top of page

በድንገት ራስን መሳት፦ ቀላል ድካም ነው ወይስ ሌላ በሽታ?

5 hours ago
4 min read
ሰው በድንገት ወድቆ ራሱን ሲስት አይተው ያውቃሉ?

እስቲ ያንን ቅጽበት ያስታውሱት። ምን እያደረገ ነበር? ገና መራመድ መጀመሩ ነበር ወይስ ቆሞ ከሰዎች ጋር እየተጨዋወተ?

በአንድ ቅጽበት ፊቱ ይገረጣል፤ ዓይኖቹ ይዞራሉ፤ ሳይታሰብም መሬት ላይ ይወድቃል። በአካባቢው ያሉ ሰዎች ተደናግጠው ውሃ ይረጩታል፤ ያራግቡለታል። ከጥቂት ሰከንዶች በኋላ ግን ዓይኑን ገልጦ ይነሳል። "ምንም አልሆንኩም፣ ትንሽ አዙሮኝ ነው" ብሎ ፈገግ ይላል።


ሁላችንም እፎይ እንላለን። ከዚያም "በረሃብ ነው"፣ "ሙቀቱ ነው" ወይም "ስራ ስለበዛበት ደክሞት ነው" ብለን ጉዳዩን በቀላሉ እንረሳዋለን።


ግን ቆም ብለው አስበው ያውቃሉ? ያ የሰከንዶች መውደቅ በዝምታ የሚነገር የህይወት ማስጠንቀቂያ ቢሆንስ?


እውነታው ይህ ነው፦ በድንገት ራስን መሳት ሁልጊዜ ተራ ድካም አይደለም። አንዳንድ ጊዜ የከባድ የልብ ሕመም፣ የልብ ምት መዛባት ወይም ሌላ አደገኛ የጤና እክል የመጀመሪያ የማስጠንቀቂያ ደወል ሊሆን ይችላል።


ሰውየው ዛሬ ተነስቶ ስለሄደ ብቻ ነገም ይተርፋል ማለት አይደለም። መንስኤውን ሳያውቁ "አሁን ተሽሎኛል" ብሎ ቸል ማለት፤ ነገ ዳግም ላይመለስ የሚችል ትልቅ አደጋን መጋበዝ ነው።


ታዲያ ሰውነታችን ለምን እንዲህ ይሆናል? መቼስ ነው ጉዳዩ አስጊ የሚሆነው? ህይወትን ሊያድን የሚችለውን እውነታ አብረን እንመልከት።


ለምን ሰዎች በድንገት ራስን ይስታሉ?

አንድ ሰው በድንገት ራሱን የሚስትበት ምክንያት ከቀላል የዕለት ተዕለት ሁኔታዎች አንስቶ እስከ ህይወት የሚያሳጡ ከባድ የጤና እክሎች ድረስ ሊደርስ ይችላል። ዋና ዋናዎቹን ምክንያቶች እስቲ እንመልከት፦


  1. የደም ግፊት በድንገት መቀነስ (Low Blood Pressure)


ይህ በጣም የተለመደው የመሳት መንስኤ ነው። ደም ወደ አንጎል በበቂ ሁኔታ ለመድረስ የተወሰነ ግፊት ያስፈልገዋል። ይህ ግፊት በድንገት ሲወርድ አንጎል ደም ያጣና ሰውየው ይወድቃል። ይህ የሚሆነው፦

  • ለረጅም ጊዜ ተቀምጠው ወይም ተኝተው በድንገት ሲነሱ፣

  • በቀን ውስጥ በቂ ውሃ ሳይጠጡ ሲቀሩና ሰውነትዎ ፈሳሽ ሲያጣ (Dehydration)፣

  • በከፍተኛ ሙቀት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ቆይተው በላብ ብዙ ፈሳሽ ሲያጡ፣

  • የደም ግፊት መድኃኒቶችን ጨምሮ አንዳንድ መድኃኒቶች በሚያመጡት ተፅዕኖ ምክንያት ነው።

  1. የልብ ሕመም (Heart Problems)

ይህ በተለይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ምክንያት ነው!

ልብ ደምን ወደ አንጎልና ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች የሚያሰራጭ ዋና አካል ነው። ልብ በትክክል መስራት ካልቻለ ወደ አንጎል የሚደርሰው የደም አቅርቦት ሊቀንስ ይችላል። ድንገተኛ መሳትን የሚያስከትሉ የልብ ችግሮች የሚከተሉት ናቸው፦


  • የልብ ምት መዛባት (Arrhythmia): ልብ በጣም በፍጥነት፣ በጣም በዝግታ ወይም ስርዓቱን ሳይጠብቅ ሲመታ፤

  • የልብ ጡንቻ ችግር (Cardiomyopathy): የልብ ጡንቻ ሲወፈር ወይም ሲዳከም፤

  • የልብ ቧንቧ ችግር (Valvular Heart Disease): የልብ ቧንቧዎች በትክክል መክፈት ወይም መዝጋት ሲያቅታቸው፤

  • የልብ የደም አቅርቦት ችግር: የልብ ጡንቻ በራሱ በቂ ደም ሳያገኝ ሲቀር ራስን መሳት ሊከተል


እነዚህ የልብ ችግሮች ካሉ፣ ራስን መሳት ተራ ድካም ሳይሆን የከባድ የልብ አደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ነው!


