ቀለም ምን አሳሳበን?
የጥርስ ቀለም ብዙ ጊዜ ላይ የጥርስ ንጽህና አመላካች ሊሆን ይችላል። ይህ ደግም ከጥርስ መቦርቦርና ኢንፌክሽን፣ እስከ ድድ መቆጣት ድረስ ሊያስከትል ይችላል።
የጥርስ ቀለም ለውጥ የምንለው ምንድነው?
ጥርስ ከተፈጥሮ መልኩ በተለያዩ ምክንያቶች ሲቀየር ፤ የጥርስ ቀለም ተለወጠ እንላለን። ይህም የቀለም ለውጥ የጥርስን መስታወትን ብቻ ሲነካ እና እስከ ደንቲን ሲደርስ ልዩነት አለው።

የውጭ የቀለም ለውጥ የቀለም ነጠብጣቦች የጥርስ መስታወት ላይ ሲያርፉ ይፈጠራል። በውጭ በኩል ስላለ ለማስለቀቅ ቀላል ነው። በጥርስ ብሩሽ ብቻ በቀላሉ ሊጸዳ ይችላል። ይህም በቡና ፣ በሻይ ፣ በሲጋራ፣ በምግብ ቀለሞች እንዲሁም በጥርስ ንጽህና ጉድለት ሊከሰት ይችላል።
የጥርስ መስታወትን አልፎ ፤ ቀለሙ እስከ ጥርስ ውስጠኛ ክፍል ከደረሰ ግን ፤ በጥርስ ብሩሽ ማስወገድ ያዳግታል። ይህም በእድሜ በሚመጡ ለውጦች ፣ በልጅነት ዘመን ለከፍተኛ ፍሎራይድ በመጋለጥ፣ በልጅነት ዘመን በሚወሰዱ አንዳንድ መድሀኒቶች ሊከሰት ይችላል። የጥርስ ውስጣዊ ክፍል ላይ ያለ ደም መፍሰስም ይህን ሊያመጣ ይችላል። ሆኖም ግን አንዳንዶቹ ዘላቂ ናቸው። እነኝህን ቀለሞች ለማጽዳት የጤና ባለሙያ ያማክሩ።
የጥርስ ቀለም ለውጥ መንስኤዎች
ከዓለም ህዝብ መሀል ከ 60-75% የሚሆኑት አዋቂዎች የጥርስ ቀለማቸው ከተፈጥሮው ለውጥ እንዳለው መረጃዎች ይጠቁማሉ። በአገራችን በኢትዮጵያም ይህ እንዲኖር ከሚያደርጉ ምክንያቶች መሀከል የሚከተሉት ይገኙበታል።

ቡና እና ሻይ አብዝቶ መጠጣት
ቡናም ሻይም በውስጣቸው የሚያቀልሙ ኬሚካሎች (ወይም ክሮሞጅንስ / chromogens) አላቸው። በተለይም ታኒን (Tanin) የሚባለው ውህድ የጥርስ መስታወትን (enamel) መልክ ወደ ቢጫ እና ቡናማ ይለውጣል።
በተለይ በኢትዮጵያ የምንጠጣው ሻይ ቅጠል ፤ በልዩ ስሙ ጥቁር ሻይ (black tea) ሲባል ፤ በውስጡ ይህን ውህድ በከፍተኛ መጠን ይዟል። ለዚህም ሻይ መጠጣት ከቡና በላይ ጥርስን አብዝቶ ያቀልማል።
ከዚህም ባሻገር ሁለቱም መጠነኛ አሲዳማነት ስላላቸው ፤ የጥርስን መስታወት ያሳሳሉ። የሳሳውም የጥርስ መስታወት በቀላሉ ይቦረቦራል።

