top of page

ስለ Post-Pill ማወቅ ያለብዎት፡ ጥቅሙ እና ጉዳቱ

11 minutes ago
5 min read
“አሁን ምን አደርጋለሁ?”

ይህ ጥያቄ ብዙዎች ደህንነቱን ያልጠበቀ ግንኙነት ካደረጉ በኋላ፤ በድንጋጤና በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ሆነው የሚጠይቁት ነው። “ምን እሆን ይሆን?” የሚለው ሃሳብ ጭንቅላታቸውን ያውከዋል። ግንኙነቱን ያደረጉት ከተወሰኑለት የፍቅር አጋራቸው ጋር ቢሆንም እንኳ፤ “ልጆች ቢመጡስ?” የሚለው ፍርሃት አይለቃቸውም።


የጥቂት ደቂቃዎች አፍላ ስሜት ያሳለፈው ውሳኔ፤ ላልታሰበ እና ላልተዘጋጁበት ነገ እንዳይዳርጋቸው ይሰጋሉ። ምክንያቱም ያለእቅድ በድንገት የሚመጣ አንድ ህጻን፤ በቤተሰብ ህይወት ላይ ያልታሰበ የምስቅልቅል ስሜት ሊፈጥር ይችላል።


እርግጥ ነው፣ “ቀድሞውኑ ጥንቃቄ ቢደረግ ወይም የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ቢወሰድ ኖሮ መልካም ነበር!

ታዲያ አሁን ምን ይሻላል?

ለዚህ አስጨናቂ ጥያቄ በከተማችንም ሆነ በሀገራችን በስፋት በመፍትሄነት እየተወሰደ ያለው “Post-Pill” ወይም የድንገተኛ ጊዜ እርግዝና መከላከያ ኪኒን (Emergency Contraceptive Pill) ነው።


ይሁን እንጂ፤ በዚህ ኪኒን ዙሪያ በማህበረሰባችን ውስጥ የተለያዩና የተጋጩ አመለካከቶች አሉ። አንዳንዶች “እጅግ አስተማማኝ ነው፤ ከአላስፈላጊ እርግዝና ይታደጋል” ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ “ብዙ ጊዜ ከተወሰደ ማህፀን ላይ ችግር ያስከትላል ፣ ወደፊት ልጅ የመውለድ እድልን ይቀንሳል (መካን ያደርጋል)” በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ። ክኒኑ የሚሰራውም ጽንስ ከተፈጠረ በኋላ በማጨንገፍ ወይም በማክሸፍ የሚመስላቸው ጥቂት አይደሉም።

ታዲያ እውነቱ የትኛው ነው?

በመጀመሪያ፦ Post-pill ምንድነው?

ፖስት ፒል በሕክምናው ዓለም የድንገተኛ ጊዜ እርግዝና መከላከያ ኪኒን (Emergency Contraceptive Pill) ይባላል። ስሙ ራሱ እንደሚናገረው፤ ዋና ዓላማው ከአፍላ ወይም ካልታሰበ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት በኋላ፣ እርግዝና እንዳይፈጠር አስቀድሞ መከላከል ነው። ይህም በሚከተሉት አስገዳጅ ሁኔታዎች ውስጥ መጠቀም ይቻላል።


  • ምንም ዓይነት መከላከያ ሳይጠቀሙ ግንኙነት ከተፈጠረ፣

  • በግንኙነት ወቅት ኮንዶም ከተቀደደ ወይም ከወለቀ፣

  • መደበኛ የእርግዝና መከላከያዎችን ሳይወስዱ ከረሱ፣

  • ወይም ደግሞ አስገዳጅ የሆነ የጾታ ጥቃት ከተከሰተ... ይህ የድንገተኛ መከላከያ ከትልቅ ስጋት ሊታደግ ይችላል።


እዚህ ላይ ግን አበክረን ልናስምርበት የሚገባ አንድ ትልቅ ልዩነት አለ

ፖስት ፒል ማለት ባልታሰበ አደጋ ጊዜ የምንጠቀምበት አማራጭ እንጂ፤ ሁልጊዜ የምንመካበት መደበኛ መከላከያ ዘዴ አይደለም።

 ፖስት ፒል እንዴት ነው የሚሰራው? (ጽንስ ያጨነግፋል?)

