top of page

አካል ጉዳት እና ግንዛቤው - 2

Updated: Apr 27

በመንደሩ ከነበሩ ልጆች ተጫዋች እና ቀልብ ሳቢ የነበረው አወል ፤ አድጎ ፤ ተመርቆ ፤በማናጀርነት ይሰራ ነበር። ታድያ አንድ ቀን ጠዋት ወደ ስራ ሲሄድ ፤ የነበረበት ታክሲ እየበረረ ስለነበር ፣ ከ ገልባጭ መኪና ጋር ተጋጨ። በወቅቱ ከባድ አደጋ ቢያጋጠመውም፣ ከተረፉት ሰዎች መሀከል በመሆኑ እርሱም ቤተሰቦቹም እጅጉን ደስተኛ ነበሩ። ሆኖም ግን በአደጋው ሁለቱም እግሮቹ እጅጉን ከባድ ጉዳት ስለደረሰባቸው ፤ እግሮቹን ማትረፍ አልተቻለም ነበር።


ስንቶቻችን ነን ጠዋት ላይ የትራፊክ ሪፖርት ስንሰማ ከሟች ቁጥር አልፈን ስለ ተረፈው የምናስበው? የተረፈው ሰውስ ቋሚ የአካል ጉዳት አጋጥሞት ቢሆንስ?

እንደዚህ አይነት ታሪክ ስንሰማ እኔን አያጋጥምም ብሎ ማሰብ እጅጉን ቀላል ነው። በአዲስ አበባ ብቻ ወደ 47,000 የሚጠጉ አካል ጉዳተኞች ይኖራሉ። አብዛኞቹም አንደ አወል የሆነ ወቅት ጤነኛ ነበሩ። በእንደዚህች አይነት ቀን ፣ በአንድ ስህተት ፤ ስራ ቦታ ላይ በሚፈጠር መዘናጋት ፤  ለዘመናት ሲደረጅ ችላ በተባለ ህመም ፤ አካል ጉዳተኛ ሆነው የቀሩ ብዙሀን ናቸው። ከ አካል ጉዳት ጋር በተያያዘ ከስራ ገበታቸው የተነሱም አሉ።


አካልጉዳተኝነት ማንንም አያገለም። ካልተጠነቀቅን ማናችንንም አይምረንም። እኔም ፣ አንቺም፣ አንተም፣ ባልታሰበ ክስተት ወይም ባልታከምነው ህመም አካል ጉዳተኛ ልንሆን እንችላለን። በቅጸበቶች ውስጥ የሚያጋጥም የሁላችን እጣፈንታ ሊሆን ይችላል።


ለዛ ነው ግንዛቤ የሚያስፈልገን!

ለዛ ነው መከላከል የሚያስፈልገን!

ለዛ ነው መረዳት የሚያስፈልገን!


ግንዛቤ


አካላዊ አካል ጉዳትኝነት ማለት በህመም ሆነ በተለያየ እክል የተነሳ ፤ የአንድ ግለሰብ የመንቀሳቀስ ችሎታ ፣ አካላዊ ክህሎት እና አቅም ለተወሰነ ጊዜም ይሁን ለእድሜ ልክ ሲገደብ ነው። አካላዊ አካል ጉዳተኝነት ከወሊድ ጋር በተያያዙ ፤ አልያም ከወሊድ በኋላ በሚፈጠሩ ክስተቶች ሊመጣ ይችላል። ከመንስኢዎቹ ጥቂቶቹ፡-


🧬ከዘረመል ጋር የተያያዙ ችግሮች


  • ዘረመል ላይ ያሉ የሚፈጠሩ ችግሮች ከማህጸን ጀምሮ እስከ ኋለኛ ህይወት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የአካል ጉዳቶችን ያመጣሉ።


🏥 የእናችቶች እና ህጻናት ጤና አጠባበቅ ችግር 


  • እናቶች በእርግዝና ጊዜ በሚፈጠሩ የጤና እክሎች፣ ያልተገቡ ባህሪያት (አልኮል መጠጣት፣ ማጨስ፣ ወ.ዘ.ተ...) እና ከወሊድ ጋር የተያያዙ ችግሮች የተነሳ ፤ ጽንስ ማህጸን ውስጥ እያለ ጉዳት እንዲደርስበት ፣ ከወሊድም በኋላም እክል እንዲያጋጥም ሊያደርጉ ይችላሉ። ለዚህም ክለብ እግር (የተቆለመሙ እግሮች) ፣  ስኮሊዮሲስ (መጉበጥ) እና ስረብራል ፓልሲ ተጠቃሽ ህመሞች ሊሆኑ ይችላሉ።


  • በልጅነት ጊዜያትም የሚያጋጥሙ ጉዳቶች ፣ የተመጣጠነ ምግብ ጉድለቶች፣ እንዲሁም ህመሞች (እንደ ፖሊዮ/ልጅነት ልምሻ ፣ ማጅራት ገትር እና ጂቢኤስ የመሳሰሉት)  በህጻንነት እድሜ ለአካል ጉዳት ያጋልጣሉ።

