ለሳምንታት የቆየው የዳንስ ወረርሽኝ ፡ ከ 500 አመት በኋላ ያልተፈታ ሚስጥር
- Zebeaman Tibebu
- 1 day ago
- 6 min read
የምትጨፍረዋ ሴት
በምናባችን 508 አመት ወደ ኋላ እንመለስ። እ.ኤ.አ. በ1518 ዓ.ም በፈረንጆቹ ጁላይ (ሐምሌ) ወር በስታርስበርግ (Strasbourg) ከተማ ሞቃታማ የበጋ ወቅት ነበር። ከተማዋ አሁን በፈረንሳይ አካል ብትሆንም ፤ በጊዜው የሮማ መንግስት ግዛት ስር ነበረች።

የከተማው ጎዳናዎች እንደተለመደው ደምቀው ነበር። ነዋሪው ከጸሀይ እኩል ነቅቶ ፤ የዕለት ስራውን ለመጀመር ይጣደፋል። ነጋዴዎች ሸቀጣቸውን ደርድረው ገበያተኛ ይጠባበቃሉ። የቤተክርስቲያን ደወሎች ፤ በቤቶች ጣራ ላይ ሲያስተጋቡ ይሰማል።
ዕለቱ እንደማንኛውም የአዘቦት ቀን ይመስል ነበር...
በዚህ ተራ ቀን በታሪክ የሚመዘገብ ትንግርታዊ ክስተት እንደሚጀመር የገመተ ሰው አልነበረም።
ታድያ ድንገት ፍራው ትሮፌያ (Frau Troffea) የተባለች ነዋሪ ፤ ከጎዳና ወጥታ ያለምንም ምክንያትና ቅድመ ማስጠንቀቂያ መጨፈር ጀመረች።

የሚያስጨፍራት ምንም ዓይነት የሙዚቃ ድምፅ አልነበረም። በወቅቱ የተካሄደ አይነት ፌስቲቫል/ድግስም አልነበረም። ያለ ሰርግ ፤ ያለ ሙዚቃ ዝም ብላ ትደንስ ጀመር።
በመጀመሪያ ላይ እምብዛም ትኩረት አላገኘችም ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደምታቆም ይገመት ነበር። ነገር ግን እሷ እየጨፈረች ፤ ደቂቃዎች ወደ ሰዓታት ተቀየሩ።
የበጋው ሐሩር ጸሀይ በስትራስቡርግ ሰማይ ላይ ፤ እንደ ሰንደቅ ከፍ ብላ ስትሰቅልም ፤ እሷ ግን ከሰአታት በኋላም ዳንስ ላይ ናት!
ወደ ቀትር ላይ ፤ ጉዳዩ የገረማቸው ነዋሪዎች በዙሪያዋ መሰብሰብ ጀመሩ። አንዳንዶቹ ሳቁ! ሌሎቹ አፍጥጠው ተመለከቱ። ጥቂቶች ደግሞ በአግርሞት ራሳቸውን እየነቀነቁ ወደ ስራቸው ተመለሱ። “እንዲያው በገዛ ፈቃዷ ትደክማለች” ብለው አሰቡ።
እንዳሰቡትም ደከማት...
እግሮቿ ዝልፍልፍ ብለው መሸከም ሲያቅታቸው ፤ የጎዳናው የኮብል ጥርብ ድንጋይ ላይ ተዘረረች። ለብዙዎች ይህ የዳንስ ትዕይንቱ ማገባደጃ መሰላቸው።
... ሆኖም አላበቃም ነበር!
እሷም ትንፋሿን ሰብስባ ፤ መልሳ ቆመች። ከዚያም እንደገና መደነስ ጀመረች። ምክንያቷን የተረዳ ማንም አልነበረም። እሷ የተከተለችው ሙዚቃ፤ የምታዝናናው ታዳሚ ፤ የምትደሰትበትም በዓል አልነበረም። ላያት መቆም ያቃታትና ሰውነቷን መቆጣጠር ያልቻለች አንድ ምስኪን ሴት ነበረች። ታሳዝን ነበር!
ቀትርም አልፎ ደንገዝገዝ ሲል ፤ ጎዳናዎቹም ጭር ማለት ጀመሩ። ፍራው ትሮፊያ ግን አሁንም እየጨፈረች ነበር። እንቅስቃሴዋ በጨለማ አልተገታም ነበር። ጎህ ሲቀድም እሷ ጭፈራ ላይ ነበረች።
እስከ ዛሬ የተረፉት የታሪክ ሰነዶች በጥቃቅን ዝርዝሮች ላይ ይለያዩ እንጂ ፤ ዋናው ጉዳይ ላይ ይስማማሉ። እሷ ዳንሷን ፈጽማ አላቆመችም ነበር። ሲደክማት ወይም ሰውነቷ ሲሸነፍ ትወድቃለች። ወድቃም አትቀርም ፤ ተነስታ ትቀጥላላች።

