ከማህጸን ውጭ ያለ እርግዝና (Ectopic Pregnancy)፦ መንስኤዎች፣ ምልክቶች እና ሊደረጉ የሚገቡ ጥንቃቄዎች
በጉጉት የሚጠበቀው ያ አስደሳች ቅጽበት ደረሰ!
የወር አበባ ቀርቷል! የእርግዝና ምርመራም እርጉዝ መሆንሽን አረጋግጧል። ደስታሽ ወደር የለሽ ሆነ!

ሆኖምግን ያንን ደስታ የሚያደበዝዝ አንድ ያልተጠበቀ ስሜት ማስተዋል ጀመርሽ። ከታችኛው የሆድ ክፍልሽ ጋር በአንድ በኩል ብቻ የሚሰማ እረፍት የሚነሳ ሕመም!
ይህ መደበኛ የእርግዝና ምልክት ይሆን? ወይስ አሳሳቢ ጉዳይ?
ብዙዎቻችን እርግዝና ሲባል በማህጸን ውስጥ የሚፈጠርና የሚያድግ ፅንስን ብቻ እናስባለን። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ጽንስ ከማህጸን ውጭ ማደግ ይጀምራል። ይህ የሕክምና ሁኔታ ከማህጸን ውጭ ያለ እርግዝና (Ectopic Pregnancy) ይባላል።
ይህ ሁኔታ ቀድሞ ካልታወቀ፤ የእናትን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል ነው። ስለዚህ ምልክቶቹን በጊዜ መለየትና አስቸኳይ ሕክምና ማግኘት ፤ የእናትን ህይወት መታደግ ነው።
ታዲያ ይህ ሁኔታ እንዴት ይከሰታል? ምልክቶቹ ምንድን ናቸው? ማንስ ለዚህ አደጋ ይበልጥ ተጋላጭ ነው? እንዴትስ መከላከልና ማከም ይቻላል?
ከማህጸን ውጭ ያለ እርግዝና (Ectopic Pregnancy) ምንድነው?

በመደበኛ እርግዝና ወቅት የሚገርመው የሰውነታችን ጉዞ እንዲህ ነው....
የወንድ ዘር ሕዋስ እና እንቁላል በማህጸን ቱቦ (Fallopian tube) ውስጥ ይገናኛሉ። ከዚያም የተፈጠረው ፅንስ ጉዞውን በመቀጠል ማህጸን ላይ ያርፋል። እዚያው ግድግዳው ላይ ተጣብቆም ማደግ ይጀምራል።
ነገር ግን ይህ የተፈጥሮ ሂደት ሲስተጓጎልና፤ የተፀነሰው እንቁላል ወደ ማህጸን ሳይደርስ ከማህጸን ውጭ ባለ ሌላ አካል ላይ ተጣብቆ ማደግ ሲጀምር ከማህጸን ውጭ ያለ እርግዝና (Ectopic Pregnancy) ይከሰታል።
የሚያስገርመው፣ ከ90% በላይ የሚሆኑት የዚህ ዓይነት እርግዝናዎች የሚፈጠሩት በዚሁ ጠባብ የማህጸን ቱቦ ውስጥ ነው። በጣም አልፎ አልፎ ግን በእንቁላል አመንጪ አካል (Ovary)፣ በማህጸን ጫፍ (Cervix) ወይም በሆድ ዕቃ ውስጥ ሊከሰቱ ይችላሉ።
ታዲያ ትልቁ ችግር ምንድነው?

ማህጸን ለፅንስ መሸከሚያና ማሳደጊያ ተብሎ የተሰራ፤ እንደ ፊኛ የመለጠጥ ተፈጥሯዊ ብቃት ያለው ልዩ አካል ነው። ሌሎቹ የሰውነት ክፍሎች ግን ለፅንስ መደበኛና ደህንነቱ የተጠበቀ እድገት ምቹ አይደሉም። ስለዚህ እርግዝናው ከቀጠለ ለእናትየው ሕይወት አደገኛ የሆነ የውስጥ ደም መፍሰስንና ሌሎች ከባድ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል።
ለምን ይከሰታል? ማን ለአደጋው ይበልጥ ተጋላጭ ነው?
የዚህ አደገኛ እክል ዋነኛ መንስኤ አንድ ነው!
የተፀነሰው እንቁላል ወደ ማህጸን የሚያደርገው ተፈጥሯዊ ጉዞ መስተጓጎሉ! ይህ አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰተው ጠባቡ የማህጸን ቱቦ በመዘጋቱ፤ በመጥበቡ ወይም በመጎዳቱ ምክንያት ነው።

