ቲማቲም አሜባን ይቀሰቅስ ይሆን? ስለ አሜባ በሽታ እና መከላከያ መንገዶች ይወቁ!
- Zebeaman Tibebu
- Jun 30
- 5 min read
ቲማቲም ይወዳሉ? አሜባስ አሰቃይትዎ ያውቃል? እንግዲያውስ እንዲህ ሲባል ሰምተዋል፦ "ቲማቲም አትብላ!"
"ሰላጣ ከበላህ አሜባህ ይነሳል!"

ይህን ብዙ ኢትዮጵያዊያን ሰምተነዋል። እንደ ሳይንሳዊ እውነታ ከመቀበላችንም የተነሳ፤ አንድ ሰው ጥሬ ቲማቲም በልቶ ወዲያው ሆዱን ሲያመ፤ በዙሪያው ያለው ማህበረሰብም ያለ ምንም ማቅማማት፦ “አሜባው ተነሳብህ እንዴ?” ሲሉ ይሰማል።
ለብዙዎች ይህ ፍፁም እውነታ ነው። እንዲያውም “እከሌ እኮ ቲማቲም በልቶ ነው አሜባው የተነሳበት” ብለው የታዘቡትን ምስክርነት የሚያቀርቡም አይጠፉም።
ግን ለመሆኑ አሜባ በእርግጥ እንዲህ ዓይነት በሽታ ነውን?
አንድ ሕያው ጥገኛ ተውሳክ (parasite) በሰውነት ውስጥ ለዓመታት በዝምታ ሰንብቶ፤ ቲማቲም ሲበላ በድንገት ነቅቶ ሊያጠቃ ይችላልን? ቲማቲምስ በውስጡ ይህንን የማድረግ አቅም አለውን? ምን ይመስልዎታል!?
ይህንን ጥያቄ ለመመለስ፤ መጀመሪያ ስለ አሜባ በጥልቀት መረዳት ይኖርብናል።
🦠 አሜባ ምንድን ነው?

የአሜባ በሽታ የሚመጣው ኢንታሜባ ሂስቶሊቲካ(Entamoeba Histolytica) በሚባል፤ በዓይን በማይታይ ረቂቅ ጥገኛ ተውሳክ ነው። ይህ ተውሳክ ፕሮቶዞአ(protozoa) ከሚባሉት ; ባለአንድ ሕዋስ ፍጥረታት ወገን ይመደባል።
ተውሳኩ ወደ ሰውነት ከገባ በኋላ በዋናነት በትልቁ አንጀት ውስጥ ሰፍሮ ይኖራል። በሕይወት ዑደቱ ውስጥ በሁለት የተለያዩ ደረጃዎች አሉት። እነኝህም ፦
የመጀመሪያው “ሲስት” (Cyst) ወይም የእንቁላል ደረጃ ነው፦ እዚህ ደረጃ ላይ አሜባው ራሱን ከውጭ አካባቢ ጥቃት የሚከላከልበት ጠንካራ ቅርፊት አለው። ይህ ቅርፊት ምቹ ሁኔታ እስኪያገኝ ድረስ ተኝቶ የሚቆይበት ምሽጉ ነው። ሲስቶች ከሰውነት ውጭ በተለይም በተበከለ ውሃ፣ አፈር፣ ምግብ ውስጥ ለረጅም ጊዜ መቆየት ይችላሉ። ኢንፌክሽኑ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው የሚተላለፈውም በዚህ ደረጃ ነው።

ሁለተኛው “ትሮፎዞይት” (Trophozoite) ወይም የጎልማሳነት ደረጃ ነው፦ የሰው ልጅ የተበከለ ምግብ ሲመገብ፤ ሲስቱ የጨጓራ አሲድን ተቋቁሞ አልፎ አንጀት ውስጥ ይደርሳል። እዚያም ጠንካራ ቅርፊቱን ሰብሮ በመውጣት ወደ ተንቀሳቃሽና ጎልማሳ አሜባ ያድጋል። ይህ ደረጃ በትልቁ አንጀት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የሚራባበትና ለጥቃት የሚያሰናዳበት ነው።
አሜባ በብዙ ሰዎች አንጀት ውስጥ ምንም ዓይነት የሚስተዋል የሕመም ምልክት ሳያስከትል በዝምታ ሊቀመጥ ይችላል። ነገር ግን፤ የትልቁን አንጀት ግድግዳ መውረር ሲጀምር ከባድ የአንጀት መቆጣት፣ ቁስለት፣ የደም ተቅማጥ ያስከትላል።
ከዚህም ባለፈ፤ አሜባ በአንጀት ላይ ብቻ የሚወሰን አይደለም። አልፎ አልፎ በደም አማካኝነት ወደ ጉበት አልያም ወደ አንጎል በመጓዝ ለሕይወት አስጊ የሆኑ ከባድ የጤና እክሎችን ሊፈጥር ይችላል።
ሰዎች አሜባን እንዴት ይይዛቸዋል?