እሷ እየደነሰች ፤ ቀናቶች ይቆጠሩ ጀመር። አንድ ቀን ወደ ሁለት ቀናት ተቀየረ። ከዚያም ሶስት፤ ከዚያም አራት፤ እሷ እየጨፈረች ነበር።
እግሮቿ የታዛቢዎችን ትኩረት ስበው ነበር። በጠንካራው ድንጋይ ላይ ሳታቋርጥ በመጨፈሯ ቆስለው ነበር። ሆኖም ግን እግሮቿ እየደሙ እንኳን ፤ አላቆመችም።
ባለቤቷ እንድታቆም እንደለመናትና ጎረቤቶቿም እንደተማጸኗት የታሪክ መረጃዎች ይናገራሉ። ቢሆንም የተቀየረ ነገር አልነበረም። እሷ ልትቆጣጠረውም ሆነ ልትቋቋመው በማትችለው እንቅስቃሴ ውስጥ ታስራ ነበር።
ይህ አስገራሚ ወሬ በከተማው በፍጥነት በመናፈሱ ፤ ብዙኃን ይህችን መቆም ያቃታትን በዳንስ አባዜ የተነደፈችውን ሴት ለማየት ስራቸውን ትተው ይመጡ ነበር። ሁኔታዋን የተመለከቷ አንዳንዶች በፍርሃት ሲያማትቡ ፤ ሌሎች እርግማን ብለው ይንሾካሸካሉ። ብዙዎች በድንጋጤ እና በግርምት ይታዘቡ ነበር።
የወረርሽኙ መጀመሪያ
የሷ የማያቋርጥ ዳንስ መሰል እንቅስቃሴ ከቀናት ወደ ሳምንት ሲሻገር ፤ ለሕክምና ሳይንስ እንቆቅልሽ የሆነ አንድ ክስተት ተፈጠረ።
እሷን ተከትሎ ፤ አንድ ሌላ የከተማው ነዋሪ መደነስ ጀመረ። ከዚያም ሌላ... ከዚያም ሌላ...

