top of page

የሽንት ቀለም ስለ ጤናችን ምን ይነግረናል?

1 minute ago
5 min read

ጠዋት ከእንቅልፍዎ ተነስተው የሚያደርጉት የመጀመሪያ ነገር ምንድነው? ሽንትቤት ይጠቀማሉን? ለመሆኑ ሽንት ቤት ሲጠቀሙ፤ የሽንትዎን ሁኔታ አይተው ጥያቄ አጭሮብዎት ያውቃል?

ብዙዎች የሽንት መጠን ሲቀንስ “ውሃ አንሶኛል” ፤ መጠኑ ሲበዛ ደግሞ “በቂ ውሃ ጠጥቻለሁ” ብለው ያስባሉ። ምን ያህሎቻችን ስለ ቀለሙስ እናስተውላለን?


ወይስ መቼም “ሽንትማ ምንጊዜም ቢጫ ነው!” ብለን በቸልታ እንዘለዋለን?


ቆም ብለን ብንመለከት፤ የሽንታችን ቀለም ሰውነታችን ውስጥ ስላለው ሁኔታ አስገራሚ ታሪክ ሊነግረን ይችላል።


ሽንት በአብዛኛው ቢጫ ነው። ግን ቀለሙ ከቀን ወደ ቀን፤ ከጠዋት ወደ ማታ፤ እንዲሁም በጠጣነው ውሃ መጠን፣ በበላነው ምግብና በወሰድነው መድኃኒት ቀለሙ ይደምቃል፤ ይፈዛል፣ አንዳንዴም አዲስ መልክ ይይዛል። አንዳንዴም ይህ ቀለም የሰውነታችንን የጤና ሁኔታ የሚነግረን ድምፅ የሌለው የውስጣችን መልዕክተኛ ይሆናል።

ነገር ግን ሁሉም የሽንት ቀለም ለውጥ በሽታ ማለት ነውን?

በጭራሽ!


እያንዳንዱ ቀለም የራሱ የሆነ የጀርባ ታሪክ አለው። እስቲ የተለመዱትንና ያልተለመዱትን የሽንት ቀለሞች ምሥጢር አብረን እንፈትሽ።

🟡ፈዛዛ ቢጫ ቀለም

ይህም ለብዙዎቻችን መደበኛና የተለመደ የሽንት ቀለም ነው።

ለመሆኑ ሽንት ይህንን ቢጫ ቀለም ከየት እንደሚያገኘው ያውቃሉ?

ዩሮቢሊን (Urobilin) ከተባለ ተፈጥሯዊ ንጥረ ነገር ነው። ሰውነታችን በየቀኑ ያረጁ ቀይ የደም ሴሎችን (Red Blood Cells) ሰባብሮ በአዲስ በሚተካበት ጊዜ፤ ሄሞግሎቢን ተሰባብሮ ወደ ቢሊሩቢን፤ ከዚያም ወደዚህ ቢጫ ቀለም ፈሳሽነት ይቀየራል።


የሽንትዎ ቀለም ፈዘዝ ያለ ቢጫ ከሆነ... እንኳን ደስ አለዎት!


ይህ በአብዛኛው በቂ ፈሳሽ እየወሰዱ መሆኑን ሊያመለክት ይችላል!


🟡ደማቅ ቢጫ ቀለም

“ሽንትዎ ደማቅ ቢጫ ሆኖ አስተውለው ያውቃሉ?


ይህ የሽንት ቀለምን የሚያመጣው ንጥረ ነገር መብዛቱን (Concentrated) የሚያሳይ ነው።  ምክንያቱ ደግሞ በጣም ቀላል ነው፦ በሽንትዎ ውስጥ ያለው የዩሮክሮም ንጥረ ነገር መጠን ከፈሳሹ (ውሃው) አንጻር እጅግ የላቀ ሆኗል ማለት ነው።


ለረጅም ሰዓታት ውሃ ካልጠጡ፣ በከባድ ፀሐይ ውስጥ ከቆዩ፣ አልኮል አብዝተው ከወሰዱ ወይም በስፖርት ምክንያት ብዙ ላብ ካፈሰሱ ይህ ቀለም ጎልቶ ይወጣል። በሚገርም ሁኔታ ኩላሊትዎ ያለውን ጥቂት ውሃ ለዋና ዋና የሰውነት ክፍሎች በቁጠባ ለመጠቀም ሲሞክር የሚፈጠር የተፈጥሮ መከላከያ ዘዴ ነው።