ጫት መቃም
አብዛኞቻችን እንደምናስተውለው ፤ ረዥም ጊዜ ጫት የሚቅሙ ሰዎች ጥርሳቸው ነትቦ ይስተዋላል።
ይህም በአንድ በኩል ታኒን የሚባለው ውህድ ጫት ውስጥ በመገኝቱ እንዲሁም በጫት አሲዳማነት ይመጣል።
ከዚህም ባሻገር ጫት የምራቅን መጠን ስለሚቀንስ አፍን ያደርቃል። ይህም የጥርስ ንጽህናን ያስተጓጉላል። እዚህ ላይ ጫት ጋር የሚወሰዱ ጣፋጭ መጠጦች ፣ ስኳር ፣ እንዲሁም አቾሎኒ ጥርስን ይብሱኑ ያቆሽሻሉ። እነሱን የሚመገቡት ባክቴሪያዎች ደግሞ ጥርስን ይቦረቡራሉ።

ሲጋራ ማጨስ
ሲጋራ በውስጡ ካሉ ኬሚካሎች መካከል ጥርስ ላይ በይበልጥ ጉዳት የሚያደርሱት ሁለት ናቸው። እነኝህም ኒኮቲን (Nicotine) እና ታር (Tar) ይሰኛሉ። ሁለቱ የጥርስን መስታወትን ያሻክራሉ። ለዚህም ሌሎች ቀለሞች ጥርስ ላይ በቀላሉ እንዲቀሩ እድል ይፈጥራል።
ኒኮቲን መልክ አልባ ቢሆንም ፤ ከ አየር (ኦክስጅን) ጋር ሲገናኝ ቢጫ ይሆናል። የጥርስን መስታወት አልፎ ገብቶ ፤ የጥርስን ቀለም ወደ ቢጫ አልያም ቡናማ ቀለም ሊለውጥ ይችላል። ደም ስርንም ስለሚያጠብ ፤ የጥርስ መበስበስን ያፋጥናል።
ታር በበኩሉ ከኒኮቲን በላይ የጥርስን ቀለም ይለውጣል። የጥርስ መስታወት ላይ እንደ ጥላሸት የጠቆሩ ፤ በብሩሽ ለማስለቀቅ የሚያስቸግሩ ቀለማትን ይተዋል። የጥርስ ጉዳትም እንዲፋጠን ያደርጋል።

ፍሎራይድ የበዛበት የከርሰምድር ውሀ የሚጠቀሙ ማህበረሰቦች
የመጠጥ ውሀ ውስጡ ያለው የፍሎራይድ መጠን ከ 1.5 ppm በላይ ከሆነ ፤ የጥርስ አመሰራረት ላይ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል። ይህም የፍሎራይድ መጠን ጥርስን የሚሰሩትን አሚዮብላስት(ameoblasts) የሚባሉትን ህዋሳት ያሰናክላል። ለዚህም ጥርስ አመሰራረቱ ይለወጣል።
ይህም ጥርሳቸው መብቀል የጀመረ ፤ ከ 8 አመት በታች ያሉ ልጆችን ያጠቃል። በህጻንነታቸው ፍሎራይድ የበዛበት ውሀ ሲጠጡ ያደጉ ህጻናት ጥርሳቸው ቀለሙም ቢጫ፣ ቡናማ ወይም ጥቁር ሊመስል ይችላል። ለውጡም ቋሚ/ዘላቂ ነው።
ለዚህም ቀዳሚ ምሳሌ የሚሆኑት የናዝሬት ተወላጆች ናቸው።

ጣፋጭ እና የታሸጉ ምግቦችን መመገብ
እነኝህ በውስጣቸው ለመፈጨት ቀላል የሆኑ ስኳሮችን ( ካርቦሃይድሬቶችን ) ይይዛሉ። አብዝተው ሲመገቧቸው ፤ ከእርሶ ባሻገር ለጥርስ ባክቴሪያዎች ምግብ ይሆናሉ። ተመግብው አቅማቸው የበረታው እነኝህ ባክቴሪያዎችም ፤ የሚያመርቱት አሲድ ጥርስን ያሳሳል።
ለዚህም እነኝህ ምግቦች ጥርስን ያቆሽሻሉ ፤ መስታወቱን ያሳሳሉ ፤ ቀለሙን ይለውጣሉ። እንዲሁም ጥርስን እንዲበሰብስ አልያም እንዲቦረቦር እድል ይሰጣሉ።

