እያገረሸ ያለው የኤች አይቪ/ኤድስ ስርጭት
- Zebeaman Tibebu
- Apr 5
- 4 min read
ኤች አይቪ በ ኢትዮጵያ የ 40 አመት እድሜ ያለው ጎልማሳ ህመም ነው። የመጀመሪያው የኤች አይቪ ቫይረስ እ.ኤ.አ በ1984 በአንድ ወንድና በአንድ ሴት ላይ የተገኘ ሲሆን ፤ የኤድስ ህመም ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ደግሞ ከ ሁለት አመት በኋላ በ 1986 ዓ.ም ነው። ላለፉት 4 አስርት አመታት ሀገሪቷ ከህመሙ ጋር ፈታኝ ትግል አካሂዳለች። ትግሉ ላይ ላገኘችው አመርቂ ለውጥ ፤ የዛሬ 12 አመት በፊት በአለም ተጨብጭቦላት ነበር።

ሆኖም ግን ባለፉት ጥቂት አመታት ውስጥ እየተገኙ ያሉት መረጃዎች ምናልባት ከድሉ ብስራቱን አስቀድመን ይሆን እንዴ ፤ ብለን እንድናስብ ያስገድዱናል። መረጃዎቹ እንደሚያሳዩት የኤች አይ ቪ ታማሚዎች ቁጥር በ ሀገሪቷ እየጨመረ ነው። በተለይም ደግሞ በከተሞች እና በግጭት በተጠቁ ክልሎች በሚኖሩ ተጋላጭ ማህበረሰቦች መሀል እያገረሸ ነው።
እውነታውን አመላካች ቁጥሮች
የኤች አይቪ ስርጭት መጠን እ.ኤ.አ በ 2000 ዓ.ም ከነበረበት 3.3 ፐርሰንት ወደ 0.9 በ 17 አመት ጊዜ ውስጥ ቀንሷል።
ከ 3 አመት በፊት የነበረ ጥናት እንደሚያመላክተው መልሶ ወደ 1. 54 ፐርሰንት አንሰራርቷል። በዋነኝነት በ ጋምቤላ (4.52%)፣ በአዲስአበባ (3.52%) እና በድሬዳዋ (2.6%) ከተሞች ጨምሯል።
በከተሞች ቫይረሱ በዋነኝነት በሆቴሎች፣ በ ገስት ሀውሶች እና በቤርጎ አከባቢዎች እየተንሰራፋ ይገኛል።
ከ ወራት በፊት የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ ፤ በትግራይ ክልል ግጭቱን ተከትሎ የየኤች አይቪ መጠን በእጥፍ አድጓል (ከ 1.4 % ወደ 3% ጨምሯል)።
ከትግራይ ክልል ከተፈናቀሉ ሰዎች መካከል የስርጭት መጠኑ 5.5% ደርሷል።
በሴት ሴተኛ አዳሪዎች መካከል ደግሞ ወደ 8.5% ከፍ ብሏል።
የቫይረሱ መስፋፋት በበኩሉ ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ ይበዛል።
ለምን እንዲህ ተንሰራፋ?
ለዚህ መስፋፋት በርካታ ምክንያቶች አሉ።
1. በሚዲያ ላይ ይደረግ የነበረ የግንዛቤ ማስጨበጥ መቀነስ።
የበሽታውን መንሰራፋትን መቆጣጠር ያስቻለንን ድል የተጎናጸፍነው ፤ በወቅቱ በመንግስት እና ባለድርሻ አካላት መካከል ተደርጎ በነበረ ፤ ያላሰለሰ ጥረት የተነሳ ነው። በጊዜው ግንዛቤ የማስጨበጥ ዘመቻ በሁሉም የሚዲያ አውታሮች አዘውትሮ ይካሄድ ነበር። አርቲስቶችም የዚህ ዘመቻ አባል በመሆናቸው ፤ እንደ 'ማለባበስ ይቅር' አይነት ብዙ ግንዛቤ ማስጨበጫ ዘፈኖች ከማህበረሰቡ ልቦና ተቀርጸው ቀርተው ፤ የብዙሀንን አስተሳሰብ ሊለውጡ ችለው ነበር። የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርታዊ መልእክቶቹም ፤ እንደ 'ሶስቱ የመ ህጎች' ከማህበረሰቡ ጋር ተቆራኝተው ፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚያውቃቸው ነበሩ።