በጥቂት ቀናት ውስጥ በርካታ ሰዎች ተቀላቀሏት። በሳምንቱ መጨረሻ፤ ከሰላሳ በላይ ሰዎች በከተማው ጎዳናዎች ይጨፍሩ ጀመር። አንዳንዶቹ ብቻቸውን ፤ ሌሎቹ ደግሞ በትንንሽ ቡድኖች ተሰባስብው ነበር የሚጨፍሩት።
የወቅቱ ዘገባዎች እንደሚገልጹት፤
"እንቅስቃሴያቸው በሰዓታት የሚቆጠር እጅግ የፈጠነና ተደጋጋሚ ነበር። አብዛኞቹ ከደስታ ይልቅ ጭንቀት ይነበብባቸው ነበር። አንዳንዶቹ ይዝለፈለፉና መልሰው ተነስተው ዳንሳቸውን ይቀጥላሉ። ቀናት እያለፉ ሲሄዱ፣ በሰውነታቸው ላይ መቁሰል፣ መገጣጠሚያ ማበጥና የደማ እግር የተለመዱ እይታዎች ሆኑ።"
የከተማው ነዋሪ ፤ እንደ ወረርሽኝ የዳንሰኞቹ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ምን እንደተሰማው ፤ በእርግጥ አይታወቅም። ምናልባት ፍርሃት ሊሆን ይችላል፤ ወይም አለማመን፤ አልያም ይህ እንግዳ ክስተት እንደጀመረው ሁሉ በድንገት ያበቃል የሚል ድምፅ አልባ ተስፋ ተሰምቷቸው ይሆናል።
ሆኖም ግን ይህ የዳንስ ወረርሽኝ ጀመረ እንጂ አላበቃም ነበር።
ይልቁንም፤ በየማለዳው አዳዲስ ዳንሰኞችን ይገኙ ነበር። በአንድ ወቅት ነጋዴዎች ስለ እህልና ስለ ጨርቅ ዋጋ የሚከራከሩባቸው ጎዳናዎች፤ አሁን የዛሉ እግሮች ከድንጋይ ጋር ሲጋጩ በሚያሰሙት የማያቁርጥ የዳንስ ድምፅ ተዋጡ።
ዳንሰኞቹ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የመጡ ነበሩ። አንዳንዶቹ ወንዶች፤ ሌሎቹ ሴቶች ነበሩ። ወጣትም አዛውንትም ከመሀላቸው ይታይ ነበር።
ከተማዋ እንደዚህ ያለ ነገር ጨርሶ አይታ አታውቅም። ቀናት እያለፉ ሲሄዱ፤ የከተማው ግርምት ቀስ በቀስ ወደ ከፍተኛ ስጋት ተቀየረ። ይህ በአንዲት ምስኪን ሴት ላይ ብቻ የመጣ ጣጣ ሆኖ አልቀረም። ችላ ተብሎ የሚታለፍ ጉዳይ ሊሆን አልቻለም።
በወሩ መጨረሻ ላይ ከሰላሳ በላይ ሰዎች በስትራስቡርግ ከተማ እየደነሱ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። ቁጥሩ ግን በዚህ አላበቃም። በዚህ ወረርሽኝ ወቅት እስከ አራት መቶ የሚቆጠሩ ሰዎች እየደነሱ እንደነበር ይገመታል።
ዘመናዊ የታሪክ ተመራማሪዎች ይህ ቁጥር ማረጋገጥ እንደማይቻል ቢያመላክቱም ፤ ወረርሽኙ ከተማዋን ሊቆጣጠረው በሚችል ደረጃ ማደጉ ላይ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለም።
እውነታው ይህ ነው። ስትራስቡርግ ከተማ ከዚህ በፊት አጋጥሟት የማያውቀው ዓይነት ቀውስ ውስጥ ነበረች። ለዚህም መፍትሔ ፍለጋም ጀመረች።
ያልተሳካው አስገራሚ መፍትሔ

የከተማዋ ሐኪሞች ማብራሪያ ፍለጋ ብዙ ደከሙ። እዚህ ጋር በ16ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የነበረው ህክምና ከዛሬው የሕክምና ሳይንስ ፍጹም የተለየ ነበር። ረቂቅ የበሽታ አምጪ ተሕዋሳትን ማየት የሚያስችል ማይክሮስኮፕ አልነበረም። ለዚህም ስለ ባክቴሪያ፣ ቫይረስ፣ ወይም በሽታ አምጪ ተሕዋስ ምንም ዓይነት ግንዛቤ አልነበረም። ዛሬ እንደምናውቀው ስለ ሳይኮሎጂ (የስነ-ልቦና ሳይንስ) እውቀት አልነበረም።
በጊዜው በሽታዎች የሚታዩት "የአራቱ የሰውነት ፈሳሾች መላምት" (Four Humors) በተሰኘ አስተሳሰብ ነበር። ለዚህም አንድ ሰው ጤና እንዲኖረው የአራቱን የሰውነት ፈሳሾች ስስ ሚዛን ጠብቆ ማቆየት አለበት ተብሎ ይታሰባል።ሚዛኑ ከተዛባ ግን በሽታ ይከተላል።
ለዚህም ሐኪሞቹ ዳንሰኞቹን ከመረመሩ በኋላ፤ አንድ ድምዳሜ ላይ ደረሱ። ህመምተኞቹ በሰውነታቸው “የሞቀ ደም” (hot blood) በመብዛቱ ይህ ችግር ተፈጥሯል ብለው አመኑ።
የእነሱ አመክንዮ በዚያ ዘመን ከነበረው የሕክምና ግንዛቤ አንጻር ሲታይ ትክክል ይመስል ነበር። ሰውነት በጣም መደነስ የፈለገው፤ ራሱን ለማቀዝቀዝ እየሞከረ ስለሆነ ነው ብለው አሰቡ ። ምናልባት መፍትሔው ዳንሱን መጨረስ ነው። በሽታውም ከሰውነት ሊወጣ የሚችለው ያኔ ብቻ ነው ተብሎ ታሰበ።
ይህ ውሳኔ ታሪክ ሁልጊዜ በግርምት የሚያስታውሰው ሆነ።
ለዚህም ባለሥልጣናቱ ዳንሱን ከመከልከል ይልቅ... እንዲቀጥል አበረታቱት!

