የጆሮ ደግፍ ሕመም
ጆሮ ደግፍ አምዎት ያውቃል?
እስቲ በአእምሮዎ ያስቡት፤ አንድ አዘቦት ጠዋት ከእንቅልፍዎ ሲነቁ የሆነ ያልተለመደ ነገር ይሰማዎታል፤ ወደ መስታወት ጠጋ ብለው እራሶን ሲያዩ… በአንድ በኩል ጉንጭዎ አብጧል! በእጅዎ ሲነኩት ደግሞ የሚጠዘጥዝ ከባድ ሕመም አለው። ቁርስ ለመቅመስ ሲያስቡ፣ ሲመገቡ፣ እና ምራቅዎን ሲውጡ ሕመሙ ይበልጥ ይበረታል።
በዚያች ቅጽበት በአእምሮዎ ውስጥ የሚመላለሱት ጥያቄዎች ምንድናቸው?
“የጥርስ ሕመም ይሆን?”
“ወይስ ጉሮሮዬ ተቆጥቶ ነው?”
ነገር ግን ዋናው ምክንያት ከእነዚህ ሁሉ የተለየ ሊሆን ይችላል። ማለትም ከጆሮ በታች የምራቅ እጢ እብጠት ወይም በሕክምና መጠሪያው ፓሮታይቲስ (Parotitis) የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው። እኛ በለመድነው አጠራር ደግሞ “ጆሮ ደግፍ” የምንለው ማለት ነው።

ብዙዎቻችን «ጆሮ ደግፍ» ሲባል ወዲያው ትዝ የሚለን በሕፃንነት ዕድሜያችን በትምህርት ቤት ፈጣን ተላላፊ በሆነው እና በ ‘መምፕስ’ (Mumps) ቫይረስ አማካኝነት የሚከሰተው ሕመም ነው። ነገር ግን ትልቁ ሚስጥር እዚህ ላይ ነው፦ በአዋቂዎች ላይ የሚከሰተው የጆሮ ደግፍ ሕመም ከጀርባው ሌሎች በርካታ አስገራሚ ምክንያቶች አሉት!
ከባክቴሪያ ኢንፌክሽን እስከ ምራቅ ጠጠር፣ አልፎ ተርፎም ከሰውነት በሽታ የመከላከል ሥርዓት መዛባት ጋር ሊያያዝ ይችላል።
ታዲያ ይህ ሕመም እንዴት ይከሰታል? መቼስ ነው አደገኛ የሚሆነው?
ዛሬ ስለ ጆሮ ደግፍ (Parotitis) ድብቅ ምክንያቶች፣ ምልክቶችና መፍትሔዎች እያንዳንዱን ነጥብ በጥልቀት እንመለከታለን።
ጆሮ ደግፍ ምንድነው?
በቀላል ቋንቋ ሰንገልጸው፡ በጉንጫችን ውስጥ ምራቅ የሚያመነጩ እጢዎች አሉ፤ ከእነዚህ መካከል ትልቁ 'ፓሮቲድ ግላንድ (parotid gland)'ሲሆን፤ ከሁለቱም ጆሮዎቻችን ፊት ለፊትና በታችኛው በኩል ይገኛል።
ይህም ምራቅ አመንጪ እጢ ሲያብጥ ወይም ሲቆጣ የሚከሰተውን እብጠት 'ፓሮታይተስ parotitis' እንለዋለን።
እብጠቱ በአንድ በኩል ብቻ አልያም፤ በሁለቱም ጎኖች ሊከሰት ይችላል።
ግን ምን ሊያሳብጠው ይችላል?
ጆሮ ደግፍ በባክቴርያ፣በቫይረስ፣ በምራቅ ቱቦ መደፈን እንዲሁም በሌሎች ምክነያቶች ሊከሰት ይችላል።

