top of page

በኢቦላ የሚጠረጠሩ ሰዎች ቁጥር ወደ 1000 እየተጠጋ ይገኛል።

አለማችን ከኮቪድ-19 አስከፊ ማዕበል አገግማ መተንፈስ ከጀመረች ገና ጥቂት ዓመታት እየሆናት ነው። ያኔ የነበረው ስጋትና ፍርሃት ምን ይመስል እንደነበር አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ያስታውሰዋል። ሆኖም የጤናው ዘርፍ አሁንም እረፍት ያገኘ አይመስልም። በቅርቡ የተከሰቱት የኤምፖክስ (Mpox) እንዲሁም የማርበርግ ወረርሽኝ ሁላችንንም ስጋት ላይ ጥለው የነበረ ቢሆንም፤ በተቀናጀ የህዝብ ጤና ጥረትና ንቃት በሽታዎቹን መቆጣጠርና መግታት ተችሏል። በተመሳሳይ መልኩ የአለም ጤና ድርጅት (WHO) የሃንታ ቫይረስ (Hantavirus) ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ሌላ ዓለም አቀፍ ቀውስ እንዳይፈጥር ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ ባለፉት ሳምንታት ሲከላከል ቆይቷል።



አሁን ግን መላው ዓለም ከዚህ ቀደም ከነበሩት ገዳይነቱ ከፍ ያለ ፤ አሳሳቢና አስፈሪ ስጋት ተደቅኖበታል። እ.ኤ.አ. ሜይ 17 ቀን 2026 የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር በአሁኑ ወቅት የተከሰተውን የኢቦላ ወረርሽኝ "ዓለም አቀፍ አሳሳቢነት ያለው የሕዝብ ጤና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ" በማለት በይፋ አውጀዋል። ባለፉት ሳምንታትም በሽታው በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ የመጣ ሲሆን፤ የአለም የዜና አውታሮች እንዲሁም የሕክምና ተቋማት እንደዘገቡት ይህ ቀውስ በአሳሳቢ ሁኔታ እያደገ ነው። በመሆኑም የዓለምን ትኩረት ስቧል።


የበሽታው ስርጭት

በኢቦላ ወረርሽኝ የተጠቁ ሀገራት እና ግዛቶች
በኢቦላ ወረርሽኝ የተጠቁ ሀገራት እና ግዛቶች

በኮንጎ እና በኡጋንዳ በአሁኑ ወቅት ወደ 1,000 የሚጠጉ ሰዎች በኢቦላ ቫይረስ መያዛቸው ተጠርጥሯል። ሪሊፍ ዌብ (Relief Web) ባወጣው የቅርብ ጊዜ መረጃ መሠረት፣ በኮንጎ ብቻ ወደ 977 የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ ሲጠረጠሩ፣ 228 ያህሉ ደግሞ በበሽታው ምክንያት ሳይሞቱ እንዳልቀረ ይገመታል። 


ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኮንጎ ጤና ሚኒስቴር ግንቦት 26 ቀን 2026 በሰጠው ይፋዊ መግለጫ በኢቱሪ፣ በሰሜን ኪቩ እና በደቡብ ኪቩ ግዛቶች አጠቃላይ የላብራቶሪ ምርመራ የተረጋገጠባቸው ታማሚዎች ቁጥር 121 መድረሱን እና ከእነዚህም ውስጥ አስራ ሰባቱ መሞታቸውን አስታውቋል። ይኸው የሚኒስቴሩ ሪፖርት በተጨማሪም በመላ ሀገሪቱ 1,077 ሰዎች በቫይረሱ መጠርጠራቸውንና ከእነርሱም መካከል የ238 ሰዎች ሕይወት ማለፉን በዝርዝር ያሳያል። 


በሌላ በኩል፣ ጎረቤት ሀገር ኡጋንዳ በአሁኑ ወቅት ሁለቱን ግንባር ቀደም የጤና ባለሙያዎች ጨምሮ በላብራቶሪ የተረጋገጡ 7 የኢቦላ ታማሚዎችን መዝግባለች። ከእነዚህም ውስጥ የአንድ ሰው ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ ይህም በአጠቃላይ ክልላዊ የወረርሽኙን የመግደል አቅም (case-fatality rate) ከፍተኛ እንደሆነ(14.3%) ይጠቁማል።