የሰረብራል ፓልሲ ህመምተኛ ልጅ ምስል
የሰረብራል ፓልሲ ህመምተኛ ልጅ ምስል

💉 ኢንፌክሽኖች


  • ህብለሰረሰርን  እንዲሁም ጭንቅላትን የሚያጠቁ ኢንፌክሽኖች ለእድሜ ልክ ቀሪ የሆነ የአካል ጉዳት እንዲፈጠር ሊያደርጉ ይችላሉ። ከዚህም ባሻገር እንደጋንግሪን እና ቲታነስ ያሉ እጅን ወይም እግርን ብቻ የሚያጠቁ ኢንፌክሽኖችም ለ አካል ጉዳት ያጋልጣሉ።


🚗 የመንገድ ደህንነት ችግር


  • ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ  ካለባቸው ሀገሮች ተርታ ትጠራለች። እንደ አወል ባልታሰበ ቅጽበት በትራፊክ አደጋ ህይወታቸው የተለወጡ ሰዎችም ጥቂቶች አይደሉም።


🩺 ዘግይቶ የተገኙ ወይም ክትትል የሌላቸው ህመሞች


  • ስኳር፣ ደም ግፊት፣ የስኳር መዛባት ፣ ስትሮክ  እና ካንሰርን የመሳሰሉ ህመሞች ቀድመው ካልተገኙ ፣ ወቅታዊ ህክምና እና ክትትል ካልተደረገላቸው ቋሚ የሆነ የአካል ጉዳት ሊያመጡ ይችላሉ።


💣  ግጭቶች እና አደጋዎች 


  • ሰውነታችን ላይ ጥቃት ሊያደርሱ የሚችሉ የተፈጥሮ አደጋዎች እንዲሁም ግጭቶች ለአካል ጉዳት ያጋልጣሉ።


መከላከል ይቻላልን?

አዎ! እነኝህ ለ አካል ጉዳተኝነት ከሚያጋልጡ መንስኤዎች ውስጥ አብዛኞቹን መከላከል እንችላለን።  እንዴት?


  1. እናቶች በወሊድ ጊዜ የተሟላ ቅድመ ክትትል ማድረግ ይኖርባቸዋል። በወሊድ ጊዜ የሚሰጡ መከላከያዎችን እና መድሀኒቶችን ስርአት ጠብቀው በመውሰድ ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን አካል ጉዳት መከላከል ይችላሉ።  


  2. ሀገራችን ኢትዮጵያ ያላትን የክትባት መርሀግብር በመከተል ፤ ልጅዎ ሙሉ ክትባት እንዲወስድ በማድረግ እንደ ፖሊዮ እና ማጅራት ገትርን የመሳሰሉትን ፤ በህጻንነት ጊዜ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ኢንፌክሽኖችን ሊከላከሉ ይችላሉ። ይህም ደግሞ በእነኝህ ህመሞች ምክንያት የሚመጣ አካል ጉዳትን ይከላከላል።


  3. ሲወለድ ጀምሮ እንደ ክለብ እግር፣ ሰረብራል ፓልሲ አይነት ህመም ያላቸውን ህጻናት ከ መጀመሪያ ቀናት ጀምሮ የህክምና ክትትል እንዲያደርጉ ማድረግ ይኖርብናል። ይህም ደግሞ ያለውን የአካል ጉዳት በህክምና እርዳታ እንዲመለስ ወይም የጉዳቱ መጠን እንዲቀንስ ማድረግ ይችላል።



  4. የመንገድ ደህንነትን በመጠበቅ ራስን ከትራፊክ አደጋ ጋር ተያይዞ ከሚመጣ አካል ጉዳት መጠበቅ ይቻላል።


  5. በስራ ቦታ ላይም ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ፣ ባለመዘናጋት በስራ ቦታ ከሚያጋጥም አካል ጉዳት ራስን መጠበቅ ይቻላል።


  6. መደበኛ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል። የበሽታ/ህመም ምልክት ሲታይ አፋጣኝ ህክምናን ማድረግም መልካም ነው። ይህም እንደ ካንሰር ያሉ ህመሞች ስር ሳይሰዱ ህክምና በማድረግ አካል ጉዳትን መከላከል ይቻላል።


  7. የስኳር፣ የደም ግፊት ፣ የስብ መዛባት ህመሞች  ካልተቆጣጠርናቸው ስትሮክ ህመም አምጥተው ፤ አካል ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ። ለዚህም መደበኛ የህክምና ክትትል በማድረግ እና መድሀኒት በአግባቡ በመውሰድ ልንከላከል እንችላለን።


