top of page

ሥራዬን እወደዋለሁ ግን መሄድ ሰልችቶኛል፦ ሥራ እና የአእምሮ ጤና

“ሥራዬን እወደዋለሁ… ግን ከእንግዲህ ወደ ሥራ መሄድ አልፈልግም።”

“ቀኑን ሙሉ ደክሞኛል.... እቤት ስመጣም ለቤተሰቦቼ ጊዜ የለኝም።”

“በፊት ደስ የሚያሰኙኝ ነገሮች፤ አሁን ምንም አይሰማኝም።”

“ሁሌ እጨነቃለሁ… ግን ምን እንደሆነኩኝ አላውቅም።”


እነዚህ አማራጮች ሰነፍ ወይም መሥራት የሰለቻቸው ሰዎች የፈጠሯቸው ሰበቦች አይደሉም። እነዚህ በሀገራችን በብዙ የሥራ ዘርፎች ውስጥ በየቀኑ የሚሰሙ፤ ነገር ግን አብዛኛው ሰው ትኩረት የማይሰጣቸው የጤና እክል ምልክቶች ናቸው።


ከፍተኛ የሥራ ጫና፣ ረጅም የሥራ ሰዓት፣ በቂ እረፍት ማጣት እና የሥራ ዋስትና ማጣት የአንድን ጠንካራ ሠራተኛ አእምሮ ቀስ በቀስ ያደክማሉ። ከዚህም በላይ በሥራ ቦታ የሚፈጠሩ ግጭቶች፣ አድልዎ እና የልፋት እውቅና አለመሰጠት የሰውን ውስጣዊ አቅም ያመናምኑታል።



ይህ በሥራ ቦታ የሚፈጠር ሥር የሰደደ ውጥረት በአግባቡ ካልተያዘና መፍትሔ ካልተበጀለት፣ ቀስ በቀስ ወደ ከባድ የድብርት (Depression) እና የጭንቀት (Anxiety) ሕመም ሊያመራ ይችላል። አእምሯችንም እንደ አካላችን ይታመማል። ድካሙን ችላ ማለት ሊያስከፍለን ይችላል።


መጀመሪያ ልዩነቱን እንወቅ

ብዙዎቻችን እላይ ያነሳናቸውን ስሜቶች በአንድ ላይ እንቀላቅላቸዋለን። ነገር ግን መፍትሔ ለማግኘት በመጀመሪያ በሥራ ጭንቀት፣ በሥራ በከፍተኛ ሁኔታ መዳከም (Burnout) እና በድብርት መካከል ያለውን ልዩነት መለየት ይኖርብናል።


1️⃣ የሥራ ጭንቀት — “ብዙ ነገር ተደራርቦብኛል”

ጭንቀት ራሱ ሁልጊዜ በሽታ አይደለም። የሥራ ጫና ሲጨምር፣ አስቸኳይ ሥራ ሲኖር ወይም በሥራ ቦታ ፈታኝ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ መጨነቅ የተለመደ የሰውነትና የአእምሮ ምላሽ ነው። ነገር ግን ይህ ጫና ያለማቋረጥ ከቀጠለ፤ ሰውነትና አእምሮ ከሥራው ጋር መላመድ ሊያቅታቸው ይችላል። ያኔ የሚከተሉት ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ፦

  • ሁልጊዜ መጨነቅና ስጋት መግባት

  • በቀላሉ መበሳጨትና መቆጣት

  • የራስ ምታት

  • የልብ ምት መጨመር

  • የእንቅልፍ ችግርና ትኩረት ማጣት

  • የማያቋርጥ የሰውነት ድካም መሰማት

2️⃣ ከፍተኛ የሥራ ድካም — Burnout (ስራ ለመስራት አቅም ማጣት)

“Burnout” ማለት በቀላሉ “ደከመኝ” ማለት አይደለም።

ዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ከፍተኛ የሥራ ድካምን (burnout)በሥራ ላይ ያለ፤ ለረጅም ጊዜ የቆየና በሥራ ጫና የሚመጣ የአእምሮ መዛል ሁኔታ እንደሆነ ይገልጸዋል። ይህ ሲኖር በዋናነት ሦስት ነገሮች ጎልተው ይታያሉ፦