ይህ ምናልባትም ከሁሉም በላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ወሳኝ ጥያቄ ነው። ሰዎች በአሜባ በሽታ የሚያዙት፤ የአሜባ በሽታ አምጪ ተህዋስ/ተውሳክ በአፍ በኩል ወደ አንጀታቸው ሲገባ ነው። ይህም ማለትም ሲመገቡ ወይም ሲጠጡ ነው።
ለዚህም በአሜባ የተበከለ የመጠጥ ውሃ ሲጠጡ፤ በአሜባ የተበከለ ምግብ ሲመገቡ፤ እንዲሁም በንጹህ ውሃ በአግባቡ ባልታጠቡ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች ሲጠቀሙ በሽታው በቀላሉ ይተላለፋል። ከዚህም ባሻገር፤ ከሰው አይነምድር ጋር ንክኪ ሲኖር ወይም ሽንትቤት ከተጠቀሙ በኋላ እጅን በአግባቡ ሳይታጠቡ ወደ አፍ ካስጠጉ አሜባ በቀጥታ ወደ ሰውነት ይገባል።
የአሜባ መተላለፊያ መንገዶች ሁሉ ከግልና ከአካባቢ ንጽህና ጉድለት ጋር የተያያዙ ናቸው።
ቲማቲም በእርግጥ አሜባን "ሊቀሰቅስ" ይችላል?

አንድ ሰው በምሳ ሰዓት ጥሬ ቲማቲም በልቶ፤ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ድንገተኛ የሆድ ቁርጠት ወይም ተቅማጥ ሊጀም ይችላል። በዚህ ጊዜ መጀመሪያ በአእምሮው የሚመጣው ሃሳብ “የበላሁት ቲማቲም አሜባዬን ቀሰቀሰው” የሚል ነው። ነገር ግን ሁለት ድርጊቶች ተከታትለው ስለመጡ ብቻ፤ አንዱ የሌላኛው ምክንያት ነው ብሎ ማሰብ ትክልል አይደለም።
በመጀመሪያ ደረጃ፤ ብዙዎች በየመኖሪያ ቤታቸው “አሜባ” ብለው የሚፈርጁት በሽታ ፤ በላብራቶሪ ምርመራ የተረጋገጠውን የአሜባ ኢንፌክሽን ሳይሆን፤ ማንኛውንም ዓይነት ተቅማጥና የሆድ ህመምን ነው። "የቲማቲም፣ ቃሪያ፣ ወተት፣ እንቁላል ወይም ቀዝቃዛ መጠጦች አንጀት ውስጥ የሚገኘውን አሜባ ይቀሰቅሳል "የሚለውን አስተሳሰብ በህክምናው አለም የተደገፈ አይደለም።

ቲማቲም በተፈጥሮው ራሱ አሜባን አያመርትም።ነገር ግን ቲማቲሙ በአሜባ የተበከለ አፈር ከነካ፤ በቆሸሸ እጅ ከተያዘ፤ ወይም ጥሬው ከመበላቱ በፊት በስርዓቱ ንጹህ ባልሆነ ውሃ ከታጠበ እላዩ ላይ የአሜባ እንቁላሎች ሊኖሩት ይችላሉ። ይህ ሁኔታ ለአዲስ አሜባ ኢንፌክሽን ያጋልጣል እንጂ ፤ ተኝቶ የነበረውን አያስነሳም።
እንዲያውም አሁን የተመገቡት አሜባ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ አንጀት ላይ ደርሶ በሽታ ሊያመጣ አይችልም።ተውሳኩ አንጀት ውስጥ ገብቶ ጥቃት ማድረስ እስኪጀምር ድረስ፤ የራሱ የሆነ ጊዜ (የመፈልፈያ ጊዜ) ይፈልጋል። በመሆኑም ቲማቲም በተበላ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ የሚከሰተው የሆድ መታወክ፤ ምናልባት ከቲማቲሙ ጋር አብረው ወደ ሆድ ከገቡና ኢንፌክሽን ከሚያመጡ ባክቴሪያዎች ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል።
በተጨማሪም፤ ቲማቲም ያለው አሲዳማ ተፈጥሮ የጨጓራ ህመምን ሊያባብሰው ይችላል። ይህም ቀድሞ የነበረውን የጨጓራ መቆጣት ህመም ተባባሰ እንጂ አሜባ ተቀሰቀሰ ማለት አይደለም።
⚠️ የአሜባ በሽታ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