ለዚህ አደጋ ይበልጥ የሚያጋልጡ (Risk Factors) ዋና ዋና ሁኔታዎች የሚከተሉት ናቸው፦
ቀደም ሲል ከማህጸን ውጭ ያለ እርግዝና አጋጥሞ ከሆነ፦ ከዚህ በፊት ከማህጸን ውጭ እርግዝና ያጋጠማት ሴት፤ በቀጣይ እርግዝናዋ ላይ ተመሳሳይ አደጋ የመደገም ዕድሉ ከፍተኛ ነው።
የዳሌ አካባቢ ኢንፌክሽኖች/ የአባላዘር በሽታዎች፦ በተለይም በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ እንደ ክላሚዲያ (Chlamydia) እና ጨብጥ (Gonorrhea) ያሉ ኢንፌክሽኖች ማህጸን ቱቦን በማቁሰልና በማጥበብ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ።
በማህጸን ቱቦ ላይ የተደረገ ቀዶ ጥገና፦ ቀደም ሲል በቱቦዎቹ ላይ የተደረጉ ማናቸውም ቀዶ ጥገናዎች ቱቦው እንዲጠብ ሊያደርጉ ስለሚችሉ፤ ከማህጸን ውጭ ያለ እርግዝና እንዲያጋጥም እድል ይከፍታሉ።

የመካንነት ችግር እና የመራባት ሕክምናዎች፦ የመሀንነት ችግር የነበረባቸው አልያም ለመውለድ እንደ አይቪኤፍ(IVF) ያሉ የሕክምና እገዛዎችን የተጠቀሙ ሴቶች ላይ ከማህጸን ውጭ ያለ እርግዝና የማጋጠም ዕድሉ ከፍተኛ ነው።
ሲጋራ ማጨስ፦ ማጨስ የማህጸን ቱቦዎች ያላቸው ፅንሱን ወደ ማህጸን የመግፋት ተፈጥሯዊ እንቅስቃሴያቸውን እንዲያጡ ስለሚያደርግ ይህንን ያስከትላል።
ዕድሜ፦ በተለይ ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በላይ የሆኑ እናቶች ለዚህ አደጋ ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው።
ማህጸን ውስጥ የሚቀበር የወሊድ መቆጣጠርያ(IUD) እያለ ማርገዝ፦ ይህ በአጠቃላይ እርግዝናን ይከላከላል። ሆኖም መሳሪያው ማህጸን ውስጥ እያለ እርግዝና ከተፈጠረ፣ እርግዝናው ከማህጸን ውጭ የመሆን እድሉ ከፍ ይላል።
ነገር ግን በፍጹም ሊዘነጋ የማይገባው ወሳኝ እውነታ አለ!
ይህ ችግር ከላይ የተጠቀሱት አጋላጭ ምክንያቶች በሌሉባቸው ሴቶች ላይም ሊከሰት ይችላል። ስለዚህ ምንም ዓይነት የተጋላጭነት ታሪክ የሌለዎት መሆኑ ብቻ ከችግሩ ሙሉ በሙሉ ነፃ ነዎት ማለት አይደለም።
ምልክቶች ምንድናቸው?

