ንቅሳትና ጤና፡ የክርስቲያኖ ሮናልዶ ምርጫ
- Zebeaman Tibebu
- Jan 11
- 4 min read
በአለማችን በእግርኳስ ብቃታቸው ከሚሞገሱ ተጨዋቾች መካከል ክሪስቲያኖር ሮናልዶ በቅድሚያ ይጠቀሳል። ስቴዲየም በደጋፊዎች ሲያጓራ ፤ ክርስቲያኖ ኳስ ላይ የሚያሳየውን ተአምራዊ ጥበብ ተከታትለናል። በዚህም ችሎታው አምስት ጊዜ ባላንዶር ያሸነፈ ፤ እውን ምርጥ ተጫዋች ነው።

እንደን ንስር አይን ካሜራም እሱ ላይ ተተክሎ ፤ እያንዳንዱን እንቅስቃሴውን ፤ ከሌሎች ተጫዋቾች ጋር ያለውን መስተጋብር ፤ ኳስን ከመረብ ጋር የማገናኘት ተአምራዊ ብቃቱን አሳይቶናል። አድንቀናል! ተደምመናል!
ከ አስር አመታት በላይ በቴሌቭዥናችን መስታወት በጨዋታዎቹ እና በሚሰራቸው ማስታወቂያዎች ጥሩ ተክለቁመናው አለም አድንቆለታል። ታድያ ግን ላስተዋለ ከብዙ ቡድን አጋሮቹ ለየት የሚያደርገው አንድ ጉዳይ አለ።
ሰውነቱ ላይ ምንም ንቅሳት የለም።

ንቅሳት የውበት ማድመቂያ የማንነት መግለጫ በሚደረግበት ዘመን ፤ ብዙ ታዋቂ ሰዎች ተነቅሰዋል። ከመነቀስም ባሻገር ንቅሳታቸውን ለአለም አሳይተዋል። አድናቆትም ተችረዋል።
ታድያ ለምን አልተነቀሰም? ንቅሳት ጠልቶ ይሆን?
ይህ የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም። ምክንያታዊ ውሳኔ ነው። ከፋሽንና መገለጫነት የተሻገረ ፤ የሌሎችን ጤና ያማከለ ውሳኔ።
እንዴት!? ማለት ጥሩ...
በምግባሩ መልካምነት እና ታታሪነቱ የሚታወቀው ይህ ኳስ ተጫዋች ፤ ለጋሽ ነው። በመደበኛ ሁኔታ ደም ይለግሳል። የቡድን አጋሩ ካሮሎስ ማርቲኒ ልጅ ከታመመ በኋላም ደግሞ የአጥንት መቅኔ መለገስ ጀምሯል። ደም ከመለገስ ባሻገሩም ሌሎች የሱን አርአያነት እንዲከተሉ ይገፋፋል። ሌሎችም እንዲለግሱም እንደ ቢ ዘ ዋን (Be the 1) አይነት የደም ልገሳ እንቅስቃሴዎችን አካሂዷል።

ይህም ንቅሳት ከመነቀስ እንዲቆጠብ ካደረጉት ምክንያቶቹ መካከል አንዱ እንደሆነ ጠቁሟል። ለእርሱ ንቅሳት ከጌጥነት ይልቅ ፤ በጎ አድራጎቱን የሚያሰናክል ድርጊት ነው።
ለመሆኑ ግን የተነቀሰ መለገስ አይችልምን?
አዎም! አይም!

