top of page

ተዋርደን ይሆን!? ታዋቂው ዩቲዩበር በኢትዮጵያ ያጋጠመው ህመም ምንድን ነው?

ጉብኝቱ ለረዥም ጊዜ ተጠብቋል። ሆኖም አመጣጡ ግን ድንገተኛ ነበር!


በዩቱዩብ ብእር ስሙ አይ ሾው ስፒድ በመባል የሚታወቀው አሜሪካዊው ዳረን ጄሰን ዋትኪንስ ጁኒየር ከ 3 ቀን በፊት ኢትዮጵያን ጎብኘቷል። ይህ ዩቲዩበር በዩቲዩብ ቀጥታ በሚያደርጋቸው መስተጋብሮች በአለም ዙሪያ የተወደደ ነው። ለዚህም የተለያዩ ሽልማቶች ያገኘ ሲሆን በፈረንጆቹ 2025 ራሱ እጅጉን ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ ተብሎ በ ሮሊንግ ስቶንስ ተሸልሟል።




ይህም የሱን ጉብኝት ለየት ያደርገዋል። ጉብኝቱ ቀጥታ ስለሆነ ፤ ብቻውን ሳይሆን በአለም ዙሪያ ያሉ ተከታዮቹም አብረውት ይጎበኛሉ። የኢትዮጵያውን "Irl stream in Ethiopia" በወቅቱ ወደ 9 ሚሊየን ሰዎች በኢንተርኔት ተከታትለውታል። ጉብኝቱ በቀጥታ ለተላለፈበት 4 ሰአት ከ 52 ደቂቃ የአለም አይኖች ኢትዮጵያ ላይ አተኩረው ነበር። ለብዙዎቹም አስደማሚ እሱም እጅጉን የወደደው ጉብኝት ነበር።


ጉድ እና ጅራት ከበስተኋላ ነው እንዲሉ...

ጥሬ ስጋ ከበላ ጮማ ከቆረጠ፣ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦቹን ካጣጣመ በኋላ፤ ድንገት ሆዱን ታመመ። ሽንትቤትም ቆይቶ ሲወጣ ያሉ ምስሎች በማህበራዊ ድህረ ገጾች በስፋት ተጋርተዋል።


አይሾው ስፒድ ጥሬ ስጋ ሲበላ

ይህ አሳፋሪ ጉዳይ ይሆን? ስለ ኢትዮጵያ አለም ያለውን ምስልስ አጠልሽቶ ይሆን?


ካስተዋሉ ይህ የዚህ ዩቲዩበር ችግር ብቻ አይደለም።


ጥቂት የማይባሉ ጎብኚዎችን ያጋጥማል። ይህ የህክምና ክስተት በየአመቱ በአፍሪካ፣ በእስያ እና በላቲን አሜሪካ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጎብኝዎችን ይጎዳል።


ለምን?

ይህን ለመረዳት ማስተዋል ያለብዎት ነጥቦች እነሆ፡


 1️⃣ተቅማጥ በሽታ አይደለም ፤ ምልክት ነው።


በህክምና ተቅማጥ ራሱን እንደቻለ በሽታ አይታዩም። አንጀት ጋር ቁርኝት ያላቸው በሽታዎች የሚያሳዩት ምልክት ነው። በሽታ መኖሩን የሚናገር መልእክት ነው።


በህክምናው ቀጠን ያለ አልያም ውሀ የሆነ ሰገራ ፤ ከተለመደው በላይ አልያም በ 24 ሰአት ውስጥ ለ 3 ጊዜ ካጋጠመ ፤ ተቅማጥ ይባላል።

ይህም አንጀት እንግዳ ለሆነበት ፣ ለሚጎዳው እንዲሁም ከአቅሙ በላይ ለሆነበት ነገር ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ያሳያል። የተጓዦች አንጀት ደግሞ ፣ ለሚጎበኙት አገር ባይተዋር ነው።


2️⃣ አንጀት ትውስታ አለው - እና ተጓዦች ይህ አይኖራቸውም።



በኢትዮጵያ ስንኖር የምንለምደው አየሩን ብቻ አይደለም። በሀገራችን ተስፋፍተው የሚገኙ በሽታ አምጪ ተህዋሳት ጋር ሰውነታችን ተላምዷል። የምንጠጣው ውሀ የምንመገብው ምግብ ውስጥ ሊገኙ የሚችሉ ረቂቅ ተሕዋስያን ለአንጀታችን እንግዳ አይደሉም። እነሱን ከዚህ በፊት የሚያውቃቸው የበሽታ መከላከያ ስርዓታችንም አፋጣኝ እና በቂ ምላሽ ስለሚሰጥ ፤ በለመድናቸው ተሕዋሳት እምብዛም አንታመምም።


