top of page

እያንዳንዱ ወንድ ሊያውቀው የሚገባው የፕሮስቴት ካንሰር

Aug 20
5 min read

Updated: Aug 20

የጤና ችግር ብዙ ጊዜ በትልቅ ምልክት አይጀምርም.... ቀስ በቀስ፤ እምብዛም ትኩረት በማይስቡ የሰውነት ለውጦች ሊጀምር ይችላል።

በ50ዎቹ ወይም 60ዎቹ ዕድሜው ላይ ያለ አንድ ጎልማሳ ወንድን በምሳሌነት እንውሰድ። በድንገት ማታ ማታ በተደጋጋሚ ለሽንት መነሳት ሲያበዛ፤ ለመቆጣጠር በቀን የሚጠጣውን የውሃ መጠን ቀነሰ። ሆኖም ግን ለውጥ የለውም። ሽንት ሲሽናም የሽንቱ ፍሰት የተዳከመ ነበር። ሽንት መሽናት ለመጀመር ጊዜ ይፈጅበት ጀመር። ሽንት ሸንቶ ጨርሶ ራሱ፤ የቀረ ያለ ይመስለዋል።


ከዚያም ለራሱ

“እያረጀሁ ይሆናል።”

ብሎ አሰበ።

ምንም አሳሳቢ ምልክት ስላላየ ችላ አለው። ለዚህም ቀናት ሳምንታትን ወለዱ፤ ሳምንታት ደግሞ ወራትን ተኩ። ምልክቶቹ ግን እየባሱ እና እየጠነከሩ መጡ። በመጨረሻ ምልክቶቹ ሊታለፍ የማይችል ደረጃ ላይ ሲደርሱ ወደ ሕክምና ተቋም አመራ።


በሰማውና ጓደኞቹ በነገሩት መነሻነት፣ የፕሮስቴት እጢ ማበጥ (BPH) ሳይሆን አይቀርም ብሎ ገመተ።


እርግጥ ነው....

...በአብዛኛው የሽንት መቆራረጥ የፕሮስቴት እጢ ማደግ ምልክት ሊሆን ይችላል።


ነገር ግን የዚህ ሰው የአልትራሳውንድ እና የላብራቶሪ ምርመራ ውጤት ፍጹም የተለየ ሆነ፤ የፕሮስቴት ካንሰር። ይባስ ብሎ ደግሞ ካንሰሩ ወደ አቅራቢያው አካላት ተሰራጭቷል።


ይህ በሀገራችን በብዙ ወንዶች ላይ የሚደገም እውነተኛ እና ልብ ሰባሪ ታሪክ ነው። በኢትዮጵያ አብዛኛው የፕሮስቴት ካንሰር ታማሚ ወደ ሕክምና የሚመጣው በጣም ከረፈደ እና የበሽታው ደረጃ ከፍ ካለ በኋላ ነው።


ታዲያ ወንዶች ምን ማድረግ አለባቸው? የሽንት ችግር ሁልጊዜ ከፕሮስቴት ጋር የተያያዘ ነው? ካንሰሩን ቀድሞ እንዴት መለየት ይቻላል? ይህንን በደንብ ለመረዳት መጀመሪያ ፕሮስቴት ምን እንደሆነ እንወቅ።


ፕሮስቴት ምንድነው?


ፕሮስቴት በወንዶች ላይ ብቻ የሚገኝ፤ የለውዝ ፍሬ ያህል መጠን ያለው ትንሽ እጢ ነው። የሚገኘውም ከሽንት ፊኛ በታች ሲሆን፤ ከፊኛ ሽንትን ወደ ውጭ የሚያስወጣውን የሽንት መስመር (Urethra) በከፊል ከብቦት ይኖራል። የወንድ የዘር ፈሳሽን ከሚያመነጩ አክላት መሃል አንዱ ነው።


ታድያ ፕሮስቴት ካንሰር ምንድነው?