  • ከፍተኛ የአካልና የአእምሮ ዝለት (Exhaustion)፦ በቀላሉ ሊቀረፍ የማይችል፤ የማያቋርጥ የመዛል (የመዝለፍለፍ) ስሜት።

  • ከሥራ መራቅ እና መማረር (Cynicism/Detachment)፦ ከሥራ ጋር በተያያዘ የአሉታዊነት፣ የተስፋ መቁረጥ፣ የመበሳጨት ወይም ከሥራው የመሸሽ (የመራቅ) ስሜት።

  • የውጤታማነት እና የችሎታ መቀነስ (Reduced Professional Efficacy)፦ "ምንም ብሠራ ለውጥ አላመጣም" በሚል ስሜት በራስ መተማመንን ማጣት እና በሥራ ላይ ፍሬያማ አለመሆን።


ስለዚህ ቀድሞ ለሥራዎ የነበረዎት ፍቅር፣ ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት እጅግ ከፍተኛ የነበረ ቢሆንም፤ በሂደት ግን ይህ የረጅም ጊዜ ያልተፈታ የሥራ ጫና ያንን ጉልበትዎን ሙሉ በሙሉ ሊያሟጥጠው ይችላል። በዚህም ምክንያት በአንድ ወቅት በትልቅ ምኞትና ደስታ ይሠሩት የነበረውን የሥራ መስክ፤ በጊዜ ሂደት “ከእንግዲህ ይህን ሥራ አልፈልገውም፣ አልችልበትምም” ወደሚል ፍጹም ተስፋ የመቁረጥ፣ የመማረር እና የማንነት ቀውስ ደረጃ ላይ ሊያደርስዎት ይችላል። ይህ የባዶነት ስሜት ከሥራ ገበታዎ አልፎ በዕለት ተዕለት የግል ሕይወትዎ ላይም ጥላ ማሳረፉ አይቀሬ ነው።


በዚህ ዙሪያ በሀገራችን ያለውን ጫና ለማየት አንድ ማሳያ እንውሰድ፦ በኢትዮጵያ ከ4,000 በላይ ጤና ባለሙያዎች ላይ የተደረገ ጥናት ከግማሽ በላይ የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች (52.9% ) ጭንቀት ሲታይባቸው ፤ ከ አንድ ሶስተኛ (39.1%)በላይ የሚሆኑት ከፍተኛ የሥራ ድካም ስሜት(burnout) አሳይተዋል። ችግሩ ግን በጤና ባለሙያዎች ብቻ የተወሰነ አይደለም። በሁሉም የሥራ ዘርፎች ላይ ይስተዋላል።


3️⃣ድብርት — Depression

እዚህ ላይ ግን አንድ ጠቃሚ እና ወሳኝ የሕክምና ልዩነት አለ። ከፍተኛ የሥራ ድካም (burnout) በዋናነት ከሥራ ጋር ብቻ የተያያዘ ነው። ድብርት በሥራ ቦታ አስገዳጅ ሁኔታዎች ብቻ የሚቀሰቀስ አይደለም። በተፈጥሮ፣ በቤተሰብ፣ በሕይወት አጋጣሚዎች ወይም የሥነ-ልቦና ምክንያቶች ሊመጣ ይችላል። ለዚህም ከፍተኛ የሥራ ድካም አንድ ሰው ከሥራው ሲርቅ ወይም የሥራ አካባቢው ሲቀየር ሊሻሻል ይችላል። ድብርት ግን ግለሰቡ የትም ቦታ ቢሆን አብሮት የሚጓዝ ስሜት ነው።


ድብርት ሲኖር አንድ ሰው፦

  • ለብዙ ቀናት ከባድ የሐዘን ወይም የባዶነት ስሜት ሊሰማው ይችላል።

  • ቀድሞ ያስደስቱት የነበሩ ነገሮች (ቤተሰብ፣ ጓደኛ፣ ስፖርት) ጨርሶ ደስታ ሊያጡበት ይችላሉ።

  • የእንቅልፍ ችግር ሊያጋጥም እንዲሁም ሰውነት አብዝቶ ሊደክም ይችላል።

  • በትናንሽ ነገሮች ላይ እንኳ ትኩረት ሊያጣ ይችላል።

  • የማይጠቅም፣ አቅም የሌለው ወይም ሙሉ በሙሉ የማይችል ሰው እንደሆነ ሊሰማው ይችላል።


እነዚህ ምልክቶች በሥራ ገበታ ላይ ብቻ ሳይሆን በቤት፣ በቤተሰብ እና በማኅበራዊ ሕይወትም ውስጥ በግልጽ ሊታዩ ይችላሉ።


ከሁሉም በላይ ሊያሰጋን የሚገባው ምንድነው?