አሜባ ያለበት ሰው ሁሉ ወዲያውኑ ይታመማል ማለት አይደለም!
እንዲያውም ብዙዎቹ ተውሳኩን በአንጀታቸው ውስጥ ተሸክመው፤ እነሱ መታመማቸውን ሳያውቁት ፤ ወደ ሌሎች ሊያስተላልፉ ይችላሉ። ነገር ግን ምልክቶቹ መታየት በሚጀምሩበት ጊዜ ፤ ከቀላል ምቾት ማጣት እስከ ከባድና ለሕይወት አስጊ በሽታ ሊደርሱ ይችላሉ። አንዳንድ ሰዎች ምልክቶቹን ለጥቂት ቀናት ብቻ ሲያዩት፤ ሌሎች ደግሞ ለብዙ ሳምንታት እየመጣ ፤ እየሄደ ያስቸግራቸዋል። የአሜባን ምልክቶች መለስተኛ እና ከባድ ብለን መክፈል እንችላለን።
መለስተኛ ምልክቶቹ፦
እነዚህ ምልክቶች ብዙውን ጊዜ በሽታው ገና በጅምር ላይ መሆኑን የሚያሳዩ ሲሆኑ፤ የሚከተሉትን ያካትታሉ፦
ተደጋጋሚ ተቅማጥ ወይም ቀጭን ሰገራ፣
የሆድ ቁርጠት፣
የሆድ መነፋት፣
ከልክ ያለፈ ጋዝ/ፈስ መምጣት
የማቅለሽለሽ ስሜት፣
የምግብ ፍላጎት ማጣትና፣
መጠነኛ ድካም

ከባድ ምልክቶች ፦
የሚከተሉትን ምልክቶች ካዩ ፤ በአፋጣኝ የሕክምና እርዳታ መፈለግ ይመከራል፦
ደም የተቀላቀለበት ተቅማጥ፣
በሰገራ ውስጥ ንፍጥ መታየት፣
ከፍተኛ የሆድ ህመም፣
ትኩሳት፣
ከፍተኛ የውሃ ጥማትና፣ የአፍ መድረቅ፣
የክብደት መቀነስ፣
ከፍተኛ ድካምና፣
ግራ መጋባት
በሽታው ወደ ከፋ ደረጃ ከመድረሱ በፊት የሚደረግ ፈጣን ሕክምና፤ ከባድ የሆኑ የጤና ውስብስብ ችግሮችንና የሕይወት መጥፋትን በቀላሉ መከላከል ይችላል።
የአሜባ በሽታ እንዴት ይታወቃል?

አሜባን መኖሩን ለማወቅ ትክክለኛውን ምርመራ ማድረግ የመጀመሪያው ወሳኝ እርምጃ ነው። ሐኪሞች በሽታውን በእርግጠኝነት ለመለየት የሰገራ ምርመራ (Stool Test) ያዛሉ። በዚህ ምርመራ አማካኝነት ጥገኛ ተውሳኩ ወይም የእንቁላል ደረጃው (ሲስቱ) በአጉሊ መነጽር ታይቶ ይረጋገጣል።
በሽታው ወደ ከፋ ደረጃ ደርሶ ወደ ጉበት ወይም ወደ ሌሎች የውስጥ አካላት መሰራጨቱ ከተጠረጠረ ግን፤
የደም ምርመራ፣
የአልትራሳውንድ (Ultrasound) ወይም
የሲቲ ስካን (CT scan) ተጨማሪ ምርመራዎች ሊያስፈልጉ ይችላሉ።
ህክምናው ምንድነው?