የፕሮስቲት እጢ ህዋሳት  ተፈጥሯዊ ባህሪያቸውን ቀይረው የካንሰር ባህሪ ማሳየት ሲጀምሩ በሽታው ይከሰታል። በዚህ ጊዜ እነዚህ ሕዋሳት ያለ አግባብና ያለ ቁጥጥር በማደግ የፕሮስቴትን መደበኛ ሥራ ከማሰናከላቸውም በላይ፣ አቅም አግኝተው ወደ አቅራቢያ አካላት ሊሰራጩ ይችላሉ።


ሆኖም ግን ማወቅ ያለብን አንድ ትልቅ እውነት አለ። ሁሉም የፕሮስቴት ካንሰር አንድ ዓይነት አይደለም። የካንሰሩ ዓይነትና ጠባይ የሚወሰነው ከተነሳበት ሕዋስ ተፈጥሮ ላይ ነው። በዚህም ምክንያት አንዳንዶቹ የካንሰር ዓይነቶች በጣም ኃይለኛና በሰውነት ውስጥ በፈጣን የሚስፋፉ ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ደግሞ ለማደግም ሆነ ለመሰራጨት ዓመታትን የሚፈጁ ሊሆኑ ይችላሉ።



የፕሮስቴት መጨመር እና ካንሰር ለምን ይደባለቃሉ?

ብዙ ወንዶችን የሚያሳስብ አንድ ትልቅ ጥያቄ አለ። የፕሮስቴት መጨመር እና የፕሮስቴት ካንሰር ለምን ይደባለቃሉ? ለምንስ አንዱን ከሌላው መለየት እንዲህ ግራ ያጋባል?

ነገሩ እንዲህ ነው...ወንዶች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ፤ በሕክምናው ዓለም የፕሮስቴት እጢ እብጠት ወይም ቢፒኤች (Benign Prostatic Hyperplasia) የሚባል የተለመደ የጤና ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። ይህ በቀላል ቋንቋ፤ የፕሮስቴት እጢ ያለምንም የካንሰር ጠባይ ዝም ብሎ ሲያድግ/ሲያብጥ ነው።

ይህ ፈጽሞ ካንሰር አይደለም፤ ወደ ካንሰርነትም አይቀየርም።

ነገር ግን ዋናው ችግር የሚመጣው እዚህ ጋር ነው። ይህ ተራ የፕሮስቴት የሚያሳያቸው ምልክቶች፤ አስፈሪው የፕሮስቴት ካንሰር መጀመሪያ አካባቢ ከሚያሳያቸው ምልክቶች ጋር አንድ ዓይነት መሆናቸው ነው። እጢው ሲያብጥ፤ መሃል ለመሃል የሚያልፈውን የሽንት ቱቦ ይጫነዋል። በዚህ ምክንያት ከፕሮስቴት ካንሰር ጋር ተመሳሳይ ምልክቶች ያሳያል። ለዚህም በምልክት ብቻ አንዱን ካንዱ ለመለየት አዳጋች ይሆናል።


ስለዚህ ማስተዋል ያለብን ትልቁ ነጥብ፤ እነዚህ ምልክቶች ብቻ ካንሰር መኖሩን ወይም አለመኖሩን ፍንጭ ሊሰጡን አይችሉም።


እርስዎም በሽንትዎ ላይ ለውጥ ሲያዩ “ዕድሜ ያመጣው ጣጣ ነው” ብለው በቸልታ መተውም ሆነ፤ ገና ሳይመረመሩ “ካንሰር ይዞኛል” ብለው መደምደም እና መጨነቅ የለብዎትም። ትክክለኛውና ብቸኛው እርምጃ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ በምርመራ ማረጋገጥ ብቻ ነው።


የፕሮስቴት ካንሰር ምልክቶች

እላይ እንደገለጽነው፤ መጀመሪያ አካባቢ የሚታዩት ምልክቶች ልክ እንደ እጢ ማበጡ ሁሉ ከሽንት ጋር የተያያዙ ናቸው።

  • ሽንት ለመጀመር መቸገር፣

  • የሽንት ፍሰት መዳከም ወይም መቆራረጥ፣

  • በቀን ውስጥ በተደጋጋሚ ሽንት መምጣት፣

  • በሌሊት እንቅልፍን አጥቶ በተደጋጋሚ ሽንት ቤት መመላለስ ፣

  • ሸንተው ጨርሰው እንኳን እንደ ቀረ የሚሰማ ስሜት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ካንሰሩ ይበልጥ እየገፋ ሲሄድ ግን ምልክቶቹ ይለወጣሉ። በሽንት ወይም በዘር ፈሳሽ ውስጥ የደም ቀለም መታየት ይጀምራል። ይባስ ብሎ ደግሞ ካንሰሩ ከእጢው ወጥቶ ወደ አጥንት መሰራጨት ሲጀምር፤ የወገብ፣ የዳሌ ወይም የጭን አካባቢ የማይለቅ፣ የማያቋርጥና ጥልቅ የሆነ ሕመም መሰማት ይጀምራል።


ሐኪሞች የፕሮስቴት ካንሰርን እንዴት ነው በእርግጠኝነት የሚለዩት?