ይህን ለመረዳት በዝርዝር እናውራ።
እንደ አለም ጤና ድርጅት መመሪያ ከሆነ አንድ ደም ለጋሽ ቢያንስ ቢያንስ ከተነቀሰ ለ 6 ወራት ደም ከመለገስ እንዲቆጠብ ይመክራል። የደም ልገሳ መመሪያቸውን ሙሉ በሙሉ በዚህ ላይ የመሰረቱ ሀገራትም በበኩላቸው ይህንን ተግባራዊ ያደርጋሉ።
በአንዳንድ የተሻለ ክትትል ባላቸው ሀገራት ይህ የጊዜ ገደብ ከ3 እስከ አራት ወር ሊወርድ ይችላል። ይህ የሚሆነው ግን ንቅሳቱ ትክክለኛ ፈቃድ ባለውና ጤናማነቱ በተረጋገጠ የንቅሳት ስፍራ ሲከናወን ነው። የንቅሳት ባለሙያውም ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚውል የንቅሳት መርፌ እና ቀለም መጠቀም ይኖርበታል።
የደም ተላላፊ በሽታዎች በተንሰራፉባቸው ሀገራት ደግሞ ይህ የጊዜ ገደብ ወደ አንድ አመት ከፍ ሊል ይችላል።
📌 የጊዜ ገደቡ ለምን አስፈለገ?
ንቅሳት በሚሰራበት ጊዜ ፤ የንቅሳቱ መርፌ ቆዳን በስቶ ፤ የንቅሳቱን ቀለም ከቆዳ ስር ያስቀምጣል። የዚህን ጊዜ ከደም ጋር ንክኪ ይኖረዋል። ታድያ ከእርሶ በፊት የተነቀሰው ሰው በደም የሚተላለፍ ኢንፌክሽን ካለበት ተጋላጭነት ይኖርዎታል። በዚህም የተነሳ እንደ ሔፕታይተስ ቢ እና ሲ አይነት የጉበት ቫይረሶች እንዲሁም ለኤች አይቪ (አልፎ አልፎ የሚያጋጥም) ይጋለጣሉ።
ችግሩ ታድያ...
እነኝህ ቫይረሶች ደም ውስጥ ገብተው እስኪንሰራፉ ጊዜ ይፈጃሉ። የተነቀሰው ሰው ደም ውስጥ ቫይረሶቹ ቢኖሩም ፤ መጠናቸው አነስተኛ በመሆኑ ፤ ሙሉ ኢንፌክሽን እስኪያመጡ በላብራቶሪ ምርመራ አይገኙም።

ይህን ጊዜ ቢመረመሩ የላብራቶሪ ምርመራዎ በስህተት ጤነኛ እንደሆኑ ይጠቁማል። ደም ለግሰውም ከሆነ የለገሱት ደምም ሆነ አካል ከኢንፌክሽን የጸዳ ሆኖ ይታያል። ለዚህም እርግጠኛ ለመሆን የተሰጠውን የጊዜ ገደብ መቆየት መልካም ነው። ኢንፌክሽኑ ከለጋሽ ወደ ተቀባይ እንዳይተላለፍ ይህ የጊዜ ገደብ አስፈላጊ ነው።
ታድያ ደም አዘውትሮ የሚለግስ ግለሰብ ፤ ይህንን ማወቅ እና ማክበር ይኖርበታል።
ክርስቲያኖም ለወራት እንኳን ደሞ መለገስን ላለማቆም ሲል አለመነቀስን መረጠ።
እስከአሁን ያወራነው ስለ ተቀባዩ ጤና ነው። አንድ ጥያቄ እንጠይቅ። የለጋሹ ጤናስ ? ለማስተላለፍ ለጋሹ መያዝ አለበት እኮ። በተለይም ክህሎታቸው በጤና ሁኔታቸው ላይ ለሚመሰረት አትሌቶች ፤ ይህን ተጋላጭነት መቀነሱ ይመከራል።
📌ይህን ያውቃሉ?
ንቅሳት ዘላቂ የሚሆነው ሰውነትዎ ቀለሙን ስለተቀበለው ሳይሆን ማስወገድ ስለሚሳነው ነው።
እስቲ በጥልቀት እናንሳ....
የንቅሳት ቀለም እጣፈንታ ምንድንነው?

የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳይቱ ከሆነ ፤ የንቅሳት ቀለም ጠብታዎች በንቅሳቱ አከባቢ ብቻ አይቆዩም። እርቀው ይጓዛሉ። አንዳንድ ጥናቶች የንቅሳት ቀለም ጠብታዎች(ቅንጣቶች) ከንቅሳት ስፍራ አልፈው ንፍፊት ውስጥ እንደተገኙ ይጠቁማሉ። ይህም በተለይ ጥቁር ካርበን (carbon black) ያላቸው ቀለሞች ላይ ተስተውሏል።
'
ታድያ ህክምናዊ አንድምታው ምንድነው?
ንፍፊት የሰውነት መከላከያ ስርአት ማሰማሪያ ካምፕ እንደመሆኑ ፤ እነኝህ ቀለማት የሰውነት መቆጣት ላይ ተጽእኖ ያሳድራሉ። የበሽታ የመከላከያ ስርአታችን ለረዥም ጊዜ ተቆጥቶ እንዲቆይ ሊያደርጉ እንደሚችል ጥናቶች ይጠቁማሉ። ታድያ ግን ሰውነት ቢቆጣም ፤ የሚስተዋል አካላዊ ምልክት ላይኖር ይችላል።

የንቅሳት ቀለም ያጠቆራቸው ንፍፊቶች በናሙና ምርመራ ጊዜ ግራ ያጋባሉ። ከስር ያለ በሽታን ይከልላሉ። የሌለ በሽታም መስለው ምርመራን ሊያሳስቱ ይችላሉ።
ንቅሳት ቆዳን በማቅለሙ ደግሞ ፤ የቆዳ በሽታዎችን በቀለሙ ይደብቃል። የቆዳ ምርመራዎችን አስቸጋሪ ያደርጋል። ይብሱኑ የቆዳ ካንሰር ቅድሚያ እንዳይታወቅ ሊሸሽግ ይችላል። ለዚህም ንቅሳት ቦታ ላይ የሚነሱ የቆዳ ካንሰሮች አርፍደው ሊገኙ ይችላሉ።
📌ያስተውሉ ንቅሳት ካንሰርን ያስከትላል ማለት አይደለም። ነገርግን ካንሰር በቅድሚያ እንዳይያዝ ሊያሰናክል ይችላል። ይህም በህይወት እና ሞት መሀክል ለውጥ ያመጣል።
ይህ መላምት አይደለም። በጥናት የተረጋገጠ ሳይንሳዊ እውነታ ነው!
የንቅሳት ቀለሞች ባህሪስ ምን ይመስላል?
ዘመናዊ የንቅሳት ቀለሞች የሚከተሉት ይኖሯቸዋል።
ጥቁር ካርበን
አዞ የሚባሉ ውህዶች
እንደ ኒኬል፣ ክሮሚየምና ኮባልት አይነት ብረት አስተኔ ላይ የተመሰረቱ የጨው ውህዶች ይኖሯቸዋል።

እነኝህ ውህዶች ለጸሀይ አልትራቫዮሌት ብርሃን ወይም ሌዘር ሲጋለጡ ይፈርሳሉ። ባህሪያቸውን ይለውጣሉ። ሲፈርሱ አንዳንዶቹ መርዛማ ሲሆኑ ሌሎች ለካንሰር አጋላጭ ወደሆኑ ውህዶች (carcinogenic amines) ይቀየራሉ። ከእነኝህም መሀል አለርጂ የማምጣት ባህሪ ያላቸው በመኖራቸው ፤ ከአመታት በኋላ አለርጂ ሊመጣ ይችላል።
ለዚህም ነው የቆዳ ሀኪሞች ንቅሳት ጉዳይ ላይ ጠንቃቃ ሲሆኑ የሚታዩት።
ከንቅሳት ለማገገም ቆዳ ምን ያህል ጊዜ ይፈጅብታል?
ለአይን እይታ ቆዳ በ2-3 ሳምንታት ውስጥ የጠገነ ይመስላል። ሆኖም ከደረሰበት ጉዳት ሙሉ በሙሉ ለማገገም ረጅም ጊዜ ይወስድበታል። የቆዳ መቆጣቱ እስኪለዝብ እስከ 2 ወር (6-8 ሳምንት) ሊፈጅ ይችላል። ከወራት በኋላ እራሱ ንቅሳት ስፍራ ላይ የበሽታ መከላከያ ህዋሳት ዘብ ቆመው ሊስተዋሉ ይችላሉ።

