ችላ ልንለው የማንችለው ቀውስ
- Zebeaman Tibebu
- Mar 17
- 4 min read
Updated: Mar 18
በአለማችን በየአመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፤ ራሳቸውን በማጥፋት ህይወታቸውን እንደሚያጡ ይገመታል። ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ዕድሜያቸው 50 ዓመት አይሞላም። ይብሱኑ በወጣትነት እድሜ ክልል (ከ15 እስከ 29 ዓመት) ያሉትን የዚህ ዋነኛ ተጠቂ ናቸው።
በኢትዮጵያ ውስጥ 9 ፐርሰንት የሚሆነው የማህበረሰብ ክፍል በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ራሱን ስለማጥፋት ያስባል። ከ እነኝህ ውስጥ 4 ፐርሰንት የሚያክሉት ከ ሀሳብም አልፈው ፤ ራስን የመግደል ሙከራ ያደርጋሉ። ለዚህም ወንዶች በእጥፍ ከሴቶች ይልቅ ተጋላጭነት አላቸው። ባለፉት አመታት ውስጥ በሀገራችን ራስን ማጥፋት እየጨመረ እየመጣ ይገኛል። ለዚህም ይሆናል ከወትሮው በበለጠ መልኩ ፤ በሚዲያ እንዲሁም በአከባቢያችን ራሳቸውን ስላጠፉ ሰዎች አብዝተን መስማት የጀመርነው።
ራስን ማጥፋት በአንድ ግለሰብ የሚፈጸም አስዛኝ ተግባር ብቻ አይደለም ፤ ማህበረሰብን የሚያቆስልም ህመም ነው።
ስንተ ተስፋ ያለው/ያላት ወጣት ራሷን አጠፋች ፤ ብሎ መስማት እየመረረን የምንጋተው እውነታ ከሆነ ሰንብቷል። ብዙዎችም ራሳቸውን ከመኖር ቀመር ሰርዘው ፤ የትውስታችን አካል ሆነው ቀርተዋል።
ግን ለምን?
ራሱን አብልጦ የሚወደው፤ በጥቅሙ የማይደራደረው የሰው ልጅ ለምን ራሱን ያጠፋል?
እንዴትስ በራሱ ላይ እንዲህ የከፋ እርምጃ ይወስዳል?
በአለማዊውም በ እምነትም ትክክል አለመሆኑን እያወቀ ለምን አንድ ኢትዮጵያዊ ህይወቱን ያጠፋል?
ኢትዮጵያውያን ለምን ራሳቸውን ያጠፋሉ?
ራስን ማጥፋት ድንገተኛ ድርጊት አይደለም ። ቀስ በቀስ እየጎለበተ የሚመጣ የመገለል እና የተስፋ መቁረጥ ድምር ውጤት ነው። ይህ ቀውስ በተወሳሰቡ ምክንያቶች ሊመጣ ይችላል። አንዱም በሌላው ላይ እየተመረኮዘ፤ እርስ በእርስ እየተመጋገበ ራስን ማጥፋት ደረጃ ያደርሳል። እነኝህንም ምክንያቶች በተለያየ ደረጃ አድርገን እንያቸው።
ደረጃ 1፡ ድምጽ አልባው ትግል - የአእምሮ ጤና እክል

ይህ ሁሉ የሚጀምረው በአእምሮ ውስጥ በሚደረግ ውጊያ ነው። ውጊያው የጥይት እሩምታም ሆነ ፤ የተጎጂ ሲቃ አይሰማበትም። ዝም ያለ ነው። የብቻ ትግል ነው፤ ማንም የማያቀው፤ ማንም የማይሰማው። ለዚህም ድብርት፣ ጭንቀት እና ሌሎች የአእምሮ ሕመሞች በሩን ይከፍታሉ። ብዙዎች እነዚህ ሁኔታዎች ከምክንያታዊ ስጋቶች ይልቅ የመንፈሳዊ ድክመት ወይም የግል ውድቀት ምልክቶች እንደሆኑ ያምናሉ። ለዚህም ብዙ ጊዜ ቦታ አይሰጣቸውም። ርኅራኄና እንክብካቤ ከማግኘት ይልቅ፣ በሥቃይ ላይ ያሉት ሰዎች ችግራቸውን ሲያዋዩ ተድባብሶ ያልፋል። ጆሮ የሰጠ ሰው ቢኖር “በርታ ፤ጠንካራ ሰው አይደለህ” ብሎ ያልፈዋል። ሌላም ጊዜ አስተሳሰባቸውን ዘልፈን፤ ኅፍረት እና የመገለል ስሜትን እንዲሰማቸው እናደርጋለን። ይህ መገለል ስለጭንቀታቸው በግልጽ እንዳይወያዩ ፤ በዝምታ እንዲሰቃዩ ያደርጋል።
ደረጃ 2፡ መደበቂያ ማጣት

