አንዳንድ ሰዎች መኪና ውስጥ ለምን ይታመማሉ?
- Zebeaman Tibebu
- Jun 25
- 5 min read

ማለዳ ነው። ታክሲው ከሜክሲኮ ወደ አራት ኪሎ ጉዞ ጀምሯል። አንዳንዶቹ ተሳፋሪዎች በመስኮት የሚታየውን የከተማዋን ውበት እያደነቁ ነው፤ ሌሎች ከጓደኞቻቸው ጋር በደስታ ያወራሉ፤ ጥቂቶቹ ደግሞ በጆሮ ማዳመጫቸው ሙዚቃ ያደምጣሉ።
ነገር ግን በዚሁ ተሽከርካሪ ውስጥ አንድ ተሳፋሪ ከባድ ጭንቀት ውስጥ ነው። ባልተለመደ ሁኔታ ዝም ብሏል፤ ፊቱ ገረጥቷል፤ ግንባሩ ላይ ቀዝቃዛ ላብ ይስተዋላል፤ ሆዱም መገላበጥ ጀምሯል። ሳይቆይም በከባድ ድምፅ፦ "ሹፌር! መኪናውን አቁምልኝ ፤ ሊያመኝ ነው!" አለ። .......

ይህ ሁኔታ ለአብዛኞቻችን አዲስ አይደለም። ምናልባት በራሳችን ላይ ደርሶ ወይም ሕጻናት፣ ወጣቶች፣ እና ነፍሰ ጡር ሴቶች ሲቸገሩ አይተን ይሆናል። አንዳንዶች መቆጣጠር አቅቷቸው እዛው ታክሲ ውስጥ ሲያስመልሳቸው፣ ባህሪያቸውን ቀድመው የሚያውቁ ደግሞ ላስቲክ (ፌስታል) ይዘው ይገባሉ።
የሚገርመው ነገር፤ በተሽከርካሪው ውስጥ ያሉ ተሳፋሪዎች በሙሉ የሚያደርጉት ያንን አንድ አይነት ጉዞ ነው። ሆኖም ህመሙ የሚሰማቸው ጥቂቶቹን ብቻ ነው።
እነዚህ ሰዎች ከባድ ምግብ ሳይበሉ ወይም ቀድሞ የነበረ የጤና ችግር ሳይኖርባቸው ለምን እንዲህ ይሆናሉ? ሙሉ በሙሉ ጤነኛ የሆነ ሰው በጉዞ ወቅት ለምን ማዞር፣ ማቅለሽለሽ ወይም ማስመለስ ያጋጥመዋል?
ይህ የጤና እክል በህክምናው "ሞሽን ሲክነስ" (Motion Sickness) ወይም በእንቅስቃሴ ጊዜ የሚከሰት የጉዞ ህመም ይባላል። ዛሬ የምንዳስሰው ስለዚህ ጉዳይ ይሆናል።
የተለመደው የሰው ልጅ ተሞክሮ

ይህ በጉዞ ወቅት የሚከሰት ሕመም በመኪናዎች ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም። ሰዎች በየብስም ተጓዙ፣ በአየርም ሆነ በባሕር ይህ ፈተና ያጋጥማቸዋል። አንዳንዶች በመኪና ውስጥ እንደሚታመሙት ሁሉ፣ ሌሎች ደግሞ በመርከብ፣ በአውሮፕላን ወይም በባቡር ሲጓዙ ተመሳሳይ ስሜት ያስቸግራቸዋል።
እንዲያውም የሚገርመው፤ ዘመን ያመጣቸውን የቨርቹዋል ሪያሊቲ (VR) ሄድሴቶችን አድርገው ምናባዊ ጨዋታዎችን በሚጫወቱበት ወቅት ሕመሙ የሚቀሰቀስባቸው ሰዎች አሉ። ይህ ችግር በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎችን ለዘመናት የፈተነ ጉዳይ ነው።
ነገር ግን አንድ መታወቅ ያለበት እውነታ አለ፦ «ሞሽን ሲክነስ» በራሱ በሽታ አይደለም!
ይህ ሁኔታ ሰውነታችን ላጋጠመው የስሜት ሕዋሳት መደነጋገር (Sensory Confusion) የሚሰጠው ተፈጥሯዊ ምላሽ ነው። ታዲያ ይህንን መደናገር በትክክል ለመረዳት፣ መጀመሪያ ሰውነታችን ውስብስብ በሆነው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ ሚዛኑን እንዴት እንደሚጠብቅ ማወቅ ይኖርብናል።
የሰውነታችንን ሚዛን የሚጠብቀው አስደናቂው ስርዓት