 የአለም ጤና ድርጅት ሁኔታውን ከፍተኛው ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት ደረጃ አድርጎ የፈረጀውም ለዚህ ነው።

በእነኝህ ሀገራት የሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች ከበሽታ ተጠቂ ስዎች ጋር ንክኪ የነበራቸውን 3,600 ሰዎች  አፈላልጎ ለመለየት ከጊዜ ጋር እየተሽቀዳደሙ ይገኛሉ። ለዚህም እንዲያግዝ በአሁኑ ወቅት 2,000 የምርመራ መሣሪያዎች ወረርሽኙ ባጋጠመበት ቦታ ላይ የደረሱ ሲሆን፤ የበሽታውን ትክክለኛ ስርጭት ለማወቅ ተጨማሪ 4,000 የምርመራ መሣሪያዎች በፍጥነት ወደ ስፍራው እየተላኩ ይገኛል።


ኢቦላ ምንድነው?

የኢቦላ ቫይረስ ምስል
የኢቦላ ቫይረስ ምስል

የኢቦላ በሽታ ፊሎቪሪደ (Filoviridae) በተሰኘ የቫይረስ ቤተሰብ አባል በሆነው የኢቦላ ቫይረስ የሚመጣ፣ ከባድ እና በአብዛኛው ለሕይወት አስጊ የሆነ የጤና እክል ነው። በሽታው ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው የሚተላለፈው በቫይረሱ ከተያዘ ግለሰብ ደም፣ ትውከት፣ ምራቅ፣ ላብ፣ ሽንት፣ ሰገራ እና የዘር ፈሳሽ ጋር፣ እንዲሁም በቫይረሱ ከተበከሉ ቁሶች ወይም በበሽታው ካረፉ ሰዎች አስክሬን ጋር በሚደረግ ቀጥተኛ ንክኪ ነው።


የኢቦላ ወረርሽኝ ለዓለማችን አዲስ አይደለም። እስከ አሁን ድረስ የተለያዩ የኢቦላ ቫይረስ ዝርያዎች የተከሰቱ ሲሆን፤ በተለይም ከ2014 እስከ 2016 እ.ኤ.አ. ያጋጠመው የዛየር ዝርያ (Zaire ebolavirus) እጅግ አስከፊ የነበረና የሚታወስ ነው።


ነገር ግን፤ የዘንድሮውን ወረርሽኝ ልዩ እና ፈታኝ የሚያደርጉት ሳይንሳዊ ምክንያቶች አሉ፡-

  1. ይህ ወረርሽኝ የተከሰተው በቦንዲቡግዮ ዝርያ (Bundibugyo Strain) ነው። ይህ ዝር ያ እ.እ.አ. በ2007 ለመጀመሪያ ጊዜ ወረርሽኝ ያስከተለ ሲሆን ፤ ከዚያ ወዲህ አራት ጊዜ ወረርሽኝ አምጥቷል።

  2.  ለተለመደው የዛየር (Zaire strain) የኢቦላ ዝርያ ውጤታማ የሆኑ ክትባቶች ቢኖሩም፤ እነዚያ ክትባቶች አሁን እየተሰራጨ ላለው የቦንዲቡግዮ ዝርያ አይጠቅሙም/አይሆኑም።

  3. በአሁኑ ወቅት ለቦንዲቡግዮ (Bundibugyo) የቫይረስ ዝርያ የጸደቀ መደበኛ የሕክምና መድኃኒት የለም። በመሆኑም የጤና ባለሙያዎች ሙሉ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ሕመምተኞችን በማግለል፣ የሕመም ምልክቶችን የሚያስታግስና ደጋፊ የሕክምና እንክብካቤ (Supportive care) ብቻ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።


የኢቦላ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

የመጀመሪያዎቹ የኢቦላ ምልክቶች ከሌሎች የተለመዱ በሽታዎች ጋር ሊመሳሰሉ ስለሚችሉ ፤ በሽታውን አስቀድሞ ለማወቅ አስቸጋሪ ያደርገዋል።


ዋና ዋናዎቹ የመጀመሪያ ምልክቶች፡-

  • ትኩሳት፣

  • ከፍተኛ ድካም፣

  • የጡንቻ ሕመም፣

  • ራስ ምታት እና የጉሮሮ መቁሰል ናቸው።


በሽታው እየገፋ ሲሄድ ግን...