ይህም ጥረት በወቅቱ የ ኤች አይቪ/ ኤድስን እድገት መግታት እንድንችል አድርጎን ነበር። መገለል ቀንሶ ነበር። ሆኖም ግን ድላችንን ያበሰርን ዋዜማ ጥረት ቀነስን።
እውነት ነው የ ኤች አይቪ/ ኤድስን ህክምና ተደራሽነትን ለመጨመር ብዙ ተሰርቷል ፤ እየተሰራም ይገኛል። የህክምና መከታተያ ሲስተሙ እጅጉን ዘምኗል። መድሀኒቶች እና ህክምናን ተደራሽ ለማድረግ በብዛት ቢሰራም ፤ የማህበረሰብ ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ ያለው ስራ ግን በፊት በነበረበት መጠን አልቀጠለም።
በአሁኑ ጊዜ በሚዲያ ስለ ኤች አይቪ እምብዛም አይወራም። ምናልባት ሀገሪቷ ያሏት አንገብጋቢ ጉዳዮች ፊታችንን አንድናዞር አስገድደውን ይሆናል። ምክንያቱ ምንም ቢሆን እውነታው የጥረት መቀነስን ያመላክታል።
ክጓዳ ወደ ገበያ አውጥተን ፤ ፍርጥርጥ አድርገን ፤ መደበቂያ ያሳጣነው ህመም ፤ አሁን መልሶ ከመኝታ ቤታችን ከትሞ ፤ በህቡዕ የምንወያየው ገበናችን ሆኗል። ይሄም ታማሚዎች መድህኒታቸውን በስርአት እንዳይወስዱ ጫና ከማሳደሩም ባሻገር ፤ የበሽታውን የመተላለፍ እድል ይጨምራል።
2. የግጭት እና የፆታዊ ጥቃት ተጽእኖ

በቅርቡ በሀገሪቷ እንደ ሰደድ እሳት እየተስፋፋ ያለው ግጭት የብዙ ሰውን ህይወት ከማጥፋቱ ባሻገር ፤ በህይወት የተረፉት ላይ የማይሽር ቁስል እየጣለ ሄዷል። ግጭቱን ተከትሎ ብዙ ጾታዊ ጥቃቶች እንደተፈጸሙ ፤ የኢትዮጵያም ይሁን የውጭ ምንጮች ይገልጻሉ። ብዙ የመውለድ እድሚ ላይ ያሉ (ከ15 እስከ 49 ዓመት የሆናቸው ሴቶች እና ልጃገረዶች) በደረሰባቸው ጥቃት ለኤች አይቪ ተጋላጭ ሆነዋል። ከግጭቱ ጋር በተያያዘ የጤና ተቋማት አለመስራታቸው ጥቃት የደረሰባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች የኤች አይቪ መከላከያ መድሀኒት በጊዜ አይወሰዱም። ለዚህም በቫይረሱ ይያዛሉ።
የነዚህ ተቋማት መውደም ወይም አገልግሎት የማይሰጡበት ደረጃ ላይ መሆን ፤ በአከባቢው ያሉ ታካሚዎች የኤችአይቪ ምርመራ፣ የፀረ ኤችአይቪ ሕክምና (ART) እና ሌሎች አስፈላጊ አገልግሎቶችን እንዳያገኙ ፤ እንቅፋት ሆኗል። ይህም ቫይረሱ ባልተመረመሩ እና ባልታከሙ ታካሚዎች መሪነት ውስጥ ለውስጥ እንዲስፋፋ ያደርጋል።
3. ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች

የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖዎች ለ ቫይረሱ መስፋፋት ከፍተኛ ሚናን ይጫወታሉ። ኢትዮጵያ እያሳለፈቻቸው ባሉ ተግዳሮትች የተነሳ እየታዩ ያሉት የፍልሰት መጨመር ፣ የከተሞች መስፋፋት እና የማህበረሰባዊነት አውታሮች መፍረስ ፤ ለ እንደዚህ አይነት በሽታዎች መስፋፋት ተጠቃሽ መንስኤዎች መሆናቸው በአለም ዙሪያ ያሉ ጥናቶች ያመላክታሉ። እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት ፣ የስራ እድሎች ውስንነት ለሴተኛ አዳሪነት (ግብይት ወሲብ) መበራከት አስተዋእጾ አለው። ይህ ጫና ሲያይል ፤ ወንዶች ለኤች አይቪ መስፋፋት የሚያጋልጡ አደገኛ ባህሪያትን እንዲያሳዩ ያደርጋል። ይህ ከኮንዶም እጥረት እና የመከላከል አገልግሎት አቅርቦት ውስንነት ጋር ሲጨመር የኤችአይቪ ስርጭት ተጋላጭነትን ከፍ አድርጎታል።
4. በወጣቶች መካከል የኤችአይቪ ምርመራ መቀነስ