ጆሯችን የሚያገለግለው ለመስማት ብቻ ይመስለናል፤ ነገር ግን እውነታው ከዚህ የተለየ ነው። በውስጠኛው ጆሯችን ጥልቅ ክፍል ውስጥ «ቬስቲቡላር ሲስተም» (Vestibular System) በመባል የሚታወቅ አስደናቂ የተፈጥሮ መዋቅር አለ። ይህ መዋቅር የሰውነታችንን አቅጣጫ፣ እንቅስቃሴ፣ ፍጥነት እና አቀማመጥ ልክ እንደ ስማርት ስልክ «ጂፒኤስ» ያለማቋረጥ እየለካ ለአንጎላችን መረጃ ያደርሳል።
በተመሳሳይ ሰዓት ደግሞ ሌሎች ሁለት ታማኝ ረዳቶች ሥራቸውን ያከናውናሉ፦
ዓይኖቻችን፦ አካባቢያችንን በንቃት እየቃኙ፣ በዙሪያችን ስላለው ነገር ምስላዊ መረጃ ለአእምሮአችን ያስተላልፋሉ።
ጡንቻዎቻችን እና መገጣጠሚያዎቻችን (Proprioception)፦ ስለ ሰውነታችን አቀማመጥ እና የስበት ኃይል ለውጦች የራሳቸውን ምልክት ለአንጎል ይልካሉ።
እነዚህ ሦስት ሥርዓቶች (ጆሮ፣ ዓይን እና ጡንቻዎች) እጅና ጓንት ሆነው፣ ፍጹም በሆነ ስምምነት ይሠራሉ። ከአንጎል ጋር ያለማቋረጥ በመገናኘትም አንድ ወሳኝ መረጃ ይሰጣሉ፦
«ሰውነታችን አሁን የት ነው ያለው? እንዴትስ እየተንቀሳቀሰ ነው?»
ችግሩ እንዴት ይጀምራል? የዓይን እና ጆሮ ግጭት

እስኪ በአንድ ፍጥነት በሚጓዝ መኪና የኋላ ወንበር ላይ ተቀምጠው መጽሐፍ እያነበቡ እንደሆነ ያስቡ። ዓይኖችዎ በገጹ ላይ አርፈዋል። ከዓይኖችዎ እይታ አንጻር የሚንቀሳቀስ ምንም ነገር የለም፤ መጽሐፉ ሙሉ በሙሉ የቆመ ይመስላል። በመሆኑም ዓይንዎ ለአእምሮዎ፦ «እየተንቀሳቀስን አይደለም፣ ሙሉ በሙሉ ቆመናል!» የሚል መረጃ ይልካል።
በተመሳሳይ ሰዓት ግን፤ የውስጠኛው ጆሮዎ ፈጽሞ የተለየ ነገር እያስተዋለ ነው። መኪናው የሚጓዝበትን ፍጥነት፣ መታጠፊያዎችን፣ ፍሬን መያዙን፣ የጥልቁን ጉብታዎችና ንዝረቶች በንቃት እየመዘገበ ነው። ስለዚህ የውስጠኛው ጆሮዎ ለአእምሮዎ፦ «በከፍተኛ ፍጥነት እየተንቀሳቀስን ነው!» ይላል።
አሁን አንጎላችን ትልቅ ችግር አጋጥሞታል! የደረሱት መረጃዎች እርስ በርሳቸው አይገጥሙም። ሳይንቲስቶች ይህንን ሁኔታ «ሴንሰሪ ኮንፍሊክት» (Sensory Conflict/Mismatch) ወይም የስሜት ሕዋሳት ግጭት ይሉታል። ይህ በእይታ እና በእንቅስቃሴ መረጃዎች መካከል የሚፈጠረው አለመጣጣም በበዛ ቁጥር፣ የሕመሙ የመከሰት ዕድል እጅግ ከፍተኛ ይሆናል።