ይህንን ድብቅ በሽታ ለመለየት ሕክምናው ዓለም የጤና ባለሙያዎች የሚከተሉትን ምርመራዎ ሊያደርጉ ይችላሉ።

በመጀመሪያ ምልክቶቹን እና ያለውን የጤና ሁኔታ ያማከሩት ባለሙያ፤ በፊንጢጣ በኩል የፕሮስቴት እጢን ሊመረምር ይችላል። በዚህ ምርመራ ጊዜ ሐኪሙ በፊንጢጣ በኩል ፤ በጣቱ የፕሮስቴትን የፊተኛው ክፍል በመንካት ጥንካሬውን፣ ልስላሴውንና ያልተለመደ እብጠት መኖሩን በጥቂት ሰኮንዶች ሊለይ ይችላል።


ከዚህም ጎን ለጎን ፤ የደም ምርመራ ያስፈልጋል። ሐኪሞች የፒኤስ ኤ(PSA (Prostate-Specific Antigen)) የደም ምርመራ ያዛሉ። ይህ በራሱ በፕሮስቴት እጢ የሚመረት ፕሮቲን ሲሆን፤ በደም ውስጥ መጠኑ በጣም ከፍ ብሎ ከተገኘ በፕሮስቴት ላይ አንድ ችግር (የእጢ ማበጥ፣ ኢንፌክሽን ወይም ካንሰር) መኖሩን ይጠቁማል።

ከዚህም ባሻገር ያላቸውን ጥርጣሬ ለማረጋገጥ ሐኪሞች የፕሮስቴት እጤን እብጠት፣ ቅርጽ እና መጠን የሚያሳዩ የአልትራሳውንድ እና የ ኤም አር አይ ምርመራዎች እንደ አስፈላጊነታቸው ሊያዙ ይችላሉ።


ሆኖም ግን እነዚህ ሁሉ ምርመራዎች፤ ካንሰር ይሁን አይሁን ቢጠቁሙም፤ አያረጋግጡም። ካንሰር መሆን አለመሆኑ የሚረጋገጠው በ ናሙና /ባዮፕሲ (Biopsy)  ምርመራ ብቻ ነው።


በሽታውን ለመከላከል ቅድመ ምርመራ ማድረግ ይቻል ይሆን?

ምላሹ አዎ ነው።

ቅድመ ምርመራ ምንም ዓይነት የበሽታው ምልክት ሳይታይብን፤ በደኅና ጊዜያችን ሄደን የፕሮስቴት ጤና የምንመረምርበት ነው።

ታዲያ አንድ ወንድ ይህንን ምርመራ መቼ እና በምን ዕድሜ መጀመር አለበት?


የዓለም አቀፍ የሕክምና መመሪያዎች እንደሚያሳዩት፤ የዕድሜ ጣሪያው በሰውየው የጤና ታሪክ እና ተጋላጭነት ላይ ይወሰናል፡-

  • ከ 50 አመት ዕድሜው ጀምሮ የቅድመ ምርመራ እንዲያደርግ ይመከራል።

  • አንድ የቤተሰብ አባልዎ (በተለይ አባት፣ ወንድም ወይም አጎት) በፕሮስቴት ካንሰር የተያዙ ካሉ፤ በሽታው በዘር የመተላለፍ ዕድል ስላለው ከ45 ዓመትዎ ምርመራውን መጀመር አለብዎት።

  • ከአንድ በላይ የቅርብ የቤተሰብ አባላት በዚህ ካንሰር የተጠቁ ከሆነ፤ ቅድመ ምርመራውን መጀመር ያለብዎ፤ በ40 ዓመት ዕድሜዎ ነው።

ይህ የቅድመ ምርመራ ለማድረግ ሐኪሞች የ ፔኤስ ኤ የደም ምርመራን እና በፊንጢጣ በኩል የሚደረገውን ምርመራ ይጠቀማሉ።


እንደ ምርመራው ውጤት አሳሳቢነት፤ ሐኪምዎ ምርመራውን በየዓመቱ ወይም በየሁለት ዓመቱ እንዲያደርጉ ሊያዝዎት ይችላል።


የፕሮስቴት ካንሰር ሕክምናዎች ምንድናቸው?