በተለይም የጠዋት መጀመሪያ ሽንት በዚህ ቀለም መታየቱ ፍጹም የተለመደ ነው፤ ምክንያቱም ሌሊቱን ሙሉ ከ6 እስከ 8 ሰዓታት ምንም አይነት ፈሳሽ ሳይጠጡ ስለሚያሳልፉ ነው። ስለዚህ ይህ ቀለም በሽታ ሳይሆን፣ ሰውነትዎ “ድርቀትን እየተከላከልኩ ነው፣ እባክዎ አሁኑኑ ውሃ ያጠጡኝ!” እያለ የሚያሳየው መልዕክት ነው።


አንዳንድ ጊዜ እንደ የቫይታሚን ቢ-ኮምፕሌክስ (Vitamin B-complex) ያሉ መድኒቶችም ይህንን የቀለም ለውጥ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ መስተዋል ይኖርበታል።


⚪ እንደ ውሃ የጠራ ቀለም

በተቃራኒው ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ሽንትዎ ምንም አይነት ቀለም ሳይኖረው፣ ልክ እንደ ቧንቧ ውሃ ሊጠራ ይችላል።


በአብዛኛው ይህ ከመጠን በላይ (Over-hydration) ፈሳሽ እየጠጡ መሆንዎን እና ሽንትዎ መቅጠኑን ያሳያል። ብዙ ውሃ መጠጣት መልካም ቢሆንም፤ ሽንት ሁልጊዜ ሙሉ በሙሉ ነጭ መሆኑ ግን በሰውነታችን ውስጥ ያሉትን እንደ ሶዲየም እና ፖታሲየም ያሉ ወሳኝ ኤሌክትሮላይቶችን (Electrolytes) ሊያቀጥናቸው ይችላል።


ነገር ግን እዚህ ላይ አንድ ትልቅ ሳይንሳዊ ሚስጥር አለ!

ውሃ ብዙ ሳይጠጡ ነገር ግን ሽንትዎ ሁልጊዜ እጅግ ግልጽ ከሆነ፤ በተለይም ከፍተኛ የውሃ ጥማትና የሽንት መጠን በጣም መጨመር (Polyuria) ካለዎት መዘናጋት የለብዎትም። ይህ ምናልባት ሰውነትዎ ስኳርን በአግባቡ መቆጣጠር ሲያቅተውና ኩላሊትዎ ግሉኮስን ለማስወገድ ሲታገል የሚታይ የስኳር በሽታ (Diabetes Mellitus )ወይም አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ለዲያቤቲስ ኢንሲፒደስ (Diabetes Insipidus) የመጀመሪያው ስውር ምልክት ሊሆን ስለሚችል፤ ወደ ህክምና ማምራቱ ብልህነት ነው።


🟠ብርቱካናማ የሽንት ቀለም

ሽንትዎ ወደ ደማቅ ብርቱካናማነት (Orange) ከተቀየረ፣ ነገሩን በጥንቃቄ መመርመር መጀመር አለብዎት። ሳይንሳዊ ምክንያቱ በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ይከፈላል፦


  • ከፍተኛ የውሃ እጥረት(Severe Dehydration)፦ ሰውነትዎ እጅግ በጣም ፈሳሽ ሲያጣ፤ ቀለሙ ከደማቅ ቢጫነት አልፎ በመጠኑ ወደ ብርቱካናማነት ሊያደላ ይችላል። ይህ የመጀመሪያው እና ቀላሉ ምክንያት ነው።


  • መድኃኒቶችና ቫይታሚኖች፦ የሚወስዷቸው አንዳንድ መድኃኒቶች የቀለም ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ። ለምሳሌ ለሳንባ ነቀርሳ (TB) የሚሰጠው ሪፋምፒሲን (Rifampicin) ወይም ለቁርጥማት የሚሰጠው ሰልፋሳላዚን (Sulfasalazine) መውሰድ ይህንን ለውጥ ሊያስከትሉ ይችላሉ።


  • የውስጥ አካላት (የጉበት ወይም የሃሞት) እክል፦ ይህ በጣም ልናስተውለው የሚገባ ነጥብ ነው! ብርቱካናማ ሽንት ከማየትዎ ጋር ተያይዞ ቆዳዎ ወይም የዓይንዎ ነጭ ክፍል ቢጫ መሆን (Jaundice) ካለው፤ እንዲሁም ሰገራዎ ከነጣ (Pale stool) ፤ ጉበትዎ ወይም የሃሞት ከረጢትዎ ችግር እንዳለ ፍንጭ ሊሆን ይችላል። ይህን ጊዜ በአስቸኳይ ሕክምና ማድረግ ያስፈልጋል።።