ጆሮ ደግፍ ራሱ አንድ በሽታ ሳይሆን የተለያዩ ችግሮች ምልክት ሊሆን ይችላል።
1. Mumps — በብዙዎች የሚታወቀው
ይህ በmumps virus የሚከሰት ተላላፊ በሽታ ሲሆን በተለይም የparotid እጢን ያሳብጣል።
ሀመሙ ሲጀምር እንደ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የጡንቻ ሕመም፣ ድካም እንዲሁም የምግብ ፍላጎት መቀነስ ሊኖረው ይችላል።
ከዚያም በጆሮ ስር ያለው አካባቢ አብጦ፤የመንጋጋው ጠርዝ እንዳይታይ ሊያደርግ እና ጆሮውን ወደ ላይና ወደ ውጭ የተገፋ እንዲመስል ሊያደርግ ይችላል።
በMumps የተያዘ ሰው ምልክቶቹን ከ2–4 ሳምንታት ውስጥ ማሳየት ይጀምራል፤የparotid እብጠቱም በአማካይ ለ5 ቀናት ያህል ሲቆይ ፤ አብዛኛው ሰው በሁለት ሳምንታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ያገገማል ተበሎ ይገመታል።
2. የምራቅ ቱቦ መዘጋት
አንዳንድ ጊዜ ችግሩ ቫይረስ ሳይሆን የምራቅ እጢው ቱቦ መዘጋት ሊሆን ይችላል። ይህ በዋናነት የምራቅ እጢ ላይ በሚከሰት ጠጠር (salivary stone) ይመጣል።
የዚህ ቱቦ መዘጋት ከምግብ መመገብ ጋር ተያየዞ ሕመሙን ወይም እብጠቱን ይጨምረዋል። ይሀም የሚሆነው፤ምግብ ስናይ ወይም ስንመገብ የምራቅ እጢዎቻችን ተጨማሪ ምራቅ በብዛት ለማመንጨት ሲሞክሩ ጫናውን ስለሚጨምሩት ነው።
3. የባክቴሪያ ኢንፌክሽን
በተለያዩ ምክኛቶች የምራቅ ፍሰት ከቀነሰ ወይም ከተዘጋ፣ አፋቸ ወስጥ ያለው የባክቴሪያ መጠን የጨምራል ይህ በምራቅ እጢ ውስጥ በመብዛት ኢንፌክሽን እንዲከሰትና የምራቅ እጢዎቹ እንዲቆጡ ሊያድርግ ይችላል።
በዚህ ሁኔታ እብጠት፣ ሕመም እና ትኩሳት ሊከሰት ይችላሉ።
4. ሌሎች ምክንያቶችም አሉ
ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ቫይረሶች፣ አንዳንድ የሰውነት የመከላከያ ችግሮች(autoimmune diseases)፣ የእጢው የራሱ የአፈጣጠር (የመዋቅር) ችግሮች እና አንዳንድ መድኃኒቶችም parotitis ሊያስከትሉ ይችላሉ።
ስለዚህ “ጉንጬ አብጧል = mumps ነው” ብሎ መደምደም ትክክል አይደለም።
የሊምፍ ኖድ ( የንፍፊት) እብጠት ወይስ የጆሮ ደግፍ (Parotitis)?
ይህን መለየት እጅጉን ጠቃሚ ነው!
በአንገት አካባቢ የሚገኙ ሊምፍ ኖዶች ሲያብጡ በጆሮ ስር ወይም በመንጋጋ አካባቢ እብጠት ሊታይ ይችላል እንጂ የጆሮ አቀማመጥ አይቀየርም ፤ ነገር ግን የparotid እብጠት ሲኖር የጆሮው አቀማመጥ ሊቀየር እና በመንጋጋ ጠርዝ ላይ ያለው ቅርጽ ሊጠፋ ይችላል። የህም ማለት የሊምፍ ኖድ እብጠት ብዙውን ጊዜ በተወሰነ ቦታ የተከለለ እብጠት ይሆናል።