ጥርስን ንጽህና በአግባቡ አለመጠቀም
የጥርስን ንጽህና በአግባቡ አለመጠበቅ ጉዳት አለው። ጥርስ ላይ ቆሻሻ እንዲከማች ፤ ጥርስን የሚያዳክሙ ባክቴሪያዎች እንዲበራከቱ ያደርጋል። ይህም ጥርስዎ ጥርስዎ እንዲቦረቦር እድል ይከፍታል።
ታድያ ለምንድነው ጥርሳችንን እስክንታመም ፤ የጥርስ ሐኪም የማናየው?
ጥርስን ወደ ተፈጥሮ ንጻቱ መመለሻ አማራጮች
ጥርስ ከጤማናነት ባሻገር ፤ የውብት መገለጫ ነው። ከማንነት ጋር ቁርኝትም ስላለው ፤ ብዙዎች ጥርሳቸውን ወደ ተፈጥሮ ንጻቱ ለመለለስ ሲሞክሩ ይታያሉ። አንዳንዶች ከሰው በሰሙት ጥርሳቸውን አደጋ ላይ የሚጥሉ አማራጮች ሲጠቀሙ ፤ ሌሎች ደግሞ አስፈላጊውን እንክብካቤ ሲያደርጉ ይስተዋላል።
ጥርስን ንጻት ለመመለስ በማህበረሰባችን ውስጥ ከሚደረጉ አማራጮች ጥቂቱን እንመልከት።

1. የጥርስ ብሩሽ እና ሳሙና
ይህ የጥርስን የመስታወት ግድግዳ ማጽጃ ፤ መጥረጊያ ነው። ቆሻሻን ያስወግዳል። ነጠብጣቦችን ያጸዳል።
የጥርስ ሳሙናዎች በውስጣቸው ብዙ አይነት ኬሚካል አላቸው። ከዚህም ውስጥ ፍሎራይድ የጥርስ መስታወትን ያጠናክራል። ፀረ-ባክቴሪያ ውህዶች ደግሞ ጥርስን የሚጎዱትን ባክቴሪያዎችን ያጠፋሉ።
ጥናቶችም ይህን ይደግፋሉ!
በቀን ሁለት ጊዜ መቦረሽ የጥርስ ቆሻሻን በእጅጉ ይቀንሳል።
የጥርስ ሳሙና አዘውትሮ መጠቀም ፤ ጥርስ መስታወት ላይ ያሉ የቀለም ለውጦችን ከ15-30% ይቀንሳል።
ፍሎራይድ ያለው የጥርስ ሳሙና መጠቀም ደግሞ ፤ የጥርስ መቦርቦርን እስከ 40% ይቀንሳል።
ታድያ ግን ለጥርስዎ መስታወት ጤና ፤ ከጠንካራ ብሩሾች ለስላሳ ብሩሾችን እንዲመርጡ ይመከራል።
የጥርስ ሳሙናዎች ዋጋቸው ተመጣጣኝ ከመሆኑም ባሻገር ፤ ለእለታዊ አጠቃቀም ምቹ ናቸው። ጥርስን የማንጻት አቅማቸው ግን የተገደበ ነው። ጥርስን የሚያነጹት ቀስ በቀስ ፤ ደጋግሞ በመጠቀም ነው። ቢሆንም ግን ጥርስ ያለበት ጉዳት እንዳይባባስ ይጠብቃሉ።
ለዚህም ተመራጭ ናቸው።

2. ቤኪንግ ሶዳ (Baking Soda)
ጥርስን ለማንጻት ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ፤ ይህን ውህድ ይጠቀማሉ ። ውህዱ በባህሪው ቤዝ ስለሆነ ፤ የጥርስ ባክቴሪያዎች ያመነጩትን አሲድ ይቃወማል። ጥርስንም በጊዜያዊነት ያነጻል።
ችግሩ ግን ይህ ውህድ የጥርስን መስታወት ያሳሳል። ለውጡም ዘላቂ አይደለም። የጥርስን መቦርቦርንም አይቃወምም። ይልቁኑ ጥርስን ለሌላ አደጋ ተጋላጭ ያደርጋል።
ለዚህም በህክምናው ፈጽሞ አይመከርም!