በአሁኑ ወቅቱ ካሉት የኢትዮጵያ ውጣቶች መካከል ፤ አንድ ሶስተኛ የሚጠጋው ብቻ የኤችአይቪ ምርመራ አድርጎ ፤ ያለበትን የጤና ሁኔታ ያውቃል። የተቀረው ሁለት ሶስተኛ ወጣት አሳሳቢ አደጋ ላይ ነው ያለው። የትምህርት ደረጃ ማነስ ፣ ድህነት ፣ እንዲሁም የግንዛቤ ጉድለት በ እነኝህ ወጣቶች መካከል ሳይታወቅ ፤ እንዲሰራጭ ያስችለዋል።
5. የአሜሪካ መንግስት እርዳታ መቋረጥ (የሚመጣው ተግዳሮት)

እስከአሁን ድረስ ላገኘነው ድል የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የአሜሪካ መንግስት እርዳት ተቋርጣል። የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስተር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሊያም በ 2018 በተደረገ ስብሰባ ላይ የ ፔፕፋር ፈንድ ላገኘነው ትልቅ እመርታ ከፍተኛ አስተዋእጾ እንዳለው ገልጸው ነበር።
የዚህ ፈንድ መቋረጥ በ ኤች አይቪ/ ኤድስ ስርጭት ላይ ብዙ እክልን እንደሚፈጥር መገመት አያዳግትም። ከተቋረጠ ወራት ጊዜ ውስጥ መሰናክሎችን ማየት ጀምረናል። ይህንን ክፍተት ለመሙላት መንግስት እና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ጥረት ካላደረጉ ያለው መስፋፋት ከዚህም በላይ ሊጨምር ይችላል።
ቀጣይ መንገድ፡ እንዴት እንግታው?
እውነታው አሳሳቢ ነው። ነገር ግን ሊቀለበስ ይቻላል። ቆራጥ እርምጃ ከወሰድን እንደበፊቱ ዳግም ልንገታው እንችላለን።

ግንዛቤ የማደስ ዘመቻዎች
በተለይ በወጣቶች ዘንድ የኤችአይቪ ግንዛቤ መታደስ አለበት። መልእክቱ ጮክ ብሎ፣ ግልጽ እና ከዘመናቸን ወጣቶች ጋር በሚግባባ መንገድ መገለጽ አለበት። ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች በዚህ ዙሪያ ላይ ከፍተኛ ድርሻ መውሰድ አለባቸው። ከማህበረሰብ መሪዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት እና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጋር በመሆን ስለ በሽታው መከላከል፣ ምርመራ እና ህክምና መልካም አስተሳሰብን የሚፈጥሩ መልዕክቶችን ፤ ማሰራጨት ያስፈልጋል።
የኤች አይቪ ህክምና ተደራሽነትን ማሳደግ
የኮንዶም አጠቃቀምን ትምህርትን በተለይ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ማዳረስ ይኖርብናል። የኤች አይቪ/ ኤድስን ህክምና እና መከላከያ ትምህርቶች ለሁለም የማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ እንዲሆኑ በይበልጡኑ መሰራት ይኖርበታል።
የኤችአይቪ ቅድመ ምርመራ ማጠናከር
መደበኛ ኤች አይቪ ምርመራ በተለይ ተጋላጭ በሆኑ የማህበረሰብ አካላት መካከል እንዲለመድ መሰራት አለበት ።
መገለል ፈጽሞ ይቁም
ሰዎች እርዳታ እንዳይፈልጉ የሚከለክለውን መገለልን በዋነኝነት መዋጋት አለብን።
ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተጋላጭነቶችን መፍታት
ድህነት፣ ስራ አጥነት እና ማህበራዊ እኩልነት ኤች አይቪ/ ኤድስን ወረርሽኙን ለሚያስፋፉ አደገኛ ባህሪያት አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። ለዚህም የኢኮኖሚ ማጎልበት ፕሮግራሞች፣ የሙያ ስልጠና እና የማህበራዊ ድጋፍ አገልግሎቶች ተጋላጭነት ላለባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች መዳረስ አለባቸው።
Comments