🔴የቀላ ሽንት ቀለም

ይህ በቀላሉ ሊታለፍና በፍጹም ቸል ሊባል የማይገባ ትልቅ የቀለም ለውጥ ነው። ምክንያቱም የቀላ ሽንት በሕክምናው ዓለም ሄማቱሪያ (Hematuria) ወይም በሽንት ውስጥ ደም መኖርን ሊያመለክት ይችላል።

ነገር ግን ከመደንገጥዎ በፊት ነገሩን በሁለት ሳይንሳዊ መንገዶች ከፍለን እንየው፦


  1. የምግብ ምክንያቶች (ቀላሉ መንገድ)፦ በትናንትናው ዕለት ቀይ ስር (Beetroot)፣ ብላክቤሪ (Blackberries) ወይም ሰው ሰራሽ ቀይ ቀለም ያላቸውን ምግቦች በብዛት ተመግበው ከሆነ፤ በውስጣቸው ያለው ቤታኒን (Betanin) የተባለ የተፈጥሮ ማቅለሚያ በሽንት በኩል ስለሚወጣ፤ ቀለሙ ቀይ ሊሆን ይችላል።


  1. የሕክምና ምክንያቶች (የጥንቃቄው ደወል)፦ ምንም አይነት ቀይ ምግብ ሳይበሉ ይህንን ካዩ ግን ነገሩ ከባድ ሊሆን ይችላል። የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን (UTI)፣ የኩላሊት ጠጠር፣ የፕሮስቴት እጢ ማበጥ (BPH)፣ ወይም የከፋ የኩላሊትና የሽንት ፊኛ ሕመሞች በሽንት ውስጥ ደም እንዲታይ ሊያደርጉ ይችላሉ። በተለይ ምክንያቱ ግልጽ ካልሆነ፣ የሆድ ወይም የወገብ ህመም ካለውና ቀለሙ ከቀጠለ በአስቸኳይ የሕክምና ምርመራ ማድረግ ከሁሉ በላይ ብልህነት ነው።


🟤ወደ ቡናማ የሚጠጋ መልክ አልያም የሻይ ቀለም ያለው ሽንት


ይህ ቀለም በተለይ በተደጋጋሚና ለአንዴም ሳይቋረጥ ከታየ ከፍተኛ ትኩረትና ፈጣን እርምጃ ይሻል። በጣም ከባድ የውሃ እጥረት ሽንትን ወደ ቡናማነት ሊያስጠጋው ቢችልም፤ ከዚያ ባለፈ የሻይ ወይም የኮካ ኮላ መልክ ያለው ሽንት ከሁለት ትላልቅ አደጋዎች ጋር ይገናኛል፦

  • የጉበት ሕመም፦ እንደ ሄፓታይተስ ያሉ የጉበት በሽታዎች ቢሊሩቢን የተባለውን ንጥረ ነገር ኩላሊት በከፍተኛ መጠን እንድያስወገድ ስለሚያስገድዱ ሽንት የሻይ መልክ ይይዛል።

  • የጡንቻ መጎዳት (Rhabdomyolysis)፦ ከባድና ከአቅም በላይ ስፖርት ሲሰሩ ወይም ከባድ አደጋ ሲያጋጥም፤ ጡንቻዎች ይጎዳሉ፤ ይፈራርሳሉ። በዚህ ጊዜ በጡንቻ ውስጥ ያለው ብዙ ማዮግሎቢን (Myoglobin) ወደ ደም ገብቶ ኩላሊትን ሊጎዳ ይችላል። ይህም ንጥረ ነገር ሽንትንም ጥቁር ቡናማ ወይም የኮካ ኮላ መልክ ሊያሰጠው ይችላል። ስለዚህ ይህንን ቀለም ካዩ ሐኪም ማማከር ምርጫ ሳይሆን፤ ግዴታ ነው!


ይህ ምስል ትክክለኛ የሽንት ፎቶ አይደለም!
ይህ ምስል ትክክለኛ የሽንት ፎቶ አይደለም!

🟢🔵አረንጓዴ ወይም ሰማያዊ ሽንት ፦ እጅግ እንግዳው ክስተት

ይህንን ቀለም በመጸዳጃዎ ውስጥ ካዩ በጣም ሊደነግጡ ይችላሉ። እውነት ነው! በጣም አልፎ አልፎ የሚከሰት እንግዳ ነገር ነው።


  • ማቅለሚያዎች (Dyes)፦ ለተወሰኑ የኩላሊት ወይም የፊኛ ሕክምና ምርመራዎች የሚሰጡ እንደ ሜቲሊን ብሉ (Methylene blue) ያሉ ማቅለሚያዎች ሽንትን ወደ ሰማያዊ ወይም አረንጓዴ ይቀይራሉ።