አንድ ቀን መድከም፣ አልፎ አልፎ በሥራ መበሳጨት ወይም ከከባድ ሳምንት በኋላ ዝልፍልፍ ማለት የአእምሮ ሕመም ምልክት አይደለም። ሰውነትዎና አእምሮዎ ከዕለታዊ ሩጫ በኋላ ዕረፍት መፈለጋቸው ተፈጥሯዊ ነው።


ነገር ግን ቀይ መስመሩ የሚታለፈው እዚህ ጋር ነው፦ ችግሩ ያለማቋረጥ ከቀጠለ፣ የሥራው ጫና ቀልሎ ወይም የዕረፍት ቀናት መጥተው እንኳን የድካምና የጭንቀት ስሜቱ ካልተሻሻለ፣ ከሥራ ውጭ ባለው የግል ሕይወትዎ ላይ ጥቁር ጥላ ከጣለ እና መደበኛ የዕለት ተዕለት ተግባራትን ማከናወን ከአቅም በላይ ሆኖ ሲገኝ ጉዳዩን ፈጽሞ ችላ ማለት የለብዎትም። ይህ አእምሮዎ በአስቸኳይ እርዳታ እየጠየቀ መሆኑን የሚያሳይ የሕክምና ማስጠንቀቂያ ምልክት ነው።


ችላ እንዳይሉ!

እንግዲህ ችግሩ የእርስዎ ብቻ ነው?

ፈጽሞ አይደለም!

ይህ ምናልባት የዚህ ጽሑፍ በጣም አስፈላጊው መልዕክት ነው።

ማኅበረሰባችን ውስጥ “ጠንካራ ሁን”፣ “ተቋቋመው”፣ “ሥራ እኮ እንዲህ ነው” በማለት በጭንቀት ላይ ጭንቀት መደርደር የተለመደ ነው። ነገር ግን ሰውን ማስገደድ ሁልጊዜ መፍትሔ አይሆንም። የሥራ ቦታ የአንድን ሰው የአእምሮ ጤና በቀጥታ የመጉዳትና የመሰባበር ከፍተኛ አቅም አለው።


ዓለም አቀፍ መረጃዎች የሥራ ቦታ የአእምሮ ጤና ጉዳይ ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ ያሳያሉ። የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚገልጸው፤ በየዓመቱ 12 ቢሊዮን የሥራ ቀናት በድብርትና በጭንቀት ምክንያት ይጠፋሉ። በዓለም ዙሪያ ካሉ ሠራተኞች መካከል ከ40% በላይ የሚሆኑት በየቀኑ ከሥራ ቦታ ጋር በተያያዘ  ከፍተኛ ጭንቀት ያጋጥማቸዋል። ይባስ ብሎም ወደ 43% የሚጠጋው የሰው ኃይል ደግሞ  የከፍተኛ የሥራ ድካም (Burnout) ሰለባ ነው።  በሀገራችን ኢትዮጵያም በተወሰኑ የመንግሥት ሆስፒታሎችና ተቋማት ላይ የተደረጉ ጥናቶች ደግሞ ይህ ቁጥር እስከ 54.7% ከፍ ሊል እንደሚችል ያመለክታሉ።

ይህ አስደንጋጭ ቁጥር የሚያሳየው ችግሩ የአንድ ሰነፍ ሰው የግል ሰበብ ሳይሆን፤ በማኅበረሰባችን ውስጥ በስውር እየተስፋፋ ያለ ወረርሽኝ መሆኑን ነው። የአእምሮ ጤናን የመጠበቅ ኃላፊነት ደግሞ የሠራተኛው ብቻ አይደለም። የሥራ ቦታዎችና ተቋማትም የሠራተኞቻቸውን አእምሯዊ ደኅንነት የመጠበቅና ምቹ አካባቢን የመፍጠር ትልቅ የሕክምናም ሆነ የሞራል ግዴታ አለባቸው።


እርስዎ ምን ማድረግ ይችላሉ?

ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች እርስዎ ላይ ከታዩ፣ እጅ ከመስጠትዎ በፊት እነዚህን ወሳኝ የስነ-ልቦና እርምጃዎች ይውሰዱ፦

1. ችግሩን ለራስዎ አምነው ይቀበሉ፦ “ሌሎችም እኮ ይሠራሉ፣ እኔ ምን ሆኜ ነው?” በማለት ውስጣዊ ስብራትዎን አይካዱ። ሰውነትዎና አእምሮዎ እርዳታ እየጠየቁ መሆኑን፤ በቅንነት መቀበል የመፍትሔው መጀመሪያ ነው።


2. ከሚያምኑት ሰው ጋር ይነጋገሩ፦ ስሜትዎን በውስጥዎ አፍነው አይያዙ። የሥራ ባልደረባ፣ የቅርብ ጓደኛ፣ የቤተሰብ አባል ወይም የአእምሮ ጤና ባለሙያ ሊሆን ይችላል፤ ይንገሯቸው። ስለ ገጠመዎት ፈተና በግልጽ መናገር ድክመት ሳይሆን የጥንካሬ ምልክት ነው።


3. ከተቻለ የሥራ ጫናዎን ይገምግሙ፦ ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ለመጨረስ በመሞከር ራስዎን አያድክሙ። ከሥራዎት ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠውን ደረጃ ይለዩ። ከተቻለም ሥራዎችን ለሌሎች ያካፍሉ ወይም ድጋፍ ይጠይቁ።


4. እረፍትን እንደ ቅንጦት አይቁጠሩ፦ በቂ እንቅልፍ፣ መደበኛ ዕረፍት፣ መጠነኛ አካላዊ እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም ከቤተሰብና ከጓደኞች ጋር ጥራት ያለው ጊዜ ማሳለፍ ለአእምሮ ጤናዎ የሚሰጡት ዋነኛ መድኃኒቶች ናቸው።


5. ምልክቶቹ ከቀጠሉ የጤና ባለሙያ ያነጋግሩ፦ በተለይ ከባድ የድብርት ስሜት፣ ከፍተኛ ጭንቀት፣ የማያቋርጥ የእንቅልፍ መታወክ፣ ራስን የመጥላት ስሜት ካዩ እንዲሁም ዕለታዊ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን ከተቸገሩ፤ ሳይዘገዩ የአእምሮ ጤና ባለሙያ (Psychiatrist/Psychologist) ማማከር ይኖርብዎታል።


🌱 ሥራ ሕይወታችንን ሊያሻሽል እንጂ ሊያፈርስ አይገባም!

ሥራ ለሕይወታችን እጅግ አስፈላጊ ነው። ገቢ ይሰጠናል። ማኅበራዊ ክብር ያጎናጽፈናል። በዕለት ተዕለት ውሎአችንም ውስጥ ግልጽ ዓላማ እንዲኖረን ያደርጋል።


ነገር ግን ሥራ ሁልጊዜ የሚያስፈራን፣ ሰላም የሚነሳን፣ የሚያስጨንቀን እና ለቤታችንና ለቤተሰባችን እንኳን ትርፍ ጉልበት የማይተውልን ከሆነ፤ ችግሩን “እኔ ደካማ ስለሆንኩ ነው” ብለን በራስ መውቀስ መደምደም የለብንም።


ምናልባት የቅርብ ድጋፍ ያስፈልገን ይሆናል። ምናልባት የሥራ ጫናው ሊቀነስልን ይገባል። ምናልባት የሥራ አካባቢያችን ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል። አልያም የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልገን ደረጃ ደርሰን ይሆናል።


የአእምሮ ጤና ችግር ድክመት አይደለም እርዳታ መፈለግም ፈጽሞ አያሳፍርም። አእምሮዎን መጠበቅ ሥራዎን መጥላት ሳይሆን፣ ውድ ሕይወትዎን እና ራስዎን መታደግ ነው!


🚨 አስቸኳይ መልዕክት


አንድ ሰው በከፍተኛ ጭንቀት ምክንያት ራሱን ለመጉዳት ወይም ሕይወቱን ለማጥፋት የሚያስብ ከሆነ፤ ጉዳዩን በፍጹም በሚስጥር አይያዙት። ብቻውን እንዳይሆን በማድረግ፤ በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመውሰድ አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ እንዲያገኝ ያድርጉ።

1 Comment


azwellgi@gmail.com
15 hours ago

Very important point thank you

Like
bottom of page