ጥርስን መፋቅ
ጥርስን በተለያዩ አይነት መፋቂያዎች መፋቅ ጠቀሜታ አለው። ጥርስ ላይ የሚከማች ቆሻሻን ወዲያውኑ ለማስወገድ ይጠቅማል። ጥርስም አዲስ ቀለም እንዳያመጣ ይከላከላል። ሆኖም ግን ጥርስ ላይ የሰነበቱ ቀለሞች ለማጥፋት ያዳግተዋል። ለዚህም ለወየበ ጥርስ መፍትሔ አይሆንም።
አንዳንዶች ጥርስን ለማንጻት አብዝተው አልያም በኃይል ሲፍቁ ይስተዋላል። ይህ ደግሞ ፈጽሞ አይመከርም። ለጥርስ ጉዳት አለው። አብዝተው ሲፍቁ የጥርስ መስታወት ሊበሳሳ ይችላል። መስታወቱን ከሳሳ ጥርስ ከመንጻት ይልቅ ፤ ከስር ያለውን የደንቲን ቢጫ ቀለም ይይዛል።
በጤና ባለሙያ የሚደረግ የጥርስ ማጽዳት
ይህ ጥርስ ላይ የተከማቹ ቆሻሻዎችን ፣ አንኳሮችን (calculus) ያስወግዳል። ለመልቀቅ የሚያስቸግሩ የጥርስ ቀለሞችንም ያጸዳል። እንዲሁም የጥርስ መስታወትን አንጸባራቂነት ወደ ነበረበት እንዲመለስ ያደርጋል።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ፤ በዚህ መንገድ እስከ 90% የሚሆነውን የጥርስን ንጻት ወደነበረበት መመለስ ይቻላል።
በጣም ውጤታማ ሲሆን ፤ የድድንም ጤና ያሻሽላል።
ይህም ብዙዎች የማይመርጡት ከሒሳብ አንጻር ነው።
ጥርስን በኬሚካል የማጽዳት ህክምና
ይህ የጥርስን መስታወት ዘልቆ የሚገባ የኬሚካል እጥበት ነው። ለእጥበት ፐርኦክሳይድ የሚባል ውህድ ይጠቀማል። ጥርስን እጅጉን ሊያነጻ ፤ ሀጫ በረዶ ሊያስመስል ይችላል። በዚህ ህክምና የሚያገኙት የንጻት መጠን ፤ በጥርሶችዎ ላይ በተከማቸው ቆሻሻ መጠንና በጥርስዎ መስታወት ውፍረት ላይ የተመሰረተ ነው።

ይህ ህክምና እጅጉን አመርቂ ውጤት ቢያሳይም ፤ ጥርስን ለቀናት ቁጡ (ሙቀትና ቅዝቃዜ የማይችል) ሊያደርግ ይችላል። ድድንም ሊያስቆጣ ይችላል።
የባለሙያም ክትትል ያስፈልገዋል።
አማራጮችዎ እንዲህ ቢሆኑይመረጣል!
ለመከላከልና የጥርስዎን ጤና ለመጠበቅ ፤ በጥርስ ሳሙና በቀን ሁለቴ መቦረሽ ይመረጣል።
መለስተኛ ነጠብጣቦች ለማስለቀቅ ፤ በባለሙያ ጥርስን ማጽዳት ይሻላል።
የማይለቁ ጥልቅ ነጠብጣቦች ካሉ ፤ ጥርስን በባለሙያ በኬሚካል እጥበት ማጽዳት ይችላሉ።





Comments