ማገገሙ እንዳለ ሆኖ ሲነቀሱ...
ቆዶ ጥቃት ደርሶበታል። ሰውነትዎ ለኢንፌክሽን ተጋልጧል። ጠባሳ የማጋጠም እድሉም ከፍ ያለ ነው።
ይህ ራሱን የቻለ አደጋ አለው።
ዶክተሮች ለምን አለመነቀስን ይመክራሉ?
የቱ ይሻላል መከላከል አልያም ማስታመም
ከመከላከያ አንጻር ስናየው -
ባለመነቀስዎ ፤ ንቅሳትን ተከትለው የሚመጡ ችግሮችን ሙሉ በሙሉ ሊያስወግዱ ይችላሉ።
ከውበት ባሻገር ፤ በህክምናው ንቅሳት የተረጋገጠ ጥቅም የለውም።
ያሉት አደጋዎች ትንሽ ቢመስሉም ፤ ተደማምረው ብዙ እክል ሊያመጡ ይችላሉ። ከዚህም ባሻገር ዘላቂ ናቸው።

ለዚህም ነው የስፖርት ሐኪሞች ፣ ደም ልገሳ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች እና የቆዳ ስፔሻሉስቶችን አለመነቀስን የሚመክሩት።
በተለይም ለኢንፌክሽን ተጋላጭነት ሊኖራቸው የማይገባ ግለሰቦች ላይ (ዝርዝሩ በቴሌግራም ገጻችን ላይ አለ) መነቀስ አይመከርም።
ታሪካዊ ዳራው
ንቅሳት ለዘመናት የቆየ ነው። በየባህሉ የተለያየ ትርጓሜ እና ምክንያት አለው። የጥንት ግብፃውያን ንቅሳትን ለአምልኮ ሥርዓት ይጠቀሙ ነበር። በሌሎች አፍሪካ አገራትም ንቅሳት ማንነትን፣ ጎሳን፣ እምነትን ይገልጽ ነበር። በጥንታዊ ኢትዮጵያም የታየው ተመሳሳይ ነበር።
ታድያ አሁን ዘመናዊ መሣሪያዎች የምንጠቀም ቢሆንም ፤ እነኝህ መሣሪያዎች የንቅሳትን ህክምናዊ ምህዳር አልለወጡትም።
ኤች አይቪ ኤድስ ተመልሶ እየተስፋፋባት ባለባት አዲስ አበባ ፤ የጉበት ቫይረስ ስርጭት ከፍተኛ በሆነባት ኢትዮጵያ ፤ መነቀስ ምን አይነት ዳፋ ይዞ ሊመጣ ይችል ይሆን?
ምላሹ የእርስዎ ነው!
🧠 ታድያ የሮናልዶ ውሳኔ ሲተነተን ይህን ይመስላል።
ንቅሳትን ማስወገድ ከኢንፌክሽን ተጋላጭነቱን ይቀንሳል።
የደም ልገሳው እንዳይቋረጥ ያደርጋል።
የሰውነት በሽታ መከላከል አላስፈላጊ መቆጣት እንዳይኖረው ያደርጋል።
በቆዳ ምርመራዎች ላይ መሰናክል እንዳይጋጥም ያደርጋል።
አላስፈላጊ የሰውነት ጉዳትን ይቀንሳል።
ለዚህም ይህ ውሳኔው በዘመናዊ ሳይንስ የተደገፈ ነው።





Comments