በመጀመሪያው ሳምንታት ከማህጸን ውጭ ያለ እርግዝና (Ectopic Pregnancy) ምልክቶች እንደማንኛውም መደበኛ እርግዝና ሊመስሉ ይችላሉ። የወር አበባ መቅረት፣ ማቅለሽለሽ እና የጡት ማበጥ ወይም ሕመም ሊታዩ ስለሚችሉ በቀላሉ መለየት ሊያዳግት ይችላል።
ነገር ግን ከማህጸን ውጭ ያለው እርግዝና እያደገ ሲሄድ፤ አንዳንድ ሴቶች የሚከተሉትን ምልክቶች ማሳየት ይጀምራሉ፦
ከታችኛው የሆድ ወይም የዳሌ አካባቢ ሕመም፦ ብዙ ጊዜ በአንድ በኩል ብቻ የሚሰማ፣ ቀስ በቀስ እየበረታ የሚሄድ ወይም በድንገት የሚቀሰቅስ እረፍት የሚነሳ ሕመም ነው።
ያልተለመደ የሴት ብልት ደም መፍሰስ፦ ከመደበኛ የወር አበባ የተለየ፣ መጠኑ አነስተኛ የሆነና ብዙውን ጊዜ ቀለሙ ወደ ቡናማነት ያደላ ደም ሊታይ ይችላል።

በትከሻ ጫፍ ላይ የሚሰማ ሕመም፦ ይህ ብዙዎች የማይጠረጥሩት አስገራሚ ምልክት ነው! በማህጸን ቱቦ መቅደድ ምክንያት በሆድ ዕቃ ውስጥ ደም መፍሰስ ሲኖር፤ በትከሻ ጫፍ ላይ ሕመም ሊሰማ ይችላል።
ማዞር፣ ከፍተኛ ድካም ወይም መሳት፦ ይህም ምልክት ከፍተኛ የውስጥ ደም መፍሰስ መኖሩን የሚያሳይ እጅግ አስቸኳይ ሕክምና የሚሻ ምልክት ነው።
በሽንት ወይም በሰገራ ጊዜ ምቾት ማጣት፦ ፅንሱና የሚፈሰው ደም በአካባቢው ባሉ የሰውነት ክፍሎች ላይ ጫና ስለሚፈጥሩ፤ በሽንት ጊዜ የመለብለብ ወይም ሰገራ ሲወጡ የመግፋትና የሕመም ስሜት ሊስተዋል ይችላል።
አስታውሺ!
የማህጸን ቱቦ መቀደድ በውጭ የሚታየው ደም ብዙ ባይሆንም፤ ከፍተኛ የውስጥ ደም መፍሰስን ሊያስከትል ይችላል። እላይ የገለጽናቸው የደም መፍሰስ ምልክቶች ካጋጠሙሽ ሳትዘገዪ ወደ ቅርብ የጤና ተቋም በአስቸኳይ ሂጂ።
እንዴት ይታከማል?

የሕክምና ዘዴው እንደ ሴቷ የጤና ሁኔታ፣ የእርግዝናው ደረጃ፣ የፅንሱ መጠንና የደም ምርመራ ውጤት ይለያያል። በዋናነት ሦስት የሕክምና አማራጮች አሉ፦
በቅርብ ክትትል መጠበቅ (Expectant Management)
እርግዝናው በጣም ትንሽ ሲሆን፣ ምልክቶች ከሌሉ ወይም ቀላል ሲሆኑ፣ የhCG መጠንም በራሱ እየቀነሰ ከሆነ በሐኪም ቅርብ ክትትል ሕክምና ሳይሰጥ መጠበቅ ሊቻል ይችላል። ይህ ግን ያለ ሐኪም ክትትል በቤት መጠበቅ ማለት አይደለም።
በመድኃኒት ማከም (Medical Management)
በተመረጡ ቀደምት ሁኔታዎች መድኃኒት በመርፌ ሊሰጥ ይችላል። መድኃኒቱ የፅንሱን ሕዋሳት እድገት በማቆም ሰውነት ቀስ በቀስ እንዲያስወግደው ያደርጋል። ከዚህ በኋላ የhCG መጠን እስኪወርድ ድረስ ተደጋጋሚ የደም ምርመራ ያስፈልጋል።