ለጭፈራ እንዲመችም ፤ አዳራሾች ተከፈቱ። የእንጨት መድረኮች ተሰሩ። ሙዚቀኞች ተቀጠሩ። ከበሮ መቺዎች ፣ ባለዋሽንቶች ተጠርተው ከተማዋ ለዳንኪራ ምቹ ሆነች። በሽታውን ከሰውነታቸው ውስጥ “በደንብ ደንሰው እንዲያወጡት” ለመርዳት በማሰብ፤ መቆም ካቃታቸው ሰዎች ጋር አብረዋቸው የሚደንሱ አበረታች ባለሙያ ዳንሰኞች ጭምር ተቀጠሩ!
ለአሁኑ ዘመን ሰው ይህ ምላሽ ሙሉ በሙሉ የማይታመን ተረት ሊመስል ይችላል። ሆኖም የከተማዋ መሪዎች በዚያ ሰዓት በተገኘው የሕክምና ምክር ላይ ተመስርተው እየሰሩ ነበር። ግድ የለሾች አልነበሩም፤ የሰዎችን ሕይወት ለማዳን እየሞከሩ ነበር።
ግን ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ። ሕክምናው ችግሩን ይበልጥ ያባባሰው መሰለ።
ሙዚቃው በስትራስቡርግ ጎዳናዎች ላይ ሲያስተጋባ፤ ዳንሰኞቹ አሁንም ቀጠሉበት።
አንዳንዶቹ የታሪክ ተመራማሪዎች "ይህ ታላቅ ትዕይንት በራሱ ቁጥሩ 400 እስኪደርስ ብዙ ሰዎች እንዲቀላቀሉ አበረታቶ ከሆነስ?" ብለው ይጠይቃሉ ። የታሪክ መዝገቦች ግልጽ የሚያደርጉት ግን የከተማዋ መፍትሔ ሙሉ በሙሉ መክሸፉን ነው።

ከዳንሰኞቹ መሀል የሚሞቱም ነበሩ። ይህ የዳንስ እንቅስቃሴ ሰውነት ላይ በሚያሳድረው ከፍተኛ ውጥረት ምክንያት፤ በልብ ድካም፣ በስትሮክ፣ በከፍተኛ መዛል ወይም በረሃብ ይሞቱ ነበር። በትክክል ስንት ሰው እንደሞተ ማወቅ አይቻልም። ወደኋላ የመጡ የታሪክ ጸሐፊዎች ፤ በቀን እስከ አስራ አምስት ሰዎች ይሞቱ እንደነበር ቢዘግቡም ፤ ዘመናዊ የታሪክ ተመራማሪዎች ግን ቁጥሩን በጥንቃቄ እንድንመለከተው ያሳስባሉ።
ይህ ክስተት እውነተኛ ስቃይ ማድረሱን ግን አያጠራጥርም። ይህ ፌሽታ አልነበረም። በዝግታ እየተከናወነ ያለ የህዝብ ሰቆቃ ነበር።
በመጨረሻም፣ የስትራስቡርግ መሪዎች ያንን መራራ እውነት ተቀበሉት። መፍትሔያቸው ከሽፏል።
ከከሸፈው መፍትሔ በኋላስ?
ሙዚቃው ቆመ። መድረኮቹ ፈረሱ። ባለሙያ ዳንሰኞቹ ተሰናበቱ። ከተማዋ ከሕክምና ፊቷን አዞረች... ወደ እምነትም አመራች።