ቀደም ሲል እንዳየነው ሁሉም የፕሮስቴት ካንሰር አንድ ዓይነት ባለመሆኑ፤ ሕክምናው በካንሰሩ ደረጃ፣ በስጋቱ መጠን፣ በታካሚው ዕድሜና አጠቃላይ ጤና ላይ ይመሰረታል።


ካንሰሩ


  •  ካንሰሩ በጣም ቀስ ብሎ የሚያድግ እና ለሕይወት አስቸኳይ አደጋ የማይደቅን ከሆነ፤ ወዲያውኑ ቀዶ ጥገና ወይም መድኃኒት አያስፈልገውም። በዚህ ፈንታ፤ ሐኪሞች የPSA የደም ምርመራንና አልትራሳውንድን በየጊዜው በማድረግ ካንሰሩን በንቃት ይከታተሉታል።

  • ካንሰሩ አሳስቢ ከሆነ እና መጀመሪያ ደረጃ ላይ እያለ ክተደረሰበት፤  ሙሉውን የፕሮስቴት እጢ ቀዶ ጥገና በማድረግ ነቅሎ ማውጣት ይቻላል።

  • ካንሰሩ በፕሮስቴት እጢ ላይ ብቻ ወይም ወደ አቅራቢያው ሕብረ ሕዋሳት ብቻ በመጠኑ ተሰራጭቶ ከሆነ፤ የጨረር ሕክምና ሊደረግ ይችላል።

  • ኃይለኛ ካንሰር ከሆነ ከፕሮስቴት ወጥቶ ወደ አጥንት ወይም ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ከተሰራጨ፤ ኬሞቴራፒ ዋነኛው አማራጭ ይሆናል።

  •  የፕሮስቴት ካንሰር ሕዋሳት እንዲያድጉ እና እንዲባዙ የሚያደርጋቸው ቴስቶስትሮን (Testosterone) ሆርሞን መጠንንም የሚቀንሱ የሕክምና አማራጮች አሉ። እነኝህም የካንሰሩን እድገት ለመግታት ጥቅም ከሌሎች ህክምናዎች ጋር ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ።

ቀድሞ የተገኘ ካንሰር ሙሉ በሙሉ የመፈወስና የመዳን ዕድሉ እጅግ ከፍተኛ ነው!

የፕሮስቴት ካንሰርን መከላከል ይቻላል?

እውነቱን ለመነጋገር፤ በሽታውን 100% ሙሉ በሙሉ መከላከል የሚችል በሳይንስ የተረጋገጠ ፍጹም ዘዴ እስካሁን የለም።


ምክንያቱም እንደ ዕድሜ መጨመር፣ የቤተሰብ የሕክምና ታሪክ፣ የዘር ችግር እና አንዳንድ የዘረመል ለውጦች ጋር የተያያዙ ተጋላጭነቶችን በምንም ዓይነት መንገድ ልንቀይራቸው አንችልም።


ነገር ግን ይህ ማለት እጅና እግራችንን አጣጥፈን እንቀመጥ ማለት አይደለም። ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን መከተል ለአጠቃላይ የሰውነት ጤናችን ብቻ ሳይሆን፤ የካንሰር የመያዝ ዕድላችንን በመቀነስ ረገድ የራሱ የሆነ ትልቅ አስተዋጽዖ አለው። ለዚህም የሚከተሉትን ጥንቃቄዎች ማድረግ ይመከራል፡-


  • የተመጣጠነ ምግብ ይመገቡ።

  • በመደበኛነት አካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ።

  • ጤናማ የሰውነት ክብደት ለመጠበቅ ይሞክሩ።

  • ሲጋራን ያስወግዱ።

  • አልኮልን ከመጠን በላይ አይጠቀሙ።


እነኝህን እያደረጉ ተጋላጭነትዎን ቢቀንሱም፤ ዕድሜዎ ሲገፋ እላይ በገለጽነው መሰረት የ ቅድመ ምርመራ ያድርጉ።


ያስታውሱ

ምልክቶቹን እስኪያዩ አይጠብቁ። ቅድመ ምርመራ ያድርጉ!


ምልክቶቹንም ካስተዋሉ፤ ችላ አይበሉ። እርጅና አይደለም! አቅራቢያዎ ያለ የጤና ተቋም ይጎብኙ!



Comments


bottom of page