አንጎል በዚህ መረጃ ሲደናገርና ግራ ሲጋባ፤ በውስጡ የሚገኙትን የማቅለሽለሽ እና የማስመለስ የነርቭ ክፍሎችን በድንገት ያነቃቃቸዋል። በዚህም ምክንያት የሚከተሉት የሕመም ምልክቶች ይከሰታሉ፦
ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ
ከባድ ማዞር እና የራስ ምታት
ከፍተኛ ድካም እና ቀዝቃዛ ላብ
የአፍ ምራቅ መብዛት እና አጠቃላይ ደስ የማይል ስሜት
እነዚህ ምልክቶች ብዙውን ጊዜ ቀስ በቀስ ነው የሚጀምሩት። መጀመሪያ ላይ ቀላል ያልተመቸ ስሜት ይፈጠራል፤ ነገር ግን ጉዞው ካልቆመና ከቀጠለ ሕመሙ ይበልጥ እየበረታና እየከበደ ይሄዳል።
ሕፃናት ለምን በብዛት ይጠቃሉ?

ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው በጉዞ ወቅት ይበልጥ እንደሚታመሙና እንደሚቸገሩ ያስተውላሉ። ይህ የወላጆች ምልከታ በሳይንሳዊ ምርምር ሙሉ በሙሉ የተደገፈ እውነታ ነው።
ጨቅላ ሕፃናት፦ ዕድሜያቸው በጣም አነስተኛ በሆኑ ጨቅላ ሕፃናት ላይ የጉዞ ሕመም እምብዛም አይከሰትም።
ከ2 እስከ 12 ዓመት ያሉ ሕፃናት፦ በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ልጆች ግን ለሕመሙ እጅግ ከፍተኛ ተጋላጭ ናቸው። ምክንያቱም የእነዚህ ሕፃናት አንጎል ገና በእድገት ላይ ያለ በመሆኑ፣ ከተለያዩ የስሜት ሕዋሳት የሚመጡ መረጃዎችን የማቀነባበርና የማጣጣም አቅሙ ገና ሙሉ በሙሉ አልዳበረም።
ይሁን እንጂ ሕመሙ በልጅነት ብቻ የሚቀር አይደለም፤ በተለያዩ ምክንያቶች የብዙ ሰዎችን ሕይወት እየተፈታተነ እስከ አዋቂነት ዕድሜ ክልል ድረስ አብሮ ሊቀጥል ይችላል።
አዋቂዎችስ ለምን ይታመማሉ?

የጉዞ ሕመም የልጅነት ችግር ብቻ ቢሆን ኖሮ፤ አውሮፕላኖችና መርከቦች ለሁሉም አዋቂዎች እጅግ ምቹ በሆኑ ነበር።
የሕክምና ምርምሮች እንደሚያሳዩት አዋቂዎች ከላይ ካነሳነው የተፈጥሮ ተጋላጭነት ባሻገር በተለያዩ ምክንያቶች ለዚህ ሕመም ሊጋለጡ ይችላሉ።
ለምሳሌ፦
የማይግሬን ራስ ምታት፦ ይህ ችግር ያለባቸው ሰዎች ከሌላው ሰው በላቀ ደረጃ ለጉዞ ሕመም የመጋለጥ ዕድል አላቸው።
የጾታ ልዩነት፦ ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ተጋላጭነታቸው የላቀ ነው። በተለይም በእርግዝና ወቅት ወይም በወር አበባ ዑደት በሚፈጠር የሆርሞን መለዋወጥ ምክንያት ለዚህ ሕመም የመጋለጥ ዕድላቸው ይጨምራል።
የዘር ተጋላጭነት (Genetics)፦ ከዚህም ባሻገር ይህ ሕመም በቤተሰብ ታሪክ ውስጥ በዘር ተወራራሽነት ሊተላለፍ እንደሚችልም መታወቅ አለበት።
ስልኮች፣ ታብሌቶች እና መጽሐፍት ህመሙን የሚያባብሱት ለምንድን ነው?