  • ትውከት፣

  • ከባድ ተቅማጥ፣

  • የሆድ ሕመም እና

  • ከፍተኛ የሰውነት ፈሳሽ ማጣት (dehydration) ይከሰታል።


እጅጉን ሲብስ ደግሞ ፤ እንደ ጉበት እና ኩላሊት ያሉ የውስጥ አካላት ሥራ ሊያቆሙ ይችላሉ።

ከዚህም ባሻገር ፤

  • ከአፍንጫ ወይም ከድድ መድማት፣

  • በሰገራ ወይም በትውከት ደም መታየት፣ እና

  • ሰውነት ውስጥ ደም መፍሰስ ሊያጋጥም ይችላል።


ነገር ግን ማስታወስ ያለብን፤ ሁሉም የኢቦላ ታካሚዎች ላይ ፤የሚታይ ደም መፍሰስ ላይኖር ይችላል።


የኢቦላ ህክምና


ለኢቦላ በሽታ "ፈውስ" የሚባል መድሐኒት ባይኖርም፤ ቀደምት የሕክምና መረጃዎች እንደሚያሳዩት ፈጣን የድጋፍ ሕክምናዎች (supportive care) የሰዎችን የመትረፍ ዕድል በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራሉ። በደም ሥር የሚሰጡ ፈሳሾች (IV fluids)፤ የሰውነት ማዕድናትን መጠበቅ እና የደም ግፊትን መቆጣጠር የሰውነት መከላከያ ሥርዓት ቫይረሱን ለመዋጋት ጊዜ እንዲያገኝ ይረዳዋል። በዚህም የእገዛ ህክምና ሰውነት በራሱ ቫይረሱን ያስወግደዋል።


ይህን ወረርሽኝ ያመጣው የኢቦላ ቫይረስ ክትባት የለውም። በአሁኑ ወቅት ተስፋ የተጣለው በአሜሪካ የሙከራ ደረጃ ላይ ያለ መድሀኒት (experimental antibody) በፍጥነት ሥራ ላይ ለማዋል በሚደረገው ጥረት ላይ ነው።


የበሽታ እና ጦርነት ጥምረት


የአሁኑ ወረርሽኝን አሳስቢ የሚያደርገው ፤ በግጭት መሀል መከሰቱ ነው። ወረርሽኙ ባጋጠመበት የኮንጎ አከባቢ የሕክምና ማዕከላት ጥቃት እየደረሰባቸው ነው። ድንበሮች እየተዘጉ ነው። በዚህ ከፍተኛ የጸጥታ እጥረት መካከል ፤ ይህንን ወረርሽኝ መቆጣጠር እጅጉን አስቸጋሪ ነው።


የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ገብረኢየሱስ በኢቱሪ (Ituri) እና በሰሜን ኪቩ (North Kivu) ግዛቶች ያለው ሁኔታ "የበሽታ እና የጦርነት አስከፊ ጥምረት" ብለው ገልጸውታል።


“በብዙ በበሽታው በተጠቁ አካባቢዎች፤ የጤና ተቋማት በሰላም እጥረት ምክንያት ሥራ አቁመዋል፤ ወይም በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እየሠሩ ይገኛሉ” ሲሉ ዶ/ር ቴዎድሮስ ተናግረዋል። “የመንገድ ችግሮችም አስፈላጊ የሰብአዊ ድጋፎችን እንቅስቃሴ የበለጠ ይገድባሉም።” ብለዋል።

ባለፉት ቀናት በተከሰቱ ግጭቶች ቢያንስ አራት የኢቦላ ሕክምና ማዕከላት ላይ ጥቃት ደርሷል። ከ2021 ጀምሮ በወታደራዊ አገዛዝ ስር ባለችው ኢቱሪ፤ በከፍተኛ የጸጥታ እጥረት እና በፈራረሱ መንገዶች ምክንያት የአካባቢው ጤና ተቋማት ሙሉ በሙሉ ሥራ አቁመዋል፤ ወይም በከፍተኛ ችግር ውስጥ ናቸው።


ግጭቱ ከፍተኛ የሕዝብ መፈናቀልን እያስከተለ ሲሆን፤ ተጋላጭነት ያላቸው ሰዎችም ወደ ተጨናነቁ የስደተኛ ካምፖች እንዲሰደዱ በማድረግ የበሽታውን ስርጭት እያስፋፋ ይገኛል። በሽታዎን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረትም እያፈረሰ ይገኛል።



ኢትዮጵያ በአደጋ ውስጥ ልትሆን ትችላለች?



በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተጠረጠረ ሆነ የተረጋገጠ የኢቦላ ታማሚ የለም። ነገር ግን አለም በዘመናዊ ትራንስፖርት በተሳሰረችበት በዚህ ዘመን፤ ይህ የራቀ የሚመስለውን በሽታ ከደጃችን ሊመጣ የሚችልበት አጋጣሚ አይጠፋም።


ታሪክ ደጋግሞ እንዳሳየው ተላላፊ በሽታዎች ድንበርን፣ ቋንቋን፣ ወይም መልክዓ ምድርን አይመርጡም። ኮቪድ-19 ይህንን እውነታ ለዓለም በግልጽ አስተምሯል። ዛሬ በኮንጎ እና ኡጋንዳ በፍጥነት እየተስፋፋ ያለውን ወረርሽኝ ለመግታት የአለም ሀገራት በሚታገሉበት በዚህ ወቅት፤ እኛም የበሽታውን ሂደት በትኩረት ልንከታተለው ይገባል። የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም አስፈላጊውን ዝግጅት እና ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባቸዋል።


የሚያስፈራሩ የሐሰት ወሬዎች የሚጫወቱት ሚና

የኢቦላ ወረርሽኝ የሚመከተው በሆስፒታሎች ውስጥ ብቻ አይደለም። ትግሉ በየማሕበረሰቡ ውስጥም ጭምር ነው። የሀሰት ወሬዎች ከራሱ ከበሽታው በበለጠ ለሞት ሊዳርጉ ይችላሉ። ባለፉት ወረርሽኞች የታዩ የተሳሳቱ መረጃዎች ቤተሰቦች የታመሙ ዘመዶቻቸውን እንዲደብቁ፤ ማኅበረሰቡ በጤና ባለሙያዎች ላይ ያለውን እምነት እንዲያጣ እና ሕመምተኞች ወደ ሕክምና ማዕከላት እንዳይመጡ አድርገዋል።


ፍርሃት ከቫይረሱ በበለጠ ፍጥነት ይሰራጫል። ለዚህ ነው ትክክለኛና ሳይንሳዊ የሆነ የሕዝብ ትምህርት እጅግ አስፈላጊ የሚሆነው።


አለም አቀፍ መፍትሔዎች


በአንድ ቦታ የሚከሰት ወረርሽኝ ለሁሉም ቦታ ስጋት ስለሆነ፤ የአለም አገራት ቫይረሱን ለመለየት እና ለመግታት ጥንቃቄ እና ዝግጅት እያደረጉ ነው፡- እያደረጓቸው ካሉት ዝግጅቶች መካከል


  • የድንበር መዘጋት፦ ኡጋንዳ ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጋር ያለውን ድንበር ሙሉ በሙሉ የዘጋች ሲሆን፤ በከፍተኛ የሕክምና ክትትል ስር ለሚጓዙ የጸጥታ፣ የጤና እና የሰብአዊ እርዳታ አቅራቢዎች ብቻ ፈቃድ ሰጥታለች።

  • የጉዞ እገዳዎች፦ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ እና ባሃማስ ከወረርሽኙ አካባቢ ለሚመጡ መንገደኞች አስገዳጅ የጉዞ እገዳዎች እና የ90 ቀናት የማግለል (isolation) ፕሮቶኮሎችን አውጥተዋል።

  • የአውሮፕላን ማረፊያ ፍተሻዎች፦ ዋና ዋና ዓለም አቀፍ የአየር ማረፊያዎች የመንገደኞችን ከፍተኛ ትኩሳት ለመፈተሽ ጠንካራ የጤና ምርመራዎችን ጀምረዋል።


እርስዎም በበኩልዎ ስለበሽታው ስርጭት እና መከላከያ መንገዶች ከ ጤና አካላት የሚሰጡትን መልዕክቶች ይከታተሉ።


Comments


bottom of page