አንድ ሰው እርዳታ እንደሚያስፈልገው ቢያውቅም የት መሄድ ይችላል? በኢትዮጵያ ውስጥ የአእምሮ ጤና አገልግሎት በጣም አናሳ ነው። አንድ ስነ አእምሮ ሐኪም ተደራሽነቱ ለአንድ ሚሊዮን ሕዝብ ነው። ያሉንም ሀኪሞች በጥቂት ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ የተከማቹ በመሆናቸው ፤ የገጠሩ ህዝብ እንክብካቤ አያገኝም። ለዚህም የማማከር አገልግሎቶች ብርቅዬ ናቸው። መድሃኒቶቹ ብዙ ጊዜ አይገኙም ፤ ወይም ሊገዙ አይችሉም።
ያለ ሙያዊ ድጋፍ ራስን በራስ የማጥፋት ሃሳባቸውን የሚታገሉት ደግሞ ፤ ምንም አይነት የሚያበረታታቸው የደህንነት መረብ የላቸውም። ከወደቁበት ባህር ዋኝተው ለመውጣት ቢሞክሩም ፤ ዳርቻውንም የሚያመላክታቸው ሆነ መንገድ የሚጠቁማቸው ማንም የለም። በራሳቸው ዳርቻውን ካገኙት እሰየው ነው፤ አልያም ለመዋኘት ሲፍጨረጨሩ ቆይተው ፤ ሲደክማቸው እጅ ይሰጣሉ።
ደረጃ 3: መጨፍለቅ- ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች

የአእምሮ ጭንቀት ሳይታከም እንዲባባስ ውጫዊ ግፊቶች ሸክሙን ያጠናክራሉ። ሥራ አጥነት፣ ድህነት፣ የትምህርት፣ የስራ ፣ እንዲሁም የትዳር ውጥረት እና የቤተሰብ ችግሮች ፤ አንድን ግለሰብ ወደ ተስፋ ቢስ አዙሪት ይከታሉ። ጥቂት በፍትሀዊነት ያልተከፋፈለ የስራ እድል ባለበት ሥርዓት ውስጥ ፤ ወጣቶች ስኬታማ እንዲሆኑ ከፍተኛ ጫና ይደርስባቸዋል። ስኬታቸው የቤተሰብ ሲሆን ፤ ውድቀታቸው ደግሞ የራሳቸው ሆኖ እንዲያስቡ ይደረጋሉ። ህልማቸው የማይደረስ እና ትግላቸው ማለቂያ የሌለው ሲመስላቸው ፤ ተስፋ መቁረጥ እየጨመረ ይሄዳል።
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ እንዲሁም በዙሪያችው ህልማቸው ላይ የደረሱ የሚመስሏቸው እኩዮቻቸውን ሲያዩ ጫናው ያይላል ። ህሊናቸው ይከሳቸዋል። በአእምሮአቸው ሸንጎ ይወድቃሉ። የወደፊት እጣ ፈንታቸው ብርሃን የሌለበት ይሆናል። በጨለማ የተዋጠው ነገአቸው ውስጥ እንዳይኖሩም ፤ የአእምሮ ህመሙ ሰላም ይነፍጋቸዋል። ትግላቸውን ተረድቶ፤ ጥንካሬያቸው እንደመስታወት ሆኖ ሊያሳያቸው የሚችል፤ የሚያጀግናቸው ሰው በአቅራቢያቸው ቢኖር መልካም ነበር።
ደረጃ 4፡ አሳፋሪው ጉዳይ - እርዳታ እንዳያገኙ የሚያደርጉ እንቅፋቶች