ብዙ ሰዎች በጉዞ ወቅት አንድ ዓይነት ተመሳሳይ ልማድ ያስተውላሉ፦ መስኮት ላይ ሆነው ወደ ውጭ እየተመለከቱ ሳሉ ምንም አይሰማቸውም፤ ነገር ግን ስልካቸውን መነካካት ወይም መጽሐፍ ማንበብ እንደጀመሩ ወዲያውኑ ሕመሙ ይቀሰቀሳል።
ይህ በፍጹም በአጋጣሚ የሚከሰት አይደለም!
ምክንያቱም፦
ዓይኖች ሙሉ በሙሉ በማይንቀሳቀስ ነገር ላይ ስለሚያተኩሩ '፤ ለአንጎል «ቆመናል» የሚል መልዕክት ይልካሉ።
የውስጠኛው ጆሮ የመኪናውን መናወጥ፣ መታጠፍ እና ፍጥነት ለአእምሮ ይነግራል።
በዚህ ምክንያት በስሜት ሕዋሳቱ መካከል የሚፈጠረው ግራ የተጋባ መልዕክት ይበልጥ ይጠነክራል። አንጎልም ከመጠን በላይ ይደነጋገራል። ማቅለሽለሽ፣ ማዞር እና ማስመለስም በከፍተኛ ፍጥነት የሚከሰተው ለዚህ ነው። በሚንቀሳቀስ መኪና ውስጥ ስልክ ማየት ወይም መጽሐፍ ማንበብ ለጉዞ ሕመም ዋነኛው ጠንቅ የሚሆነው በዚህ ሳይንሳዊ ምክንያት ነው።
ይህንን መከላከል ይቻላል?(የተግባር መፍትሔዎች)

የጉዞ ሕመምን ሁልጊዜ ሙሉ በሙሉ መከላከል ባይቻልም፣ የሚከተሉትን ቀላል እና ጠቃሚ የተግባር ስልቶች በመጠቀም የሕመሙን ተጋላጭነት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ይቻላል፦
አይኖት ሩቅ ያሉ ነገሮች ላይ ይረፍ፦ ዓይንዎ መኪና ውስጥ ከመሆን ይልቅ፤ ከመኪና ባሻገር ያሉ ከመንገድ ዳር በሚታዩ ነገሮች ላይ ያተኩር። ሩቅ ላይ ባሉ ተራሮች፣ መንገዶች፣ ሕንፃዎች ወይም የአድማስ መስመር (Horizon) ላይ ሲያተኩሩ፣ ዓይኖችዎ የውስጠኛው ጆሮዎ የሚሰማውን ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ማየት ይጀምራሉ። በዚህ ጊዜ ለአንጎል የሚላኩት መረጃዎች ወጥ ስለሚሆን ፤ መደናገሩ ይቀንሳል።
በጉዞ ወቅት ማንበብ ያቁሙ፦ በጉዞ ወቅት መጽሐፍትን፣ ስልኮችን እና ታብሌቶችን በፍጹም አይንኩ፤ ያስቀምጧቸው።
መኪና ውስጥ የሚቀመጡበትን ቦታ በጥንቃቄ ይምረጡ፦ የመኪናው መናወጥና እንቅስቃሴ አነስተኛ በሆነበት ቦታ ላይ ይቀመጡ። ለምሳሌ፦ በመኪና ውስጥ የፊት ወንበር፣ በአውሮፕላን የክንፉ አቅራቢያ፣ ወይም በባሕር ጉዞ ወቅት የመርከቡ መካከለኛ ክፍል ላይ መቀመጥ ይመረጣል።
መኪናውን ውስጥ አየር እንዲናፈስ መስኮት ይክፈቱ። የመኪናውን መስኮት በመክፈት ንጹሕ አየር እንዲገባ ፤ መኪናው እንዲናፈስ በማድረግ የብዙ ሰዎችን ምቾት በፍጥነት መመለስ ይቻላል።
ከጉዞ በፊት ከባድ ምግቦችን ያስወግዱ፦ ከጉዞ ቀደም ብሎ ቅባት የበዛባቸው ወይም ከባድ ምግቦችን መመገብ ማቅለሽለሽና ማስመለስን ይበልጥ ያባብሳል። በምትኩ ቀለል ያሉ ምግቦችን ይመገቡ።
በረጅም ጉዞዎች ወቅት እረፍት ማድረግ ይኖርብዎታል፦ ረጅም መንገድ በሚጓዙበት ጊዜ ፤ መኪናው ለአጭር ጊዜ ቆሞ እረፍት ማድረግ ይመከራል። ለአጭር ጊዜ ንጹሕ አየር ማግኘትና ማረፍ ሰውነት እንዲረጋጋ ይረዳል።
የመድኃኒት አጠቃቀምን ጊዜ ማወቅ፦ ይህንን የሕመም ስሜት ለማጥፋት ፤ ያለሐኪም ትዕዛዝ የሚወሰዱ ፀረ-ሂስታሚን (Antihistamines ) ወይም በሐኪም የሚታዘዙ በጆሮ ጀርባ የሚለጠፉ መድኃኒቶች (Scopolamine patches) ይጠቅማሉ።ሆኖም ግን እነዚህ መድኃኒቶች ቅድመ-መከላከያ መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም። ከጉዞው ከ30 እስከ 60 ደቂቃዎች በፊት መወሰድ አለባቸው። አንዴ ማቅለሽለሽና ማስታወክ ከጀመረ በኋላ መድኃኒቶቹ የመሥራት አቅማቸው በጣም ዝቅተኛ ነው።
ሐኪም ማየት ያለብዎት መቼ ነው?