ጎብኚዎች ግን ይህ ትውስታ የላቸውም።

ለዚህም ተመሳሳይ ምግብ ተመግበው ፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ብዙውን ጊዜ ምንም ምልክት አይታይባቸውም። ጎብኚዎች ግን ምልክቶች ይሳያሉ። ወደ ገጠሪቷ ኢትዮጵያ ሄደው እርሶም ይህ አጋጥሞት ይሆናል።


ያስተውሉ! ልዩነቱ የበሽታ መከላከያ ስርአት እንጂ ንፅህና አይደለም።

3️⃣ ዋናው ተጠርጣሪ ፡ የተጓዥ ተቅማጥ


በአለም አቀፍ ዙሪያ ይህ ህመም ስያሜ አለው። የተጓዥ ተቅማጥ ተብሎ ይጠራል። ወደ ዝቅተኛ  እና መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው አገሮች የሚጓዙ ከ30-70% የሚሆኑት ሰዎችን ያጠቃል



📌 ይህም በተለያዩ በሽታ አምጪ ተህዋሳት የሚመጣ ሲሆን፤ በጣም የተለመዱት የሚከተሉት ናቸው

  1. ኢንቴሮቶክሲጅኒክ ኢ. ኮላይ (ETEC)

  2. ካምፓሎባክተር

  3. ሺጌላ

  4. ሳልሞኔላ

ከዚህም ባሻገር እንደ ኖሮ ቫይረስ ባሉ ቫይረሶች እንዲሁም እንደ ጂያርዲያ ባሉ ፓራሳይቶች ይመጣል።


እነዚህ ተህዋሳትን ለመለየት ታድያ የላብራቶሪ ምርመራ ያስፈልጋል።


4️⃣ምግብ እና ውሃ ፡ የተህዋሳቱ መኖሪያ


አደጋው "የኢትዮጵያ ምግብ" አይደለም ።

ረቂቅ ተሕዋስያን መጋለጥ ነው። ጎብኚዎች ብዙ ጊዜ እንዲጋለጡ የሚያደርጉ ምንጮች መሀከል የሚከተሉት በብዛት ይጠቀሳሉ።

  • ያልታከመ ወይም በበቂ ያልታከመ ውሃ

  • መጠጥ ላይ የሚደባለቁ የበረዶ አንኳሮች

  • ያልበሰሉ አትክልቶች

  • ንጽህናው ባልተጠበቀ ውሀ የታጠቡ ፍራፍሬዎች

  • ንጽህናው በጥንቃቄ ክትትል ያልተደረገለት የጎዳና ላይ ምግቦች ብዙ ጊዜ ተጓዦች ላይ ህመሙ እንዲታይ ያደርጋሉ።


ከዚህም ባሻገር በስርአት ባልታከመ ውሃ ጥርስን መቦረሽ እንኳን  ይህንን በሽታ ሊያስከትል ይችላል።


5️⃣ምግቡ ንጹህ ሆኖ አንጀት ሊያምጽ ይችላል።


ሁሉም ምግብን ተከትሎ የሚመጣ የተቅማጥ በሽታ በበሽታ አምጪ ተህዋስ አይመጣም። ባክቴሪያ፣ ቫይረስና ፓራሳይት በሌለበት ሁኔታ ራሱ ተቅማጥ ሊያጋጥም ይችላል።



አንጀት ላለመደው የምግብ አይነት ሲጋለጥ ተቅማጥ ሊያጋጥም ይችላል። በተለይም

  • እንደ እንጀራ ያሉ ፈርመንትድ ሆነው የሚዘጋጁ ምግቦችን ሲመገቡ

  • ውስጣቸው ከፍተኛ-ፋይበር/አሰር ያላቸው ምግቦችን ሲመገቡ (እንጀራ ከፍተኛ ፋይበር አለው)