ይህ ምናልባት በማህበረሰባችን ውስጥ ትልቁና ዋነኛው ውዥንብር ያለበት ነጥብ ነው። ብዙዎች ፖስት ፒል የሚሰራው ጽንስ ከተፈጠረ በኋላ በማጨንገፍ ወይም በማክሸፍ ይመስላቸዋል። በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የህሊና ጸጸትና ፍርሃት የሚሰማቸው ጥቂት አይደሉም።

ነገር ግን ሳይንሱ ከዚህ ፍጹም የተለየ እውነታን ያስቀምጣል።
ፖስት ፒል ፍጹም የፅንስ ማጨንገፊያ (Abortion pill) አይደለም።

ዋናው ስራው እንቁላል ከማህፀን ወደ ውጭ የሚለቀቅበትን ጊዜ ማዘግየት ወይም መከልከል ነው። በሌላ አነጋገር፤ የወንዱ ዘር (Sperm) ወደ ማህፀን በሚገባበት ጊዜ ሊያገኘው የሚችለውን እንቁላል አስቀድሞ በመደበቅ እርግዝና እንዳይፈጠር በር መዝጋት ነው።

ስለዚህ፣ ጽንስ አስቀድሞ ከተፈጠረ (ከተከሰተ) በኋላ ፖስት ፒል ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ እርግዝናውንም አያቋርጥም። መድኃኒቱ አስቀድሞ ለተፈጠረ ፅንስ ጥበቃ እንጂ ጥፋት አያመጣም።


በኢትዮጵያ ምን ያህል ጥቅም ላይ ውሏል?

“ፖስት ፒል በመላው ኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው” ብሎ በቀጥታ ለመደምደም የሚያስችል የተሟላና የቅርብ ጊዜ ብሔራዊ መረጃ ማግኘት ይከብዳል። ነገር ግን ከተለያዩ የሀገራችን ጥናቶች የምንረዳው አንድ ግልጽ እውነት አለ፦ በተለይ በወጣቶች መካከል የድንገተኛ መከላከያ አጠቃቀም በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቷል።


ነገሩን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ጥቂት እውነተኛ ማሳያዎችን እንመልከት፦

  • እ.ኤ.አ. በ2020 የታተመ እና 12 የሀገራችንን ጥናቶች ያካተተ ሰፊ ግምገማ (Meta-analysis) እንደሚያሳየው፤ ከ 3 ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች መካከል አንዷ የድንገተኛ መከላከያ እንደምትጠቀም( 34.5%) ያሳያል።  

  • ሌላው ደግሞ እ.ኤ.አ. በ2021 በአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ የተደረገ ጥናት ነው። በጥናቱ ከተሳተፉት መካከል 98.8% የሚሆኑት ስለ ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ ጠንቅቀው የሚያውቁ ሲሆን፣ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ካደረጉት ወጣት ሴቶች መካከል ደግሞ 91.2% የሚሆኑት ቢያንስ አንድ ጊዜ ፖስት ፒልን እንደተጠቀሙ ተናግረዋል።


እነዚህ ቁጥሮች የአጠቃላይ ሀገሪቱን እውነታ ሙሉ በሙሉ ባያንጸባርቁም፤ መልእክታቸው ግን አንድና ግልጽ ነው፦


ፖስት ፒል በኢትዮጵያ በተለይም በከተማና በወጣቶች ዘንድ በሰፊው ጥቅም ላይ እየየዋለ ያለ መከላከያ ነው።

አሳሳቢው ጉዳይ ግን፤ የመድኃኒቱ መኖር ወይም አለመኖር ሳይሆን፣ ስለ ትክክለኛ አጠቃቀሙና ስለ የጎንዮሽ ጉዳቶቹ ያለው ዕውቀት ውስን መሆኑ ነው።


እዚህ ላይ ትልቁ ጥያቄ፦ “Post-pill አደገኛ ነው?”