  1. የደም ስኳር መጠን መቀነስ (Hypoglycemia)

አንጎላችን ያለማቋረጥ እንዲሰራ ስኳር (ግሉኮስ) እንደ ነዳጅ ያስፈልገዋል። የደም ስኳር መጠን ከመጠን በላይ ሲቀንስ አንጎል የሚያስፈልገውን ኃይል ማግኘት ይቸገራል። ይህ በተለይ ኢንሱሊን ወይም የስኳር መቀነሻ መድኃኒቶችን በሚጠቀሙ የስኳር ሕመምተኞች ላይ ሊከሰት ይችላል። በረሃብም ጊዜ ሊመጣ


በዚህ ምክንያት ከመሳትዎ በፊት ላብ ማላብ፣ መንቀጥቀጥ፣ ከፍተኛ ረሃብ፣ የልብ ምት መፍጠንና ግራ መጋባት ሊሰማዎት ይችላል።

  1. ሌሎች ምክንያቶች


  • ከባድ ህመም፣ ድንገተኛ ፍርሃት ወይም ድንጋጤ፣

  • ለረጅም ሰዓት ሳይንቀሳቀሱ በአንድ ቦታ መቆም፣

  • ከባድ የደም ማነስ (Severe Anemia) ወይም የደም መፍሰስ፣

  • የሳንባ የደም ቧንቧ መዘጋት (Pulmonary Embolism)፣

  • ጭንቅላትን መመታት፣ የሚጥል በሽታ (Seizure)፣ ስትሮክ እና ሌሎች የአንጎል ችግሮች ራስን መሳት ሊያስከትሉ ይችላሉ።


ራስዎን ከመሳትዎ በፊት ሰውነትዎ ምን ምልክት ያሳያል?

አንዳንድ ጊዜ ሰውነታችን ሊወድቅ መሆኑን አስቀድሞ በምልክት ይነግረናል። ራስዎን ከመሳትዎ በፊት እነዚህን ስሜቶች ሊያስተውሉ ይችላሉ፦

  • ራስ ማዞርና የመንገዳገድ ስሜት፣

  • ዓይን መጨለም ወይም እይታ መደብዘዝ፣

  • በድንገት ላብ ማላብ፣

  • ማቅለሽለሽ፣

  • የሰውነት መዛልና የሙቀት ስሜት፣

  • ጆሮ መጮህ ሊያስተውሉ ይችላሉ።

ነገር ግን አንድ በጣም አስፈላጊ ነገር ያስታውሱ፦

ከልብ ችግር ጋር የተያያዘ መሳት ብዙ ጊዜ ምንም ዓይነት የማስጠንቀቂያ ምልክት ሳይሰጥ፣ በቅጽበት ሰውን ሊጥል ይችላል።



 መቼ ራስን መሳት እጅግ አደገኛ ይሆናል?  (ቸል የማይባሉ ምልክቶች!)

ሁሉም የመሳት ክስተቶች እኩል አደገኛ አይደሉም።አንዳንዶቹ ቀላል ቢሆኑም፣ ሌሎቹ ግን በቅጽበት ህይወትን ሊነጥቁ የሚችሉ ከባድ የልብ ወይም የአንጎል አደጋዎች ምልክት ናቸው።


ከሚከተሉት ምልክቶች አንዱ እንኳ ካጋጠመዎት፣ "ትንሽ ቆይቼ ልየው" አይበሉ። ወዲያውኑ ወደ ሕክምና ተቋም ይሂዱ፦


  • እየተራመዱ ወይም የአካል እንቅስቃሴ እያደረጉ ከሳቱ፦ ሰውነትዎ ኃይል በሚፈልግበት ሰዓት መውደቅ የልብ እክል ዋነኛ ምልክት ነው።

  • ተኝተው ሳሉ እራስዎን ከሳቱ፦ በተኙበት መሳት ፈጽሞ የተለመደ አይደለም፤ ከባድ የልብ ምት መዛባትን ያሳያል።

  • ከመሳት በፊት የደረት ሕመም ወይም የልብ ምት መዛባት ካለ፦ ልብዎ እየተቸገረ መሆኑን እየነገረዎት ነው።

  • ከወደቁ በኋላ ቶሎ ካልነቁ፤ በአንድ ደቂቃ ውስጥ ንቃተ ህሊና መመለስ ካልቻለ፤

  • ከነቁ በኋላ የስትሮክ ምልክቶች ካሉ፦ መናገር መቸገር፣ የአንድ የሰውነት ክፍል መድከም ወይም ከባድ ራስ ምታት ካለ አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋል።