ምርመራው እንዴት ይደረጋል?
ሐኪሙ በመጀመሪያ እብጠቱ የት እንደሚገኝ፣ መቼ እንደጀመረ፣የሕመም አይነቱን፣ ትኩሳት እንዳለ እና ከምግብ ጋር ግንኙነት እንዳለው ይጠይቃል።
አንዳንድ ጊዜ የአፍ ውስጥና የምራቅ ቱቦዎች ምርመራም ያስፈልጋል።
Mumps ከተጠረጠረ ግን ምርመራ በምልክት ብቻ መወሰን አይገባም። የRT-PCR የተባለ ምርመራ ከጉንጭ ውስጥ በሚወሰድ ናሙና ሊደረግ ይችላል፤ ከምልክቱ መጀመር በኋላ ከ3 ቀናት በላይ ከሆነ የደም (IgM) ምርመራም ሊጨመር ይችላል።

ህክምናውስ?
ሕክምናው የሚወሰነው parotitis ያስከተለው ምክንያት ላይ ነው።
Mumps እንደሆነ ከተረጋገጠ ልዩ የቫይረስ መድኃኒት በመደበኛነት አይሰጥም። እረፍት፣ በቂ ፈሳሽ፣ ተገቢ የሕመምና የትኩሳት መቆጣጠሪያ እና ቀላል ምግብ መመገብ ምልክቶቹን ለመቋቋም ይረዳሉ።
ነገር ግን የባክቴሪያ ኢንፌክሽን ወይም የምራቅ ቱቦ መዘጋት ካለ ሕክምናው ፈጽሞ የተለየ ሊሆን ስለሚችል፣ ራስዎን በራስዎ አንቲባዮቲክ መጀመር አይመከርም።
Mumps ከሆነ ለሌሎች ሰዎች ማስተላለፍ ይችላሉን?
አዎ! Mumps በምራቅ ይተላለፋል።

አንድ ሰው በበሽታው ከተያዘ በኋላ ምልክት ከመታየቱ በፊትም ቫይረሱን ለሌሎች ሊያስተላልፉ ይችላሉ።
Mumps ከተጠረጠረ ወይም ከተረጋገጠ ሰው የparotid እብጠት ከጀመረበት ቀን ጀምሮ 5 ቀናት ድረስ ከሌሎች ሰዎች መራቅ ይኖርበታል።
ሊያሳስበን የሚገባው ምንድነው?
“ምንም አይደለም፣ mumps ነው እንጂ” ብሎ መተው ጥሩ ሀሳብ አይደለም።
ብዙ የmumps በሽታዎች ቀላል ቢሆኑም፣ አንዳንድ ሰዎችን ለከፋ ችግር ሊዳርጋቸው ይችላሉ።
ከነዚህም ውስጥ የጭንቅላት ሽፋን እብጠት (meningitis)፣ የአእምሮ እብጠት (encephalitis)፣ የመስማት ችግር፣ እና በወጣት ወንዶች የዘር ፍሬ እብጠት (orchitis) በዋናነት የጠቀሳሉ።
ስለዚህ ከጉንጭ እብጠቱ ጋር ከፍተኛ ትኩሳት፣ ከባድ ራስ ምታት፣ አንገት መደንደን፣ መደናገር፣ የመስማት ችግር፣ ወይም በወንዶች የዘር ፍሬ ከባድ ሕመምና እብጠት ካለ፣ በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ማምራት ግድ የላል።
መከላከል ይቻላል?
ጆሮ ደግፉ የተከሰተው በMumps ምክንያት ከሆነ፣የMMR ክትባት በመውሰድ መከላከል ይችላል። ይህ ክተባት ማምፕስን ለመከላከል ዋነኛው መንገድ ነው።

ግን አንድ ነገር አይርሱ፦
የጆሮ ስር ያለው ጉንጭ ቢያብጥ፣ ወዲያውኑ “mumps ነው” ብለው አይወስኑ።
Parotitis ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩት ይችላል። እብጠቱ ለምን እንደመጣ መለየቱ ደግሞ ትክክለኛውን ሕክምና ለመምረጥ ወሳኝ ነው።
አንድ ያበጠ ጉንጭ ትንሽ ምልክት ሊመስል ይችላል—ግን ምክንያቱን ማወቅ የሕክምናው መጀመሪያ ነው።




Comments