የምርመራው ውጤት የአሜባ ኢንፌክሽን መኖሩን ካረጋገጠ በኋላ፤ በሐኪም በሚታዘዙ ፀረ-ተውሳክ (Antiparasitic) መድኃኒቶች ይታከማል። ብዙውን ጊዜ ሜትሮኒዳዞል (Metronidazole) ወይም ቲኒዳዞል (Tinidazole) አይነት መድኃኒቶች በትልቁ አንጀት ውስጥ ያሉትን አሜባዎች ለማጥፋት ይሰጣሉ።
መድኃኒቱን በሐኪም ትዕዛዝ መሠረት ቀኑንና ሰዓቱን ጠብቆ እስከ መጨረሻው መውሰድ ግዴታ ነው። ምክንያቱም ምልክቶቹ ስለጠፉ ብቻ መድኃኒት ማቋረጥ ፤ አሜባው ተመልሶ እንዲያገረሽና መድኃኒቶችን እንዲላመድ ያደርጋል።
ብዙዎች የሚሳሳቱት ስህተት

በኢትዮጵያ ውስጥ ተቅማጥ ወይም የሆድ ህመም ያለው ሰው ፤ ከፋርማሲ “ሜትሮኒዳዞል” (Metronidazole) ገዝቶ መውሰድ የተለመደ ነው። ችግሩ ግን እያንዳንዱ ተቅማጥ በአሜባ ምክንያት የሚመጣ አለመሆኑ ነው።
ምክንያቱም ብዙ ባክቴሪያዎች፣ ቫይረሶች፣ የትላትል ህመሞች፣ የምግብ መመረዝ፣ የወተት አለመስማማት፣ እንዲሁም የአንጀት መቆጣት ሙሉ በሙሉ ተመሳሳይ ምልክት ሊያሳዩ ይችላሉ። እውነተኛውን ምክንያት ሳያረጋግጡ ራስን ማከም፤ ትክክለኛውን ምርመራ ሊያዘገይ እና በሽታው ይበልጥ እንዲባባስ ሊያደርግ ይችላል። ለመድሐኒት መላመድም ያጋልጣል።
አሜባ አለብኝ ብለው ካሰቡ ምን ያድርጉ?
የአሜባ በሽታ መኖሩ በምርመራ ከተረጋገጠ በኋላ፤ መድኃኒት ከመውሰድ ጎን ለጎን የምግብ ምርጫና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎ ማገገምዎ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ አላቸው።

ለዚህም እነኝህን ያድርጉ ፦
በተቅማጥ ምክንያት የጠፋውን ውሃ፣ ጨው፣ ማዕድናት ለመተካት ፈሳሽ አብዝተው ይጠጡ። አጥሚት ፣ ኦአርኤስ ይጠጡ።
እንደ ሙዝ፣ የተቀቀለ ድንች፣ ነጭ ሩዝ፣ የደረቀ ዳቦ ቢመገቡ፤ በተቅማጥ ምክንያት የሚመጣውን ጉዳት ይቀንሳሉ።
ለሰውነት ጉልበት የሚሰጡና ለስላሳ የሆኑ የዶሮ ሾርባዎችን መጠቀም።
ኃይልዎን ለማደስ ሙሉ ዕረፍት ማድረግና በቂ እንቅልፍ መተኛት ይኖርብዎታል።
ወደ ቤተሰብ አባልዎ እንዳይተላላፍ የግል ንጽህናዎን ይጠብቁ። ሽንትቤት ከተጠቀሙ በኋላ እና ምግብ ከመንካት በፊት እጅዎን፤ በሳሙናና በንጹህ ውሃ በሚገባ ይታጠቡ።
እነኝህን ደግሞ ያስወግዱ ፦
አትክልትና ፍራፍሬዎችን እንዲሁም የፍራፍሬ ጭማቂዎችን አይመገቡ። በንጽህና ካልተዘጋጁ ከላያቸው ባክቴሪያ ሊኖር ስለሚችል ለተጨማሪ አንጀት መቆጣት ሊያጋልጡ ይችላሉ። እንዲሁም ከፍተኛ የአሰር መጠን ስላላቸው የአንጀት እንቅስቃሴን ያፋጥናሉ።
ለጊዜው ያልበሰሉ ምግቦችን ከመመገብ ይቆጠቡ።
ሰውነትን የሚያደክሙ እንቅስቃሴዎችን አያድርጉ።

ከዛሬ በኋላ
አንድ ሰው "ቲማቲም አትብላ፤ አሜባህ ይነሳል" ቢልዎ፤ የሚያስፈራዎት ቲማቲሙ አይሁን።
የሚያስፈራዎት የንጽህና ጉድለት ይሁን!
ምክንያቱም አሜባ ቲማቲምን ሳይሆን፤ የንጽህና ጉድለትን ብቻ ነው የሚፈልገው።




Comments