  • የመድኃኒት ውጤት፦ እንደ አሚትሪፕቲሊን (Amitriptyline - የጭንቀት መድኃኒት)፣ ፕሮፖፎል (Propofol - ማደንዘዣ) ወይም ኢንዶሜታሲን (Indomethacin) ያሉ መድኃኒቶች ከሰውነት ሲወጡ ሽንትን ሰማያዊ/አረንጓዴ ሊያደርጉት ይችላሉ።


  • የባክቴሪያ ኢንፌክሽን፦ አልፎ አልፎ ደግሞ Pseudomonas የተባለ ባክቴሪያ የሚያመጣው የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን ሽንትን አረንጓዴ ሊያደርገው ይችላል። ይህም የሚሆነው ባክቴሪያው በሚያመርተው አረንጓዴ ንጥረ ነገር (Pyocyanin) ነው።



ግን የሽንት ቀለም ብቻ በሽታ ለመመርመር በቂ ነውን?

በፍጹም አይደለም!

ይህ ሁላችንም በደማቅ መስመር ልንገነዘበው የሚገባ እጅግ ወሳኝ የሕክምና እውነት ነው። የሽንት ቀለም ስለ ሰውነታችን አጠቃላይ የፈሳሽ መጠንና አንዳንድ ስውር ፍንጮችን ሊሰጠን ይችላል እንጂ፣ በቀለም ብቻ “ይህ በሽታ ይዞሃል” ብሎ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።


ሳይንሱ የሚነግረን አስገራሚ እውነታ አለ! አንድ ሰው የከፋ የኩላሊት ድክመት (Chronic Kidney Disease) ቢኖርበትም እንኳ፤ ሽንቱ ምንም አይነት የቀለም ለውጥ ሳያሳይ ፍጹም መደበኛ ቢጫ ወይም እንደ ውሃ የጠራ ሊሆን ይችላል!


ምክንያቱም ብዙዎቹ የኩላሊት ቆሻሻዎች፣ ፕሮቲኖች ወይም ጥቃቅን የደም ህዋሳትን ለማወቅ የማይክሮስኮፕና የቤተ-ሙከራ (Urinalysis) ኬሚካላዊ ምርመራ እንዲሁም ሌሎች ምርመራዎች ያስፈልጋሉ።


ስለዚህ “ሽንቴ መደበኛ ቢጫ ነው፤ ስለዚህ ጤናዬ ፍጹም አስተማማኝ ነው” ብሎ መዘናጋትም ሆነ፣ በሽንትዎ ቀለም ለውጥ መደናገጥ አይገባም።


🩺 መቼ ነው በአስቸኳይ ሐኪም ማማከር ያለብን?

የሽንት ቀለም ለውጥ ከሚከተሉት የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ጋር አብሮ ከታየ ወደ ህክምና ተቋም ለመሄድ ቀጠሮ አይስጡ፦

  • ያለምክንያት የቀላ ሽንት ካስተዋሉ፣

  • የሻይ ወይም የኮካ-ኮላ ቀለም ያለው ሽንት ካለ፣

  • ከቆዳ ወይም ከዓይን ነጭ ክፍል ቢጫ መሆን ጋር የተያያዘ ሽንት ቀለም ለውጥ፣

  • በሚሸኑበት ጊዜ ህመም፣ መውጋት ወይም ማቃጠል ካለ፣

  • በግልጽ የሚታይ የደም ጠብታ ወይም መርጋት ካለ፣

  • ከፍተኛ ትኩሳት፣ የጎን ወይም የጀርባ ህመም ካለ፣

  • በተደጋጋሚ መሽናት ወይም የሽንት መቆራረጥ/መውጣት አለመቻል ካስተዋሉ፣

  • ከፍተኛ የውሃ ጥማት እያለ የሽንት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ከጨመረ፣


📌 ለማጠቃለል…

ያስታውሱ፣ አንድ አይነት ቀለም ስላዩ ብቻ ወዲያውኑ ድምዳሜ ላይ ደርሰው ራሳችሁን በበሽታ መፈረጅ የለብዎትም። የሽንት ቀለምን ሁልጊዜ ከበላነው ምግብ፣ ከጠጣነው ውሃና ከወሰድናቸው መድኃኒቶች ጋር በአንድነት አመዛዝኖ ማየት ያስፈልጋል።


አሳሳቢ የሽንት ለውጥ ወይም ሌሎች ምልክቶች ካሉዎት የሽንት ምርመራን ጨምሮ ተገቢውን የሕክምና ምርመራ ያድርጉ።



🩺 ጤናዎን ይጠብቁ። የተለየ ምልክት ሲያሳስብዎ ሁልጊዜ የባለሙያ እገዛ ያግኙ!

Comments


bottom of page