  • ሲወድቁ ከባድ የአካል ጉዳት ከደረሰብዎት፦ በተለይም ጭንቅላትዎን ከተመቱ፤

  • በቤተሰብ ውስጥ ከ50 ዓመት በታች ድንገተኛ ሞት አጋጥሞ ከነበረ ፤ የአስቸኳይ ሕክምና እርዳታ ይጠይቁ።



 አጠገብዎ ያለ ሰው በድንገት ራሱን ቢስት ምን ማድረግ አለብዎት?

አንድ ሰው በድንገት ሲወድቅ በአጠገቡ ያሉ ሰዎች የሚወስዱት እርምጃ ህይወቱን ሊያድን ወይም ሊያጠፋ ይችላል። ድንጋጤ ውስጥ ከመግባት ይልቅ እነዚህን ቀላል እርምጃዎች ይከተሉ፦


  1. በጀርባው ያስተኙት፦ ምንም ዓይነት ስብራት ወይም ጉዳት ከሌለበት ደም ወደ አንጎሉ በቀላሉ እንዲመለስ እግሮቹን ከልቡ ከፍ አድርገው በትራስ ወይም በእጅዎ ይደግፉለት።


  2. ንቃተ ህሊናውንና አተነፋፈሱን ይፈትሹ፦ የወደቀውን ሰው ሻውን ነካ አድርገው ይጥሩት። በደንብ እየተነፈሰ መሆኑን ያረጋግጡ።


  1. በጎኑ ያስተኙት፦ ሰውየው እየተነፈሰ ሆኖ ግን ንቃተ ህሊናው ካልተመለሰ፤በትውከት ወይም በምራቅ እንዳይታፈን በጎኑ አዙረው ያስተኙት።


  2. አስቸኳይ እርዳታ ይጥሩ፦ ሰውየው በደንብ እየተነፈሰ ካልሆነ ወይም በአንድ ደቂቃ ውስጥ ካልነቃ ወዲያውኑ አምቡላንስ ይጥሩ። ስልጠናው ካለዎት የልብ እና የሳንባ ማነቃቂያ የመጀመሪያ እርዳታ (CPR) ይጀምሩ።


በፍጹም ማድረግ የሌለብዎት አደገኛ ልማዶች!

ሰውየው ሙሉ በሙሉ ሳይነቃ ውሃ፣ ምግብ ወይም መድኃኒት በአፉ አይስጡት (ወደ ሳንባው ገብቶ ሊያፍነው ይችላል)። እንዲሁም ፊቱን በውሃ መርጨት፣ በጥፊ መምታት አይመከርም።


እንዲሁም በግድ ደግፎ ማቆምም ወይም ከወገብ ቀና ማድረግ ደም ወደ አንጎሉ እንዳይመለስ ስለሚያደርግ ፈጽሞ ተገቢ አይደለም!


ራስ መሳትን መከላከል ይቻላል?

አዎ!

አንዴ ምክንያቱ ከታወቀና ተገቢው ጥንቃቄ ከተደረገ፣ ድንገተኛ መሳትን በቀላሉ መከላከል ይቻላል፦


  • በቂ ውሃ ይጠጡ።

  • ከተኙበት ወይም ከተቀመጡበት ቀስ ብለው ይነሱ።

  • ለረጅም ጊዜ ያለ እንቅስቃሴ ቆመው አይቆዩ።

  • ምግብዎን በሰዓቱ ይመገቡ።

  • ሕመምዎን ይቆጣጠሩ። የደም ግፊት ወይም የስኳር ሕመም ካለብዎት ክትትልዎን አያቋርጡ።

  • ሐኪምዎን ያማክሩ። የሚወስዱት መድኃኒት ግፊትዎን በጣም እያወረደው ከሆነ ሐኪምዎን ያማክሩ (ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መድኃኒት ማቆምም ሆነ ጨው ማብዛት አደገኛ ነው)።



ያስታውሱ!

ራስን መሳት ሁልጊዜ ከባድ በሽታ አይደለም። ነገር ግን ሁልጊዜ ቀላል ነው ብሎ ማለፍ፤ ህይወትን አደጋ ላይ ይጥላል። ምክንያቱን ለማወቅ ዛሬውኑ የጤና ባለሙያ ያማክሩ!


ጤና ከሕመም መዳን ብቻ ሳይሆን ሕመምን ቀድሞ ማወቅና መከላከልም ነው!

Comments


bottom of page