ለብዙ ትውልዶች፤ በመካከለኛው አውሮፓ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ቅዱስ ቪተስ (Saint Vitus) ያለፈቃድ የሚደረጉ የዳንስ እንቅስቃሴዎችን ጋር የተያያዙ በሽታዎችን ያድናል ብለው ያምኑ ነበር። የአካባቢው ያለው ትውፊት ቅዱሱን ያስቆጡ ሰዎች ሊገታ በማይችል ዳንስ ሊረገሙ እንደሚችሉ ይጠቁማል።
የከተማዋ መሪዎች ይህንን በእውነት አምነውበት ይሁን ፤ ወይም ሌላ መፍትሔ ስላጡ ልናውቅ አንችልም። የምናውቀው ግን ቀጥሎ የሆነውን ነው....
በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ፤ በበሽታው የተጠቁት ብዙዎቹ ሰዎች በአቅራቢያው ባለ ኮረብታ ላይ ወደሚገኘው የቅዱስ ቪተስ ደብር ሄዱ።
ወረርሽኙም... ልክ እንደጀመረው ሁሉ በተአምራዊ ሁኔታ... ቀስ በቀስ እየጠፋ ሄደ።
ህዝቡ ተበተነ። ነጋዴዎች ወደ ሱቆቻቸው ተመለሱ። የቤተክርስቲያን ደወሎች እንደገና በስትራስቡርግ ውስጥ ከፍተኛው ድምፅ ሆኑ። ሕይወት ቀስ በቀስ ወደ ቀድሞው መደበኛ ምት ተመለሰች።
ነገር ግን አንድ ታላቅ ጥያቄ ሳይመለስ ቀረ።
የስትራስቡርግ ህዝብ በትክክል ምን ነበር ያጋጠመው?
ከአምስት መቶ ዓመታት በላይ በኋላም፤ እነዚያ ጥያቄዎች አሁንም መልስ አላገኙም። በአንዳንድ የታሪክ ተመራማሪዎች እና የሳይንስ ሰዎች ፤ የሚከተሉት መላምቶች ተሰጥተው ነበር።
የተመረዘ ዳቦ በልተው ቢሆንስ?
ይህ ማብራሪያ በሀያኛው ክፍለ ዘመን ሰፊ ትኩረትን ስቦ ነበር።

ምናልባት ዳንሰኞቹ ተመርዘው ቢሆንስ?
ለዚህ ዋና ተጠርጣሪ ኤርጎት (ergot) የተባለ በገብስ/በስንዴ (rye) ላይ የሚበቅል ፈንገስ አይነት ነበር። በተለይም ከከፍተኛ ጎርፍን ተከትሎ ከሚመጣ ወበቃማ አየር በኋላ፤ ኤርጎት እንጀራ/ዳቦ ለመስራት የሚውለውን እህል ሊበክል ይችላል። ይህ ፈንገስ በነርቭ ሥርዓት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ኬሚካሎችን ያመነጫል። ይህም መንቀጥቀጥን፣ የጡንቻ መኮማተርን፣ ቅዠትን፣ የሚቃጠል ህመምንና ከፍተኛ የአስተሳሰብ መለዋወጥን ያስከትላል።
ይህ መላምት የብዙዎችን አእምሮ ቢማርክም ፤ አንዳንድ ተመራማሪዎች ማስረጃዎቹን በቅርበት ሲመረምሩ ችግሮች መታየት ጀመሩ። በከፍተኛ የኤርጎት መመረዝ የሚሰቃዩ ሰዎች ብዙውን ጊዜ በጣም ይታመማሉ። አብዛኞቹ ለከባድ የጡንቻ መኮማተር፣ ለግራ መጋባት፣ ለደነዘዘ ስሜት ወይም ወደ ጣቶቻቸው የሚሄደው የደም ፍሰት በመቀነሱ ምክንያት ለጋንግሪን (gangrene) በሽታ ይጋለጣሉ።
ለዚህም በዚህ ፈንገስ የተመረዙት ታማሚዎች ፤ ቀና ብለው ለመቆም እንኳ ይቸገራሉ እንጂ ፤ ለቀናት ያለ ማቋረጥ ሊደንሱ አይችሉም። እንዲሁም በተለያየ አዝዕርት በማይጠቀሙ የአለም ክፍሎች፤ ተቀራራቢ የሆነ የዳንስ እብደት (choreomania) ታይቶ ያውቃል። በዚህም የተነሳ ይህ መላምት የተፈጠረውን ክስተት ሙሉ በሙሉ ሊያብራራ አይችልም
የነርቭ በሽታ (Neurological Disease) ሊሆን ይችል ይሆን?