በአጭሩ፦ በትክክለኛው መንገድ ሲጠቀሙበት ፖስት ፒል እንደ አደገኛ መድኃኒት አይቆጠርም።

በተለይ በሀገራችን በስፋት በጥቅም ላይ የሚውሉት የሌቮኖርጌስትሬል (Levonorgestrel) የድንገተኛ መከላከያ ኪኒኖች በዓለም አቀፍ ደረጃ ደህንነታቸው የተረጋገጠ መሆኑን ጥናቶች በሙሉ ያሳያሉ።


ይሁን እንጂ፤ መድኃኒቱ ሆርሞን ስለሆነ የተወሰኑ የጎንዮሽ ተፅዕኖዎች ሊታዩበት ይችላሉ። እነዚህ ተፅዕኖዎች ግን ብዙውን ጊዜ ቀላልና ጊዜያዊ ናቸው። ለምሳሌ፦ ማቅለሽለሽ ወይም የማስታወክ ስሜት፣ ራስ ምታት፣ የሰውነት ድካም፣ የጡት ሕመም ስሜት እና በተለይ... የወር አበባ ዑደት መለዋወጥ ተጠቃሽ ናቸው።


ስለዚህ ፖስት ፒል ከወሰዱ በኋላ የወር አበባዎ ከቀድሞው ጊዜ ጥቂት ቀናት ቀድሞ ወይም ዘግይቶ ሊመጣ ይችላል፤ አልፎ ተርፎም የደሙ መጠን ሊበዛ ወይም ሊያንስ ይችላል።

ይህ ግን ፍጹም ተፈጥሯዊ የሆርሞን ምላሽ እንጂ፤ ማህፀን ላይ የደረሰ ጉዳት አመላካች አይደለም።



“Post-pill መካን ያደርጋል” የሚለውስ?

ይህን ወሬ የሚያረጋግጥ አንዲትም ሳይንሳዊ ማስረጃ የለም።

የድንገተኛ እርግዝና መከላከያ ኪኒኖች ወደፊት ልጅ የመውለድ ችሎታ ላይ ቅንጣት ታክል ዘላቂ ጉዳት እንደማያደርሱ በጥናት ተረጋግጧል። ቀደም ብለን እንደተወያየነው፤ ፖስት ፒል ከፅንስ ማጨንገፊያ (Abortion pill) መድኃኒቶች ፍጹም የተለየ ነው። እርግዝና ከተፈጠረ በኋላ ቢወሰድ እንኳ እርግዝናውን የማቋረጥ አቅም የለውም። መድኃኒቱ ስራውን ጨርሶ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከሰውነት ስለሚወጣ፤ የማህፀን ተፈጥሯዊ የመውለድ ሂደት ወዲያውኑ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ይመለሳል።


ስለዚህ “ብዙ ጊዜ ፖስት ፒል ወስጃለሁ፤ ወደፊት ልጅ የመውለድ ዕድሌ ጠፍቷል” የሚለው ፍርሃት በሳይንሳዊ ማስረጃ የማይደገፍ ባዶ ስጋት ነው።


ታዲያ ለምን ብዙ ጊዜ መጠቀም አይመከርም?

እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ብዙ ጊዜ ግራ መጋባት የሚፈጠረው። “በተደጋጋሚ መወሰድ የለበትም” ማለት “መድኃኒቱ መርዛማ ነው” ማለት አይደለም።


ዋናው ጉዳይ የሚከተለው ነው።

ፖስት ፒል እንደ ስሙ የተዘጋጀው ለ“ድንገተኛ” ጊዜ ብቻ ነው። የዕለት ተዕለት ወይም የመደበኛ ወሲባዊ ግንኙነት መከላከያ እንዲሆን አልተሰራም።


ምክንያቱም ከመደበኛ የመከላከያ ዘዴዎች (እንደ የየቀኑ ኪኒን፣ ኮንዶም፣ ወይም የክንድ ውስጥ መከላከያ) ጋር ሲነፃፀር እርግዝናን በመከላከል ረገድ ያለው አቅም አነስተኛ ነው። ለዚህም መደበኛ የመከላከያ መንገዶችን ከተካ እርግዝና የማጋጠም እድልን ይጨምራል።


በተጨማሪም፤ በአንድ የወር አበባ ዑደት ውስጥ መድኃኒቱን በተደጋጋሚ መውሰድ የወር አበባ መዛባትን፣ ድንገተኛ የደም መፍሰስንና ሌሎችንም የጎንዮሽ ተፅዕኖዎች ያበዛል።



አንድ ነገር ግን ፈጽሞ አይርሱ! ፖስት ፒል ከአባላዘር በሽታዎች አይከላከልም!

ፖስት ፒል የተሰራው ለአንድ እና ለአንድ ዓላማ ብቻ ነው።

እሱም እርግዝናን መከላከል!