3. በቀዶ ጥገና ማከም (Surgical Management)
የማህጸን ቱቦው ከተቀደደ፣ ከፍተኛ ደም መፍሰስ ካለ ወይም ሌሎቹ የሕክምና ዘዴዎች ተስማሚ ካልሆኑ ቀዶ ጥገና ያስፈልጋል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ፅንሱን ከቱቦው ጋር ማስወገድ ያስፈልጋል፤ በሌሎች ሁኔታዎች ግን ቱቦውን በማቆየት ፅንሱን ማስወገድ ሊቻል ይችላል።
ሆኖም ግን ትክክለኛውን የሕክምና ዘዴ መወሰን ያለበት የጤና ባለሙያ ነው።
ያስተውሉ! በቤት ውስጥ በመድኃኒት፣ በባህላዊ ሕክምና ወይም በመጠበቅ ለማከም መሞከር አደገኛ ነው።
ከማህጸን ውጭ ያለ እርግዝና ካጋጠመ በኋላ እንደገና ማርገዝ ይቻላል?

ይህ ብዙ ሴቶችና ቤተሰቦቻቸውን ሌሊትና ቀን እረፍት የሚነሳ ትልቅ ጥያቄ ነው።
መልሱ አጭር ነው፦ አዎን፣ ይቻላል!
ይህንን አስቸጋሪ የጤና እክል ካስተናገዱ እናቶች መካከል፤ አብዛኛዎቹ በቀጣይ ጊዜያት ምንም ዓይነት ችግር ሳይገጥማቸው ፍጹም ጤናማ የማህጸን ውስጥ እርግዝና የመሸከም ዕድል አላቸው። እርግጥ ነው! የወደፊቱ የማርገዝ ዕድል በተቀረው ሁለተኛው ማህጸን ቱቦ ጤንነት፣ እናትየው ባላት የቀደመው የዳሌ አካባቢ የጤና ታሪክ እና ከዚህ በፊት ለማህጸን ውጭ እርግዝናው (Ectopic Pregnancy) በተደረገው የሕክምና ዓይነት (በመድኃኒት ወይስ ቱቦውን በቀዶ ጥገና በማውጣት) ላይ ይወሰናል።
አንድ የቀረው ቱቦ ጤናማ እስከሆነ ድረስ፤ አንድ እናት በተፈጥሮ በራሷ መንገድ በድጋሚ የማርገዝ ሙሉ ዕድል አላት።

ነገር ግን በቀጣይ እርግዝና ላይ ሊደረግ የሚገባው ወሳኝ ጥንቃቄ አለ!
ቀደም ሲል Ectopic Pregnancy ያጋጠማት ሴት በቀጣይም ተመሳሳይ የማጋጠም ዕድሏ ከፍ ያለ ነው። ስለዚህ በድጋሚ ማርገዟን እንዳወቀች (የወር አበባዋ በቀረ የመጀመሪያ ቀናቶች ውስጥ)፤ ሳትዘገይ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም መሄድ ይኖርባታል። ክትትል ቀድማ መጀመር ይኖርባታል።
እንዴት መከላከል ይቻላል?

ሁሉንም ከማህጸን ውጭ ያሉ እርግዝናዎች (Ectopic Pregnancy)መከላከል ባይቻልም አንዳንድ እርምጃዎች አደጋውን ሊቀንሱ ይችላሉ። ለምሳሌ፦
አባላዘር በሽታዎችን መከላከልና ከተያዙ በጊዜ ማከም።
ኮንዶምን በትክክል መጠቀም።
ሲጋራ አለማጨስ።
የዳሌ አካባቢ ኢንፌክሽን ምልክቶች ሲኖሩ ሕክምና በቶሎ መፈለግ።
በተለይም ከዚህ በፊት ከማህጸን ውጭ እርግዝና ያጋጠማቸው ሴቶች እርግዝና ሲኖር ቀድመው የጤና ባለሙያን ማማከር ይኖርባቸዋል።
አስታውሺ!
የእርግዝና ምርመራ ፖዘቲቭ መሆኑ እርግዝና መኖሩን ያሳያል እንጂ፤ ፅንሱ ማህጸን ውስጥ መሆኑን አያረጋግጥም። በእርግዝናሽ ወራት ምልክቶቹን ካየሽ የጤና ተቋም ሄደሽ ባለሙያ አማክሪ ። ቀድሞ ህክምና ማግኘት፤ ህይወት ያድናል።




Comments