  • አንጀት ያለመዳቸውን ቅመሞች ሲመገቡ ፤ ለምሳሌ ሰናፍጭ፣ አዋዜ እና የመሳሰሉትን ሲመገቡ

  • ከፍተኛ ፕሮቲን እና ስብ/ቅባት ያላቸውን ምግቦች ሲመገቡ ተቅማጥ ሊያጋጥም ይችላል።


ይህም እንደ ምግቡ አይነት በህክምናው ኦስሞቲክ አልያም ፈንክሽናል ተቅማጥ የሚባሉትን የተቅማጥ አይነቶች ያስከትላል።


ይህ አደገኛ አይደለም! ቢሆንም ምልክቶቹ ግን ለጊዜው ቢሆን ያሰቃያሉ።


በቀላል አማርኛ አንጀት ገና አልተላመደም።

ምናልባት ጥሬ ስጋ እና የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦችን አለመልመዱ ቢሆንስ?


6️⃣ ምልክቶችስ ለምን በፍጥነትና በከባድ ሁኔታ ይመጣሉ ?


ይህን ለመረዳት ሂደቱን መረዳት ይኖርብናል። ለበሽታ አምጪ ተህዋሳት ሲጋለጡ ፤ በሽታ አምጪ ተህዋሳቱ የአንጀትን ሚዛን የሚያዛቡ ፤ የአንጀት ግድግዳን የሚያጠቁ መርዞች ይለቃሉ። አንጀትም ውሀ እና ማእድናት ወደ ውስጡ ይስባል/ይከታል። ከዛም ሰውነት ያጋጠመውን እንግዳ ነገር/በሽታ አምጪ ተህዋስ ጠራርጎ በፍጥነት ለማውጣት ይምክራል።


ይህን ጊዜ የሚያሩሩጥ የውሀ ተቅማጥ ይጋጥማል።

ሰውነት ቶሎ ማውጣት ነው የሚፈልገው። ይህ የሰውነቶት መከላከያ እንጂ የአንጀቶት ድክመት አይደለም።

ታድያ ግን ያስተውሉ፡ ይህ ከዚህ በሽታ ጋር ያለ ተቅማጥ ሂደት እንጂ ለሁሉም ተቅማጥ አይሆንም

እነኝህን ምልክቶች ካሰተዋሉ ታድያ ፤ በአፋጣኝ የህክምና እርዳታ ይፈልጉ።

🚨ደም ከቀላቀለ

🚨 ትኩሳት ካለው

🚨ሰውነትዎ ውሀ ካነሰው (ምልክቶቹ የከንፈር እና ቆዳ መድረቅ ከጀመረ፣ ድካም፣ ራስምታት ያካትታሉ)

🚨 አብሮት ደጋግሞ የሚመጣ ትውከት ካለ።

🚨 ምልክቶቹ ከ 2 ቀናት በላይ ከቆዩ 🚨 ራስ መሳት ካለ


ይህን ጊዜ በአፋጣኝ የህክምና እርዳታ ይፈልጉ።


7️⃣ ተዋርደን ይሆን?


ይህ የትም ሀገር ሊያጋጥም የሚችል የህክምና ክስተት ነው። በሚኖርበት አገረ አሜሪካ እራሱ ከዚህ በፊት ያልተመገበውን ምግብ አይነት ተመግቦ ቢሆን ይህ ያጋጥመው ነበር።


በራሱም አንደበት እንዲህ ሲል ተሰምቷል። "ወንድም! (ወደ ኢትዮጵያው አይሾው ስፒድ እየተመለከተ) ጥሬ ስጋ ስበላ አንጎሌ እስኪወጣ ሽንት ቤት እንደሚያስቀምጠኝ መናገር ነበረብህ። ለወደፊቱ ንገረኝ"

አይ ሾው ስፒድ ስለ ሆድ ህመሙ ሲናገር

የትኛው ነው የሚለውን ለመለየት የላብራቶሪ ምርመራ ቢያስፈልግም ፤ በሱ ሁኔታ ለአንጀቱ እንግዳ ከሆነ ጥሬ ስጋ እና ጥሬ ስጋ ለመብላት የምንጠቀማቸው ቅመሞች (ሰናፍጭ፣ አዋዜ፣ ወ.ዘ.ተ..) ጋር ተያያዥነት ያለው ይመስላል።


ይህ በማንኛውም አገር ፤ በማንኛውም ቦታ ፣ ማንንም ሰው ሊያጋጥም የሚችል ክስተት ነው።

Comments


bottom of page