ይህ መድኃኒት እንደ ኤችአይቪ (HIV)፣ ጨብጡ (Gonorrhea)፣ ክላሚዲያ (Chlamydia)፣ ቂጥኝ (Syphilis) እና ሌሎች በግብረ-ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ የአባለዘር በሽታዎችን (STIs) የመከላከል አቅም ፍጹም የለውም።


ስለዚህ “ፖስት ፒል ወስጃለሁ፣ እንግዲህ ከማንኛውም ስጋት ነፃ ነኝ” ብሎ መዘናጋት ጨርሶ አይቻልም። ከአላስፈላጊ እርግዝና ጎን ለጎን ከአባለዘር በሽታዎች ሙሉ ጥበቃን የሚፈልጉ ሰዎች፣ በተገቢውና በትክክለኛው መንገድ ኮንዶምን መጠቀም ይኖርባቸዋል።


ከግንኙነት በኋላ መቼ መውሰድ አለበት?

ከግንኙነት በኋላ መቼ መውሰድ አለበት? እዚህ ላይ ነው፤ ሰዓት እና ጊዜ ወሳኝ የሚሆነው።


በተለይ በሀገራችን በብዛት የሚገኘው ሌቮኖርጌስትሬል (Levonorgestrel) ያለባቸው የድንገተኛ መከላከያ ኪኒኖች፤ ግንኙነቱ እንደተፈጠረ በተቻለ ፍጥነት መወሰድ አለባቸው።


በአጠቃላይ የድንገተኛ መከላከያ ኪኒኖች እስከ 120 ሰዓታት (5 ቀናት) ድረስ የመስራት አቅም ቢኖራቸውም፤ ከግንኙነት በኋላ ለመውሰድ ረዥም ጊዜ በወሰደ ቁጥር ውጤታማነታቸው ይቀንሳል።


በተጨማሪም ሌላኛው አማራጭ

ግንኙነት በተደረገ በ5 ቀናት ውስጥ በጤና ባለሙያ አማካኝነት፤ በማህፀን ውስጥ የሚቀመጥ የኮፐር አይዩዲ (Copper IUD/ሉፕ)፣ እጅግ ከፍተኛ ውጤታማነት ያለው ሌላኛው የድንገተኛ መከላከያ ዘዴ ነው።


Post-pill ከወሰዱ በኋላ የወር አበባዎ ቢዘገይስ?

ይህን ጊዜ እባክዎ አይደንግጡ!

ቀደም ሲል እንደተወያየነው፤ ፖስት ፒል በሰውነታችን ሆርሞን ላይ ጊዜያዊ ተፅዕኖ ስለሚያሳድር የወር አበባዎን ቀን በጥቂት ሊያዛባው ይችላል።


ነገር ግን የወር አበባዎ ከተለመደው ቀን በጣም ከዘገየ፤ ወይም ደግሞ የተለየ የእርግዝና ምልክት ከተሰማዎት፤ የመጀመሪያው እርምጃዎ መረጋጋትና ፋርማሲ ሄደው የእርግዝና ምርመራ (Pregnancy Test) ማድረግ መሆን አለበት።


በተለይም ፖስት ፒል ከወሰዱ በኋላ የሚከተሉት ምልክቶች ከታዩዎት ግን ጊዜ ሊሰጡ አይገባም።

  • ከባድና ሊታገሱት የማይችሉት የሆድ ሕመም፣

  • ከፍተኛ የማዞር ወይም የመሳት ስሜት፣

  • ወይም ደግሞ ያልተለመደና ከባድ የደም መፍሰስ ካጋጠመዎት...


አቅራቢያ ወዳለ የጤና ተቋም በመሄድ የጤና ባለሙያን ማማከር ይገባል። ከማህጸን ውጭ ያል እርግዝና ሊሆን ስለሚችል።


💡 ታዲያ ትክክለኛው መልዕክት ምንድነው?

ፖስት ፒል አደገኛ አይደለም፤ እንዲሁም የመደበኛ መከላከያ ምትክ አይደለም። በተገቢው ሰዓት ሲወሰድ ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል ጠቃሚ የሆነ የድንገተኛ መፍትሔ ነው።


ነገር ግን ደጋግመሽ የፖስት ፒል የምትጠቀሚ ከሆነ፤ ጥያቄሽ “ፖስት ፒል አደገኛ ነው?” ብቻ መሆን የለበትም።

ይልቁኑ “ለእኔ የሚስማማው መደበኛ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ ምንድነው?” መሆን አለበት።

Comments


bottom of page