እንዲህ ከባድ ቀውስ ውስጥ እራሱ እያሉ ፤ ብዙ ኢትዮጵያውያን ስለ አእምሮ ጭንቀታችው ማውራት እንደማይችሉ ይሰማቸዋል። ስለ ራስ ማጥፋትማ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው! ካነሱም አፍ አፋቸው እንላችዋለን። ካዋዩንም ደግሞ ‘እንዴት እንዲህ ታስባለህ? በሰላም ነው!? አንቺ ደህና ሴት አልነበርሽም? እንዲህ ያሰብሽው ክፉ ሴት ስለሆንሽ መሆን አለበት’ ብለን እናሸማቅቃቸዋለን።
አልተረዳነውም እንጂ ይህ የ እርዳታ ጥሪ የሚያደርጉበት ፤ የመጀመሪያም የመጨረሻም ጊዜ ነው። ሆኖም ግን ምላሾቻችን፤ በሙሉ ነጻነት እራሳቸውን እንዳይገልጹ ፤ ሃሳባቸውን ጭንቀታቸውን እንዳያዋዩን ያደርጋቸዋል። ባህላችን ፣ ዘይቤያችን፣ ለሰው ደራሽነታችን የአእምሮ ህመምን አያካትትም። ራስን ማጥፋት አያካትትም። በእምነትም የተወገዘ ስለሆነ ገና ሲያነሱት እናጥላለን።
ታድያ እንዴት እርዳት ይጠይቁን?
እኛስ ያላወቅነውን ችግር እንዴት መፍታት እንችላለን?
የኔ የሚሉት ሰው መኖር፣ ሀይማኖተኛ መሆን፣ መልካም እና ጠንካራ የማህበረሰብ ትስስር መኖር ፤ በህክምናው የደህንነት መረብ ተደርጎ ይወሰዳል። እንደዚህ አይነት የደህንነት መረብ ያላቸው ሰዎች ራሳችውን ለማጥፋት የሚገፋፉ ብዙ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም ፤ ከድርጊቱ ይቆጠባሉ። ለዚህም ለአእምሮ ህሙማን የደህንነት መረብ ማጠናከር ይመከራል።
ታድያ ግን ካልሰማናቸው፣ ካሸማቀቅናቸው እና ካገለልናቸው እንዴት የመፍትሔ አካል እንሆናለን? ሀይማኖት ቢከልክልም፤ ከኛ በላይ የሀይማኖት መጽሀፍትን ህጎችን ቢያቁም፤ ችግሩ ካየለባቸው ራሳችውን ከማጥፋት አይመለሱም። ለዚህም ነው አንዳንዴ ሀይማኖተኛ ሰዎች ራሳቸውን ማጥፋታቸውን እየሰማን የምንገኘው።
ደረጃ 5፡ ሽንፈት - አሳዛኙ መደምደሚያ

መሄጃ ሲጠፋ ፤ ህመሙን መቋቋም ሲያቅታቸው፤ ነገ ከተስፋ ይልቅ ስቃይን ስትሰንቅ፤ እጅ መስጠት ይመጣል። የስነ ልቦና ሀኪም ማግኘት የሚችሉት ራሱ እርዳታ እንዳያገኙ እብድ መባል ይፈራሉ። ብቻቸውን የታገሉት ትግል ማብቂያ ሊኖረው ካልቻለ፣ ህይወት ትርጉም አጥታ ከመኖራቸው ሞታችው ከተሻለ ራስን ማጥፋት ብቸኛ አማራጫቸው አድርገው ያስቡታል። ከስቃያቸው ሽሽት ያገኙትን አማራጭ ይወስዳሉ። አለመኖርን ይመርጣሉ። ምርጫው ፍጹም ቀላል አይደለም። ግን ለራሳቸው የሚሰጡት መፍትሔ ነው። እርዳታ ያለገኘው ረዥሙ የመከራ ትግል አሳዛኝ መጨረሻ ይሄ ይሆናል።
አሁንም ከመርፈዱ በፊት በህይወት ላሉት እንድረስላቸው።
ይበቃናል! ዝምታው ይሰበር
ራስን ማጥፋት መከላከል ይቻላል። ይህም ደግሞ ስለ አእምሮ ህመም ከመገንዘብ እና ከተግባር ይጀምራል። ምን እናድርግ ታድያ?

1. የአዕምሮ ጤና ንግግሮችን መደበኛ ማድረግ - ስለ ወባ ወይም ስለ ስኳር በሽታ እንደምንነጋገር ሁሉ ስለ ድብርት እና ራስን ማጥፋት ያለ ሃፍረት ማውራት አለብን።
2. የአእምሮ ጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ማሳደግ - መንግስት እና የግሉ ሴክተሮች በአእምሮ ጤና አገልግሎቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ፣ ባለሙያዎችን ማሰልጠን እና የማዳረስ ፕሮግራሞችን ማስፋፋት አለባቸው።
3. እርስ በርሳችሁ መደጋገፍ - አንድ ሰው ሲያፈገፍግ፣ ለሕይወት ያለው ፍላጎት ሲያጣ ወይም የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሲገልጽ ካስተዋሉ ይድረሱ። ቀላል "ደህና ነህ?" ለውጥ ማምጣት ይችላል።
4. እምነትን እና ማህበረሰብን መጠቀም - የሀይማኖት እና የባህል መሪዎች ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። እንደዚህ ህመም ላይ ላሉ ሰዎች ምክራቸው የ አእምሮ እረፍት ሊሰጥ ይችላል። ድምፃቸውም ስለ አእምሮ ጤና እና ራስን ስለ ማጥፋት ባህላዊ ግንዛቤን ለመቀየር ይረዳል።
አይዞህ/ሽ ብቻህን አይደለህም/ሽም
እርስዎ ወይም የሚያውቁት ሰው እየታገለ ከሆነ ፤ እባክዎን እርዳታ ይጠይቁ። ድጋፍ ለመጠየቅ ምንም የሚያሳፍር ነገር የለም.።
ስለዚህ ዝምታችን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ይሰበር። ሹክሹክታ እናቁም። ከወሬ አልፈን ፤ እውነተኛ እርምጃ መውሰድ የምንጀምርበት ጊዜ አሁን ነው።
Comments