ዳንሰኞቹ ቀደም ሲል ባልታወቀ የሕክምና እክል ተጠቅተው ቢሆንስ?
ባለፉት ዓመታት ተመራማሪዎች በተለያዩ ጊዜያት የሚጥል የማንቀጥቀጥ በሽታ (epilepsy)፣ የአንጎል መቆጣት (encephalitis)፣ ታይፈስ (typhus)፣ እና ሌሎች በርካታ የነርቭ በሽታዎችን እንደ ምክንያት አቅርበዋል።
የሚጥል በሽታ በእርግጥም ያለፈቃድ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ሊያመጣ ይችላል፤ ይህ ለሰአታት ሊያጋጥም አይችልም። ሙሉ በሙሉ ሰውነትን አንቀጥቅጦ ከ15 ደቂቃ በላይ ካለፈ፤ ሳንባ ላይ በሚያደርሰው ጉዳት ለሞት ሊዳርግ ይችላል። እንዲሁም ይህ በሽታ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወደ መላው ማህበረሰብ ሊዛመት አይችልም።
የአንጎል መቆጣትም ቢሆን ፤ በእንቅስቃሴና በባህሪ ላይ ተፅእኖ ሊያሳድር ይችላል። የአንጎል መቆጣት ከፍተኛ ትኩሳትን፣ ግራ መጋባትን፣ ኮማን ወይም ሞትን ያስከትል ነበር። ታይፈስም በበኩሉ፤ ከባድ ህመም ያመጣል፤ እንጂ የሳምንታት ዳንስ አይፈጥርም።
ለዚህም እስከ አሁን የሕክምና ሳይንስ የሚያውቃቸው የነርቭ በሽታዎች ይህንን ክስተት ሊገልጹት አይችሉም።
ታዲያ ምን ሊሆን ይችላል?

ዛሬ ብዙ የታሪክ ተመራማሪዎችና የሕክምና ተመራማሪዎች በጣም ጠንካራው ማብራሪያ፤ የጋራ ስነ-ልቦናህመም (በተለይም Mass psychogenic illness ወይም Mass sociogenic illness) እንደሆነ ያምናሉ።
ስሙ የስነ ልቦና ይሁን እንጂ፤ ዳንሰኞቹ ምልክቶቹን በአእምሯቸው ፈጥረውታል ወይም ሆን ብለው የታመሙ አስመስለዋል ማለት አይደለም። ምልክቶቹ እውነተኛ ነበሩ።
ተመሳሳይ ክስተቶች በዘመናዊ ትምህርት ቤቶች፣ ፋብሪካዎችና፣ ማህበረሰቦች ውስጥ ተመዝግበዋል። ሰዎች ምንም ዓይነት የሕክምና ምክንያት ሳይኖርባቸው መውደቅን፣ መንቀጥቀጥን፣ የመተንፈስ ችግርን ወይም ጊዜያዊ ሽባ መሆንን አስተናግደዋል።
ታዲያ ዳንሱ የዚሁ ክስተት ሌላ መገለጫ ሊሆን ይችላል?
ብዙ ተመራማሪዎች አዎ ብለው ያምናሉ።
በወቅቱም ማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድሩ ሁኔታዎች ተፈጥረው ነበር። ከ 1518 በፊት በነበሩት አመታት ስትራስቡርግ ጎርፍን፣ ድርቅን፣ ረሃብን፣ በሽታንና ማህበራዊ ቀውስን አስተናግዳለች። የምግብ እጥረት፣ ፈንጣጣና ቂጥኝ የማያቋርጡ ስጋቶች ነበሩ።
የሕክምና ታሪክ ተመራማሪው ጆን ዋለር (John Waller) እንደሚገልጹት፤ እነዚህ መከራዎች ለየት ያለ የጋራ ስነ-ልቦናች ችግር እንዲከሰት ምቹ ሁኔታን ፈጥረው ነበር። የከተማው ነዋሪዎች አእምሮ ዝም ብሎ የዘፈቀደ ምልክቶችን አላመጣም። ይልቁንም በዚያ ሰዓት ላጋጠማቸው ሰዎች ትርጉም የሚሰጥ ምልክትን ፈጠረ ይላሉ። እሳቸው ሲያብራሩም ብዙዎች ቅዱስ ቪተስ ሰዎችን በማይገታ ዳንስ ሊረግም ይችላል ብለው በሚያምኑበት ማህበረሰብ ውስጥ፤ ከፍተኛ የአእምሮ ውጥረት እራሱን ከእምነታቸው ጋር በሚስማማ መልኩ ገለጠው ይላሉ።
ሆኖም ይህ ማብራሪያ እንኳ ሙሉውን ታሪክ ላይነግረን ይችላል!
ጸሐፍት ታሪኩን መዝግበው አስቀምጠዋል። ሳይንስ በተረዳው ልክ ተንትኖታል። ሁሉንም የሚገልጽ መልስ ግን አሁንም አልተገኘም። ክርክሩ ከተጀመረ ከ500 ዓመታት በላይ ሆኖታል። ገና የሚያበቃ አይመስልምም!
እርስዎ ምን ያስባሉ? ምን የተከሰተ ይመስልዎታል?



Comments