የጉዞ ሕመም በአብዛኛው ጊዜ በራሱ ዘላቂ ጉዳት የለውም፤ ጉዞው ሲቆም ወይም ከተሽከርካሪው ሲወርዱ ምልክቶቹ ወዲያውኑ ይጠፋሉ። ሆኖም ግን፣ የሚከተሉት የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ከተስተዋሉ፤ አስቸኳይ የሕክምና ምርመራ ማድረግ ተገቢ ነው፦
🔴 ከመጠን ያለፈ ህመም፦ ምልክቶቹ ባልተለመደ ሁኔታ በጣም ከባድ፣ ለሕይወት አስቸጋሪ ወይም ሙሉ በሙሉ አቅም የሚያሳጡ ከሆኑ፤
🔴 ያለ ጉዞ መከሰት፦ ምልክቶቹ ምንም ዓይነት ጉዞ በማያደርጉበት፣ ሙሉ በሙሉ ዕረፍት ላይ በሆኑበት ወይም በተቀመጡበት ጊዜም የሚከሰቱ ከሆነ፤
🔴 የጆሮ ሕመም ምልክቶች፦ ከጉዞ ሕመሙ ጋር ተያይዞ የመስማት ችግር፣ በጆሮ ውስጥ የማያቋርጥ መጮህ ወይም የሰውነት ሚዛን መዛባት ካለ፤
🔴 ከባድ ራስ ምታት፦ ከማቅለሽለሹ ጋር አብሮ የሚመጣው የራስ ምታት እጅግ በጣም የበረታ ከሆነ።
🔴 የፈሳሽ ማጣት አደጋ፦ ማስታወኩ በተደጋጋሚ በመከሰቱ ምክንያት ሰውነት ከፍተኛ የፈሳሽ ማነስ (Dehydration) ካጋጠመው፤
በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ፣ ችግሩ ከተራ የጉዞ ሕመም ይልቅ ከጀርባ ተያይዞ ያለ የሌላ ከባድ የጤና እክል ጠቋሚ ሊሆን ስለሚችል፣ ፈጥነው የሕክምና ባለሙያ ማማከር ይኖርብዎታል።
ሁልጊዜም ለጤናዎ ቀዳሚ ቦታ በመስጠት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ያድርጉ።
መልካም እና ጤናማ ጉዞ!




Comments