  8. ነገርን በንግግር ለመፍታት በመሞከር ፤ ወደ ግጭት ከሚያመሩ ጉዳዮች መቆጠብ እንችላለን።


መረዳት


አካላዊ ጉዳት ተፈጥሮአዊ አቅምን አይገታም።  አእምሮአችን እና ሰውነታችን እጅጉን ተላማጅ ናቸው። አእምሮአችን ከአካል ጉዳት በኋላ እራሱን እንደ አዲስ ሊቀርጽ/ሊያበጅ ይችላል። ይህ ኒውሮ ፕላስቲሲቲ ይባላል። ለዚህም አካላዊ ጉዳት ያለባቸው ሰዎች አእምሮአቸው በሚያደርገው ስር ነቀል ለውጥ ፤ አዲስ  መክሊቶች ይኖራቸዋል። ከዚህ በፊት ያልነበረ ጥንካሬን ሊያመጡ ይችላሉ። በፊት ከሚያስቡት ገደብ አልፈው ብዙ ሊሰሩ ፤ እጅጉን ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ።


ይህ ተፈጥሮአችን በማገገም ህክምና (rehabilitation therapy) ሲታገዝ ደግሞ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። አሁን ሳይንስ በደረሰበት አቅም  ተገጣሚ ሮቦቶች፣ ፕሮስተቲክ አካላት እንዲሁም አርተፍሻል የውጭ አጥንቶች አመርቂ ደረጃ ደርሰዋል።


 

ሆኖም ግን ለአካል ጉዳተኞች ትልቁ ችግር አካላዊ ጉዳቱ ሳይሆን እሱን ተከትሎ የሚመጣው የማህበረሰባዊ እክሎች ናቸው።

ለምሳሌ በኢትዮጵያ ውስጥ

  • ባብዛኞቹ ህንጻዎች አካል ጉዳተኞቹን ያማከሉ አይደሉም።


  • ትራንስፖርቶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አይደሉም ።


  • ት/ቤቶችና ስራ ቦታዎች አካል ጉዳተኞች ተደራሽ አይደሉም ።


መልካሙ ዜና


  • በደረሰንበት ስልጣኔ ከሰውነት ጋር የሚነጋገሩ ፤ እንደ አካላችን የሚያገለግሉ ሮቦቶች ፤ ከልብወለድ አልፈው የዘመናችን እውነታ ሆነዋል።


  • የተፈጻሚነት ደረጃው ቢሊያየም ፤ ብዙ የአለም ሀገራት አከባቢን ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ለማድረግን እና ልማት ላይ አካል ጉዳተኞችን ለማካተት ፤ በፖሊሲ ደረጃ ቀርጸው አስቀምጠዋል።


  • በአለም አቀፍ ደረጃ አካል ጉዳተኞችን ያካተቱ ስፖርቶች ፤ የስፖርት ፍቅር ያላቸው አካል ጉዳተኞችን ተደራሽ አድርገዋል።



  • የ ኢትዮጵያ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስተርም በአካል ጉዳተኝነት ዙሪያ ላይ ስትራቲጂክ እቅድ አውጥቶ እየሰራ ይገኛል።


  • የተለያዩ ባለድርሻ አካላት (እንደ ቀይ መስቀል፣ ኢሲዲዲ ፣ ወ.ዘ.ተ...) አካል ጉዳተኞችን የስራ ክህሎት እያሰለጠኑ ፤ በስራ ዘርፍ እያሰማሩ ይገኛሉ። ከዚህም ባሻገር የማህበረሰብን አስተሳሰብ ለመቀየር እየሰሩ ይገኛሉ። 


ግን ይሄም በቂ አይደለም!


የአወል እጣ...

ከጉዳቱ በኋላ አወል ከአካላዊ ጉዳት አልፎ ፤ ሰነልቦናዊ ቀውስ አጋጥሞት ስለነበረ ፤ አዲሱን የህይወት ምህዳር ተቀብሎ ፤ ኑሮውን ለመምራት ተቸግሮ ነበር። ለዚህም ለወራት የማገገም ህክምና ከወሰደ በኋላ ግን ፤ እይታው ተለወጠ። አሁን ከስራ ገበታው ተመልሶ ገብቶ በውጤታማነት እየሰራ ይገኛል።

 


እንደ አወል ዛሬም የማገገም ህክምና እድል የሚያስፈልጋቸው ብዙዎች ናቸው። እነርሱም እርዳታን ፣ ግንዛቤን እና ምቹ እድልን ይጠብቃሉ።


አካል ጉዳተኝነት የእርስዎም እጣፈንታ ሊሆን ይችላል። አካል ጉዳተኞችን አያግልሉ። አከባቢዎትን ለእነሱ ተደራሽ ያድርጉ።


አካል ጉዳትኞችን ያላካተተ ልማት ምሉዕ ስለማይሆን ፤ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላትም ከዚህም አብልጠው መስራት ይኖርባቸዋል።



Comments


bottom of page